አባ ሙሴ ጸሊም

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቅዱሳንን ከተለያየ ዓለማዊ ሥራ ጠርቶ ቃሉን ለመስበክ፣ ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ያበቃቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡

በዛሬው ዝግጅታችን በኃጢአት ሕይወት ከኖሩ በኋላ በንስሓ ከተመለሱ ቅዱሳን መካከል አንዱ የኾኑትን በዓለ ዕረፍታቸው ሰኔ ፳፬ ቀን የሚዘከረዉን የአባ ሙሴ ጸሊምን ታሪክ በአጭሩ እናቀርብላችኋለን፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን በሊቀ ነቢያት ሙሴ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም አንዱ አባ ሙሴ ጸሊም /ጥቁሩ ሙሴ/ ሲኾኑ በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ጸሊም /ጥቁር/ በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ፡፡ እኒህ ቅዱስ ለሰማዕትነት ክብር ከመብቃታቸው በፊት በቆዳቸው ብቻ ሳይኾን በግብራቸውም ጥቁር ማለትም ኀጢአትን የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ያለመጠን ይበሉና ይጠጡ፣ ይቀሙና ያመነዝሩ እንዲሁም ሰው ይገድሉ ነበር፡፡

በሥጋቸው ጠንካራ፣ በጉልበታቸውም ኃይለኛ በመኾናቸውም ሊቋቋማቸው የሚችል ማንም አልነበረም፡፡ *እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል* ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፲፩፥፲፪/ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍተዋታል፤ ማለትም የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያወርሰውን የጽድቅ ሥራ ትተው ወደ ገሃነም በሚያስጥል ኃጢአት ኖረዋል፡፡

እግዚአብሔርን ካለማወቃቸው የተነሣ በባዕድ አምልኮ ተይዘው የኖሩት አባ ሙሴ ጸሊም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይም ነበሩ፡፡ በዚህ ዓይነት ልማድ እየኖሩ ሳሉ የሰውን ጠፍቶ መቅረት የማይወደው አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ወደ ቤቱ ሊመልሳቸው በወደደ ጊዜ የፀሐይን ፍጡርነትና ግዑዝነት ስለገለጸላቸው ብዙ ጊዜ ወደ ፀሐይ በማንጋጠጥ *ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ፤* ደግሞም *የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ* ይሉ ነበር፡፡

አባ ሙሴ ጸሊም በዚህ ዓይነት ልማድ ሲኖሩ የገዳመ አስቄጥስ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ያዩታል፤ እንዲሁም ያነጋግሩታል እየተባለ ሲነገር ይሰሙ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ስሙን እንዲቀድሱ፣ መንግሥቱንም እንዲወርሱና ሊያደርጋቸው ወድዷልና ወደ ገዳሙ ይሔዱ ዘንድ አነሣሣቸው፡፡ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደዉም ከካህናቱ አንዱ የኾኑትን አባ ኤስድሮስን *እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጥቻለሁ* አሏቸው፡፡

እርሳቸውም እግዚአብሔርን ፍለጋ ወደ ገዳሙ መምጣታቸዉን አድንቀው ከአባ መቃርስ ጋር አገናኟቸው፡፡ አባ መቃርስም የክርስትና ሃይማኖትን አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ከዚያ በኋላ *ታግሠህ የማስተምርህን ትምህርተ ወንጌል ከጠበክ እግዚአብሔርን ታየዋለህ* እያሉ በተስፋ ቃል ያጽናኗቸው ነበር፡፡

ከዓመታት በኋላም በልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ፈትነው አመነኰሷቸው፡፡ አባ ሙሴ ጸሊምም ብዙ ገድልን ከሚጋደሉ ቅዱሳን አብልጠው መጋደል በጀመሩ ጊዜ ሰይጣን ለማሰናከልና ከገዳሙ ለማስወጣት በማሰብ ቀድሞ ያሠራቸው በነበረው ግብረ ኃጢአት ሊዋጋቸው ጀመረ፡፡ አባ ኤስድሮስም እያጽናኑና እየመከሩ በተጋድሏቸው ይበልጥ እንዲጸኑ ያተጓቸው ነበር፡፡

አባ ሙሴ የውኃ መቅጃ ሥፍራው ሩቅ ነበርና አረጋውያን መነኮሳት በመንገድ እንዳይደክሙ ዘወትር ውኃ እየቀዱ በሚተኙበት ጊዜ በየበዓታቸው ደጃፍ በማስቀመጥ ያገለግሏቸውና ድካማቸውን ይቀንሱላቸው ነበር፡፡ እንዲህ እያደረጉ በመጋደልና በማገልገል ለብዙ ዓመታት ሲኖሩ ጸላዔ ሠናያት ሰይጣን እግራቸውን በከባድ ደዌ መታቸውና ለብዙ ቀናት የአልጋ ቁራኛ ኾነው ኖሩ፡፡ እርሳቸውም በደዌ የሚፈታተናቸው ጥንተ ጠላት ሰይጣን መኾኑን ተረድተው ሰውነታቸው ደርቆ በእሳት የተቃጠለ እንጨት እስኪመስል ድረስ ተጋድሏቸውን እጅግ አበዙ፡፡ እግዚአብሔርም ትዕግሥታቸውን ዓይቶ ከደዌያቸው ፈወሳቸው፤ የሰይጣንንም ውጊያ አርቆ ጸጋውን አሳደረባቸው፡፡

ከዚህ በኋላ እርሳቸው ወደሚኖሩበት ገዳም የተሰበሰቡ ፭፻ የሚኾኑ ወንድሞች መነኮሳትን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ እያሉ ቅዱስ ጳውሎስ *በመልካም ለሚያገለግሉት ከፍተኛውን ሹመት ይስጧቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብዙ ባለሟልነት አለና* /፩ኛጢሞ.፫፥፲፫/ በማለት እንዳስተማረው በማኅበረ መነኮሳቱ ለቅስና መዓርግ ተመረጡ፡፡ ሊሾሟቸው ወደ ቤተ መቅደስ በአቀረቧቸው ጊዜ ግን ሊቀ ጳጳሳቱ የቅስናን መዓርግ ሊሰጧቸው አልፈቀዱም ነበርና አረጋውያኑን *ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አውጡት* አሏቸው፡፡

አባ ሙሴም ይህን ቃል ከሊቀ ጳጳሳቱ ሲሰሙ *መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ መልካም አደረጉብህ* እያሉ ራሳቸውን እየገሠፁ ከቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ በሌላው ቀን ጽናታቸውንና ትዕግሥታቸውን የተመለከቱት ሊቀ ጳጳሳቱ አስጠርተው በአንብሮተ እድ በቅስና መዓርግ ሾሟቸውና *ሙሴ ሆይ እነሆ በውስጥም በውጭም ኹለመናህ ነጭ ኾነ* በሚል የደስታ ቃል ተናገሯቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በተቀበሉት መዓርግ እግዚአብሔርን፣ መነኮሳቱንና ገዳሙን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡

እግዚአብሔር በአባ ሙሴ ላይ አድሮ ከአደረጋቸው ተአምራት መካከል ያለ ወቅቱ ዝናብ እንዲዘንብ ማድረጋቸው አንደኛው ነው፤ ከዕለታት አንድ ቀን በበዓታቸው ምንም ውኃ በሌለበት ቀን አረጋውያን በእንግድነት መጡባቸው፡፡ ውኃ የሚቀዳበት ቦታ በጣም ሩቅ ነበርና የሚያደርጉትን አጡ፡፡ እንግዶቹን ወደ በዓታቸው ካስገቡ በኋላም እግዚአብሔርን *ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ?* እያሉ በጸሎት ይጠይቁት ጀመሩ፡፡ በስሙ ለሚታመኑ ድንቅ ሥራውን መግለጥ ልማዱ የኾነው እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ዝናብ አዘነበላቸውና የውኃ ጉድጓዶችን ሞላላቸው፡፡

እንግዶቹንም እንደ ሥርዓቱ እግራቸውን አጥበው፣ ምግብና ውኃ ሰጥተው አስተናገዷቸው፡፡ አረጋውያኑም በዝናቡ መጣል እየተገረሙ አባ ሙሴን *ብዙ ጊዜ ትወጣ፣ ትገባ የነበረው ለምንድን ነው?* ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም *እግዚአብሔርን ውኃ እንዲሰጠኝ እየተማጸንኩት ነበር፡፡ በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን* አሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቅዱሳኑ አድሮ ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን የሚገልጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ በአባ ሙሴ ቅድስናም ተደነቁ፡፡

በአንዲት ዕለትም አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርስ በሔዱ ጊዜ አባ መቃርስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው *ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ* በማለት ለአባ ሙሴ ጸሊም ስለተዘገጀው የሰማዕትነት ክብር አስቀድመው ትንቢት ተናገሩ፡፡ አባ ሙሴም ይህን ቃል ሲሰሙ *አባቴ ሆይ እኔ እሆናለሁ፡፡ /በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው/ የሚል ጽሑፍ አለና* ብለው መለሱ፡፡

በብሉይ ኪዳን በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይሙት፤ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ፤ ወዘተ የሚል ሕግ ነበር /ዘፀ.፳፩፥፳፬-፳፭፤ ማቴ.፭፥፴፰/፤ አባ ሙሴ ጸሊምም ለገዳማዊ ሕይወት ከመብቃታቸው በፊት ሰዎችን በሰይፍ ሲያጠፉ እንደነበሩት ኹሉ እርሳቸውም በሰይፍ መሞት እንደሚገባቸው በማመን ራሳቸውን ለሞት አዘጋጁ፡፡ ይህም በንጹሕ ልቡናቸው ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸውን የሚያመለክት ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ያገኙትን ኹሉ በሰይፍ የሚገድሉ የበርበር ሰዎች ወደ በዓታቸው መጡ፡፡ አባ ሙሴም አብረዋቸው የነበሩትን መነኮሳት *መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ* አሏቸው፡፡ እነርሱም *አባታችን አንተስ አትሸሽምን?* አሏቸው፡፡ እርሳቸውም እኔ */በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላል/ ስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ይቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠባበቃት ኖሬአለሁ* በማለት ለሰማዕትነት መዘጋጀታቸውን ነገሯቸው፡፡

ይህን እየተነጋገሩ ሳሉም የበርበር ሰዎች ከበዓታቸው ገብተው በሰይፍ ቈርጠው ገደሏቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋርም ሰባት መነኮሳት ተገደሉ፡፡ አንደኛውም ከምንጣፍ ውስጥ ተሠውረው ከቆዩ በኋላ በእጁ አክሊል የያዘ የእግዚአብሔር መልአክ ቆሞ ሲጠባበቅ በተመለከቱ ጊዜ ከተሠወሩበት በመውጣት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አባ መቃርስ *ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ* በማለት የተናገሩት ትንቢት ተፈጸመ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም *አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው* ሲል የተናገረው ቃል ደረሰ /ሮሜ.፰፥፴/፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም በሰማዕትነት ያረፉት ሰኔ ፳፬ ቀን ሲኾን፣ ሥጋቸውም በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ እንደሚገኝና ከእርሱም ብዙ ድንቃ ድንቅና ተአምራት እንደሚታዩ በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፏል፡፡

በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር እቅፍ ርቀን የምንኖር ኹሉ፤ ከሃዲና ነፍሰ ገዳይ፣ ቀማኛና ዘማዊ የነበረውን ሰው ወደ አሚነ እግዚአብሔርና ወደ ገቢረ ጽድቅ በመለወጥ ደግ አባት፣ መምህር፣ የሚያጽናና ሥርዓትን የሚሠራ ካህን፣ እንዲሁም ሰማዕት፤ በተጨማሪም በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ስሙ ለዘለዓለሙ እንዲጠራ ያደረገችውን የንስሓን ኃይል በማስተዋል ዛሬዉኑ በንስሓ ልንመለስ ይገባል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን፣ ኃጢአትንም ይቅር የሚል አምላክ ነውና ኀጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድ ዘወትር እንማጸነው /ዘፀ.፴፬፥፯፤ ማቴ.፮፥፲፪/፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በአባ ሙሴ ጸሊምና በሰማዕታት ሁሉ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፬ ቀን፡፡

ንጉሥ ሰሎሞን ወልደ ዳዊት

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፳፫ ቀን በዛሬው ዕለት ንጉሥ ሰሎሞን፣ አባ ኖብ፣ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ፣ ቅዱስ ፊልጶስና ሌሎችም ቅዱሳን ይታወሳሉ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በመጽሐፈ ስንክሳር የተመዘገበዉን የንጉሥ ሰሎሞንን ታሪክ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ንጉሥ ዳዊት ሕግ ተላልፎ ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር ኀጢአት በሠራ ጊዜ ባሏን በማስገደሉ፤ ከእርሷ ጋርም በደል በመፈጸሙ እግዚአብሔር ነቢዩን ልኮ ከገሠፀው በኋላ ንስሐ ገብቶ መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ እግዚአብሔርም ንስሐዉን ተቀብሎ ኀጢአቱን ይቅር አለው፡፡ በኋላም በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤርሳቤህን ሚስቱ አደረጋትና ሰሎሞንን ወለዱ፡፡ ሰሎሞን ሲያድግም በዙፋኑ እንደሚተካው ንጉሥ ዳዊት ለቤርሳቤህ ቃል ገባላት፡፡

ሰሎሞን ፲፪ ዓመት በሞላው ጊዜም አዶንያስ በዳዊት ምትክ ለመንገሥ ዐስቦ በሮጌል ምድር ምንጭ አጠገብ ኤልቲ ዘዘኤልቲ በሚባል ቦታ ላሞችን፣ በጎችንና ፍየሎችን አርዶ የሠራዊት አለቆችን፤ የንጉሥ አሽከሮችንና ካህኑ አብያታርንም ጠርቶ ግብዣ አደረገ፡፡ እነርሱም *አዶንያስ ሺሕ ዓመት ያንግሥህ* እያሉ አወደሱት፡፡

ዳዊትም የአዶንያስን ሥራ ከቤርሳቤህና ከነቢዩ ከናታን በሰማ ጊዜ የዮዳሄን ልጅ ብንያስንና ካህኑ ሳዶቅን፣ ነቢዩ ናታንንም፣ ግራዝማችና ቀኛዝማቹን ኹሉ አስጠርቶ ሰሎሞንን በራሱ በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን እንዲያወርዱትና በዚያም ነቢዩ ናታንና ካህኑ ሳዶቅም ቀብተው እንዲያነግሡት፤ ሰሎሞንም በአባቱ ፈንታ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ አዘዘ፡፡

ካህኑ ሳዶቅም እንደታዘዘው ሰሎሞንን የንግሥና ቅባትን ቀባው፡፡ ቀርነ መለከቱንም ነፉ፤ ሕዝቡም ኹሉ ሰሎሞንን *ሺሕ ዓመት ያንግሥህ* እያሉ ተከትለዉት ወጡ፡፡ ከበሮም መቱ፤ ታላቅ ደስታም አደረጉ፡፡ ከድምፃቸውም የተነሣ ምድሪቱ ተናወጠች፡፡ ሰሎሞንም በመንግሥት ዙፋን ተቀመጠ፡፡ የንጉሡ አሽከሮችም *እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያድርገው፤ ዙፋኑንም ከዙፋንህ ይልቅ ከፍ ከፍ ያድርገው* እያሉ ዳዊትን አመሰገኑት፡፡ ዳዊትም *ዐይኖቼ እያዩ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ለእኔ ለባሪያው ዛሬ የሰጠ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን* አለ፡፡

የሚሞትበት ጊዜ በደረሰ ጊዜም ልጁ ሰሎሞንን *እኔ ሰው ኹሉ በሚሔድበት በሞት ጐዳና እሔዳለሁ፡፡ አንተ ግን ጽና፤ ብልህ ሰውም ኹን፡፡ በሕጉ ጸንተህ ትኖር ዘንድ በሙሴ ሕግ የተጻፈዉን የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ ጠብቅ* ብሎ አዘዘው፡፡

ከዳዊት ዕረፍትም በኋላ ሰሎሞን በገባዖን ምድር መሥዋዕትን በሠዋ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጾ *እሰጥህ ዘንድ ልብህ ያሰበዉን ለምነኝ* አለው፡፡ ሰሎሞንም *እኔ ባሪያህ መግቢያዬንና መውጫዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝና ለዚህ ለብዙ ወገንህ በእውነት እፈርድ፤ ክፉዉን ከበጎዉ ለይቼ ዐውቅ ዘንድ ዕውቀትን ስጠኝ* ብሎ ለመነው፡፡

እግዚአብሔርም *ብዙ ዘመንንና ባለጠግነትን፤ የጠላቶችህንም ጥፋት አለመንኸኝምና፡፡ ነገር ግን ፍርድ መስማትን ታውቅ ዘንድ ለምነሃልና እንሆ እንዳልህ አደረግሁልህ፡፡ እነሆ ከአንተ አስቀድሞ እንዳልነበረ፤ ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ እንዳይነሣ አድርጌ ብልህና አስተዋይ ልቡናን፤ ያለመንኸኝን ባለጠግነትንና ክብርንም በዘመንህ ኹሉ ሰጠሁህ* አለው፡፡

ሰሎሞንም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እውነተኛ ሕልም እንዳለመ ዐወቀ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶም በጽዮን በእግዚአብሔር ታቦተ ሕግ አንጻር ባለው መሠዊያ ፊት ቆሞ የሰላም መሥዋዕትን አቀረበ፡፡ ለሰዎቹና ለእሱም ታላቅ ግብዣ አደረገ፡፡

በዚያን ጊዜም ሁለት አመንዝራ ሴቶች ወደ እርሱ መጥተው በአንድ ቤት እንደሚኖሩና በሦስት ቀን ልዩነት ልጆችን እንደ ወለዱ፤ አንደኛዋ ሴትም ልጇን በሌሊት ተጭናው በሞተባት ጊዜ ያልመተዉን የሌላኛዋን ልጅ ወስዳ የሞተዉን ልጅ እንዳስታቀፈቻት በማብራራት የሞተው ልጅ ያንቺ ነው፤ ደኅናው ልጅ የኔ ነው የሚል ክሳቸዉን ለንጉሡ አሰሙ፡፡

ንጉሡም የሁለቱንም ንግግር ካደመጠ በኋላ *ደኅነኛዉን ልጅ በሰይፍ ቈርጣችሁ እኵል አካፍሏቸው* ብሎ አዘዘ፡፡

ያልሞተው ልጅ እናትም *ልጁን አትግደሉት፡፡ ደኅናዉን ለእርሷ ስጧት ስትል፤ ሁለተኛዋ ሴት ግን ቈርጣችሁ አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእርሷም አይሁን* አለች፡፡

ንጉሡም *ልጁን አትግደሉት* ላለችው ሴት ደኅነኛዉን ሕፃን ስጧት፤ እርሷ እናቱ ናትና ብሎ ፈረደ፡፡

እስራኤልም ኹሉ ቅን ፍርድ ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በእርሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና ንጉሡን ፈሩት፡፡

ከዚህ በኋላ እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በ፬፻፹ኛው፤ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በ፬ኛው ዓመት፣ በ፪ኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ጀምሮ በ፲፩ኛው ዘመነ መንግሥቱ፣ በ፰ኛው ወር ሠርቶ በ፯ ዓመታት ውስጥ ፈጸመው፡፡ የራሱን ቤትም በ፲፫ ዓመት ሠርቶ ጨረሰ፡፡

ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና የራሱን ቤት ከፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሎች፣ የነገድና የአባቶቻቸዉን ቤት አለቆች ኹሉ በ፯ኛው ወር (በጥቅምት) በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው፡፡ ካህናቱም ታቦቷን፣ የምስክሩን ድንኳንና ንዋያተ ቅድሳቱን ኹሉ ተሸክመው ንጉሡና ሕዝቡም በታቦቷ ፊት ሥፍር ቍጥር የሌላቸዉን በጎችንና ላሞችን እየሠዉ ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አገቧት፡፡

ከዚህ በኋላ ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ የእግዚአብሔር ብርሃን ቤተ መቅደሱን ሞላው፡፡ ካህናቱም ሥራቸዉን መሥራትና ከብርሃኑ ፊቱ መቆም ተሳናቸው፡፡ ያንጊዜም ሰሎሞን *እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁ ብሏል፤ እኔም ለዘለዓለም የምትኖርበት ማደሪያህ ቤተ መቅደሱን በእውነት ሠራሁልህ* አለ፡፡ ከዚያም ፊቱን ወደ መሠዊያው መልሶ፣ እጆቹን ዘርግቶ፣ በጕልበቱ ተንበርክኮ ሰገደና ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አደረሰ፤ ሕዝቡንም ኹሉ መረቃቸው፡፡

ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላም ከመሠዊያው ፊት ተነሥቶ ቆመና *ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን* እያለ በታላቅ ቃል የእስራኤልን ማኅበር መረቃቸው፡፡ ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርበው ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ፡፡ ሰሎሞን ስለ ሰላም ለእግዚአብሔር የሠዋቸው በጎችም ፳፪ ሺሕ ነበሩ፡፡

ዳግመኛም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጾ *የለመንኸኝን ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ፤ እንደ ልመናህም ኹሉ አደረግሁልህ፡፡ ስሜ በዚያ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸዉን ቤተ መቅደስ አከበርሁት፡፡ ልቡናዬም፣ ዐይኖቼም በዘመኑ ኹሉ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ* አለው፡፡

እግዚአብሔር ብዙ ጥበብና ጸጋን የሰጠው ይህ ታላቅ ንጉሥ ለዐርባ ዓመት እስራኤልን በቅንነት አስተዳድሯል፡፡ ከንግሥናው በተጨማሪም ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅሙ፣ ትንቢትንና ትምህርትን የያዙ የጥበብና የመዝሙር መጻሕፍትንም ጽፏል፤ እነዚህም፡- መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፣ መጽሐፈ መክብብ፣ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መጽሐፈ ተግሣፅና መጽሐፈ ጥበብ ናቸው፡፡

ንጉሥ ሰሎሞን ከመንገሡ በፊት ፲፪፤ ከንግሥናው በኋላ ፵፤ በድምሩ ፶፪ ዓመታት በሕይወተ ሥጋ ከኖረ በኋላ በዛሬው ዕለት ሰኔ ፳፫ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፏል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን፡፡ የአባቶቻችን በረከት ይደርብን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፫ ቀን፡፡

*ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እየገነባን እኛ ከቤቱ ርቀናል*

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በደብረ ማርቆስ ማእከልና በዝግጅት ክፍሉ

ይህ ኃይለ ቃል የብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ንግግር ሲኾን፣ ኃይለ ቃሉን የተናገሩትም በደብረ ማርቆስ ከተማ ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የባሕረ ጥምቀት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠበት ዕለት ነው፡፡

በሥርዓቱ ላይም ብፁዕነታቸውን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ በከተማው የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ካህናትና የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ታቦተ ሕግ በማክበር፤ እንደዚሁም የምሥራቅ ጐጃም ዞን አስተዳደር፣ የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባና ሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በዕለቱ ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ የባሕረ ጥምቀቱ የመሠረት ድንጋይ በቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን (በበዓለ ኀምሳ) መቀመጡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ የሚያሳይ መኾኑን ጠቅሰው *የቀድሞ አባቶቻችን ቤታቸዉ ሳይቀር ቤተ ክርስቲያን ነበር፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እየገነባን እኛ ከቤቱ ርቀናል፡፡ ስለኾነም ከኹሉም አስቀድሞ ራሳችንን ወደ ቤተ ክርስቲያን ማቅረብ ያስፈልጋል* ሲሉ አባታዊ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕነታቸው አያይዘውም በባሕረ ጥምቀቱ ቦታ ላይ የጸበል መጠመቂያ ገንዳ፣ ዐዉደ ምሕረት፣ አጥርና የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች እንደሚከናወኑና የግንባታዉ ጠቅላላ ወጪም ከ፲፰ እስከ ፳ ሚሊዮን ብር እንደሚጠይቅ የባለሙያዎችን ጥናት መነሻ በማድረግ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ለቦታዉ መከበርና ለግንባታዉ መፋጠን ኹሉም ምእመናን ሃይማኖታዊ ሓላፊታቸዉን መወጣት እንደሚገባቸው አባታዊ ምክራቸዉን ለግሰዋል፡፡

የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ቆሞስ አባ እንባቆም ጫኔ የባሕረ ጥምቀቱን ቦታ አስመልክቶ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከኰሚቴው ጎን በመሰለፍ ቦታውን ለማስከበር ልዩ ልዩ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረውን የደብረ ማርቆስ ሕዝብ አመስግነው *ይህንን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥራ በመፈጸም ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል መላው ሕዝበ ክርስቲያን በጸሎቱ፣ በዐሳቡ፣ በዕውቀቱ፣ በገንዘቡና በጉልበቱ ድጋፉ እንዳይለየን* ሲሉ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የምሥራቅ ጐጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ ምግባሩ ከበደ በዕለቱ ንግግር ሲያደርጉ *ጥያቄያችሁ መልስ በማግኘቱ እንኳን ደስ አላችሁ* ካሉ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱን *ቤተ ክርስቲያን ለረዥም ጊዜ ጠብቃ ያቆየችዉን ወርቃማ የሥነ ምግባር፣ የሰላምና የፍቅር አስተምህሮ የማስጠበቂያ ቦታ ማድረግ ይገባል* ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የዕለቱ መርሐ ግብር ተፈጽሟል፡፡

የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት በብፁዕ አቡነ ማርቆስ መመሪያ ሰጭነት መስከረም ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በተቋቋመው ኰሚቴ ጥያቄ መሠረት ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለባሕረ ጥምቀት አገልግሎት የሚዉል ፶ ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ መረከቡን ከደብረ ማርቆስ ማእከል የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡

ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበልን ሰኔ ፳ ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኀ በሦስት ድንጋዮች በተወደደ ልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታነጸበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከሚከብሩ ከእመቤታችን በዓላት አንደኛው ሲኾን ታሪኩንም በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ጌታችን በዐረገ በስምንተኛው ዓመት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ገብተው በክርስቶስ ስም አሳምነው ብዙ አሕዛብን ካጠመቁ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩላቸው ወደዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ርእሰ ሐዋርያት እያለ እኛ መሥራት አይገባንም ብለው በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ላኩበት፡፡ እርሱም ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር መጥቶ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ በርናባስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኙ፡፡

በዚያም በአንድነት ሱባዔ ይዘው ከቆዩ በኋላ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶ ቅዱሳን ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ አገር ሰብስቦ ‹‹በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራዉን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቤአችኋለሁ›› ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬፤ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰም እሳት ሲያገኘው እንዲለመልም፣ ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳበላቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመዉታል፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራዉም ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲኾን፣ በ፳፩ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፤ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ኾኖ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላ ‹‹እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ›› ብሎ አዝዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡

ይህ ታሪክ ብዙ ምሳሌዎች አሉት፡፡ ይኸውም፡- የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት በነገሥታት ዘመን የነበሩ የ፳፬ቱ ነቢያት፤ አንድም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ሲኾን፣ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲኾኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፤ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መኾኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል፡፡ የሠሩትም ሦስት ክፍል አድርገው ሲኾን፣ ይህም የመጀመሪያው የታቦተ አዳም፤ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፤ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የመጀመሪያው የጽርሐ አርያም፣ ሁለተኛው የኢዮር፣ ሦስተኛው የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡

አንድም መጀመሪያው የኤረር፣ ሁለተኛው የራማ፣ ሦስተኛው የኢዮር አምሳል ነው፡፡ በኤረር፡- መላእክት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፤ በራማ፡- ሥልጣናት፣ መናብርት፣ አርባብ፤ በኢዮር፡- ኃይላት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዘጠኙ ነገደ መላእክት የዘጠኙ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን (መዓርጋተ ክህነት) አምሳል ሲኾኑ፣ ይኸውም መላእክት – የመዘምራን፤ መኳንንት – የአናጕንስጢሳውያን፤ ሊቃናት – የንፍቀ ዲያቆናት፤ ሥልጣናት – የዲያቆናት፤ መናብርት – የቀሳውስት፤ አርባብ – የቆሞሳት፤ ኃይላት – የኤጲስ ቆጶሳት፤ ሱራፌል – የጳጳሳት፤ ኪሩቤል – የሊቃነ ጳጳሳት አምሳሎች ናቸው፡፡

ይህም በታች (በምድር) የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ከቅዱሳን በቀር ወደ ላይ (ወደ ሰማይ) መውጣት እንደማይቻላቸው፣ ከመዘምራን እስከ ጳጳሳት ድረስ ያሉ ካህናትም ከእነርሱ በላይ ያሉትን መዓርግ መሥራት (መፈጸም) እንደማይቻላቸው ያጠይቃል፡፡ እንደዚሁም በላይ የሚኖሩ መላእክት ወደ ታች መውረድ እንደሚቻላቸው ሊቃነ ጳጳሳትም ከእነርሱ በታች ያሉ ካህናትን ተልእኮ መፈጸም (መሥራት) እንደሚቻላቸው ያስረዳል፡፡

በጽርሐ አርያም መንበረ ብርሃን (የብርሃን መንበር)፤ ታቦተ ብርሃን (የብርሃን ታቦት)፤ መንጦላዕተ ብርሃን (የብርሃን መጋረጃ)፤ እንደዚሁም ፬ ፀወርተ መንበር (መንበሩን የሚሸከሙ)፤ ፳፬ አጠንተ መንበር (መንበሩን የሚያጥኑ) መላእክት አሉ፡፡ ጽርሐ አርያም – የመቅደስ፤ መንበረ ብርሃን – የመንበር፤ መንጦላዕተ ብርሃን – የቤተ መቅደሱ መጋረጃ፤ ፬ቱ ፀወርተ መንበር – የ፬ቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የመንበሩ እግሮች፤ ፳፬ቱ አጠንተ መንበር – የጳጳሳት (የኤጲስ ቆጶሳት) አምሳሎች ናቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳ ቀን፡፡
  • መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፫፻፵፱ – ፫፻፶፩፡፡

የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ዛሬ አስመረቀ፡፡

ሰኔ ፲፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ለአምስትና ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ዛሬ ረፋድ ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ አስመረቀ፡፡

በምረቃው ሥርዓት ላይም ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያዎች ሓላፊዎች፣ የሀገረ ስብከት ሠራተኞች፣ የገዳማት፣ የአድባራትና የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ የኮሌጁ መምህራን፣ ደቀ መዛሙርትና ሠራተኞች፣ እንደዚሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂዎች ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ኮሌጁ ከተመሠረተበት ከ፲፱፴፭ ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ሊቃውንትን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው በዛሬው ዕለትም በቀኑና በማታው መርሐ ግብር ትርጓሜ መጻሕፍትን ተምረው በድምሩ ፪፴፮ (ሁለት መቶ ሠላሳ ስድስት) ዕጩ መምህራን መመረቃቸዉን፤ ከእነዚህ መካከልም አንደኛው ማየት የተሳናቸው፤ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች መኾናቸውን ተናገረዋል፡፡

በዕለቱ በመንፈሳዊ ኮሌጁ ደቀ መዘሙርትና ዕጩ መምህራን ያሬዳዊ ዝማሬ የቀረበ ሲኾን፣ በተጨማሪም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን የሚያወድሱ፤ አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲስተካከሉ የሚጠቁሙ ቅኔያት ከተበረከቱ በኋላ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎች ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከብፁዕ ሥራ አስኪያጁ እጅ የሽልማትና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

ተመራቂ መምህራኑም በተወካያቸው አማካኝነት የዓቋም መግለጫቸዉን ያሰሙ ሲኾን፣ በዓቋም መግለጫቸውም ለመምህራን የበጀት ማስተካከያ እንዲደረግና በኮሌጁ ከሚሰጡት የብሉያትና የሐዲሳት ትርጓሜ ትምህርቶች በተጨማሪ መጻሕፍተ ሊቃውንትና መነኮሳትም መካተት እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ተመራቂዎቹ አያይዘውም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጠብቀው እንደሚያስጠብቁ፤ የመናፍቃንን (የሐራ ጥቃዎችን) የኑፋቄ ትምህርት በጽናት እንደሚታገሉ፤ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸዉም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሕይወታቸዉን አሳልፈው እንደሚሰጡ፤ እንደዚሁም ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያወጣቸውን ቀኖናዎችን በማክበር ቤተ ክርስቲያንን በታዛዥነት እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በምረቃ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ሲያደርጉ እንደገለጹት መንፈሳዊ ኮሌጁ ያሉበት ችግሮች መዋቅራቸዉን ጠብቀው ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለቅዱስ ሲኖዶስ ቢቀርቡ ተገቢ እንደ ኾነ ገልጸው *ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጉዳዮችን በማጣራት ለችግሮቹ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነው* ብለዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊም አባታዊ ቃለ ምዕዳን በሰጡበት ወቅት ስብከተ ወንጌል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አገልግሎት መኾኑን ጠቅሰው የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጨምሮ ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ግንባር ቀደም በመኾን የጊዜውን የኑሮ ኹኔታ ባገናዘበ መልኩ የመምህራኑንና የደቀ መዛሙርቱን በጀት ለማስተካከል መዘጋጀት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ የምረቃ ሥርዓቱ ከቀኑ 6፡25 ተፈጽሟል፡፡

ወረደ መንፈስ ቅዱስ

ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መንፈስ ቅዱስ ማለት ከሦስቱ አካላት (ከቅድስት ሥላሴ) አንዱ፤ የእግዚአብሔር አብ፣ የእግዚአብሔር ወልድና የራሱም አካላዊ እስትንፋስ የኾነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

*ወረደ መንፈስ ቅዱስ* የሚለው የግእዝ ዓረፍተ ነገርም *መንፈስ ቅዱስ ወረደ* የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን፣ ይህ ሲባልም በሰዉኛ ቋንቋ ከከፍታ ወደ ዝቅታ፣ ከሩቅ ወደ ቅርብ መምጣቱን ወይም መውረዱን ሳይኾን የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያት ላይ አድሮ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብን መግለጹንና ልዩ ልዩ ጸጋን ማደሉን ያመላክታል፡፡

ይህ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለጊዜው ለሐዋርያት ቢሰጥም፣ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይገደብ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ በምእመናን ላይም አድሮ ይኖራል፡፡

ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ወረደ የሚለው ትምህርት መንፈስ ቅዱስን በቦታ፣ በጊዜና በወሰን መገደቡን አያመለክትም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በዓለሙ ኹሉ የሞላ ነውና፡፡ በሰው ላይ አድሮ ጥበብን ሲገልጽ ግን ሞላ፤ አደረ፤ ወረደ ተብሎ ይነገራል፡፡ ይኸውም ሥራዉን በሰው ላይ መግለጡን፣ ጸጋዉንም ማብዛቱን ለማመልከት የሚያገለግል ቋንቋ ነው፡፡

ከላይ እንደ ተገለጸው እግዚአብሔር በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ፍርኃትን አስወግዶ ጥብዓትን (ጭካኔን)፣ ስጋትን አጥፍቶ ቈራጥነትን (ድፍረትን) ማሳደሩን፤ እንደዚሁም ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብንና ጸጋን እንዲያገኙ ማድረጉን፤ በዚህም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌልና ለሰማዕትነት የሚያበቃ ቅድስና ላይ መድረሳቸዉን ያመለክታል፡፡

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት፣ በተጠመቀባትና ከሞታን ተለይቶ በተነሣባት በዕለተ ሰንበት (በሰንበት ክርስቲያን) ሲኾን፣ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ሰንበት (ከኀምሳኛው ቀን) ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሰንበት ያለው ጊዜም (ስምንቱ ቀናት) ዘመነ ጰራቅሊጦስ ወይም ሰሙነ ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ስለ መውረዱና በምእመናን ላይ ስለ ማደሩ የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡

በዚህ ሰሙን በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር፣ የሚሰጠውም ትምህርት የመንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ መውረድ የሚመለከት ነው፡፡ ስለዚህም ከኀምሳኛው ቀን (ከበዓለ ጰራቅሊጦስ) ቀጥሎ በሚመጣው እሑድ (በስምንተኛው ቀን) በሌሊት በሊቃውንቱ የሚዘመረው መዝሙር፡- *ወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሐዋርያት ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኵሉ በሐውርት* የሚል ሲኾን፣ ትርጕሙም መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በሐዋርያት ላይ መውረዱንና በእርሱ ኃይል በዓለሙ ኹሉ ቋንቋዎች መናገራቸዉን የሚያስረዳ ነው፡፡

በዚህ ዕለት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም፡- የሚከተሉት ናቸው፤ ኤፌ.፬፥፩-፲፯፤ ፩ኛዮሐ.፪፥፩-፲፰፤ ሐዋ.፪፥፩-፲፰፤ መዝ.፷፯፥፲፰ (ምስባክ)፤ ዮሐ.፲፬፥፩-፳፪ (ወንጌል)፡፡

የምንባባቱ ፍሬ ዐሳብም የጳውሎስ መልእክት፡- እያንዳንዳችን መንፈስ ቅዱስ በገለጸልን መጠን የየራሳችን ልዩ ልዩ ጸጋ እንዳለን፤ የዮሐንስ መልእክት፡- የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ለዘለዓለም ሕያው እንደ ኾነ፤ የሐዋርያት ሥራ፡- መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ እንደ ወረደና በዓለሙ ኹሉ ቋንቋዎች መናገር እንደቻሉ፤ መዝሙረ ዳዊት (ምስባኩ)፡- እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ልዩ ልዩ ጸጋን እንደሚሰጥ፤ የዮሐንስ ወንጌል፡- እግዚአብሔር እኛን ልጆቹን እንደ ወላጅ አልባ እንደማይተወን ያስረዳሉ፡፡

ቅዳሴውም ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ሲኾን፣ ይህም ምሥጢረ ሥላሴን፣ የጌታችንን ሰው መኾን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉን፣ ዕርገቱንና መንፈስ ቅዱስን መላኩን ይናገራል፡፡

ቅድስት በኾነች በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደው የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በኹላችን ላይ ይደር፤ እጽፍ ድርብም ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጰራቅሊጦስ ከሣቴ ምሥጢር

ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በመምህር ማዕበል ፈጠነ

ጰራቅሊጦስ ማለት ከሣቴ ምሥጢር ማለት ነው፡፡ ይኸውም በግብሩ ታውቋል፡፡ በበዓለ ጰራቅሊጦስ አበው ሐዋርያት ብዙ ምሥጢር በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ብሉይና ሐዲስን ተርጕመዋል፡፡

ማለትም ወደ ኋላ ተመልሰው *እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን ሥጋ በለበሰ ኹሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፡፡ ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤* ተብሎ የተነገረውን ትንቢት ጠቅሰው፣ በመብረቅ መጽሔት ተሞልተው ወደ ፊት የሰው ልጅ በሃይማኖትና በምግባር የሚወርሳትን የመንግሥተ ሰማይን ተስፋ አብሥረዋል /ሐዋ.፪፥፲፯፤ ኢዩ.፪፥፲፰/፡፡

ከቀደመው ቋንቋቸው ሌላ ፸፩ ቋንቋ ተገልጾላቸው በ፸፪ ቋንቋ አስተምረዋል፡፡ ይህ ሲባል ግን በዘመኑ የነበረው ሕዝብ እርስበርስ ይግባባቸው የነበሩት ቋንቋዎች ፸፪ ስለ ነበሩ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ ከዚህም በላይ ቋንቋዎችንና ጥበብን መግለጽ እንደሚቻለው ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ጥንተ ነገሩስ እንደምን ነው ቢሉ ጌታችን በዚህ ዓለም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌለ መንግሥትን አስተምሮ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ በሲኦል የነበሩ ነፍሳተ ሙታንን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ አውጥቶ የሲኦልን በር ዘግቷል፡፡

በዚህ ዓለም ደግሞ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ፵ ቀን ለአበው ሐዋርያት በመጽሐፈ ኪዳን የተገለጹ ረቂቅ ምሥጢራትን አስተምሮ መንፈስ ቅዱስ ትርጕሙን እንደሚነግራቸው፤ በሰዓቱ ግን መሸከም እንደማይችሉ ነግሯቸው ባረገ በ፲ኛው ቀን ለ፲፪ቱ ሐዋርያት፣ ለ፸፪ቱ አርድእትና ለ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ ለ፻፳ው ቤተሰብ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በአዲስ ልሳን መናገር ጀምረዋል፡፡

አዲስ ልሳን ሲባልም በዓለም የሌለ ሌላ ባዕድ ቋንቋ ማለት አይደለም፡፡ የዓለም ቋንቋዎች ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት በሐዋርያት አንደበት ተዋሐዱ፤ በልቦናቸው አደሩ፤ ሐዋርያት በዕውቀት ታነፁ ማለት ነው እንጂ፡፡ እንደሚታውቀው የሰው ልጅ የዓለማትን ቋንቋ በሙሉ ተምሮ ለማወቅ አይቻለዉም፡፡ አበው ሐዋርያት ግን ከሥጋዊ፣ ከደማዊ መምህር በመማር፤ መልክአ ፊደል በማጥናት ሳይኾን፣ መንፈስ ቅዱስ ገልጾላቸው አንደበታቸው ሰይፍ፣ ልሳናቸው ርቱዕ፣ ኾኖ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች መናገር ችለዋል፡፡

ነገር ግን ሐዋርያት ባዕድ ቋንቋ አላመጡም፡፡ ጌታም የገለጸላቸው የዚህ ዓለም ብርሃን እንደመኾናቸው በዓለም የሚነገሩ ቋንቋዎችን ነው፡፡ ሰው የማይሰማውን ቋንቋ ቢናገሩ ኖሮ ከነፋስ ጋር እንደመናገር ይቈጠር ነበር /፩ኛቆሮ.፲፬፥፱/፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ *ወአኀዙ ይንብቡ ዘዘዚአሆሙ በነገረ ኵሉ በሐውርት በከመ ወሀቦሙ መንፈስ ቅዱስ፤ ኹሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፡፡ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዳደላቸው መጠንም እየራሳቸው በአገሩ ኹሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩ፤* በማለት ገልጾታል /ሐዋ.፪፥፬/፡፡

በዚህ ጊዜ ቤተ አይሁድ በከፊል አንጎራጎሩ፤ አሕዛብ ተደመሙ፡፡ ሐዋርያትን በገዛ ቋንቋቸው ሲናገሩ ሰምተው *እኛ የጳርቴ፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች ስንኾን፣ በእኛ ቋንቋ እነሆ የእግዚአብሔርን ጌትነት ሲናገሩ እንሰማዋቸዋልን* ሲሉ አደነቁ፤ ከእግራቸው ሥርም ወደቁ፡፡ በቅፅበትም ሦስት ሺህ ነፍሳት አምነው ተጠመቁ፡፡

በዚህ ዘመን በግላቸው ቤተ እምነት መሥርተው የሚኖሩ ባዕዳን *መንፈስ ቅዱስ ወረደልን፤ አዲስ ልሳን ተገለጠልን፤ እልል በሉ፤* እያሉ ዐይናቸውን ይጨፍናሉ፤ አእምሯቸውን ይስታሉ፡፡ በአንደበታቸውም እነርሱ የማያውቁትን፤ ሌላ ሰውም ሊሰማው የማይችለዉን ትርጕም የሌለዉን ጩኸት፣ እነርሱ ልሳን የሚሉትን ድምፅ ያነበንባሉ፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ዓላማ ሰዎች እርስበርስ እንዲግባቡ ትርጕም ያለዉን ቋንቋ መግለጽ እና ኹሉም በየቋንቋው የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል እንዲማር፣ እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ ነው፡፡ ልሳን ማለትም ሰው ሊረዳውና ሊግባባት የሚችል ቋንቋ ማለት እንጂ ድምፅ በማውጣት ብቻ የሚገለጽ ጩኸት አይደለም፡፡ መናፍቃኑ ልሳን የሚሉት ግን ይህንኑ ዓይነት ባዶ ጩኸት ነው፡፡ ይህም ከሰይጣን እንጂ ከመንፈስ ቅዱስ እንዳልኾነ ያጠይቃል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ የሆነው አዲስ ልሳን ግን ትናንት በአበው ሐዋርያት ዘመን የነበረ፤ ዛሬም በእኛ ዘመን ያለ፤ ለመጭው ትውልድም የሚተላለፍ ሕያው ልሳን ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከሣቴ ምሥጢሩ (ምሥጢር ገላጩ) መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡

እንግዲህ በነቢያት የተነገረው፣ በሐዋርያት ልቡና በእሳት አምሳል የተገለጠው ምሥጢረ መንፈስ ቅዱስ ይህ ነው፡፡ ይህ ምሥጢር ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፎ በሐዋርያት ልቡና ቀርቷል፤ ከሐዋርያት ልቡና ያልደረሰው ደግሞ በልበ መንፈስ ቅዱስ ቀርቷል፡፡ ዓውደ ትምህርቱ ይህ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

አባ ገሪማ ዘመደራ

ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲቆን ኤፍሬም የኔሰው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘውን፣ በኋላም በጉባኤ ኬልቄዶን ጊዜ በመለካውያን አማካኝነት የመጣውን የሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርይ የኑፋቄ እምነት አንቀበልም በማለታቸው በባዛንታይን ነገሥታት ስቃይ የጸናባቸው ተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን መነኮሳት ከሶርያና ከታናሽ እስያ ተሰደው በአልአሜዳ ዘመነ መንግሥት በ፬፻፹ ዓ.ም ወደ አገራችን ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡

በዘመኑ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትም ከአባቶቹ በወረሰው የደግነትና እንግዳ ተቀባይነት ባህሉ በፍቅር ተቀብሏቸዋል፡፡

እነዚህ ዘጠኙ ቅዱሳን በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል፤ በወቅቱ ብሔራዊ ቋንቋ የነበረዉን ግእዝ በሚገባ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስትና ከጽርዕ ቋንቋዎች ወደ ግእዝ ተርጕመዋል፡፡ እንደዚሁም በስማቸው የሚጠሩ ገዳማትንና ሌሎችንም አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከፈጸሟቸው መንፈሳውያን ተልእኮዎች፣ ካደረጓቸው ተአምራትና መልካም ሥራዎች አኳያ ቅዱሳን በሚል መዓርግ ትጠራቸዋለች፤ በስማቸውም ጽላት ቀርፃ በዓላቸውን ታከብርላቸዋለች፡፡

ዘጠኙ ቅዱሳን የሚባሉት አባቶችም፡- አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ አፍጼ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጉባ፣ አባ ይምአታ፣ አባ ጰንጠሌዎን እና አባ ጽሕማ ናቸው፡፡ /ምንጭ፡- የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.ታ፣ አባ ጎርጎርዮስ ዘሸዋ፣ ፲፱፻፺፩ ዓ.ም፤ ገጽ ፳፫-፳፬/፡፡

በዛሬው ዝግጅታችን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የኾኑትን የአባ ገሪማን ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤

በሮም አገር መስፍንያኖስ የሚባል ንጉሥ ነበረ፤ ሚስቱም ሰፍንግያ ትባላለች፡፡ መካን ስለነበረች በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በመማጸን ልጅ እንዲሰጣት እግዚአብሔርን ስትለምን ከኖረች በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ይስሐቅ አለችው፡፡ የያን ጊዜው ይስሐቅ የኋላው አባ ገሪማ በመንፈሳዊ ሥርዓት ካደገ በኋላም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምሮ በዲቁና ማገልገል ጀመረ፡፡

ይስሐቅ ወላጅ አባቱ ሲሞትም በአባቱ ዙፋን ተተክቶ ለሰባት ዓመታት ሮምን በንጉሥነት ሲያስተዳድር ከቆየ በኋላ በዋሻ ይኖሩ የነበሩት አባ ጰንጠሌዎን ዘጾማዕት *ይስሐቅ ሆይ፣ ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸውና የማያልፈዉን የክርስቶስን መንግሥት ትሻ ዘንድ ወደ እኔ ና፤* ብለው ላኩበት፡፡ መልእክቱ እንደ ደረሰውም መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ወደ አባ ጰንጠሌዎን ሲሔድ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ በብርሃናውያን ክንፎቹ ተሸክሞ ዐሥር ወር የሚወስደዉን መንገድ በሦስት ሰዓታት አስጉዞ ከአባ ጰንጠሌዎን ደጅ አደረሰው፡፡

አባ ይስሐቅ (አባ ገሪማ) በአባ ጰንጠሌዎን እጅ ከመነኰሱ በኋላ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተጠምደው ቆዳቸው ከዐፅማቸው እስኪጣበቅ ድረስ ተጋድሎ ሲፈጸሙ ከቆዩ በኋላ ወደ መደራ ሔደው በእግዚአብሔር ኃይል ድንቆችንና ተአምራትን እየያደረጉ፣ በሽተኞችን እየፈወሱ፣ አጋንንትን እያስወጡ ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡

ካደረጓቸው ተአምራት መካከልም በጠዋት ሥንዴ ዘርተው፣ በሠርክ ሰብስበው መሥዋዕት ካሳረጉ በኋላ በማግሥቱ ከግራር ዛፍ ላይ በሬዎችን አውጥተው ሥንዴዉን አበራይተው ሰባ ሰባት የእንቅብ መሥፈሪያ መሰብሰባቸው አንደኛው ሲኾን፣ ዳግመኛም በዓለት የተከሏት ወይን ወዲያው በቅላ፣ አብባ አፍርታለች፤ በዚህም መሥዋዕት አሳርገዋል፡፡

እንደዚሁም አንድ ቀን መጽሐፍ እየጻፉ ሳሉ ፀሐይ ሊጠልቅ በተቃረበ ጊዜ ጸሎት አድርሰው ጽሕፈታቸዉን እስኪፈጽሙ ድረስ እንደ ኢያሱ ፀሐይን በቦታው እንዲቆም አድርገዋል፡፡ ምራቃቸዉን ትፍ ያሉበት ሥፍራም እስከ ዛሬ ድረስ ሕሙማን ይፈዉሳል፡፡ እንደዚሁም ከእጃቸው የወደቀው ብርዕ ወዲያው መብቀሉንና አቈጥቍጦ ማደጉን መጸሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡

በአንዲት ዕለትም መቅኑናቸውን ተቀብለው ከመነኮሳት ጋር ሲሔዱ መንገድ ላይ ቤተ ክርስቲያን አግኝተው ሲጸልዩ ካህናቱ ቅዳሴ እንዲያሟሉላቸው በጠየቋቸው ጊዜ ሌሎቹ ምግብ በልተው ነበርና አንችልም ሲሉ አባ ይስሐቅ ግን ምግብ አልተመገቡም ነበርና መቅኑናቸዉን አስቀምጠው ቅዳሴውን አሟልተዋል፡፡ ባልንጀሮቻቸው ግን በልተው የቀደሱ መስሏቸው ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው *ቀሲስ ይስሐቅ ከበላ በኋላ ቀደሰ* ብለው ከሰሷቸው፡፡

አባ ጰንጠሌዎንም አባ ይስሐቅ ሲመለስ *የምጠይቅህ ምሥጢር ስላለኝ ሰዎችን ከአጠገብህ ገለል አድርጋቸው* ሲሏቸው አባ ይስሐቅም *ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ገለል ይበሉ* ብለው መለሱላቸው፡፡ ወዲያዉኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ከቦታቸው ሸሹ፡፡

በዚህ ጊዜ አባ ጰንጠሌዎን *ኦ ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ፤ ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ* ሲሉ አደነቋቸው፡፡ አባ ገሪማ ተብለው መጠራት የጀመሩትም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ *ገሪማ ገረምከኒ አስኬማከኒ አልባቲ ሙስና፤ አባ ገሪማ አስገረምኸኝ፡፡ ለምንኵስናህም እንከን የለባትም፤* በማለት አመስግኗቸዋል፡፡

አባ ገሪማን ሳያዉቁ የከሰሷቸው መነኮሳትም ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ከዚያም መደራ ገብተው በዓት ሠርተው ለ፳፫ ዓመታት በትኅርምት ኖረው መልካም ተጋድሏቸውንና የቀና አካሔዳቸዉን በፈጸሙ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኔ ፲፯ ቀን ተገልጦ ስማቸውን የሚጠሩትን፣ መታሰቢያቸዉን የሚያደርጉትን፣ ገድላቸዉን የሚጽፉ፣ የሚያነቡና የሚተረጕሙትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንፁትንና የሚያገለግሉትን ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍላቸው ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡

አባ ገሪማም ይህንን ታላቅ ሀብት የሰጣቸዉን እግዚአብሔርን አመስግነው ከተደሰቱ በኋላ በብርሃን ሠረገላ ተነጥቀው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል፡፡ አባ ገሪማ የተሠወሩበት ሰኔ ፲፯ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን በተለይ በገዳማቸው በመደራ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸዉም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፲፯ ቀን፡፡

መዝገበ ታሪክ ክፍል ፪፣ መ/ር ኅሩይ ኤርምያስ፣ ገጽ ፺፱-፻፡፡

፫.ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት

ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

እንደሚታወቀው በዓለ ጰራቅሊጦስን ተከትለው ሁለት ዐበይት አጽዋማት ይጀመራሉ፡፡ እነዚህም ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ) ሲኾኑ፣ ቍጥራቸውም ከሰባቱ አጽዋማት ውስጥ ነው፡፡ ስለኾነም ኹላችንም ልንጾማቸው እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሕግ ታዝዟል፡፡ ይህም ከቀደሙ አባቶቻችን ጀምሮ የመጣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት እንጂ እንግዳ ሕግ አይደለም፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚናገሩት በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማሩ በፊት ጾሟል /ዘፀ.፴፬፥፳፰/፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም የተስፋውን ቃል መፈጸም እየተጠባበቁ እግዚአብሔርን ውረድ፤ ተወለድ እያሉ ይጾሙ፣ ይጸልዩ ነበር፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጾም የምግባር መሠረት መኾኑን ሊያስተምረን ወንጌልን ከመስበኩ አስቀድሞ ጾሟል /ማቴ.፬፥፩-፲፩/፤ ሐዋርያትም በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ሕገ ወንጌልን ለሕዝቡ ከማስተማራቸው አስቀድሞ ጾመዋል፡፡

እኛም እነርሱን ተከትለን፣ በእነርሱ ሥርዓት በመመራት፣ በሐዋርያት ላይ ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብት በእኛም ላይ እንዲያድርብን በየዓመቱ ጾመ ሐዋርያትንና ሌሎችንም አጽዋማት መጾም እንደሚገባን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል /ፍት.ነገ. ፲፭፥፭፻፹፮/፡፡

ጾመ ድኅነት ስሙ እንደሚያመለክተው የመዳን ጾም ማለት ሲኾን፣ ይህም በብሉይ ኪዳኑ አጽዋማት በጾመ አስቴር እና በጾመ ዮዲት የተተካ የሐዲስ ኪዳን ጾም ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በሐማ ምክንያት በእስራኤል ላይ ታውጆ የነበረው ሞት በጾመ አስቴር እንደ ተሻረ ኹሉ፣ በሐዲስ ኪዳንም በዕለተ ረቡዕ በጌታችን ላይ በተፈጸመው ምክር የሰይጣን ሴራ ፈርሷልና በጾመ አስቴር ምትክ ረቡዕን እንጾማለን፡፡

እንደዚሁም በብሉይ ኪዳን በጾመ ዮዲት ምክንያት ሆሎሆርኒስ ድል እንደ ተደረገበት ኹሉ፣ በሐዲስ ኪዳንም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነት ዲያብሎስ ድል ተደርጓልና በጾመ ዮዲት ምትክ ዓርብን እንጾማለን፡፡ የእነዚህ የሁለቱ ቀናት (የረቡዕና ዓርብ) ጾም ጾመ ድኅነት ይባላል፡፡

በአጠቃላይ ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት እንደ ጾመ ነነዌና ዐቢይ ጾም የበዓላትና የአጽዋማት ማውጫ ቀመርን ተከትለው የሚመጡ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል የሚመደቡ ጾሞች ናቸው፡፡ የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ (መፈጸሚያ) የቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በዓለ ዕረፍት (ሐምሌ ፭ ቀን) ሲኾን፣ ጾመ ድኅነት ግን ከበዓለ ኀምሳ በስተቀር ዓመቱን ሙሉ የሚጾም ጾም ነው፡፡

ዕለተ ረቡዕ የጌታ ሞት የተመከረበት፤ ዓርብም አምላካችን የተሰቀለበት ዕለት ነውና በመስቀሉ መሥዋዕትነት ያገኘውን ድኅነት ዘወትር ማሰብ ስለሚገባን ሁልጊዜ እንድንጾማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ሥርዓት ተሠርቶልናል፡፡ በዚህ ዓመት ጾመ ሐዋርያት ሰኔ ፲፫፤ ጾመ ድኅነት ደግሞ ሰኔ ፲፭ ቀን ይጀመራሉ፡፡

በመኾኑም የምንጠቀመው በራሳችን መልካም ተግባር፤ የምንወቀሰውም በራሳችን መጥፎ ድርጊት መኾኑን ተረድተን ይኼ የቄሶች፤ ይኼ የመነኰሳት ነው የሚል ሰበብ ሳንፈጥር ኹላችንም በአንድነት ብንጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘው ጸጋና ሀብት ይበዛልናልና ራሳችንን ለጾም እናዘጋጅ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የጰራቅሊጦስ መዝሙርና ምንባባት

ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዓለ ጰራቅሊጦስ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ሲኾን በዕለቱ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው የቅዱስ ያሬድ መዝሙርም ይትፌሣሕ የሚለው የትንሣኤ መዝሙር ነው፡፡ እንደ መዝሙሩ ኹሉ በጰራቅሊጦስ በዓል በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችም በትንሣኤ ዕለት የተነበቡት ምንባባት ናቸው፡፡

እነዚህም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ፣ በማረጉና መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት በመላኩ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ቈርሶ፣ ደሙን አፍስሶ የሰውን ልጅ ከዘለዓለም ሞት በማዳኑ የሰው ዘር ብቻ ሳይኾን የሰማይ መላእክት፣ የምድር ፍጥረታት ሳይቀሩ ሐሤት እንደሚያደርጉ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም በመንጻቷ የጌታችንን ትንሣኤ በደስታ እንደምታከብር ያስረዳሉ፡፡

በበዓለ ጰራቅሊጦስ ውስጥ ባሉት ሰንበታት (እሑዶች) የሚዘመሩ መዝሙራት ትንሣኤን፣ ዕርገትንና የመንፈስ ቅዱስን መውረድ የሚያስረዱ ሲኾኑ፣ ዓላማቸውም ከሙታን ተለይቶ ለተነሣው፣ አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ ባርነትና ከሲኦል ላወጣቸው ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ ነው፡፡

እንደ መዝሙሩ ኹሉ በጰራቅሊጦስ በዓል በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችም በትንሣኤ ዕለት የተነበቡ ምንባባት ሲኾኑ፣ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፤

ከጳውሎስ መልእክታት፡- ፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፥፳-፵፩፤

ከሌሎች መልእክታት፡- ፩ኛ ጴጥሮስ ፩፥፩-፲፫፤

የሐዋርያት ሥራ ፪፥፳፪-፴፯፤

ምስባክ፡- መዝሙር ፻፲፯፥፳፬፤

ወንጌል፡- ዮሐንስ ፳፥፩-፲፱፤

ቅዳሴ፡- ዲዮስቆሮስ፡፡