ምኩራብ

ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት «ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ»

«ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ» እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ምኩራብ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡ የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 21፡12-13 ተጠቅሷል፡፡

ቆላስ 2፡16-23 «እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፣ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፣ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል፡፡ ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ት ምህር ት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደሰው ሥርዓትና ት ምህር ት፡- አትያዝ አትቅመስ፣ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም ሁሉ እንደምትኖሩ ስለምን ትገዛላችሁ) እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና፡፡ ይህ እንደገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቈን ጥበብ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፡፡»

ያዕ 2፡14-26 « ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል) እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን) ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል) እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡
 
ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡ በእግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡ አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን) አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን) እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን) መጽሐፍም አብርሃምም እግዚአብሔር አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን) ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡»
 
የሐዋ.ሥራ 1ዐ፡1-9 « በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፡፡ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፡- ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ ጌታ ሆይ ምንድር ነው) አለ፡፡ መልአኩም አለው፡- ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረገ፡፡ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ፡፡ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፣ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፣ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው፡፡ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፣ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ፡፡
 
መዝ 68፡9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡
 
የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡
 
ዮሐ 2፡12-25 «ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፡፡ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ፡፡ ስለዚህ አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክ ት ታሳየናለህ) አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን) አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡
 
በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡»
 

                        ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቅርሶች ዘረፋን ለመከላከል

የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የረጅም ዘመን ታሪክና የበርካታ ውድና ምትክ የሌላቸው እንዲሁም ማንኛውም መጠን ያለው ገንዘብ የማይተካቸው ታሪካዊና ዓለማቀፋዊ እውቅና ያላቸው ቅርሶች ባለቤት ነች፡፡ እነዚህ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶቻችን ከቀደምት አባቶቻችንና አያቶቻችን የወረሰናቸው እኛም በተራችን ጠብቀንና ተንከባክበን ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ለሀገራዊ ልማት እያዋልን ለመጪው ትውልድ የምናስተላልፋቸው መተኪያ የሌላቸው እሴቶቻችን ናቸው፡፡ ቅርሶች ያለፈውን፣ ነባሩንና ተተኪውን ትውልድ የሚያገናኙ የኅብረ ትውልድ ድልድዮች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእነዚህ ንዋይ ሊተምነው የማይችል ቅርሶች ግምጃ ቤት መሆኗ እና እኛም ልጆቿ የዚህ ታሪክ ተረካቢዎች በመሆናቸን መንፈሳዊ ፍስሐ ይሰማናል፡፡

ስለ አገራችን ቅርስ ሲነሣ በአብዛኛው በቅርስነት የተመዘገቡትና የሚጎበኙት የቤተክርስቲያናችን ቅርሶች ናቸው፡፡ ይህም ሁኔታ የኢትዮጵያ ታሪክና የቤተክርስቲያን ታሪክ የማይነጣጠሉ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የሀገሪቱ ዜጎች ስለ ቅርስ ጥበቃ የሚኖረን ግንዛቤ ለታሪካችን ካለን አመለካከት የሚነሳ ነው፡፡ አንድ ሕዝብ ቅርስ አለው ስንል ታሪክ አለው፣ ክብር አለው፣ ተደማጭነት እንዲያገኝ የሚያደርግ ማሰረጃ አለው ማለት ስለሆነ ለቅርስ የሚደረግ እንክብካቤና ጥበቃ በታሪክ መዘክርነት ለሚቀርብ ማስረጃ የሚደረግ ጥበቃ መሆኑን ተገንዝበን ለቅርስ ጥበቃው ከግል ፍላጎትና እምነት ነፃ ሆነን ሀገራዊና ሕዝባዊ አስተያየትን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡
 
ይሁን እንጂ ዛሬ ብዙ ሃይማኖታዊ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቅርስ ሀብት እንዳለን ስንገልጽ፣ በርካታ ቅርሶቻችንን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ማጣታችን መዘንጋት የለብንም፡፡ እንዲሁም እያየን ነው፡፡ ይልቁንም አሁን በእጃችን ካለው የቅርስ ሀብታችን አብዛኛዎቹ አንድም ባሳለፍናቸው የእርስ በእርስ ግጭቶችና ያለተቋረጡ የባዕድ ወራሪዎችን ለመከላከል በተደረጉ ጦርነቶች ወድመዋል ተመዝብረዋል፡፡ ከዚያም ያለፈው በራሳችን ሰዎች፣ በወራሪ ኃይሎች፣ በጎብኚዎች፣ በተመራማሪነት ስምና በልዩ ልዩ ዲኘሎማሲያዊ መብቶች ሽፋን በየጊዜው በሚመጡ ግለሰቦች ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡
 
በጦርነት የወደመውን የቅርስ ሀብታችንን «የፈሰሰ ውሃ» እንዲሉ አበው መፍትሔ ባናገኝለትም እንኳ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም ባሕላዊ ቅርሶቻችን ታሪኩ ታሪካቸው ባሕሉ ባሕላቸው፤ ሆኖ በማይዘክሩለት ባዕዳን ሀገራት እጅ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ ለእነዚህ አካላት የገቢ ምንጭ ሆነዋል እነዚህን ቅርሶች ስለ ሀገሩ ባሕል፣ ታሪክና ሃይማኖት እንዲሁም ወግ ለማጥናት የፈለገ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ከፍተኛ ገንዘብ  በማውጣት ያባቶቹን ሀብትና የእሱነቱን መገለጫ የታሪክ ቅርስ መረጃዎችን ለማግኘት በባዕዳን ሙዚየሞችና ቤተ መጻሕፍት እየዞረ የመንከራተቱ መራር እውነት በብዙ ወንድሞቻችን አንደበት በየጊዜው የሚነገር ነው፡፡ ይሄን እውነት እነርሱ እንኳን ብንለው ችግሩ ከቶ ሊያስረሳን አይችልም፡፡
 
ለዚህም አብነቶችን ማንሣት ይቻላል፡፡ በእንግሊዝ ሠራዊት የተዘረፈውን አንድን የመጾር መስቀል ፎቶ ግራፍ ለማንሳት ብቻ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ ቅርሱን በያዘው ክፍል መጠየቁ እንዲሁም የቅዱስ ላሊበላ አፍሮ አይገባ መስቀላችንን ከቤልጅም በከፍተኛ ዋጋ መግዛታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው፡፡
 
ይህ አልበቃ ብሎ ቅርሶቻችን ያለ አግባብ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እየወጡ በአሜሪካና አውሮፖ በመረጃ መረቦች አማካ ኝነት በግልጽ እየተቸበቸቡ ይገኛሉ፡፡ ዛሬም ቅርሶች የሚገኙባቸው አድባራት፣ ገዳማትና አብያት ክርስቲያናት፣ ተቋማት መካነ ቅርሶች መደፈራቸውና በውስጣቸው የሚገኙ ብርቅና ድንቅ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች መዘረፋቸው አልተገታም፡፡
 
ቅርሶች ለጊዜያዊ አፍቅሮተ ንዋይ ሲባል ያለ አግባብ የመዘረፋቸው የመበላሽታቸውና የመባከናቸው መርዶ አልቆመም፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ ወቅት ለእኛ ለአሁን ትውልድ ወጣቶች፣ ለቤተክርስቲያን አባቶችና ለመንግሥት ሁለት ሊታለፉ የማይችሉ ፈተናዎች ለምርጫ ከፊት ለፊታችን ተደቅነዋል፡፡ እነዚህ ምርጫዎች አንድም ቅርሳችንን ሕገ ወጥ ዝርፊያ ማስቆም፣ ያለ አግባብ የተዘረፉትን ለማስመለስ በተጀመረው ጥረት ሳይታክቱና ሳይሰለቹ መቀጠልና በእጃችን ያሉትን ጠብቆና ተንከባክቦ ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ለሀገር ልማት እያመቻቹ ለተተኪው ትውልድ በማስተለለፍ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መውጣት፤ ወይም አሁን በአብዛኞቻችን እየተደረገ እንዳለው ዘረፋና ጥፋቱን በግዴለሽነት በመመልከት ድሀ ደካማና መረጃ አልባ ሀገር እና ቤተክርስቲያን ለትውልድ ጥሎ በማለፍ የታሪክና ትውልድ ተወቃሽ መሆን ናቸው፡፡
 
ያለ ማወላወል ለማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ አገልጋይ ካህናት እንዲሁም ሀገር ወዳድ እና ቅን ዜጋ ምርጫ ሊሆን የሚገባውና የሚሆነው የመጀመሪያው ነው፡፡ በመጀመሪያው ምርጫችን መሠረት ከመንግሥት ለቅርስ እንክብካቤ የሚጠበቀው ሚና ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማልማት በርካታ ሕጐችን፣ አዋጆችንና ፖሊሰዎችን ማውጣቱንና ዓለም ዓቀፋዊ እና አህጉራዊ የቅርስ ስምምነቶችን መፈራረሙ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጸ 91 ላይ ስለ ቅርስ መደንገጉ የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ መውጣቱ፣ የባሕል ፖሊሲ መቀረጹ እና ሀገሪቱ ቅርሱን አስመልክቶ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን መፈራረሟ የሚያሳየው መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ነው፡፡
 
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መፈራረምና ሕጎችንና አዋጆችን ቢወጡም አሁን የሚታየውን የቅርስ ዘረፋ ቀጥሏል፡፡ በቅርስ ዘረፋ ተሰማርተው ለተያዙት ሰዎች የሚሰጠውም ቅጣት ለሌሎች አስተማሪ ባለመሆኑም ለዘራፊዎች መበራከት ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡ የቅርስ ዘረፋን አስመልክቶ ቀድሞም ሆነ አሁን  ተሻሽለው የወጡት ሕጎችና አዋጆች ግን ጉዳዩን አስመልክተው ያወጡት የቅጣት ውሳኔ ከፍተኛ ነበር፡፡ በቅርስ ጉዳይ ላይ በወጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚደረጉት ቅርሶች ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር በሕገ ወጥ መንገድ እንዳይተላለፍ ለመከላከል በማሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያም እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በመፈራረሟ በስምምነቱ  ተጠቃሚ ልትሆን ይገባት ነበር፡፡ ሀገራችን ከውጪ ወደ ውስጥ የምታስገባው ቅርስ ባይኖረም፤ ከእርሷ ግን ብዙ ቅርሶች በሕገ ወጥ መንገድ የተዘረፋት ቅርሶች ወደ የሀገራችው እንዳመለሱ ያዛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ እና የተዘረፍብን ቅርሶችን ወደ ሀገር ለማስመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ቢሆንም በውጪ ካለን የቅርስ ብዛት አንፃር ሲመዘን ከቁጥር የሚገባ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የሕገ አስፈጻሚ አካላት ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ቅርሶችን አስመልክቶ የወጡት ሕጎች በትክክል እንዲፈጸሙ ገቢራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
 
የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች የእምነቱ ተከታዮች የቅርሰ ዘረፋን ሕገ ወጥ ዝውውርን ይበልጥ የመንከባ ከብና የመጠበቅ ግዴታ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 2ዐ9/1992 ዓ.ም ላይ የቅርስ ባለቤት የሆነ ሰው በእጅ የሚገኘውን ቅርስ ተገቢውን  ጠበቃና እንክብካቤ ካላደረገ… ለቅርሱ አጠባበቅ የሚወጡ ደንቦችንና መመሪያዎችን ያላከበረ እንደሆነ ወይም በይዞታው እንዲጠቀምበት በተሰጠው መሬት ላይ የሚገኝ ቅርስ በሚገባ የማይጠብቅ ከሆነ ወይም ቅርሱን የሚያሰተላልፍ ሰው የቅርሱን ማስተላለፍ ለባለስልጣኑ /ለመንግሥት/ ያላሳወቀ እንደሆነ… ይህን አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ የማያስፈጸም ከሆነ እሰከ ስድስት ወር እስራት እንደሚቀጣና ወይም እስከ 1 ሺሕ አምስት መቶ ብር እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡
 
በየጊዜው ትኩረት እየተሰጣቸው አዋጆች ገቢራዊ እንዲሆኑ  የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ክትትል ማድረግ አለባቸው፡፡ በቅድሚያ የአገራችን ሕዝብ ሁሉ የኢትዮጵያ መገለጫና የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቅርሶች የአገራቸው ሀብት በመሆናቸው በባዕዳን ሲዘረፉ ሲቃጠሉ በቸልታ መመልከት የለባቸውም፡፡ ምእመናንም ቀደምት አበው ቀን በጽሕፈት ሌሊት  በጸሎት ተገተው ያዘጋጇቸው መጻሕፍት የገዳሟቸው ገዳማት ያካበቷቸው ንዋያተ ቅድሳት የእምነታቸው መገለጫ በመሆናቸው በእኔነት ስሜት ሊጠብቋቸው፤ ተዘርፈው ሲሄዱ ጥብቅና ሊቆሙላቸው ይገባል፡፡

የቅርስ ባለቤት የሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያን በየገዳማቱና አድባራቱ የሚገኙ ቅርሶቿን ሥርዐት ባለው መንገድ መመዝገ ብና ስለ ቅርሶቿ ተጨባጭ የሆነ መረጃ መስጠት አለባት፡፡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋርም በመቀናጀት ቅርሶች ሲዘረፉ፣ ሲቃጠሉ በፍጥነት ለሕግ አስፈጻሚ አካላት ተገቢን እገዛ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ይኸውም ባለቤት በማጣት በግለሰቦችና በእግዚቢትነት ተይዞ የሚገኝ ቅርሶቿን ለማስመለሰ ይረዳታል፡፡
 
በአጠቃላይ ቅርሶች የሀገራችን ሀብታት የቀደሙት አበው ሥልጣኔ መገለጫ ዛሬ ላይ ቁጨ ብለን የትላንትን የምናይባቸው የክብራችን ገላጭ የእኛነታችን መለያ አሻራ በመሆናቸው በኅብረት እንክብካቤ ልናደርግላቸውና ጥብቅና ልንቆምላቸው ይገባል፡፡
የሕግ አስፈጻሚ አካላት ቢሆኑም በቅርስ ዙሪያ የወጡ ሕጎችንና አዋጆችን በትክክል መፈጸማቸውን ይከታተል፤ የቅርስ ዘረፋን እና ሕገወጥ ዝውውርን ለመግታት ሕጎች በትክክል ሊፈጸሙ ይገባል፡፡

 

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የተዘጉ በሮች ይከፈቱ

ብዙዎቻችን ከእኛ ውጭ ስላሉ አካላት ሲነገረን ለማድመጥ የምንፈልገው የሆኑትንና እውነታውን ሳይሆን እኛ ሊሆኑት የምንፈልገውን ነው፡፡ ስለዚህም ስለምንነቅፋቸው አካላት የሚከሰሱበትንና የሚጐነተሉበትን እንጂ እውነታውን መስማት አሁን አሁን የኮሶ ያህል የሚሰቀጥጥ፣ የሞትም ያህል የሚያስደነግጥ ሆኖአል፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች የሚከሰቱት ደግሞ በሁሉም ማኅበረሰብ መሆኑ ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
ፖለቲከኞች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት ሰባክያንና መዘምራን፣ … እንዲሁም ሌሎችም ከዚህ ወጥመድ ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል የእስልምና መምህራኑ ስለ ክርስትና የሚሰሙት ክርስቲያኖች የሚሉትን ሳይሆን የአሉባልታ ዶክመንቶች የሚሉትን መሆኑ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የሃይማኖት ልዩነት በሌለበት እንኳ አንዱ ስለሌላው የሚናገረውና ሊሰማ የሚፈልገው አሁን አሁን አስፈሪነት እየታየበት ነው፡፡
 
ችግሩ የሐሳብ፣ የአመለካከት፣ የሃይማኖት፣ የርእዮተ ዓለም ልዩነት መኖሩ አይደለም፡፡ አንዱ የሌላውን በትክክል ተረድቶ ተጠየቃዊ በሆነ መንገድ የሐሳብ ክርክር መኖሩም ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ጤናማ በሆነ አመለካከትና መረጃዎችን በመተንተን ላይ የተመሠረተ ከሆነ ልዩነትን አንጥሮ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በሐሳብ ለመሳሳብና ለመቀራረብም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በሃይማኖትም ቢሆን አንዱ ሌላውን ሳይሰድብ የሚያምነውን በትክክል ተረድቶ ያንን እምነት እንዴት ስሕተት እንደሆነ ማሳየትም የሚጠበቅና ጤናማ ጠባይ ነው፡፡ ችግሩ ግን ሁሉም ስለሌላው የሚናገረው እምነቱን የሚመራበትን መጽሐፍ ለራሱ አሳብ አስረጂ አድርጎ በማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ሊሆን የሚገባው ግን መጽሐፉ የሚያስተላልፈውን ትርጉም በአማኞቹ ዘንድ ያለውንም በመረዳት ጭምር ቢሆን ነበር፡፡
 
ከዚህም አልፎ በአንድ ተቋም ሥር ያሉ አስፈጻሚዎች እርስ በርሳቸው በተለያዩ የሐሳብ ማዕዘናት ላይ ተቀምጠዋል፡፡ አንዱ ሌላውን በጐሪጥ ከማየት አልፎ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሰጠው ትንታኔ አንድን ዘውግ መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ያን ሸሽቼ አመልጠዋለሁ በማለት ሌላ ጽንፍ ውስጥይወድቃል፡፡ … መንገዱ ሁሉ የዳጥና የመሰናክል፤ የተዛባ ትርጓሜና ጽንፈ ኝነትና ጎጠኝነት የበረዙት ሆኖአል፡፡
 
እነዚህን ችግሮች የማይቀበልም ያለ አይመልስም፡፡ ፖለቲከኞችም፣ የሃይማኖት ሰዎችም፤ ሌሎች ማኅበራትና ተቋማትም ችግሮቻችን ከእነዚህ የሚመነጩ እንደሆኑ ይስማማሉ፡፡ ሁሉም በሁሉም ላይ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ሌሎችን ችግሩ ውስጥ አሉ ይላል፤ ራሱ ግን ነጻ ነው፡፡ ሌሎች ከችግራቸው እንዲወጡ ሐሳብ ያቀርባል፤ ርእዮቱን፣ ትንታኔውንም ያቀርባል፤ ከዚህም አልፎ ስለሀገሩም ሆነ ስለሌላው ሐሳብ ሲሰጥ በሐዘንና በቁጭት ነው፡፡ እጅግ የሚያዝነውም ሌሎቹ የእርሱን ሐሳብ ለመስማት ባለመዘጋጀታቸው ነው፡፡ እርሱ ራሱም ግን በሌሎቹ እንዲህ እንደ ሚታዘንበት ትንሽ እንኳ ግምትና ጥርጣሬ የለውም፡፡ ሌሎች እርሱን በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዱትና የትንታኔያቸውም ስሕተት ከዚህ እንደሚመነጭ ይጠቅሳል፡፡ የእርሱ ትንታኔ እንደዚህ ዓይነት ችግር ሊኖርበት እንደሚችል ግን አይገምትም፤ ቢነገሩትም አይሰማም፤ ቢሰማም አያዳምጥም፤ ቢያዳምጥም አይቀበልም፡፡ በሐሳብና በአመለካከት ወጪ እንጂ ገቢ የለውም፡፡
 
የዚህ ሁሉ ችግሩ ምንድን ነው? መደማመጥስ እንዴት ጠፋ? መመለሻውስ ምን ይሆን) … ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሣ እንገደዳለን፡፡ ችግሩ አንድና አንድ ነው፡፡ በየሰው ልቡና የተዘጉ በሮች አሉ፡፡ እነዚያ መከፈት ይገባቸዋል፡፡ ካለበለዚያ ደረቅ ጩኸትና ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡
 
አይሁድ ጌታን /የስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና/ አንዴ የዮሴፍ ልጅ ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋኔን ያደረበት ነው፤ ሌላ ጊዜ በዓል ይሽራል፤ … እያሉ በእርሱ አምነው ከመጠቀም የተከለ ከሉት ሊሰሙት የሚፈልጉት ይህንኑ ብቻ በመሆኑና እውነቱን ለማድመጥ ደግሞ የልባቸው በር ስለተዘጋ ነበር፡፡ መዘጋቱን የማይቀበሉት ደግሞ ለእግዚአብሔራቸው የበለጠ የቀኑ ስለሚመስላቸው ነበር፡፡ ይህን በመንፈስ ቅዱስ የተመለከተው ቅዱስ ዳዊት «መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ፣ የክብር ንጉሥ ይግባ» ሲል ተናግሮአል፡፡ መዝ.23-2  በርግጥም የብዙዎቻችን ችግር ይህ ነው፡፡ እንደተጻፈውም እውነት የሆነው ጌታ ብቻ ነው፡፡ ያለ እውነት እርሱን ልናገኝም፤ ያለእርሱም እውነተኞች ልንሆን አንችልም፡፡ እርሱን ለመቀበል፤ እውነቱንም ለመረዳት ግን የልቡናችን በር ተዘግቷል፤ ተቆልፎአልም፡፡
 
ጌታ ለዮሐንስ ወንጌላዊ እንደገለጸው «በደጅህ ቁሜ አንኳኳለሁ፤ ለሚከፍትልኝ ሁሉ ወደ እርሱ እገባለሁ …» ብሎናል፡፡ ራዕ3-20 በርግጥም አሁን እግዚአብሔር የትው ልዱን የተቆለፈ ደጅ እየመታ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኅኑም፣ ቃለ እግዚአብሔርም፣ ሌላውም ሁሉ ሳያውቁትም ቢሆን እንደነ ሊቀ ካህናት ሀናና ቀያፋ እውነቱን የሚናገሩበት አጋጣሚ አልጠፋም፡፡ ነገር ግን ስለመቻቻል የሚሰብኩት ሲችሉ አይታዩም፤ ስለ እውነት የሚሰብኩትም እውነት መናገር ተስኖአቸዋል፡፡ ስለ ፍቅር የሚነግሩን በጥላቻ ሰክረዋል፤ ስለነጻነት የሚተርኩልንም በቂም አርግዘዋል፤ አፋቸው ተከፈተ እንጂ የልቡናቸው በር አሁንም እንደተዘጋ ነውና፡፡
 
ስለዚህ መፍትሔው የልቡናችን በር መክፈት ነው፡፡ በዘረኝነት፣ በጎሰኝነት፣ በዘውገኝነት፣ በጽንፈኝነት፣ በጥላቻና በመሳሰሉት የተዘጉት ሁሉ መከፈት አለባቸው፡፡ ይምረረንም፣ ይጣፍጠንም፣ እስኪ ልቡናችንን ከፍተን አእምሮአችንን ከጥመት፣ ከፍርሃትና ከጥርጣሬ አጽድተን እናዳምጥ፡፡ በርግጥስ እውነታው የቱ ነው) በትዕግሥትና በበጎ ኅሊና ካደመጥን ሌሎቹ እንኳ ተሳስተው ከሆነ ቢያንስ ስሕተታቸውን በትክክል ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ይህ ደግሞ ስሕተታቸው የምንለውን ገልጦ ለማስረዳትና በሐሳብ ለመሳሳብ ወደ አንድነትም ለመምጣት ይረዳናል፡፡ ያ እንኳ ባይሆን ባልሆኑት እንዳንነቀፍ ለመጠበቅ ያስችለናል፡፡

በሀገር ላይ ለውጥ ይምጣ፣ መነቃቀፎችና መጠላላቶችም ባሉበት ይቁሙ የምንል ከሆነ የተዘጋ ልቡናችን መከፈት ይኖርበታል፡፡ በጊዜው ያልተከፈተ የተዘጋ ደጅ ደግሞ በኋላ ቢከፈት እንኳ እውነቱን ለመረዳት ያስቸግረናል፡፡ በመኃልየ መኃልይ ላይ እንደተገለጸው «እግሬን ታጥቤያለሁ እንዴት አቆሽሸዋለሁ? ልብሴን አውልቄያለሁ እንዴት እለብሰዋለሁ? ተኝቻለሁ እንዴት እነሣለሁ?…» እያልን ምክንያቶችን በመደርደር ደጃችንን ካልከፈትን የእውነት ጌታ ከእኛ ይሔዳል፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ «ብንፈልገውም አናገኘውም»፡፡ መኃ.5-2-7 ከዚህም አልፎ የከተማው ጠባቂዎች የተባሉት ክፉዎች መናፍስት አግኝተው ይቀጠቅጡናል፡፡ ስለዚህም ወደባሰ የኅሊና ጉዳትና ቁስል እንሸጋገራለን፡፡ ያን ጊዜ «… ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው» የተባለው ይፈጸምብናል፡፡ ሮሜ1-28 ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ጆሮአችን ይስማ፤ አእምሮአችን ያድምጥ፤ ልቡናችንም ያስተውል፤ ያን ጊዜ የተዘጋው በር ይከፈታል፤ የቆመውም ጌታ ወደ ልቡናችን ይገባና እንፈወሳለን፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በተለያየ የፍልስፍና ቁልፎች የዘጋነውን የልባችን ደጆች እንክፈት፡፡ አርኅው ልኀተ መኳንንት ይባዕ ንጉሠ ስብሐት፤ መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ፤ የክብር ንጉሥ ይግባ፡፡ መዝ.23-7፡፡

 

የይሁዳ ሰላምታ የቀሪ ሒሳብ ማስተካከያ ነው

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁዳን ከሐዋርያት እንደ አንዱ የመረጠበት ምስጢር እጅግ ጥልቅ ነው፡፡ ይህን ባናውቅ፣ ታሪኩ ባይጻፍና መምህራኑም በየጊዜው ባይነግሩን ኖሮ ዛሬ ብዙዎቻችን እንጨነቅ እንታወክም ነበር፡፡ እርሱን እንድናስታውሰው ያደረገን ደግሞ «ሃይማኖተ አበው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር» ያቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ነበር፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ተሰጥቶት የመንቀሳቀስ ጥያቄ፡፡ ጉዳዩን በቀጥታ ከማየታችን በፊት ግን ጌታችን ይሁዳን ሐዋርያ አድርጎ በመምረጡ ካስተማረን ትምህርት እንነሣ፡፡
በትውፊት እንደሚታወቀው ይሁዳ ሳያውቀውም ቢሆን አባቱን ገድሎ እናቱን አግብቶ ይኖርበት ከነበረው ሕይወት የመጣ ሰው ነው፡፡ ጌታችን ንስሐውን ተቀብሎ እርሱን ከሐዋርያት እናቱንም ከቅዱሳት አንስት ደመራቸው፡፡ ጌታ አምላክ ነውና የይሁዳን ምንነት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ርሱንም እንደሚሸጠው እያወቀ ለምን ሐዋርያው አደረገው) ልንል እንችላለን፡፡ ቢያንስ የሚከተሉትን ነገሮች እንድንማር ነው፡፡

ጌታ ለሚመለሱት ሁሉ እውነተኛ መሐሪ ነው፡፡ በተመለ ሰበት ጊዜ ፈጽሞ ይቅር ብሎ ወደ ማኅበረ ሐዋርያት ማም ጣቱ ፍጹም ፍቅሩንና ለተልእኮ የሚመርጠውም ሰው ተነሳሒ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ጌታችን ድንግላዊ ዮሐንስን ብቻ አልመረጠም፤ ይህ እንግዲህ የሐዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ተነሳሕያን ለቅድስና የሚያበቃ የጽድቅ በር መክ ፈቷን የሚያውጅ ነበር፡፡ በዚህም የጌታችንን ፍጹም ይቅር ታና የምርጫውን ፍጹምነት እንማርበታለን፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ጌታችን ምንም አምላክ በመሆኑ የነገውን የይሁዳን ድርጊት ቢያውቅም ገና ባልበደለው በደል ግን ቀድሞ አልገፋውም፡፡ በዛሬ ማንነቱ ብቻ የተቀበለውን ሰው ክብሩንም ሓሳሩንም የሚወስነው ዛሬውኑ በሠራው ሥራ መሆኑን ለማስተማር ነው፡፡ የዚህ ተጨማሪ ጉዳይ ደግሞ ክፉን ሰው ምክንያት ማሳጣት የሚገባ መሆኑንም ለመናገር ነው፡፡
 
ይሁዳን በመዋዕለ ስብከቱ ከክብር ሳያሳንስ፣ መዓርግ በመስጠት ያኖረው በኋላ ሹመት አጉድሎብኝ ነው እንዳይ ለውም ጭምር ነበር፡፡ በዐሥራት ላይ ሾሞ፤ የገንዘብ ፍላጐቱንም እንደተመኘ ይወጣለት ዘንድ ነጻ ፈቃድን ሰጥቶ ስርቆቱን ታግሶታል፡፡ ጌታ ዐሥራቱን በሌላ ሐዋርያ እጅ ቢያደርገው እንዲጠበቅ እያወቀ ለይሁዳ የሰጠው ጾሩ ቢቀልለት ብሎ ብቻ ሳይሆን ምክንያትም ሊያሳጣው ነውና፡፡ ይህም ከሆነ በኋላ ሲሰርቅ በፍጹም ታግሦታል፡፡ ስለዚህም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ እንደ ይሁዳ ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡትን እንደ ይሁዳ ታግሣቸው ትኖራለች፡፡ የይሁዳን የሌብነት ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን ያየነው ደግሞ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ማታ እጁን ከወጭቱ መስደዱን ጌታ ገልጦ በመናገሩ ነው፡፡ «የለመደ ልማድ ከማድ ያሰርቃል» እንደሚሉት እንኳን ለሌላ ከመጣው ለራሱም ከተሰጠው የሚሰርቅ ምን ያህል ቢከፋ ይሆን) ዛሬም እንደ ይሁዳ ውሳጤ ውሳጢት /ቅድስተ ቅዱሳን/ ገብተው ለእነርሱ ብቻ የተፈቀ ደው ምስጢር ላይ እጃቸውን ያለአግባብ የሚጭኑኮ መጻሕፍቱንና ንዋያቱን የሚሰርቁ ሲያጋጥሙ ቤተ ክርስቲያን ብታዝንም የማትታወከው ነገሩን ቀድማ ከይሁዳ ሕይወት ስለ ተረዳችው ነው፡፡ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁሉ ብዙ ጊዜ ሰምተናቸው ይሆናል፡፡ ችግሮቹም በየጊዜው የሚገጥሙን ስለሆነ አሁን አሁን አያስደንቁንም፡፡

ትልቁና ዋናው ጉዳይ ይልቁንም ለዛሬው ጉዳይችን የሚቀ ርበው ይሁዳ በመጨረሻው ሰዓት የፈጸመው ድርጊት ነው፡፡ ይሁዳ ተጠቃሚ ስለነበር ከሐዋርያት ጋር ጌታን እየተከተለ ይቆይ እንጂ ልቡ እንደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበር፡፡ ይህም የታወቀው ሠላሳ ብር የጐደለበት በመሰለውና ማንነቱ በተነገ ረው ጊዜ ወደ እነርሱ በማምራቱ ነበር፡፡ ጌታም ራሱ ይሁዳ ባለበት ስለይሁዳ የተናገረው በአካል ከሐዋርያት ጋር ቢሆንም በምግባርና በአመለካከት ከእነ ሀና እና ቀያፋ ጋር በመሆኑ ነበር፡፡ በይሁዳ ሕሊና ያለው ግን አሁንም ሌላ ብልጠት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ራሱን የተሻለ አሳቢ አድርጎ ስለወሰደ ከሐዋርያት ተደብቆ ከፈሪሳውያን ገንዘብ ተቀብሎ ጌታን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጌታ በተአምራት ሲሰወርለት ገንዘቡንም አግኝቶ ከሐዋርያትም ጋር ሆኖ ለመኖር ነበር፡፡ ይህ ባልተሳካለት ጊዜ /ጌታ ራሱን አሳልፎ በሰጠ ጊዜ/ ደግሞ ፈጥኖ የታነቀው ሲኦል ገብቼ ካገኘኝም ትቶኝ አይወጣም ብሎ ጽድቁንም በብልጠትና በቀመር ሊፈጽም ነበር፡፡ ሁሉም ግን አልተሳካም፡፡ ድኅነትን በየዋሕነትና በእውነተኛ ንስሐ እንጂ በብልጠትና በቀመር ሊያገኙት አይቻልምና፡፡

ይሁዳ ከማርያም ባለሽቱዋ ቀረብኝ ያለውን ገንዘብ ለማግኘት የተጠቀመበት ስልት «ሰላምታ» ነበር፡፡ ነገሩን ከሊቃነ ካህናቱ ጋር ከጨረሰ በኋላ እርሱ «ሰላም» ብሎ ሊሰጥ በዚህም እነርሱ ጌታን ይይዛሉ፤ ለእርሱ ደግሞ እንደመሰለው በስውር ገንዘቡን ተቀብሎ ከጌታም ጋር ሊኖር ነበር፡፡ የዚህ ነገር ፍጻሜው ታላቅ ጥፋት መሆኑን ብናውቅም ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ይህን ስልት እየተጠቀሙ ደሟን የሚያፈስሱ ጠላቶቿ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያን እንደማይጠፉ እውነተኛውን ትምህ ርት ትቶልን አለፈ፡፡

በዕሥራ ምእቱ መጨረሻ በ«ሃይማኖተ አበው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር» ስም የሚወጡት የሚወርዱት «ውስጠ ዘ» ዎች ጥያቄም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እንደ ይሁዳ ቤተ ክርስቲያን ነበሩ፤ እንደ እርሱ ኮረጆአቸውን ይዘው ከዓለም አቀፍ የፕሮቴስታንት ተቋማት የሚፈልጉትን ሰበሰቡ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን እንደ ይሁዳ አቅርባ ሾመቻቸው፡፡ ከአንድም ሁለት ጊዜ ጥያቄያቸውን ተቀብላ ፈቃድ ሰጥታ ቢሮ ከፍታ ሰየመቻቸው፡፡ እነርሱ ግን ከግብራቸው አልተመለሱምና ማኅ በሩ በይፋ ተዘጋ፡፡ ደግነቱ ይሁዳ ገንዘቡን ለራሱ በተመኘ ጊዜ ሐዋርያትን ጨምሮ ለማሳመጽ «ይህ ሽቶ ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ለምንድን ነው?» በሚል ደስ በሚያሰኝ ቃል ቅስቀ ሳውን ቢያደርግም ከሐዋርያት የተከተለው አለመኖሩ ነው፡፡ ሃይማኖተ አበውም ከጥንቶቹ ቀናዕያንና ንጹሐን አባላቱ እር ሱን የተከተለው የለም፡፡ እነርሱ እንደ ሐዋርያት በታማኝነት አገልግሎታቸውን ቀጥለዋልና፡፡ ይሁን እንጂ በመካከለኛ ዕድሜ ከነበሩ ወጣት ዘማርያን መካከል ለሙሉ ወንጌል፣ ለሬማና ለመሳሰሉት የገበራቸው ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን የሚዘነጉ አይደሉም፤ አሁንም የሚያሳዝኑን ሆነው ቀርተዋልና፡፡

ይህ ሁሉ ሳያንሰው አሁንም በተድበሰበሰ መንገድ እንደገና ፈቃድ ይሰጠኝ፤ ቢሮ ልክፈት የሚለው ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ይህ ጥያቄ ጥንት ማኅበሩን መሥርተው በቅን መንገድ ቤተ ክርስቲያንን አገልግለው፤ የማኅበሩ አመራር ማኅበሩን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሲወሰደውም እነርሱ በቤተ ክርስቲያናቸው ጸንተው ከቀጠሉትና አሁንም እያገለገሉ ካሉት እውተኛ ልጆቿ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ያስደሰት ነበር፡፡ ስለዚህም እነዚህን አካላቱን ለስምና ለዝና ብቻ የሚፈልጋቸውና የተደበቀ ጅምር ዓላማውን /ፕሮቴስታንት የማድረግ ግቡን/ ይዞ ሲንቀሳ ቀስ የኖረው የማኅበሩ አመራር ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ በኩልና ራሱም አድበስብሶ ያለ ማንም ሰው ፊርማ ያቀረበው ጥያቄ ዝም ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡

ማእምረ ኅቡአት ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰወረውን ዓላማ የሚ ገልጥበት ጊዜው ሩቅ ባይሆንም እንዲህ ያለው ቀረቤታ ከይ ሁዳ ሰላምታ ተለይቶ የሚታይ ሊሆንም አይችልም፡፡ ይሁዳ ጌታችንን ሰላም ያለው በአይሁድ ለማስያዝና ቀረብኝ ያለውን ገንዘብ ለማግኘት እንደነበረው ሁሉ የዚህ ጥያቄ ዓላማም ያው ቀሪ ሒሳቤን ላወራርድ የማለት ይመስላል፡፡ ለእርሱ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን የዚህን «ሰላምታ» ትርጉም ነገሮናል፤ መልእክቱንም አስተምሮናል፡፡ ምክንያቱም ጌታ ይሁዳን ንስሐም ሲገባ ያውቀዋል፤ ሊያታልለውም ሲመጣ ያውቀዋል፡፡ ይሁዳ አጥፍቶ ነው የወጣው፤ ስለዚህ ሲመለስ ንስሐ ይጠበቅበት ነበር፡፡ የእርሱ መልስ ግን ቀሪ ሒሳብ የማወራረድ ስለነበር ለንስሐ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ስለዚህም በሰላምታው ሸንግሎ ቀሪ ሒሳቡን ለመውሰድ የመጨረሻ ዕድሉን ተጠቀመ፡፡

የ«ሃይማኖተ አበው» መሪዎችም እውነተኞች ቢሆኑ ኖሮ ማኅበር እንደመሆኑ መጠን ያጠፉትን ጥፋት ራሳቸው ዘርዝረው አቅርበው፤ ለዚያ የዳረጋቸውን ምክንያቱን ለይተው ቤተ ክርስቲያንን ለበደሉበት ይቅርታ ጠይቀው አጥፍተዋቸው ለቀሩት ልጆቿ እውነተኛ ንስሐ ገብተው ቢመለሱ እንዴት ባማረባቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቢቻል ሌላ ሃይማኖት የገቡትን ለመመለስና ለንስሐ ለማብቃት ቢጥሩ በይፋ ስሕተታቸውን ገልጸው ጥፋታቸውን ነግረው ቢመለሱ ኑሮ አሁንም ያለው አገልግሎት እንኳን ለእነርሱ ሌላም ቢፈጠር የሚጋብዝ ነበር፡፡ ይህን ግን አላደረጉትም፡፡ ሊያደርጉት ሲጥሩም አይታዩም፡፡ ይልቁንም ውስጥ ለውስጥና በድብቅ እንደገና የጨለማ ሥራ፤ የይሁዳ ሸንጐ፡፡ ለሃይማኖተ አበው አመራርና ደጋፊዎቹም ሁልጊዜም ቤተ ክርስቲያን አልገባት /አልበራላት/ ብሎ እንጂ እነርሱማ አይሳሳቱማ፡፡ «እግዚአብሔር ሰማዩን ጠቅልሎ ሸሸ» እንዳለ ሰይጣን፤ «እኔ ወረድኩ» ማለትንማ አይሞክራትማ፡፡ እንዲህ ካለማ እውነት ሊወጣው ነው፡፡ አሁንም ግን ለትክክለኛው መንገድ ጊዜው አልመሸም፤ ልቡ ካለ፡፡
 
ካለበለዚያ ግን ጥያቄው ከይሁዳ ሰላምታ ፍጻሜውም ከእርሱ ፍጻሜ አያልፍም፡፡ ለዚህ ጉዳይ የቀድሞ እውነተኞቹ አባላት ዛሬም እንደ ጥንቱ ሓላፊነት አለባችሁ፡፡ በጎውን ዓላማ ማጥፋትና መንገዱን ማሳታቸው ሳያንሳቸው ጥፋታቸውን በስማችሁ ለማሳት መምጣታቸውን መግለጥ ያለባችሁ እናንተ ናችሁና፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችም ጌታቸውን በመመሰል ይሁዳን እንደ አመጣጡ እንደሚመልሱት የታመነው ነው፡፡ ንስሐ ሲገባ ይቀበሉታል፤ አሳልፎ ሊሰጥ ሲመጣማ ጌታችን እንደጠየቀው «ለምን ነገር መጣህ)» ብለው ይጠይቁታል እንጂ ዝም አይሉትም፡፡ ስለዚህም ተጠየቅ፤ ለምን ነገር መጣህ) አብረውህስ ያሉት እነማን ናቸው? ሾተሉና ዱላውስ የማን ነው?

 

Characters display problem

Problem Descirption

The problem with display of characters is based on fonts that are installed on your machine. Fonts can be considered as the drawing instruction/picture for the computer so as to give us the display of the characters we are familiar with. Unfortunately, there are different fonts in use which cover different ranges of character sets.

Note: This site works with Unicode characters and is styled to work with the Nyala gee’z font 

Solutions

The solution to problem of characters display can be resolved as follows:

  1. Download and install font
    You can download the font by clicking here!. After download, put the file in your fonts directory(in windows/fonts for windows xp)
  2. Font embedding (for IE users only) – font embedding is a solution of downloading the font dynamically the first time the page is opened. We have successfully tested the embedding of the "Nyala" gee’z font on this site. If you are an IE user and still have problems with display of characters, please contact us with more details using our contact page.