በዓለ ደብረ ታቦር

ነሐሴ ፲፩፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በታቦር ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ዕለት ነሐሴ ፲፫ ”በዓለ ደብረ ታቦር‘ የከበረ በዓል ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ነች፤ ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ደቀ መዛሙርቱን ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ ካወጣቸው በኋላ መልኩ በፊታቸው ተለውጦ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። ጌታችንም ”የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲመጣ እስከሚያዩት ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል ሞትን የማይቀምሱት አሉ‘ በማለት ተናገራቸው።

እነርሱም እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ፣ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደ እርሱ መጡ። ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው፤ ”አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን? ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፤ አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።‘

ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነቱ የተንጸባረቀው ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ ሲናገር ነው። ትሕትናው ደግሞ ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ለመሥራት ስላሳሰበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና። “ስለ ሐዋርያትም የእውቀት ማነስ አታድንቅ፤ በዚያን ጊዜ ፍጹማን አልሆኑምና” በሚልበት ጊዜ ጌታችን ሰዎች ማደሪያ ሊሠሩለት የማይሻ መሆኑን ለቅዱስ ጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው።

በዚያም ሰዓት እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ”ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤  እርሱንም ስሙት።‘ የአብንም ቃል በሰሙ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም ብለው በምድር ላይ ወደቁ፤ እንደ ሙታንም ሆኑ። ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ፤ከዓለም አስቀድሞ ከእርሱ ጋራ በህልውና እንዳለ ለልጁ አብ ምስክርን ሆነ፤ ወዲያውኑ ሙሴ ወደ መቃብሩ ኤልያስም ወደ ቦታው ተመለሱ።

ጌታችንም ስለ መምጣቱ የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነቢያትና ሐዋርያት ደስ ተሰኙ። የጌታችን ጌትነት በዚህን ጊዜ ተገልጦ ነበርና የአብን ቃል በሰሙ ጊዜም ከእነርሱ ሥውር የነበረ የወልድ ዋሕድን በእውነት ሰው መሆን ተረድተዋል፤ ሐዋርያት የተረዱት ይህን ብቻ አልነበረም፤ እርሱ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ፣ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው፣ ኤልያስንም ያሳረገው፣ አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ ነበር። ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለምና ከዐሳረገው ከእርሱ በቀር ማንም ማን ኤልያስ ያለበትን የሚያውቅ የለምና። በሰማይና በምድር ሥልጣን ካለው ከሁሉ ጌታ በቀር ሙታንን አድኖ ሊያስነሣቸው ማንም አይችልም።

ሐዋርያትንም በአነቃቸው ጊዜ ከብቻው ጌታችን በቀር ማንንም አላገኙም። ከባሕርያችን የተዋሐደና ሥጋችንን የለበሰ ፍጹም አምላክ እንደሆነ በዚህ ሐዋርያት አስተማሩ።

ምንጭ፡- ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘነሐሴ ፲፫