ጥር 7/2004 ዓ.ም
{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}Temkete{/gallery}
መግቢያ
ይህ ጽሑፍ መጽሐፈ ምሥጢር ከሚባለው ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ድርሰት የተወሰደ ሲሆን አባ ጊዮርጊስ ጥምቀትን አስመልክቶ የሰጠውን ድንቅ የሆነ አስተምህሮ እናስተውልበታለን፡፡
“…እነሆ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስን “የክርስቶስ ሕይወት” በማለት ሰየመው መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ ሕይወት ከሆነ እንዴት አያየውም? ከማየት ዐሳብ ይቀድማልና ከውጫዊ እይታ የአእምሮ እይታ ይበልጣልና ዳግመኛ ቅዱስ ጳውሎስ የሰውን ዐሳብ ከራሱ ከሰውየው በቀር የሚያውቅ የለም፡፡ እኛ ግን የተሰወረውን ገልጦ ጥልቁን መርምሮ የሚያውቅ የእግዚአብሔር መንፈስ አለን” 1ቆሮ.2፥11 አለ፡፡ አንተ ግብዝ ሆይ አብን እንደሚያውቀው ዕወቅ /አስተውል/፡፡ በወንጌል እንደተነገረው ወልድ ብቻውን ምንም ምን ሊያደርግ አይችልም ከአብ ያየውን ይሠራል እንጂ፡፡ አብ የሚሠራውን ወልድም ይህንኑ እንደእሱ ይሠራል፣ አብ ልጁን ይወዳልን የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፡፡ ከዚህም የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል፣ እናንተም ታውቁና ታደንቁ ዘንድ ስለ መንፈስ ቅድስም አስቀድመን ነገርናችሁ፡፡ በደለኞች ሆይ ከዛሬ ጀምሮ “ወልድ ከአብ ያንሳል አያህለውም” አትበሉ፡፡ “መንፈስ ቅዱስም ከወልድ ያንሳል አያህለውም ” አትበሉ፡፡
እኛ ግን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ባሕርይ፤ አንድ መንግሥት አንድ መገለጥ አንድ አኗኗር አንድ ሥልጣን አንድ አመለካከት አንድ መለኮት አንድ ዐሳብ አንድ ፈቃድና ሥርዐት አላቸው እንላለን፡፡ ፈቃዳቸው አንድ ነው ዐሳባቸው አንድ ነው፣ ሥርዐታቸውና ሕጋቸው አንድ ነው፣ ኀይላቸው አንድ ነው፣ እንደ አሕዛብ ልማድ ሦስት አማልክት አይባሉም፡፡ በሦስት አካል አንድ አምላክ ይባላሉ እንጂ፡፡ አንዱ አንዱን አይከተለውም ሁለተኛውም ሦስተኛውን አይከተለውም ከያዕቆብ አስቀድሞ ይስሐቅ ከይስሐቅ አስቀድሞ አብርሃም እንደነበረ ሁሉ ከአንዱ በፊት አንዱ አልነበረም፡፡
የአብ አኗኗር ከወልድ በፊት አልነበረም የመባርቅት ብልጭታ መታየት ታህል የዐይን ሽፋን እንቅስቃሴን የምታህል አይቀድመውም፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ታመናለች እንዲህም ታሳምናለች፡፡
እናታችንም ቤተ ክርስቲያን በረድኤተ እግዚአብሔር ጥላ ሥር ጸንታ ትኖራለች፡፡ አቤቱ በረድኤት ጥላ ሥር ጸንቶ የሚኖር ማን ነው? መቅደስህም በተሠራበት ቦታ አድሮ የሚኖር ማነው? ተብሎ እንደተጻፈ በሙሽራዋ ክርስቶስ ደስ እያላት የወልድን ኀይል አምና በምእመናን ፀንታ ትኖራለች፡፡ ቀኝ ክንዱ ታቅፈዋለች ግራ ክንዱም ከራሴ በታች ናት ተብሎ እንደተጻፈ በመንፈስ ቅዱስ ብርሃንነት ወደ ገነት ዓፀዶች ትመራለች፡፡ መንፈሰ ረድኤትህ መርቶ ወደ ምድረ ጽድቅ ያድርሰኝ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ /መዝ.14፥1/
ከዚህም በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅን ስትፈልግ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ትመለሳለች፤ በዮርዳኖስ ወንዝ ለልጁ በመሰከረ በእግዚአብሔር አብ ስም አንድ ጊዜ ትጠመቅ ዘንድ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ትወርዳለች፡፡ ዳግመኛም በዘካርያስ ልጅ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀ በእግዚአብሔር ወልድ ስም ትጠመቅ ዘንድ ሁለተኛ ትወርዳለች፡፡ ዳግመኛም በዘካርያስ ልጅ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀ በእግዚአብሔር ወልድ ስም ትጠመቅ ዘንድ ሁለተኛ ትወርዳለች የርግብ መልክ ባለው አካል አምሳል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በተቀመጠ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስም ሦስተኛ ትጠመቃለች፡፡
ከዚህም በኋላ ከዮርዳኖስ ወንዝ ወጥታ አመተ ክርስቶስ ትባል ዘንድ ቅብዓ ሜሮንን ተቀብታ ማዕተበ ክርስትናን ገንዘብ ታደርጋለች፡፡ ቅብዓ ሜሮን የሃይማኖት ኀይል ነውና ሐዋርያት በዲዲስቅልያ መጽሐፋቸው እንደገለጹት በጥምቀት የተወለደ ሰው አምላክ ከድንግል የተወለደውን ልደት ይመስላል፤ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም እንደተወለደ ከርሷም ከተወለደ በኋላ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ተገኘ፡፡
በጥምቀት የተወለደ ሰውም እንደዚሁ ነው ከውኃውም ከወጣ በኋላ ወደ ጥምቀተ ባሕር የገባበትና የወጣበት ምልክቱ አይገኝም፤ መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው ተብሎ በመዝሙረ ዳዊት እንደተነገረ ዱካህም ከጥልቅ ውኃ ውስጥ ነው ፍለጋህም አይታወቅም፡፡
ወደ እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አርእስተ ነገር እንመለስ፡፡ ከዚህም በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰላም የተሰበከላችሁን የወንጌል ኀይል ተጫምታችሁ ያለውን ቃል ሰምታ የወንጌልን ቃል ጫማ በመጫማት አካሔዷን አሳምራ ወደ እግዚአብሔር ቤት ትገባለች ኤፌ.6፥15 በራሷም ላይ የዕንቊን ዘውድ ትቀዳጃለች ይኸውም የሃይማኖት አክሊል ነው ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በራሳችሁ ላይ የሚያድነውን የራኀስ ቊር ድፉ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ በእጃችሁ ያዙ ይሄውም የእግዚአብሔር ቃል ነው ብሎ እንደተናገረ፡፡ ኤፌ.6፥17 በጣቶቿ ላይም የክብር ቀለበትን ታደርጋለች ይሔውም የድኅነት ምልክት የሆነ የክብር ማዕተብ ነው፡፡
ከዚህም በኋላ አብርሃም ወዳለባት ይስሐቅም በበግ መሥዋዕትነት ወደ ዳነባት ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ የእግዚአብሔር መላእክትም ሲወጡባትና ሲወርዱባት ያዕቆብ ባያት የወርቅ መሰላል ወደ ሙሸራው አዳራሽ ትገባለች፤ በእስራኤል ልጆች በደል ምክንያት ምስክር የሚሆኑ ሕግና ትእዛዝ የተጻፈባት ሙሴ የተሸከማት ጽላት ናት መልከጼዴቅም የቤተ ክርስቲያንን ምሥጢረ ቊርባን ሥርዐት የሚገልጽ የኅብስትና የወይን ግብር ያቀረበባት ናት ዘፍ.14፥18
ዳዊትም አቤቱ አንተ ታቦትህን ይዘህ ወደምታርፍባት ቦታ ተነሥ፡፡ እያለ የእግዚአብሔር ሕግ በተጻፈባት ታቦት ተነሥ፤ እያለ የእግዚአብሔር ሕግ በተጻፈባት ታቦት ፊት ምስጋና ያቀረበባት ናት አሳፍ የተቀኘላት፣ የቆሬ ልጆችም በምስጋና መሰንቆዎች የሚዘመሩላት የቆሬ ልጆችም በምስጋና መሰንቆዎች የሚዘምሩላት ናት፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ዐለቱን ሰንጥቆ የደብተራ ኦሪቱን ንዋየ ቅድሳት ያስቀመጠባት፣ የተሠነጠቀችውን ዐለት መልሶ እንደነበረችው ያደረጋት፣ እንደ ብረት መዝጊያም የሆነችለት፣ ቁልፎቿንም ለፀሐይ አደራ የሰጠባት ናት፡፡ መዝ.131፥8፣ ተረፈ ኤር.83፥18
ኤልያስ መልአኩ ያቀረበለትን የተዘጋጀ ኅብስት የበላባት፣ በተመገበው ምግብ ኀይልም ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት የተጓዘባት ናት፡፡ ዕዝራ ሱቱኤል መጻሕፍተ ብሉያትን የምታሳውቀውን ከመልአኩ ዑራኤል እጅ ተቀብሎ የምስጋና ጽዋን የጠጣባት፣ አእምሮውም በዕውቀት ተሞልቶ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ብሉያትን አፉ ከመናገር ሳያቋርጥ የቆየባት ናት፡፡ /1ነገ.19፥5-8 ዕ.ሱ.3 40/ ዘካርያስ ነጫጭና ጥርኝ ፈረሶችን ያየባት ናት፡፡ ዘካ.1፥8
ዳንኤልም የእሳት ሠረገላን ያየባት ናት፤ ዘመናት የማይወስኑት አምላክ ከሰው ልጅ ጋር ከበላያቸው ላይ የተቀመጠባቸውን ዙፋኖች ዳንኤል ያየባት ናት፤ ዕንባቆም በሁለቱ እንስሳት መካከል እግዚአብሔርን ያየባት ነቢያትም ሁሉ ደስ የሚያሰኝ ድምጽ የትንቢት ምስጋናን የሚያሰሙባት ናት፡፡ የገሊላ ሕፃናትም ኅሊናን የሚመስጥ፣ ልቡናን የሚማርክ፣ አጥንትን የሚያለመልመውን ማኅሌታዊ ምስጋናን የሚያመሰግኑባት ናት፡፡ ዳን.7፥9፣ ዕን.3፥2
ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፍ የተቀበለባት፤ ጳውሎስም የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ይሆን ዘንድ የተጠራባት፤ ዮሐንስም እንደነጋሪት ድምጽ እያሰማ ምሥጢረ መለኮትን የሰበከላት፤ ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን በአምሳለ እሳት የተቀበሉባት ናት፡፡ የእግዚአብሔርን መሥዋዕት የሚያቀርቡበትን መንበረ ታቦት ለመጐብኘት ማኅበረ መላእክት የሚፈሯት ማኅበረ ሰማዕታትም የመከራቸውን ዋጋ ተቀብለው የክብር አክሊልን የሚቀዳጁባት ናት፡፡
ከዚህም በኋላ በሙሽራይቱ መጋረጃ ውስጥ ለምእመናን ምሳ ይሆን ዘንድ ሙሽራው ይሠዋባታል፤ መሥዋዕቱንም ከማየቷ የተነሣ ጉልበቶቿ ይብረከረካሉ፤ በደሙ ጽዋ ውስጥ ደሙ ሲንጠፈጠፍ ባየችም ጊዜ አንጀቷ ይላወሳል፤ ሥጋውን በፍርሃት፤ ትበላለች ደሙንም በመንቀጥቀጥ ትጠጣለች፤ ከዚህም በኋላ የሃይማኖት ነበልባል በልቡናዋ ውስጥ ይቀጣጠላል፤ ከሆዷም ውስጥ የፍቅር ሞገድ ይናወጣል፡፡
አሁንም በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ላይ የክህደትን ቃል የተናገረውን የአርጌንስን ነቀፋ እነሆ ፈጽመን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ ለሚገዛ ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና፣ የመንግሥትና የነገሥታት ጌታ ለሆነው ለወልድ ስግደት፣ ልቡና ያሰበውን ኩላሊት የመላለሰውን መርምሮ ለሚያውቅ ለመንፈስ ቅዱስ ጌትነት ይገባል እንላለን፡፡ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ልቡናው ስንኩል ዐሳቡ ብኩን የሆነ የአርጌንስ ነቀፋው ተፈጸመ የጽዮን ወገን የምሆን የቄስ ልጅ የምሆን እኔ ጊዮርጊስ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ መለኮት የአንዱ ከአንዱ በለጠ እንዳይባል ለሥላሴ አንድነት ሦስትነት ሃይማኖት ቀንቼ እየደረስኩ በቃሌ አጻፍኳት በባሕርና በየብስ በበረሃና በደሴት ለእርሱ ክብር ምስጋና የሚገባው ነው ሥጋዊ ደማዊ የሆነ ፍጥረት ለእርሱ ሊሰገድለት ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡