tmket.jpg

«እስመ ከመዝ ተድላ ለነ ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኲሎ ጽድቀ»

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ


tmket.jpgየጎንደር መንበረ መንግሥት መድኅኔዓለም ደብር አስተዳዳሪና የአራቱ ጉባኤያት /የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የሊቃውንትና የመጻሕፍተ መነኮሳት/ የጉባኤ መምህር ከሆኑት ከሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ጋር የጥምቀትን በዓል አስመልክተን በ09/05/03 ዓ.ም አጭር ቃለ ምልልስ በስልክ አድርገናል፡፡ ለሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ከፍተኛ ምስጋናችንን እያቀረብን ለአንባቢዎቻችን የታላቁን ሊቅ ቃለ ምልልስ በማቅረብ እንኳን አደረሳችሁ እንላለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡ 

አማርኛ መካነ ድር፡- ሊቀ ሊቃውንት እንኳን አደረስዎት?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- እንኳን አብሮ አደረሰን።
 
አማርኛ መካነ ድር፡- ጤናዎት እንዴት ነው?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- ደህና ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ።

timket3.jpgአማርኛ መካነ ድር፡- የጥምቀትን በዓል ለምን እናከብራለን? ለክርስቲያኖች ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- የጥምቀት በዓል መነሻው የጌታችን የመድኅኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ነው፡፡ ጌታችን ለምን ተጠመቀ ሲባል፣ መነሻው የአዳምና የሔዋን ድኅነት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ተፈጥረው ከሥላሴ ልጅነትን ተቀብለው ዕፀ በለስን እንዳይበሉ ታዘው ለ7 ዓመታት ያህል የተሰጣቸውን አደራ ጠብቀው ከዕፀ በለስም ተቆጥበው ከቆዩ በኋላ በ7ኛው ዓመት ሰይጣን በእባብ አማካኝነት አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በስሕተት እንዲበሉ አድርጎ፣ ዕፀ በለስን በመብላታቸው ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነመ እሳት ተፈርዶባቸው 55ዐዐ ዘመን በመከራ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አዳምና ሔዋን ዕፀ በለሱን ከበሉ በኋላ እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን በመረዳት ንስሐ ገብተው ንስሐቸውን ሲጨርሱ እግዚአብሐር ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ ተስፋቸውም በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ፡፡ 55ዐዐ ዘመን ሲፈፀም ከልጅ ልጀህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ተስፋ ስለሰጣቸው ይሄን ተስፋ ለመፈፀም መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም በመጋቢት 29 ቀን ተጸንሶ ታኅሣሥ 29 ቀን ተወልዶ 3ዐ ዓመት ሲሞላው በ3ዐ ዓመቱ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ለልደቱም ለጥምቀቱ ነቢያትን እያስነሳ ትንቢት አናግሯል፡፡ የተነገረው ትንቢትና የተቆጠረው ሱባኤ ሲፈፀም በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቋል፡፡ ሲጠመቅም ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠው ተስፋና ቃልኪዳን ተፈጽሟል፡፡

የአዳምና የሔዋን የእዳ ደብዳቤያቸው የኃጢአት ሰነዳቸው ተፍቋል፡፡ ስለዚህ የመድኀኔዓለም ክርስቶስ መጠመቅ ለዓለም በጠቅላላው ሕይወት መድኀኒት በመሆኑ የጥምቀት በዓል ከመጀመሪያው ጀመሮ እስከ አሁን ድረስ እየተከበረ ከዚህ ደርሷል፡፡ የጥምቀት በዮርደኖስ አዳም የዲያብሎስ የወንድ ተገዥ ሔዋን የዲያብሎስ የሴት አገልጋይ ብሎ ጽፎ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን የዕዳ ደብዳቤ ክርስቶስ ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደሰውነቱ ረግጦ አጥፍቶልናል፡፡ በሲኦል ያስቀመጠሙንም በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ አጥፍቶልናልና ጥምቀት ለክርስቲያኖች ያለው አስተዋጽኦና ፋይዳ ይሄን ይመስላል፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡- የጥምቀት በዓል አከባበር እንዴት ተጀመረ? ጎንደር ላይ በልዩ ሁኔታ ይከበራል በዚህ መልክ መከበር የተጀመረውስ መቼ ነው?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ይዘቱና ክብሩ አንድ ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ሲጀመርም አንድ ላይ ነው የተጀመረው፡፡ ሃገራችን አንድ ጊዜ ነው ሃይማኖትን ጥምቀትን የተቀበለች፡፡ ስለዚህ አሁንም በገጠሩም በከተማም ታቦታቱ ወርደው በየወንዙ አጠገብ በድንኳን አድረው፣ የሚጸለየው ጸሎት፣ የሚቀደሰው ቅዳሴ የሚባረከው ባሕረ ጥምቀት ሁሉ አንድ ነው እና ጎንደርም ከኢትዮጵያ አንዷ ስለሆነች፣ የጥምቀቱን በዓል የጀመረችው በሰላማ ከሣቴ ብርሃን በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ስለሆነ ከዚያ ጋር ልዩነት የለውም፡፡

እንግዲህ የጎንደር ጥምቀት ልዩነት አለው የሚባለውና በምን ጊዜ ተጀመረ ለሚለው ጥምቀተ ባሕሩ የጎንደር ከሌሎቹ ሁሉ ለየት ያለ ነው፡፡ ቦታው ማለት ነው። አፄ ፋሲለደስ ያሠሩት የጥምቀተ ባሕር መቅደስ አለ፡፡ ከቤተ መቅደሱ ግርጌ ደግሞ ባሕረ ጥምቀቱ አለ፡፡ ከአፄ ፋሲል ጀምሮ በዓሉ በዚያ ስለሚከበር ታቦታት እየወረዱ፥ ከቤተ መቅደሱ አድረው፥ እዚያው ተቀድሶ፥ ማኅሌቱም ተቁሞ ፤ ባሕሩም ደግሞ ሌሎቹ ሀገሮች ከሚጠቀሙበት ለየት ያለ ስፋትና ጥራት ያለው ሁልጊዜ እንደጸበል ከአንድ ቦታ ታቦታቱ ወርደው ማደራቸው በዓሉን በጎንደር ለየት ያደርገዋል፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡-
በበዓሉ አከባበር የማኅሌትና የቅደሴ ሥርዓቱ አንዴት ነው? ከከተራ ጀምሮ?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- ከእነ አፄ ፋሲል በፊት ቀሃ ኢየሱስ ቀዳሚ ደብር ነበር፡፡ የኢየሱስ ታቦት ፥ ቀሃ ወንዝ አለ ከዚያ ይወርዳል፡፡ ዛሬ የራሱ የኢየሱስ ታቦት ቤተመቅደስ ከተሠራበት ቦታ ድንኳን ተተክሎ ታቦቱ ከዚያ አድሮ ባሕረ ጥመቀቱ ቀሃ ወንዝ ነበር የሚባረከው፡፡ ኋላ ግን ከአፄ ፋሲለደስ ንግሥና በኋላ 44ቱ ታቦታት ከዚያ ይወርዳሉ፡፡
timket2.jpgድርቡሽ /Mahdists of sudan/ የጎንደርን አብያተ ክርስቲያናትን ካቃጠለ በኋላ ግን 8 ታቦታት ብቻ ይወርዳሉ፡፡ እነዚህም-
1.    መንበረ መንግሥት መድኀኔዓለም
2.    ደብረ ነገት አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል
3.    ደብረ ጽባሕ እልፍኝ ጊዮርጊስ
4.    ደብረ ሰላም ፊት ሚካኤል
5.    ደብረ ብርሃን አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት እነዚህ ከመሐል ከተማው ይወርዳሉ፡፡ ከታች ከባሕረ ጥምቀቱ አጠገብ ደግሞ
6.    የቀሃ ኢየሱስ
7.    የቅዱስ ፋሲለደስ
8.    የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የላይኛዎቹን ጠብቀው አብረው ይገባሉ፡፡

ከዚያ በአንድ ላይ ማኅሌት ተቁሞ ያድራል፡፡ ማኅሌቱ ሲፈፀም የቅዳሴ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ የባሕረ ጥምቀቱ የቡራኬ ሥርዓትም ይካሄዳል፡፡ ከዚያ ታቦታቱ ወጥተው ሃዲጎ ተስአ ወተስአተ ነገድ የሚለው ማኅሌታዊ ዝማሬ ተዘምሮ ሁለቱ የቅ/ ሚካኤል ታቦታት ከዚያው ይቆያሉ ሌሎቹ ግን በ7 ምዕራፍ ታቦታቱ እየቆሙ የማኅሌቱ ሥርዓት የዝማሬው ሥርዓት እየተካሄደ ወደየ መንበረ ክብራቸው ይመለሳሉ፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ቤ/ክ አከባበር የማኅሌት ሥርዓቱ 7 ምዕራፍ አለው፡፡ ለእያንዳንዱ ምዕራፍም የተወሰነ ቀለም አለ፡፡

ጎንደርን ግን ለየት የሚያደርገው ማኅሌቱ የተደረሰው ጎንደር ላይ ነው ዛሬም ማስመስከሪያው ጎንደር በአታ ለማርያም ነው፡፡ የአቋቋሙ ምስክር መሆኑ የማኅሌቱ ምንጭ አጠቃላይ አቋቋሙ የተደረሰው እዚህ ስለሆነ ለየት ያደርገዋል፡፡ አንግዲህ የትርጓሜ መጻሕፍትና የአቋቋም ትምህርት መነሻው ጎንደር ስለሆነ ለየት ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዕለቱ በሥርዓተ ቅደሴው ብዙ ምእመናን በቅዱስ ቁርባን ይሳተፋሉ፡፡

llEzraHaddis.jpg

አማርኛ መካነ ድር፡- የዘንድሮው የጥምቀት ክብረ በዓል ብዙ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል በሀገረ ስብከቱም ሆነ በእናንተ ጉባኤ ቤት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት አንዲሁም ቤተክርስቲያንን ለማስተዋወቅ ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡-ይህ ነገር ቀደም ብሎ ታስቦበት ኮሚቴ ተዘጋጅቶ፤ ከሁለት ሳምንት ጀምሮ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር በአለባበስም ሆነ አንግዳ በመቀበል ጥንታዊነታችን ኢትዮጵያዊነታችን ለማስመስከር ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በስብከተ ወንጌልም ማንኛውም ሰው ወደ ንስሐ እንዲመለስ በመናፍቅነትም ወደ ሌላ ሃይማኖት የሄደ ካለ ቤተክርስቲያኑ ተመልሶ የቤተክርስቲያን ልጅ እንዲሆን ለሥጋ ወደሙ አንዲበቃ ቅስቀሳ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁንም ምግባር ፣ ትሕትና፣ ፍቅር፣ እንግዳ መቀበል ብዙ ሰዎችን ያስተምራልና ለዚህ ሁሉ ሰባክያን ብቻ ሳይሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ በእነዚህ ምግባራት ብዙ ሰዎችን እንዲስብ እየተደረገ ነው፡፡ ዛሬም በአጋጣሚ ክቡር ፕሬዜዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከሚኒስትሮች ጋር ገብተዋል ጥሩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ጥምቀተ ባሕሩ ከሚከናወንበት ቦታ ላይ ሰባት ጎጆዎች ተዘጋጅተው የቤተክርስቲያናችን የአብነት ትምህርትን /ከፊደል ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ያሉት የትምህርት ሥርዓቶች/ የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ለክቡር ፕሬዚዳንቱና ለእንግዶች ገለጻ ተደርጓል፡፡ ይኽም ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት ይቀጥላል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳንም የተዘጋጀ ኤግዚቢሽን አለ፡፡ እርሱም በእንግዶች ተጎብኝቷል፡፡ የሀገራችን ገጽታ በዘመነ አበው፣ በዘመነ ኦሪት፣ እንዲሁም በዘመነ ወንጌል ከፋፍሎ የሚያሳይ ሲሆን ቤተክርስቲያኗ በሥነ ጽሑፍ፣ በመጻሕፍት፣በሥነ ጥበብ ያበረከተችውንም ሀብታት ይዳስሳል፡፡

በዘመነ ኦሪት መሥዋዕት የተሠዋባቸው ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት በኤግዚቢሽን ቀርበው ገለጻ እየተደረገባቸው የሀገሪቱን ቀዳሚነትና ጥንታዊነት እያስተዋወቀም ይገኛል፡፡

 አማርኛ መካነ ድር፡- በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡- «እስመ ከመዝ ተድላ ለነ ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኲሎ ጽድቀ» ነው ያለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ከገሊላ መጥቶ ወደ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ሲቀርብ ዮሐንስ «ከሎ ወዐበዮ፤ አይሆንም እኔ ከአንተ እጠመቃለሁ እንጂ እኔ አንተን እንደምን አጠምቃለሁ፡፡» ሲለው ይህ ለእኔ እና ለአንተ ታላቅ ደስታችን ነው፡፡ የተነገረውን ትንቢትም ልንፈጽም ይገባናል፡፡  እኔ በአንተ እጅ ተጠምቄ ትሕትናዬ፤ አንተ እኔን አጥምቀህ ክብርህ ልዕልናህ ይገለጣል፤ ይህ ደስታችን ነው፡፡ ብሎ የአብ የመንፈስ ቅዱስን ከእርሱ ጋራ አንድ ባሕርይ አንድ ህልውና መሆናቸውን እንደገናም የእኛን ሥጋ በመዋሐዱ የእኛን ደስታ ለእርሱ የእርሱን ደስታ ለእኛ ሰጥቶ በማቴ.3.13 እንደተናገረው አሁንም ይህ የጥምቀት በዓላችን የእዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበት፣ የተደመሰሰበት በዓል ስለሆነ በ40 ቀንና በ80 ቀን ተጠምቀው በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ የተባሉ ሁሉ የጥምቀት በዓልን ሲያከብሩ የራሳቸው ነጻነት ልጅነት የተመሠረተበት መሆኑን በመረዳት በደስታና በፍቅር ማክበር ይገባል፡፡

ይህ በዓል የነጻነት በዓል፣ የኃጢአት የቁራኝነት የፍዳ ደብዳቤ የጠፋበት ስለሆነ፣ ዛሬም ማንኛውም ሰው ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ተመልሶ ከፍዳ መርገም ወደ በረከት ተመልሶ ለሥጋው ለደሙ በቅቶ ፈጣሪው ጋር ተገናኝቶ፣ በዓሉን ካከበረ በዚህ ዓለም ያከበረውን በዓል ኋላም በመንግሥተ ሰማያት ከመላእክት ጋር ለማክበር ዕድሉ ስለተሰጠው ሰው ሁሉ በዚህ በዓል ሊጠቀምበት ይገባል፡፡

እንግዲህ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን በውጭም በሀገር ውስጥም ለሚኖሩ ሁሉ የጥምቀት በዓል የሰላም የበረከት የፍቅር በዓል እንዲሆንልን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን፡፡ የሰላም ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ተገኝቶ በዓሉን በሰላም አስጀምሮ በሰላም እንዲያስፈጽመን ዛሬ በዚህ ዓመት በዓሉን ለማክበር የፈቀደልን ከርሞ በሰላም ደርሰን በዓሉን ለማክበር እንዲያበቃን የታመሙትን እንዲፈውስልን፣ የወጡትን በሰላም እንዲመልስልን ሀገራችንን በምሕረቱ፣ በይቅርታው እንዲጎበኝልን ዓለምን በጠቅላላው በዓይነ ምሕረቱ ተመልክቶ ለዓለም ምሕረቱን እንዲልክልን የአምላካችን ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡- እግዚአብሔር ይስጥልን በዕድሜ በጸጋ ይጠብቅልን፡፡

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፡– አሜን፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር