Archive for year: 2012
የትንሣኤ የቅዳሴ ምንባብ 2( 1ጴጥ.1፥1-13)
የትንሣኤ የቅዳሴ ምንባብ 1 (1ቆሮ. 15፥20-41)
የትንሣኤ የማሕሌት ምንባብ 3 (ሉቃ.24፥1-13)
ትንሣኤ /ለሕፃናት/
ሚያዝያ 6/2004 ዓ.ም.
የትንሣኤ የማሕሌት ምንባብ 2 (ማር.16፥1-ፍጻሜ )
በእሑድ ሰንበትም ማለዳ ተነሥቶ ሰባት አጋንንትን ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት አስቀድሞ ታያት፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡
የትንሣኤ የማሕሌት ምንባብ 1 (ማቴ.28፥1-ፍጻሜ )
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አረፉ
ሚያዝያ 04፣ 2004ዓ.ም
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ሚያዚያ 2/2004 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ከአባታቸው ከአቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፈለቀች የማታወርቅ በጥቅምት ወር 1924 ዓ.ም. በአንኮበር ከተማ ተወልደዋል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ አገር በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ በሥነ ስዕል በቅርፃ ቅርጽና በሥነ ሕንፃ ዲዛይን ተከታትለዋል፡፡
በነበራቸው የሥነ ስዕል ዝንባሌ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ሲሆን በወጣትነት ዘመናቸው በ1957 ዓ.ም. ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ጋር በኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እጅ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ አካዳሚዎች አባል ሲሆኑ በተሰማሩበት የሥነ ሥዕል ጥበብ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ታላላቅ ሰዎች የሚሰጠውን የዓለም ሎሬት የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ እስካሁን ድረስም ከዘጠና ሰባት በላይ የዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል፡፡
ጊዜ የማይሽራቸው ታላላቅ የሥዕል ሥራዎች ለዓለም ያበረከቱ ሲሆን በስዕሎቻቸውም ሥርዓተ አምልኮን፣ ማኅበራዊ አኗኗር የማኅበረሰቡን ደስታና ሃዘንና ጀግንነቱን ሥልጣኔውና ሀገር ወዳድነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡ በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና እምነት በመነጨ ለተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በስቱዲዮአቸውና በጸሎት ቤታቸው የሚገኙ መንፈሳዊ ስዕላትን አበርክተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከልም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ በግድግዳ ላይ የተሠሩ መንፈሳዊ ስዕላትን በቀለም ቅብ፣ በባለቀለም ጠጠሮች፣ በክርክም መስታወቶችና በሞዛይክ ከታወቁትና ስመ ጥር ከሆኑት ሰዓሊ ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ጋር ሠርተዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ውስጥም ስዕሎታቸው በክብር ተቀምጠውላቸው በጎብኚዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድም በስዕሎታቸውና በቅርፃቅርጾቻቸው አማካይነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን “ቪላ አልፋ” የተሰኘው ባለ 22 ክፍሎች መኖሪያ ቤታቸውና የግል ስቱዲዮአቸው ውስጥ ይህንኑ ለማንጸባረቅ ጥረት አድርገዋል፡፡
በቪላ አልፋ ስቱዲዮ ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅዱሳት ስዕላት፣ የተወለዱበት አንኮበር የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሚያስደንቁ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ እሴቶችን አካቶ የያዘ ነው፡፡
በንግግራቸው ስመ እግዚአብሔርን መጥራት የሚያዘወትሩት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በዋናው መግቢያ በራቸው ላይ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚል ጥቅስ በትልቁ ጽፈዋል፡፡ “እንደማንኛውም ዓይነት የጥበብ ሥራ በሠራሁ ጊዜ እኔ በጥበቤ ታላቅ ነኝ የሚል ትምክህት እንዳይቀርበኝ ዘወትር እንዳነበው ነው የጻፍሁት” በማለት ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን ለሚታተመው ሐመር መጽሔት ጋዜጠኞች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በዓለማችን ላይ ከሚገኙ ስመጥርና ታላላቅ ከተሰኙ 200 ሰዎች ጋር የሕይወት ታሪካቸውንና የኢትዮጵያ ባንዲራ በጨረቃ ላይ እንዲያርፍ የተደረገ ሲሆን በደረሰባቸው የጨጓራ አልሰር ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ማክሰኞ ምሽት ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸው ሚያዚያ 6/2004 ዓ.ም. ቅዳሜ በቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡
ዝግጅት ክፍላችን ለመላው ቤተሰቦቻቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡
ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ሊቶስጥራ
{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}Sekelete2{/gallery}
ቅዳሴን በካሴት ማስቀደስ ይቻላል?
ሚያዚያ 3/2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
እድሜ ለቴክኖሎጂ ይድረስና ድካምን የሚቀንሱ በርካታ የሥልጣኔ ውጤቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መቅረጸ ድምጽ ሲሆን ያለፈን ለማስታወስ የለው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ መዝሙሮች ቅዳሴዎች፣ ትምህርቶች እና የአባቶች ምክር በካሴትና በሲዲ በምስልና በድምጽ እየተዘጋጁ የሚሰጡት አገልግሎት እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ከምትገለገልበት ሥርዐተ አምልኮ መካከል ቅዳሴ አንዱ ሲሆን በካሴት ተቀርጾ በገበያ ላይ ይሸጣል፡፡ እኔም ቅዳሴን በካሴት ከቤት ውስጥ ሆኖ ማስቀደስ ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚል ጥያቄ በውስጤ ይመላለሳል፡፡
እባካችሁ ቅዳሴን በካሴት በቤት ውስጥ ሆኖ ማስቀደስ ይቻል ወይም አይቻል እንደሆነ መልስ ስጡኝ?”
የተከበሩ ጠያቂያችን በቅድሚያ ስላቀረቡልን ጥያቄ ምስጋናችንን ስናቀርብ ከልብ ነው፡፡ ማንነትዎንና ያሉበትን ቦታ ስላልገለጡልን ለምንመልሰው መልስ አቅጣጫ ለመጠቆም አልረዳንም፡፡ ቢሆንም መሠረታዊ የሆነው ጥያቄዎ ስለተገለጠ አስቸጋሪ ነገር አይኖረውም፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆኑትን ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘን እና በማኅበረ ቅዱሳን የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል አርታኢ የሆኑትን መምህር ተስፋ ሚካኤል ታከለ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡን ጋብዘናቸዋል፡፡
ሊቀ ጠብብት ሐረገወይን “ቅዳሴን በካሴት በቤት ውስጥ ሆኖ ማስቀደስ ይገባል?” የሚለውን ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ይላሉ፡፡ “የቅዳሴ ዓላማው አንድ ነው፡፡ እሱም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ፈትቶ ለምእመናን ማቅረብ ሲሆን አባቶች እንደሚሉት ቅዳሴ የሕዝብ ነው፡፡ ሰዓታት የሚባለውን የቤተ ክርስቲያን ጸሎት ካህናት ሲያደርሱ ምእመናን ቢሳተፉበት በረከተ ሥጋና በረከተ ነፍስን ያገኙበታል፡፡ ማኅሌት ሲቆም ኪዳን ሲደርስ ምእመናን ቢገኙ በረከትን ያገኛሉ፡፡
ቅዳሴ ግን ለሕዝብ የሚፈጸም ሥርዐተ ጸሎት በመሆኑ ቀዳስያኑ እና ምእመናኑ ፊት ለፊት እየተያዩ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ደጅ ሲጠኑ ይታያሉ፡፡ ሥርዐተ ቅዳሴ ሲፈጸምም በካህናትና በምእመናን ተሳትፎ ይከናወናል፡፡ ቴክኖሎጂው በወለደልን ጥበብ ተጠቅሞ መዝሙርን ማዳመጥ ቅዳሴውን መስማት ይቻላል፡፡የተቀረጸውን መስማት ብቻ ሳይሆን ልንማርበትም እንችል ይሆናል፡፡ ከዚህ አልፎ የቤተ ክርስቲያኑን ጸሎተ ቅዳሴ በካሴት በተቀረጸ ድምጽ ማስቀደስ አይቻልም፡፡
በአሕዛብ አገር የሚኖሩ ሰዎች በአንድ የጸሎት ቤት ተሰብስበው ቅዳሴ በቴፕ ያስቀድሱ እንደነበረ ሰምቻለሁ እነዚህ ምእመናን ከቤታቸው ወጥተው መንገድ ሔደው ቆመው ቅዳሴውን በቴፕ እየሰሙ “እትው በሰላም” /በሰላም ወደቤታችሁ ግቡ/ ሲባሉ ይሰነባበታሉ፡፡ ይህ በጎ አሳባቸውን እግዚአብሔር ተመልክቶ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ ካህናቱም ቀድሰው እንዲያቆርቧቸው ረድቷቸዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን ካህናት ያቀርቡት የነበረው መሥዋዕተ ኦሪት ለሐዲስ ኪዳኑ (አማናዊው) መሥዋዕት ምሳሌ ሆኖ እንዳደረሳቸው ከችግር አንጻር ቅዳሴን ለማስቀደስ ካላቸው ልባዊ ፍላጎት ተነሣሥተው ያን ማድረጋቸው አያስወቅሳቸውም፡፡ ያም ሆኖ ግን በመኖሪያ ቤታቸው ሳይሆን ከቤታቸው ወጥተው መንገድ ተጉዘው የፈጸሙት ተጋድሎ የሚበረታታ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ዝም ብሎ ተኝቶ ቅዳሴን ሰምቶ አስቀድሻለሁ ማለት ድፍረት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቴክኖሎጂ ቅዳሴ የላትም ቅዳሴውም በምንም ዐይነት መንገድ በቴፕ ድምጽ አይተካም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ያልታነጸችበት ቦታ አለ ለማለት ትንሽ ያስቸግራል ስለዚህ ቅዳሴን ማስቀደስ የሚገባው በቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ ነው”
መምህር ተስፋም በማያያዝ ምክራቸውን እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡፡ “ሊቀ ጠበብት የሰጡት አባታዊ ትምህርት እንደተጠበቀ ነው፡፡ የተለየም ዐሳብ የለኝም ቅዳሴ የሚቀደሰው በተቀደሰ ቦታ ነው፡፡ ይህ ማለት ታቦት ባለበት፣ ካህናት በተገኙበት፣ ውግረተ እጣን በሚደርስበት፣ ቡራኬ በሚፈጸምበት ቅዱስ ቦታ ይከናወናል፡፡ በቅዳሴው ጊዜ እጣን አለ፤ ጧፍ ይበራል፤ መሥዋዕት ይሰዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ቅዳሴን ማስቀደስ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ይህ ካልሆነ ቅዳሴው ቅዳሴ አይሆንም እላለሁ፡፡”
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ እምነቷን ዶግማዋን እና ትውፊቷን ጠብቃ ጸሎተ ቅዳሴን ታከናውናለች፡፡ ጸሎተ ቅዳሴ ተግባራዊ የሆነ አምልኮ የምንፈጽምበት፣ መሠረታዊ እምነታችንን የምንገልጥበት ወደ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን /ምሥጢረ ቊርባን/ የምንደርስበት በምድር ያለ ሰማያዊ ሥርዐት ነው፡፡ በዕለተ ሰንበት በዐበይት በዓላት የሚቻለው አስቀድሶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላል፡፡ በንስሓ ራሱን ያላዘጋጀ ምእመን ደግሞ አስቀድሶ ጠበል ጠጥቶ መስቀል ተሳልሞ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡
ሥርዐተ ቅዳሴ በካህናት መሪነት በዲያቆናት አስተናባሪነት በምዕመናን ተሳትፎ በኅብረት የሚፈጸም ሥርዐት ነው፡፡ ሠራኢ ካህን ከመንበሩ በስተምዕራብ ቆሞ፣ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልስ ንፍቁ ካህን ከመንበሩ በስተደቡብ ፊቱን ወደ ሰሜን መልሶ፣ ሠራኢ ዲያቆኑ በስተምሥራቅ ፊቱን ወደ ምዕራብ፣ ንፍቁ ዲያቆን በሰሜን ፊቱን ወደ ደቡብ በመቆም መንበሩን ይከቡታል፡፡ አምስተኛው ልዑክም ከሠራኢው ካህን በስተግራ ቆሞ ለካህኑ መብራት ያበራለታል፡፡ መጽሐፉ በመንበር ላይ የሚቀመጥ ስለሆነ ሲገልጥ ጠሚችለው ንፍቁ ቄስ ወይም ሌላ ቄስ ብቻ ነው፡፡ ይህ መደበኛ አቋቋማቸው ሲሆን ሥርዐተ ቅዳሴው በሚከናወንበት ጊዜ ለቡራኬ ለጸሎተ እጣን ለስግደት ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፡፡
በቅኔ ማኅሌት በቅድስትና በመቅደስ ቆመው የሚያስቀድሱና የሚያገለግሉ የምእመናን ወገንና ካህናት አሉ፡፡ በቅኔ ማኅሌት በሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ያለ የአገልግሎት ክፍል ወንዶች ምእመናን ቆመው ያስቀድሱበታል፡፡ በቅድስት ምዕራባዊ ክፍል ቆሞሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ያስቀድሱበታል፡፡ በስተደቡብ በኩልም ደናግል መነኮሳይያት የካህናት የዲያቆናት ሚስቶችና የሚቆርቡ ምእመናን ቆመው ያስቀድሱበታል፡፡ በዚህ ክፍል ቆመው ያስቀደሱ ምእመናን ሥርዐተ ቁርባን ይፈጽሙበታል፡፡ ይህ የቤተ መቅደሱ አሠራር ቤተ ንጉሥ የሆነ እንዳልሆነ ነው፡፡ በመቅደሱ ክፍል ልኡካኑ የሚቀድሱበት ሥጋ ወደሙ የሚፈትቱበት ካህናት ብቻ የሚገቡበት ልዩ ቦታ ነው፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ከላይ ያስቀመጥናቸውና ያልገለጥናቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ይከናወኑበታል፡፡ ሥርዐተ ቅዳሴ ሲፈጸም ካህናትና ምእመናን የድርሻቸውን ቃለ እግዚአብሔር እየተቀባበሉ እየሰገዱ እየተባረኩ ሥርዐቱ ይከናወናል፡፡ ለዚህም ነው ሥርዐተ ቅዳሴ የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ የሚሰማ ክዋኔ አለው የምንለው፡፡ ቅዳሴን በካሴት መስማት /ማዳመጥ/ ይቻል ይሆናል እንጂ ቡራኬ የማስገኘት የምሥጢራት ተካፋይ የማድረግ እድል አያሰጥም፡፡ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም እንደታደዘዘው ካህኑ ቅዳሴን ከመጀመሩ በፊት ሊያስተውል ከሚገባው ጉዳዮች አንዲ ምዕመናን መሰባሰባቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ዐይኖች በቤተ መቅደስ ነው፡፡ ጆሮዎቹም ወደ ምእመናን ጸሎት ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ዐይኑንና ልቡን በመቅደሱ ሊያኖር ቃል ስለገባልን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ የምሥጢራቱም ተካፋይ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ “በጎ እንደሆነ አውቆ ለማይሠራው ለዚያ ሰው ኀጢአት ነው” ያዕ.4፥17 እንዳለው ሐዋርያው ማስቀደስ ንስሓ መግባት ሥጋ ወደሙ መቀበል መልካም ነገር ማድረግ በጎ እንደሆነ እያወቁ ያን አለመፈጸም ኀጢአት ነው፡፡ “በዚህ ሥፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፡፡ ጆሮቼም ያዳምጣሉ አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናል” 2ዜና.7፥15-17 ተብሎ እንደተጻፈ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደን የምንጸልየው ጸሎት የምንፈጽመው ሥርዐተ አምልኮ በረከት የሚያሰጥ እንደሆነ አምላካችን ነግሮናል፡፡ አበው ሐዋርያትም ጸሎትን በቤተ መቅደስ በመገኘት ያደርጉ ነበር፡፡ “ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ሐዋ.3፥6 ስለዚህ በአንድነት ለጸሎት በቤተ ክርስቲያን መሰብሰብ ሐዋርያት ትምህርት ነውና ልንፈጽመው ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር