ዲያቆን ታደሰ ወርቁ
እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡
1. ሁለቱ ሐዋርያት ሲጠሩ የነበሩበት ሕይወት
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው በቤተ ሳይዳ ሲወለድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በጠርሴስ ከተማ ተወለደ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ዓሣ ማሥገር ጀመረ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በ 15 ዓመት ዕድሜው በገማልያ ትምህርት ቤት በመግባት የአይሁድን ሕግና ሥርዓት ተምሯል፡፡ በ30 ዓመቱም የአይሁድ ሸንጎ አባል ሆኗል፡፡ /1ቆሮ.1.17፤ሐዋ.22.3/
ቅዱስ ጴጥሮስ ባለትዳር ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በድንግልና የኖረ አባት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ /ባለ ትዳር/ ሆኖ ይኖር እንደነበር በማቴዎስ ወንጌል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጴጥሮስን አማት ማዳኑ መጠቀሱ አመላካች ሲሆን ጳዉሎስ ድንግል ስለመሆኑ ደግሞ ራሱ ለቆሮንቶስ ምእመናን በጻፈው ላይ ያረጋገጠው ነው፡፡ /ማቴ.8.14-15፣ 1ቆሮ.7.8፣9.5/ ይህም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያገቡትንም ሆነ በድንግልና የሚኖሩትን ለአገልግሎት እንደሚቀበል አመላካች መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
2. የሁለቱ ሐዋርያት ተክለ ቁመና
ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቱ ሰፋ ያለ ሲሆን መካከለኛ ቁመት የነበረው፤ ራሰ በራ ሰው ነው፡፡ በማናቸውም ነገር ፈጣንና ቀልጣፋ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ ጭንቅላቱ ትልቅ ሲሆን ራሰ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ቅንድቦቹ ጠጉር የተጋጠሙ፤ ዓይኖቹ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ ዘወትር ብሩሃን ነበሩ፡፡ አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ናቸው፡፡ አንገቱ አጠር ያለ ሆኖ ትከሻው ክብና ጎባባ፤ ቁመቱም አጠር ያለ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ /ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ ገጽ. 65 እና 125/
3.የእግዚአብሔር ጥሪ እና የሁለቱ ሐዋርያት መልስ
እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ዘር በሙሉ ለቅድስና፣ ለምግባር፣ ለትሩፋትና ለሰማዕትነት በተለያዩ ዘመናት ጠርቷል፡፡ ጥሪውን አድምጠው የተጠሩበትን ዓላማ ተረድተው፤ እንደ እርሱ ፈቃድ የተጓዙ ጥቂቶች ናቸው፡፡ /ማቴ.22.14/ ከጥቂቶቹም መካከል ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለት የቤተክርስቲያን ፈርጥ የሆኑ ሐዋርያት ለአገልግሎት የተጠሩበት መንገድ ለየቅል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ልዩ ስሟ ጌንሴሬጥ በምትባል መንደር ዓሣ ያሠግሩ ነበር፡፡ በዚህን ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ፡፡» በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ከወንድሙ ጋር ጠራው፡፡ /ማቴ.4.18/ በዚህ ጥሪ መሠረትም መተዳደሪያው የነበረውን መረቡንና ታንኳውን እንዲሁም አባቱን ትቶ ጌታውን ተከተለ፡፡ ለሐዋርያነት አገልግሎት ሲታጭ ዕድሜው 55 ዓመት እንደነበርም ይነገራል፡፡ /ዜና ሐዋርያት ገጽ. 3-15/
ምንም እንኳን ቅዱስ ጳዉሎስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የተጠራበት የአገልግሎት ዓላማ አንድ ቢሆንም የተጠራበት መንገድ ከቅዱስ ጴጥሮስ በእጅጉ ይለያል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ጋር አልነበረም፤ ቀጥታ ከጌታም አልተማረም ነበር፡፡ በወቅቱ ግን በኢየሩሳሌም ስለነበረ የጌታን አገልግሎት ያውቅ ነበር፡፡ ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ በመሆኑ ክርስቲያኖችን በማናቸውም አጋጣሚ ይቃወም ነበር፡፡ በ32 ዓመት ዕድሜውም ከኢየሩሳሌም ሁለት መቶ ሃያ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የደማስቆ ከተማ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ሲሰማ፤ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የሚያስችለውን የፈቃድ ደብዳቤ ከባለሥልጣናቱ አገኘ፡፡
እርሱም ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ከተማ አመራ፡፡ በዚያም ከሰማይ ብርሃን ወረደ፡፡ የወረደውም የብርሃን ነጸብራቅ ቅዱስ ጳዉሎስን ከመሬት ላይ ጣለው፡፡ በብርሃኑ ውስጥም «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛልህ)» የሚለውን አምላካዊ ድምፅ አሰማው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስም «ጌታ ሆይ ማን ነህ)» ብሎ ጠየቀ፡፡ ለጠየቀውም ጥያቄ «አንተ የምታሳድድኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡» የሚል መልስ አገኘ፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም በወደቀበት ሆኖ እየተንቀጠቀጠ «ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ)» ሲል ከእርሱ የሚጠበቀውን ግዴታውን ጠየቀ፡፡ ጌታም ተነሥቶ ወደ ደማስቆ እንዲገባና ማድረግ የሚገባውን ወደሚነግረው ወደ ካህኑ ሐናንያ ላከው፡፡ /የሐዋ.9.1/
ቅዱስ ጳዉሎስም በዚህ መልኩ የእግዚአብሔርን የአገልግሎት ጥሪ ተቀብሎ በካህኑ ሐናንያ እጅ ተጠምቆ ወደ ሐዋርያነት ኅብረት ተቀላቀለ፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ቅዱስ ጴጥሮስ የቀደመ ግብሩን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ጌታን እንደተከተለ ሁሉ ቅዱስ ጳውሎስም የቀደመ የጥፋት ግብሩን በመተው የጌታ ተከታይ የሆኑትን ወንድሞቹን ሐዋርያትን ተቀላቀለ፡፡ እንደ እነርሱም ለጌታ ጥሪ ተገቢውን መልስ ሰጠ፡፡
ቅዱስ ጳወሎስ የተጠራው ሦስት ጊዜ ነው፡፡ የተጠራው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ የእርሱ ጥሪ በአብ ስም የተከናወነው በእናቱ ማኅፀን ነው፡፡ ይህንንም ራሱ ቅዱስ ጳዉሎስ ሲገልጽ «ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ፤ በጸጋውም የጠራኝ፤ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ በእኔ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤» በማለት ነው፡፡ በዚህም አብ እግዚአብሔር በሚለው አምላካዊ ስሙ እንዳጠራው በምስጢር እንረዳለን፡፡ /ገላ.1.15-16/ ሌላኛው ጥሪ ደግሞ በወልድ የተከናወነው ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለጽነው እግዚአብሔር ወልድ በደማስቆ ጎዳና ላይ «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ» ብሎ ከገሰጸው በኋላ ወደ ካህኑ ሐናንያ በላከው ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅትም ጌታ ቅዱስ ጳዉሎስን ለምን እንደመረጠው ለካህኑ ሐናንያም ሲያስረዳ «ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና፤» በማለት ነው፡፡ /የሐዋ.9.15/
ቅዱስ ጳዉሎስ ከአብና ከወልድ ባሻገር በመንፈስ ቅዱስም ለአገልግሎት የተመረጠ ነው፡፡ ይህም የሆነው መንፈስ ቅዱስ ለአባቶቻችን «በርናባስንና ሳዉልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ» /ሐዋ.13.21/ ባለበት ወቅት እና እንዲሁም «በዚያን ጊዜም ከጦሙ፤ ከጸለዩም፤ እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው፡፡ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሰሌውቅያ ወረዱ፤» በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት ነው፡፡ /የሐዋ.13.3-4/ በመሆኑም የቅዱስ ጳዉሎስ መጠራት ከጥሪነት ባሻገር ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነው፡፡ በእርሱ መመረጥ ውስጥ የቅድስት ሥላሴ ልዩ አንድነትና ሦስትነት ተገልጧል፤ /ተመስክሯል/፡፡
4. የአገልግሎት ምድባቸው
ግብረ ሐዋርያት የሚጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ ሥራ ሲሆን የምዕራፉም መጨረሻ የሚጠናቀቀው በቅዱስ ጳዉሎስ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁድን /የተገረዙትን/ በአባትነት እንዲጠብቅ ሲሾም በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ አሕዛብን /ያልተገረዙትን/ እንዲጠብቅና እንዲያስተምር ተሹሞ ነበር፡፡ ስለዚህም ነገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ «… ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ እዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንድሆን ለጴጥሮስ የሠራለት ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና፡፡» በማለት ነው የገለጸው፡፡/የሐዋ.2.7-9/
በዚሁ ምድባቸው መሠረት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም፣ በአንጾኪያ፣ በይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም በስደት ላሉ አይሁድ መንግሥተ እግዚአብሔርን ሲሰብክ ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በቆጵሮስ፣ በመቄዶንያ፣ በግሪክ፣ በተሰሎንቄ በፊልጵስዩስ፣ በቆሮንቶስ፣ በኤፌሶን፣ በሮምና በሌሎችም ቦታዎች ሰብኳል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ጳዉሎስ እነዚህን አካባቢዎችና በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩትን ሕዝብና አሕዛብ ተከፋፍለው ሲያስተምሩ የየራሳቸውን አካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታ ይጠቀሙም ነበር፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድ መምህር እንደመሆኑ መጠን በስብከቱና በጻፈው መልእክቱ አዘውትሮ ከብሉይ ኪዳንና ከመዝሙረ ዳዊት የተለያዩ ጥቅሶችን ይጠቀም ነበር፡፡ ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ሌላ ሰው ለመምረጥ በተገናኙ ወቅት ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ስለ እርሱ በመዝሙር መጽሐፍ «መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን፤ የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአል፡፡» በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተናገረውን ጠቅሶ ተናግሯል፡፡ /የሐዋ.1.20-22፣ መዝ.68.25፣ መዝ.108.8/
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ከወረደ በኋላ ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በምዕራፍ 2.2-32 ላይ የተናገረውን ጠቅሶ ጽፏል፡፡ ይኸውም «እግዚአብሔር ይላል- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሸማግሌዎቻችሁም ህልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡. .. » የሚለውን ነው፡፡ /የሐዋ.2.17-21/ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ ቅዱስ ጴጥሮስ ከመዝሙረ ዳዊት ጠቅሶ ተናግሯል፡፡ ይኸውም «ዳዊትም ስለ እርሱ /ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ/ እንዲህ አለ- እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና፡፡ ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሴት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ፡፡ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና፡፡» የሚለውን በመዝሙር 15.8 የሚገኘውን ሲሆን፤ ይኽም በጌታ መፈጸሙን ለማረጋገጥ የጠቀሰው ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጴጥሮስ ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስ የተለያዩ ጥቅሶችን በሁለቱ መልእክታት ላይ ተጠቅሟል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክታቱ ውስጥ የብሉይ ኪዳን ጥቀሶችን እምብዛም አልጠቀሰም፡፡ ጠቀሰ ቢባል በዕብራውያን መልእክቱ ብቻ ነው፡፡ ይህ ከብሉይ ኪዳን ጥቅሶች መጥቀስና አለመጥቀስ የተከሰተው የትምህርታቸው የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑ ሕዝብና አሕዛብ አኳያ መሆኑንን ልብ ይሏል፡፡
5. ጌታ እና ሁለቱ ሐዋርያት
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ከሰባ ሁለቱ አርድእት ወገን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ወገን መሆኑ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኝ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ጋር ኖሯል፤ በልቷል ጠጥቷል፡፡ እንዲሁም ከዘመነ ሥጋዌው እስከ ዕርገቱ አብሮት በመሆን የቃሉን ትምህርት እና ስብከቱን አድምጧል፤ የእጁን ተአምራት በዐይኑ ዐይቷል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ግን ይህን ዕድል በወቅቱና በጊዜው እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ አላገኘም፡፡ እርሱ በዚያን ወቅት ቤተክርስቲያንን ያሳድድ ነበር፡፡ /1ጢሞ. 1.13/ በኋላ ግን ቅዱስ ጳዉሎስ በአሳዳጅነቱ አልቀጠለም፡፡ በዚህም ክርስቶስን አወቀው፤ በራእይም ተመልክቶት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጌታ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በአካል ባያገኘውም በደማስቆ በብርሃን አምሳል ተገልጦ አነጋግሮታል፡፡ /የሐዋ. 9.1/ በቆሮንቶስም በምሽት በራእይ ተገልጦለት አነጋግሮታል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ «ጌታም በራእይ ጳዉሎስን እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፤ ነገር ግን ተናገር፤ ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው፡፡» እንዲል፡፡ /የሐዋ.18.10/
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በአካለ ሥጋ አግኝቶት ቅዱስ ጳዉሎስን ባያነጋግረውም ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ጸሎት ሲያደርስ ተገልጦ አነጋግሮታል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይኽን ሲገልጽ «ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለስሁ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፣ እርሱም ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፣ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት፡፡ … ሒድ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁ አለኝ፡፡» በማለት ነው፡፡ /የሐዋ.22.17-21/
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን ለአገልግሎት ከመረጠው በኋላ አብሮት ስላለ በየጊዜው ያበረታታው ነበር፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስን በራእይ እየተገለጠለት ያጽናናው ያበረታውም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ጌታ በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ሌሊት በአጠገቡ ቆሞ «ጳዉሎስ ሆይ፣ በኢየሩሳሌም ለእኔ እንደመሰከርክ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሀል፤ አይዞህ» በማለት አዝዞታል፤ አጽናንቶታል፡፡/የሐዋ.23.11/
6. የጴጥሮስ እና የጳዉሎስ መልእክታት
እንግዲህ የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳዉሎስ ከጌታ ጋር ያላቸው ግንኙነት ይህን ይመስላል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ትምህርቱን፣ ምክሩንና ተግሣጹን ቀጥታ ያገኘ ቢሆንም ቅዱስ ጳዉሎስም የጌታ ትምህርቱ፣ ምክሩና ተግሣጹ አልቀረበትም፡፡ በዚሁ መሠረት የመልእክቶቻቸውንም ጭብጥ ከዚህ ዐውድ አኳያ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ የትምህርት ትኩረት አቅጣጫዎቻቸው ከምን አንፃር እንደሆነም ማስተዋል ይቻላል፡፡
በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስም ሆነ ቅዱስ ጳዉሎስ የጻፉት ወንጌልን ሳይሆን መልእክታትን ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለት መልእክታትን ሲጽፍ ቅዱስ ጳዉሎስ ዐሥራ አራት መልእክታትን ጽፏል፡፡ የአጻጻፍ ስልታቸውም ሆነ የትኩረት አቅጣጫቸው የራሱ የሆነ ዐውድ አለው፡፡ መልእክታቱንም ሲጽፉ ከየራሳቸው ዐውድ አኳያ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዶግማ በቅድስና ሕይወት ዙሪያ ሲያተኩር ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ከቅድስና ሕይወት ጎን ለጎን በዶግማና በነገረ እግዚአብሔር ላይ ያተኩራል፡፡
ይህን አተያይ ከቅዱስ ጴጥሮስ አኳያ ስንመለከት ራሱ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልእክቱ እንደ አሠፈረው ነው፡፡ ይህም «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡» ብሎ እንደጠቀሰው ነው፡፡ /1ጴጥ.1.15/ ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ይኽን ሲገልጽ «… በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ፡፡» በማለት ሲሆን በዚሁ ምዕራፍ ላይ «የእምነታቸውን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ…» እና «ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው)» በማለት ገልጾታል፡፡ /1ጴጥ.1.1-9፤ 4.18/
በሌላ መልኩ ደግሞ ከዚህ ከመልእክት የትኩረት አቅጣጫ አኳያ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ በመግለጽና በማብራራት የሚያተኩረው በነገረ እግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የእርሱ መልእክታት ስለ ጸጋ እግዚአብሔር፣ ስለ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካልነት፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል ስለሚገኝ ድኅነት፣ ስለ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን /ስለ ምስጢረ ክህነት፣ ቁርባን፣ ጥምቀት፣ ጋብቻ፣ ትንሣኤ ሙታን/ ያተኩራሉ፡፡ የእነዚህ ሁለት ሐዋርያት መልእክታት በአጭሩ በዚህ መልክ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡
7. ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ በጌታችን ስም ያደረጓቸው ተአምራት
እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በዘመናቸው ተአምራት ያደርጉ ነበር፡፡ ያደረጓቸውም ተአምራት ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ታላቅ አስተዋጽኦ ነበሯቸው፡፡ ሁለቱም በተአምራት ሙት አስነሥተዋል፤ ድውይ ፈውሰዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይኸውም ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታ የተባለች በኢዮጴ የምትኖር አንዲት ሴትን ከሞት በተአምራት አስነሥቷል፡፡ ይህች ሴት ለሰው ሁሉ መልካም የምታደርግ፤ ምጽዋትን የምትሰጥ፣ ለተለያዩ ደሃ ሴቶች የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትን በመሥራት ትለግስም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ መልካም ነገር የምትፈጽም ሴት ታማ ሞተች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በተአምራት ከሞት አዳናት፡፡ /የሐዋ.9.36-40/
ቅዱስ ጳዉሎስም እንዲሁ የሚጠቀስ ተአምር አለው፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም ቃለ እግዚአብሔርን እያስተማረ አውጤኩስ የተባለ አንድ ወጣት አንቀላፋ፡፡ በእንቅልፉም ክብደት ምክንያት ከተቀመጠበት ወድቆ ይሞታል፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም ይህን ወጣት በተአምር ከሞት አስነሥቶታል፡፡ /የሐዋ.20.9-12/
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በልብሳቸውና በጥላቸው በተአምራት ሕሙማንን እየፈወሱ ሕመምተኞችንም የክርስቶስ የመንግሥቱ ዜጎች ያደርጉ ነበር፡፡ ተአምራቱም ችግረኞቹን ከችግራቸው ከማላቀቅ ባለፈ ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት እጅጉን ይጠቅም ነበር፡፡ /የሐዋ.5.15-16፤ 19.12/
ቅዱሰ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ሰማዕትነት እንደተቀበሉ የሚያሳዩ
8. ሰማዕተ ጽድቅ ጴጥሮስ ወጳዉሎስ
የቤተክርስቲያን ጉዞ ሁልጊዜ በመስቀል ላይ ነው፡፡ ይህ የመስቀል ጉዞ ደግሞ መሥዋዕትነትን /መከራ መቀበልን/ ይጠይቃል፡፡ ከዚህም የተነሣ በሰይፍ የተመተሩ፤ በመጋዝ የተተረተሩ፣ በእሳት የተቃጠሉ ለአናብስት የተጣሉ በአጠቃላይ በብዙ ስቃይ የተፈተኑ ቅዱሳን ሐዋርያት አሉ፡፡ ከእነዚህ ሐዋርያት ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሱት እነዚህ ሁለት ሐዋርያት ናቸው፡፡ «ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ፡፡» የሚለውን የጌታችንን ቃል መመሪያ አድርገው ለቤተክርስቲያን ሁሉን አድርገው፤ ሁሉን ሆነው የሰማዕትነትን ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስትና ሃይማኖት የአይሁድ መሪዎችንና ሊቃነ ካህናቱን ይሞግት፤ ከእነርሱም ፊት ምስክርነት ይሰጥ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድን ሊቃነ ካህናት «ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል» እያለ በሸንጎ ይሟገት ነበር፡፡ /የሐዋ.5.29/ በዚህም ብዙውን ጊዜ ይገረፍ ይታሰር ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስም የተለያዩ የመከራ ጽዋን ተቀብሏል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ እርሱና ሌሎች ሐዋርያት ስለክርስቶስ መከራ መቀበላቸውን ሲገልጽ «በሁሉ መከራ ስንቀበል አንጨነቅም፣ እንናቃለን አንዋረድም፤ እንሰደዳለን አንጣልም፤ እንጨነቃለን አንጠፋም፡፡» በማለት ነው፡፡ /2ቆሮ 4.8-11/ ከዚህም በተጨማሪ «በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣትም» በማለት የሰማዕትነት ሕይወቱን ገልጿል፡፡ /2ቆሮ.6.4-5፣ 1ቆሮ. 11.22-28/
በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰበትን መከራ ሁሉ በዚህ መልኩ ገልጿል፡፡ እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በዚህ መልኩ ስለ ወንጌልና ስለክርስቶስ መከራ ከተቀበሉ በኋላ ከዚህ ምድር ያለፉት በሰማዕትነት ነው፡፡ ሁለቱም በሰማዕትነት ያለፉት በዘመነ ኔሮን ሐምሌ 5 ቀን 67 ዓ.ም ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ያረፈው የቁልቁሊት ተሰቅሎ ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ አንገቱን ተሠይፎ ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት ታላላቅ የጌታችን ሐዋርያት ረድኤት በረከት አማላጅነት ሁላችንንም አይለየን፤ አሜን፡፡
ዲያቆን ታደሰ ወርቁ
እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡