የጎንደር ማእከል ፮ኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አካሔደ፡፡

ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በጎንደር ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል ግንቦት ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ፮ኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደንቢያ ወረዳ በግራርጌ መካነ ሕይወት አባ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን አካሔደ፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአካባቢው ምእመናን፣ የየወረዳ ማእከላት አባላት፣ የደንቢያ ከተማ መንፈሳውያን ማኅበራት እና የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የተገኙ ሲኾን፣ በአጠቃላይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጨምሮ ከ፲፭፻ በላይ ምእመናን በጉባኤው ተሳትፈዋል፡፡ በዕለቱ በተደረገው ጉባኤም በጎንደር ማእከል የመዝሙርና የኪነ ጥበባት ክፍል አባላት መዝሙርና መንፈሳዊ ሥነ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡

በጠዋቱ መርሐ ግብር የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ በአስተዳዳሪው ከተነገረ በኋላ እጅግ ጠቢብ አትሁን /ጥበ.፯፥፲፯/ በሚል ኃይለ ቃል በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ትምህርተ ወንጌል የቀረበ ሲኾን፣ በመቀጠልም የአብርሃም ቤት እንግዳ ተጋባዥ የኾኑት በማኅበረ ቅዱሳን ቅዱሳት መካናት እና ገዳማት ክፍል ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረትና እስከ ዛሬ ድረስ ስላለው የአገልግሎት ኹኔታ ሰፋ ያለ ገለጻ በማድረግ የሕይወት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

በተጨማሪም ማኅበረ ቅዱሳን ለገዳማት፣ ለአብያተ ክርስቲያናት እና ለአብነት ትምህርት ቤቶች እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ተናግረዋል፡፡

ከሰዓት በቀጠለው መርሐ ግብርም በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ የመጻሕፍት ጉባኤ ቤት ደቀ መዝሙር የኾኑት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ መንግሥተ ሰማያት በመካከላችሁ ናት /ሉቃ.፲፯፥፳፩/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ከሰጡ በኋላ ሰባኬ ወንጌል ዋኬ ጉንዳ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ሀገረ ስብከት ዙሪያ ያለውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ኹኔታ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

ሰባኬ ወንጌል ዋኬ አያይዘውም የመተከል ሀገረ ስብከት የሰባክያነ ወንጌል፣ የአገልጋይ ካህናትና የሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት እጥረት ያለበት አካባቢ መኾኑን ጠቅሰው ምእመናኑ ቃለ እግዚአብሔርን ለተራቡ ለአካባቢው ወገኖች ሰፊ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዕለቱ በወጣትነት እና ክርስትና፣ በክርስቲያናዊ አለባበስ፣ በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በ፵ ቀን ዕድል፣ በካህኑ መልከ ጼዴቅ የዘር ሐረግ፣ ለአብርሃም በተገለጹት ሥላሴ ዙሪያ ከምእመናን የተነሡ ጥያቄዎች በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ሰፊ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የማእከሉ ሰብሳቢ መምህር ዓለማየሁ ይደግ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዲህ አይነት መርሐ ግብራት መዘጋጀታቸው በዓለም የባዘኑትን ምእመናን ሕይወት ለመለወጥ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹ ሲኾን፣ በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ ምእመናንም ጉባኤው አእምሯቸውን ያጎለመሱበት፣ መንፈሳቸውን ያደሱበት፣ ሕይወታቸውን የተፈተሹበትና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የተረዱበት መኾኑን ገልጸው እንደዚህ ዓይነቱ መርሐ ግብር ለወደፊቱ በዓመት ሦስት አራት ጊዜ ቢዘጋጅ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ለቤተ ክርስቲያኑ ገቢ የሚሆን ገንዘብ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ከተሰበሰ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል፡፡