ደብረ ታቦርና ቡሄ

 ነሐሴ 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው። በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበረው ይህ በዓል መሠረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ደብረ ታቦር ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደ ፀሐይ የበራበት፣ ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት፣ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው።

ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር።

 

ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና፡ ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ማቴ. ፲፯፡፩-፭ በቤተ ክርስቲያን ደብረታቦር ከቤተክርስቲያን ውጭ አከባበሩ ቡሄ እየተባለ የሚከበረው በዓል በሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚዘለቅበት ወገግታ ፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ የሚሸጋገርበት ወቅት በመሆኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ በዚህ መሰረት የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየውም በዚህ በዓል አካባቢ ስለሆነ ይቺ ዕለት ‘ቡሄ’ የሚለውን ስያሜ አገኘ። ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብረሃን የታየበት ድምጸ መለኮት የተሰማበት ስለሆነ፤ ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓልም ይባላል፡፡

 

በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ። መነሻ የሆናቸው ትውፊት ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ እረኞችም ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል ፡፡ያንን ለማስታወስ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የሚከበረው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ የንጋት ወጋገን ሲፈናጠቅ ልጆች በከባድ ድምጽና በጅራፍ ጩኸት የሚታጀብ፣ በገደላገደል ስር እንዲያስተጋባ ተደርጎ ብዛት ባላቸው ህጻናት በከፍተኛ ድምጽ የሚዘመር ነው ቡሄ ። የጅራፉ ጩኸትም እግዚአብሔር አብ “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ሲል ሐዋርያት ራሳቸውን ስተው የወደቁበትን የመለኮት ድምፅ ለማስታወስ ነው፡፡

 

ደብረታቦር ወይም ቡሄ በአብነት ተማሪዎች “ስለ ደብረ ታቦር” እያሉ እህል፣ ፣ ጌሾ ለምነው ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምዕመናን በመጋበዝ በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡ ይህ ትውፊት መምህረ ሐዋርያት የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ይዞ ሄዶ የተገለጠ ምስጢር ስለሆነ ከመምህራቸው ጋር በመሆን በዓለ ደብረ ታቦርን /ቡሄን ያከብራሉ፡፡ ስሙን ይጠራሉ፡፡

የደብረ ታቦር ወይም የቡሄ ግጥሞች

ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና

ያዕቆብ ዮሃንስ ሆ! እንዲሁም ጴጥሮስ
አምላክን አዩት ሆ! ሙሴ ኤልያስ
አባቱም አለ ሆ! ልጄን ስሙት
ቃሌ ነውና ሆ! የወለለድኩት

ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና።
መጣና መጣና ደጅ ልንጥና

መጣና ባመቱ እንዴት ሰነበቱ፣
ክፈት በለዉ በሩን የጌታዪን
ክፈት በለዉ ተነሳ ያንን አንበሳ፣

የመሳሰሉት

 

awa mer 2006 1

በሐዋሳ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ ሰባኪያነ ወንጌል ተመረቁ

ነሐሴ 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

በዲ/ን ያለው ታምራት ከሐዋሳ ማእከል

awa mer 2006 1በማኅበረ ቅዳሳን ሐዋሳ ማዕከል በተለያዩ አምስት ቋንቋዎች የሚያስተምሩ 33  ሰባኪያነ ወንጌል በሐዋሳ ካህናት ማሠልጠኛ ለአንድ ወር በቀንና በማታ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን እና ሥልጠናዎችን ሲከታተሉ ቆይተው ብፁዕ አቡነ ገብርኤል  የሲዳማ፣ የጌዲኦ፣ የአማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት  ሐምሌ 27 ቀን 2006 ዓ.ም በሐዋሳ ደብረ ምጥማቅ  መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በድምቀት አስመረቀ፡፡

awa mer 2006 2ተመራቂ ሰልጣኞቹ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ባልተስፋፋባቸው የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከሲዳማ፣ ከጌዲኦ፣ ከአማሮና ከቡርጂ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ ሲሆን፤ በሲዳምኛ፤ በጌዲኦኛ፤በኩየርኛ፤በቡርጂኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በአንድ ወር ቆይታቸውም ከሚሰጣቸው መንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ በስብከት ዘዴ ላይ ያተኮረ የልምምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ለተመራቂዎቹ የምስክር ወረቀት፤ ለአገልግሎት የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ እና ማጣቀሻ መጸሕፍትን ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት “ከአማርኛ እና ግዕዝ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማስተማር ግዴታችን ነው፤ ሥልጠናውም ወደፊት ተጠናክሮ በመቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡

 

በዕለቱ ተመራቂ ሠልጣኞች በደብረ ምጥማቅ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ለተገኘኙ ምእመናን በቋንቋቸው በማስተማር ያገለገሉ ሲሆን፤ ምዕመናንም ይህን ላደረገ እግዚአብሔር በእልልታ እና በጭብጨባ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

የሐዋሳ ማእከል ሰብሳቢ ቀሲስ ደረጀ ሚደቅሶ በበኩላቸው ማኅበረ ቅዱሳን የሐዋሳ ማእከል በተከታታይ ለስድስት ዓመታት በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች ያሰለጠናቸው ሰባኪያነ ወንጌል ቁጥር 274 ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞችም ወደ መጡበት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ተመልሰው ምእመናን በሚገባቸው ቋንቋ እያስተማሩ በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፤ ወደ ሌላ እምነት የተቀየሩትንም አስተምረው ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸው እንዲመልሱ የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ከሀገረ ሰብከቱ ሊቀ ጳጳስ በተጨማሪ የሀገረ ሰብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የደብር አለቆች፣ ካህናትና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

adama 2006 1

የአዳማ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤትን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ነሐሴ 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

adama 2006 1በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ለሚያስገነባው የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የአጸደ ሕፃናትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳይ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የበላይ ሓላፊ ሐምሌ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኖሩ፡፡

adama 2006 2በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳይ መሪነት፤ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ የናዝሬት ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና አገልጋዮች፤ የማእከሉ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ምእመናን በተገኙበት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ ብፁዕነታቸው የመሠረት ድንጋይ ባኖሩበት ወቅት በሰጡት ቃለ ምእዳን “ከሁሉም ነገር በፊት የሰው ሀብት ዕውቀት ነው፡፡ ዕውቀት ደግሞ የማይሠረቅ ሀብት በመሆኑ የማይሠረቀውን፤ የማይዘረፈውን ሀብተ እግዚአብሔርን መያዝ መልካም ነው፤ የመሠረት ድንጋይ የምናኖረውም ድንቁርናን ለማጥፋት ነው” ብለዋል፡፡

ማኅበሩ የሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራትና ለቤተ ክርስቲያን እያበረከተ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው “ሁላችንም የምንሠራው የቤተ ክርስቲያናችንን ሥራ በመሆኑ፤ መሠረቱም፤ ጣሪያውም አንድ ነው፡፡ የማኅበሩ አባላት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንደምትወዱ፤ እንደምታከብሩም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታውቃለች፤ ሁላችንም እንመሠክራለን፡፡ ትውልድን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ ተገቢ በመሆኑ ከጎናችሁ ነን፤ በርቱ” በማለት የትምህርት ቤቱ ሕንፃ ግንባታ በፍጥነት ተጀምሮ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተመኝተዋል፡፡

adama 2006 3ቀሲስ እሸቱ ታደሰ የማኅበሩን መልእክት ሲያስተላልፉ “ማኅበረ ቅዱሳን የተማረ ትውልድን ለመቅረጽ፤ ትምህርት ለማስፋፋት እንደ አንድ ዓላማ አድርጎ በመያዝ በየአኅጉረ ስብከቱ ዐሥር ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ቤተ ክርስቲያንን የሚያውቅና በዕውቀት የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት በመሥራት ላይ ነው፡፡ የአዳማ ማእከል ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ቤት ተከራይቶ የዐፀደ ሕፃናትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመክፈት አገልግሎት እየሠጠ ቢሆንም፤ የተማሪዎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ በመምጣቱ ሰፋ ያለ ቦታ ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን በማስፈቀድ በአንድ ሚሊዮን ብር ከአባላት በማሰባሰብ በአዳማ ከተማ መሬት በመግዛት በዛሬው እለት በብፁዕነታቸው የመሠረት ድንጋይ ለማኖር በቅተናል” ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ሕፃናትን በቃለ እግዚአብሔር ኮትኩቶ ማሣደግን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ እንደነበር የገለጹት ቀሲስ እሸቱ ከብፁዕነታቸው ኅልፈት በኋላም በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሣይ ቀጣይነት ኖሮት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት፤ እንዲሁም በሀገረ ስብከታቸው የሚያከናውኗቸው የትምህርትና የልማት ሥራዎች ለሁሉም አርአያ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

የአዳማ አቡነ ጎርጎርዮስ የአጸደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2004 ዓ.ም. ቤት ተከራይቶ 32 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረ ሲሆን፤ የማእከሉ አባላት የቤት ኪራይ በመክፈል፤ የጽዳት ሥራውን በማሰራት፤ እንዲሁም ጊዜያቸውን መሥዋዕት በማድረግ በነጻ ያስተምሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው እንደሆነ አባላቱ ይገልጻሉ፡፡

በ2300 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው ባለ4 ፎቅ የተማሪዎች መማሪያ ሕንፃ 12 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅም ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

የጎንደር መካነ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን

 ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

ክፍል ሦስት

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤ እንቅስቃሴ

በጎንደር በአራት ቦታዎች ላይ የትርጓሜ መጻሕፍት ጉባኤ ቤቶች ይገኛሉ፤ ትምህርትም በተጠናከረ ሁኔታ ይሰጥባቸዋል፡፡ ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆኑት የመምህር ኤስድሮስ ወንበር በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ታጥፏል፡፡ ይህንን ገጽታ ለመቀየርና የመምህር ኤስድሮስን ወንበር ወደነበረበት ለመመለስ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ጉባኤ ቤቶቹን ዳግም ወደነበሩበት ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ለፍጻሜ ሳይበቃ ወደ ደቡብ ጎንደር ተቀይረው ሄዱ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ተግባራዊ ባይሆንም በቅርቡ አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስተዳደሩና ሰበካ ጉባኤው ይገልጻሉ፡፡ ወደፊት ሊሰሩ ከታቀዱ ሥራዎች መካከል አንዱ የጉባኤ ቤቱን ጥንት ወደነበረበት መመለስ ይገኝበታል፡፡

ከታቀዱት የልማትና የአገልግሎት ሥራዎች መካከል ቅድሚያ የሚያደርጉት ቤተ ክርስቲያኗ ሙሉ አገልግሎት መስጠት የምትችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት በመሆኑ፤ ካህናቱ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ በትምህርት ብቃታቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሠራ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ብቃት ያላቸው መምህራንን በማዘጋጀት፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል ጋር በመተባበር በወንጌል ትምህርት በቂ ልምድ እንዲኖራቸው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

“በልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጥላ ዘቅዝቆ መለመን አይቻልም፡፡ ምእመናን ሳይሳቀቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው በነፃነት ጸሎት አድርሰው፤ ቡራኬ ተቀብለው እንዲሄዱ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረናል ለማለት እንችላለን፡፡ ምእመናንን በልመና ማሳቀቅ አይገባም፤ አስበውና ደስ ብሏቸው ነው መሥጠት የሚኖርባቸው” በማለት የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑ ይገልጻሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ አገልገሎት አይቋረጥም፤ ሊቃውንቱም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቀው ያገለግላሉ፡፡ ለአብነት ተማሪዎች ቤት ተሰጥቷቸው፤ የመብራትና ውኃ ተከፍሎላቸው በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በእንተ ስማ ለማርያም በሚሰማሩበትም ወቅት ምእመናን ስለሚያውቋቸው ያላቸውን ሰጥተው ይሸኗቸዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኗ ጽ/ቤት በእያንዳንዱ አገልጋይ ካህን ስም ፋይል ከፍቶ የንስሐ ልጆቻቸውን ስም ዝርዝር እንዲያስመዘግቡ ተደርጓል፡፡ እያንዳንዳቸው የንስሐ ልጆቻቸውን በአግባቡ በመያዝና በመምከር፤ ቢያንስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ፤ በየቤታቸው እየተገኙ ጸሎት አድርስው፤ ጠበል ረጭተውና አስተምረው የመመለስ ግዴታ እንዳለባቸው በመረዳት ይህንኑ በተግባር ላይ እያዋሉት ይገኛሉ፡፡ አስተዳደሩም ይከታተላል፡፡ የንስሐ አባቶቻቸው የሚፈለግባቸውን ሓላፊነት ካልተወጡና የሥነ ምግባር ችግር እንዳለባቸው ካረጋገጡ ምእመናን ወደ ጽ/ቤት በመምጣት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ አስተዳደሩም ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ አንስቶ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡

ምእመናን ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግ ረገድ ለካህናት ብቻ የተተወ ባለመሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር መምህራንን በመመደብ፤ ትምህርተ ወንጌል የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት አንድ ክርስቲያን በክርስትና ሕይወት ውስጥ እስካለ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ምእመናን ሓላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ አሥራት በኩራት ከማውጣት አንስቶ ንስሐ በመግባት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመቀበል በሕይወታቸው ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ምእመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው በመጨመር እየፈሩ ነው፡፡

የልማት እቀዶች፡-

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በ400 ሺህ ብር የዳቦ መጋገሪያ ማሽን አስገብቷል፤ ሦስት ቋት ያለው ወፍጮና አንድ ማበጠሪያ በመትከል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ዙሪያ ሰፊ ቦታ ስላለ ባለ አራት ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ በመሥራትና በማከራየት ራሷን የምትችልበት ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኗን በአዲስ መልክ በጥሩ ዲዛይን ለማነጽ በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡ ለታቦቱ ማረፊያ የሚሆን ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ምእመናን ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል፡፡ የጎንደር መምህራን ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አዳራሽ ለመገንባት ለቤተ ክርስቲያኗ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ተፈቅዶላቸው ግንባታውን በማጠናቀቅ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

የጠበሉ ቦታን በማስተካከል ምእመናን ሳይቸገሩ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ በማመቻቸት የግንባታ ሥራው ይከናወናል፡፡

የልደታ ለማርያም የጥምቀተ ባሕር ቦታ ለሙስሊሞች ተሰጥቶ ስለነበር ከፍተኛ ችግር ተከስቶ ቆይቷል፡፡ በተለይም በ2001 ዓ.ም. የተፈጠሩት ግጭቶች አስቸጋሪ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የችግሩ አሳሳቢነት ቀጥሎም ጥምቀተ ባሕሩ ከሙስሊሞች ተወስዶ ለአንድ ጀርመናዊ ባለ ሀብት ተሰጠ፡፡ ነገር ግን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና በከተማው ወጣቶችና ምእመናን ብርቱ ጥረት ሳይሳከላቸው ቀርቷል፡፡

ቦታው የቤተ ክርስቲያን ሃብት በመሆኑ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ በማመን ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ለአማራ ክልላዊ መንግሥት ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ጎንደር ከተማ አስተዳደር አስተላልፎት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

ቦታው 46 ሺህ ካሬ ሜትር የሚገመት ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው ይህን ሥፍራ ለጥምቀተ ባሕርና ለልማት ለማዋል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በቦታውም የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ቤት፤ ሁለገብ ሕንፃ፤ የአረንጓዴ መናፈሻ፤ የኪነ ጥበብ ማእከል፤ መዋኛ ገንዳ፤ ሁለገብ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎችንም ያቀፈ እንዲሆን ተደርጎ ዲዛይኑን በማዘጋጀት ለከተማ አስተዳደሩ ገብቷል፡፡ የሚመለከተው አካል ያጸድቀዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡  

መራሕያን ምድብ ተውላጠ ስሞች /Pronoun/

 ሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ደሴ ቀለብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ መምህር

መራሕያን ማለት “መሪዎች” ማለት ሲሆን በግእዝ ቋንቋ አስር /10/ የሚሆኑ ተውላጠ ስሞች /መራሕያን/ አሉ፡፡ እነርሱም፡-

  1. አነ …………………..እኔ

  2. አንተ…………………. አንተ

  3. አንቲ ………………… አንቺ

  4. ውእቱ ………………. እርሱ

  5. ይእቲ ……………….  እርሷ

  6. ንሕነ ………………… እኛ

  7. አንትሙ………………. እናንተ /ለቅርብ ወንዶች/

  8. አንትን ………………. እናንተ /ለቅርብ ሴቶች/

  9. ወእቶሙ ……………… እነዚያ /ለወንዶች/

  10. ውእቶን …………….. እነዚያ /ለሴቶች/

መራሕያን በዐረፍተ ነገር

ቀደሰ (ቀዳማይ አንቀጽ Past tense) = አመሰገነ

 

  1. አነ ቀደስኩ                     6. ንሕነ ቀደስነ

  2. አንተ ቀደስከ                    7. አንትሙ ቀደስክሙ

  3. አንቲ ቀደስኪ                    8. አንትን ቀደስክን

  4. ውእቱ ቀደሰ                     9. ወእቶሙ ቀደሱ

  5. ይእቲ ቀደሰት                   10. ወእቶን ቀደሳ

የግሱ የመጨረሻ ፊደል “ከ” ከሆነ ያንኑ መለየት አለብን፡፡ ምሳሌ ሰበከ ብሎ አነ ሰበኩ (“ኩ” ይጠብቃል) ይላል እንጂ ሰበክኩ አይልም ስለዚህ ማጥበቅ አለብን ማለት ነው፡፡

1.1. ነባር አንቀጽ (Verb to be)

ውእቱ , ነው፣ ነበር፣ ነሽ፣ ነህ፣ ናችሁ

ይእቲ , ናት፣ ነበረች

ውእቶሙ (ሙንቱ) , ናቸው፣ ነበሩ (ለወንዶች)

ወእቶን (እማንቱ), ናቸው፣ ነበሩ (ለሴቶች )

ምሳሌ፡- አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ

        አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም

        አንተ ውእቱ ቤዛ ኩሉ ዓለም

       ማርያም ይእቲ መሠረተ ሕይወት

       ጳውሎስ ወጴጥሮስ መምህራን ውእቶሙ

       ሰሎሜ ወኤልሳቤጥ ቅዱሳት ውእቶን

1.2. ሥርዓተ ዐረፍተ ነገር በምሳሌ

ሕዝቅኤል ነቢይ

  • ሕዝቅኤል ነቢይ ውእቱ

  • ነቢይ ውእቱ ሕዝቅኤል

  • አኮ /አይደለም/ ነቢይ ሕዝቅኤል

“ውእቱ” ለሚለው አዎን አለው “አኮ” ነው፡፡

የሚከተሉት ከመራሕያን ከግሶች ጋር አዛምድ/አስተፃምር/

 

  1. አንትን                         ሀ ነበርኩ
  2. ውእቱ                         ለ በላዕነ
  3. አነ                             ሐ ሖርኪ
  4. ውእቶን                       መ ጸለዩ
  5. ይእቲ                          ሠ ቀተልክን

ረ መጽአት

ሰ ኖምክሙ

ሸ ሖራ

ቀ በልዐ 

ወልጥ ኀበ ልሳነ አምሃራ (ወደ አማርኛ መልስ)

  1. ንሕነ ሖርነ ኀበ አክሱም ወላስታ

  2. አንቲ ውእቱ እመ ብርሃን

  3. ማርያም ወለደት ወልደ ዘበኩራ

  4. አንተ ወአነ ሰማእነ ቃለ እግዚአብሔር

  5. እለ መኑ /አነማን/ ውእቶሙ ዘሖሩ ኀበ ገዳመ ሲና

ወደ ግእዝ መልስ /ወልጥ ኀበ ልሳነ ግእዝ/

  1. ወደ ጸሎት ቤት ሄድን

  2. እኔ ነኝ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሄድኩ፡፡ (ዘ=የ)

  3. እነርሱ በኅብረት ተቀመጠ (ኅቡረ = በኅብረት)

  4. ቶማስ እና ጴጥሮስ መምህራን ናቸው፡፡

  5. ማርያም ድንግል የአሮን በትር (በትር = ብትር) ናት፡፡

  6. አንተ የክርስቶስ ወንጌል ሰበክህ፡፡

  7. አንተ ሰባኪ አይደለህም፡፡

አስተካክለህ ጻፍ (ጹሑፍ በሥርዓተ ሰዋሰው)

ምሳሌ /ሐዘነ/ ማርያም አመ ተሰቅለ ክርስቶስ/ ኀዘነት ማርያም /አመተሰቅለ ክርስቶስ/

  1. /ኖመ/ አንተ ላዕለ አራት /አልጋ/

  2. /ሖረ/ አንትን ኀበ ደብረ ጽጌ

  3. /ቆመ/ ማርያ ወማርያም ቅድመ ቤተ መቅደስ

  4. /ኀደረ/ ፍሬ ጽድቅ ውስተ ቤተ አርድእት /ተማሪዎች/

  5. /አርመመ/ ሚካኤል አመ ተሰቅለ አምላክ

  6. /ተፈሥሑ/ ጻድቃን በእግዚአብሔር

 

 

abnet 2006 2

ለአብነት ተማሪዎች የአልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ድጋፍ በመደረግ ላይ ነው

 ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

  • በ150 አብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ ለ10 ሺህ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች ለማዳረስ ሥርጭቱ ይቀጥላል፡፡

  • “ያለኝ አንድ የተቀደደ ሱሪና አንድ ሸሚዝ ብቻ ነበር ፤ ቅያሪ ስለሌለኝ በመጨነቅ ላይ ሳለሁ በመድረሳችሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ከአብነት ተማሪዎች አንዱ::

abnet 2006 2
በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት “ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል ከምእመናን አልባሳትና ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በየአኅጉረ ስብከቱ ለሚገኙ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች የአልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

“ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ከሐምሌ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሔድ ላይ ባለው የሥርጭት መርሐ ግብር የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ውስጥ በሚገኙ አገልጋዮችና በየማእከላቱ ተወካዮች አማካይነት በየአኅጉረ ስብከቱ በመንቀሳቀስ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

abnet 2006 1በዚህም መሠረት በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት /ለሐይቅ እስጠፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ አንድነት ገዳም፤ ለቦሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ፤ ለከሚሴ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት/፤ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት /ለመርሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ለራማ ደብረ ሲና ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም/፤ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት /ለደብረ ብርሃን ሥላሴ፤ ለአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፤ ለአበራ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ለመንበረ መንግስት መድኃኔዓለም፤ ለግምጃ ቤት ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት/ ውስጥ ለሚገኙ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች የአልባሳትና የሳሙና ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

በደቡብ ጎንደር /ለመንበረ ልዑል አስቻ ቅዱስ ሚካኤል፤ ለጽርሐ አርያም ዙር አባ አቡነ አረጋዊ ገዳም፤ ለቅድስት ቤተልሔም፤ ለደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም፤ ለእስቴ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ፤ መሸለሚያ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፤ አባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል፤ ለማቢ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፤ ለቆማ ፋሲለደስ፤ ለእስቴ ቅዱስ ሚካኤል ወቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት/፤ በምዕራብ ጎጃም /ለናዳ ቅድስት ማርያም ገዳም፤ ለብጡላ ኢየሱስ፤ ለቆጋ ቅዱስ ጊዮርጊስ/፤ እንዲሁ ተመሳሳይ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን፤ በአራቱ ጉባኤያትና በማስመስከሪያ ትምህርት ቤቶች ከአልባሳትና ከሳሙና በተጨማሪ የጫማ፤ የክብሪት፤ የውኃ አጋርና ልብስ መስፊያ ክሮች አሠራጭቷል፡፡

የአብነት ትምህርት ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን የአልባሳት እጥረት ለመቅረፍ ከምእመናን አልባሳትን “ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል በማሰባበስብ እየተሠራጨ በሚገኝበት ወቅት ከየማእከላቱ በተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የአብነት ተማሪዎች እንዴት የአካባቢና የግል ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ትምህርት እየተሰጣቸውም ይገኛል፡፡

በ150 አብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ 10 ሺህ ተማሪዎች የአልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለማሠራጨት ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፤ በዚህ ሥርጭት እስካሁን በ23 አድባራትና ገዳማት ውስጥ ለሚገኙ 4110 /አራት ሺህ አንድ መቶ አሥር/ በላይ ለሚሆኑ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች ለማዳረስ ተችሏል፡፡ ሥርጭቱ በየአኅጉረ ስብከቱ የሚገኙ አብነት ትምህርት ቤቶችን ያካተተ በመሆኑ እንቅስቃሴው ቀጥሏል፡፡

የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለአብነት ተማሪዎቹ አልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሲሰጥ ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት “ሥጦታው መልካም ነው፤ መሆንም የሚገባው ነው፡፡ ንቃትና ትጋት ከተማሪዎች የሚጠበቅ ሲሆን፤ ጤናቸው ተጠብቆ ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ ማስተማርም ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመርሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር የሆኑት መጋቤ ምሥጢር መምህር ፍሬ ስብሐት ምሥጋናው በበኩላቸው “በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ በሚወጡትና ወደ ከተማ ኮብልለው በሚቀሩት ተማሪዎች ባዝንም፤ አንድ ገበሬ አርሶ ፍሬውን ሲሰበስብ እንደሚደሰተው ሁሉ ተማሪዎቼ ለጥሩ ውጤት ሲበቁ ነፍሴ ይደሰታል፡፡ ያሳደገኝም፤ ያስተማረኝም ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ እንድማር፤ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ድጎማ እያደረገልኝ ለዚህ አብቅቶኛል፡፡ የተዘረጋው ወንበር በችግር ምክንያት እንዳይታጠፍ ማኅበሩ ለተማሪዎች ባደረገው ድጋፍ በጣም ተደስቻለሁ” ብለዋል፡፡

“መምህራኖቻችን በችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እኛም ተምረን የእነሱ እጣ እንዳይደርሰን እንሠጋለን፡፡ ችግሩን መቋቋም የተሳናቸው ወደ ከተማ እየኮበለሉ በጥበቃ ወይም በቀን ሠራተኛነት እየተቀጠሩ ነው፡፡ እኛ ግን የልብሳችንና የቀለባችን መሸፈን ተስኖናል፡፡ እኔን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፤ ያለኝ አንድ የተቀደደ ሱሪና አንድ ሸሚዝ ብቻ ነበር፤ ቅያሪ ስለሌለኝ በመጨነቅ ላይ ሳለሁ በመድረሳችሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ሲል በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በራማ ደብረ ሲና ኪዳነ ምሕረት abenet 2006 4አንድነት ገዳም ከሚገኙ የቅዳሴ ተማሪዎች አንዱ ይገልጻል፡፡

በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት የመጀመሪያው ዙር “ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በ2003 ዓ.ም. በማካሔድ ለበርካታ አብነት ትምህርት ተማሪዎች ማዳረስ መቻሉ ይታወሳል፡፡

ይህ መርሐ ግብር ወደፊትም እንደሚቀጥል ከዋና ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

meg 28 2006 01

ቅዱስ ፓትርያርኩ ጾመ ፍለሰታን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ

 ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዲ/ን ፍቃዱ ዓለሙ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ ከነሐሴ 1 እስከ 16 የሚጾመው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጾም ዘንድሮም የፊታችን ሐሙስ ይጀምራል፡፡

meg 28 2006 01 ይህን አስመልክቶ በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅትብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ “የቅድስት ድንግል ማርያምን በዓለ ትንሣኤ ምክንያት አድርገን የምንጾመው ይህ ጾም ለሀገራችን፤ ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ መዳንን፤ ምሕረትንና ይቅርታን ለማስገኘት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቅዱስነታቸው፣ በጾሙ ወቅት ሁሉም ክርስቲያን የተራቡትን በማጉረስ፣ የታረዙትን በማልበስና የተቸገሩትን በመርዳት ጾሙን ለመጾም ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊትና ጥንታዊት እንደመሆኗ መጠን ከጥንት ጀምሮ ይህንን ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም ጠብቃ እስካሁን አቆይታለች፤ ለወደፊትም እስከ ዕለተ ምጽአት በዚሁ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡ ጾመ ፍልሰታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን በአዋጅ ከሚጾሙ ሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆን ከሕጻናት ጀምሮ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን በፍጹም ትጋት የሚጾሙት የበረከት ጾም ነው፡፡