ሰባቱ ኪዳናት

ክፍል አንድ

ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን  

ታኅሣሥ ፳፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ኪዳን ምንድን ነው?

ኪዳን ቃሉ ተካየደ ተማማለ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “ውል ስምምነት” የሚል ነው። በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ተዘምዶንና መቀራረብን መዋደድን አንዱ ለአንዱ ያለውን  ፍቅር ያመለክታል። ኪዳን ብዙውን ጊዜ የሚፈጸመው በቃል ስለሆነ “ቃል” የሚል አሳብ ተጨምሮለት ‘ቃል ኪዳን’ ይባላል። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት፣ በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፭፻፳፱)

ኪዳን በሰውና በእግዚአብሔር እንዲሁም በሰውና በሰው መካከል የሚመሠረት ስምምነት ነው። በሰዎች ደረጃ ያለውን ኪዳን እንደ ማስረጃ የምናየው የአብርሃምንና የአቤሜሌክን ታሪክ ነው። አቤሜሌክ በእርሱና በልጆቹ ላይ አብርሃም ክፉ እንዳያደርግበት ከእርሱ ጋር ተማምሎ ነበር፡፡ (ዘፍ.፳፩፥፳፪-፴፪) አብርሃምና አቤሜሌክ ያደረጉት ስምምነት ለጊዜው የአብርሃምን ኃያልነት ያሳይ እንጂ አብርሃምም ከአቤሜሌክ እንዲዋዋል ያደረገው የኪዳኑ መነሻ አለው። የአብርሃምን አየን እንጂ ኢያሱና በከነዓን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እንዲሁም ዳዊት ከእስራኤል ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን እንደ ማስረጃነት ይጠቀሳል። (ኢያ.፱፥፲፭፣፳፬፥፳፭፣ ፪ሳሙ.፭፥፫)

ሌላውና ዋናው ጉዳያችን እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር የሚያደርገው ቃል ኪዳን ነው። በባሕርይ የማይታየው እግዚአብሔር ምሕረቱ የበዛ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ከፍጥረቱ ጋር መሐላ ፈጽሟል። ከብዙ አበው ጋርም ቃል ኪዳን አድርጓል። የማይታይና ኃያል እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር የሚያደርገውን ውል ለተመለከተ ቸር አምላክ እንዳለው ያውቃል።

እናም ቃል ኪዳኑን ትውልድ እንደ ርስት እየተቀበለው የሚቀጥል ነው። “ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘለለም ኪዳን አቆማለሁ፤ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ” እንዲል (ዘፍ.፲፯፥፯)

“ለአባቶቻችን የገባኸውን መሐላ አስብ” መባሉ ለዚህ ነው። ምሕረቱን በአበው ቃል ኪዳን በኩል ጠብቆ እንዲፈጽም የተዋዋላቸውን ቅዱሳንን እያነሡ እግዚአብሔርን መጠየቅ የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ነው። እግዚአብሔርም መሐላውን አስቦ ስለ ዕገሌ ይህን አደርጋለሁ ይላልና። “ስለ ባሪያየ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ” ብሎ እንደ ተናገረው (ዘፍ.፳፮፥፩፬)። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቤተ ክርስቲያናችን የሚታወቁ ሰባት ኪዳናት አሉ። ከእነዚህም ኪዳናት መካከል አንደኛውና ቀዳሚው ኪዳነ አዳም ነው።

    ኪዳነ አዳም

ኪዳነ አዳም ማለት እግዚአብሔር ለአዳም የገባለት የምሕረት ቃል ኪዳን ማለት ነው። አምላካችን እግዚአብሔር አዳም ከበደለ በኋላ ወደ ገነት ተመልሶ እንደሚያስገባውና እንደሚያድነው  ቃል ኪዳን ገባለት። ዋናው የምሕረቱ ቃል ኪዳንም ያለው እዚህ ላይ ነው። “በሐሙስ ዕለት ወበ መንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ እወለዳለሁ ብሎ ኪዳኑን ሰጠው። (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ፪፥፳፫)

አዳም ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ቃል ኪዳኑን ተስፋ ሲያደረግ ቆይቷል። በፍርዱ ፈታሒነቱን በኪዳኑ ደግሞ መሐሪነቱን እያሰበ መቆየት ለአዳም ይገባው ነበርና፡፡ ዘመኑ ሲደርስ ደግሞ ከእመቤታችን ተወልዶ የገባለትን ቃል ኪዳን ፈጽሞለታል። “እወለዳለሁ” ብሎ ለአዳም እንደነገረው በመወለዱም ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ብርሃንና ጨለማ ታርቀዋል። የእነዚህ ሁሉ መታረቅ ግን እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ኪዳን ጊዜው ደርሶ ሲፈጸም ነው። ጊዜው ደረሰና በዘመነ ሥጋዌ ተወለደ።

ለአዳም የልጅነት ጸጋውን ቀራንዮ ላይ ተሰቅሎ የደም ዋጋ ከፍሎ መልሶለታል። ከገነት ሲወጣ “አድንሃለሁ” ብሎ የገባለት ቃል ኪዳንም ፍጻሜውን ያገኘው በቀራንዮ የተቆረሰውን ሥጋውን፣ የፈሰሰው ደሙን የአዳም ልጆች ሁሉ በመቀበል በክርስቶስ ጉንድነት ላይ ቅርንጫፍ ሆኖ በመብቀል ነው። ይህም ፈያታዊ ዘየማን ደመ ማኅተሙን ይዞ ገነትን በመክፈቱ ታውቋል።  እግዚአብሔር ለአዳምና ለልጆቹ ያለውን ፍጹም ፍቅርም ሰው ሆኖ በአዳም የተፈረደውን መከራ ተቀብሎ በማዳኑ ተገልጧል።

የአዳም ልጆች የሚባሉ የሰው ልጅ በሙሉ ለአዳም የተገባው ቃል ኪዳን ለሁላችንም በመሆኑ ሰው ሆኖ ያዳነን አምላክ ከማመስገን ጋራ በንስሓ፣ በንጽሕና ሆነን ሥጋውንና ደሙን በመቀበል የልጅነቱ ተካፋዮች በመሆን የገነት ወራሾች መሆን ይገባናል። ለዚህ የበቃን ያድርገን!

ይቆየን!