ዓለም አቀፍ ሙቀትን በመከላከል ረገድ የገዳማትና አድባራት ብዝኀ ሕይወት እንክብካቤ ይሻል
የካቲት 22/2004 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት መጨመርን ለመቀነስ ያሏት ብዝኀ ሕይወት አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ መሆኑን በማኅበረ ቅዱሳን ሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል ሓላፊ ዶ/ር ሳሙኤል ኀይለ ማርያም አስታወቁ፡፡
ሓላፊው እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን በእቅድ ሊሠራቸው ካቀዳቸው መካከል የብዝኀ ሕይወት ጥበቃ በታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ገዳማትና አድባራት ያሏት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ለጥናት መመረጡ ለጥናቱ መከናወን አመቺነት ካለው የቦታ ቅርበትና ከገዳሙ የብዝኀ ሕይወት ይዘትና ጥራት አንጻር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በደብረ ሊባኖስ ገዳም በጀመረው በዚህ ጥናት ላይ የግብርና ባለሞያዎች፣ የግብርና ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች እና በካርበን ልቀት ዙሪያ ልምድና ምርምር ያደርጉ ባለሞያዎች ያሉት ቡድን አቋቁሟል፡፡ ቡድኑ ከገዳሙ አመራር አካላትና ከማኅበረ ቅዱሳን ፍቼ ማእከል ጋር በመሆን ጥናቱን እያከናወነ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ጠቅሰው በጥናቱ ውጤትም ላይ መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት በገዳሙ ላይ የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥናቱም የገዳሙን የብዝኀ ሕይወት ያለበትን ደረጃ እንዲሁም በብዝኀ ሕይወቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱትን ነገሮች መለየት፣ የዚህ ጥናት በመነሣት በቀጣይ መሠራት የሚገባቸውን ጉዳዮች ጭምር መሠረት ያደረገ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም የብዝኀ ሕይወት ጥናት ቡድን ፕሮጀክቱን ሲተገብር የገዳሙ የአካባቢ ልማት እቅድ የሚወጣለት ሲሆን በገዳሙ ያሉት ብዝኀ ሕይወት ያለባቸው ቦታዎች ተለይተው ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ይሆናል፡፡ የገዳሙም አኗኗር ብዝኀ ሕይወቱን ከመጠበቅ አንጻር መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለብዝኀ ሕይወት ጥበቃ ከመቼውም በላይ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሞያዎችና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በጥምረት ይሠራል ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸው ተፈጥሮአዊ ነገሮችን መንከባከብም ሆነ መጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታም መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የብዝኀ ሕይወት ጥናት በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ ሲሆን በዓለማችን በየጊዜው በሚፈጠረው የሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት ዓለማችንን አስጊ ደረጃ እያደረሳት ይገኛል፡፡






ብፁዕ አቡነ አብሳዲ በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ቅዳሜ የካቲት 10/2004 ዓ.ም. ለእሑድ አጥቢያ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ብፁዕነታቸው በትግራይ ክፍለ ሀገር ሽሬ በ1912 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በ1926 ዓ.ም ከሽሬ ወደ ኤርትራ በመሔድና ደብረ ማርያም ገዳም በመግባት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመከታተል ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ፣ ቅስናን ደግሞ ከአቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡ በደብረ ማርያም ገዳም ውስጥ በቆዩባቸው ዐሥር ዓመታት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ዲያቆናትንና ካህናትን በማስተማር አፍርተዋል፡፡
ነገር ግን ብዙዎቻችን በጦም ራስን መግዛትን ከምንለማመድ ይልቅ ለሥጋ ምቾቶቻችን መትጋታችን የሚያስገርም ነው፡፡ እኛ ለራሳችን የተጠነቀቅን መስሎን ደስታን ይፈጥሩልናል የምንላቸውን ምግቦችንና መጠጦችን አብዝተን እንበላለን እንጠጣለን፡፡ … ነገር ግን መጨረሻችን ሕማምና ስቃይ ይሆንብናል፡፡ የሥጋን ምቾት የናቁና በጦም በጸሎት እንዲሁም በትኅርምት ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚመሩ ቅዱሳን ግን ሥጋና ነፍሳቸውን ሕያዋን አድርገው በመልካም ጤንነት ያኖሯቸዋል፡፡ በተድላና በምቾት ይኖር የነበረው ሰውነታችን በሞት ሲያንቀላፋ ከውስጡ ከሚወጣው ክፉ ጠረን የተነሣ ሽቶ በራሱ ላይ እናርከፈክፍበታለን፡፡ ነገር ግን የቅዱሳን ሰውነት በሕይወት ሳሉም ቢሆን በሞት ከሥጋቸው መልካም መዓዛ ይመነጫል፡፡ ይህ እጅግ ድንቅ የሆነ ነገር ነው ፡፡ እኛ ለሥጋችን ምቾት በመጠንቀቅ ራሳችንን ስናጠፋ እነርሱ ግን ሥጋቸውን ለነፍሳቸው በጦምና በጸሎት በማስገዛታቸው ሥጋቸውን ይቀድሷታል፡፡ የነፍሳቸውን በጎ መዓዛ በመጠበቃቸውም ሥጋቸው መልካም መዓዛን እንድታፈልቅ ሆነች፡፡