በአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃግብሩ የመጀመሪያ ቀን ከ175ዐ በላይ አልባሳት ተሰበሰበ

                                                                   በፈትለወርቅ ደስታ
 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን «ሁለት ልብሶች ያሉት….» በሚል ስያሜ የሚከናወነው የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በይፋ ተከፈተ በመጀመሪያው ዕለትም ከ175ዐ በላይ አልባሳት  ተሰብስቧል፡፡

ካህናት አባቶች የማኅበሩ አባላትና ምዕመናን በተገኙበት መርሃግብር በጸሎት የከፈቱት ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ሙሉጌታ «ሁለት ልብሶች ያሉት አንዱን ለሌላው ይስጥ» በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3÷11 » ላይ ያለውን የወንጌል ቃል መነሻ በማድረግ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም በማኅበሩ አባላት የመዝሙር ክፍልና በአባላት ህፃናት ልጆች መዝሙር ቀርቦ የቅዱሳን መካናት ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት በወ/ሮ ዓለምፀሀይ መሠረት ስለመርሃግብሩ ዓላማና አስፈላጊነት ገለፃ ተደርጓል፡፡

በጉባዔው ላይ የተሳተፉት ምዕመናን ስለ ጉባዔው ያላቸውን አስተያየት ሲገልፁ «እግዚአብሔር ፍጥረቱን ተጠቅሞ ማንኛውንም ሥራ ይሠራል ማህበሩም በዚህ ዘርፍ ብዙ እየሠራ ነው፡፡» በየገዳማቱ ያሉትንም እንዲህ ማሰቡ በጣም ጥሩና ይበል የሚያሰኝ ነው አሁን ያየሁት እነሱ በልብስ ተራቁተዋል እኛ ግን በመንፈስ ተራቁተናል ጅምሩ ጥሩ ነው በዚሁ ይቀጥል፤ ዓላማው ያስማማናል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት» ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በማኅበሩ ሰብሳቢ በቀሲሲ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዮም የመዝጊያ ንግግርና በመርሃግብሩ ለሚሳተፉ ምዕመናን ምሥጋና አቅርበሙ በጸሎት ተዘግቷል ጠዋት የጀመረው የአልባሳት ማሰባሰብ መርሃግብር ቀጥሎ በዕለቱ ከምዕመናን ከ1750 በላይ የወንዶች፣ የሴቶችና የህፃናት አልባሳት ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡

                               
ወስብሐት ለእግዚአብሔር