«አቤቱ፥ አምናላሁ፤ ነገር ግን አለማመኔን ርዳው» (ማር.፱፥፳፬)

መምህር ኃይለማርያም ላቀው

«እምነትስ፣ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፥ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት» (ዕብ. ፲፩፥፩) እንደተባለው ሰው ተስፋን ከአምነት ያገኛል፡፡ አዳም ቢበድልም እንኳን ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር በኋላ ዘመን ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል በጋባለት ጊዜ  ተስፋ አግኝቷል፡፡ የመዳኑ ነገር በእምነቱ ተስፋ ሆነለት፡፡ እምነት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት፣ እርሱን ደስ የምናሰኝበት የሕይወት መሠረት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያስረዳ «ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም» ብሏል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፮)

በዘመነ ብሉይ የነበሩ በእምነት ጥንካሬአቸው የተመሰከረላቸው አበውና እመው በእግዚአብሔር በመታመናቸው በሚያቃጥል የእሳት ነበልባል ውስጥ በመጣል፣ ወደ አንበሳ ጉድጓድ በመወርወር፣ በሰይፍ በመተርተር እምነታቸውን ገልጠዋል፡፡ እግዚአብሔርም በቅዱሳን የእምነት ጥንካሬ የልበ ደንዳኖችን ልብ ማርኳል፡፡ ንጉሡ ናቡከደነጾር ለጣዖት አንሰግድም ብለው እምነታቸውን የገለጡትን ሠለስቱ ደቂቅን ርዝማኔው አስራ ስድስት ክንድ ከሚደርስ የእሳት ነበልባል ውስጥ በሰንሰለት አስሮ ቢወርወራቸውም ሰውነታቸው አንዳች ሳይቃጠል ድነዋል፤ «በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ፥ የአብደናጎም አምላክ ይመስገን» (ዳን. ፫፥፳፰) ሲልም የሠለስቱ ደቂቅን አምላክ አክብሯል፡፡

በዘመነ ሐዲስ በሰው ፍቅር ተስቦ ወደዚህ ዓለም የመጣው ቸሩ አምላክ ለአገልግሎት ከመረጣቸው ሰዎች አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት መሠረታዊ የሃይማኖት ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎችን የመረጠው በዘመኑ በዕውቀታቸው የሚታበዩ ሰዎችን ዕውቀት ከንቱ ለማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን የዓለምን ጥበብ ከንቱ ለማድረግ አላዋቂዎችን እንደመረጠ ሲያስረዳ፤ «ነገርግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ሊያሳፍር የዚህን ዓለም ሰነፎች መረጠ፤ ኀይለኞችንም ያሳፍር ዘንድ እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ደካሞች መረጠ፡፡አለን የሚሉትንም ያሳፍር ዘንድ የሌላቸውና የተናቁትን፥ከቊጥርም ያልገቡትን እግዚአብሔር መረጠ»ብሏል፡፡(፩ኛቆሮ.፩፥፳፯-፳፰)

እግዚአብሔር ለእምነት አገልግሎት ሰዎችን ሲመርጥ ሞኞች ጠቢባን ይሆናሉ፤ ዐላዋቂዎች ሀብተ ዕውቀት ያገኛሉ፤ ደካማዎች ብርቱዎች ይሆናሉ፡፡ ዐላዋቂ የነበሩት ተከታዮቹ ጠቢባን፤ ደካማ የነበሩት ብርቱዎች እስከሚሆኑ ድረስ ለቀጣይ የእምነት ሕይወታቸው ብርታት እንዲሆናቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጌታችን ያቀርቡ ነበር፡፡

ጌታችን የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የተከተሉትን ለሕይወት ደኅንነት የሆነውን ትምህርቱ በነፍስ የታመሙትን፣ ተስፋ የቆረጡትን፣ ባዶነት የሚሰማቸውን፣ መንፈሳዊ ዝለት የገጠማቸውን ሲያድን፤ በተአምራቱ ደግሞ በሕማመ ሥጋ የታመሙትን ፈውሷል፡፡ የጌታችንን ትምህርት ፈልገው የተከተሉ አብዛኛዎች በተከፈለ ልብ ነበር፡፡ መድኃኒታችን የተከፈለ ልብ ያላቸውን ማረጋጋት፣ ያዘኑትን ማጽናናት ግብሩ በመሆኑ ድክመታቸውን ሳይሸሸጉ የሚቀርቡትን ፈጣን ምላሽ ይሰጣል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይከተሉ ከነበሩ ሰዎች አንዱ ወደ እርሱ ተጠግቶ ልጁን ዲዳ ጋኔን ስለያዘው እንዲፈውስለት ተማጸነው፡፡ እንዲህም አለው፤ «ብዙጊዜ ሊገድለው ወደ ገደል ወደ እሳትም ወደ ውኃም ይጥለዋል፤ ነገር ግን ቢቻልህ እዘንልኝ፤ ርዳኝም» አለው፡፡ ጌታችንም መልሶ «ቢቻልህ ብለሃል፤ ብታምንስ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል» አለው፡፡ የዚያ ብላቴና አባትም፥  «አቤቱ፥ አምናላሁ፤ ነገር ግን አለማመኔን ርዳው ብሎ ጮኸ፡፡ጌታችን ኢየሱስም አንተ ዲዳ፥ ደንቆሮም ጋኔን ከእርሱ እንድትወጣ፥ ዳግመኛም እንዳትመለስበት እኔ አዝዤሃለሁ» ብሎ ጋኔኑን ገሠጸውና አስወጣለት፡፡ (ማር.፱፥፳፪-፳፮)

የጌታችን ደቀ መዛሙርት ልጁን እንዲፈውስለት የወሰደው ሰው፤ ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ የእምነት ማነስ የተነሣ ፍቱን መፍትሔ ቢያጣም ከጌታችን ዘንድ መጥቶ የእምነቱ ጉድለት በጌታችን እንዲስተካክልለት የልጁን ሕማም ሁኔታ ለጌታ ሲነግረው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ «ቢቻልህ የሚለውን» የጥርጣሬ ቃል «ቢቻልህ ብለሃል፤ ብታምንስ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል» በሚል ቃል ሲያርመው የተቸገረው ሰው አለማመኑ በእርሱ እንዲጠገንለት «በታላቅ ድምፅ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው» ብሎታል፡፡ ይህ ሰው አምናለሁ አለማመኔን እርዳው በማለት በእምነት ሕይወት ውስጥ ያለበትን ችግር ሳይሸሸግ መናገሩን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እያመን የማናምን፣ ንስሓ እየገባን የማንፀፀት፣ እየቆረብን ለሥጋ ወደሙ ክብር የማንሰጥ፣ እየቀደስን ያልተቀደስን ብዙዎች ነን፡፡ እኛም እናምናለን ነገር ግን እምነታችን በአንተ ይታገዝ ርዳን ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ መወለዱን፣ መጠመቁን፣ ከሙታን መነሣቱን (ትንሣኤውን መግለጡን) ያምናሉ፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እና ተስፋ ግን ይጠራጠራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እያመንን በእምነት ሕይወት ውስጥ አንኖርም ለዚህ ማለዘቢያ ግን እምነታችን፣ አለማወቃችንና ድካማችን በጌታችን እንዲደገፍ መማጸን ነው፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያት የታመመውን ልጅ ለመፈወስ አቅም ያጡበትን ምክንያት ለመረዳት፤ «ስለምንእኛ ማውጣት ተሳነን?» ሲሉ ጌታችንን ጠይቀውታል፡፡ (ማቴ.፲፯፥፲፱) ይህ ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የተሰጠኝን ሓላፊነት ያልተወጣሁት ስለምንድነው? ያልቆረብኩት ስለምንድነው? ከልቤ ውስጥ የሚጉላላውን ቂም ያላወጣሁት ስለምንድነው? የበደልኩትን ያልካስኩት ስለምንድነው? የሚፈታተነኝን የሰይጣን ፈተና ማለፍ ያልቻልኩት ስለምንድነው? መንፈሳዊ ሕይወቴ ማደግ ያልቻለው፣ ራሴን ማወቅ መረዳት ያልቻልኩት ስለምንድነው? ብለን እንድንጠይቅ የቅዱሳን ሐዋርያት ጥያቄ ይረዳናል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እግዚአብሔር ከጎናቸው እያለ የእምነት ጉድለት ስለታየባቸው ማድረግ የሚገባቸውን ለመፈጸም አልቻሉም፤ ነገር ግን በልባቸው የነበረውን ጥያቄ መጠየቃቸው መልካም ነበር፡፡ ምክንያቱም በእምነት ሊያደርጉት የሚቻላቸውን ነገር ማድረግ የተሣናቸው ስለእምነታቸው ጉድለት መሆኑን ጌታችን አስረግጦ እንዲህ በማለት ነግሯቸዋል፡፡ «የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ብትኖራችሁ ይህችን ሾላ ከሥርሽ ተነቅለሽ በባሕር ውስጥ ተተከዪ ብትሉአት ትታዘዝላችኋለች» (ሉቃ.፲፯፥፮) ብሏቸዋል፡፡ «ማመን፣ ያመኑትን ማድረግ» ከባድ ነገር ነው፡፡ ዛሬ ስለእምነት፣  በእምነት ሕይወት ስለመኖር፣ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ የቅዱሳንን ገድልና ትሩፋት በመግለጥ ብዙ ነገር ተነግሮናል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቻችን ቃሉ በጭንጫ ላይ የተዘራ ዘር ሆኖብናል፤ «ጌታችን በጭንጫ ላይ ዘር ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ደረቀ» ያለውን ሲፈታ «በጭንጫ ላይ የተዘራውም  ቃሉን የሚሰማና ፈጥኖ በደስታ የሚቀበለው ነው፡፡ ነገር ግን፥ ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ላይ ሥር የለውም፤ በቃሉም ምክንያት መከራ፥ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይክዳል» ብሏል፡፡ (ማቴ. ፲፫፥፳-፳፩)

በእምነት መንፈሳዊ ሕይወታቸው አልጸና ብሎአቸው ይቸገሩ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን ያቀረቡት ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ አግኝቶ፤ የሰውነታቸው ለልብሳቸው፤ የልብሳቸው ለጥላቸው አልፎ ሕሙም ከመፈወስ ሙት እስከ ማስነሣት ደርሰዋል፡፡ ይኸውም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በዚህም አገልግሎታቸው እንደ ሠመረላቸው መረዳት ይቻላል፡፡

እኛም «በሃይማኖት ስትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ» ተብሎ እንደተነገረን፤ በቅድሚያ መንፈሳዊ ሕይወቴ ያላደገው ለምንድነው? ብለን ያለንን የእምነት ጥንካሬና ድክመት መመዘን አለብን፡፡ በማስከተል እንደ ታመመው ልጅ አባት «አለማመኔን ርዳው» የሚል ጥያቄ አቅርበን፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ፍጹም እምነት ሲኖረን ጌታችን እንዳለው ተራራ የሆነብን ትዕቢት፣ ከፊታችን የተደቀነው ክፋት፣ ምቀኝነት ከሕይወታችን ይነቀላል፡፡ አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ካለንበት ችግር፣ ከመጣብን ቸነፈር እንጠበቃለን፡፡

ያ በእምነት ያልጸናው ሰው ለእግዚአብሔር አምላኩ «አለማመኔን ርዳው» ሲል ያቀረበው ጥያቄ የሁላችንንም ሕይወት የሚወክል ነው፡፡ ዛሬ እምነቱ ሥርዓቱ፣ ትውፊቱ እያለን በፍጹም ልብ ያለማመናችን ያመጣብን ብዙ ችግር አለ፡፡ ልጁ የታመመበት ሰው «አለማመኔን ርዳው»  ሲል በአንተ ታምኜ የምኖርበትን ኃይል ለአንተ የሚገዛ ልብና ሕይወት ስጠኝ ማለቱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ከአባቶቻችን የተቀበልነው እምነት የፈተና ጎርፍ ሳይሸረሽረው ነፋስ ሳያዘመው በዐለት ላይ ተመሥርቶ እንዲጸናልን ዘወትር «ጌታ ሆይ አለማመኔን ርዳው» ማለት አለብን፡፡ ያለማመናችን ችግር በእግዚአብሔር ካልተረዳ «ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ» በማለት ብቻ መንግሥተ ሰማያትን እንደማንወርስ ተነግሮናል፡፡ በመሆኑም ልባሞች ከመብራታቸው ጋር ዘይት ይዘው ሙሽራውን እንደጠበቁ፤ ባለማመን የጠወለገውን ሕይወታችንን በቃሉ ዝናምነት በማለምለም አለማመናችን በእግዚአብሔር ቃል መረዳት አለበት፡፡

ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን በእምነት ከጸናን የማናልፈው ነገር የለም፡፡ የማንዘለው የችግር እና የመከራ ግንብ፣ የማንሻገረው ባሕር እና መሰናክል የለም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር ከኖርን የሚያስፈራን አንዳች ነገር አለመኖሩን ሲያስረዳ «በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል» (መዝ. ፳፪፥፬) ብሏል፡፡

ቅዱስ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ መውደቅ መነሣት ያጋጠመው ሰው ቢሆንም በእምነት በመጽናቱ ፍጻሜው ሠምሮ ልበ አምላክ ለመባል በቅቷል፡፡ በመሆኑም ዛሬ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የተደቀነብንን ፈተና የምናልፈው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በእምነት ነው፡፡ የሚመጣውን ነገር በተስፋ የሚያስረዳንም እምነት በመሆኑ አለማመናችንን ርዳው እያልን መጮህ ይገባል፡፡

አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ወይም በእምነት ስንጸና ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ኃያላን የሆኑትን አራዊት ሳይቀር ገራም ያደርግልናል፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ዳንኤል ከአናብስት ጉድጓድ ሲወረወር የተራቡት አንበሶች ለነቢዩ ገራም የሆኑት የእምነት ሰው በመሆኑ ነው፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸው ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አናምርት /ነብሮች/ እና አናብስት /አንበሶች/ የእግራቸውን ትቢያ እየላሱ የታዘዙላቸው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በእምነት ነው፡፡

ዛሬ ዲያብሎስ «እንደተራበ አንበሳ በፊታችን በሚያደባበት ዘመን የእምነትን ጥሩር መልበስ ያስፈልጋል፡፡ ለቀደሙት አባቶች ሥጋት የነበሩት ነገሮች ቀሊልና ታዛዥ እንደሆኑ ለእኛም ይሆኑልናል፡፡ ብዙ ጊዜ ፈቃደ ሥጋችን ፈቃደ ነፍሳችንን ሲጫነው የምንወደውን ሳይሆን የማንወደውን እናደርጋለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ያንየምወደውንም በጎ ነገር የማደርግ አይደለም፤ ነገር ግን ያን የምጠላውን ክፉውን አደርጋለሁ» (ሮሜ. ፯፥፲፱) ሲል እንደተናገረው፤ የሥጋችን ፈቃድ ብዙ ጊዜ «ነፍሴ ብይ፣ ጠጪ ደስ ይበልሽ» ወደ ማለት ቢያዘነብልም ቅሉ ወደ ፈቃደ ነፍስም መለስ ብሎ እኔ ማነኝ? ጉዞዬስ ወዴት ነው? ተስፋዬስ ማን ነው? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፈቃደ ሥጋው እያየለ ሲያስቸግረው፤ በእንባው መኝታውን እያራሰ በእግዚአብሔር ፊት ቢያለቅስ፤ የኃጢአት አሽክላ እየተቆረጠለት በእምነቱ የሚደሰት ጻድቅ ሰው ሆኗል፡፡

በእምነት ጉድለት በዲያብሎስ ሽንገላ የእምነት አቅም አጥተን ከቤተክርስቲያን ከቅድስና ሕይወት የራቅን ወገኖች፤ አለማመናችንን እግዚአብሔር እንዲረዳው ሳንሰለች ጥያቄ ማቅረብ አለብን፡፡ አስቀድመን እንደገለጽነው በእምነት ጉድለት ምክንያት ያጣነውን በረከት፣ ያጣነውን ጽናት፣ ሰላም፣ ፍቅር እናገኛለን፡፡ ልባሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ይህን ለመፈጸም ለምን እኛን ተሳነን? ብለው እንደጠየቁ፤ እኛም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ በጎ መሥራት ለምን ተሳነን?

የሰው ልጅ ወደ እምነት ፍጹምነት ውስጥ ሲገባ ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር እጅ እንደሆነ ይረዳል፤ ከጭንቀትም ያርፋል፡፡ በአቅማችንና በፈቃዳችን የተቸገረን መርዳት፣ አምላክን ከልብ መውደድ፣ ማመስገን የእምነት ሰው መገለጫ ናቸው፡፡

በእምነት የጸኑ አባቶችን በአንበሳ ጉድጓድ፣ በእሳት ውስጥ፣ በወህኒ ቤት በተጣሉ ጊዜ የተረዳና የእምነታቸውን ዋጋ የከፈለ እግዚአብሔር ዛሬም አለ፡፡ በመሆኑም መንፈሳዊ ሕይወታችንን በእምነት አሳድገን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር