«ሙሽራ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው»

ከመስከረም 26 እስከ ሕዳር 6 ቀን ያለው ጊዜ ዘመነ ጽጌ ይባላል፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ አምስት ወይም ስድስት እሑዶች ይውላሉ፡፡

    በእነዚህ እሑዶች በቤተክርስቲያን የሚሰጡትን ትምህርቶች አቅርበናል፡፡

    የመጀመሪያ እሑድ

   

ዮሐ. 3-29

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በልደቱ ጌታን በ6 ወር እንደሚቀድመው ሁሉ በይሁዳ አካባቢዎች እየተዘዋወረ «መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» አያለ ማስተማር የጀመረውም ጌታችን ማስተማር ከመጀመሩ 6 ወር ያህል ቀድሞ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተሞላና ትምህርቱ የሰዎችን ልብ የሚነካ ስለነበር፣ አለባበሱም አስደናቂ ስለነበር እንዲሁም እርሱ እስኪመጣ ድረስ አይሁድ ለ300 ዓመታት ያህል ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ አይተው ስለማያውቁ በርካታ ሰዎች ትምህርቱን ተቀብለውትና ተከትለውት ነበር፡፡ እርሱም ስለ ኃጢአታቸው እየወቀሰ፣ ንሰሐ እንዲገቡ እያስተማረና ማድረግና መተው የሚገባቸውን እየነገረ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቃቸው ነበር፡፡

በዚህም ጊዜ አይሁድ ቅዱስ ዮሐንስን «ይመጣል የተባልከው መሲህ አንተ ነህን?» እያሉ ይጠይቁት ነበር፣ እርሱ ግን «እኔ መሲህ አይደለሁም፤ እኔ የእርሱን መንገድ ለመጥረግ ከፊቱ የተላክሁ መንገደኛ ነኝ፤ እርሱ ግን ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ የማጠምቃችሁ በውኃ ነው፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፡፡ እርሱን ለመቀበል በንስሓ ልቡናችሁንና ሰውነታችሁን አዘጋጁ» እያለ ያስተምራቸው ነበር፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ መልኩ ለ6 ወራት ያህል ከአገለገለ በኋላ ጌታ ወደ እርሱ ዘንድ  መጣ፤ ተጠመቀም፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ከእኔ በፊት የነበረው፣ ነገር ግን ከእኔ በኋላ የሚመጣው ያልኳችሁ እርሱ ነው፡፡»  ብሎ ለደቀ መዛሙርቱና አብረውት ለነበሩት አስተማራቸው፤ ብዙዎችም ጌታችንን ተከተሉ፡፡

ከዚህ በኋላ ጌታችን በገሊላ «ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ» እያለ ማስተማር ጀመረ /ማር.1-15/፡፡ ብዙዎችም ተከተሉት፡፡ ደቀ መዛሙርቱንም ይዞ ወደ ይሁዳ ሄደ፡፡ በይሁዳም የጌታችን ደቀመዛሙርት እንደ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሓ ጥምቀት ማጥመቅ ጀመሩ፡፡ /ዮሐ.3-22፤ 4-2/ ብዙ ሰዎችም የጌታችን ደቀመዛሙርት ሆኑ፡፡

«በዚህን ጊዜ ዮሐንስ በሳሌም አቅራቢያ ሪምን በተባለ ሥፍራ ብዙ ውኃ ሳለ ያጠምቅ ነበር፣ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር፡፡ . . . » ወደ ዮሐንስም መጥተው «ረቢ /መምህር/ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው እነሆ ያጠምቃል፤ ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሐሄደ ነው» አሉት፡፡ /ዮሐ.3-23- 27/፡፡

ጠያቂዎቹ ነገሮችን በሥጋዊ ዓይን ይመለከቱ ስለነበር በሁለቱ /በቅዱስ ዮሐንስና በጌታችን/ መካከል ውድድርና ፉክክር ያለ መስሏቸው ነበር፡፡ ንግግራቸው «የአንተ ነገር አበቃለት፣ ሰው ሁሉ ወደዚያ አንተ ወደ መሰከርህለት እየሔሄ ነው፡፡» የሚል መንፈስ ነበረው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ «ከሰማይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ነገርን ገንዘብ ማድረግ አይችልም፡፡ እኔ ክርስቶስ /ይመጣል ተብሎ ትንቢት የተነገረለት አዳኝ መሲህ/ አይደለሁም ብዬ እንደተናገርሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ /ታውቃላችሁ/፡፡» በማለት የሆነው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ዓላማና ፈቃድ እንደሆነ፣ እነርሱም ያሰቡት ነገር ከንቱ መሆኑን፣ እንዲሁም እርሱ ዓላማው ሰዎችን ወደ እውነተኛው መድኃኒት ማቅረብ እና መምራት እንጂ ሰዎችን በዙሪያው መሰብሰብ እንዳልሆነ ነገራቸው፡፡ በመቀጠልም የሰዎች ወደ ጌታችን መሄድ እነርሱ እንዳሰቡት እርሱን የሚያሳዝነው ሳይሆን የበለጠ የሚያስደስተው መሆኑን እንዲህ ሲል ገለጠላቸው፡፡

«ሙሽራ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ድምፁን ለመስማት አጠገቡ የሚቆሙ ሚዜ ግን የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፡፡ እርሱም አሁን ተፈጽሟል፡፡ እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ላንስ ይገባል፡፡»/ዮሐ 3. /

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በሙሽራ በሙሽሪት እና በሚዜ መስሎ የተናገረው የክርስቶስን፣ የቤተክርስቲያንን እና እንደ ራሱ ያሉ አገልጋዮችን ነገር ነው፡፡ በክርስቶስ እና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት በሙሽራ እና በሙሽሪት /በባል እና በሚስት/ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር የሚያመሳስሉት በርካታ ነገሮች አሉ፡፡

–    ሙሽሪትን /ሚስቱን/ የሚመርጣት፣ የሚያጫት ሙሽራው /ባል/ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመረጣትና ሙሽራው እንድትሆን ያደረጋት ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡

–    ባል ሚስቱን መጠበቅ፣ መንከባከብ ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ መውደድ ይጠበቅበታል፤ ክርስቶስም ስለ ቤተክርስቲያን ይህንን አድርጓል፡፡ ሚስት ራሷን ለባሏ ራሷን ማስገዛት አለባት፡፡ ቤተክርስቲያንም ለክርስቶስ እንዲሁ ማድረግ አለባት፡፡

–    ሙሽሪት በሰርጓ ቀን ራሷን አስውባ ትቀርባለች፤ ክርስቶስም ቤተክርስቲያንን ወደ ራሱ ያቀረባት ሙሽራው ያደረጋት በሥጋውና በደሙ አንጽቶ፤ ነውሯን አስወግዶና አስውቦ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን እና የሰው ልጆችን ግንኙነት በሙሽራና በሙሽሪት /በባልና በሚስት/ እየመሰሉ በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም ብዙዎች አስተምረዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ከነበሩት መካከል በፍቅር ግጥም መልክ የተጻፈው መኅልየ መኅልይ ዘሰሎሞን፣ ትንቢተ ሕዝቅኤል /ምዕራፍ 16/፣ ትንቢተ ሆሴዕ /ምዕ.1/ ተጠቃሸ ናቸው፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ በሁለተኛው የቆሮንቶስ መልእክቱ «እናንተ እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁ» /11-2/ ብሎ ጽፏል፡፡ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱም እንዲህ ይላል፤

«ሚስቶች ሆይ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነው ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው፡፡ ባሎች ሆይ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ በቃሉ አማካኝነት በማንፃት እንድትቀደስ. . . አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተክርስቲያን አድርጎ ሊያቀርባት ነው. . . ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይኽንን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን እናገራለሁ፡፡» /5-22-32/፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ነባቤ መለኮትም በራእይ መጽሐፉ ሰማያዊት ቤተክርስቲያን የሆነች አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን የበጉ ሙሽራ ይላታል፡፡

«ቅድሰቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» /21-1-9/፡፡

በዚህ ትምህርት ይህን በሙሽራ እና በሙሽሪት መካከል ባለው የፍቅር ግንኙነት የተመሰለውን የክርስቶስ /የእግዚአብሔር/ እና የቤተክርስቲያን /የእኛን/ ግንኙነት በሁለት ከፍለን እንመለከታለን

    1. እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ምን ይመለከታል
    2. እኛስ በእግዚአብሔር ውስጥ ምን እንመለከታለን

1.   እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ምን ይመለከታል? እርሱ እንደወደደን የሚያደርግ ምን አለ?

በሕዝቅኤል የትንቢት መጽሐፍ ስለዚህ ጉዳይ የተጻፈው እንዲህ ይላል፤

«ኢየሩሳሌም    /እስራኤል/ ሆይ….. በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቆረጠም፤ ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፤ በጨውም አልተወለወልሽም፤ በጨረቅም አልተጠቀለልሽም፤ በጭንም አልታቀፍሽም፡፡ በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጉስቁልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፤ ማንም አላዘነልሽም፡፡

«በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ ‘ከደምሽ ዳኝ አልሁ’. . . አንቺም አደግሽ፤ ታላቅም ሆንሽ፤ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ገባሽ፤ ጡቶችሽም አጎጠጎጡ፤ ጠጉርሽም አደገ፤ . . . በውኃም አጠብሁሽ፣ ከደምሽም አጠራሁሽ. . . ዘይትም ቀባሁሽ፣ ወርቀዘቦም አለበስሁሽ፣. . . በጌጥም አስጌጥሁሽ. . . እጅግም ውብ ሆንሽ፤ ለመንግሥትም የተዘጋጀሸ አደረግሁሽ . . .» /16.4-14/፡፡

እግዚአብሔር የሚያየን ትንሽ ፣በኀጢአት የቆሸሸች ¬፣ የማታምርና የተመልካችን ዓይን የማትስብ ጎስቋላ ነፍስ ሆነን ነው፡፡

ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ሲየየን እርሱ የማያየው ዛሬ የሆንነውን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ልንሆን የሚችለውን ነው፡፡ ኃጢአቶቻችን፣ ቆሻሻችንን አለማማራችንን አይወድም፡፡ ነገር ግን እነዚህን በንስሓ ብናስወግዳቸው የሚኖረን ውበት ያውቃል፡፡ይህም ይስበዋል፡፡

ስለዚህም ጠፍተን ሳለን ካለንበት ከወደቅንበት መጥቶ ከነቆሻሻችን ይወስደናል፡፡ አስተምሮ፣ ለውጦ፣ የተሻልን ያደርገናል፤ አጥቦ ያነጻናል፤ወዳጆቹ ሙሽሮቹ ያደርገናል፡፡

ሰዎች አብረዋቸው እንዲሆኑ የሚፈልጉት በራሳቸው ደረጃ ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ በሌሎችም ሰዎች ዘንድ እንዲሆን የሚጠበቀው ይኸው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይኽን ድንበር ሲያልፉና ከእነርሱ በጣም ዝቅ ካሉ ሰዎች ጋር ተወዳጅተው ማየት ብዙዎቻችንን ያስደንቃል፡፡ እስቲ የእኛን ኃጢአትና የእግዚአብሔርን ቅድስና እናስበውና በመካከላችን ያለውን ልዩነት ደግሞ እናስተውለው፡፡ የእርሱ ከእኛ ጋር መወዳጀት እንዴት አስደናቂ ነው! 

እንግዲህ እግዚአብሔር እኛን የሚወደን እንዲህ ሆነን እየተመለከተን መሆኑን ሁል ጊዜ ማሰብ ይገባናል፤ በእውነት በእርሱ እንድንወደድ የሚያደርግ ምንም መልካም ነገር የለንም፡፡    ስለዚህ ለጸሎት በፊቱ ስንቆም፣ ወደ ቤተክርስቲያንም ስንገባ ከልባችን በፍርሃት ሰግደን ይቅርታውን መጠየቅ አለብን፡፡ «ይኽ የእግዚአብሔር ቤት ነው፣ የቅዱሳን፣ የመላእክቱም ማደሪያ ነው፤ እንዴት እዚህ ልገኝ እችላለሁ?» ልንል ይገባናል፡፡ አስቀድመን እንዳልነው የሚወደው ኃጢአታችንን ሳይሆን ይህንን ስናስወግድ የሚኖረንን ውበት መሆኑን ተረድተን ውለታውን እያሰብን በተሰጠን ጊዜ ለንጽህና ለቅድስና ልንተጋ ይገባል፡፡ስብሐት ለክርስቶስ ዘአፍቀረነ፡፡

2. እኛ በእርሱ ውስጥ ምን እናያለን? በእርሱ እንድንሳብ የሚያደርገን ምን ነገር አለ?

ከላይ እንዳየነው እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዲሁ ነው፡፡ የሰው ልጆች ግን ለመውደድ ምክንያት (ድጋፍ) ያስፈልገናልና እርሱን ለመውደድ የሚያበቁ ነገሮችን እርሱ ራሱ አዘጋጅቶልናል፡፡

ይቅርታው

ከላይ እንደተመለከትነው አምላካችንን ስናስብ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ሊያነጻን መውደዱን እናስባለን፡፡ ይቅር የተባለ ሰው ደግሞ ይቅር ያለውን አብዝቶ ይወዳል፤

እኛ እንደ ጠፋው ልጅ ትተነው ሄደን በጣም ርቀን ያለንን ሁሉ አጥተን ተመልሰን ስንመጣ እርሱ ቆሞ ሲጠብቀን እናገኘዋለን፤ በመምጣታችን ደስ ይለዋል እንጂ በመቆየታችን፣ እርሱን በመካዳችን አይቆጣንም፡፡ ስለዚህ እንደ ማርያም እንተ እፍረት በፍቅር በእግሩ ላይ ሽቱ እንድናፈስ፣ እንድንጠርገው እንገደዳለን፡፡

ሰማያዊ ድኅነት

በዕለተ አርብ ከጌታችን ጎን ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ጌታችን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚወሰደው መሆኑን ተረዳ፡፡ ስለዚህም «በመንግሥትህ አስበኝ» ሲል ተማፀነ፡፡ «ከአንተ ጋር ውሰደኝ» እንደማለት ያለ ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚገኝበት ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ እርሱም ይህንን ሊሰጠን ፈቅዷል፡፡ ይህም እንድንወደው በፍቅሩ እንድንወድቅ ያደርገናል፡፡

ምድራዊ ድኅነት

በችግር ውስጥ የነበረና በእግዚአብሔር ችግሩ የተቀረፈለት ሰው እግዚአብሔርን ይወዳል፡፡ እግዚአብሔር በየቀኑ በተለያዩ መንገዶች ያድነናል፤ በጸሎተ ቅዳሴ ላይ ካህኑ እንዲህ እያለ ይጸልያል፡፡ «ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ  ይቅር ባይና መሐሪ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፣ ከመከራ ሰውሮናልና፣ ጠብቆናልና፣ ረድቶናልና፣ ወደ እርሱም ተቀብሎናልና፣ አጽንቶ ጠብቆናልና. . . እስከዚህም ሰዓት አድርሶናልና»

የፍቅር ዝንባሌ
 
ሰዎች በባሕርያችን መውደድንና መወደድን የመፈለግ ከፍተኛ ዝንባሌ አለን፡፡ ይህ ፍቅርም ዘለዓለማዊ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ «ለዘለዓለም እወድሃለሁ፤ እወድሻለሁ» የሚለው አባባልም ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡

እግዚአብሔር ይኽንን ዝንባሌ በውስጣችን ያስቀመጠው እርሱን እንወድበት ዘንድ ነው፡፡ በዚህ ምድር ያሉትን የቤተሰብ፣ የወንድም፣ የጓደኛ እና ጾታዊ ፍቅሮችንም ያዘጋጀው ከእርሱ ጋር ወደሚኖረን ፍፁምና ሰማያዊ ፍቅር የሚያደርሱ መለማመጃዎች፣ ቅምሻዎች. . . እንዲሆኑ ነው፡፡ፍጻሜያቸው ግን ከእርሱ ጋር የሚኖረን ዘለዓለማዊ ፍቅር ነው፡፡

ስለዚህ ይህ እርሱ ራሱ በውስጣችን ያስቀመጠው ዝንባሌ እርሱን ወደ መውደድ ያመራናል፤ እርሱ ምን ያህል እንደወደደን ስናስብም እኛም ለእርሱ ያለን ፍቅር ይጨምራል፡፡
 
እንግዲህ እግዚአብሔር እኛን ያለዋጋ ወዶናል፤ እርሱን እንወደው ዘንድ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አዘጋጅቶ ቆሞ ይጠብቀናል፤ ደጃችንንም ያንኴኴል፤ ስለዚህም ጊዜያችን ሳያልፍ፤ እርሱም ከእኛ ፈቀቅ ሳይል ጥሪውን ልንሰማ፤ የልባችንን በር ከፍተን በፍቅር ልናስተናግደው ይገባናል፤ ቅዱስ ዳዊት አንድም ስለ ንጽሕት ነፍስ አንድም ንጽሕት ስለሆነች ስለ እመቤታችን በዘመረው መዝሙር ነፍሳችንን እንዲህ ይላታል፤ ”ልጄ ሆይ አድምጪ አስተውዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት እርሽ፡፡ንጉሥ በውበትሽ ተማርኴልና፡፡” /መዝ 46-10-11/

 ወስብሐት ለእግዚአብሔ

«የእግዚአብሔር መንግስት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ህዝብ ትሰጣለች»

አራተኛ እሑድ

 /ማቴ.21-46/

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ የተወለደው፣ ያዳገው፣ እየተመላለሰም የመንግስተ ሰማያትን መቅረብ ወንጌል /የምስራች/ ያስተማረው ለዚህ ዓላማ አስቀድሞ ባዘጋጀው ሕዝብ /በአይሁድ/ መካከል ነው፡፡
አምላክ ሰው ሆኖ ወደዚህ ምድር ሲመጣ በእውነት እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ /አምላክ/ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ይህ ነገር እንደሚሆን አስቀድሞ ተነግሯቸው በተስፋ የሚጠብቁ ህዝቦች ያስፈልጉ ነበር፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ከአብርሃም፣ ከይስሃቅና ከያዕቆብ ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ይህንን ህዝብ የማዘጋጀቱን ሥራ ጀመረ፡፡

በኋላም ይህንን ህዝብ አምላክነቱን በግልጽ በሚያስረዳ መልኩ በብዙ ተአምራት ከግብጽ በማውጣት፣ ህግ እና የአምልኮ ሥርዓት በመስጠት፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር በማስገባት ነገሩን አጠናከረ፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም ነቢያትን በመላክ፣ በማስተማርና ትንቢት በማናገር ቀስ በቀስ ይህ ህዝብ ዓለምን የሚያድነውን የመሲህን መምጣት ተስፋ እንዲያደርግ አደረገ፡፡ እንግዲህ አምላክ ሰው ሆኖ የተወለደው ይህ ሁሉ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ አይሁድ መሲሁ የሚወለድበት ቦታ ቤቴልሔም እንደሆነ ሳይቀር ከተናገሩት ትንቢቶች የተነሳ ያውቁ ነበር፡፡ (ማቴ. 2-5)

ነገር ግን ጌታችን ሰው ሆኖ በተናገረው ትንቢት መሠረት በተወለደ ጊዜ አይሁድ ፣ በተለይም ካህናቱና ጸሐፍቱ /የመጻሕፍት መተርጉማኑ/ ሊቀበሉት አልወደዱም፡፡ «ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል» በማለትም ይከሱት ሊያጠፉትም ይሞክሩ ነበር፡፡

ጌታችን ግን የሰውን ድካም የሚያውቅና የሚሸከም አምላክ በመሆኑ በአንድ በኩል ይህን ችግራቸውን ለመቅረፍ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ አለመሆኑን የሚያስረዱ ነገሮችን /ራሱን ዝቅ በማድረግ ሳይቀር/ እያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ ማንነቱን ተረድተው ይቀበሉትና ይድኑ ዘንድ አምላክነቱን የሚገልጡ ተአምራትን በማድረግ ከ 3 ዓመታት በላይ አስተማራቸው፡፡ እነርሱ ግን ልባቸውን አደነደኑ፡፡

ጌታችንም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ካደረገ በኋላ  ይህንን ዓለም ሞቶ የሚያድንበት ወቅት በደረሰ ጊዜ አምላክነቱንና የመጣበትን ዓላማ በግልጽ ማሳየትና መናገር ጀመረ፡፡ በአህያ እና በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ንጉስነቱን፤ መሲህነቱን በሚገልጥ አኳሃን «በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው» እየተባለለት ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፣ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ «ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት» እያለ በቤተመቅደሱ ንግድ የሚነግዱትን በታላቅ ስልጣን አስወጣቸው፡፡(ማቴ 21)

እነዚህንና ሌሎች አምላክነቱን በግልጽ የሚመሰክሩ ነገሮች ማድረጉን ሲመለከቱ ወደ እርሱ እየቀረቡ «እስኪ ንገረን ይህንን በማን ስልጣን ታደርጋለህ፤ ወይስ ይህን ስልጣን የሰጠህ ማን ነው ብለው ጠየቁት» /ማቴ. 21-23/

ጌታችንም ጊዜው ደርሷልና ማንነቱን፣ የመጣበትን ዓላማ እና ወደፊት የሚሆኑ ነገሮችን በምሳሌ እያደረገ በግልጽ ነገራቸው፡፡ ከእነዚህ ምሳሌዎች አንዱ በእግዚአብሔር እና በሕዝበ እስራኤል /በአይሁድ/ መካከል ያለውን ግንኙነት፣ የእርሱንም ማንነት ያስተማረበት በወይኑ ቦታ ያሉ ገበሬዎች /ጢሰኞች/ ምሳሌ ነው፤ ጌታችን እንዲህ አላቸው፡፡ /ማቴ. 21-35-96/

«ሌላ ምሳሌ ስሙ የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፣ መጥመቂያም ማሰለት ግንብም ሰራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ ሀገር ሄደ፡፡ የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፣ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ፡፡ ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱንም ገደሉት፤  ሌላውንም ወገሩት፡፡ ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ እንዲሁም አደረጉባቸው፡፡ በኋላ ግን ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው፡፡ ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ፡፡ ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት፡፡ እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚወጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋ » እርሱም « ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል » አሉት፡፡

ጌታም እንዲህ አላቸው…… « የእግዚአብሔር መንግስት በእናንተ ትወስዳለች፡- ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች »…. የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ሊይዙትም ሲፈልጉ ሣለ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለዩት ፈሩአቸው፡፡

በዚህ ምሳሌ ወይን ተብለው የተጋለጡት አይሁድ ናቸው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 34-5-1 ላይ

 
«ከግብጽ የወይን ግንድ አወጣህ፣
እህዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ፣
በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፣
ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች
……..
ቅርንጫፎችዋም እስከ ባህር፣ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች» /መዝ. 79-8-11/

ያለውን ቅዱስ አውግስጢኖስ ሲተረጉም የሚከተሉትን ነጥቦች ያስቀምጣል፡
– ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ የተባለው እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ ስላወጣቸው ነው፡፡
– አህዛብን አባረርህ ፤ እርስዋንም ተከልህ የተባለው እግዚአብሔር የተስፋይቱን ምድር ለእስራኤል የሰጠው አሞራውያንን፣ ኬጤያውያንን፣ ኢያቡሳውያንን፣….. ሌሎቹንም በዚያ የነበሩትን ህዝቦች አባሮ በመሆኑ ነው፡፡
– በፊትዋም ስፍራ አዘጋጀህ፣ ሥሮችዋንም ተከልህ የተባለው እስራኤል ማርና ወተት በምታፈሰው ምድር ርስት ሁና ስለተሰጠቻቸው /ስለተተከሉባት/ ነው፡፡
– ቅርንጫፎችዋ እስከ ባህር፣ ቡቃያዋም እስከ ወንዙ ዘረጋች የተባለው ለእስራኤል የተሰጣቸው የተስፋይቱ ምድር የተዘረጋቸው ከሜዲትራንያን /ታላቁ/ ባህር እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ በመሆኑ ነው/ ዘፍ-34-5፣ መዝ-72-8/ /st.Augstine, Exposition on the Psalms, /
ቅዱስ ዳዊት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነቢያትም ህዝበ እስራኤልን በወይን መስለው አስተምረዋል፡፡

ጌታችንም በወይን ቦታ፣ በወይን ቦታ ገበሬዎች እና በወይን ቦታ ባለቤት መስሎ የተናገረው በዘመናት የነበረውን በመግቢያችን ያየነውን የአይሁድን እና የእግዚአብሔርን ግንኙነት ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ምሳሌ አስመልክቶ ባስተማረው ትምህርት /ስብከት/ ላይ «ጌታችን በዚህ ምሳሌ በርካታ ነገሮችን አመልክቷል» ካለ በኋላ የሚከተሉትን ይዘረዝራል፤ /Homily 68

– ከመጀመሪያው ጀምሮ እግዚአብሔር ለህዝቡ የነበረው ቸርነት ጠብቆት መግቦትና ቸርነት
– እነርሱ /አይሁድ/ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ገዳዬች እንደነበሩ /ሰራተኞች ነቢያትን መግደላቸው/
– እነርሱ በዘመናት ሁሉ ክፉ ቢሆኑም እግዚአብሔር ግን ልጁን ከመላክ ወደ ኋላ እንዳላለ
– የብሉይና የሐዲስ ኪዳን አምላክ አንድ እንደሆነ
– ጌታ አይሁድ እንደሚገድሉት አስቀድሞ እንደሚያውቅና እነርሱም ይህ ምን አይነት ቅጣት እንደሚያስከትልባቸው
– የአይሁድን ከተስፋው መውጣትና የአህዛብን የእግዚአብሔር ሕዝብ መባል፡፡

በመጀመሪያ ከዚህ ምሳሌ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር እናያለን፡፡ ወይኑን የተከለው፣ ቅጥር የቀጠረለት፣ መጥመቂያ የማሰላት ፣ የወይኑ ባለቤት ነው፡፡ ይህ ግን የገበሬዎቿ ሥራ ነበር፡፡ እርሱ ግን ሌላውን ሁሉ ሰርቶ ለእነርሱ መጠበቅን ብቻ ተወላቸው፡፡ ይህም እግዚአብሔር ከግብጽ አውጥቶ ህዝቡ ባደረጋቸው ጊዜ ለእነርሱ ባለው ፍቅር ምክንያት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን መግባተን፣ ህግ ፣ ከተማ፣ መቅደስ፣ መሠዊያ፣ የአምልኮ ሥርዓት በመስጠቱ የሚያመለክት ነው፡፡

ይህንንም ሰጥቶ ባለቤቱ ርቆ ሄዷል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ህግጋቱን አለመፈፀማቸውን፣ ቃል ኪዳናቸውን አለመጠበቃቸውን በየቀኑ አለመቆጣጠሩን ትዕግስቱ መብዛቱን የሚያመለክት ነው፡፡

ከዚህ በኋላ የወይኑን ፍሬ ማለትም መታዘዛቸውን፣ መገዛታቸውን አምልኮታቸውን ለመቀበል አገልጋዩቹን ነቢያትን ላከ፡፡ እነርሱ ግን ይህንን ፍሬ  አልሰጡም፡፡ ነቢያቱን ገደሉ፣ አቃለሉ እንጂ ፤ መልሶም በዚህኛው ስራቸው ተጸጽተው ወደ እርሱ ይመለሱ ዘንድ ሌሎች አገልጋዬችን ላከ፡፡ እነዚህንም ግን እንደ ቀደሙት አደረጓቸው፡፡ ከክፉ ነገራቸው ፈቀቅ አላሉም፡፡

በኋላ «ልጄንስ ያፍሩት ይሆናል» ብሎ ልጁን ላከው፡፡ ነበያቱን ሁሉ ባልተቀበሉ ጊዜ ነቢያት ከሠሩት የበለጠ የሚሰራው የነቢያት አምላክ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሁኖ መሲህ ተብሎ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ «…ልጄንስ ያፍሩት ይሆናል» ማለቱ የሚያመለክተው እግዚአብሔር በኋላ እነርሱ የሚያደርጉትን (እንዳይቀበሉት) አለማወቁን አይደለም፡፡ እርሱስ ሁሉን አዋቂ ነው፡፡ ጌታ በምሳሌው እንዲህ ያለው እነርሱ ሊያደርጉ ይገባቸው የነበረውን ለማመልከት ነው፡፡ አዎ፤ ወደ እርሱ ሮጠው መሄድና ይቅርታ ወጠየቅ ነበረባቸው፡፡

እነርሱ ግን ምን አደረጉ፤ «እንግደለው» ተባባሉ፡፡ ጌታችን እንደሚገድሉት ማወቅን ብቻ ሳይሆን የት እንደሚገድሉት /ከከተማ ውጪ/  ማወቁንም «ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት» በማለት አመልክቷል፡፡

ጌታችን ይህንን ካደረገ በኋላ በራሳቸው ላይ እንዲፈርዱ አደረጋቸው፡፡ ይህም ነቢዩ ናታን ንጉስ ዳዊት በኦርዮ ላይ በደል ከፈፀመ በኋላ በራሱ ላይ እንዲፈርድ እንዳደረገው ነው፡፡

እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው «የወይኑ አትክልት ጌታ በመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል»፤ እነርሱም እንዲህ ብለው በራሳቸው ላይ ፈረዱ፤

«ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል፡፡»

ጌታም  የፈረዱት በራሳቸው ላይ መሆኑን በማመልከት «የእግዚአብሔር መንግስት ከእናንት ትወሰዳለች፣ ፍሬዋንም ለሚያደርግ ህዝብ ትሰጣለች» በማለት እነርሱ አስቀድመው ለእግዚአብሔር ህዝብ ለመሆን የተመረጡ ቢሆንም በእምቢተኝነታቸውና መድኃኒታቸውን ባለመቀበላቸው ምክንያት እንደማይድኑ፤ ከእነርሱ ይልቅ ድኅነት ተስፋውንም ሆነ ትንቢቱን ለማያውቁ አሕዛብ እንደምትሆን ነገራቸው፡፡
 
በዚህ ጊዜ አይሁድ ምሳሌዎቹን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን፤ የፈረዱትም በራሳቸው ላይ መሆኑን ተረዱ፡፡ ይህንን ተረድተውም ግን ከክፋታቸው ለመለሱ አልወደዱም ቅዱስ ማቴዎስ እንደሚነግረን ህዝቡን እንደ ነቢይ ስላዩት ህዝቡን ፈርተው ተውት እንጂ ሊገድሉት ፈልገው ነበር፡፡ በስልጣን ፍቅር እና በከንቱ ውዳሴ ፍትወት ዓይናቸው ታውሮ ነበርና ምሳሌው፣ ትንቢቱም ሆነ የህዝቡ ጌታን መቀበል ሊመልሳቸው አልቻለም፡፡

ስለዚህ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጌታን ለመግደል ምክራቸውን /ውሳኔያቸውን/ ፈፀሙ፤ በምክራቸው መሠረትም ይዘው ሰቀሉት፡፡ ከተስፋው፣ ከድኅነቱ ወጥተው ቀሩ፡፡

«የእግዚአብሔር  መንግስት ከእርሱ ተወሰደች፡፡» ተስፋውን ትንቢቱን የማያውቁ አሕዛብ ግን የክርስቶስን  ወልደ እግዚአብሔርነትና መድኃኒትነት ተቀብለው የእግዚአብሔር ሕዝቦች ክርስቲያኖች ተባሉ ፤ «የእግዚአብሔር መንገስት ፍሬዋን ለሚያደርግ ሕዝብ ተሰጠች»   

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

«ለራሱ ገንዘብ የሚያመቻች በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ባለጠጋ ያልሆነ ሰው እንዲህ ነው»

ሦስተኛ እሑድ

 

 /ሉቃ. 12.21/

ጌታችን በይሁዳ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ከህዝቡ አንድ ሰው ቀርቦ፡- «መምህር ሆይ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው» አለው፡፡ ጌታችን ግን ወደዚህ ምድር የመጣው፣ ለመለኮታዊ /ሰማያዊ/ ዓላማና የሰውን ልጆች ለማዳን እንጂ በሰዎች ምድራዊ ኑሮ ገብቶ ሃብትን ለማከፋፈል ባለመሆኑ፣ ዳግመኛም እርሱ የመጣው ራስን ለሰው መስጠትን፣ ፍቅርንና አንድ መሆንን የምትሰብከውን ወንጌልን ለመስራት በመሆኑ «አንተ ሰው ፈራጅና አካፋይ እንዲሆን በላያችሁ ማን ሾመኝ?» በማለት ይህንን ሊያደርግ እንደማይወድ ከተናገረ በኋላ አጋጣሚውን በመጠቀም አብረውት ለነበሩት እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፤ «የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፤ ከመጎመጀትም ሁሉ ተጠበቁ»፡፡
ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል፡- «አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት፡፡ እርሱም፡- ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ፡፡ እንዲህ አደርጋሁ ጎተራዬን አፍርሼ ሌላ እሰራለሁ በዚያም ፍሬዬንም በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፡፡ ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ ዕረፊ፤ ብዩ፤ ጠጪ፤ ደስ ይበልሽ፤ እላታለሁ አለ፡፡ እግዚአብሔር ግን አንተ ሰነፍ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዷት ይፈልጓታል፡፡ ይህስ የሰበሰብከው ለማን ይሆናል? አለው፡፡ ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው፡፡»

ጌታችን በምሳሌ ካስተማረ ከዚህ ትምህርት ሁለት ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡

1. ስለ ሀብት ያለን አመለካከትና የሃብት አጠቃቀማችን ምን ሊሆን እንደሚገባ፤- ይህ የጌታችን ትምህርት ለሐብት ያለን አመለካከትና የሐብት አጠቃቀማችን ክርስቲያናዊ መሆን  እንዳለበት የሚያስተምር እንጂ ሐብትን እና ባለሐብትነትን ወይም ባሐብቶችን የሚነቅፍ አስፈላጊ አይደሉም የሚል አይደለም፡፡

ሐብት /ገንዘብ/ መሰብሰብ፣ መማርና ማወቅና በተለያየ ደረጃ መመረቅ፣ ወይም እነዚህን የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ለአንድ ሰው የሕይወቱ ግብ ሊሆኑ አይገባቸውም፤ አይችሉም፡፡ ቁሳዊና አእምሮአዊ ሐብቶች ሲገኙ ጠቃሚ የሚሆኑትና ትርጉም የሚኖራቸው እንደ የአንድ ዓላማ /ግብ/ ማስፈፀሚያ መንገዶች /ስልቶች/ ሲታሰቡ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነና፣ ለምን እንደምንፈልጋቸው፣ ሲገኙም ለምን እንደምናውላቸው በትክክል ሳናውቅ /ሳናስብ/ ብንሰበስባቸው ሲገኙ ትርፋቸው «ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ» ብሎ መጨነቅና ከዚያም ያለ ዓላማ የተሰበሰቡ ስለሆኑ በእነርሱው መገኘት ብቻ መደሰት መጀመር «አንቺ ነፍስ ለብዙ ዘመን የሚቀር በርከት አለሽ… ደስ ይበልሽ» ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡

እኛ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ስንኖር ዓላማችን ድኅነት /መዳን/ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት ሐብት /ቁሳዊ፣ አእምሮአዊ…/ ለማግኘት ማሰብና ለዚህም መውጣት፣ መውረድ፣ መድከም የሚገባን፤ ካገኘነውም በኋላ ልንጠቀምበ የሚገባን፤ ከዚሁ አለማችን ከድኅነት አንጻር /ወደዚያ እንደሚያደርስ መንገድ/ ብቻ ነው፡፡ ባዕለ ጠግነታችን እንዲህ ያለ ካልሆነ «አንተ ሰነፍ»፣ «በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ ያልሆንክ» አስብሎ ያስወቅሳል፡፡

ትክክለኛው የሀብት አጠቃቀምና «በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ የሚያደርግ» አካሄድስ እንዴት ያለ እንደሆነ?

ቅዱስ አውግስጢኖስ /Augstine/ እና ቅዱስ አምብሮስ /Ambrose/ የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜዎቻቸው ላይ የሚከተለውን አስተምረዋል፤

ቅዱስ አውግስጢኖስ

ጠቢቡ ሰሎሞን  በመጽሐፈ ምሳሌ «ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብት ነው» ይላል /ምሳ-13-8/ ይህ ቂል ሰው ግን እንዲህ ያለ /ለነፍሱ ቤዛ የሚሆን/ ሃብት አልነበረውም፡፡ በግልጽ እንደሚታየው ለድሆች እርዳታ በመስጠት /እፎይታ በመሆን/ ነፍሱን እያዳናት አልነበረም፡፡ የሚጠፉ ሰብሎችን /ፍሬዎችን/ እያሰባሰበ ነበር፤ እደግመዋለሁ፤ በፊቱ ሊቆም ግድ ለሆነው ለጌታ ምንም ነገር ባለመስጠቱ ምክንያት ለመጥፋት ተቃርቦ ሳለ እርሱ ግን የሚጠፉ ሰብሎችን ይሰበስብ ነበር፡፡ ለፍርድ ሲቀርብና «ተርቤ አላበላኝም» የሚለውን ቃል ሲሰማ የት ይገባ ይሆን? ነፍሱን በተትረፈረፈና አላስፈላጊ በሆነ ምግብና ድግስ ለመሙላት እያቀደና እነዚያን ሁሉ የተራቡ የድሆች ሆዶች በልበ ሙሉነት ችላ እያለ ነበር፡፡ የድሆች ሆዶች ከእርሱ ጎተራ በተሻለ ሀብቱን በደኅንነት ሊጠብቁለት የሚችሉ ቦታዎች መሆናቸውን ግን አልተረዳም ነበር፡፡ …ሃብቱን በድሆች ሆድ ውስጥ ቢያስቀምጠው ኑሮ በምድር ላይ በእርግጥም ወደ አፈርነት ይለወጥ ነበር፤ በሰማያት ግን ከምንም በላይ በደኅንነት ይቀመጥለት ነበር፡፡ ለሰው ነፍስ ቤዙው ሀብቱ ነው፡፡

ቅዱስ አምብሮስ

ይህ ሰው እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ሳይረዳ ለእርሱ ጥቅም በሌለው መልኩ ሀብትን እያከማቸ ነው… የዚህ ዓለም ነገሮች ሁሉ የሚቀሩት በዚህ ዓለም ነው፤ ምንም ያህል ሃብት ብንሰበስብም ለወራሾቻችን ትተነው እንሄዳለን፡፡ ከእኛ ጋር ልንወስዳቸው የማንችላቸው ነገሮች ደግሞ የእኛ አይደሉም፡፡ የሞቱ ሰዎችን የሚከተላቸው መልካም ምግባር ብቻ ነው፡፡ ርኅራሄና በጎነት ብቻ ነው፡፡ ወደ መንግስተ ሰማያት መርቶ የሚወስደን ይህ ነው፡፡

በማይረባው ገንዘብ በመንግስተ ሰማያት ያማሩ መኖሪያዎችን እንግዛ ነው፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ አስተምሮናል «የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ ለራሳችሁ ወዳጆችን አድርጉ፡፡» /ሉቃ. 16-9/
/Ancient Christian Commentary on Scripture/ volume3 /Luke/ page 208/

2/ ሁለተኛው ከዚህ ጌታችን በምሳሌ ካስተማረው ትምህርት የምንማረው ያለነውና የምንኖረው እያንዳንዷን ቀን የምናሳልፈው በእርሱ ቸርነት መሆኑን መዘንጋት እንደሌለብን ነው፡፡

ይህ ሰው ልክ ዕድሜውን ሰፍሮ በእጁ የያዙ ይመስል፣ ወይም ዕድሜ እንደ ሰብል ተዘርቶ ከመሬት ይገኝ ይመስል እንዲህ ሲል እናገኘዋለን፡፡ «አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለው፣ ዕረፉ ብዬ ጠጪ ደስ ይበልሽ….»

ነገር ግን እንኳን ለብዙ ዘመናት ሊኖር ቀርቶ ያቺን ሌሊት አልፎ የሚቀጥለውን ቀን ፀሐይ እንኳን እንደማያይ ተነገረው፡፡ «አንተ ሰነፍ፤ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዷት ይፈልጓታል፡፡» ተባለ፡፡

ይህ የሁላችንም ችግር ነው ስለ ኑሯችን፣ አገልግሎታችን እና ህይወታችን ስናቅድ የእግዚአብሔርን ቸርነት ረስተን ሁሉ ነገር በእጃችን ያለ እናስመስለዋለን፡፡ ይህ ግን አለማስተዋልና «አንተ ሰነፍ» አስብሎ የሚያስወቅስ ነው፡፡

ማድረግ የሚገባንን ግን ከቅዱስ ዳዊት እንማራለን፤ ቅዱስ ዳዊት ደካማነቱን በመታመን እንዲህ እያለ በትሁት ልብ ይዘምራል፤

«ሰው በዘመኑ እንደ ሳር ነው
እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል
ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና
ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና»
የእግዚአብሔር ምህረት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፡፡» /መዝ.102-11/

እኛም እንደርሱ ህይወታችን አንድ ጊዜ ወጥቶ ወዲያው ፀሐይ እንደሚያጠወልገው ሳር፣ ከበቀለ በኋላ ለዓመት እንኳን መቆየት እንደማይችል የዱር አበባ ቆይታው አጭርና በእኛ እጅ ያልተወሰነ መሆኑንና ደካማነታችንን ማሰብ ይገባናል፡፡ ይህንን አስበንም እንደ ቅዱስ ዳዊት፤

አባት ልጆቹ እንደሚራራ እግዚአብሔር እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤
ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና…አቤቱ አፈር እንደሆንን አስብ፤
ሰው ዘመኑ እንደ ስር ነው፡፡»

እያልን ደካማነታችንን በማመን ፈቃዱን፣ ቸርነቱን ልንጠይቅ፤ ይገባናል፡፡ ዕቅዳችንም፤ ቅዱስ ያዕቆብ እንዳስተማረን ከአፍ ሳይሆን ከልብ «እግዚአብሔር ቢፈቅድ… ይህንንና ያንን እናደርጋን /ያዕ.4-15 / የሚል መሆን አለበት፡፡

 
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
St.Mary.JPG

ቅድስት ድንግል ማርያም

St.Mary.JPG

ጾመ ነቢያት

ዘመኑ ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለ ተፈጸመበት እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ስለ ጾሙ ስለ ጸለዩ ነው፡፡ ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡

ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር «የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡ በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት ይህ ጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡

ዘመነ ስብከት

ከታኅሣሥ 7 ቀን እስከ ታኅሣሥ 13 ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት ናቸው፡፡ ምን ጊዜም ወደ ታኅሣሥ 6 አይወርድም ወደ 14ም አይወጣም፡፡ ስብከት ማለት ዐዋጅ ትምህርት ማለት ነው፡፡ ይህም ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ያለው ትውልድ የሚታሰብበት ፤ ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያት በትንቢት፣ ዳዊት በመዝሙሩ በብዙ ምሳሌ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ የተናገሩት የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ መዝ.143-7 ፤ ኢሳ 64-1፡፡ የሚዘመረው መዝሙር «ወልደ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ፤ ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን» የሚል ነው ቅዱስ ያሬድ፡፡ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩለትንና ሱባዔ የቆጠሩለትን ሐዋርያት ያላቸውን ትተው ተከተሉት ፈቃዱንም ፈጸሙ፡፡ ስለዚህ ምእመናን ክፉ ሐሳባቸውን አርቀው ርኩሰትን አስወግደው ፍጹም ለእግዚአብሔር እንዲገዙ ትምህርት ይሰጣል፣ ስብከት ይሰበካል፡፡ የሚነበበውም ምንባብ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ ዮሐ.1-44-49 ፤ ዕብ.1-1-2፡፡

ብርሃን

ከስብከት ቀጥሎ ያለችው ሰንበት ስትሆን እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስተምህሮ ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን ያለው 14 ትውልድ ይታሰብበታል፡፡ ክቡር ዳዊት «አቤቱ ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42-3/ እያለ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ወገን እንዲወለድ ትንቢት ስለተናገረ ይህ የሚታሰብበት ነው፡፡ ነቢዩ ዓለም በጨለማ ስለሆነች ብርሃንህን ላክ፣ ሐሰትና የሐሰት አባት ነግሦባታልና እውነትህን ላክ አለ፡፡ ወልድን ላክልን ማለቱ ነው፡፡ ይህንም ቅዱስ ዮሐንስ «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ» ብሎ ሲመሰክር ጌታም ራሱ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም» ብሎ ተናግሯቸዋል፡፡ ዮሐ. 8-12 እንዲሁም ብርሃንን እውነት ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ላክልን ሲል ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ስደድልን ማለቱ ነው፡፡

ከጨለማ ወደ ብርሃን አውጣን፣ ሥጋህንና ደምህን ስጠን ሲልም ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሚዘመሩት መዝሙራት «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ወይዜንዎ ለጽዮን በቃለ ትፍሥሕት፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፣ የምስጋናን ቃል ለጽዮን የሚነግራት ወልድ በክብር፣ በጌትነት እንደሚመጣ አስቀድሞ በኦሪት ነገረ፤ አስታወቀ፡፡» የሚሉ ናቸው፡፡ ንስሐ ከመግባት ቸል እንዳይሉ ይነግራቸዋል፡፡ ነቢያት የጥል ግድግዳን ሰብሮ መለያየትን አጥፍቶ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣቸውን ሽተው ውረድ ተወለድ አድነንም እያሉ ጮኹ፣ እውነተኛ ብርሃን ጌታችን ጊዜው ሲደርስ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ በመምጣቱም በጨለማ ያለው በብርሃን እንዲገለጥ ለሰው ልጆች እግዚአብሔርን የሚያውቁባት ዕውቀት ተሰጠች፡፡

ኖላዊ

ኖላዊ ተብሎ የሚጠራው ከብርሃን ቀጥሎ ያለው ሳምንት ነው፡፡ የቃሉ ፍች እረኛ ማለት ነው፡፡ እረኞች ለበጎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሣር ውኃ ሳያጓድሉ እንዲጠብቁ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በነፍስ በሥጋ የሚጠብቅ ቸር እረኛ ነው፡፡ ይኽንን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲያብራሩ ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው 14 ትውልድ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ዘመን እሥራኤላውያን ከሀገራቸው ተሰደው በባቢሎን 70 ዘመን ከኖሩ በኋላ ዘሩባቤልን አንግሦላቸው ይዟቸው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በፊት እሥራኤል ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ተበታትነው ሲኖሩ ነቢያት ከኪሩቤል ላይ የሚገለጥ እረኛቸው እንዲገለጥ የእሥራኤል ጠባቂያቸው ሆይ፣ አድምጥ እያሉ የጠየቁበት መታሰቢያ ነው፡፡ መዝ.79-1-3፡፡

መዝሙሩም «ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃለ እግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅና ቃሉ የሆነ ክርስቶስ ከላይ የወረደ ወደ ዓለም የመጣ እረኛ» የሚል ሲሆን የሚነበበው ደግሞ አንቀጸ አባግዕ የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ ዮሐ.10-1-22፡፡ እረኛ የሌለው በግ ተኩላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ከትጉኅ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም በሲኦል አጋንንት በርትተውበት ሲጠቀጠቅ ኖሯል፡፡ እንዲሁም ከመንጋውና ከእረኛው የተለየ በግ እንዲቅበዘበዝ አምላኩን ዐውቆ አምልኮቱን ከመግለጽ የወጣው ሕዝብ በየተራራው መስገጃዎችን እየሠራ የሚታደገውን አምላክ በመፈለግ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር» እንዳለ፡፡ 1ኛ ጴጥ.2-25፡፡ ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚቅበዘበዙትን ሕዝቡን በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንዲወለድ ስለተናገሩ ያን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተባለ፡፡

ገሃድ/ ጾመ ድራረ ጥምቀት

ይህ ጾም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት በማሰብ የጥምቀትን ዋዜማ መጾም ነው፡፡ ይህም ማለት በጥምቀት ዋዜማ ከምግብ መከልከል ነው፡፡ የሚቆርብ ሰው አክፍሎ የሚያድር ስለሆነም የጥምቀትን ድራር መጾም ነው፡፡ ሐዋርያት «ልደት ጥምቀት ዓርብ ረቡዕ ቢውል በሌሊት ቀድሰው ሥጋውን ደሙን ይቀበሉ፤ ከሌሊቱ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ብለው አይፍረዱ» ብለዋል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15/፡፡ የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የጥሉላት ምግብ በጠዋት በመብላት ምእመናን በዓሉን እንዲያከብሩ ታዟል፡፡

ይህም እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ የእግዚአብሔር በዓላት በመሆናቸው ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ በሚውልበት ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ ማክሰኞንና ሐሙስን በመጾማችን ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል፡፡ በዚህም የጾምና የበዓል ማክበር ሥራ ይከናወናል፡፡ የጥምቀትን ዋዜማ ጥሉላት መባልዕትን መተው ነው፡፡ ይህንንም እንደ ዘይቤው ገሀድ ይለዋል፣ መገለጫ፣ ግልጥ፣ ይፋ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ጋድ ይለዋል፣ ለውጥ፣ ልዋጭ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ረቡዕ ዓርብ ሲውል በዚያ ለውጥ ማክሰኞ ሐሙስ ይጾማልና ጋድ አለው፡፡ እንዲሁም አንድ ጊዜ ሲጾም አንድ ጊዜ ሲቀር እንዳይረሳና ቅዳሜ ወይም እሑድ በሰንበት ቀን ይጾሙ ዘንድ አይቻልም፣ ነገር ግን እህል ውኃ እንጂ ጥሉላት ከመብላት መጠበቅ ይገባል፡፡

ልደት የሚውልባቸው ረቡዕና ዓርብ ቢሆኑ የፍሥክ /የሚበላባቸው/ ቀናት ሆነው እንዲከበሩ ሐዋርያት ያዘዙ ቢሆንም በዋዜማው የሚገኙት ማክሰኞና ሐሙስ ከጾመ ነቢያት ጋር የተያያዙ ስለሆኑ መጾማቸው ግድ ነው፡፡ ሆኖም የነቢያትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች በመላው የጾሙ ቀናት ሲበሉ ቆይተው በዋዜማው ብቻ ገሀድ ነው ብለው ይጾማሉ፡፡ ነገር ግን ለጾመ ነቢያት ገሀድ የለውም፡፡ ጾሙ የጥምቀት ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለጾመ ነቢያት ገሀድ እንዳለው የሚናገሩም አሉ፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ እስከ ምሽት መጾሙን ነው፡፡ ይህም «አድልው ለጾም፤ ለጾም አድሉ፡፡» እንዲሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቢጾም የሚያከራክር ወይንም ስህተት ነው የሚያሰኝ አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

ነቢያት ይወርዳል፣ ይወለዳል ብለው የተናገሩት ቃል ይፈጸም ዘንድ የሰው ልጆችም ድኅነት ማረጋገጫ እውን ይሆን ዘንድ እንደ ጾሙ እንደ ጸለዩ በልደቱም እንስሳት፣ ሰዎች እንዲሁም መላእክት በአንድነት በደስታ እንደዘመሩ የእኛም ደስታ የተረጋገጠበት ነው፡፡ በመሆኑም በፍቅር፣ በጾም በጸሎት ዛሬም እናስበዋለን፡፡ ነቢያት በረከት እንዳገኙ እኛም ከእግዚአብሔር በረከት እናገኛለን፡፡ ለዚህም አምላካችን ይርዳን አሜን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የድንግል ማርያም ስሞች

ከመንግስተአብ
 
ስም ለፈጣሪም ሆነ ለፍጡራን ለመጠሪያነት ያገለግላል፡፡ ይህም ስም አንዱን ከሌላው ለይቶ የሚያሳውቅ የፍቅር መግለጫ ነው፡፡ በጽሑፍም ሆነ በቃል ማስተላለፍ የሚቻለው በስም አማካኝነት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ለሚወዳቸውና ለመረጣቸው ሰዎች ስም ያወጣ እንደ ነበር ሁሉ፤ ሰዎችም ያወጡ መጠሪያ ይሰጡ ነበር፡፡ ይህም ስም የሚሰየመው ወይም መጠሪያ ሆኖ የሚሰጠው እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን መሠረታዊ ምሥጢርና ትርጉም አለው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን «እስመ ስሙ ይመርህ ኀበ ግብሩ» በማለት ስም ግብርን ሁኔታን እንደሚገልጽ መሥክረዋል፡፡
St.Mary.jpg

 
 
 
 
 
 
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች ምስክርነት ከስም አጠራሯ በመጀመር ለስመ ድንግል ማርያም ዘርፍ /ቅጽል/ አልያም ምትክ አድርገን የምንጠቀምባቸው ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው ንጽሕናዋን፣ ቅድስናዋን፣ ድንግልናዋን፣ ወዘተ የሚመሰክሩ በርካታ ስሞች አሏት፡፡ ስለ እመቤታችን ስሞች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ፍቅር የተነሣ አብዝተው፣ አምልተው፣ አስፍተው፣ አመስጥረው ከተረጐሙት ጥቂቱን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
ምልዕተ ጸጋ፡- መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ይህን ቃል ከእመቤታችን በቀር ለማንም እንዳልተነገረ እንረዳለን፡፡ አዳም ከፍጥረት ሁሉ አልቆ አግንኖ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጥረት ነበር፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ምክንያት የተሰጠው ጸጋ ተገፈፈ፡፡ አብርሃም ወዳጁ ነበር፡፡ ዳዊትም እንደልቤ ያለው ነው ሙሴንም ከ570 ጊዜ በላይ ቃል በቃል አነጋግሮታል፡፡ በዘመነ ሐዲስም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን «አንተ ብፁዕ ነህ» ብሎ መስክሮለታል ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው ቃል እንደ እመቤታችን «ጸጋ የሞላብህ» «ጸጋ የሞላብሽ» የተባሉ ሌሎች አልተገኙም፡፡ እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ ተመርጣ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ እግዚአብሔር የጠበቃት፣ ያደረባት «የከተመባት ረቂቅ ከተማ» መሆኗን መልአኩ በመሰከረበት ቃል «ምልዕተ ጸጋ» እያልን እንጠራታለን፡፡ ሉቃ.1-26፡፡ እመቤታችን የተለየች ናትና «ጸጋ የሞላብሽ» /የጸጋ ግምጃ ቤት/ ተብላለች፡፡
እምነ /«ም» ጠብቆ ይነበብ/ ጽዮን፡- እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን አባት «አባታችን ሆይ» ብለን እንደምንጠራው ሁሉ ወላዲተ አምላክንም እናታችን ብለን እንጠራታለን፡፡ ማቴ.6-9፡፡ ቅዱስ ዳዊትም «እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፡ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል» በማለት እመቤታችን አማናዊት ጽዮን መሆኗን አስረድቷል፡፡ መዝ.86-5፡፡ እምነ ጽዮን ማለት እናታችን ጽዮን ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያይቱ የሰው ልጆች ሁሉ እናት ሔዋን አማካኝነት ከርስታችን ወጥተን መጠጊያ አጥተን ነበር በዳግማዊቱ ሔዋን በድንግል ማርያም ደግሞ ወደ ርስታችን ተመልሰናልና እናታችን ጽዮን እንላታለን፡፡ ጽዮን ማለት አንባ መጠጊያ ማለት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስም ድንግል ማርያምን ጽዮን በማለት ይጠራታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት «እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና ማደሪያውም ትሆን ዘንድ ወድዶአታልና እንዲህ ብሎ ይህች የዘላለም ማደሪያዬ ናትና በዚህች አድራለሁ፡፡» መዝ.131-13፡፡ በማለት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ልዑል እግዚአብሔር ከሴቶች ሁሉ ለይቶ ድንግል ማርያምን ለእናትነት የመረጣት መሆኑንና ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ የወደዳት መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ መዝ.47-12፤86-5፡፡
መድኃኒታችን በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ በመስቀሉ ላይ ሳለ ለፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ «እነኋት እናትህ» በማለት በደቀ መዝሙሩ አማካኝነት እናቱን ድንግል ማርያምን ሥጋውን ለቆረሰላቸው ደሙን ላፈሰሰላቸው ምእመናን እናት ትሆን ዘንድ ሰጥቷታልና ከላይ እንዳየነው ጽዮን የድንግል ማርያም ስም ነውና ጌታችን እናት አድርጎ የሰጠንን እመቤት እምነ ጽዮን /እናታችን ጽዮን/ እንለታለን፡፡
እመ ብርሃን፡- እመ ብርሃን ማለት የብርሃን እናት ማለት ነው፡፡ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» ያለውን ብርሃነ ዓለም /የዓለም ብርሃን/ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን የወለደች ናትና የብርሃን እናቱ /እመ ብርሃን/ ትባላለች፡፡ ዮሐ.8-22፡፡ ጌታውን ይወድድ የነበረና ጌታውም ይወደው የነበረ የከበረ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ዮሐንስ «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡» በማለት የመሰከረለትን ጌታ በብሥራተ መልአክ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አማናዊውን /እውነተኛውን/ ብርሃን ጌታችንን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ የወለደች በመሆኗ እመ ብርሃን እንላታለን፡፡ ሊቁ «እመ ብርሃን አንቲ ነዓብየኪ በስብሐት ወበውዳሴ፡- አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ የብርሃን እናት ነሽና አንቺን በክብር በምስጋና እናገንሻለን» በማለት እንዳመሰገናት፡፡
ሰአሊተ ምሕረት፡- ሰዓሊተ ምሕረት ማለት ምሕረትን የምትለምን ማለት ነው፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ምስክርነት እንደምናገኘው ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘች እመቤት ናትና ልመናዋ /ምልጃ ጸሎቷ/ ይሰማል የእናት ልመና አንገት አያስቀልስ ፊት አያስመልስ ነውና፡፡ ሉቃ.1-30፡፡
በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኙ ቅዱሳን ምሕረት ቸርነትን ለምነው አግኝተዋል፡፡ ዘፍ.18-3፣ 23-32፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን በፊቴ ሞገስን ስላገኘህ በስምህ ስላወቅሁህ ስለ ሕዝቡ የለመንኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ ብሎታል፡፡ ዘጸ.33-12-20፡፡ «ስለ ሙሴ ቃልም ዘወትር ለሕዝቡ ይራራላቸው ነበር» ዘጸ.32-11-14፡፡ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ በለመነ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ ይለው ነበር፡፡ ዘኁ.14-20፡፡ በመልአከ ብሥራት በቅዱስ ገብርኤል «በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻል» ተብሎ የተመሰከረላት ድንግል ማርያም የተሰጣት ሞገስ እንደ እናትነቷ ከሁሉ የበለጠ በመሆኑ አጠያያቂ አይደለምና ሰአሊተ ምሕረት እንላታለን፡፡ ማርያም ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ዠማዕምንት ሰአሊተ ምህረት ለውሉደ ሰብእ፡- ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናት ለሰዎች ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት» /ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ አንቀጽ 6/
እመቤታችን፡- እመቤት ማለት በአንድ ቤተሰብ መካከል አስተዳዳሪና ሓላፊ የሆነች ታላቅ ሴት ማለት ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን «ማርያም» የሚለውን በምሥጢራዊ ዘይቤ ሲተረጉሙ እግዝእተ ብዙኃን /የብዙኀን እመቤት/ ብለው ተርጉመውልናል፡፡
በአዳምና በሄዋን አማካኝነት ወደ ዓለም የገባውን መርገም የሻረ ጌታ እግዚአብሔር ከእርስዋ በመወለዱ እምቤታችን /የብዙዎች እመቤት/ ትባላለች፡፡ ሮሜ.5-6-11፡፡ እንዲሁም ዓለም ሁሉ በዳነበት በክርስቶስ የማዳን ሥራ ያመን ክርስቲያኖች ሁሉ በክርስቶስ አንድ ቤተሰብ በመሆናችን ቅድስት እናቱ ድንግል ማርያም እመቤታችን ናት፡፡ ዮሐ.19-26፡፡ ልጇ ጌታችን ነውና እርሷም እመቤታችን ናት፡፡ ሉቃ.1-43፡፡
ቤዛዊተ ዓለም፡- የዓለም መድኃኒት ማለት ነው ድንግል ማርያም የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን በመሆኗ ቤዛዊተ ዓለም እንላታለን በልጇ ቤዛነት ድነናልና፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም /ለድኅነተ ዓለም/ በቀራንዮ ኮረብታ የቆረሰው ሥጋ ያፈሰሰው ደም ከድንግል ማርያም የነሣው በመሆኑ ቤዛዊተ ዓለም ትባላለች፡፡ ዕብ.9-22፡፡ የሕያዋን ሁሉ እናት ድንግል ማርያም ለሔዋን ካሣዋ እንደሆነች ሁሉ ለአንስተ ዓለም ሁሉ ካሣ ቤዛ ናት ስድበ አንስትን ወቀሳ ከሰሳ አንስትን አስቀርታለችና፡፡ እንዲሁም ለዓለሙ ሁሉ የምታማልድ በልመናዋ ፍጥረትን የምታስምርና መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባ በመሆኗ ቤዛዊተ ዓለም እንላታለን፡፡
ወላዲተ አምላክ፡- ወላዲተ አምላክ ማለት አምላክን የወለደች ማለት ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡» በማለት የጌታችንን አምላክ ወልደ አምላክነት የድንግል ማርያምን እመ አምላክ ወላዲተ አምላክነት አስረድቶአል፡፡ ሉቃ.1-35 ቅድስት አልሳቤጥም «የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?» ሉቃ.1-44 በማለት እንዳስረዳችው ድንግል ማርያም ጌታችንን የወለደች የጌታችን እናት ናትና ወላዲተ አምላክ እንላታለን፡፡ ድንግል ማርያም «ወላዲተ አምላክ» «አምላክን የወለደች» ተብላ እንድትጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ በ200 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ተዘጋጅቶ በቅዱስ ቄርሎስ አፈ ጉባኤነት የተመራው 3ኛው ዓለም አቀፋዊ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ የቀረበው የንስጥሮስ የክህደት ትምህርት «ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባትም» የሚል ሲሆን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ንስጥሮሳዊውን ትምህርት አውግዘው ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም የነበረውን አምላክ ለዘመን በሥጋ ስለወለደችው በእውነት አምላክን የወለደች /ወላዲተ አምላክ/ ናት በማለት ትምህርተ ሐዋርያትን አጽንተዋል፡፡ 
 
በቤተ ልሔም በከብቶች ግርግም ከድንግል የተወለደው የዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያም ፣ እመ እግዚአብሔር ፣ ወላዲተ አምላክ ተብላ ትጠራለች፡፡ 1ዮሐ.5-20፤ ቲቶ.2-13፡፡
ኪዳነ ምሕረት፡- የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግሥት በመመለስ የሰውን ሕይወት ለዘለዓለሙ ለመጠበቅ በመጀመሪያ ከስህተቱ በንስሐ ከተመለሰው ከአዳም፣ ቀጥሎም ከጻድቁ ከኖኅ፣ ከዚያም በእምነትና በምግባሩ ቀናነት የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ ከተሰየመው ከአብርሃም…. ከሌሎችም ቅዱሳን ጋር ለመላው የሰው ዘር የሚሆን የምህረትና የበረከት ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡
«ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ» መዝ.88-3 በማለት በተናገረው መሠረት ከምርጦቹ ጋር ቃል ኪዳን የሚያደርግ ልዑል አምላክ ከተመረጡ የተመጠረች በመሆኗ /ዋ/ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የካቲት 16 ቀን ቃል ኪዳን ሰጥቷታልና ወር በገባ በ16 ቀን ወርኃዊ በዓሏን እናከብራለን፡፡
ይህንንም ለማመልከት ኪዳነ ምሕረት /የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለች/ ትባላለች፡፡ በዚህም ምክንያት፡-
በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ
ቅድስት ሆይ ለምኝልን
በእንተ ስማ ለማርያም ወዘተ
በማለት የተሰጣትን ቃል ኪዳን መማጸኛ በማድረግ እንጠራታለን፡፡ ምሳሌዋ የሆነች ሐመረ ኖኅ /የኖኅ መርከብ/ በተሰጣት ቃል ኪዳን ከማየ አይኅ /ከጥፋት ውኃ/ ነፍሳትን እንደ አዳነች ቅድስት ድንግል ማርያምም በተሰጣት ቃል ኪዳን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ታድነናለችና ኪዳነ ምሕረት /የምሕረት ቃል ኪዳን/ የተሰጠሽ እንላታለን፡፡
ቅድስተ ቅዱሳን፡- ይህ ስም ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ለሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕናና ቅድስና መገለጫ ሆኖ የተሰጣት ልዩ ስም ነው፡፡ ቅድስተ ቅዱሳን ማለት ከተለዩ የተለየች ከተመረጡ የተመረጠች፣ ከተከበሩ የተከበረች ማለት ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ክፍል ተሰመይኪ ፍቅርተ ኦ ቡርክት እምአንስት አንቲ ውእቱ ዳግሚት ቀመር እንተ ትሰመይ ቅድስተ ቅዱሳን፡- ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ የተወደድሽ ተባልሽ ከተለዩ የተለየሽ» በማለት ቅድስናዋን መስክሯል /የእሑድ ውዳሴ ማርያም አንቀጽ 1/
ከአንስተ ዓለም ተለይተው ቅድስናን ገንዘብ ያደረጉ በርካታ ሴቶች ቢኖሩም ድንግል ማርያም ግን የነዚህ ሁሉ ፊት አውራሪ /ግንባር ቀደም/ እና ከሌሎች አንስት የተለየች ቅድስት /ቅድስተ ቅዱሳን/ ትባላለች፡፡ «አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ» በማለት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መስክሮላታል፡፡ ሉቃ.1-28፡፡ ከዚህም ጋር በተግባረ ቃል ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው «የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኲሎሙ ቅዱሳን፡- ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል» / ዘረቡዕ ውዳሴ ማርያም አንቀጽ .7/ በማለት የድንግል ማርያምን ቅድስና መስክሯል፤ ከዚህም የተነሳ በከበረ ስሟ ቅድስተ ቅዱሳን እያልን እንጠራታለን፡፡

ንጽሕተ ንጹሐን፡- ነጽሐ ነጻ ካለው ግሥ የወጣ ሲሆን ንጽሕት ማለትም የነጻች የጠራች ማለት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ንጽሕና «ዘንጹሕ ልቡ ወንጹሕ እደዊሁ፡- እጆቹም ልቡም ንጹሕ የሆነ»፣ «ብፁዓን ንጹሓነ ልብ ወይለብሱ ንጹሐ፡- ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው ንጽሕናን ይለብሳሉ»፣ «ሕያዋት ወንጹሓት፡- ሕያዋንና ንጹሓን»፣ «ንጽሕት ወብርህት፡- የነጻች የምታበራ» በማለት የንጽሕናን ሁኔታ ያስረዳሉ፡፡ መዝ.23፣ ማቴ.5-8፣ ራእ.15፣ ዘሌ.14-4፡፡ ውዳሴ ማርያም ዘአርብ፡፡

በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሴቶች የልማደ አንስት ኃጢአት ሰውነታቸውን ያላጐደፋቸው ወይም ያላረከሳቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሁንና ከገቢረ ኃጢአት ንጹሓን ይሁኑ እንጂ ከነቢብና ከሐልዮ ኃጢአት /በመናገርና በማሰብ ከሚሠራ ኃጢአት/ አልነጹም፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከገቢር ከነቢብ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ስለሆነች ንጽሕተ ንጹሐን እንላታለን፡፡

ወትረ ድንግል /ዘላለማዊት ድንግል/፡- ቅድስተ ቅዱሳን ወላዲተ አምላክ ማርያም ጌታን ከመጽነሷ በፊት፤ ጌታን በጸነሰች ጊዜ፤ ከጸነሰችም በኋላ፤ ከመውለዷ በፊት፤ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደች በኋላ ድንግል ናት ከዚህም የተነሳ ድንግል ዘላለም እንላታለን፡፡ ክህነትን ከነቢይነት ጋር አስተባብሮ የያዘው ሕዝቅኤል ዘላለማዊ ድንግልናዋን መስክሯል፡፡ ሕዝ.44-1-2፡፡

የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ሳዊሮስ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና በተናገረበት ክፍል «አምላክን የወለደች ማርያም ለዘለዓለሙ ድንግል እንደሆነች መውለዷም የማይመረመር ድንቅ እንደሆነ ከወለደችም በኋላ በድንግልና ጸንታ እንደኖረች አስረዳን» በማለት ስለ ዘላለማዊ ድንግልናዋ መስክሯል፡፡ ኢሳ.7.14፤ ሉቃ.1.27፡፡
ድንግል በክልኤ፡- በሁለት ወገን ድንግል ማለት ነው፡፡ በሁለት ወገን በሥጋም በነፍስም በሐልዮ /በሐሳብ/ በገቢር /በመሥራት/ በውስጥ በአፍአ ድንግል መሆኗን ያመለክተናል፡፡
ሌሎች ሰዎች ከገቢር ከነቢብ ቢጠበቁ ከሐልዮ /ከሃሳብ/ ኃጢአት መጠበቅ ግን አይቻላቸውም፡፡ ድንግል ማርያም ግን በሁለት ወገን ንጽሕት ቅድስት ናት ስለዚህ ድንግል በክልኤ /በሁለት ወገን ድንግል/ ትባላለች፡፡

ድንግል ወእም፡- እናትም ድንግልም ማለት ነው፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብሮ መገኘት ለፍጥረታዊ ሰው የማይቻል ቢሆንም ድንግል ማርያም ግን ሁለቱንም አስተባብራ ይዛለችና ድንግል ወእም ትባላለች፡፡

ሴቶች በልጅ ጸጋ ከከበሩ ድንግልናቸውን ያጣሉ በድንግልና ተወስነው ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት ከወሰኑ ደግሞ ከልጅ ጸጋ ይለያሉ፡፡ ሁለቱንም አስተባብረው ይዘው መገኘት አይሆንላቸውም፡፡ ድንግል ማርያም ግን ድንግልናን ከእናትነት እናትንትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ ይዛ የተገኘች በመሆንዋ ድንግል ወእም እናትም ድንግልም ሆናለች፡፡ ሉቃ.1-26-38፡፡
ልጇ ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ /ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው/ ሲባል እንዲኖር እርሷም ድንግል ወእም ስትባል ትኖራለች ስትወልደው ማኅተመ ድነግልናዋ እንዳልተለወጠ ሁሉ ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም» እንዳለ፡፡ ሚል.3-6፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው የእመቤታችን ስሞች የተገለጹት /የተነገሩት/ በራሱ በልዑል እግዚአብሔር እንዲሁም በቅዱሳን ነቢያት፣ በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታትና በሌሎችም ቅዱሳን አባቶች ነው፡፡
ይህም ምሥጢር የትምህርተ ሃይማኖት አንዱ አካል ሲሆን እኛም በቅዱሳን የተገለጸውን የእመቤታችንን ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው ስሞች ተረድተን የትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀታችንን ልናሳድግ ቅድስት ድንግል ማርያምንም ልናከብር እንዲገባን መገንዘብ አለብን፡፡ የቅዱሳንም አስተምህሮት ይህ ነውና፡፡

ስም አጠራሯ የከበረ ቅድስተ ቅዱሳን፣ እመ ብርሃን፣ ሰአሊተ ምሕረት፣ ድንግል ወእም፣ ወላዲተ አምላክ፣ እየተባለች የምትጠራ ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከቷ አማላጅነቷ አይለየን፡፡ አሜን፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔ

Sinod.JPG

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስት መምሪያዎች በሊቃነ ጳጳሳት እንዲመሩ ውሳኔ ሰጠ

በሻምበል ጥላሁን

በሰኖዶሱ አባላት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሰላም መፈታቱንም ገለጸ

ከጥቅምት 12 እስከ 19/ 2002 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሰንበት ትምህርት ቤት ማደረጃ መምሪያን ጨምሮ ሌሎች ሁለት መምሪያዎችን በበላይ የሚመሩ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳትን በመምረጥና 10 ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠ ናቀቀ፡፡

Sinod.JPG

 

 

 

 

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን እስከ ግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ድረስ ልማት ኮሚሽንን እንዲያስተዳድሩም መርጧል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔውን ያሳለፈውና ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጠው ከጥቅምት 12 እስከ 19/ 2002 ዓ.ም ከተወያየ በኋላ ነው፡፡

በውይይቱ መሠረትም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሥር የሚገኙት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በብፁዓን አባቶች የበላይ አመራር ሰጪነት እንዲተዳደሩ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ሦስቱን መምሪያዎች በበላይ ተቆጣጣሪነትና አመራር ሰጪነት እንዲመሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተመ ረጡት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩና አሁን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መመሪያን በበላይነት በሙሉ ጊዜ የሚያሰተዳድሩ፤ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ የነበሩና አሁን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያን በሙሉ ጊዜ በበላይነት የሚማሩ፡፡ የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ያሬድ አሁን በሙሉ ጊዜ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን በበላይነት እንዲመሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተመድበዋል፡፡

መምሪያዎቹ በሊቃነ ጳጳሳቱ አመራር ሰጪነት በሙሉ ጊዜ  መመራታቸው የአገልግሎት ክፍሎቹን ለማ ጠናከር ቤተክርስቲያን ቁርጠኛ አቋም መውሰዷን እንደሚያመለክት ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡ ምእመናን ገልጸዋል፡፡

ለውጡ በተለይ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያን በሓላፊነት ይመሩ በነበሩት ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት እንደሚፈታውም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በስብሰባው ማጠቃለያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ ለ2002 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ የሥራ ሪፖርትን ማድመጡንና ለ2002 ዓ.ም የቀረበውን የሥራ በጀት በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ገልጿል፡፡

በተለያየ ምክንያት የሥራ ዝውውር እንዲደረግላቸው ለጠየቁ ስድስት ሊቃነ ጳጳሳት ዝውውሩን ጉባኤው መቀበሉን ያመለከተው መግለጫው፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተም ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል፡፡

በውሳኔው መሠረት ሀገረ ስብከቱ ካለው ስፋት አንፃር መልካምና ቀልጣፋ አስተዳደርን ለመገንባት በዞን እንዲከፈል ማድረግ በማስፈለጉ አፈጻጸሙን አባቶች ካልተመደቡላቸው አህጉረ ስብከት ጋር በአጥኝ ኮሜቴ ተመቻችቶ ለግንቦቱ የርክበ ካህናት ጉባኤ ይቀርብ ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቶ መወሰኑን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ጉባኤው ከቤተክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ተመርቀው ለሚወጡ ደቀ መዛሙርት ሊመደብ ስለሚገባው መነሻ በጀት፣ ጉዳይ ተወያየቶ የበጀቱን ሁኔታ ለሚመለከተው ኮሚቴ ተጠንቶ ለግንቦቱ የርክበ ካህናት ጉባኤ እንዲቀርብ መወሰኑንም ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት የተነበበው መግለጫ አመልክቷል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን የሥራ እንቅስቃሴ እንዲያቀላጥፍ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጦ የነበረው የሊቃነ ጳጳሳት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኮሚቴው የሚመራበት የመተዳደሪያ ደንብ በማስፈለጉ ጉባኤው መተዳደሪያ ደንቡ ቃለ ዓዋዲውንና ሕገ ቤተክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት በአስረጂነት ያሉበት ውስጠ ደንብ በሕግ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ለግንቦቱ ጉባኤ እንዲቀርብ መወሰኑ ንም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ የነበሩት የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልንም ጉዳይ ውሳኔ ማሳለፉን በቅዱስ ፓትርያርኩ የተነበበው መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሊመደቡበት የሚገባ ቦታ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በሚገኙበት ኮሚቴ እንዲጠና መደረጉን ያመለከተው መግለጫው፤ አጥኚው ኮሚቴው ጠቁሞ ካቀረባቸው አራት ቦታዎች መካከል ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል  ከጥቅምት 20 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦቱ የርክበ ካህናት ጉባኤ ድረስ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ጊዜያዋ ሓላፊ ሆነው እንዲሠሩ መወሰኑን መግለጫው አስረድቷል፡፡

ሲኖዶሱ ባለፈው ሐምሌ ወር 2001ዓ.ም በድንገት ተፈጥሮ ከነበረው የሥራ አለመግባባት የተነሣ ያልተ ጠበቀ አሳዛኝ ድርጊት ተፈጽሞ መገኘቱ ሁሉንም ያሳዘነ ቢሆንም የሰላም መልእክተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ በአባላቱ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በዕርቅ እንዲፈታ በማድረግ ጉባኤው በሰላም መካሄዱንም አመልክቷል፡፡

ችግሩ በአባቶች ቀኖናዊ  ዕይታ መፈታቱንም መግለጫው አመልክቶ፤ ለሀገር አንድነትና ደኀንነት ስትጸልይ የኖረችውና የምትኖረው ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የራሷን ችግር በራሷ የመፈታት አቅሟን አጎልብታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተከሥቶ የነበረ ውንና ቅዱስ ሲኖዶሱን አሳዘኖ ያለፈውን ችግር በመፍታት እርቅ ሰላ ሙን ለማስፈን መብቃቷንም መግለጫው አብራርቷል፡፡

በመሆኑም ሐምሌ 2001 ዓ.ም ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ ፈተና የምትቆጥረው ቢሆንም አባቶች የሰጡትና የሚሰጡት ቃለ ትምህርትና ቃለ ምዕዳን ትኩረትን አግኘቶ ተፈጥሮ የነበረው ጊዜያዊ አለመግባባት ተወግዶ መፍ ትሔ በመገኘቱ ደስታዋን ሁሉም እንዲረዳው በአጽንኦት ማብሰሯንም በቅዱስ ፓትርያርኩ የተነበበው መግለጫ አስረድቷል፡፡
               

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 17ኛ ዓመት ቁጥር 4/ቅጽ 17 ቁጥር 189 ከኅዳር 1-15 2002 ዓ.ም  

Gambela_1.JPG

የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡቦንግና የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተጠመቁ

በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው ቤተክርስቲያን ተመረቀ፡፡                  

በተከስተ አዳፍራቸው

የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነርና የካቢኔ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነት ተቀብለው ተጠመቁ፡፡ በጋምቤላ ሀገረ ስብከት በአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የደብረ መድኃኒት ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱም ተከብሯል፡፡Gambela_1.JPG

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ¬ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት የክብር ፕሬዝዳንት የክልሉን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ካጠመቁ በኋላ እንደ ተናገሩት፣ ልጆቻችን የኢትዮጵያን ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ እምነት ተምረው በመጠመቃቸው ቤተክርስቲያን እጅግ የላቀ ደስታ ይሰማታል፡፡
Gambela.JPG
«ቤተክርስቲያን ከበረቱ ውጪ ያሉ ብዙ በጎች አሏት» ያሉት ቅዱስነታቸው፤ እንደነ ጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያሉ ብዙ ታላላቅ ሰዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነትና ሥርዐት ተቀብለው ሀገራቸውን በተረጋጋ ሰላምና ልማት መምራታቸውን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡቦንግ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስ ቲያንን እምነት መሠረታዊ ትምህርቶችን ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና ከሊቃውንቱ ዘንድ በሚገባ በመከታተል ከነመላ ቤተሰባቸው መጠመቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከፍተኛ ደስታና መረጋጋት እንደተሰማቸው የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቤተክርስቲያኒቱ ከምታስ ተምራቸው መሠረታዊ የእምነቱ ሥርዓቶች በተጓዳኝ በልማቱና በሰላሙ መስክ ኅብረተሰቡን ለማገልገል የምታደርገው እንቅስቃሴ ወደ ክርስትናው እንደሳባቸው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት በመጽናትና በሥነ ምግባር በመታነጽ የሰላም አምባሳደር ለመሆን እንደሚጥሩ የጠቆሙት አቶ ኡሞድ፤ በቤተክርስቲያኒቱ የልማት ሥራ ላይ በመሳተፍ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውንም እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ቤተሰቦቻቸው ጋር በመጠመቅ የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኙት ወን ድሞች መካከል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡቲያንግ ኡቻንና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የካቢኔ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ አሙሉ ኡቻን ይገኙበታል፡፡

በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት አንዳንድ ምእመናን በሰጡት አስተያ የት፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የእግዚአብሔርን ልጅነት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
Church.JPG

 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
«የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና እምነት ተቀብለው ለመኖር ብዙ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ» ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ እነዚህን ወገኖች ለማምጣት ምእመናንም ሆኑ የቤተክርስቲ ያኒቱ አገልጋዮች ሁሉም በየደረጃው ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ከጥምቀተ ክርስትና ሥነ ሥርዓቱ በኋላም በአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር የተገነባው የደብረ መድኃኒት ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በቅዱስ ¬ፓትርያርኩ ከብሯል፡፡ ቅዱስነታቸው በዚሁ ጊዜ እንደ ተናገረሩት፤ የጋምቤላ ምእመናን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይሔንን የመሰለ ቤተክርስቲያን አጠናቀው ለአገልግሎት ማብቃታቸው ለእምነታቸው ያላቸውን ጽናት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ ምእመናኑ ይህንን የእምነት ጽናት በማሳደግ ቤተክርስቲያናቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ቅዱስነታቸው አሳስበው፤ በልማቱም ዘርፍ እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከጋምቤላ ከተማና ገጠራማ አካባቢዎች የመጡ በርካታ ምእመናንና ጥሪ የተደረገላ ቸው እንግዶች መገኘታቸውም ታውቋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 17ኛ ዓመት ቁጥር 4/ቅጽ 17 ቁጥር 189 ከኅዳር 1-15 2002 ዓ.ም

የመከሩ መሰብሰቢያ ጊዜው አሁን ነው

ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለ ጠቢቡ የሚሠራበትም ሆነ መሥራት የሚቻልበት ጊዜ አለው፡፡ ነገሮች ሁሉ የሚከናወኑበት፣ ቀና የሚሆኑበት፣ የሰው ልቡና ለበጎ ነገር የሚነሣሣበት ያለሙት የሚሠምርበት የዘሩት፣ የተከሉት ሁሉ የሚያፈሩበትና የሚጸድቅበት ጊዜ አለ፡፡
ያለንበትን ዘመን ስንቃኘው የመጨረሻው ዘመን ዋዜማ ምልክቶች የሚታዩበት ፍቅር ከሰዎች መካከል የቀዘቀዘበት አስጨናቂ ዘመን ቢሆንም ሕዝቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የሚፈልግበት፣ ስብከተ ወንጌል የተጠማበት፣ ገዳማትን ለመርዳት የተፋጠነበት፣ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትን የሚጠግንበት፣ የተዘጉት አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስከፍትበት እንዲሁም ጉባኤያትን እያዘጋጀ መምህራንን የሚጋብዝበት፣ በኅብረት ቤተክርስቲያንን ለማገልግል የሚዘምትበት፣ ከአካባቢው ሕዝብ ሌላ ዐይቷቸው የማያውቃቸውን ጥንታውያን ገዳማትና አድባራትን ሳይቀር ቆላ ደጋ ወጥቶ ወርዶ የሚሳለምበት፤ ከዘፈን መዝሙርን፣ ከዳንስ ማኅሌትን፣ ከዘልማድ ጋብቻ ተክሊልን፣ የመረጠበት ቅዱሳት መጽሐፍትን ከምግቡ ቆጠቦ የሚገዛበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡

አሁን ያለንበት ዘመን ምንም እንኳን የኢ-አማንያንና የመናፍቃን ሴራና ዘመቻ ያየለበት ተልእኮአቸውና ተንኮላቸው የረቀቀበትና በቤተክርስቲያን መስለው ገብተው የሚፈነጩበት እንዲሁም ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ አፉን ከፍቶ እንደ ቀትር እባብ የሚራወጥበት ጊዜ ቢሆንም፤ ኃጢአት በበዛበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች ነውና ሠራተኛው ያለችውን ጥቂት ዕረፍቱን ለጉባኤ፣ የኮሌጅ ተማሪው እንደ ዕንቁ የተወደደች ጊዜውን ለወንጌል፣ ነጋዴውና ባለሥልጣኑ በገንዘብና በብዙ ሥራ የምትተመን ጊዜውን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጠበትና ለቤተ ክርስቲያንም መልካም አጋጣሚ የተፈጠረበት  ነው፡፡

ከሀገር ውጪና በጠረፋማ የሀገሪቱ አካባቢ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ የቻሉ ቤተክርስቲያን እየተከሉ፣ ያልቻሉ ጉባኤ እየመሠረቱ ይህም ባይሳካ በጽዋ ማኅበር ተሰብስበው በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጥላ ሥር ተጠልለው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከትም ደፋ ቀና የሚሉበትም ጊዜ ነው፡፡

አባቶች ከልጆች ጋር ለመሥራት የተነሡበት፣ አህጉረ ስብከት ካህናትን ለማሠልጠንና ሕዝቡን በጉባኤ ለማስተማር የተጉበት፤ በምዕራብ በምሥራቅና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ከግራኝ ወረራ በኋላ ተረሠቶ የነበረው ሥርዓተ ገዳም በትጉኃን ጳጳሳት ጥረትና በቅዱስ ሲኖዶስ ድጋፍ መስፋፋት የጀመረበት ጊዜም ነው፡፡

የምእመኑ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት መልካም አጋጣሚ ስለፈጠረና ጥቂትም ስለሠራን ነው በርቀት ሆነው ታሪኳንና ቀጥተኝነቷን በዝና ብቻ የሚያውቋትና ወደ እርሷም ለመመለስ ይናፍቋት የነበሩት ወገኖቻችን ወደዚህች ቅድስትና ንጽሕት ወደ ሆነች ቤተክርስቲያን እየተመለሱ በሥርዓቷም ለመገልገልና ለማገልገል እየተፋጠኑ የሚታዩት፡፡

«በአዝመራ ጊዜ ጐበዝ ገበሬ ምርቱን መሰብሰብ ካልቻለ ዝንጀሮ ይጫወትበታል» እንደሚባለው፤ እኛም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በመናፈቅና በመፈልግ እየመጡ ያሉትን ወገኖችና ለአገልግሎት የተነሡትን ምእመናን በአግባቡ ካልያዝን የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ሕግን ለማፍለስ የተሰለፉ፤ ገዳማትና አድባራትን ጠፍ ለማድረግ ያሰፈሰፉ፤ የቤተክርስቲያንን ይዞታ ለመንጠቅ የዘመቱ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያናችንን በኑፋቄ መርዝ ለመበከል የታጠቁ፣ ቅርስዋንና ንዋየ ቅድሳቷን በመዝረፍ ለመክበር የቋመጡ የውስጥ አርበኞች ወደ ቤተክርስቲያን እየመጡ ያሉትንና ለአገልግሎት የሚፋጠኑትን ማሰናከላቸው አይቀሬ ነው፡፡

የሕዝቡ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት በራሱ አስደሳችና መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ካልሠራንበት፤ አጋጣሚው ብቻውን በጐ ቢሆን ውጤት አያመጣም፡፡ በጐ አጋጣሚዎችን አግኝተው፤  በአጋጣሚዎቹ ተጠቅመው ሳይሠሩ ያለፉ አሉና፡፡ በዘመነ ሐዋርያት ከጌታችን ደቀ መዛሙርት ገጽ በገጽ መማር እየቻሉ  አጋጣሚውን ያልተጠቀሙ ነበሩ፡፡

በዚህ ዘመንም ቅድስት ንጽሕት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወድደውና ፈቅደው የሚመጡ ወገኖቻችን ተገቢውን የቤተክርስቲያን ትምህርት ተጠንቅቀን ካላስተማርን፣ ገዳማትና አድባራትን ለመርዳት ሲነሡ ተቀናጅተው ውጤት የሚያመጡበትን መንገድ ካልመራናቸው፣ የተዘጉትን በሚያስከፍቱበት ጊዜ በቂ አገልጋይ ካላሠማራንላቸው፤ ጉባኤያትን እያዘጋጁ የመምህራን ያለህ ሲሉ ቦታና ሰው ሳንመርጥ በዕለት ድካምና በሰበብ አስባቡ ሳናመካኝ ካልተገኘንላቸው ተሰባስበው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ሲነሡ ከመንቀፍ ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ደንብና ሥርዓት የሚሠማሩበትን ካልቀየስንላቸው፣ ገዳማትና አድባራትን ለመሳለም በሚዘጋጁበት ጊዜ ተገቢውን አቀባበልና ትምህርት እየሰጠን ከቅዱሱ ቦታ በረከት የሚያገኙበትን ሁኔታ ካላመቻቸንላቸው፣ ከዘፈን መዝሙር መርጠው ሲመጡ ትክክለኛውን ያሬዳዊ መዝሙር ካላቀረብንላቸው፣ ከዘልማድ ጋብቻ ተክሊልን መርጠው ሲመጡ ስለትዳር የሚያስተምሩትንና የሚመክሩትን መምህራን በትክክል ካላገኙ፣ ከዕለት ጉርሱ ከዓመት ልብሱ ቆጥቦ ቅዱሳት መጻሕፍትን ገዝቶ ለማንበብ ሲነሣ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወቱን የሚያንጹለትና የሚገነቡለትን ቅዱሳት መጻሕፍት ካላዘጋጀንለት፣ ጋዜጠኛው አርቲስቱ፣ ነጋዴው ሠራተኛው ተማሪው ወታደሩ፣ ¬ፖለቲከኛው ሹፊሩ ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ ችግሩን ሊፈቱለት አስቀደመው የተጠሩ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ መዘምራን፣ አስተናባሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮች፣ ደክመውና ሰልችተው በሥጋዋና ግላዊ ምክንያቶች ተጠላልፈው፤ እርስ በእርሳቸው እየተነቃቀፉ ተቃቅረው እንዳይገኙና ዘመኑን ባርኮና ምቹ አድርጎ የሰጠ እግዚአብሔር እንዳያዝን መንቃት ያስፈልጋል፡፡

ትናንት ሲያስተምሩ፣ ሲዘመሩ፣ ከአጥቢያዎቻቸው ውጪ በየገጠሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ሲመሠርቱ፣ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ያለ እንቅልፍ ሲያገለግሉ የነበሩ፤ በየገጠሩ ገብተው ሕዝቡን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ሲቀሰቅሱ፣ የነበሩና ያልተጠመቁትን ለማስጠመቅ የተጉት፣ የሚበሉትና የሚለብሱት፣ የሚያርፉበትና የሚተኙበት ጊዜ አጥተው ለቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተሰልፈው የነበሩ ሁሉ፤ ሩጫቸውን የፈጸሙ እንዳይመስላቸው ያልተወረሰ ብዙ መሬት ገና መቅረቱን የሚረዱበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ኢያ. 13.1፡፡

ከኋላ የነበሩት ወደፊት ሲመጡ ከፊት የነበሩት ወደ ኋላ እንዳይሄዱ፣ በጨለማ የነበሩት ወደ ብርሃን ሲመጡ፣ በብርሃን የነበሩት ወደ ጨለማ እንዳይመለሱ፣ ጥቂቶች እያሉ ብዙ የሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ሲያበዛላቸው እንዳይደክሙና እንዳይዝሉ የማሰቢያና ብዙ የመሥሪያ አጋጣሚው አሁን ነው፡፡

በዚህ የፍጻሜ ዘመን መጨረሻ ወደ ቤተክርስቲያን እየመጣ ያለውን ሕዝብና ለአገልግሎት እየተጋ ያለውን ምእመን እንደ አመጣጡና እንድ እድሜ ገደቡ ትምህርት በመስጠት በእምነት ልናጸናው፣ በአገልግሎት ልናበረታው ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም መምህራን፣ ካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የየራሳችን ድርሻ አለን፡፡

በአጠቃላይ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን የመጡና እየመጡ ያሉትን ወገኖቻችንን የምንቀበልበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ጀንበር ሳለ ለሚሮጥ፣ የጋለውን ለሚቀጠቅጥ፣ ቀን ሳለ የብርሃን ሥራ ለሚሠራ፣ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ የሚያፈራበት ዘመን ዛሬ ነው፡፡ እናም እግዚአብሔርን የተጠሙ ነፍሳትን የምናድንበትና በቤተክርስቲያን ሥርዓት እንዲኖሩ የምናደርግበት የመከሩ መሰብሰቢያ ጊዜው አሁን ነውና እንጠቀምበት፡፡   

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 17ኛ ዓመት ቁጥር 4/ቅጽ 17 ቁጥር 189 ከኅዳር 1-15 2002 ዓ.ም