አዕማድ

መምህር በትረማርያም አበባው

ጥር ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ስምንቱን የግሥ አርእስት አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና አምስቱ አዕማድን እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!

መልመጃ

፩) የሚከተሉትን ቃላት አርእስታቸውን ለዩ!

    ግእዝ……………..አማርኛ

ሀ) ከሠተ……………..ገለጠ

ለ) ርእሰ………………አለቃ ሆነ

ሐ) ሠለሰ……………ሦስት አደረገ

መ) ጋህግሀ…..ክፍትፍት አደረገ

ሠ) ሰንሰለ…………አያያዘ/አቆራኘ

ረ) ሌለየ……………ለየ

፪) ከሚከተሉት ቃላት የሤመን፣ የቆመን እና የኀሠን ቤቶች ለዩ!

                 ግእዝ………አማርኛ

                 ሀ) ጼሐ……..ጠረገ

                 ለ) ሞተ……..ሞተ

                 ሐ) ከበ……..ከበበ

                 መ) ሮዘ…….ወለወለ

 

የጥያቄዎቹ መልሶች

 ፩)    ሀ) ቀተለ

        ለ) ክህለ

        ሐ) ቀደሰ

        መ) ማህረከ

        ሠ) ተንበለ

        ረ) ዴገነ

)

     ሀ) ሤመ

     ለ) ቆመ

     ሐ) ኀሠ

     መ) ቆመ

ውድ አንባብያን! ጥያቄዎቹን በትክክል ከመለሳችሁ ትምህርቱ ገብቷችኋልና በርቱ! ስለዚህ የዚህን ክፍለ ጊዜ ትምህርታችን ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አዕማድ የሚባሉት አምስት ናቸው፤ እነዚህም፦

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ቀተለ ገደለ
ተደራጊ ተቀትለ ተገደለ
አስደራጊ አቅተለ አስገደለ
ተደራራጊ ተቃተለ ተገዳደለ
አደራራጊ አስተቃተለ አገዳደለ

አንዳንድ ግሦች በአምስቱም አዕማድ ላይዘልቁ ይችላሉ። ለምሳሌ ተሞተ አይባልም። አንዳንዱ ግሥ በዐራቱ አንዳንዱ ግሥ በሦስቱ አንዳንዱ ግሥ ደግሞ በሁለቱ አእማድ ብቻ ሊዘልቅ ይችላል። የስምንቱን አርእስተ ግሥ አእማድ ካወቅን የሌላውንም በአጭሩ ልንረዳው እንችላለን። ከላይ መጀመሪያ ላይ የቀተለን አርእስት አይተናል። ቀጥለን የቀደሰን እንመልከት፦

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ቀደሰ አመሰገነ
ተደራጊ ተቀደሰ ተመሰገነ
አስደራጊ አቀደሰ አስመሰገነ
ተደራራጊ ተቃደሰ ተመሰጋገነ
አደራራጊ አስተቃደሰ አመሰጋገነ

በአስደራጊ ከአቀደሰ በተጨማሪ አቅደሰ፣ አስተቅደሰ ይላል። ተደራራጊው እና አደራራጊው ማለትም ተቃደሰ እና አስተቃደሰ ላልተው ይነበባሉ። ቀደሰ፣ ተቀደሰ እና አቀደሰ ግን ጠብቀው ይነበባሉ። ቀጥለን የተንበለን እንመልከት፦

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ተንበለ ለመነ
ተደራጊ ተተንበለ ተለመነ
አስደራጊ አተንበለ አስለመነ
ተደራራጊ ተተናበለ ተለማመነ
አደራራጊ አስተተናበለ አለማመነ

የባረከ ቤት ደግሞ እንደሚከተለው ነው፦                

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ባረከ አመሰገነ
ተደራጊ ተባረከ ተመሰገነ
አስደራጊ አባረከ አስመሰገነ
ተደራራጊ ተባረከ ተመሰጋገነ
አደራራጊ አስተባረከ አመሰጋገነ

የማህረከ ደግሞ ቀጣዩ ነው።

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ማህረከ ማረከ
ተደራጊ ተማህረከ ተማረከ
አስደራጊ አማህረከ አስማረከ
ተደራራጊ ተማሃረከ ተመራረከ
አደራራጊ አስተማሃረከ አመራረከ

የሴሰየ ደግሞ እንደሚከተለው ነው።

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ሴሰየ መገበ
ተደራጊ ተሴሰየ ተመገበ
አስደራጊ አሴሰየ አስመገበ
ተደራራጊ ተሴያሰየ ተመጋገበ
አደራራጊ አስተሴያሰየ አመጋገበ

የሴሰየ ቤት በተደራራጊ ከተሴያሰየ በተጨማሪ ተሲያሰየ፣ ተሰያሰየ ይላል። በአደራራጊ ደግሞ ከአስተሴያሰየ በተጨማሪ አስተሲያሰየ አስተሰያሰየ ይላል። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የክህለ ቤትን እንመልከት።

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ክህለ ቻለ
ተደራጊ ተክህለ ተቻለ
አስደራጊ አክሃለ አስቻለ
ተደራራጊ ተካሃለ ተቻቻለ
አደራራጊ አስተካሃለ አቻቻለ

          ቀጥሎ ያለው ደግሞ የጦመረ ቤት ነው።

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ጦመረ ጻፈ
ተደራጊ ተጦመረ ተጻፈ
አስደራጊ አጦመረ አስጻፈ
ተደራራጊ ተጡዋመረ ተጻጻፈ
አደራራጊ አስተጡዋመረ አጻጻፈ

በተደራራጊ ከተጡዋመረ በተጨማሪ ተጥዋመረ፣ ተጦዋመረ ተጠዋመረ ይላል። በአደራራጊም ከአስተጡዋመረ በተጨማሪ አስተጠዋመረ፣ አስተጦዋመረ፣ አስተጥዋመረ ይላል። የስምንቱ አርእስት አእማድ ይህን ይመስላል።  ከዚህ በተጨማሪ የቆመን፣ የሤመን፣ እና የገብረን ቤቶች እንይና የዛሬውን ትምህርታችንን እናጠቃልላለን።

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ቆመ ቆመ
ተደራጊ ተቆመ ተቆመ**
አስደራጊ አቀመ አስቆመ
ተደራራጊ ተቃወመ ተቋቋመ
አደራራጊ አስተቃወመ አቋቋመ

ለቆመ በተደራጊ ተቆመ አይባልም። ነገር ግን ቆመን የመሰሉ ግሦች ቢመጡ ይህንን ይመስላል ለማለት ተቆመ አልን እንጂ አይባልም። ለምሳሌ ሞአ….አሸነፈ ማለት ነው። በተደራጊ ተሞአ….ተሸነፈ ይላል። መስቀል ሞአ ሞት ተሞአ (መስቀል አሸነፈ ሞት ተሸነፈ) እንዲል ድጓ።

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ሤመ ሾመ
ተደራጊ ተሠይመ/ተሤመ ተሾመ
አስደራጊ አሤመ አስሾመ
ተደራራጊ ተሣየመ ተሿሿመ
አደራራጊ አስተሣየመ አሿሿመ

በመጨረሻም የገብረን ቤት እንመልከት፦

ግእዝ አማርኛ
አድራጊ ገብረ አደረገ
ተደራጊ ተገብረ ተደረገ
አስደራጊ አግበረ አስደረገ
ተደራራጊ ተጋበረ ተደራረገ
አደራራጊ አስተጋበረ አደራረገ

ስለዚህ በዚህ መልኩ አዕማደ ግሥን ማውጣት እንችላለን ማለት ነው።

  የመልመጃ ጥያቄዎች

የሚከተሉትን ግሦች አእማድ አውጣ

      ፩)  ሰቀለ….ሰቀለ

      ፪)  ወደሰ….አመሰገነ

      ፫)  ኮነነ……ገዛ

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።