multimedia.jpg

ማኅበረ ቅዱሳን የህብር ሚዲያ መካነ ድር አገልግሎት ጀመረ

  በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በፊት ከነበሩት የአማርኛ(www.eotcmk.org) እና የእንግሊዘኛ (www.eotcmk.org/site-en) መካነ ድሮች በተጨማሪ አዲስ የህብር ሚዲያ መካነ ድር (multimedia website) አገልግሎት ጀምሯል።  

multimedia.jpg

 

 

"multimedia.eotc-mkidusan.org" በሚል አድራሻ የተለቀቀው ይኸው መካነ ድር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓት እምነትና ክርስቲያናዊ ትውፊት የጠበቁ የምስል ወድምጽ ስብከቶችና ተከታታይ ትምህርቶች፣ ዜማዎችና፣ መዝሙራት እንዲሁም የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜና ንባብ ያስተላልፋል። ቅዱሳት ሥዕላትና የቅዱሳት መካናት ፎቶዎችም ከመግለጫ ጋር ይኖሩታል::(http://multimedia.eotc-mkidusan.org/video/?video=2364766985) 

 
በመካነ ድሩ የሚተላለፉ የምስልና የድምጽ ውጤቶች የቤተክርስቲያንን ትምህርትና የስብከተ ወንጌልን  ተደራሽነት እንዲጨምሩና በተለያዩ ቦታዎች ለሚሰጡ ትምህርቶችና ስልጠናዎች እንደ ግብአትነትና ምንጭነት እንዲያገለግሉ ታቅዶ አገልግሎቱ ተጀምሯል። ይህም ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ  ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
 
መካነ ድሩን ለአጠቃቀም ምቹ ለማድረግ የምስል ወድምጽ፣ የድምጽ፣ እና የምስል ዝግጅቶች እያንዳንዳቸው በተለያዩ ክፍሎች (ዐምዶች) ተደራጅተው ቀርበዋል። ተጠቃሚዎች ዝጅቶቹን መካነ ድሩ ላይ በቀጥታ በማጫወት(streaming) ወይም በማውረድ(downloading) መጠቀም የሚችሉበት መንገድም ተመቻችቷል።
 
መካነ ድሩ በአንድ የማኅበሩ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አገልጋይ የተሠራ ሲሆን በገንዘብ ሲተመን ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ሊያወጣ እንደሚችል ይገመታል፡፡ መካነ ድሩ በሳምንት ከ10 ሰዓታት በላይ የምስል ወድምጽ ዝግጅቶችን ማቅረብ የሚጀምር ሲሆን የኢንተርኔት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ለሌለባቸው አካባቢዎች እነዚህ ዝግጅቶች በሲዲ የሚሰራጩበት መንገድም ከማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ፕሮግራም ጋር በመተባበር እየተመቻቸ ነው ።
 
የህብር ሚዲያ መካነ ድር መሰናዶዎች በተለያዩ ቅርጾች (formats) ማለትም በጽሑፍ፣ በድምጽ እና በተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ቋሚ ምስሎች ተዘጋጅተው በመካነ ድር የሚቀርቡበት ሚዲያ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም በመላው ዓለም በሚገኙ ታላላቅ የሚዲያ ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ እና እጅግ ብዙ የሰው ሀይል፣ ገንዘብ እና ቁሳቁስ የሚያስፈልጋቸውን ዘልማዳዊ (fotress) ሚዲያዎችን እየተካ ያለ አሰራር ነው፡፡
 
ይህንን አገልግሎት ለማሳካትና  የበለጠ ለማሳደግ  በመላው ዓለም ከሚገኙ ምእመናን የጸሎት፣የሐሳብ፣ የሙያ እና የገንዘብ ድጋፍ ይጠበቃል።ለበለጠ መረጃ፣ ለአስተያየቶችና ለድጋፍ የዝግጅት ክፍሉን ወደ mkelectronicsmedia@gmail.com በመጻፍ ማግኘት ይቻላል።

 

hyawEwnet.jpg

“ታሪክ የሚሠራው ከታሪክ ነው።”

  በኪ/ማርያም

በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል አዳራሽ ጥር 01 ቀን 2003 ዓ.ም በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ‘ሕያው እውነት’ በሚል ርዕስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የኦዲዮ ቪዥዋልና ሥነ ጥበባት ሥራዎች ማእከል አማካኝነት የተዘጋጀው መንፈሳዊ ፊልም ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተመረቀ።

በፊልሙ ምርቃት ላይ ብጹእ አቡነ ሚካኤል የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብጹእ አቡነ ያሬድ የምሥራቅ ሐረርጌ ሊቀጳጳስ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሠ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊ፣ መጋቢ ሥርዐት ዳንኤል ወልደ ገሪማ የቁልቢ ገብርኤል ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የቅ/ሥ/መ/ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር ደጉ ዓለም ካሣ፣ አባ ምንይችል ከሠተ፣ ሊቀመዘምራን ኪነጥበብ ወልደ ቂርቆስ፣ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ፣ በፊልሙ የተሳተፉና ተጋባዥ አርቲስቶች እንዲሁም ምዕመናን ተገኝተዋል።

hyawEwnet.jpg

የዚህን የፊልም ምረቃ ከሌሎች በሀገራችን ከተመረቁ ፊልሞች ለየት የሚያደርገው፣ ብዙ ሕዝብ ተገኝቶ የመረቀው ፊልም በመሆኑ ነው። የመርሐ ግብሩ መሪ ዲ/ን አባይነህ ካሴ ከዚህ በፊት በሌሎች የፊልም ምርቃት ላይ መገኘቱን አውስቶ ብዙዎቹ ፊልሞች ሲመረቁ የሚገኘው የሕዝብ /የተመልካች/ ብዛት እምብዛም ነው በማለት በመድረክ ላይ አስታውቋል።

በፊልሙ ምርቃት ላይ ሊቀመዘምራን ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ ዝማሬ አቅርበዋል፣ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ “የተደፈኑትን ጉድጓዶች አስቆፈረ”ዘጸ 26፥18 በሚል ርዕስ ትምህርተ ወንጌል ሠጥተዋል። ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሲሳይ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ሰብሳቢ  የማኅበረ ቅዱሳንን መልእክት አስተላልፈዋል።
 
የማኅበሩን አመሠራረት ከመነሻው ጠቅሰው የአገልግሎቱን ዘርፈ ብዙነትም፤ ይህም አገልግሎት ከሀገራችን አልፎ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በልዩ ልዩ የህትመት ውጤቶች፣ በራዲዮ፣ በመካነ ድርና የተለያዩ ዐውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ቤተ ክርስቲያንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት አስተዋውቋል፤ በማስተዋወቅም ላይ ይገኛል። አሁንም አገልግሎቱን በማጠናከር በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን መንፈሳዊ ፊልም አዘጋጅቶ አቅርቦላችኋል በማለት ገልጸዋል።

በመቀጠል የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያንም የሥነ ጽሑፍና የሥነ ጥበብ ምንጭ እንደመሆኗ መጠን ያላት ታሪክና የሥነ ጽሑፍ ሀብት ገና በአግባቡ ያልተዳሰሰና ብዙ  የሚያሠራ ነው። በዚህም ምክንያት ማንኛውም የፊልም ጸሐፊ የመረጠውን ጭብጥ የማቅረብ እድሉ እጅግ ሰፊ ነው። በዚህም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ማ/መ/ ማኅበረ ቅዱሳን የኦዲዮ ቪዥዋልና ሥነ ጥበባት ሥራዎች ማእከል ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በዋናነት በማንሳትና የሀገራችንን ባህልና ወግ የሚያንፀባርቅና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሠራውን ደባ መንፈሳዊ ቀናኢነት፣ ሃይማኖትን ሥልጣኔን የአባቶቻችን ጽኑ ሀገራዊ ጀግንነት በጉልህ የሚታይበት መንፈሳዊ ፊልም ሰርቶ እነሆ ዛሬ ለምረቃ አቅርቧል።

ፊልሙም በእውነት ኢትዮጵያዊ በሆነ አቀራረብ የተዘጋጀ ሲሆን በተመስጦ በዘመናት መካከል ወደ ኋላ ወስዶ የቤተ ክርስቲያንን የሥልጣኔ በር ከፋችነት በማስረዳት በቁጭት የሚያነሳሳ፣ የሚያስተምር፣ ማንነትን የሚያሳውቅ፣ አርዓያና ምሳሌ እንዲሁም ማሣያ የሚሆን መንፈሳዊ ፊልም ነው።

ዝግጅቱም በታዋቂ አርቲስቶችና ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኗ አካላት የተውጣጡ ከ400 በላይ በሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የተሠራ ነው። ‘ሕያው እውነት’ ፊልም አጠቃላይ ሥራው በአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት መሥራት የተቻለ ሲሆን የአርቲስቶቹንና የተሳታፊዎችን ነፃ ድጋፍ ሳይጨምር ከ285,000.00 ብር በላይ ወጪ እንደወጣበት ለመረዳት ተችሏል።

ይህ ፊልም ከምረቃ በኋላ ሁሉም ኅብረተሰብ እንዲያየው የማኅበሩ መዋቅር በሚደርስባቸው ቦታዎች ሁሉ ለእይታ ይቀርባል። በመጨረሻም በቪ ሲዲ ና በዲቪዲ ታትሞ ለምዕመናን የሚቀርብ ይሆናል።

በፊልሙ የሚገኘው ገቢ ማኅበሩ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ወጣት ተማሪዎችን ለማስተማርና ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የአባላትንና የምዕመናንን ጉልበትና እውቀት አስተባብሮ ገዳማትና አድባራትን በጊዜያዊነት እንዲረዱና በቋሚነት ከችግር እንዲወጡ ለማድረግ የሚውል ይሆናል።

የማኅበሩ ኦ/ቪ/ሥ/ማእከል ይህ ለቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ የሆነውን መንፈሳዊ ፊልም የማዘጋጀት ሂደት ከፍተኛ ልምድ አግኝቶበታል። በቀጣይም ይህን ልምድ በመጠቀም የተሻለ ሥራ ይዞ ለመቅረብ፣ የአፄ ዘርዐ ያዕቆብን ታሪክ ና የቅድስት እናታችን የወለተ ጴጥሮስን ገድል በፊልም መልክ በመሥራት ጽሑፉን የማዋቀር ሥራ ጀምሯል። በአጭር ጊዜም ለማጠናቀቅ ይታሰባል።

በአጠቃላይ በዚህ ደረጃውን ጠብቆ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐትና ትውፊት ሣያፋልስ ቤተ ክርስቲያን ለሀገሪቱ ያበረከተችውን ሥልጣኔ እንዲያሳይ እንዲሁም የሀገራችንን ባህልና ወግ እንዲያንፀባርቅ ተደርጎ በተሠራው መንፈሳዊ ፊልም ላይ ለተሳተፋችሁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ አርቲስቶች እንኳን ደስ! አላችሁ እያልኩ በቀጣይም ምክራችሁና የሙያ ድጋፋችሁ እንዳይለየን በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፤ ከፊልሙ ጋር መልካም ቆይታ እንድታደርጉ እጋብዛለሁ። በማለት ንግግራቸውን ጨርሰው የፊልሙን ምርቃት አብስረዋል።

ፊልሙም ታይቶ ሲያበቃ በምረቃው ላይ በተገኙ ብጹአን አባቶች፣ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ ከፊልም ባለሞያዎችና አርቲስቶች አንዲሁም ከተሣታፊዎች መካከል አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡ እድሎች ቀርበው ሃሳብ ተሰጥቷል።

ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሠ በመጀመሪያም ይህን ፊልም ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ላደረገ ለማኅበረ ቅዱሳን ምስጋናቸውን አቅርበው ከፊልሙም ያገኙትን ጭብጥ “ፊልሙ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ነው በማለት አስረድተዋል። ይህ ደግሞ ለአዲሱ ትውልድ ፈር ቀዳጅና አስተማሪ ነው። ወደ ኋላ ራሱን እንዲያስተውል የሚያደርግና ጽናቱን የሚፈትሽ በመሆኑ ፍጹም አስተማሪ ነው። ታሪክ የሚሠራው ከታሪክ ነው። ታሪክ ሕይወት አለውና በየዘመኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። ታሪክ እንደ ሰው አካል ስላለው አካሉ እንደተጠበቀ መቆየት ይኖርበታል። አካሉን ማጉደል ተጠያቂ ያደርጋልና ከዚህ መንፈሳዊ ፊልም የተማርነው መንፈሳዊ የፍትሕ አሰጣጥ፣ ጥንታዊ እይታን ወደ ኋላ እንድናስብ፣ የሽማግሌዎች ሚና እንዲሁም ባህሎቻችን፣ ሥርዐቶቻችን ምን ያህል ጠንካራ እንደነበሩ እንደናስተውልም የሚያስተምር መንፈሳዊ ፊልም ነው። ታሪክ የአንድ ሕዝብ መለኪያ መነሻና መደረሻ እንደመሆኑ መጠን ራሱን ማየት የሚችለው ራሱን ሆኖ በመሆኑ ይህ ፊልም ለኢትዮጵያውያን ራሳችንን በመስታወት እንድናይ ያስቻለ ፊልም ነው። ዘመኑንም ራስን እንዳለ ጠብቆ ነገር ግን ወደኋላ ራሱን እንዲያይ ዘመኑን እንደ መስታወት ተጠቅሞ /ቴክኖሎጂውን/ በእድገት ላይ እድገት ለመጨመር መጀመሪያ ከራስ እድገት መነሣት ስለሚገባ ፍጹም አስተማሪ ነው።” በማለት በዚህ ፊልም መደሰታቸውንና ሌሎች ፊልሞች ተዘጋጅተው አማራጮች ቢኖሩ የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የሀገራችንን ታሪክ እንድናስተውል ያደርጋል ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር የሆኑት መምህር ደጉዓለም ካሣ ይህን ፊልም ያዘጋጁትን አካላት አመስግነው ይህ ፊልም በከተማ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በተለይም በገጠሪቷ የሀገራችን ክፍል የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ያልተበረዘ እምነት የያዙ ምዕመናንን ቢያዩት ለዚህም የተለየ ቦታ ተፈልጎ ችግሩን የማያውቁት እነርሱ ናቸውና ፊልሙ ቢታይ በጣም ጥሩ ነው ብለዋል። በመጨረሻም በአቡጊዳ ትምህርት፣ በመልእክተ ዮሐንስ፣ በዳዊት፣ በዜማ፣ በቅኔ ብዙ ያልሄዳችሁ በዘመናዊ ትምህርት የበለጸጋችሁ ስትሆኑ የእናንተን አካሄድ በቤተ ክርስቲያን ቀጥ አድርጎ ያቆመ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

ከመንፈሳዊና ከሙያዊ አንጻር የተሰጡ አስተያየቶችን የመድረክ መሪው በይፋ በመቀበል በመጨረሻም ስፖንሰር ላደረጉ ድርጅቶች፣ በፊልሙ ለተሳተፉ አርቲስቶችና የተለያዩ እገዛዎችን ላደረጉ ሰዎች በብጹአን አባቶች የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በብጹእ አቡነ ሚካኤል ቡራኬ የፊልሙ ምርቃት መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።
                                                         ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                                             አሜን።
     

የቤተልሔም እንስሳት(ለህጻናት)

        ልጆች ዛሬ ስለቤተልሔም እንስሳት ነው የምንጽፍላችሁ፡፡ ቤተልሔምን ታውቃላችሁ? ቤተልሔም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ከተማ ናት፡፡ እና ልጆች የቤተልሔም እንስሳት የጌታችን መወለዱን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው «ምን ይዘን እንሒድ? ምንስ እናበርክት?» በማለት በሬዎች፣ በጎች፣ ጥጃዎች፣ አህያዎች ሌሎች እንስሳትም ተሰብስበው «ምን እናድርግ» እያሉ መወያየት ጀመሩ፡፡

ፀሐይ ልጆቿን ጨረቃንና ከዋክብትን ጠራቻቸውና

«ልጆቼ ሆይ ዛሬ ታላቅ ደስታ በኢየሩሳሌም ሀገር በቤተልሔም ከተማ ተፈጽሟል የዓለም ፈጣሪ ጌታችን ተወልዷልና ፍጥረታት ሁሉ በደስታ የምንሆንበት ቀን ነው፡፡ እና ልጆች የጥበብ ሰዎች /ሰብዓ ሰገል/ ጌታችን መወለዱን ሰምተው ከሩቅ ሀገር ተነሥተው መምጣት ፈልገዋልና ከእናንተ መሐከል ማነው ጎብዝ? እነዚያን የክብር እንግዶች ፈጥኖ ይዟቸው የሚመጣው?» ስትል ጠየቀቻቸው፡፡ ሁሉም «እኔ እኔ ካልተላኩ» ብለው ሲያስቸግሯት እናታቸው ፀሐይ ዕጣ አወጣች፡፡ ለአንዷ ኮከብ ወጣላት፣ ከደስታዋ ብዛት በሰፊው ሰማይ ላይ ክብልል ክብልል እያለች እየበረረች እንግዶች ዘንድ ደረሰች፡፡ እንግዶቹም ለታላቁ ጌታችን የምናበረክተው ብለው ዕጣን፣ወርቅ፣ከርቤ ይዘውለት ሲመጡ አገኘቻቸው፡፡ ኮከቧም በጣም ደስ አላትና ቦግ ብላ በራች፡፡ ወደ ቤተልሔም እየመራቻቸውም ሔደች፡፡

ጌታችን በተወለደባት ሌሊት በቤተልሔም ከተማ አካባቢ ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፡፡ ወዲያውም ያሉበት ቦታ በብርሃን ተጥለቀለቀ በዚህ ጨለማ ምን ብርሃን ነው የምናየው ብለው ፈርተው ሊሸሹ ሲሉ የእግዚአብሔር መልአክ «አይዞአችሁ ልጆች እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ፤አትፍሩ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ሕፃን ተጠቅልሎ ተኝቶ ታገኛላችሁ አላቸው፡፡ ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡ /ሉቃ.2፥8-20/፡፡ ልጆች ይገርማችኋል የዚያን ዕለት አበባዎች በደስታ አበቡ፣ ሣር ቅጠሎችም ለመለሙ፣ ንቦች ማራቸውን አበረከቱ፣ ላሞችም ወተታቸውን ሰጡ ሁሉም ያለውን ሰጠ፡፡ የቤተልሔም እንስሳት «እኛስ ምን እንስጥ?» እያሉ ግራ ገባቸው በመጨረሻም አህያ ከሁሉም የበለጠ ሐሳብ አመጣች «ግን ጌታችን በበረት ነው የተወለደው አይደል?» ስትል ጠየቀቻቸው «አዎን» አሏት «ታዲያ እኮ ልብስ የለውም ደግሞም እንደምታዩት ጊዜው ብርድ የበዛበት ነው፡፡» አለች፡፡

«እና አህያ ምናችን ልብስ ይሆነዋል ብለሽ አሰብሽ?» አለች በግ፡፡ «ለምን ትንፋሻችንን አንሰጥም» አለች፡፡ ሁሉም በጣም ደስ አላቸው፡፡ ትንፋሻቸውን ሊያበረክቱለት ጌታችን ወደ ተወለደበት በረት እየሮጡ ሔዱ፡፡

ልጆች እናንተስ ለጌታችን ልደት ወደ ቤተክርስቲያን ምን ይዛችሁ ልትሔዱ አሰባችሁ? ሻማ፣ ጧፍ ልትሰጡ አሰባችሁ? ጎበዞች! ልጆች እናንተም መባ ሰጥቶ መመለስ ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ቁርባንን ተቀብላችሁ መምጣት አለባችሁ፡፡ እንደ ቤቴልሔም ልጆች /እረኞች/ እየዘመራችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ እሺ? በሉ፤ ደኅና ሁኑ ልጆች፡፡

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ ፡፡ ገላ 4፣4

በመምህር ሳሙኤል

እግዚአብሔር አምላክ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፈጠረ ዘፍ 1፡1 ሌሎች ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጠሩ ሰውና መላእክት ግን ፍቅሩን ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጠሩ፡፡

የሰው ልጅን /አዳምን/ፈጥሮ የሚያስፈልገውን አዘጋጅቶ፣ዕውቀትንና ሥልጣን ሰጥቶ፣ በጸጋ አምላክነትን ሾሞ ፣መመሪያ ሰጥቶ፣በክበር እንዲኖረው ፈቀደለት  በመጀመሪያው ዕለትና ሰዓት ከተፈጠሩት መላእክት መካከል በክብር ይልቅ የነበረው ሳጥናኤል /የኋላ ስሙ ዲያብሎስ /አምላከነት በመሻቱ ተዋርዶ ሳለ አዳምንም በተዋረደበት ምኞትና ፍላጎት እንዲወድቅ ክብሩን እንዲያወጣ ከአምላኩም እንዲለይ አደረገው፡፡  እግዚአብሔርን ፣ጸጋውን፣ሹመቱን፣ወዘተ አጣ /ኃጥአ/፡፡ ኃጢአት የሚለው ከዚህ ጽንሰ ሐሳብ የተወሰደ ነው፡፡
አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱና ክብሩን በማጣቱ ተጸጽቶ ንሰሐ በመግባቱ ለሥርየተ ኃጢአት የሚሆን መስዋእትም በማቅረቡ፤እግዚአብሔር አምላክ ልመናውንና መስዋእቱን ተቀብሎ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ቃል ኪዳን ገባለት “መልዓትንና ዓመታትን በዚህ ምድር ላይ ሠራሁልህ፡፡ይኸውም እነርሱ እስኪፈጸሙ ድረስ በምድር ላይ ትኖርና ትመላለስ ዘንድ ነው፡፡ የፈጠረችህና የተላለፍካት ከገነት ያወጣችህና በወደቅህም ጊዜ ያነሳችህ ዳግመኛም አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም የምታድንህ ቃሌን እልክልሃለሁ” ገድለ አዳም ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው እዳምም አምስት ቀን ተኩል የሚለውን ቃል ከእግዚአብሔር በሰማ ጊዜ የእነዚህን ታላላቅ ነገሮች ትርጓሜ ሊያስተውል አልቻለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምስት ቀን ተኩል ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት መሆናቸውን ገልጾ አርያውና አምሳያው ለሆነው ለአዳም በቸርነቱ ተረጎመለት ያንጊዜ እርሱንና  ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠው፡፡

አዳምም ይህንን ተስፋ ለልጆቹ አስተማራቸው ልጆቹም ተስፋው የሚፈጸምበትን ጊዜ ለማወቅ በፀሐይ ፣በጨረቃና በክዋክብት /ዛሬም ቤተክርስቲያናችን ይህንን አቆጣጠር ትጠቀምበታለች/ዘመናትን እየቆጠሩ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ ያለውን አዳኝ ጌታ መወለድ በትንቢታቸው ይናገሩ ይጠብቁም ነበር፡፡ ከእነርሱም ውስጥ:-

1 ሱባኤ ሔኖክ
ሔኖክ ሱባኤውን ሲቆጥር የነበረው በአበው ትውልድ ሲሆን ሰባቱን መቶ ዓመት አንድ እያለ ቆጥሯል። በስምንተኛው ሱባኤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናግሯል። አቆጣጠሩም ከአዳም ጀምሮ ነው። 8×700=5600ዓመት ይሆናል። 5500ዓመተ ዓለም ሲፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ ያጠይቃል።

ትንቢቱም እንዲህ ይላል። “ስምንተኛይቱ ሰንበት ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅባት ሱባኤ ናት፡፡ ሰይፍም ለርሰዋ ይሰጣታል ታላቁ ንጉሥ የሚመሰገንበት ቤትም በርሰዋ ይሰራል፡፡ ምሥጋናውም ዘላለማዊ ነው፡፡” ሔኖክ 35፡ 1-2 ክፍል 91 በማለት ሲተነብይ መተርጉማን እንዲህ ይመልሱታል ለርሰዋ ሰይፍ ይሰጣታል ማለቱ ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅበት ወንጌል ያን ጊዜ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ማለት ነው፡፡ የታላቁን ንጉሥ ቤት ይሠራል ማለቱ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመሰገንበት ቤተክርስቲያን ትሰራለች ማለት ነው፡፡ ምስጋናውም ዘላለማዊ ነው ማለቱ ሰውና መላእክት በአንድነት ሆነው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ ማለት ሲሆን ስምንተኛይቱ ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠችበትን ዕለት ልደተ ክርስቶስ ናት ይሏታል፡፡

2 ሱባኤ ዳንኤል
ስለ ጌታችን ሰው መሆን ጊዜ ወስኖ ሱባኤ ቆጥሮ የተናገረው ዳንኤል ነው፡፡ የዳንኤል ሱባኤ የሚቆጠረው በዓመት ነው ፡፡ ዳንኤል ሰባው ዘመን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ ተብሎ በኤርምያስ የተነገረውን ትንቢት እያስታዋሰ ሲጸልይ መልአኩ ቅ/ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጾ እንዲህ ብሎታል፡፡ “እግዚአብሔር ልምናህን ሰምቶሃልና እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ አሁንም ነገሩን መርምር ራዕዩንም አስተዋሉ ኅጢአት የሚሰረይበትን ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታም የባህርይ ክብሩን ገንዘብ የሚያደርግበት ባለው ሰባው ሊደርስ ሊፈጸም ነው ብለህ ወገኖችህን ቅጠራቸው ብሎታል፡፡” /ዳን 9፡22- 25 ኤር 29፡1ዐ/
ሰባ ሱባኤ አራት መቶ ዘጠና ዓመት ነው /7ዐX7= 490/ ይህ ጊዜ ከሚጠት እስከ ክርስቶስ መምጣት ያለው ጊዜ ነው /ትርጓሜ ሕዝ፡4፡6/

3 ሱባኤ ኤርምያስ
ኤርምያስ ከባቢሎን እንደተመለሰ በፈረሰው ቤተ መቅደስ ውሰጥ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ራዕይ አየ በሦስተኛው ቀንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ “ፈጣሪያችንን በአንድ ቃሉ አመስግኑ የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግኑ ከዚህ በኋላ ሰው ሊሆን ሥጋ ሊለብስ ወደዚህ ዓለም ሊመጣ የቀረው 333 ሱባኤ ዕለት ነውና እርሱ ወደዚህ ዓለም ይመጣል ዐሥራ ሁለት ሐዋርያትንም ይመርጣል…፡፡” ተረፈ ኤር 11፤37 ፣38፣42-48 ኤርምያስ ሱባኤውን የጀመረበትን ትንቢቱን የተናገረበት ራዕዩን ያየበት ዘመን ዓለም በተፈጠረ በ5 ሺህ እና 54  ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ከተነገረበት እስከ ክርስቶስ ልደት ያለው ጊዜ 446 ዓመት ነው፡፡

ይኸውም በኤርምያስ ሱባኤ አንዱ 49ዐ ዕለት ነው መላው ሱባኤ 49ዐX333 = 163,170 ዕለት ሲሆን ወደ ዓመት ሲለወጥ 163, 170÷365 =446 ዓመት
ኤርምያስ ሱባኤውን መቁጥር የጀመረበት ዘመን …….. 5ዐ54 ዓመተ ዓለም
ትንቢቱ ከተነገረበት ዓመት እስከ ክርስቶስ ልደት …….  446 ዓመት
በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት 55ዐዐ ዓመት ሲፈጸም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱ በዚህ ይታወቃል፡፡

                                                     
4 ዓመተ ዓለም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምረው ሱባኤያትንና ሰንበታትን አውቀው ከአዳም እስከ ክርስቶስ ያለውን ዘመን ቁጥር 55ዐዐ ዓመት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ይኸውም ከአዳም አስከ ኖኅ …… 2256 ዓመት
ከኖኅ እስክ ሙሴ ……… 1588 ዓመት
      ከሙሴ እስከ ሰሎሞን ….  593 ዓመት 
ከሰሎሞን አስከ ክርስቶስ 1063 ዓመት
                55ዐዐ ዓመት
ጌታችን ኢየሱስ በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት /ዓመተ ዓለም ፣ዓመተ ኩነኔ ፣ዓመተ ፍዳ/ አምስት ቀን ተኩል /55ዐዐ ዓመት/ ሲፈጸም /በእግዚአሔር ዘንድ 1ዐዐዐ ቀን  እንደ አንድ ቀን ናት፡፡ 2ኛ ጴጥ 3፤8 / በ5501 ዓመት ማክሰኞ ታኀሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ስምረቱ ለሰብእ” አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ ፍጻሜ /የገባው ቃል ኪዳን፣ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባዔ/ ሲደርስ ከእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተወለደው ያጣነውን ልጅነት ሊመልስልን፣ ከተቀማነው ርስት ሊያስገባን፣ የገባንበትን እዳ ሊከፍልልን እንደሆነ ሁሉ በየዓመቱ የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር ፍቅሩን እያሰብን በኃጢያታችን ምክንያት ከልባችን ያወጣነውን የሁላችንንም አምላክ ዛሬም በልባችን እንዲወለድ ያስፈልጋል፡፡
   “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ?” ማቴ. 2÷1       
                                                             
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ብስራት

እመቤት ፈለገ

በመጋቢት 29 ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተመቅደስ ውስጥ ሆና ስትጸልይ በጣም የሚንፀባርቅ ታላቅ ብርሃን ሆነ፤ ወዲያው እጅግ የሚያምር ስሙም ገብርኤል የተባለ መልአክ አየች፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በማመስገን ሰላምታ አቀረበላትና ‹‹ከሴቶች የተለየሽ ጸጋን የተመላሽ ደስተኛይቱ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ›› አላት፡፡

 

እመቤታችን ድንግል ማርያምም ከንግግሩ የተነሳ ደነገጠችና ‹‹እንዴት እንዲህ ባለ ቃል ታመሰግነኛለህ›› አለችው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ደስ በሚያሰኝ ቃል እመቤታችንን አረጋጋትና ‹‹እነሆ ታላቅ ልጅ ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል›› አለችው፡፡ መልአኩም ‹‹እግዚአብሔር ማድረግ የማይችለው ምንም ነገር የለም፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እንኳን ካረጀች የመውለጃዋ ጊዜ ካለፈ በኋላ ጸነሰች፤ እንዲያውም ከጸነሰች ስድስት ወር ሆኖቷል፤ ስለዚህ አንቺም በድንግልና ትጸንሻለሽ፡፡›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ ፤ እግዚአብሔር ያዘዘኝን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ›› አለችው ስለዚህም እመቤታችን የአምላክ እናት ሆነች፡፡

 

ልደተ ክርስቶስ /የገና በዐል/

በአዜብ ገብሩ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? ዛሬ ስለጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት /ገና በዓል/ እንነግራችኋለን፡፡ በደንብ ተከታተሉን፡፡ እሺ?

 

ልጆች በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፡፡ አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ንጉሥ ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዘዘ፡፡ በትእዛዙ መሠረትም ሰው ሁሉ ሊቆጠር ወደየትውልድ ከተማው ሄደ፡፡ ዮሴፍና እመቤታችንም ሊቆጠሩ ከናዝሬት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ወደ ቤተልሔም ሄዱ፡፡ በቤተልሔም ሳሉም እመቤታችን የምትወልድበት ቀን ደረሰ፡፡ በዚያ ሥፍራም ብዙ እንግዳ ስለነበር እነ ዮሴፍ የሚያርፉበት ቦታ አላገኙም ነበር፡፡ ማደርያም ስላልነበራቸው በከብቶች ማደርያ በበረት ውስጥ እመቤታችን ልጅዋን ወለደችው፡፡
 
በጨርቅ ጠቅልላ እዛው በበረት ውስጥ አስተኛችው፤ በዚያ ሀገር ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ሌሊት ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ነበር፤ የእግዚአብሔር መልአክም በእረኞቹ አጠገብ ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው በራ፤ በጣምም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ‹‹እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡ ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው፡፡ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚህ እረኞች እርስ በርሳቸው ‹እስከ ቤተልሔም እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ አሉ፡፡ ፈጥነውም ሄዱ፡፡ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፡፡ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ አገኙት፡፡ በአዩትም ጊዜ የነገሩአቸውን ሰምተው በጣም ተደነቁ፡፡ እረኞቹም እንደነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው እያመሰገኑና እያከበሩ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ አያችሁ ልጆች እነዚህ ክርስቶስን ሊያዩ የመጡ ሰዎች ደስተኞች ነበሩ፤ ስለዚህ ልጆች እኛም በቤተ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በደስታ ልናከብር ይገባናል፡፡ ከመላእክት ጋር ሆነንም ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን›› እያልን እንዘምር፡፡ እንግዲህ ልጆች መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ እሺ፡፡

stlalibela1.jpg

የገና በዓል አከባበር በቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት

በወ/ኪዳን ጸጋ ኪሮስ
 
በብርሃነ ልደቱ ዋዜማ ከቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉን አስመልክቶ የማኅበረ ቅዱሳን የአማርኛ መካነ ድር በስልክ ከደብሩ ዋና አስተዳዳሪ ከሆኑት ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንንና ከአገልጋይ ካህናት ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበናል መልካም ንባብ።
 
አማርኛ መካነ ድር፦ የበዓል አከባበር ሥርዐቱ ምን ይመስላል?
ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንን፦ በዛሬው ዕለት ማለትም ታህሣሥ 29 ቀን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልና የገናናው ንጉሥ የቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል በአንድነት ይከበራል።
በዓሉ በቦታው አገልጋይ በሆኑ 670 ካህናትና በአካባቢው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሚያገለግሉ ከ500 በላይ በሚሆኑ ካህናት ታጅቦ ማህሌቱ ይካሄዳል፤ በዚህ በዓል መላው ነዋሪ ‘ካህን’ የመስሎ ሚታይበት አከባበር ነው፤ የማህሌት ሥነ ሥርዐቱ 2፡30 (ማታ) ብጹእ አቡነ ቄርሎስ  የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነትና ሌሎች ብጹአን አባቶች በሚገኙበት በየዓመቱ ይከበራል።
በዓሉ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መከበር የጀመረው ከ900 ዓመት በፊት ነው። ከታህሳስ 23(በዓለ ጊዮርጊስ) ጀምሮ እስከ ዛሬ (ታህሳስ 28) ድረስ ሁሌም 2፡00 ሰዓት ሲሆን የሥርዐተ ማህሌት ደወል ይደወልና በአገልግሎት ይታደራል።
ይህ በዋዜማው የሚካሄደው የማህሌት ሥርዐት 1፡30 አካባቢ የሚጀመር ሲሆን ልዩ የሚያደርገው የራሱ ቀለምና ዜማ ያለውና ሙሉ ሌሊቱን በወረብ ዝማሬ እየቀረበ የሚታደር መሆኑ ነው።
የማህሌት ሥነ ሥርዓቱ በብጹዕ አቡነ ቄርሎስ አባታዊ መሪነትና በአስተዳዳሪው አስተባባሪነት እንዲሁም በመሪጌታው በሚመሩ ከ7 ባልበለጡ አስተናጋጆች በሥርዓት ይካሄዳል።የማህሌቱን አካሄድ ስንመለከትም አንድ ጊዜ ከ 12 ያልበለጡ ጥንግ ድርብ የለበሱ’ አንድ ጊዜ ደግሞ ከ 12 ያልበለጡ  ጥቁር ካባ የለበሱ  በድምሩ 24 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ከቀኝና ከግራ ሆነው በተራ እያሸበሸቡ ያስኬዱታል፡፡
 
stlalibela1.jpg
ማህሌቱም ማዕጠንት በያዙ 4 ካህናትና ከ8 ያላነሱ ዲያቆናት ወርቅ ካባ ለብሰው፣ የወርቅ አክሊል ደፍተው፣ የወርቅ መስቀል ይዘው መለከት እየነፉ ዙሪያውን በመዞር ማህሌቱን ያጅቡታል። የዚህም ምሳሌነቱ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ መላእክት መለከት እንደሚነፉ ለመግለጥ ሲሆን ለማህሌቱ ትልቅ ድባብ ይፈጥራል። የማዕጠንት ሥርዐቱ ካህናቱ በሊቀ ካህናቱ፤ ዲያቆናቱ በሊቀ ዲያቆኑ ይመራሉ። 
  ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በአስራ አንዱም ቤተመቅደስ የቅዳሴ ሥርዐት ይፈጸማል። በተለይም ያሉትን ቆራብያን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስተናገድ በቤተ ማርያምና በቤተ መድኃኒዓለም በሁለት ልዑክ ቅዳሴው ይከናወናል።
 
ከ12፡00 ሰዓት ጀምሮ ጥንግ ድርብ፣ ካባ እንዲሁም ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናት ከአስራ አንዱ ቤተመቅደስ ከእያንዳንዳቸው ከአስራ ሁለት ያላነሱ ካህናት ይህንን ያሬዳዊ ዜማ ለማጀብ ወደ ማሜ ጋራ /ቤዛ ኩሉ ዓለም ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ቦታ/ ይወጣሉ።
stlalibela.jpg

 
ልክ አንድ ሰዓት ሲሆን ከላይና ከታች የሚሰለፉ ካህናት ቦታቸውን ይይዙና እስከ 4 ሰዓት በሚፈጅ ክንውን እየተቀባበሉ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለምድር ሰላም በረከት የሚጸለይበት ‘ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ’  የተባለው የቀለም ክንውን ይካሄዳል። እንግዲህ የበዓሉን አከባበር በቅዱስ ላልይበላ ልዩ የሚያደርገው አንዱ ይህ “ቤዛ ኩሉ ዓለም” የሚባለው የቀለም ዓይነት ነው።
አማርኛ መካነ ድር፡- የቅኔ ሥርዐቱስ ምን ይመስላል?
 
ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንን፡-ቅኔ የሚሠጠው የሠዓቱ ሁኔታ ታይቶ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ተጠይቀው ሲፈቅዱ ከ3 ያላነሱ የቅኔ ባለሞያዎች (የቅኔ መምህራን) ያራምዱታል (ያስኬዱታል)። በዚህ ክብረ በዓል ላይ የሚቀርቡት ቅኔዎች ጥልቅ ምስጢር ያዘሉ ናቸው፡፡
አማርኛ መካነ ድር፡-አባታችን በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
 
ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንን፡- ይህ በዓል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት በመሆኑ በውጪ ላሉ ሰዎች መተዋወቅ ያለበትና ሁላችንም ለዚህ የበኩላችንን አስተዋፅኦ መወጣት ይገባናል፡፡ ይልቁንም በመንፈሳዊ አገልግሎታችን በቤተክርስቲያናችን ሥርዐት የሚከበረው ይህ በዓል ልዩ ስሜት የሚፈጥር በመሆኑ ለሁሉም መተዋወቅ የሚገባው ነው፡፡
በመጨረሻም በዓሉን ለማክበር ከተለያየ ቦታ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከኤዥያ፣ ከአፍሪካ እንዲሁም ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ ምዕምናን በዓሉን በሰላም አክብረው ወደየመጡበት በሰላም እንዲመለሱ የእግዚአብሔር ቸርነት ይሁንልን፡፡ የጻድቁ የቅዱስ ላሊበላ በረከትም ከሁላችን ጋር ይሁን።
 
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በመላው  ዓለም የሚከበር ሲሆን  በቅዱስ ላልይበላ በድምቀት የሚከበረው ከቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል ጋር አብሮ በመሆኑ ነው።በዚህ በዓል በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምዕመናን መንፈሳዊ በዓሉን ለማክበርና በረከት ለመሳተፍ የሚጓዙ ሲሆን ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዐቱን ለመጎብኘት ነው። ይህም በዓል ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሀገራዊ ፋይዳ አለው።ይህንንም ለማስረገጥ በየዓመቱ ያለማቋረጥ ምዕመናን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መምጣታቸው ነው።
 
በተጨማሪ ኢአማንያን ይህንን መንፈሳዊ ቦታ ካዩ በኋላ ከሥላሴ ልጅነት አግኝተው ወደተለያዩ ዓለም ተመልሰዋል። ይህም በዓሉ ለአካባቢውና ለሀገራችን ብሎም ለውጭ ሀገር ዜጎች በየዓመቱ እንዲናፈቅ ሆኗል።

 

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሣህልና ምሕረት
የጻድቁ የቅዱስ ላሊበላ ረድኤትና  በረከትም ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

 

በሕይወት ያለ ማስታወሻ ለገና ሥጦታ

የዘመነ ማቴዎስ 4ኛ ወር የመጨረሻውን ቀን በሚመስጥ የሕይወት ትምህርት በመማር አሳለፍኩት፡፡ ጠዋት ከጓደኛዬ ጋር ቁርስ አድርገን እርሱ ሊወስደኝ ካሰበው ሥጦታ መስጫ ቦታ ሄድን፡፡ይህ የስጦታ መለዋወጫ ቦታ ለእነርሱ ልማድ ነው፡፡ በዓል በመጣ ቁጥር የሚሄድበት የውዴታ ግዴታ የሆነበት ልማድ በእርግጥ ሲጀምረው ጥልቅ ደስታና እርካታ የተሞላ ነበር።

እኔ ከጉዟችን መልስ በድርጊቱ ተደምሜያለሁ፣ እርሱ በዓመት ሦስቴ ለበዓላት በመሄድ ገንዘብ ያደረገው ልማድ!! ይህ የልደት በዓል በጠዋቱ መልካም የሕይወት ተሞክሮ እያስተማረኝ እንደሆነ መረዳቴ የዘመኑን መልካም ጅማሮ እንድወደው አስገደደኝ ገና ሦስት ሩብ ዓመታት ይቀራሉና!!

‹ታምሜ ጠይቃችሁኛል?…… ተርቤ አብልታችሁኛል?› የሚሉት የክርስቶስ የወንጌል ቃላት ለእርሱ የሕይወት ልምምድ መሠረቶች ነበሩ፡፡ እንዴት ልፈጽመው ከሚል በጎ መሻት የመነጨ ልምድ፣ እናም ወሮታ የማይከፈልበት ብድር ከማይመለስበት፣ ይሉኝታ ከሌለበት፣ ከሥጋዊ የራስ ጥቅም አድልዎ የነጻ ዕረፍት፣ ጥልቅ ደስታና የሕይወት እርካታ ያገኝ ዘንድ በበዓላት በሆስፒታል የተኙ ህመምተኞችን ቤት ያፈራውን በመያዝ ‹እንኳን አደረሳችሁ…..እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ እግዚአብሔር ይማራችሁ! በማለት ይጠይቃቸዋል፡፡ ከቤተሐኪም ገብቶ የሚጠይቃቸው፣ የሚያጫውታቸውና የሚያጐርሳቸው በአጠገባቸው አስታማሚ(ጠያቂ) የሌላቸውን ብቸኛ ህመምተኞች ናቸው፡፡ ይደርስላቸዋል፣ ከጐናቸው!!

አዎ! ማንም ህመምተኛ ድኖ ሲነሣ ውለታ ለመክፈል አይጨነቅም በውለታ አልታሰረምና፡፡ አያውቃቸውም አያውቁትም ቀድሞ እንዲሁ ነበር ዛሬም እንደዛው ወደፊትም እንዲያው ሊሆን ይችላል፡፡ እናም የማያውቁትን በመጠየቃቸው ብድር የማይመልሱትን እርሱም ለነገ ብድራት የማያስቀምጠውን ግን ህመምተኛ ጠያቂን ፈላጊ የሆነን ሰው እንደው ደርሶ ‹እንኳን አደረሰህ› ብሎ የፈጣሪን ምሕረት ለምኖ መጽናናትን መፍጠር እርግጥ ምን ያህል ዋጋ ያለው ደስታ ይኖረው ይሆን… ወዘተርፈ፡፡

የዓውደ ዓመት በዓል ይሄን ያህል ደስታ ይፈጥር ይሆንን? እርግጥ በቤተሰብ መሀል ለሚኖር ሰው ደስታው፣ ጨዋታው፣ ሁካታው፣ መጠያየቁ፣ መልካም ምኞቱ ደስታ ሊፈጥሩ ይተጋገዙለት ይሆናል ይሄን ቢጨምርበት ግን ደስታው ሊያገኘው ከሚታገለው እጥፍ ሲበዛለት ሲበረክትለት ወደ እርካታ ሲመራው በሕይወቱ ሊማር እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ምናልባትም የምንጠይቀው አንዱ ህመምተኛ የሕይወትን ቃል ሊያሰማን ምክንያት ቢሆንስ? ኑ እንውረድ በዓርአያችን እንደምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር ያለው ለዚህ ይሆን እንዴ?!
ይህ ነው የገና ሥጦታ የተሰጠኝ፣ የሕይወት ትምህርታዊ ገጸ በረከት! ማስተዋሉን ላደለው መልካም ትምህርት ነበር ግሩም!!

/ በዕለት ውሎ መመዝገቢዬ ለጽሑፍ በሚሆን መልክ የተቀዳ
በኤርምያስ ትዕዛዝ  ዘሐብታም
መስከረም 1 2001 ዓ.ም /

hyawEwnet.jpg

ማኅበረ ቅዱሳን የመጀመሪያ ፊልሙን ሊያስመርቅ በዝግጅት ላይ ነው፡፡

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

hyawEwnet.jpgበማኅበረ ቅዱሳን ኦዲዮ ቪዥዋልና የሥነ ጥበባት ሥራዎች ማእከል ‹‹ሕያው እውነት›› በሚል ርዕስ የተሠራው ፊልም በአዲስ አበባ የስብሰባ ማእከል ጥር 1 ቀን 2003 ዓ.ም ይመረቃል፡፡

በፋሲል ግርማ የተዘጋጀው ይህ ፊልም የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ ለሀገሪቱ ሥልጣኔ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በዋናነት ያወሣል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሰራው ደባ፣ መንፈሳዊ ቀናዒነት፣ ሃይማኖትና ስልጣኔ የአባቶቻችን ጽኑ ሀገራዊ ጀግንነት ከታሪክ ማኅደር እየተቀዳ በጉልህ የሚታይበት ነው፡፡

ፊልሙ በድርጊት የተሞላና ልብ አንጠልጣይ /suspense/  በሆነ ውብ አቀራረብ የተዘጋጀ ነው፡፡ በተመስጦ በዘመናት መካከል ወደ ኋላ ወስዶ የቤተክርስቲያንን የሥልጣኔ በር ከፋችነት በማስረዳት በሞራልና በቁጭት የሚያነሳሳ፣ የሚያስተምር፣ ማንነትን የሚያሳውቅ አርዓያና ምሳሌ የሚሆን መንፈሳዊ ፊልም ነው በማለት ከማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦዲዮ ቪዥዋልና የሥነ ጥበባት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ቶሞስ በየነ ገልጸዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ዘንድ ተወዳጅ እንደሚሆን ይገመታል ያሉት አርቲስት ቶማስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዚህ ደረጃ (standard) ፣አቀራረብና ይዘት የመጀመሪያ የሚሆን ፊልም ነው ብለዋል፡፡
በፊልሙ ላይ የአላዳንኩሽም ፊልም መሪ ተዋናይ አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲሁም በተለያዩ ፊልሞችና ቲያትሮች የምናውቃቸው አርቲስተ ሳምሶን ግርማ፣ አርቲስት ሞገስ ቸኮል፣ አርቲስት ትዕግሥት ግርማ፣ አርቲስት አብርሃም ቀናው፣ አርቲስት በፍቃደ ከበደ፣ አርቲስት ዘበነ ሞላ እንዲሁም ሌሎችም የሀገራችን ታዋቂ ተዋንያን ተሣትፈውበታል፡፡

ከ400 በላይ ሰዎች የተሳተፉበት ይህ ፊልም ከ250.000 ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ወጪውን የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የቁሳቁስ፣ የአልባሳት፣ ወዘተ ወጪ ብቻ ሲሆን ታዋቂ ተዋንያን በፊልሙ ላይ የተወኑት ያለ ክፍያ ለአገልግሎት እንደሆነ አርቲስት ቶማስ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም የኪነጥበብ ምንጭ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ማንኛውም ክርስቲያን ሙያዊ አስራት ማቅረብ አለባቸው፡፡ የኪነ ጥበብና የሙያ ሰዎችም በሙያቸው ቤተክርስቲያንን ሊያገለግሉ ይችላሉ ብለዋል፡፡

አሁንም ሊሠራ ተጽፎ ኤዲቶሪያል ቦርድ የገባ እንዲሁም ገና እየተዘጋጀ ያለ ፊልም አለን በእነዚህ ፊልሞች የካሜራ ባለሞያዎች፣ ኤዲተሮች፣ ዳይሬክተሮች የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት የልጅነት ድርሻቸውን ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ሊወጡ ይችላሉ ብለዋል፡፡

የፊልሙ ገቢም በዋናነት የማኅበሩን የስብከተ ወንጌል ለመደገፍ እንደሚውል የገለጹት አቶ ቶማስ በተጨማሪም የማኅበሩን ህንጻ ማስፈጸሚያ ገቢ እንደሚስያስገኝ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ምዕመናን በፊልሙ እየተማሩ ትሩፋትን እንዲሠሩ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በማለት ይጠቀልላሉ፡፡

ፊልሙ በማኅበሩ የሀገር ውስጥ 39 ማእከላትና በውጭም በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብጽ፣ በጅቡቲ፣ በኢየሩሳሌም፣ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስና በሌሎችም አገሮች ለእይታ ይቀርባል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ቴአትር ቤቶች በመከራየትና በቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ መድረኮች ለዕይታ ይበቃል፤ በመጨረሻም በዲቪዲና ሲዲ ታትሞ ለገበያ ይቀርባል፡፡

ledeteegzie.jpg

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል

ledeteegzie.jpg

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክቶ በመካነ ድር አድራሻችን እንዲሁም በስልክ ተደጋጋሚ ጥያቄ በመጠየቁ ይኽንን አስመልክተን ከማኅበረ ቅዱሳን የሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ ከሆኑት ከዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ጋር ጥቂት ቆይታ አድርገን የሚከተለውን ምላሽ አግኝተናል መልካም ንባብ፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡- ብዙ ምዕመናን በስልክና በኢሜል የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አርብ ነውና የሚውለው፣ ይበላል? ወይስ አይበላም? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዐት መሠረት አድርገው ምላሽ ቢሠጡን?
 
ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፡- ፆመን በመብልና በደስታ ከምናከብራቸው በዓላት ውስጥ ሦስቱ ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ናቸው፡፡ ‹‹ወእምድኅረዝ ፍትሑ ፆመክሙ እንዘ ትትፈሥሁ ወእምትሐስዩ ሶበ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ተንስአ እምነ ምውታን….››፣ ‹‹….ከዚህ በኋላ ፈፅሞ ደስ እያላችሁ ፆማችሁን በመብልና በመጠጥ አሰናብቱ…›› እንዲል ፍትሐ ነገሥት ከትንሣኤ ጋር አነካክቶ በሚናገረው አንቀጽ፡፡ ትንሣኤ ሁሌም እሑድ ቀን የሚውል በመሆኑ ቀዳሚት ስኡርን በአክፍሎት ከመፆም በቀር ሌላ ተጨማሪ ትዕዛዝ የሌለበት መሆኑን የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት መጽሐፍ ያስረዳሉ፡፡ ጥምቀትና ልደት ግን ከአዋድያት በዓላት ውስጥ ስለሆኑ የሚውሉበት (የሚከብሩበት) ዕለት የሚለዋወጥ ነው፡፡ ረቡዕና አርብን ጨምሮ በማንኛውም ዕለት ቢውሉ የሚበላ (የማይፆም) መሆኑን በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ፡- በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ፆመ ነቢያት 44 ቀን የሚፆም ሲሆን 40 ቀን የሙሴ፣ 3 ቀን የአብርሃም ሶርያዊው አንዷ ቀን ደግሞ ጋድ በመሆን ስለሚፆም በዓሉ ረቡዕም ዋለ አርብ ሁልጊዜ ይበላል እንጂ አይፆምም፡፡
በመሆኑም ይኽ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አርብ ዕለት የሚውል ቢሆንም የሚበላ (የማይፆም) መሆኑን የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡
አማርኛ መካነ ድር፡- በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት መሠረት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን እንዴት ማክበር አለብን?

ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፡-
ከላይ የጠቅስናቸው ሦስቱም በዓላት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት መሠረት ቅዳሴያቸው በመንፈቀ ሌሊት ይከናወናል፡፡ ከቆረብን በኋላም ፆሙን በመበል፣ በመጠጥ፣ በፍፁም መንፈሳዊ ደስታ ማሰናበት እንደሚገባን በመጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡ መንፈሳዊ ደስታ ሲባል ግን ጥቅም (ረብ) የሌለው ነገር በመናገር ማክበር እንደሌለብን (እንደማይገባን) የተረዳ ነው፡፡ አንድ ሰው መብል መጠጥ በማብዛት ሊደሰት አይገባውም፤ በእውነት ሌሎችም በዚህ አልተጠቀሙም፡፡ እህልን ልንሄድበት ልንቆምበት ነው እንጂ ልንሰናከልበት አልተሰጠንምና፡፡
በእነዚህ በዓላት አንድ ሰው ከቤተሰቡ በሞት እንኳ ቢለየው አያልቅስ ምክንያቱም በበዓላቱ የምናገኘው ደስታ ካጣነው ቤተሰብ ጋር የሚነፃፀር ስላልሆነ፤ በዚህ ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ያገኘ ሰው አንድ ልብስ ጠፋብኝ ብሎ እንደማያዝን፤ በጌታችንም በልደቱ፣ በጥምቀቱና በትንሣኤው ያገኘነው መንፈሳዊ በረከት ከፍተኛ ስለሆነ በእነዚህ እለታት ማዘን ማልቀስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት መጽሐፍት ቀኖና ይገባዋል ይላሉ፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡-
በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
 
ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፡- እንግዲህ በመጽሐፍትም እንደተጠቀሰው በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እንዲያደርግልን የእርሱ ፈቃድ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡