የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን

ክፍል አምስት

ዲያቆን ዳዊት አየለ
ታኅሣሥ ፳፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ስግደትና ምጽዋት

ስግደት “ሰገደ፣ ሰጊደ” “አጎነበሰ፣ ተንበረከከ፣ በሁለት በጉልበቱና በሁለት እጁ ምድርን ተመረኮዘ፤ ተደፋ፣ በግንባሩ መሬት ነካ፤ ወደቀ፡ ተነሣ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን “መስገድ፣ መውደቅ መነሣት” ማለት ነው፡፡ (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፲፩፻፷፩) የዓለማት ሁሉ ፈጣሪና ገዥ ለሆነው ለእግዚአብሔር መገዛታችንን ከምንገልጥባቸውና አምልኮታችንን ከምንፈጽምባቸው መንገዶች አንዱ ነው። “አምላክህንም እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ፥ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ…” እንደተባለው አምላካችንን በፍጹም ልባችን በመውደድ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እየሰገድን መገዛታችንን የምንገልጽበት መንገድ ነው። (ዘዳ.፮÷፭)

ጾም፣ ጸሎት፣ ምጽዋትና ስግደት መንፈሳዊ ትጥቆችና ሥጋችንን ለነፍሳችን እንዲሁም ለእግዚአብሔር የምናስገዛበት መንገዶች ሲሆኑ ስግደት ከሰው ልጅ በተጨማሪ “…መላእክቱም ሁሉ ይሰግዱለታል። ”(መዝ.፺፮÷፯) እንደተባለው ረቂቅ የሆኑ ቅዱሳን መላእክትም “…ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤…”(ኢሳ.፮÷፫) እያሉ በዙፋኑ ፊት የሚገዙበት መገለጫ ነው፤ እንዲሁም ስግደት የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ዓላማ (የሰው ልጅ የተፈጠረበት ዓላማ እግዚአብሔርን ማምለክና ክብሩን መውረስ ነው) ከሚያሳካባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡

፩) የስግደት ዓላማ

መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን በሁለት ክፍላ ታስተምረናለች፤ ይህ ማለት ስግደቱ ከሚቀርብለት አካል ማንነት አንጻር በሁለት እንከፍለዋለን ማለት ነው። የመጀመሪያው የአምልኮ (የባሕርይ) ስግደት የምንለው ሲሆን ይህም በባሕርዩ አምላክ ለሆነው ለእግዚአብሔር መገዛታችንን የምንገልጥበት “…እርሱን ብቻ አምልኩ…” እንደተባለው ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አምልኮትን የምናቀርብበት ነው፤ በዘወትር ጸሎት ላይ “ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁ” ማለቱ ይህንን ምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡ “አንዲት” የሚለው የስግደቱን መጠን ወይም ቁጥርን ለመግለጽ ሳይሆን ስግደቱ በባሕርዩ ለሚመለክ ለአንድ አምላክ የሚሰገድ፣ ለሌላ አካል የማይሰገድ የአምልኮ ስግደት መሆኑን ሲጠቁመን ነው፡፡ ይህን ስግደት ከእግዚአብሔር ውጭ ለማንኛውም ፍጡር ሆነ ፍጡር የሆነው ሰው ለሠራቸው ነገሮች መስገድ አይቻልም፤ ይህም ይታወቅ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ በሲና ተራራ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሰጠው ዓሠርቱ ትእዛዛት አንደኛውና የመጀመሪያው በሆነው ትእዛዙ “ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ…” (ዘፀ.፳፥፫) እንዳለው አብዝቶ የሚጠላውና የሚቆጣው ይህን ለእርሱ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለሌላ አካል አሳልፈን የምንሰጥ ከሆነ ነው፤ “…እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።”(ዘፀ.፳፥፭) ይላል።

ሁለተኛው እግዚአብሔር በጸጋ ላከበራቸውና ለእርሱም ምርጦቹ ለሆኑት እርሱ የባሕርዩ የሆነውን ቅድስና በጸጋ ሰጥቷቸው ቅድስናን ላገኙ ቅዱሳን ጻድቃን ሁሉ የሚሰገድ የጸጋ ስግደት ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ፣ ቅዱስ ዕፀ መስቀል ፣ ቅዱሳን መላእክት ፣ ሰማዕታት ፣ ጻድቃን ፣ ቅዱሳን ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፣ ታቦት ፣ እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ የዘወትር ጸሎት “ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁ” ብሎ አያቆምም፤ “አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምም እሰግዳለሁ፤ ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀልም እሰግዳለሁ”በማለት የጸጋ ስግደትን ለቅድስት ሥላሴ ከሚሰገደው የባሕርይ ስግደት ለይቶ እግዚአብሔር ለቀደሳቸው ሁሉ እንደሚገባ የሚያስረዳ ነው፡፡

ለቅዱሳን መስገድ እንደሚገባ እግዚአብሔር ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ለቅዱሳን መስገድ እንደሚገባ ያስረዳል፡፡ በዘፍ.፳፯÷፳፱ “አሕዛብ ይገዙልህ፤ አለቆችም ይስገዱልህ፤ ለወንድምህ ጌታ ሁን፤ የአባትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን፤ የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን” ብሎ ልጁን ያዕቆብን የባረከው ይስሐቅ ነበር፡፡ ይህን ምርቃት ማግኘት የነበረበት የያዕቆብ ታላቅና በኩር የነበረው ኤሳው ቢሆንም ያዕቆብ በእናቱ ብልሃት ታግዞ ተመረቀ፡፡ ይስሐቅን እንዲህ ብሎ እንዲመርቅ ያደረገው እግዚአብሔር አምላክም የአብርሃም ፣ የይስሐቅና የኤሳው አምላክ በመባል ፋንታ የአብርሃም ፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ተባለ፡፡ ሙሴ የአምላኩን ማንነት ለማወቅ ሽቶ በጠየቀ ጊዜ አምላካችን እግዚአብሔር እርሱ ራሱን ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የሚገልጥና ምድረ ርስትንም ሊሰጣቸው ቃል እንደገባ ለሙሴ ገልጾለታል፡፡ በይስሐቅም አንደበት አድሮ ያዕቆብን የባረከው እግዚአብሔር ነው፡፡

የንጉሥ አክአብ ባለሟል አብድዩ “ጌታዬ” ብሎ ለኤልያስ ሰግዷል።(፩ኛ ነገ.፲፰÷፯) ንጉሡ አካዝያስ በመጨረሻ ከኀምሳ ወታደሮች ጋር የላከው የኀምሳ አለቃም በኤልያስ ፊት እየሰገደ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ነፍሴና የእነዚህ የኀምሳው ባርያዎችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን፤” ብሏል። ለነቢዩ በመስገዱና የሚገባውን ክብር በመስጠቱ ልመናው ተሰምቶ እንደቀደሙት ከሰማይ በወረደ እሳት አልሞተም፤ የወታደሮቹንም ሕይወት አድኗል።(፪ኛ ነገ.፩ ÷ ፲፫) የኢያሪኮ ሰዎች ለኤልሳዕ በግምባራቸው ተደፍተው ሰግደውለታል።(፪ኛነገ.፪÷፲፭) ሱናማዊቷም ሴት በችግሯ ጊዜም በደስታዋም ጊዜ ሰግዳለታለች።(፪ኛነገ.፬÷፳፯-፴፯) በሐዲስ ኪዳንም የወኅኒው ቤት ጠባቂ ለቅዱስ ጳውሎስና ለሲላስ እየተንቀጠቀጠ በግምባሩ ተደፍቶ ሰግዶላቸዋል። (ሐዋ.፲፮÷፳፱)

፪) በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የስግደት አፈጻጸም ሥርዓት

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ አፈጻጸም ሥርዓት አንጻር ስግደትን በሦስት እንመድባለን፡፡ የመጀመሪያው የስግደት አፈጻጸም ሥርዐት ታላቁ ሐዋርያ በራእዩ “ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ።” እንዳለው መሬት ላይ በመውደቅ ወይም ሙሉ በሙሉ ተደፍተው የሚሰግዱት ስግደት ሲሆን በልዩ ስሙ ሰጊድ(ወዲቅ) በመባል ይታወቃል፤ (ራእ.፲፱ ፥፲) ግንባርን፣ የታጠፉ ጣቶችን፣ ጉልበትን መሬት አስነክቶ መስገድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ “ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ” (ዘፍ.፲፱ ፥ ፩)፤ “ሰገደም በግንባሩም ተደፋ”(ዘኁ.፳፪ ፥ ፴፩)፤ “በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ” (ኢያ.፭፥፲፫)፤ “ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት”(ሐዋ.፲ ፥ ፳፭) እና መሰል የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች “ወዲቅ” መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው የስግደት ዐይነት መሆኑን የሚያስረዱ ናቸው፡፡

አሁንም ከአፈጻጸም ሥርዓት አንጻር ሁለተኛው የስግደት ዐይነት የምንለው አስተብርኮ በመባል ይታወቃል፤ ይህም ስያሜው እንደሚጠቁመው ዝቅ ብሎ ጉልበትን ሸብረክ በማድረግ መሬትን በግንባር ሳይነኩ፣ በጉልበት በመቆም ወይም በመንበርከክ የሚፈጸም ነው፡፡ “በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጥቶ…”(ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ) ወዶ ፈቅዶ ራሱን ዝቅ አድርጎ በድኅነት ከፍ ላደረገን ክርስቶስ የአምልኮ ስግደትን መስገድ እንዲገባ ሲያጠይቅ “…ጉልበት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው…”በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ በላከው መልእክቱ የአስተብርኮ ስግደትን ለክርስቶስ መስገድ እንደሚገባ አስረድቷል፡፡ (ፊል.፪ ፥ ፲)

ሦስተኛው የስግደት አፈጻጸም ዓይነት አድንኖ ይባላል፤ አድንኖ ራስን፣ ግንባርን፣ አንገትን ዝቅ በማድረግ የሚሰገድ የስግደት ዓይነት ነው። በቅዳሴያችን ጸሎት መጨረሻ ላይ አገልጋዩ በሆነው ካህን እጅ እግዚአብሔር ይባርከን ዘንድ ዲያቆኑ “አድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ…ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ…” በማለት የሚያዘን ይህንኑ ነው፡፡
እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት የማይሰግድባቸው ጊዜያቶችም ተለይተው የታወቁ ናቸው፤ እነዚህም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት)፣ በበዓለ ኀምሳ፣ ከቆረብን በኋላ፣ በጌታ በዓላት፣ በድንግል ማርያም በዓላት፣ በቅዱስ ሚካኤል በዓል ናቸው፤ በእነዚህ ጊዜያት አይሰገድም። ነገር ግን በሰሙነ ሕማማት ማንኛውም በዓል ቢውል ይሰገዳል፤ የስቅለት ቀን በዓለ ማርያምም ቢውል፣ በዓለ ሚካኤልም ቢውል፣ በዓለ እግዚእም ቢውል ይሰገዳል።

የምጽዋት ሥርዓትና ልናደርጋቸው የሚገቡ ነገሮች

ምጽዋት ሰው ለሚሹት ሰዎች በገንዘብ የሚያደርገው ርኅራኄ ነው፤ እግዚአብሔር ገንዘባችሁን ለነዳያን ምጽዋት ስጡ እንዳለ እንደ ብድር ከሰጠነው ሰው መልሰን የምንቀበለው ያይደለ ልግስና ነው። “ምጽዋትስ የርኅራኄ ወገን ናት፤ ይሄውም ገንዘቡን ለሚፈልጉት ሰዎች የሰው መራራቱ ነው” እንዳሉ ፫፻ (ሠለስቱ ምዕት) ምጽዋት የይቅርታ ወገን ናት። ሰው የተቻለውን ያህል ምጽዋት በመስጠት ፈጣሪውን ይመስለዋል፤ ምጽዋት በመስጠት ለሰው መራራት ከአምላክ ባሕርይ የተገኘ ነው፤ ጌታም እንደሰማዩ አባታችሁ ለሰው የምትራሩ የምታዝኑ ሁኑ ብሏልና።

ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ብልህ ሰው ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ዘንድ አደራ መስጠቱ (ማበደሩ) ነው፤ ጠቢቡ ሰሎሞንም ”ለደኃ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” በማለት ምጽዋት ማለት ለእግዚአብሔር ማበደር እንደሆነ ያጠይቃል። (ምሳ.፲፱÷፲፯) ደካሞችን በጉልበት፣ ያልተማሩትን በዕውቀት የሙያ ርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት ምጽዋት ነው፡፡ ምጽዋት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና በሐዲስ ኪዳናት በሰፊው ተገልጦ ይገኛል፡፡ ”ድሆች ከምድር ላይ አይታጡምና በሀገር ውስጥ ላለ ደኃ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ”(ዘዳ.፲፭÷፲፩)፤ “ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው እንደ እንግዳ እንደመጻተኛ ካንተ ጋር ይኑር”(ዘሌ.፳፭÷፴፭)፤ የሚሉ መሠረታዊ ትእዛዞችን እንዲሁም ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ በነቢያቱ አንደበት ተናግሯል፡፡ “…እኔ የመረጥሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን?” (ኢሳ.፶፯÷፯)

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም በትምህርቱ ተማርከው ለመጠመቅ የመጡትን ሰዎች እንዲህ በማለት የምጽዋትን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል፡፡ ”ሁለት ልብስ ያለው ሰው ለሌላው ያካፍል ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ “እንዲል፡፡ (ሉቃ.፫÷፲፩)

መዝሙረኛው ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ”ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እርሱንም እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል” በማለት ምጽዋት የሚመጸውተውን ሰው እግዚአብሔር አምላክ ከክፉ እንደሚጠብቀው ይናገራል። (መዝ.፵÷፩-፪) ጠቢቡ ሰሎሞንም “እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው ከብዙ ዘመን በኋላ ታገኘዋለህና” እያለ ዛሬ ላይ ለነዳያን በምናደርገው ልግስና የምጽዋቱን ዋጋ በገነት በመንግሥተ ሰማያት እንደምናገኝ ያረጋግጥልናል፡፡(መክ.፲፩÷፩) በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረህ ሳትታይ ምጽዋት ስጥ ውኃ የበላው እንዳይገኝ ከዚያ ተመጽዋች ዋጋ አገኛለሁ ሳትል ምግብህን በከርሠ ርኁባን መጠጥህን በጕርዔ ጽሙኣን አኑር ማለት ነው።

ምጽዋት የማንመጸውት ከሆነ በፍርድ ሰዓት በጌታችን ፊት ስንቆም ለምንጠየቀው ጥያቄ በቂ ምላሽ አይኖረንም በመጨረሻዋ የፍርድ ጊዜም “ተርቤ አላበላችሁኝምና፤ ተጠምቼም አላጠጣችሁኝምና፤ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፤ ታርዤም አላለበሳችሁኝምና፤ ታምሜም አልጎበኛችሁኝምና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ አልጠየቃችሁኝምና” የሚል መራር የሆነ ወቀሳ ተግሣጽና ፍዳ ይጠብቀናል፡፡ (ማቴ.፳፭÷፵፪-፵፫) ሰው ከሚፈረድበት የጥፋት ሥራ አንዱ ለድሆች አለማዘንና አለመራራት ነው፡፡ “ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበም ችግረኛና ምስኪንን አሳዷልና“ ይላልና ለሰው ማዘንና ምጽዋትን ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታ(ድርሻ) ነው፤ (መዝ ፻፰÷፲፭) መንግሥተ ሰማያትንም የሚያሰጥ ነው።

ምጽዋት ስንመጸውት “ምጽዋትህ በስውር ይሁን፤ በስውር የሚያይህ አባትህም በግልጥ ዋጋህን ይሰጥሃል” እንዳለን ጌታችን ለነዳያን ስንመጸውት ከከንቱ ውዳሴ በመራቅ በስውር መሆን አለበት፤(ማቴ.፮÷፬) እንዲሁም ስንመጸውት ያለ ኀዘን በተድላ በደስታ ይሁን፤ ጸጸት አይኑር ሰጭውም ምጽዋት በሚሰጠው ሰው ላይ የሚታበይ አይሁን፤ ሰው ወዳጅ ይሁን እንጅ። በመሆኑም እነዚህንና መሰል በጎ ምግባራትን ማድረግ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ›› ብሎ እንዳስተማረን በተሰጠን ጸጋ ያለ መሰሰት ማገልገልና በልግስና መሥጠት ያስፈልጋል፤ ይህንን ብናደርግ ዋጋችን ታላቅ ነው፡፡ (ማቴ.፲፥፰)

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ምንጭ፦ ፍትሐ ነገሥት(ፍት.መን)፥ ፍትሐ ነገሥት ምን አለ? በመምህር በጽሐ ዓለሙ፥ መጽሐፈ ምዕዳን በአባ ገ/ኪዳን፥ ነገረ ቅዱሳን በቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው