የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን Encyclopedia ዝግጅት መጀመሩ ተበሠረ፡፡

ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ሰኔ ፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከረፋዱ 5፡45 ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን ሆቴል አዳራሽ ባደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን Encyclopedia (በጊዜያዊ ትርጕሙ ባሕረ ጥበባት) ዝግጅት በይፋ መጀመሩ ተበሠረ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደ ገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን በዕቅድ ከሚሠራቸው ዐበይት ተግባራት መካከል ይህ በማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል የሚሠራው የEncyclopedia ዝግጅት አንዱ መኾኑን ጠቅሰው ለዚህ ተግባር መሳካት አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመስግነዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ዶ/ር አባተ መኩሪያው የማእከሉን ዓላማ ለጉባኤው ባቀረቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙ ሀብት ምንጭ፣ የጥንታውያን ቅርሶች ባለቤትና የብዙ ሺሕ ምእመናን መገኛ ኾና ሳለ እስከ አሁን ድረስ Encyclopedia ሳይኖራት መቆየቷ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለአገርም ክፍተት የሚፈጥር መኾኑን ገልጸው የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ይህንን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባትና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለትውልድ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ባሕረ ጥበባት ለማዘጋጀት መወሰኑን አብሥረዋል፡፡

የዝግጅት ሥራውን በተመለከተ የEncyclopedia ዝግጅቱ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ የአማካሪ ቦርድ፣ እንደዚሁም የአርትዖት ክፍል አባላት እንዳሉትና በዝግጅቱም ከሦስት መቶ ሰባት ባላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሙያዎች እንደሚሳተፉበት ዶ/ር አባተ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከአማካሪ ቦርድ አባላት መካከል አንዱ የኾኑት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን በዕለቱ አስተያየት ሲሰጡ የአንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ ርምጃ ይጀምራል የሚለውን ብሂል ጠቅሰው ይህ የባሕረ ጥበባት ዝግጅትም ጥሩ ጅማሬ ነውና እንደ ጥሩ ፍጻሜ ይቈጠራል ብለዋል፡፡ ሥራው ብዙ ፈተናና ድካም እንደሚኖረው የተናገሩት መልአከ ታቦር እኛ ከማለፋን በፊት ጅማሬውን ብናየው ደስ ይለናል ካሉ በኋላ አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም በቅርቡ ለንባብ እንዲበቃ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ Encyclopedia ከሚለው ቃል ትርጕም አኳያም መድበል የሚለው ቃል በትርጕሙ ውስጥ ቢካተት የተሻለ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው የአማካሪ ቦርድ አባል ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በበኩላቸው ለዚህ ሥራ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ጥረት ሲያደርግ የቆየውን ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነው የቤተ ክርስቲያን Encyclopedia እስከ አሁን ድረስ አለመዘጋጀቱ ቢያስቈጭም እኛ ግን መቀመጥ የለብንም ብለዋል፡፡ አያይዘውም Encyclopedia የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተወሰደና ትርጕሙም የጥበብ (የዕውቀት) መገኛ (ስብስብ) ማለት መኾኑን ጠቅሰው ባሕረ ጥበባት ከሚለው ትርጕም በበለጠ ሊገልጸው የሚችል አቻ ትርጕም ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው እንደ መነሻም መዝገበ አእምሮ፣ መዝገበ ጥበባት ወይም ፈለገ አእምሮ፣ ፈለገ ጥበባት፣ ወዘተ በሚል ቢተረጐም የሚል ዐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ሌሎች የአማካሪ ቦርዱ እና የአርትዖት ክፍሉ አባላትም አስተያየት በሰጡበት ወቅት በዝግጅቱ መጀመርና የዝግጅቱ አባላት በመኾቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ይህ ሥራ በሚሠራበት ጊዜ ልዩ ልዩ ፈተናዎችና ነቀፋዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ከወዲሁ በመረዳት ኹሉንም ነገር ለበጎ መኾኑን ማስተዋልና ችግሮችንም በትዕግሥት ማለፍ አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ እንደሚገባ ለራሳቸውም ለሌሎች የዝግጅቱ አባላትም አባታዊና ወንድማዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያም የአማካሪ ቦርድ እና የአርትዖት ክፍል ሥራ አስፈጻሚ ኰሚቴ የተዋቀረ ሲኾን፣ በዚህ መሠረት ለአማካሪ ቦርዱ፡- ፕ/ር ሽፈራው በቀለ ሰብሳቢ፣ ፕ/ር ባየ ይማም ምክትል ሰብሳቢ፣ ዶ/ር አባተ መኩሪያው ጸሐፊ፤ ለአርትዖት ክፍሉ ደግሞ፡- ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ ሰብሳቢ፣ ዶ/ር አበባው ምናዬ ምክትል ሰብሳቢ፣ ዲ/ን ሙሉዓለም ካሣ ጸሐፊ ኾነው በምልዓተ ጉባኤው ተመርጠዋል፡፡

በመጨረሻም በዕለቱ የመርሐ ግብሩ መሪ የነበሩት የEncyclopedia ዝግጅት ክፍል ሰብሳቢው ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ ለጉባኤው ተሳታፊዎችና ውይይቱ የተካሔደበትን አዳራሽ በነጻ ለፈቀደው ለሰሜን ሆቴል ምስጋና ካቀረቡና ለእንግዶቹም የምሳ መስተንግዶ ከተደረገ በኋላ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል፡፡