St_Anthony_Icon_3.jpg

የበረሃዉ መልአክ ቅዱስ እንጦንስ

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
 
St_Anthony_Icon_3.jpgእንደተለመደው የኦሪት ዘፍጥረትን ትርጓሜ መሠረት ያደረገውን ተከታታይ ትምህርት ለመማር በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ውስጥ ካሉት አዳራሾች በአንዱ ተሰብስበናል፡፡  ትምህርቱ ከመጀመሩ በፊት በወረቀት ለሚጠየቁት ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ሁላችንም ስለሚያጓጓን በመጠባበቅ ተቀምጠናል። ከመምህራችን የቀረበው የዕለቱ ጥያቄ ግን ሌላ ነበር። «ዛሬ ቀኑ ስንት ነው?» የሚል፡፡ ጥር 22 በማለት መለስን፡፡ «ዛሬ የዕለቱ መታሰቢያነት ለማን ነው?» ቀጥሎ ጠየቀን፡፡ መቼም ቅዱስ ዑራኤል መሆኑን አያጣውም፣ ግን ለምን ጠየቀን? በአእምሮዬ የሚመላለስ ጥያቄ ነበር፡፡ ለነገሩ ዕለቱ የተለየ ነገር ቢኖረው ነው እንጂ አይጠይቀንም ነበር፡፡ ይሄን እያሰብኩኝ ዝምታ በሰፈነበት፥ አንድ ልጅ እጁን አነሳና «የመልአኩ የቅዱስ ዑራኤል በዓል ነው» በማለት መለሰ፡፡ መምህራችንም ጥሩ ነው በማለት ተናገረና  «ሌላስ?» አለ በተረጋጋ አንደበት፡፡ ከዚህ በላይ እንኳን የማውቀው ነገር የለም አልኩኝ ለራሴ፡፡
 
ለማንኛውም በዚህ ዕለት ታላቁ አባት ርእሰ መነኮሳት ቅዱስ እንጦንስ ያረፈበት ዕለት ነው፡፡ ጽሌውም (የጽላት ነጥላ ቁጥር) በዋና ከተማችን አዲስ አበባ በምትገኘው መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ይገኛል፡፡ በርግጥ በራሱ ስም የተሰሩ ገዳማትም አሉ። ይህ የአዲስ አበባዉ ግን የእመቤታችን ጽሌ ከመምጣቱ በፊት  በቅዱስ እንጦንስ ስም ይጠራ እንደ ነበር ሁሉ ተነገረን። ይሄንን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነበር። ለምን ለሌሎች አላካፍለውም? ሌላ ጥያቄ፤ እነሆ። (ሥዕል፦ቅዱስ እንጦንስ፥  ከታች በግራ በኩል ቅዱስ እንጦንስና የዋህ ጳውሊ ሲገናኙ )

ቅዱስ እንጦንስ በ25ዐ ዓ.ም ቅማን/Qimn El-Arouse/ በሚባል በማዕከላዊ ግብጽ ነው የተወለደው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በቤተክርስቲያን ሳለ ወንጌል ሲነበብ ጌታችን ለባለፀጋው ጎልማሳ የነገረውን «ፍፁም ልትሆን ብትወድ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች  ሰጥተህ ተከተለኝ» የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ስለሰማ ወላጆቹ ከታናሽ እህቱ ጋር ትተውለት የሞቱትን ሰፊና በመስኖ የሚለማ መሬት ቶሎ ሽጦ ለድሆች ከሰጠ በኋላ እህቱን ለደናግል ማኅበር አደራ ሰጥቶ የብሕትውና ኑሮውን ጀምሯል፡፡

ቅዱስ እንጦንስ በብዙ ተጋድሎና ፈተና በመካከለኛው የግብጽ በረሃ ውስጥ ብቻውን የኖረ ከዚያም ብዙ ተከታዮችን ያፈራ፣ የምንኩስና ሕይወትም ጀማሪ የሆነ አባት ነው፡፡

ቅዱስ እንጦንስ፣ የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ወዳጁም ነበር፡፡ ርእሰ ባህታውያን የዋህ ጳውሊንም ከፍኖ የቀበረው ቅዱስ አትናቴዎስ በሰጠው ካባ ሲሆን በመልሱም ለቅዱስ አትናቴዎስ የቅዱስ ጳውሊን ለራሱ ከዘንባባ የሠራውን እንደታታ ቅርጫት የመሰለውን ዐፅፍ ልብስ ሰጥቶታል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም በበዓለ ትንሣኤና በበዓለ ሃምሣ በውስጥ ይለብሳት ነበር፡፡

ቅዱስ እንጦንስና ዘመነ ሰማዕታት

በክርስቲያኖች ላይ መከራና ሞት በዓላውናን ነገሠታትና መኳንንት በታዘዘ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንደበግ እየተነዱ ወደሞት ይሔዱ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ከበአቱ ወጥቶ ወደ እስክንድርያ ሔደ÷ ተጠርተንም እንደሁ በእሽቅድምድም ለመሳተፍ አለበለዚያ ተሽቀዳዳሚዎችን ለመጎብኘት እንሒድ በማለት እንጦንዮስ ሰማዕትነትን ለመቀበል ከፍተኛ ጉጉት ነበረው፡፡ ነገር ግን እርሱን የብሕትውናና የምንኩስና ሕይወት አስተማሪ ይሆን ዘንድ ስለ ብዙዎች ጥቅም ጠበቀው፡፡ ሰማዕታት ለፍርድ ሲጠሩ አጅቦ ይሸኛቸዋል÷ እስኪገደሉም ድረስ አይለያቸውም፡፡ ዳኛው ድፍረቱንና የተከታዮቹን ብዛት ጽኑ መንፈሳቸውንም ባየ ጊዜ ማንም መነኩሴ ወደ ፍርድ ቤት አካባቢና በከተማው ውስጥ እንዳይታይ አዘዘ፡፡
እንጦንስ ግን ሰማዕታትን አጅቦ ከፍርድ ቤት ፊት ለፊት ዳኛው ሊያየው በሚችል ስፍራ ተገኘ። ሁሉም በመገኘቱ ሲደነቁ ኃላፊው በትሩን ይዞ ወደ እርሱ መጣ፥ እርሱ ግን የክርስቲያኖችን ጽኑ መንፈስ ያሳይ ዘንድ ምንም ሳይፈራ ቆመ።
 
    ምንጭ፡ ያረጋል አበጋዝ (ዲ/ን) ና አሉላ ጥላሁን ፣ 1997። ነገረ ቅዱሳን 3። ማኅበረ ቅዱሳን፣ አ.አ።

በአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃግብሩ የመጀመሪያ ቀን ከ175ዐ በላይ አልባሳት ተሰበሰበ

                                                                   በፈትለወርቅ ደስታ
 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን «ሁለት ልብሶች ያሉት….» በሚል ስያሜ የሚከናወነው የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በይፋ ተከፈተ በመጀመሪያው ዕለትም ከ175ዐ በላይ አልባሳት  ተሰብስቧል፡፡

ካህናት አባቶች የማኅበሩ አባላትና ምዕመናን በተገኙበት መርሃግብር በጸሎት የከፈቱት ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ሙሉጌታ «ሁለት ልብሶች ያሉት አንዱን ለሌላው ይስጥ» በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3÷11 » ላይ ያለውን የወንጌል ቃል መነሻ በማድረግ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም በማኅበሩ አባላት የመዝሙር ክፍልና በአባላት ህፃናት ልጆች መዝሙር ቀርቦ የቅዱሳን መካናት ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት በወ/ሮ ዓለምፀሀይ መሠረት ስለመርሃግብሩ ዓላማና አስፈላጊነት ገለፃ ተደርጓል፡፡

በጉባዔው ላይ የተሳተፉት ምዕመናን ስለ ጉባዔው ያላቸውን አስተያየት ሲገልፁ «እግዚአብሔር ፍጥረቱን ተጠቅሞ ማንኛውንም ሥራ ይሠራል ማህበሩም በዚህ ዘርፍ ብዙ እየሠራ ነው፡፡» በየገዳማቱ ያሉትንም እንዲህ ማሰቡ በጣም ጥሩና ይበል የሚያሰኝ ነው አሁን ያየሁት እነሱ በልብስ ተራቁተዋል እኛ ግን በመንፈስ ተራቁተናል ጅምሩ ጥሩ ነው በዚሁ ይቀጥል፤ ዓላማው ያስማማናል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት» ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በማኅበሩ ሰብሳቢ በቀሲሲ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዮም የመዝጊያ ንግግርና በመርሃግብሩ ለሚሳተፉ ምዕመናን ምሥጋና አቅርበሙ በጸሎት ተዘግቷል ጠዋት የጀመረው የአልባሳት ማሰባሰብ መርሃግብር ቀጥሎ በዕለቱ ከምዕመናን ከ1750 በላይ የወንዶች፣ የሴቶችና የህፃናት አልባሳት ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡

                               
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ለመነኮሳትና አብነት ተማሪዎች የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐግብር ተዘጋጀ።

በፈትለወርቅ ደስታ
«ሁለት ልብሶች ያሉት….» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ልዩ የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተዘጋጀ
 
የዚህ መርሃ ግብር አዘጋጅ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳን መካናት ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሲሆን ጥር 22/2003 ዓ.ም በማኅበሩ ጽ/ቤት በይፋ ይከፈታል፡፡ የቅዱሳን መካናት ልማትና ማህበራዊ ዋና ክፍል የቅስቀሳ አስተባባሪ ዲያቆን ደረጀ ግርማ ለማኅበረ ቅዱሳን የሬድዮ ክፍል እንደገለፁት «የመርሃ ግብሩ ዓላማ ብዙዎቹ ገዳማውያን መነኮሳትና የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚለብሱትን እራፊ ጨርቅ ምግባቸውን ያሰጡበታል፤ ያንኑ ምግብ ምግብ እየሸተተ መልሰው ይለብሱና ለአገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያን ይገባሉ፡፡ ይሄንን ማስቀረት ይኖርብናል፡፡ ሌላው ጌታችን መድኃኂታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 25 ላይ እንደገለጸው፥ «ታርዤ አላለበሳችሁኝም» ከሚለው ወቀሳ ለመዳንና «ታርዤ አልብሳችሁኛልና» የሚለውን ትእዛዝም ለመፈጸም ነው፡፡ በተጨማሪም በአገራችን በአልባሳት የመደጋገፍ ባሕል የለም። ይህ ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ቢያንስ በየሁለት ዓመት አንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት መርሃ ግብር ያስፈልጋል» በማለት ገልጸዋል፡፡

አክለውም «ይህ መርሃ ግብር ቢያንስ ለሁለት ዓመት ያህል የአልባሳት ችግራቸው እንዲቀረፍ በ25 ገዳማትና አድባራት ያሉ 75ዐ መነኮሳትና በ5ዐ ታላላቅ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 35ዐዐ መምህራንና ተማሪዎችን በጊዜያዊነት የሚያግዝ ይሆናል፡፡»

በጊዜው የሚሰበሰቡ የአልባሳት አይነቶች ለአብነት ትምህርት ቤቶች ሸሚዝ፣ ሱሪ፣ ኮት፣ ጃኬት፣ ጫማ፣ አንሶላ፣ ጋቢ፣ ብርድልብሶች ካኔተራና የመሳሰሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን ለመነኮሳት ደግሞ አቡጀዲ፣ ልብስ፣ ሹራብ፣ ነጠላ እና ለመነኮሳት የሚሆን ሻርፕ፣ ብትን ጨርቅ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡

በዝግጅቱ ላይም ከ5ዐዐዐ በላይ ምዕመናን እንደሚሳተፉበት ይገመታል ያሉት አስተባባሪው የአልባሳት ድጋፍ ማድረግ ያልቻሉ ምዕመናን የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

«እርስዎ የለበሱት ሌላውን ያለብሳልና» ሁሉም ምዕመን ከዚህ መርሐግብር ለመሳተፍ ወደኋላ እንዳይል አዘጋጅ ክፍሉ ያሳስባል፡፡

የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃግብር የማኅበረ ቅዱሳንን ሕንፃ ጨምሮ በ15 የሰንበት ትምህርት ቤቶች ይከናወናል፡፡ 

tsihuf2003.jpg

የጥናታዊ ጽሑፍ ግብዣ

tsihuf2003.jpg 
ttsihuf2003.jpg
gonder4.jpg

የጥምቀት በዓል ፋይዳና ተግዳሮቶቹ

በዶ/ር ቤተልሔም ግርማ
 
gonder4.jpgበስምንት ዓመት የጎንደር ቆይታዬ በየዓመቱ በዓሉን የመካፈል ዕድል አግኝቻለሁ። እያንዳንዱ ዓመት የየራሱ የሆነ ለየት ያሉ ትዕይንቶች ነበሩት። በአጠቃላይ ግን የታዳሚው ቁጥር ለማመን በሚያስቸግር መልኩ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል። በሌላ መልኩ ደግሞ ወጣቱ በበዓሉ ላይ ያለው  ተሳትፎ ለውጥም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አንፃር በጣም የሚበረታታ ነው።

 
የጥምቀት በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ቀልብ እየሳበ የመጣ ታላቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ የጌታችን የመድኀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ከሚያከብሩ ጥቂት የዓለማችን ሀገሮች አንዷ እና ዋነኛዋ ናት። ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ስለሆነም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳውም ጎን ለጎን የሚሄድ ነው። የዚህም ቋሚ ምስክር ከዚህ በዓል ጋር የሚነሱ እና የሚወሱ የሥነ-ቃል ሀብቶች ናቸው።

ለሦስት ቀናት ያህል (ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ) በተከታታይ የሚከበረው ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ ከመሆኑም በላይ ለምዕመኑ በረከት የሚያስገኝ ነው።

«እልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው» መዝ 88፥15

desie.jpgታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በክብር ወጥተው በሕዝቡ እልልታ፣ ሽብሽባ እና በካህናቱ ውብ ያሬዳዊ ዜማ ወደ ወንዝ ወይም የተዘጋጀ የውኃ ቦታ በመውረድ የሚጀምረው ይህ በዓል ሕዝቡን በሰፊው የሚያሳተፍ ነው።

ይህንን ውብና ድንቅ ክብረ በዓል ለማክበር አገር ተሻግረው ሥርዓቱን ለማየት የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ከዓመት ወደ ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። ይህም ጥንታዊት፣ ኦርቶዶክሳዊትንና ሐዋርያዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያናንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያለው ድርሻ በዓለም ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም። በማያውቁት ሀገር እና በማያውቁት ቋንቋ በሚደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሰማያዊ ሥነ- ሥርዓት መንፈሳዊ ሀይል ተማርከው የሚጠመቁም የውጭ ዜጎች አልጠፉም።

ጥምቀት በጎንደር

በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች አንዷ ጎንደር ናት። የብዙ ታቦታት ሀገር የሆነችው ይህች ከተማ በዓይነቱ ለየት ያለ ባሕረ ጥምቀትም አላት። ይህ የአፄ ፋሲል መዋኛ የነበረው ታሪካዊ ባሕረ ጥምቀት ለጥምቀት በዓሉ ትልቅ ግርማ ሞገስ የሚሰጥ ነው።

የዚህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የነገ ተስፋ እና የቅርሱና የሥርዓቱ ውርስ ተቀባይ የሆነው ወጣት gonder5.jpgበበዓሉ ላይ ትልቅ ተሳትፎ ያደርጋል። በዓሉ ከመከበሩ ከወራት በፊት በየሰንበት ትምህርት ቤቱ በልዩ ኮሚቴዎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ ቆይቷል።

በተለይ ደግሞ በዓሉ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት አካባቢን ከማስዋብ ጀምሮ በከተማዋ ለሚገቡ እንግዶች ኢትዮጵያዊ የሆነ አቀባበልና መስተንግዶም ተደርጓል።

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ታይቶ እና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ለታቦታቱ ልዩ ክብር በመስጠትም የምንጣፍ ማንጠፍ ሥነ ሥርዓትንም ጀምረዋል። ይህ አባቶችን ከማስደመም አልፎ በወጣቱ ሥነ ሥርአትም ያላቸውን እምነትም ጨምሯል። ወጣቱ ለሃይማኖቱ ያለውን ፍቅርና ተቆርቋሪነትም በግልጽ አሳይቷል።

ከዚህ ባለፈም ወጣቱ የበዓሉ ዝማሬ በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲከናወን ሥርዓት አልባ የሆኑና ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸውን ጭፈራና ሆይታም ለማስቀረት ትልቅ እና አመርቂ የሆነ አንቅስቃሴ አድርጓል።

የዘንድሮም የጥምቀት በዓል ከመቼውም ጊዜ በላይ በደማቅ መልኩ ተከብሮ አልፏል። ከላይ በጽሑፌ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እያንዳንዱ ዓመት የየራሱ መገለጫዎች እንዳሉት ሁሉ በዘንድሮውም አንዳንድ ለየት ያሉ ክስተቶች መታየታቸው አልቀረም።

ወደ መቶ ሺህ ገደማ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና መንፈሳዊ ተጓዦች የታደሙበት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በሕዝቡ ቁጥር ረገድ ከቀድሞው ዓመታት ሁሉ የላቀ ነበር። ይህንን በቁጥር የበዛ ሰው ለማስተናገድም ሲባል በባሕረ ጥምቀቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ልዩ የሆነ የመቀመጫ ቦታ ተሰናድቶ ነበር ። ይህ በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ እንዳለ ክቡር ትሪቢውን ያለ የመቀመጫ ሥፍራ በአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ ዙሪያ የተገነባ ነው። በዚህም ልዩ የሆነ ቦታ እንግዶች በክብር ሲስተናገዱ ውለዋል።

ያለ ምዕመናን?

የኢትዮጵያ ምዕመን በእንግዳ ተቀባይነቱ የታወቀ በመሆኑም ሥነ ሥርዓቱን ለመመልከት ለመጡት የውጭ ዜጎች የተለመደውን አቀባበል አድርጓል። የክብረ በዓሉ አፈጻጸም ሳያጠራጥረው ያላለፈ ግን ጥቂት አይባልም። ሕዝበ ክርስቲያኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በቅርብ ለመከታተል የሌሊቱ ጨለማና ብርድ ሳይበግረው፥ ጣፋጭ እንቅልፉ እና ሙቅ መኝታው ሳያታልለው፥ በቦታው ቢገኝም እንኳን በቅርበት ለማየት ቀርቶ በአካባቢው የሥነ ሥርዓት አስከባሪ ወደ ኋላ እንዲመለስ ተደርጓል።

ምንም እንኳን የሀገር ጎብኚዎቹ(ቱሪስቶች) ለማየት የሚመጡት ባሕረ ጥምቀቱን ካህናቱንና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ቢሆንም ለዚህ ሁሉ ውበት የሚሰጠው ምዕመኑ ጭምር ነውና ምዕመኑም እንድ መስህብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ስለዚህም ቢያንስ የተወሰነው ሰው ቀረብ ብሎ እንዲያይ(እንዲታደም) ቢደረግና የሕዝቡንም ጉጉት ለማስተናገድ ቢሞከር የተሻለ ይሆን ነበር። ብዙሃኑ ወጣት ለበዓሉ ዝግጅት እስፓልት ማጠብ እንኳን ሳይቀረው ደክሞ የበይ ተመልካች መሆኑ ቅር ማሰኘቱ አልቀረም። የሕዝቡ ቁጥር እንዳለ ሆኖ እንግዶች ቦታ ቦታ ከያዙ በኋላ እንኳን ምዕመኑ የሚገባው ክብር ተሠጥቶት ቢስተናገድ ተገቢ ነበር።

የአውሮፓውያን መንፈሳዊያን በዓላት ዓለማዊነት

በአየርላንዳውያን ዘንድ መጋቢት 17 (እ.ኤ.አ) የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል አላቸው። በዓሉ ፓትሪክስ የሚባል ከ387-461 ዓ.ም እንደኖረ የሚታመንና በአየርላንድ (በቀድሞዋ ሮማ) ታዋቂ የሆነ መንፈሳዊ አባታቸው ነው።

17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መከበር የጀመረው ይህ ክብረ በዓል፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን ንጹሕ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነበር። ቀስ በቀስ ግን የአየርላንድን ባሕል ብቻ የሚያሳይ ዓለማዊ ክብረ በዓል እየሆነ መጥቷል።

patrics1.jpgpatrics2.jpg

 
 
 
 
 
በ1990ዎቹ መካከል የአየርላንድ መንግሥት ይህን በዓልን የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባትና ባሕሏን ለማሳየት እንቅስቃሴ አድርጎ ተጠቅሞበታል።

የአየርላንድ የሃይማኖት መሪዎች በዓሉ ዓለማዊ ገጽታ እየተላበሰ መሄዱን ይገልጻሉ። በ2007 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ፋዘር ቪንሰንት የተባሉ አየርላንዳዊ ቄስ the world’s magazine በተባለ መጽሔት ላይ ባወጡት ጽሑፍ «በዓሉ የቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል፤ ዓላማውም ሃይማኖታዊ መሆኑን ማስገንዘቢያ ጊዜው አሁን ነው» ይላሉ።

patrics.jpgበያዝነው የፈረንጆች አመት መጋቢት ወር ላይም በፋሽን፣ በፈንጠዝያ፣ በሙዚቃ፣ በመንገድ ላይ ቲአትሮችና በካርኒቫል ለማክበር እቅድ ተይዟል። 

በሌላ ሁኔታ የ”Assumption Day” ከዚሁ ዕጣ ፈንታ አላለፈም። Assumption Day በሀገራችን ፍልሰታ ብለን የምናከብረው የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት በዓል ነው። ዛሬ ዛሬ በስዊዘርላንድና በብዙ የአውሮፓ ሀገሮች ምንም ዓይነት የሚታይ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሳይኖር በርችት፣ በችቦ፣ ጭፈራ፣ በህብረ ቀለማትና በመንገድ ላይ ትርዒት ብቻ የሚከበር ሆኗል።

እነዚህ በዓላት መንፈሳዊነታቸው የደበዘዘውና ሲብስም የጠፋው የምዕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት እንደ ቤተ ክርስቲያን መቆም ሲያቅታቸውና ተልዕኳቸው እየተዳከመ ሲሔድ መሆኑ አይረሳም። በኢትዮጵያ ግን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ ሳይገታ በዓሉን በመንፈሳዊ ይዘቱ የሚያክብረው ምዕመን ሳይጠፋ ማቀላቀሉ ይጠቅም ይሆን? በጥብቅ ማሰብ ያሻል!

የበዓሉ ተግዳሮት


ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ የመጣው የጥምቀት አከባበር ሌላ ትልቅ የማንነት ጥያቄም ከፊቱ ተጋርጦበት ይገኛል። ፈረንጆቹ እንዲህ አይነት የሕዝብ ስብስብ እና ሥርዓት በሃገራቸው የተለመደ ባለመሆኑ ይሄንን ክብረ በዓል ወደ ሚያውቋቸው የአደባባይ ትሪዒቶች ማጠጋጋታቸው አይቀርም። ከዚህም አንዱና ዋነኛው “ካርኒቫል” ነው። ይህ በተለይ በላቲን አሜሪካ አካባቢ የሚታወቅ የአደባባይ ትርዒት ነው። በዚህ ወቅት ብዛት ያላቸው ሰዎች ቀለም የበዛበት ወይም ለየት ያሉ አልባሳትን በመልበስ በየአደባባዩ ሲጨፍሩና ሲዝናኑ ይከርማሉ። ይህ ፍጹም አለማዊ የሆነ የአደባባይ ትርዒት ከየትኛውም መንፈሳዊ ክብረ ባህል ጋር ማወዳደር ከመቀሰፍ አያድንም።

የዘንድሮውን የጎንደር የጥምቀት በዓል ካርኒቫል እንዲኖረው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ከዚህም ውስጥ ዋነኛው በየመንገዱ ላይ ጊዜአዊ ድንኳኖችና ዳሶችን በመጣል የባህላዊ መጠጥና ምግቦች መስተንግዶ ነው። እነዚህ በዋና ዋና መንገዶችና በጥምቀተ ባህሩ አቅራቢያ የተተከሉ ዳሶች ውስጥ ምግብና መጠጥ ከመስተናገዱም ባለፈ ዓለማዊ ዘፈኖችም ይከፈታሉ። ይህ መስተንግዶ ለእንግዶች ጥሩ አቀባበል ተያያዥ ጉዳቶችንም ማምጣቱ አልቀረም። ከዚህ ባለፈ የሚያስፈራው ደግሞ ይህ አካሄድ ወደ ፊት ወደ የት ሊያመራ እንደሚችል ነው። በአህዛብና በአማሌቃያውያን ጭምር የሚከበረው የጥምቀት በዓል የሕዝብ በዓል መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሃይማኖታዊ መሠረቱ ግን መቼም ቢሆን ለአፍታ እንኳን ሊዘነጋ አይገባውም። ማንም ከየትኛውም አይነት የአደባባይ ትርዒት ጋር ቢያመሳስለው እንኳን የበዓኡን ትክክለኛ ትርጉምና አመጣጥ ማስረዳትና ማስተዋወቅ የእኛ የእምነቱ ተከታዮች ኃላፊነት ነው።

ከቱሪዝም አንፃርም ቢሆን ከፍተኛ የሃገር ውስጥ ገቢ የሚያስገኘው ይህ ክብረ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል። በዓሉም ጥንታዊነቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ ትልቅ ጥንቃቄና ትኩረትን ይሻል።

እንግዲህ ዓለምን የሚያስደምምና የሚያማልል ሃይማኖታዊ ትውፊት ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የባለቤትነት ጥቅም ትሻለች። ኢትዮጵያና ቤተ ክርስቲያንን  ቤተ ክርስቲያንንና  ኢትዮጵያን ለይቶ ማየት ይከብዳል። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የምታሰኛትን ይህችን ቤተ ክርስቲያን በክብረ በዓላቱም ብቻ ሳይሆን ሁሌም ማሰብ ግድ ይላል። በአዘቦቱም ቢሆን በመላ አገሪቱ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎች በአንድም በሌላም መንገድ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያኗን መጠበቅ ሃገራዊ ግዴታ ያደርገዋል።

የቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ ምንድን ነው?

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብርሃነ ትንሣኤው በኋላ ለምዕመናን የሚገለጠው በቤተ ክርስቲያን ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ለዓለም እንድታሣይ ታዛለች። ለዚህም ነው በዘመነ አስተርእዮ(በመገለጥ) ክርስቶስን ለመስበክ ቤተ ክርስቲያን ታቦትን ይዛ የምታወጣው። በክብረ በዓሉም የምናሳየው ደስታ ክርስቶስ በመገለጡ ምክንያት ያገኘነውን ደስታ የሚያመለክትና ይሄንን ደስታ ለዓለም ማሳየታችን ነው።

ታቦቱ ሲወጣ ሴቶች በእልልታ ወንዶች በጭብጨባ የምናሰማው ደስታ፥ እኛ ከመሠዊያው ላይ ያገኘነውን የክርስቶስ ሥጋ በልተን ደሙን ጠጥተን ደስ ብሎናል። እናንተም ከደስታው ተካፋይ ሁኑ ማለቷ ነው፣ ቤተ ክርስቲያን።

በመሠረቱ በክርስትና፥ የበዓል ድምቀት፥ የሚያከብሩት ሰዎች መንፈሳዊነት ነው። በዓሉም ደምቆ ተከበረ ማለት ምዕመናን ሥጋ ወደሙ ተቀበሉ ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ ነው የምታምነው።  

እንደ እኔ እንደ እኔ

ከኢኮኖሚ ከቱሪዝም አንጻር ስንመለከተው የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከፍ ያለ ገቢን ለማግኘት መስራት በራሱ የሚነቀፍ አይደለም። ገቢን ለማሳደግና ልማትን ለማፋጠን የሚደረገው እንቅስቃሴ ግን ለገቢው መገኘት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የበዓል ሥነ ሥርዓት እንዳያደበዝዘው ማሰብንም ይጠይቃል። ለምሳሌ የበዓሉ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓተ ከተጠናቀቀ ታዳሚው ምዕመንም ከተሰናበተ በኋላ ባሉት ተከታታይ ዕለታት ቢደረግ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም። አንዱ ሥነ ሥርዓት ሌላውን ሳይጋርደው የአንዱ ታዳሚ ሌላውን ሳይገፋው ከሁለቱም የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ (maximizing the profit) ብልህነት ነው። ከምንም በላይ በዓሉን ስናስብ ቀዳሚው ባለቤት ክርስቲያኑ ነውና ክርስቲያናዊ ፍላጎቱ ባይጎድልበት ለሁሉም ይጠቅማል። በግድ በአንድ ዕለት ይሁን ከተባለ እንኳን በቦታ መለያየቱ ሌላው አማራጭ ይሆናል። በባህረ ጥምቀቱና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው ጎዳናዎች መንፈሳዊው ሥርዓት (ዝማሬው ዕልልታው) በሌሎች ጎዳናዎችና ሜዳዎች ደግሞ የካርኒቫሉ ትርኢት ቢካሔድ ሁሉም የወደደውን ያነሣል። ማንም የወደደውን ይመርጥ ዘንድ መብቱን መስጠት የሠለጠነ አሠራር ነውና አንዱ በሌላው ላይ ሲደርብ ግን ሌላኛውን ወገን ያስከፋልና ቢታሰብበት ብንመካከርበት ይበጃል እላለሁ።
 
(ይህንን ጽሑፍ የላኩልንን ዶ/ር ቤተልሔም ግርማን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። የማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድሮችን ይጎብኙ፣ ለመካነ ድሮቻችን ይጻፉ።)
 
Timketal8n.jpg

የመርካቶ ሌላኛዉ መልክ

በአልታየ ገበየሁ
Timketal8n.jpg

Timketal6n.jpgመርካቶ የሚለውን ቃል እዚህ ጋር ስናነብ መቼም በየሕሊናችን የሚመጡ ብዙ የመርካቶ ሥዕሎች ይኖራሉ ፡፡ በተለይ ግርግሩ፣ ማጭበርበሩ፣ ሌብነቱ፣ በቀላሉ የማይገታዉ አመጹ፣ ምንም ነገር ፈልጎ የማይታጣበት መሆኑ፣ ቆሻሻው….በነዚህ ሁሉ ነገሮች እንደ መርካቶ ቅድሚያዉን የሚይዝ አካባቢ የሚኖር አይመስለኝም፡፡

Timketn.jpgዛሬ የመርካቶን ሌላኛውን መልክ እንይ፡፡ በመርካቶ ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎች እና ወጣቶች በደንብ ከሚታወቁባቸዉ  ነገሮች መካከል አንዱ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው ነዉ፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ሙሉ ቤተ ክርስቲያን የሚያሠሩ፣ ነዳያንን የሚያበሉ፣ የሚያለብሱ፣ በየዓመት በዓሉ የተቸገሩ ወገኖቻችን ከሌላው ወገናቸው ባልተናነሰ መንገድ በዓሉን እንዲያከብሩ በገንዘብ እና ለበዓላት በሚያስፈልጉ ነገሮች የሚረዱ በትክክል ገንዘባቸው ከየት እንደተገኘ የተረዱ ወገኖችን የያዘ አከባቢ መርካቶ ነው፡፡

Timketal7n.jpgመርካቶ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ ዋልታ አንዱ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ የገንዘብ እና የሰው ኀይል ምንጭ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያኒቷ ምን ያህል እንደተገነዘበች እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአራቱም ማዕዘን የሚገኙ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሕልውና እንዳይጠፋና በነዚሁ አከባቢ ለሚኖሩ ምዕመናን ተስፋ በመሆን እያገለገሉ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አለኝታ የሆኑ የክርስቲያን ወገኖችን የያዘ ቦታ መርካቶ ነው፡፡

የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ደግሞ እንዴት አድምቀው እንደሚያከብሩት ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን እንዴት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደሚያውሉት ያሳዩበትን ታላቅ ሥርዓት እንይ፡፡

Timketal5n.jpgየመርካቶ መሬት ወትሮ ከሚታወቅበት ቆሻሻነት ጸድቶ  እሱም  እንደ አዲስ ክርስቲያን ተጠምቆ በቄጠማ፣ በምንጣፍ አምሮበት ለሚያይ የወትሮው መርካቶ ነው ብሎ ለማመን በጣም ያስቸግራል፡፡ አየሩ በዕጣን መዓዛ ተሞልቶ፣ በመዝሙርና ዕልልታ ደምቆ ልዩ ልዩ ቀለማት ባሏቸው ፊኛዎችና ጥቅሶች ተውቦ ለሚያየው እውነት ይህ መርካቶ ነው ብሎ እንዲጠይቅ ያደርገዋል፡፡

በየአደባባዩና በየቦታዉ ድንኳን ተጥሎ ‹‹ካልባረክ¤ኝ አልለቅህም›› የሚለው የአባታችን የያዕቆብ የእምነት ቃል ተሰቅሎበት ምዕመናን የእግዚአብሔርን በረከት የሚጠብቁበት ብዙ ማረፊያ ቦታ ያለበት የጥምቀት በዓል በመርካቶ ነው የሚገኘዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ምዕመናን ጠበል ጸዲቅ አዘጋጅተው ለበዓሉ ታዳሚ ያደሉበት መስተንግዶ፣ በዓሉን የንግድ በዓል ለማድረግ የሚጥሩትን አንዳንድ ነጋዴዎችንም የተከላከሉበት ሥርዓት ማስከበር በመርካቶው የበዓል አከባበር ላይ የታየ አንዱ ውበት ነበር፡፡

Timketal4n.jpgወጣቶች በልዩ ልዩ ቲሸርቶችና ጥቅሶች ደምቀው ቄጠማ በመጎዝጎዝ፣ ርዝመቱ በውል የማይታወቀውን ምንጣፍ በመጠቅለል እና በመዘርጋት ታቦታቱን ያከበሩ ካህናት በባዶ አስፓልት ላይ እንዳይራመዱ የሚፋጠኑትን ወጣቶች ስናይ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ሳናደንቅ አናልፍም፡፡

መቼም ከኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት የወጡ እና በሌላ እምነት ስር ያሉ ወጣቶች ክርስቲያን ባለመሆናቸዉ ወይም በመውጣታቸዉ የሚቆጩበት ቀን ብትኖር የዛሬዋ የጥምቀት በዓል ናት የሚል እምነት አለኝ፡፡

ለወትሮ መርካቶ ውስጥ ሌባ ሲያባርሩ፣ የተጣሉ ሲያስታርቁ፣ ተራ ሲያስከብሩ የምናያቸው ፖሊሶች እንኳን ሥራ አጥተው ለበዓሉ ሞገስ ሆነው እንደማንኛዉም ምዕመን ታዳሚ ሆነው ነበር የዋሉት፡፡ ፓሊስ መሆናቸው እንኳን የሚታወቀው በለበሱት ዩኒፎርም ነው ማለት ይቻላል፡፡

Timketal2n.jpgታዲያ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንፈሳውያን ማኅበራት ይህንን ጊዜ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ጌታችን ወደኔ የመጣውን ወደውጭ አላወጣውም ብሏልና እነዚህን ወጣቶች አሳልፈን እንዳንሰጥ የተቀበልነውን አደራ እናስታዉስ፡፡ ስለዚህ ቢታሰብላቸው፡፡

kidstmaryamtimket5.jpg

የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በጃንሜዳ።

በፈትለወርቅ
 
በከተራ ዕለት
kidstmaryamtimket5.jpgየ2003 ዓ.ም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ዋዜማ የከተራ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። በዋናው በዓል ዋዜማ፥ ከሥርዓተ ቅዳሴው ፍጻሜ በኋላ ታቦታተ ሕጉ ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው በየምዕራፉ በሊቃውንት አባቶች ስብሐተ እግዚአብሔር እየተደረሰ በሰንበት ት/ቤት አባላትና ምዕመናን መዝሙር እየተዘመረ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ አምርተዋል።
 
የበዓሉ አከባበርም ከዓመት ዓመት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቀ፣ እየደመቀና እያሸበረቀ እየሔደ እንደሆነ በግልጽ ይታያል። መንገዱ ሁሉ ጽዱ፥ በሰንደቅ ዓላማና በዓሉን በሚመለከቱ ጥቅሶች አሸብርቋል። ከታቦታቱ ፊት መስቀልና ቅዱሳት ሥዕላት ጥላናkidstmaryamtimket3.jpg መረዋሕ የያዙ ዲያቆናት፥ በሰልፍ ሆነው የሚዘምሩ ጥንግ ድርብና ካባ የለበሱ መዘምራን፥ የደንብ ልብስ የለበሱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፥ ፀአዳ የለበሱ የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን የጌታችን ጥምቀት የሚመለከቱ መዝሙሮችን በመዘመር፥  ወጣቶች ግራና ቀኝ እጅ ለእጅ በመያያዝ ሕዝበ ክርስቲያኑን ወደ ቀኝና ወደ ግራ ከፊትና ከኋላ በማድረግ ያለ ምንም ትርምስና ግርግር የተለያዩ ጥምቀትን የሚመለከቱ መዝሙሮችን በመዘመር፣ ወጣቶችም ፊት በመቅደም ለታቦታቱ ክብር ያዘጋጁትን ምንጣፍ በማንጠፍና ቄጠማ በመጎዝጎዝ የእግዚአብሔር ማደሪያ ለሆኑት ታቦታተ ሕጉና ለአባቶቻችን ካህናት ልዩ ክብር በማሳየት ወደ ባሕረ ጥምቀት/ጃንሜዳ/  ደርሰዋል። 
 
kidstmaryamtimket10.jpg
በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀተ፥ ከየአቅጣጫው የሚመጡ ታቦታት የሚያድሩ ሲሆን፣ ከደቡብ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም፣ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ፣ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያምና መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል፥ ከምሥራቅ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ቀጨኔ ደብረ ስላም መድኀኔዓለምና መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ፥ ከሰሜን ገነተ ኢየሱስና አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም ከምዕራብ መካነ ሕይወት ገብረ መንፈስ ቅዱስ ናቸው።
ታቦታተ ሕጉ ቦታቸውን ይዘው ከቆሙ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በዓሉን አስመልክተው ሲገልፁ« በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ እንደሚከበርና በዓሉን የምናከብር ሁሉ የክርስቶስን ሥራ ሰላምን ለመስበክ እንጅ ሌላ እንዳልሆነ በማሳየትም ጭምር መሆኑን ገልፀው አክለውም ቱሪስቶች ወደዚች አገር የሚመጡት የተሻለውን ለመውሰድና ለመረዳት ተረድቶም ለመፈጸም ነው። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በዓሉን ስታከብር የቱሪስትን ዐይን ለመማረክ ብላ ሳይሆን፥ የእምነትን ትክክለኛ አቋም ይዛ ነው። ይህ ደግሞ የቀደሙ አባቶች ያቆዩልን ሥርዓት የየዘመኑን ትውልድ ሁሉ ያካተተ ነው። ቱሪስቶች የሚመጡት የአገሪቱን ቱሪዝም ገቢ ለመጨመር አስበው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንና የምዕመናኑ ልባዊ ፍቅር ስቧቸው ነው። ስለዚህ ፍቅራችሁ የተስማማ ይሁን፥ እናንተን እያዩ የሰማዩ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት የሚለውን ይዘን በዓሉ በሰላምና በመፈቃቀር እንዲከበር አሳስበዋል።

በዓሉን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ዶ/ር አባ ኀ/ማርያም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሓላፊ «የዛሬው በዓል የከተራ በዓል ነው። ከተራ ስንል በዋዜማው ምዕመናን ተሰብስበው በአንድነት የሚሆኑበት ነው። ከተራ ማለት መሰብሰብ ክብ ሰርቶ በአንድ ላይ ምስጋና ማቅረብን የሚያመለክት ቃል ነው። በአራቱም ማዕዘን ምዕመናን በአንድ ላይ ሆነው በዓሉን ያከብራሉkidstmaryamtimket6.jpg ይህም በዓል መገለጥ/epiphany/ ይባላል። በዕለቱ ደግሞ ነገ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ መገለጥ ሆኗል። የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት ተገልጿል። ክርስቲያኖችም ይህንን በዓል የምናከብረው ለበረከትና ለረድኤት ነው። ምዕመኑ በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራኪና አስደናቂ ነገር ለቤተ ክርስቲያኒቱ እያበረከተ መሆኑንና ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱንም የአገሪቱንም መልካም ገፅታ የሚያንፀባርቅ ይሆናል። አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታውም በጣም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንና በዓሉ በነገው ዕለትም በከፍተኛ ድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።

ከቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ በኋላ የዕለቱ ተረኛ ደብር የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሊቃውንት «ሃሌ ሉያ ወረደ ወልድ…» የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል።

በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የዕለቱ መልዕክትና በዓሉን አስመልክቶ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል። በመጨረሻም ቅዱስነታችው ቃለ ቡራኬና ምዕዳን ሰጥተው ታቦታተ ህጉ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ገብተዋል።

አገልጋዮች ካህናትና ምዕመናንም ሌሊቱን በትምህርተ ወንጌል፣ በማሕሌትና በዝማሬ አሳልፈዋል። የቅዳሴ ሥርዓቱም ከሌሊቱ 6፡00 ጀምሮ እስከ 9፡00 ሰዓት ድረስ በታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ካህናት ተከናውኗል። በዕለቱ ብዙ ምዕመናን ቅዱስ ቁርባን ተቀብለዋል።

በዓለ ጥምቀት
ቅዱስነታቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ መነኮሳት፣ ካህናት ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘው፥ በአራቱም ማዕዘን ከበው የጥምቀተ ባሕሩን የቡራኬ ሥርዓት ያደርሳሉ፡፡ በቅዳሴና በማሕሌት ከታቦታተ ሕጉ ጋር ያደሩት ምዕመናን እንዲሁም ከየቤታቸው በሌሊት ተነስተው የመጡት፥ ባሕረ ጥምቀቱን ከበው ቆመው ሥርዓቱን እየተከታተሉ ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡

በቅዱስነታቸው፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በካህናት በዕለቱ የሚደርሰው ጸሎተ አኮቴት በንባብና በዜማ ተደርሶ ባሕረ ጥምቀቱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ ምዕመናን ፀበል ተረጭተዋል፡፡

በመቀጠልም የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሊቃውንት መዘምራን ዕለቱን በተመለከተ በያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ ‹‹ሃሌ ሉያ ተሣሃልከ እግዚኦ በእንተ ልደቱ ወጥምቀቱ ለክርስቶስ ማዕከለ ባሕር ገብአ ወወጽአ በሰላም›› በማለት ወርበዋል፡፡ መዘምራኑ እንደጨረሱ የእነሱን ፈለግ ተከትለው የወጡት የገዳሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም ‹‹አጥመቆ ዮሐንስ ለኢየሱስ ወገሠሦ እንተ ኢትትገሠሥ ርእሶ›› የሚለውን ወረብ ካቀረቡ በኋላ የአጫብር ወረብ ቀርቧል።

ከዚህ በኋላ ለቃና ዘገሊላ ከሚመለሱት ሁለቱ የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት በቀር ሌሎቹ ታቦታት መስቀል በያዙ ዲያቆናትና ጽንሐሕ በያዙ ካህናት ታጅበው በታላቅ ክብር በእልልታና በዝማሬ በተዘጋጀላቸው መድረክ ቆሙ፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ በዓሉን በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርትና መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

kidstmaryamtimket12.jpg

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕለቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት ውስጥ አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓል ስታከብር በሚማርክና ለሌሎች አርአያ በሚሆን መልኩ እንደሆነና፥ ይህ መተሳሰብ፣ አርአያነትና ፍቅር ሌሎችን እየሳበ የበዓሉን አከባበር ሥርዓት ሊያዩና ሊካፈሉ ከአገር ውጭ የሚመጡት እንግዶቻችን ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። ለእንግዶችም ባስተላለፉት መልዕክት ወደዚህች አገር መጥተው ይህንን በዓል አብረው ማክበራቸው እድለኞች እንደሆኑና ሌሎችም ያላዩት እንዲያዩ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችንም የአባቶቻቸውን ፈለግ ተከትለው የአባቶቻቸውን ሥርዓትና ሕግ ሳይለቁ የበለጠ እንዲሠሩ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡ ቃለ ቡራኬና ምዕዳን ከሰጡ በኋላ ታቦታተ ሕጉ በመጡበት አኳኋን ወደ መንበረ ክብራቸው በካህናት በሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በምዕመናን መዝሙር እየተዘመረ ተጉዘዋል፡፡

kidstmaryam.jpgበመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የተገኙት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በሰጡት ትምህርት «ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማን አጠመቀው ብንባል ማን እንላለን? ዮሐንስ አጠመቀው እንበል? እኔ ግን ቅዱስ ዮሐንስ አምላክን በማጥመቁ የሰዎች ልጆች ሁላችን ነው ያጥመቅነው ብየ አምናለሁ። ኃይሌ ገ/ሥላሴ ሩጫ ቢያሸንፍ ኢትዮጵያ አሸነፈች እንደሚባለው፣ ሁሉም እንደሚደሰተው። «ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ» እንደተባለው ሰማያዊው አምላክ እግዚአብሔር ወልድ በመሬታዊው በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ፈጣሪን የምናጠምቅ ሆነን አይደለም ምን ያህል እንደወደደን ያሳያል እንጂ። ብዙ ሰማያውያን ሠራዊት ነበሩ፣ በእነርሱ እጅ መጠመቅ ይችል ነበር፤ በባሕርይ አባቱ መጠመቅ ይችል ነበር፤ በባሕርይ ሕይወቱም መጠመቅ ይችል ነበር። ፈጣሪ አምላካችን በሰው እጅ ተጠመቀ እኮ? በእውነት ምን አይነት ፍቅር ነው? ምንስ አይነት መውደድ ነው? እኛም ፈጣሪ አምላክን ለማጥመቅ በቃን እኮ!» ብለዋል።

ታቦት እንተ ውስቴታ ኦሪት እንተ ውስቴታ….እልልልልልልልkidstmaryamtimket4.jpg

tmket.jpg

«እስመ ከመዝ ተድላ ለነ ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኲሎ ጽድቀ»

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ


tmket.jpgየጎንደር መንበረ መንግሥት መድኅኔዓለም ደብር አስተዳዳሪና የአራቱ ጉባኤያት /የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የሊቃውንትና የመጻሕፍተ መነኮሳት/ የጉባኤ መምህር ከሆኑት ከሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ጋር የጥምቀትን በዓል አስመልክተን በ09/05/03 ዓ.ም አጭር ቃለ ምልልስ በስልክ አድርገናል፡፡ ለሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ከፍተኛ ምስጋናችንን እያቀረብን ለአንባቢዎቻችን የታላቁን ሊቅ ቃለ ምልልስ በማቅረብ እንኳን አደረሳችሁ እንላለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡ 

አማርኛ መካነ ድር፡- ሊቀ ሊቃውንት እንኳን አደረስዎት?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- እንኳን አብሮ አደረሰን።
 
አማርኛ መካነ ድር፡- ጤናዎት እንዴት ነው?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- ደህና ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ።

timket3.jpgአማርኛ መካነ ድር፡- የጥምቀትን በዓል ለምን እናከብራለን? ለክርስቲያኖች ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- የጥምቀት በዓል መነሻው የጌታችን የመድኅኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ነው፡፡ ጌታችን ለምን ተጠመቀ ሲባል፣ መነሻው የአዳምና የሔዋን ድኅነት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ተፈጥረው ከሥላሴ ልጅነትን ተቀብለው ዕፀ በለስን እንዳይበሉ ታዘው ለ7 ዓመታት ያህል የተሰጣቸውን አደራ ጠብቀው ከዕፀ በለስም ተቆጥበው ከቆዩ በኋላ በ7ኛው ዓመት ሰይጣን በእባብ አማካኝነት አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በስሕተት እንዲበሉ አድርጎ፣ ዕፀ በለስን በመብላታቸው ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነመ እሳት ተፈርዶባቸው 55ዐዐ ዘመን በመከራ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አዳምና ሔዋን ዕፀ በለሱን ከበሉ በኋላ እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን በመረዳት ንስሐ ገብተው ንስሐቸውን ሲጨርሱ እግዚአብሐር ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ ተስፋቸውም በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ፡፡ 55ዐዐ ዘመን ሲፈፀም ከልጅ ልጀህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ተስፋ ስለሰጣቸው ይሄን ተስፋ ለመፈፀም መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም በመጋቢት 29 ቀን ተጸንሶ ታኅሣሥ 29 ቀን ተወልዶ 3ዐ ዓመት ሲሞላው በ3ዐ ዓመቱ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ለልደቱም ለጥምቀቱ ነቢያትን እያስነሳ ትንቢት አናግሯል፡፡ የተነገረው ትንቢትና የተቆጠረው ሱባኤ ሲፈፀም በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቋል፡፡ ሲጠመቅም ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠው ተስፋና ቃልኪዳን ተፈጽሟል፡፡

የአዳምና የሔዋን የእዳ ደብዳቤያቸው የኃጢአት ሰነዳቸው ተፍቋል፡፡ ስለዚህ የመድኀኔዓለም ክርስቶስ መጠመቅ ለዓለም በጠቅላላው ሕይወት መድኀኒት በመሆኑ የጥምቀት በዓል ከመጀመሪያው ጀመሮ እስከ አሁን ድረስ እየተከበረ ከዚህ ደርሷል፡፡ የጥምቀት በዮርደኖስ አዳም የዲያብሎስ የወንድ ተገዥ ሔዋን የዲያብሎስ የሴት አገልጋይ ብሎ ጽፎ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን የዕዳ ደብዳቤ ክርስቶስ ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደሰውነቱ ረግጦ አጥፍቶልናል፡፡ በሲኦል ያስቀመጠሙንም በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ አጥፍቶልናልና ጥምቀት ለክርስቲያኖች ያለው አስተዋጽኦና ፋይዳ ይሄን ይመስላል፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡- የጥምቀት በዓል አከባበር እንዴት ተጀመረ? ጎንደር ላይ በልዩ ሁኔታ ይከበራል በዚህ መልክ መከበር የተጀመረውስ መቼ ነው?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ይዘቱና ክብሩ አንድ ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ሲጀመርም አንድ ላይ ነው የተጀመረው፡፡ ሃገራችን አንድ ጊዜ ነው ሃይማኖትን ጥምቀትን የተቀበለች፡፡ ስለዚህ አሁንም በገጠሩም በከተማም ታቦታቱ ወርደው በየወንዙ አጠገብ በድንኳን አድረው፣ የሚጸለየው ጸሎት፣ የሚቀደሰው ቅዳሴ የሚባረከው ባሕረ ጥምቀት ሁሉ አንድ ነው እና ጎንደርም ከኢትዮጵያ አንዷ ስለሆነች፣ የጥምቀቱን በዓል የጀመረችው በሰላማ ከሣቴ ብርሃን በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ስለሆነ ከዚያ ጋር ልዩነት የለውም፡፡

እንግዲህ የጎንደር ጥምቀት ልዩነት አለው የሚባለውና በምን ጊዜ ተጀመረ ለሚለው ጥምቀተ ባሕሩ የጎንደር ከሌሎቹ ሁሉ ለየት ያለ ነው፡፡ ቦታው ማለት ነው። አፄ ፋሲለደስ ያሠሩት የጥምቀተ ባሕር መቅደስ አለ፡፡ ከቤተ መቅደሱ ግርጌ ደግሞ ባሕረ ጥምቀቱ አለ፡፡ ከአፄ ፋሲል ጀምሮ በዓሉ በዚያ ስለሚከበር ታቦታት እየወረዱ፥ ከቤተ መቅደሱ አድረው፥ እዚያው ተቀድሶ፥ ማኅሌቱም ተቁሞ ፤ ባሕሩም ደግሞ ሌሎቹ ሀገሮች ከሚጠቀሙበት ለየት ያለ ስፋትና ጥራት ያለው ሁልጊዜ እንደጸበል ከአንድ ቦታ ታቦታቱ ወርደው ማደራቸው በዓሉን በጎንደር ለየት ያደርገዋል፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡-
በበዓሉ አከባበር የማኅሌትና የቅደሴ ሥርዓቱ አንዴት ነው? ከከተራ ጀምሮ?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- ከእነ አፄ ፋሲል በፊት ቀሃ ኢየሱስ ቀዳሚ ደብር ነበር፡፡ የኢየሱስ ታቦት ፥ ቀሃ ወንዝ አለ ከዚያ ይወርዳል፡፡ ዛሬ የራሱ የኢየሱስ ታቦት ቤተመቅደስ ከተሠራበት ቦታ ድንኳን ተተክሎ ታቦቱ ከዚያ አድሮ ባሕረ ጥመቀቱ ቀሃ ወንዝ ነበር የሚባረከው፡፡ ኋላ ግን ከአፄ ፋሲለደስ ንግሥና በኋላ 44ቱ ታቦታት ከዚያ ይወርዳሉ፡፡
timket2.jpgድርቡሽ /Mahdists of sudan/ የጎንደርን አብያተ ክርስቲያናትን ካቃጠለ በኋላ ግን 8 ታቦታት ብቻ ይወርዳሉ፡፡ እነዚህም-
1.    መንበረ መንግሥት መድኀኔዓለም
2.    ደብረ ነገት አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል
3.    ደብረ ጽባሕ እልፍኝ ጊዮርጊስ
4.    ደብረ ሰላም ፊት ሚካኤል
5.    ደብረ ብርሃን አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት እነዚህ ከመሐል ከተማው ይወርዳሉ፡፡ ከታች ከባሕረ ጥምቀቱ አጠገብ ደግሞ
6.    የቀሃ ኢየሱስ
7.    የቅዱስ ፋሲለደስ
8.    የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የላይኛዎቹን ጠብቀው አብረው ይገባሉ፡፡

ከዚያ በአንድ ላይ ማኅሌት ተቁሞ ያድራል፡፡ ማኅሌቱ ሲፈፀም የቅዳሴ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ የባሕረ ጥምቀቱ የቡራኬ ሥርዓትም ይካሄዳል፡፡ ከዚያ ታቦታቱ ወጥተው ሃዲጎ ተስአ ወተስአተ ነገድ የሚለው ማኅሌታዊ ዝማሬ ተዘምሮ ሁለቱ የቅ/ ሚካኤል ታቦታት ከዚያው ይቆያሉ ሌሎቹ ግን በ7 ምዕራፍ ታቦታቱ እየቆሙ የማኅሌቱ ሥርዓት የዝማሬው ሥርዓት እየተካሄደ ወደየ መንበረ ክብራቸው ይመለሳሉ፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ቤ/ክ አከባበር የማኅሌት ሥርዓቱ 7 ምዕራፍ አለው፡፡ ለእያንዳንዱ ምዕራፍም የተወሰነ ቀለም አለ፡፡

ጎንደርን ግን ለየት የሚያደርገው ማኅሌቱ የተደረሰው ጎንደር ላይ ነው ዛሬም ማስመስከሪያው ጎንደር በአታ ለማርያም ነው፡፡ የአቋቋሙ ምስክር መሆኑ የማኅሌቱ ምንጭ አጠቃላይ አቋቋሙ የተደረሰው እዚህ ስለሆነ ለየት ያደርገዋል፡፡ አንግዲህ የትርጓሜ መጻሕፍትና የአቋቋም ትምህርት መነሻው ጎንደር ስለሆነ ለየት ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዕለቱ በሥርዓተ ቅደሴው ብዙ ምእመናን በቅዱስ ቁርባን ይሳተፋሉ፡፡

llEzraHaddis.jpg

አማርኛ መካነ ድር፡- የዘንድሮው የጥምቀት ክብረ በዓል ብዙ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል በሀገረ ስብከቱም ሆነ በእናንተ ጉባኤ ቤት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት አንዲሁም ቤተክርስቲያንን ለማስተዋወቅ ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡-ይህ ነገር ቀደም ብሎ ታስቦበት ኮሚቴ ተዘጋጅቶ፤ ከሁለት ሳምንት ጀምሮ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር በአለባበስም ሆነ አንግዳ በመቀበል ጥንታዊነታችን ኢትዮጵያዊነታችን ለማስመስከር ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በስብከተ ወንጌልም ማንኛውም ሰው ወደ ንስሐ እንዲመለስ በመናፍቅነትም ወደ ሌላ ሃይማኖት የሄደ ካለ ቤተክርስቲያኑ ተመልሶ የቤተክርስቲያን ልጅ እንዲሆን ለሥጋ ወደሙ አንዲበቃ ቅስቀሳ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁንም ምግባር ፣ ትሕትና፣ ፍቅር፣ እንግዳ መቀበል ብዙ ሰዎችን ያስተምራልና ለዚህ ሁሉ ሰባክያን ብቻ ሳይሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ በእነዚህ ምግባራት ብዙ ሰዎችን እንዲስብ እየተደረገ ነው፡፡ ዛሬም በአጋጣሚ ክቡር ፕሬዜዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከሚኒስትሮች ጋር ገብተዋል ጥሩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ጥምቀተ ባሕሩ ከሚከናወንበት ቦታ ላይ ሰባት ጎጆዎች ተዘጋጅተው የቤተክርስቲያናችን የአብነት ትምህርትን /ከፊደል ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ያሉት የትምህርት ሥርዓቶች/ የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ለክቡር ፕሬዚዳንቱና ለእንግዶች ገለጻ ተደርጓል፡፡ ይኽም ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት ይቀጥላል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳንም የተዘጋጀ ኤግዚቢሽን አለ፡፡ እርሱም በእንግዶች ተጎብኝቷል፡፡ የሀገራችን ገጽታ በዘመነ አበው፣ በዘመነ ኦሪት፣ እንዲሁም በዘመነ ወንጌል ከፋፍሎ የሚያሳይ ሲሆን ቤተክርስቲያኗ በሥነ ጽሑፍ፣ በመጻሕፍት፣በሥነ ጥበብ ያበረከተችውንም ሀብታት ይዳስሳል፡፡

በዘመነ ኦሪት መሥዋዕት የተሠዋባቸው ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት በኤግዚቢሽን ቀርበው ገለጻ እየተደረገባቸው የሀገሪቱን ቀዳሚነትና ጥንታዊነት እያስተዋወቀም ይገኛል፡፡

 አማርኛ መካነ ድር፡- በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- «እስመ ከመዝ ተድላ ለነ ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኲሎ ጽድቀ» ነው ያለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ከገሊላ መጥቶ ወደ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ሲቀርብ ዮሐንስ «ከሎ ወዐበዮ፤ አይሆንም እኔ ከአንተ እጠመቃለሁ እንጂ እኔ አንተን እንደምን አጠምቃለሁ፡፡» ሲለው ይህ ለእኔ እና ለአንተ ታላቅ ደስታችን ነው፡፡ የተነገረውን ትንቢትም ልንፈጽም ይገባናል፡፡  እኔ በአንተ እጅ ተጠምቄ ትሕትናዬ፤ አንተ እኔን አጥምቀህ ክብርህ ልዕልናህ ይገለጣል፤ ይህ ደስታችን ነው፡፡ ብሎ የአብ የመንፈስ ቅዱስን ከእርሱ ጋራ አንድ ባሕርይ አንድ ህልውና መሆናቸውን እንደገናም የእኛን ሥጋ በመዋሐዱ የእኛን ደስታ ለእርሱ የእርሱን ደስታ ለእኛ ሰጥቶ በማቴ.3.13 እንደተናገረው አሁንም ይህ የጥምቀት በዓላችን የእዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበት፣ የተደመሰሰበት በዓል ስለሆነ በ40 ቀንና በ80 ቀን ተጠምቀው በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ የተባሉ ሁሉ የጥምቀት በዓልን ሲያከብሩ የራሳቸው ነጻነት ልጅነት የተመሠረተበት መሆኑን በመረዳት በደስታና በፍቅር ማክበር ይገባል፡፡

ይህ በዓል የነጻነት በዓል፣ የኃጢአት የቁራኝነት የፍዳ ደብዳቤ የጠፋበት ስለሆነ፣ ዛሬም ማንኛውም ሰው ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ተመልሶ ከፍዳ መርገም ወደ በረከት ተመልሶ ለሥጋው ለደሙ በቅቶ ፈጣሪው ጋር ተገናኝቶ፣ በዓሉን ካከበረ በዚህ ዓለም ያከበረውን በዓል ኋላም በመንግሥተ ሰማያት ከመላእክት ጋር ለማክበር ዕድሉ ስለተሰጠው ሰው ሁሉ በዚህ በዓል ሊጠቀምበት ይገባል፡፡

እንግዲህ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን በውጭም በሀገር ውስጥም ለሚኖሩ ሁሉ የጥምቀት በዓል የሰላም የበረከት የፍቅር በዓል እንዲሆንልን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን፡፡ የሰላም ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ተገኝቶ በዓሉን በሰላም አስጀምሮ በሰላም እንዲያስፈጽመን ዛሬ በዚህ ዓመት በዓሉን ለማክበር የፈቀደልን ከርሞ በሰላም ደርሰን በዓሉን ለማክበር እንዲያበቃን የታመሙትን እንዲፈውስልን፣ የወጡትን በሰላም እንዲመልስልን ሀገራችንን በምሕረቱ፣ በይቅርታው እንዲጎበኝልን ዓለምን በጠቅላላው በዓይነ ምሕረቱ ተመልክቶ ለዓለም ምሕረቱን እንዲልክልን የአምላካችን ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡- እግዚአብሔር ይስጥልን በዕድሜ በጸጋ ይጠብቅልን፡፡

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡– አሜን፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ተረት…………ተረት (ለህጻናት)

      ልጆች ዛሬ አንድ ተረት ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ ፀሐይና ነፋስ ረጅም መንገድ አብረው ጉዞ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ጓደኛሞች አብረው እየሔዱ ጨዋታ አንስተው ሲያወሩ ነፋስ ፀሐይን አንድ ጥያቄ ጠየቃት «ሰዎች የምትፈልጊውን ነገር እንዲያደርጉልሽ የምታደርጊያቸው በምንድን ነው?» ሲል ነፋስ ጠየቃት ፀሐይም የነፋስን ጥያቄ ሰማችና «እኔማ ከሰዎች የምፈልገውን መጠየቅ ብፈልግ በጣም ቢቆጡ፣ ቢሳደቡ እንኳን ቀስ አድርጌ በትህትና በፍቅር ረጋ ብዬ እጠብቃቸውና የምፈልገውን እንዲሰጡኝ /እንዲያደርጉልኝ/ አደርጋለሁ» አለችው፡፡ ነፋስ ወዲያውኑ ቀበል አደረገና «በጣም ተሳሳትሽ የምን መለማመጥ? የምትፈልጊውን ለማግኘት በጉልበት መጠቀም ነው እንጂ» አለ፡፡ «ፀሐይ እንደሱማ አይቻልም» አለች፡፡

                    

      ነፋስም እኔ እችላለሁ ተመልከች «ያ» መንገድ ላይ የሚጓዘውን ሰውዬ በደቂቃ ውስጥ ልብሱን በየተራ ብትንትን አድርጌ አስወልቀዋለሁ» ሲል ፎከረ፡፡ ነፋስም በአንዴ ኃይሉን አነሣና የሰውየውን ልብስ ለማስወለቅ መታገል ጀመረ፡፡ ይኼኔ ሰውየው ልብሱን እንዳይወስድበት በኃይል ልብሱን ጭብጥ አድርጎ አስጣለ /አዳነ/፡፡ ነፋስም ሰውየው ስላሸነፈው ተናደደና አዋራ አስነሥቶ ሰውየው ዐይን ላይ በትኖበት ጥሎት ሔደ፡፡ ፀሐይም በመገረም እየተመለተችው እሺ አያ ንፋስ አሸንፈህ የፈለከውን አገኘህ)» ብላ ጠየቀችው ነፋስም «ይገርምሻል ልብሱን አልለቅም ሲለኝ አዋራ አንሥቼ ዐይኑ ላይ ጨመርኩበት» አላት፡፡

      ፀሐይ ሳቅ እያለች «አይ አያ ነፋስ፡፡ በትግል አልሆን ሲልህ በጉልበት ለመጠቀም ሞከርክ? ግን እንደዚህ አይደለም እኔን አስተውለህ ተመልከተኝ» አለችውና ልታሳየው ወደ ሰውየው ሔደች፡፡

      ሰፊ ከሆነው ከሰማይ መቀመጫዋ ብድግ አለችና ሰውየውን ገና ጠዋት ከሚመጣው ሙቀቷ ሰላምታ አቀረበችለት ሰውየውም የፀሐይን ሙሉ ፈገግታና ትህትና በጣም ደስ አሰኝቶት ከሙቀቷ ስር ቁጭ አለ፡፡ እንደገና ከሰዓት በኋላ መንገድ ሲሔድ ሰላም አለችውና ከሙቀቱ ጭምር አደረገች፡፡ «በጣም ስለሞቀህ ለምን ኮትህን አታወልቅም?» ስትል ጠየቀችው ደስ ብሎት ምንም ሳይከፋው ፈጠን ብሎ «እሺ» አለና ውልቅ አድርጎ ያዘው፣ አሁንም ሙቀቷን ጨመረችና «ሸሚዙን ብታወልቀው» አለችው አወለቀው ሙቀቷ በጣም እየጨመረ መጣ፡፡ «ለምን በቀዝቃዛ ውኃ አትታጠብም ስትል ቀስ አድርጋ ጠየቀችው በጣም ደስ ይለኛል አለና ሰውነቱን በቀዝቃዛ ውኃ አስነከረችው፡፡»

      ይሔኔ ነፋስ በጣም ደነቀው፡፡ በራሱ ኃይለኝነት በጣም አፈረ፡፡ ሰዎች ነፋስን ብርድ በመጣ ቁጥር የበለጠ እየፈሩት ወደ ሙቀት እንደሚሸሹት አወቀ፡፡ ፀሐይ ግን በትህትና በፍቅር ሰዎችን ስለምትቀርብ ወደ ቅዝቃዜ ብትወስዳቸው እንኳን ቅር አይላቸውም፡፡ በደስታ እንደሚከተሏት ተመለከተ፡፡ የፀሐይን ጥሩ ፀባይ በጣም አደነቀ፡፡

       አዎን ልጆች ከሰፈር አብሮ አደጎቻችሁ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ እንዲሁም ከወላጆቻችሁ ጋር አብራችሁ ስትኖሩ የምትፈልጉትን ለማግኘት በመሳደብ፣ በኃይል፣ በመማታት አይደለም፡፡ ነፋስን አይታችኋል አይደል? ክፉና ኃይለኛ መሆን ሰዎች እንዲርቁን እንዲጠሉን አዋቂዎችም እንዲረግሙን ያደርገናል፡፡ እና ልጆች ልክ እንደ ፀሐይ ጥሩና ደግ ትሁትና ታዛዥ ሆናችሁ ሰዎትን ብትቀርቡ ሁሉም ይወዳችኋል፣ ይመርቃችኋል፡፡ እሺ ልጆች? ደኅና ሁኑ ልጆች ደኅና ሁኑ፡፡

mkradio.jpg

የጥምቀት በዓል የሬዲዮ መርሐ ግብር

mkradio.jpg