ሥርዓተ ንባብ
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
ወበሳኒታ ፈቀደ ይሑር ገሊላ ወረከቦ እግዚእ ኢየሱስ ለፊልጶስ ወይቤሎ ትልወኒ። ወውእቱ ፊልጶስ ዘቤተ ሳይዳ እምሀገረ እንድርያስ ወጴጥሮስ። ወረከቦ ፊልጶስ ለናትናኤል ወይቤሎ ረከብናሁ ለኢየሱስ ወልደ ዮሴፍ ዘእምናዝሬት ዘጸሐፈ ሙሴ ውስተ ኦሪት ወነቢያትኒ ተነበዩ በእንቲኣሁ። ወይቤሎ ናትናኤል ለፊልጶስ ቦኑ ይትከሀል እምናዝሬት ይጻእ ኄር ብእሲ ወይቤሎ ፊልጶስ ነዓ ትርአይ። ወሶበ ርእዮ እግዚእ ኢየሱስ ለናትናኤል እንዘ ይመጽእ ኀቤሁ ወይቤ በእንቲኣሁ ነዋ ዘበአማን እስራኤላዊ ዘአልቦ ጽልሑት ውስተ ልቡ። ወይቤሎ ናትናኤል በአይቴ ተአምረኒ፤ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ እምቅድመ ይጸውዕከ ፊልጶስ ርኢኩከ በታሕተ ዕፀ በለስ። ወአውሥአ ናትናኤል ወይቤሎ ረቢ አማን አንተ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር ወንጉሠ እስራኤል አንተ። ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ እስመ እቤለከሁ ርኢኩከ በታሕተ ዕፀ በለስ ተአምንሁ፤እምይእዜሰ ዘየዐቢ እምዝ ትሬኢ። (ዮሐ.፩፥፵፬-፶፭)
ውድ አንባብያን ባለፈው ትምህርታችን ስለወዳቂ ንባብ መጻፋችንና ከላይ የቀረበውን ምንባብ መሠረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥያቄዎችንም ማቅረባችን ይታወቃል። መልሱን እንደሚከተለው እናቅርብና ወደሚቀጥለው ትምህርት እናመራለን።
በካዕብ የሚነገር ወዳቂ፡- ረከብናሁ፣ በእንቲኣሁ፣ ቦኑ፣ ኀቤሁ፣ልቡ፣ እቤለከሁ፣ ተአምንሁ
በሣልስ የሚነገር ወዳቂ፡- ረቢ፣ እስራኤላዊ፣ ብእሲ
በራብዕ የሚነገር ወዳቂ፡- ገሊላ፣ ነዋ፣ ወበሳኒታ፣ ነዓ
በኃምስ የሚነገር ወዳቂ፡-ይቤ፣ በአይቴ
በሳብዕ የሚነገር ወዳቂ፡- ወረከቦ፣ ወይቤሎ፣ ርእዮ፣ ዘአልቦ
ውድ አንባብያን መልሱን በዚህ መልኩ መልሳችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ ቀጥለን ደግሞ ባለፉት ተከታታይ እትሞቻችን ስለ ንባብ ምንነት፣ዓይነትና ስልት እንደተመለከትን ይታወቃል፡፡ በዚህ ክፍል የመጨረሻ የሆነውን ንባብን በተመለከተ አጠቃላይ ክለሳ እናደርጋለን።
የንባብ ምንነት ፡- “አንበበ፣አነበበ” ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን በጽሑፍ የሠፈረን መልእክት ማነብነብ፣መናገር ፣ ሆሄያትን መጥራት፣ መቁጠር፣ወዘተ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድም “ንባብ በቁሙ፤ ነገር፣ ቃል፣ ጩኸት” (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ገጽ ፮፻፲፱) በማለት ይፈቱታል፡፡ አለቃ ቃል፣ ጩኸት በማለት የገለጹት ድምፅን አውጥቶ የሚያነበንቡትና የሚጠሩት መሆኑን ለማመልከት ነው።
በሌላ አገላለጽ፡- ንባብ ማለት ከአንድ የተጻፈ ነገር ላይ መሠረታዊ የሆነውን ሐሳብ መረዳት፣ ነጥሎ ማውጣት፣ የጸሓፊውን መልእክት መገንዘብ፣ ወዘተ እንደሆነ የቋንቋ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ሥርዓተ ንባብ፡- በማንኛውም ቋንቋ የአነባበብ ሥርዓት አለ፡፡ በአነባበብ ሥርዓትም የተነሣ በድምፅም፣ በቃላትም፣ በመዋቅርም ወዘተ ተመሣሣይ ከሆኑ አደረጃጀቶች (መዋቅሮች) የተለያዩ መልእክቶችን እናገኛለን፡፡ የአነባበብ ሥርዓታችንን ባለማስተካከላችን በርካታ የትርጉም ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ይህ እንደ ማንኛውም ቋንቋ ሲሆን የግእዝ ቋንቋ ደግሞ እጅግ ትኩረት የሚያሻው ነው፡፡ ለምሳሌ ቀደሳ በተነሽና በወዳቂ ሲነበብ የሚሰጠው ትርጉም የተለያየ ነው፡፡ ቀደሳ በወዳቂ ሲነበብ ትርጉሙም አከበራት የሚል ይሆናል፡፡ ቀደሳ በተነሽ ሲሆን ደግሞ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶች አመሰገኑ የሚል ይሆናል፡፡
የግእዝ ቋንቋ ሥርዓተ ንባብ፡- የግእዝ ቋንቋ ሥርዓተ ንባብን ስናነሣ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ልብ ሊባሉ ይገባል፡፡ የመጀመሪያው በግእዝ፣ በውርድና በቁም ንባብ የሚነበበው ነው፡፡
ግእዝ ንባብ፡- ይህን ንባብ አንድ ሰው ፊደል ከመለየት አልፎ ወደ ንባብ ሲሸጋገር እያንዳንዱን ፊደል እየቆጠረ ዜማ ባለው መልክ የሚያነበው ነው፡፡
ውርድ ንባብ፡- ይህ ንባብ ኃዘንና እንጉርጉሮ በሚመስል ድምፅ የሚነበብ ነው፡፡ ይህ ንባብ ብዙ ጊዜ በዕለተ ስቅለት ከዳዊት መዝሙር የተውጣጡት ምንባባት ይነበቡበታል፡፡
ቁም ንባብ፡- ይህ ምንባብ መደበኛው የንባብ ስልት ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ግእዝ ንባብና ውርድ ንባብን ካጠናቀቀ በኋላ የሚያነበው ነው፡፡ በዚህ ንባብ ፊደላትን በትክክል ለይቶ ለራሱም ሆነ ለሰሚ በተገቢው ሁኔታ የሚያነቡበት ሂደት ነው፡፡
ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ የግእዝ ቋንቋ ንባብን ስናነሣ ከቃላቱ ድምፀት ማለትም መነሣት፣ መጣል፣ ተናቦ ከመነበብ፣ ጠብቆ ከመነበብ፣ ላልቶ ከመነበብ ወዘተ ጋር ተያይዞ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ እሊህንም ዐበይት ንባባትና ንኡሳን ንባባት ብለን በሁለት ከፍለን ተመልክተናቸዋል።
ዐበይት ንባባት፡- ዐበይት ንባባት የሚባሉት አራት ሲሆኑ እነሱም ተነሽ፣ ተጣይ፣ ወዳቂና ሰያፍ ናቸው፡፡ ንኡሳን ንባባት ደግሞ ተናባቢ፣ ኢተናባቢ፣ ጠብቀው የሚነበቡ፣ ላልተው የሚነበቡ፣ በጥቅል የሚነበቡ፣ በተናጠል የሚነበቡ ወዘተ ናቸው፡፡
፩. ተነሽ፡– ይህ ንባብ ድምፅን በማንሣትና በማውጣት የሚነገር ሲሆን በአምስት ፊደላት ይነገራል፡፡ ፊደላቱም ግእዝ፣ ካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ሳብዕ ናቸው፡፡
ተነሽ በግእዝ ሲነገር፡- “እግዚአብሔር ቆመ ውስተ ማኅበረ አማልክት፤ እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ” (መዝ.፹፩፥፩) እንዲል፡፡
ተነሽ በካዕብ ሲነገር ፡- “ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፤ ወደ ፈተናም እንዳትገቡ ትግታችሁ ጸልዩ” (ማቴ.፳፮፥፵፩) እንዲል፡፡
ተነሽ በሣልስ ሲነገር፡- “ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ፤ ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሺ” (መዝ.፵፬፥፲)እንዲል ፡፡
ተነሽ በራብዕ ሲነገር፡- ወበእሑድ ሰንበት በጽባሕ አሌለያ ገይሰ ወሖራ ኀበ መቃብር ፤ በእሑድ ሰንበትም በጥዋት ማልደው ገስግሰው ወደ መቃብር ሔዱ፤ (ሉቃ.፳፬፥፩) እንዲል፡፡
ተነሽ በሳብዕ ሲነገር፡- “እግዚኦ ኵነኔከ ሀቦ ለንጉሥ፤ አቤቱ ፍርድህን ለንጉሥ ስጠው” (መዝ.፸፩፥፩) እንዲል፡፡
ማስታወሻ፡- መራሕያን ከቅርብ ብዙ ሴቶችና ከሩቅ ብዙ ሴቶች (አንትን እና ውእቶን) በቀር (አነ፣ንሕነ፣ አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ) ሁሉም ተነሽ ናቸው፡፡
-ተነሽ ከሰባቱ ፊደላት ውስጥ በሁለቱ በፍጹም አይነገርም፡፡ እነሱም ኃምስና ሳድስ ናቸው
፪. ተጣይ፡– ተጣይ ማለት በአነባበብ ሥርዓቱ ጣል ተደርጎ የሚነበብ ማለት ነው። ከመጨረሻው ፊደል ቀድሞ የሚገኘውን ፊደል ያዝ አድርጎ ይጣልና ይነበባል። ተጣይ በሳድስ ፊደል ብቻ ይጨርሳል (ይነገራል)። ምሳሌ፡- ወናሁ ሳድስ ዝንቱ ወርኅ ለእንተ ይብልዋ መካን
፫. ሰያፍ፡– ማለት በአነባበብ ሥርዓቱ በሰያፍ የሚነበብ ማለት ነው። ይህ ማለት ቀና ተደርጎ ወይም ተነሥቶ የሚነበብ እንደማለት ነው። ከመጨረሻው ፊደል ቀድሞ ከሚገኘው ጀምሮ በማንሣት ይነበባል። እንደተጣይ ሁሉ በሳድስ ብቻ ይጨርሳል (ይነገራል) ።
ምሳሌ፡- እንተ ተፍኅረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ
፬. ወዳቂ ንባብ፡- ወዳቂ ንባብ በአነባበብ ሥርዓቱ ወድቆ ወይም ተጥሎ የሚነበብ ሲሆን በሰባቱም ፊደላት ይነገራል።
ወዳቂ በግእዝ ሲነገር፡- ንግበር ሠለስተ ማኅደረ አሐደ ለከ፣ ወአሐደ ለሙሴ፣ ወአሐደ ለኤልያስ፤
ወዳቂ በካዕብ ሲነገር፡- ወሀሎ አሐዱ ብእሲ ዘስሙ ኒቆዲሞስ እምፈሪሳውያን መልአኮሙ ለአይሁድ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። (ዮሐ.፫፥፩)
ወዳቂ በሣልስ ሲነገር፡- ዘበደኃሪ መዋዕል ፈኖከ ለነ ወልደከ መድኅነ፤ በኋለኛው ዘመን መድኃኒት የሆነ ልጅህን ላክህልን። (መጽሐፈ ቅዳሴ)
ወዳቂ በራብዕ ሲነገር፡- አብሠራ ገብርኤል ለማርያም ወይቤላ ተፈሥሒ ፍሥሕት
ወዳቂ በኃምስ ሲነገር፡- ውዳሴ ወግናይ ለእመ አዶናይ
ወዳቂ በሳድስ ሲነገር፡- ዝ ውእቱ ዘእግዚአብሔር ቃል ማስታወሻ ፡- በሳድስ የሚነገር አንድ ዝ ብቻ ነው።
ወዳቂ በሳብዕ ሲነገር፡- እግዚኦ ኵነኔከ ሀቦ ለንጉሥ
ማስታወሻ ከላይ እንደተመለከትነው ወዳቂ ንባብ ከግእዝ እስከ ሳብዕ በሰባቱም ፊደላት ይነገራል። ወዳቂ የማይነገርበት ፊደል የለም።