‹‹ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው›› (መዝ.፻፳፯፥፫)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ነሐሴ ፰፤ ፳፻፲መተ ምሕረት

ከፍጥረታት ሁሉ የሰው ልጅ በቅድስት ሥላሴ አርአያና አምሳል የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው፤ የፍጥረት ሁሉ መፈጠር ትርጉም ያገኘው የሰው ልጅ ሲፈጠር ነው፤ እግዚአብሔር ፍጥረታትን በአርምሞ የፈጠራቸው፣ በመናገር የፈጠራቸው እና ካለሞኖር ወደ መኖር በማምጣት ፈጠራቸው፤ አዳምን (የሰው ልጅን) ሲፈጥር ግን በሦስቱም ግብር ነው፤ በማሰብ ‹‹…ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር›› ብሎ በመናገር፣ ከዚያም ከምድር አፈር (ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከውኃ፣ ከመሬት፣ ከነፋስ እና ከእሳት) በማበጀት በኋላም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ በማለት ፈጥሮታል፤ (ዘፍ.፩፥፳፮)ሰው ክቡር ፍጥረት ነው መባሉ ለዚህ ነው፡፡

እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነው፤ ሰው ደግሞ ከሁሉ ይልቃል፤ እግዚአብሔር አዳም በበደለ ጊዜ ልጅነቱንና ክብሩን ሲያጣ ከተድላ ገነት ተሰዶ አላውያን አጋንንት ሲያሠቃዩት፣ የብርሃን ኑሮው ወደ ጭለማ ሲቀየር ያድነው ዘንድ ከልዑል መንበሩ ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና ተወልዶ፣ መከራን ተቀብሎለትና በመስቀል ሞቶለት አዳነው፤ ነጻነትንም ሰጠው፤ ልጅነቱን ደግሞ መለሰለት፤ ከተድላ ገነት መለሰው፤ ጨለማውን ሕይወት ወደ ብርሃን ቀየረለት፤ በሞቱ ሞትን ድል ነሥቶ በትንሣኤው ትንሣኤውን አበሠረው፤ የሰው ልጅ ፈጣሪው ከልዑል መንበሩ ዝቅ ብሎ በበረት የተወለደለት በመስቀል የሞተለት ክቡር ፍጥረት ነው፡፡

አዳምን ከምድር አፈር አበጅቶ ሔዋንን ከአዳም ጎን አጥንት ነሥቶ ያስገኘ ጌታ በኪነጥበቡ ደግሞ ለአዳምና ለሔዋን ልጆችን ሰጠ፤ ስለ ሰው ልጅ አወላለድ ሰውን ከአባት አብራክ ዘርን ከፍሎ በእናት ማኅፀን በኪነ ጥበቡ እንደሚሠራው ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው እንዲህ ይነግረናል፤ ‹‹…ሕፃንን ከአባቱ ወገብ አውጥተህ ወደ ሴት ማኅፀን የምትልከው ሆይ፥ በረቂቅ ሰፋድልም የምትጠቀልለው  ውኃም ሲሆን በጥበብህ የምታረጋው የሕይወት መንፈስንም እፍ ትልበታለህ፤ በሆነ ሁኖ በአርባ ቀን ትሾመዋለህ…›› (ቅዳሴ አትናቴዎስ ገጽ ፪፻፸ ቁጥር ፻፲፫) ዘር ከአባት ወገብ ተከፍሎ በእናት ማኅፀን ከተፀነሰ ከአርባ ቀን በኋላ ተሥዕሎተ መልክ ይሰጠዋል፤             (እያንዳንዱ የሰውነቱ ክፍል፣ መልክ ይወጣለታል) ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲፈጸምም ይወለዳል፡፡

ልጆች ከእግዚአብሔር ለወላጅ በስጦታ ይሰጣሉ፤ ‹‹…ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የአብራክም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው …›› እንዲል፤ (መዝ.፻፳፯፥፫) ቅዱስ ቃሉ! የእግዚአብሔር ዋጋ የሆኑ የአብራክ ፍሬዎችን (ልጆች) ከመወለዳቸው በፊት በፅንስ ሳሉ እስኪወለዱ ድረስ አስፈላጊውን ጥበቃ፣ እንክብካቤ የማድረግ ሓላፊነት ደግሞ በአደራ የተቀበሉ የወላጆች ድርሻ ነው፤ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ በማኅፀን የሠራቸውን ፅንስ እንዳይወለዱ በማድረግ በተለያየ መንገድ ማስወገድ ተገቢ አይደለም፤ ምክንያም ከተፀነሱ ከአርባ ቀን በኋላ ለሰው ልጅ የሚያስልገው አካል ሁሉ ተስሎላቸው (ተስጥቷቸው) በማኅፀን ያለቸውን እድገት ጊዜ እየጠበቁ ናቸውና! እነዚህን ለማስወገድ መሞከር ደግሞ ‹‹አትግደል›› የሚለውን ሕግ ከመተላለፍ አይተናነስም፤ በሰው ሰውኛው ‹‹ሳንፈልገው አልያም ሳናቅድ›› በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ፅንስን ማጨናገፍ ከአባት ወገብ ዘርን ከፍሎ በእናት ማኅፀን ቋጥሮ አርግቶ ከሚፈጥር ከሠሪው ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው፤ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹..ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት፤ በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው፤ ጭቃ ሠሪውን ምን ትሠራለህ ወይስ ሥራህ እጅ የለውም ይላልን? አባትን ምን ወልደሃል ወይም ሴትን ምን አማጥሽ ለሚል ወዮ! የእስራኤል ቅዱስ ሠሪው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፤ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ…፡፡›› (ኢሳ.፵፭፥፱-፲፩)

የእግዚአብሔር ፍጥረት (ሥራ) የሆኑ ልጆች በራሳችን ፈቃድና ፍላጎት ልናስቀራቸው አልያም ልንወልዳቸው አንዳች ሥልጣንና የመወሰን አቅም የለንም፤ ሁሉ በእርሱ ይሆናል እንጂ በእኛ አይደለም፡፡ እንኳንስ ተፀንሰው ይቅርና ልጅን ላለመውለድ የዘር ፍሬውን እያስወገደ ከሚስቱ ጋር ይተኛ የነበረው አውናን በዚህ እኩይ ምግባሩ ተቀስፏል፤ ‹‹..አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ፤  ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስሰው ነበር፤ ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት እርሱንም ደግሞ ቀሰፈው …›› (ዘፍ.፴፰፥፲) እንዲል፤ ልጅ ከመፀነስ ቀድሞ የሚደረግ ይህ የልብ ክፋት እንዲህ ካስቀጣ ሰው ሆኖ በማኅፀን የተቋጠረውን ማጨናገፍማ ምን ያህል ያስጠይቅ ይሆን !? ‹‹…በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ስለሚያደርጉ ወዮላቸው…›› (ሚክ.፪፥፩) እንዲሁም ‹‹…እርሱ የሚፈልገው ምንድነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል…›› (ሚል.፪፥፲፭) ተብሏል፡፡

ልጆች ከተወለዱ በኋላ በምግባርና በሃይማኖት ኮትኩተን ልናሳድጋቸውና ልንንከባከባቸው ያስፈልጋል፤ ይህም የወላጅ ሓላፊነት ነው፤ የእግዚአብሔር መልአክ ለሶምሶን አባት ለማኑሄ እና ለሚስቱ ልጁን እንደሚወልዱ ባበሠራቸው ጊዜ ስለ ሚወለደው ልጅ አስተዳደግ ምን ማድረግ እንዳለበት ማኑኄ ጠይቋል፤  ‹‹…ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ሥርዓት ምንድር ነው? የምናደርግለትስ ምንድን ነው?…›› (መሳ.፲፫፥፲፪)  ይህ ኃይለ ቃል ልጆችን በሥርዓት የማሳደግ ሓላፊነት ወላጆች እንዳለብን ያስገነዝበናል፤ ልጆችን መውለድ ብቻ ሳይሆን የሥርዓትን መንገድንም ማሳየት ተገቢ ነው፤  ‹‹…ልጅህን በሚሄድበት መንገድ ምራው…›› እንደተባለው ማለት ነው፡፡ (ምሳ.፳፪፥፮) ካህኑ ዔሊ ልጆቹ አፊንንና ፊንሐስን በሥርዓት ቀጥቶ ከክፋታቸው እንዲመለሱ ባለማድረጉ በእነርሱ በአገርና በታቦተ ጽዮን በደረሰው ክፉ ነገር ደንግጦ ለመሞት በቅቷል፤ ‹‹..ልጆቹ የእርግማን  ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና …›› እንዲል፤ (፩ሳሙ. ፫፥፲፫) ልጆችን በሥርዓት አለማሳደግ ታላቅ ዋጋን ያስከፍላል፤ ስለዚህም ‹‹ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥፅ፤ መሞቱንም አትሻ …›› እንደተባለው (ምሳ.፲፱፥፲፰) ለልጆቻችን ቁሳዊ ነገር ከማሟላት በተጓዳኝ በቅርበት ሆነን ልንከታተላቸው፣ ሲሳሳቱ ልናርማቸው፣ ልናቀናቸውና  ልንመክራቸው ያስፈልጋል ፤

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!