መራሕያን ምድብ ተውላጠ ስሞች /Pronoun/

 ሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ደሴ ቀለብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ መምህር

መራሕያን ማለት “መሪዎች” ማለት ሲሆን በግእዝ ቋንቋ አስር /10/ የሚሆኑ ተውላጠ ስሞች /መራሕያን/ አሉ፡፡ እነርሱም፡-

 1. አነ …………………..እኔ

 2. አንተ…………………. አንተ

 3. አንቲ ………………… አንቺ

 4. ውእቱ ………………. እርሱ

 5. ይእቲ ……………….  እርሷ

 6. ንሕነ ………………… እኛ

 7. አንትሙ………………. እናንተ /ለቅርብ ወንዶች/

 8. አንትን ………………. እናንተ /ለቅርብ ሴቶች/

 9. ወእቶሙ ……………… እነዚያ /ለወንዶች/

 10. ውእቶን …………….. እነዚያ /ለሴቶች/

መራሕያን በዐረፍተ ነገር

ቀደሰ (ቀዳማይ አንቀጽ Past tense) = አመሰገነ

 

 1. አነ ቀደስኩ                     6. ንሕነ ቀደስነ

 2. አንተ ቀደስከ                    7. አንትሙ ቀደስክሙ

 3. አንቲ ቀደስኪ                    8. አንትን ቀደስክን

 4. ውእቱ ቀደሰ                     9. ወእቶሙ ቀደሱ

 5. ይእቲ ቀደሰት                   10. ወእቶን ቀደሳ

የግሱ የመጨረሻ ፊደል “ከ” ከሆነ ያንኑ መለየት አለብን፡፡ ምሳሌ ሰበከ ብሎ አነ ሰበኩ (“ኩ” ይጠብቃል) ይላል እንጂ ሰበክኩ አይልም ስለዚህ ማጥበቅ አለብን ማለት ነው፡፡

1.1. ነባር አንቀጽ (Verb to be)

ውእቱ , ነው፣ ነበር፣ ነሽ፣ ነህ፣ ናችሁ

ይእቲ , ናት፣ ነበረች

ውእቶሙ (ሙንቱ) , ናቸው፣ ነበሩ (ለወንዶች)

ወእቶን (እማንቱ), ናቸው፣ ነበሩ (ለሴቶች )

ምሳሌ፡- አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ

        አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም

        አንተ ውእቱ ቤዛ ኩሉ ዓለም

       ማርያም ይእቲ መሠረተ ሕይወት

       ጳውሎስ ወጴጥሮስ መምህራን ውእቶሙ

       ሰሎሜ ወኤልሳቤጥ ቅዱሳት ውእቶን

1.2. ሥርዓተ ዐረፍተ ነገር በምሳሌ

ሕዝቅኤል ነቢይ

 • ሕዝቅኤል ነቢይ ውእቱ

 • ነቢይ ውእቱ ሕዝቅኤል

 • አኮ /አይደለም/ ነቢይ ሕዝቅኤል

“ውእቱ” ለሚለው አዎን አለው “አኮ” ነው፡፡

የሚከተሉት ከመራሕያን ከግሶች ጋር አዛምድ/አስተፃምር/

 

 1. አንትን                         ሀ ነበርኩ
 2. ውእቱ                         ለ በላዕነ
 3. አነ                             ሐ ሖርኪ
 4. ውእቶን                       መ ጸለዩ
 5. ይእቲ                          ሠ ቀተልክን

ረ መጽአት

ሰ ኖምክሙ

ሸ ሖራ

ቀ በልዐ 

ወልጥ ኀበ ልሳነ አምሃራ (ወደ አማርኛ መልስ)

 1. ንሕነ ሖርነ ኀበ አክሱም ወላስታ

 2. አንቲ ውእቱ እመ ብርሃን

 3. ማርያም ወለደት ወልደ ዘበኩራ

 4. አንተ ወአነ ሰማእነ ቃለ እግዚአብሔር

 5. እለ መኑ /አነማን/ ውእቶሙ ዘሖሩ ኀበ ገዳመ ሲና

ወደ ግእዝ መልስ /ወልጥ ኀበ ልሳነ ግእዝ/

 1. ወደ ጸሎት ቤት ሄድን

 2. እኔ ነኝ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሄድኩ፡፡ (ዘ=የ)

 3. እነርሱ በኅብረት ተቀመጠ (ኅቡረ = በኅብረት)

 4. ቶማስ እና ጴጥሮስ መምህራን ናቸው፡፡

 5. ማርያም ድንግል የአሮን በትር (በትር = ብትር) ናት፡፡

 6. አንተ የክርስቶስ ወንጌል ሰበክህ፡፡

 7. አንተ ሰባኪ አይደለህም፡፡

አስተካክለህ ጻፍ (ጹሑፍ በሥርዓተ ሰዋሰው)

ምሳሌ /ሐዘነ/ ማርያም አመ ተሰቅለ ክርስቶስ/ ኀዘነት ማርያም /አመተሰቅለ ክርስቶስ/

 1. /ኖመ/ አንተ ላዕለ አራት /አልጋ/

 2. /ሖረ/ አንትን ኀበ ደብረ ጽጌ

 3. /ቆመ/ ማርያ ወማርያም ቅድመ ቤተ መቅደስ

 4. /ኀደረ/ ፍሬ ጽድቅ ውስተ ቤተ አርድእት /ተማሪዎች/

 5. /አርመመ/ ሚካኤል አመ ተሰቅለ አምላክ

 6. /ተፈሥሑ/ ጻድቃን በእግዚአብሔር