‹‹ስለማስመሰል ርኅራኄው ሰይጣንን ተጠንቀቀው›› ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

                                                                               መምህር ሶምሶን ወርቁ  

አምላካችን እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥረው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም እንዳልሆነ በማየቱ  ከጎኑ አንዲት አጥንትን ወስዶ ሔዋንን ፈጠረለት፡፡ በገነት እንዲኖሩም አደረጋቸው፤ ከአንዲት ዕፅ (የሞት ዛፍ) በቀር  ሁሉን እንዲበሉም አዘዛችው፤ ‹‹ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና››፡፡ (ዘፍ.  ፪፥፲፮) ነገር ግን ዲያብሎስ ወደ እነርሱ ቀርቦ ለእነርሱ ያዘነ በማስመሰል ክፉ ምክርን መከራቸው፡፡ ‹‹ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን፥ ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ፥ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ፥ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው›› (ዘፍ ፫፥፬) አላቸው፡፡ እነርሱም ዲያብሎስ ለእነርሱ አስቦና ራርቶ የመከራቸው ስለመሰላቸው ክፉ ምክሩን  ተቀብለው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አፈረሱ፡፡ አስቀድሞ ፈጣሪያቸው ለእነርሱ ያደረገላቸውን ነገር ረስተው በዲያብሎስ የሐሰትና የማስመሰል ምክር ተታለሉ፡፡ ከዚያም ከፍሬው ቆርጠው በሉ፤ ሞትንም ሞቱ፤ ገነትን ያህል ቅዱስ ሥፍራ፤ እግዚአብሔርን ያህል ኃያል ፈጣሪ አስከፉ፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሰይጣን በማስመሰል ርኅራኄው ሰዎችን እያባበለ ኃጢአት ሲያሠራ እና ከአምልኮተ እግዚአብሔር ሲለይ ኖረ፡፡ ሰይጣን ሰዎችን የሚያስትበት መንገድ ረቂቅ፣ እንደየዘመኑ ሁኔታም ተለዋዋጭ ነው፡፡ ሰይጣን ሰውን ሊያስት ሲመጣ እኔ ሰይጣን ነኝ፣ እነሆ ላስታችሁ መጥቻለሁ ተዘጋጅታችኋልን? ብሎ አይመጣም፡፡ ሰዎችን፣ ጊዜን፣ ሁኔታንና ቦታን ምክንያት እያደረገ በማታለያ ንግግሩ ቀርቦ በማስመሰል ሰዎችን ሸንግሎ ያስታል፡፡ የሰይጣን የማስመሰል ርኅራኄው የቱን ያህል አሳሳች እንደሆነ እንኳን አንረዳውም፡፡ ካሳተን በኋላም ያሳተን እርሱ መሆኑን መረዳት እየተሳነን ለውድቀታችን ሰዎችን፣ ዕድልን፣ ሁኔታዎችን እና ጊዜን ሰበብ እንድናደርግ ያደርገናል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በተለይ በየጠበሉ ‹‹እከሊት ናት መድኃኒት ያደረገችብሽ፤ እከሌ ነው መድኃኒት ያደረገብህ›› እያለ ራሱን ሲያጋልጥ የምንሰማው የሰዎች ታሪክ እማኝ ነው፡፡ ‹‹ሐሰተኛ ነውና፤ የሐሰት አባትም ነው›› እንደተባለው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፬) በዚህ ሐሰተኛነቱም አንዳንዶችን የአጋንንቱን ምስክርነት አምነው እንዲካሰሱ ባስ ሲል ወደከፋ ነገር እንዲደርሱ ያደርጋቸዋል፡፡

የሰይጣንን የማስመሰል ርኅራኄው አለማወቃችን ለጊዜ ከሚደርስብን ውድቀት በተጨማሪ በተደጋጋሚና በተመሳሳይ በኀጢአት እንድንወድቅ ያደርገናል፡፡ እርሱ ዘወትር እኛን በድካማችን ለማሳት አይሰለችምና እኛም እርሱ በእንዴት ያለ የማስመሰል ርኅራኄ ቀርቦ እንደሚያስተን ልናውቅበት እና ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡

ዛሬ ላይ ሰይጣን እንዴት ባለ የማስመሰል ርኅራኄው ሰውን እየጣለ ነው?

ሀ/  ለራሳችን በምንሰጠው የተሳሳተ ግምት የተነሣ

ዲያብሎስ ትሕትናን ስለሚፈራ ሰዎች ለራሳቸው ከፍ ያለ የተሳሳተ ግምት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሰዎችን አንደበት እየተጠቀመ ‹‹አንተ እንዲህ ነህ፤ አንች እንዲህ ነሽ›› እያለ በተሳሳተ መንገድ ይመራል፡፡ ዲያብሎስ ወጣቶችን ለማሳት ‹‹አንተ ወጣት አይደለህ?፤  በዕድሜህ ተዝናና›› በማለት በመዝናናት ውስጥ ያለውን ድቀት በመሸሸግ ለእነርሱ የራራ መስሎ ይመክራል፡፡ እኅቶቻችንን ‹‹አንቺ ወጣት አይደለሽ በዕድሜሽ አጊጪ››‹‹እግዚአብሔር ልብን ነው የሚያየው›› በማለት የምንዝር ጌጥ እንዲያጌጡ እና ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ባላሰቡትና ባልገመቱት መንገድ በፈተና እንዲወድቁ ያዳርጋቸዋል፡፡

የአንዳንድ ሰዎችን አንደበት እየተጠቀመ ዲያብሎስ መንፈሳውያንን ‹‹አንተ የእግዚአብሔር ሰው፣ አንቺ የእግዚአብሔር ሰው፣  ቅን ሰው፣  የዋህ ሰው፣ ጸሎተኛ ነህ፤ ጸሎተኛ ነሽ፤ ጾመኛ ነው፤ ጾመኛ ናት›› በማለት ልባችን ውስጥ ትዕቢት እንዲፈጠር ያደርጋል፤ እያታለለም  የሌለንን ቅድስና ያለን እንዲመስለን ያደርገናል፤ በፍጻሜያችንም መንፈሳዊ ተጋድሎዋችን ላይ ድል ይነሣናል፤ ከዚያም በኋላ በቀላሉ በኃጢአት ይጥለናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጌታችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጠቅሶ ሊፈትነው እንደሞከረው መንፈሳውያንንም ‹‹እነሆ፥ ጊንጦችንና እባቦችን፥  የጠላትንም ኃይል ሁሉ ትረግጡ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠኋችሁ፤ የሚጎዳችሁም ምንም የለም›› (ሉቃ. ፲፥፲፱) በማለት ራሳቸውን ከአደጋና ከወረርስኝ እንዳይጠብቁ፣ በሕይወታቸው ላይ ያላቸውን ድርሻ አስረስቶ ሳያውቁት እግዚአብሔርን እንዲፈታተኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ጌታችን  በዲያብሎስ በተፈተነ ጊዜ ዲያብሎስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወሰደውና በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ ‹‹ስለ አንተ መላእክቱን ያዝልሃል፤ እግርህንም በድንጋይ  እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሡሃል፤ ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ወደታች ራስህን ወርውር አለው፡፡ ኢየሱስም ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው፡፡›› (ማቴ ፬፥፮-፰) ዲያብሎስ በእምነታችን የጸናን እንዲመስለን በማድረግ የእግዚአብሔርን ጠብቆት እንድንፈታተን ያደርገናል፡፡

ባለጸጎችን ሀብትን የሰጠ እግዚአብሔር መሆኑን፤ በተገቢውም ሥርዓት ሊያስተዳድሩ እንደሚገባና በሀብት በንብረታቸው ላይ በእግዚአብሔር የተሾሙ መሆናቸውን ያስረሳቸዋል፡፡  ለድሆች ጥቂት ነገር ሲመጸውቱ፣ ለቤተክርስቲያን ሲረዱ፣ መመስገንን አጥብቀው እንዲሹ የማይገባቸውን ክብር እንዲመኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የሰዎችን አንደበት እየተጠቀመ ‹‹የአንተ ቤት የአብርሃም ቤት ነው፤ እስኪ ሌሎችን ባለጸጎች ተመልከት! ንፉጎች ናቸው›› እያለ ራሱን ከአብርሃም ጋር እያነጻጸረ ለራሱ ያልተገባ ክብር እንዲሰጥ እያደረገ በከንቱ ውዳሴ ይጥላቸዋል፡፡

አገልጋዮችን ‹‹አንተ ስትቀድስ፣ አንተ ስትሰብክ፣ አንተ ስትዘምር ይደምቃልና ጠጠር መጣያ ይጠፋል›› እያስባለ አገልጋዮች እያገለገሉ የሚገለገሉ መሆናቸውን ያዘናጋቸዋል፡፡ አንዳንዴ ከንቱ ውዳሴን ሳያውቁት እንዲሹ ያደርጋቸዋል፡፡

ለ/ ወቅታዊ የሀገር ሁኔታዎችን በመጠቀም

ዲያብሎስ አጥብቆ ከሚጠላው አንዱና ዋነኛው ነገር የሰውን በአንድ ልብ በአንድ ሀሳብ ሆኖ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎችን  የሚለያዩ ልዩ ልዩ መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ መገኛችን አባታችን አዳም መሆኑን አስዘንግቶ ሰዎች በብሔር በመከፋፈል በሰዎች መካከል ልዩነትን እንዲፈጠር አድርጎ የባላጋራነት ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች በሚሰሙትና በሚናገሩት ቋንቋ መገልገልና ማገልገል የተከለከለ አስመስሎ  ‹‹ለምን በቋንቋዬ አይሰበክም እና አይቀደስም›› በሚሉ ሀሳቦች ነገር ግን በውስጣቸው ምእመናን ከመንጋውና  ከእረኛ አባቶች የመለየት ሥውር ተልዕኮውን ይፈጽማል፡፡

ሐ/ ዓለማዊ አስተሳሰቦችን መንፈሳዊ በማስመሰል

በተለይ ዛሬ ላይ የዲያብሎስ ዋናው ማታለያው በመንፈሳዊነትና በዓለማዊነት መካከል ያለውን ድንበር በማጥፋት ለዓለማዊ አስተሳሰቦች መንፈሳዊ ሽፋን መስጠት ነው፡፡ በተደጋጋሚ የምንሰማቸው የድኅረ ዘመናዊነት፣ የባህል እና የሃይማኖት ብዝኃነት፣ የሉላዊነት እና የዓለማዊነት እይታዎች በግለሰቦች ነፃነት ስም ሃይማኖት የሰዎችን ነፃነት እንደሚገድብ አድርጎ በማቅረብና ሃይማኖተኛ መሆንን እንደጽንፈኛ አድርጎና አስመስሎ ያቀርባል፡፡ ሰዎችንም ሳያውቁት በእነዚህ አስተሳሰቦች ተጽዕኖ ከሃይማኖታቸው ወጥተው ሃይማኖት የለሽ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡

ከዲያብሎስ የማስመሰል ርህራሔው እንዴት እንጠንቀቅ?

ሀ/ ሕሊናችንን በመርመር

ዘወትር በሕሊናችን የሚመላለሱትን ሀሳቦች በጥንቃቄ ልንመረምራቸው፣ ወደ ውሳኔ ከመድረሳችንም አስቀድመን ‹‹ለምን?፣ እንዴት?፣ ከዚያስ?›› ብለን መጠየቅ ይጠበቅብናል፡፡ ባለን ዕውቀትም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኘው ትምህርት ጋር በማጣቀስ መረዳት መቻል አለብን፡፡ ‹‹የቀደመ የሕይወት ተሞክሮዬ ምን አስተምሮኛል?›› ብለንም ልንመረምረው ያስፈልጋል፡፡ ‹‹አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ እርሱ ነውና››፤ (ምሳ. ፬፥፳፫) ቅዱስ ጴጥሮስ በዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄው ወጥመድ እንዳንያዝ በንቃት እንድንኖር ያስገነዝበናል፡፡ ‹‹በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› እንዲል፡፡ (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፰)

ለ/ በትሕትና

ሰይጣን በማስመሰል ርኅራኄው በመቅረብ  የበቃውንም ሰው በትዕቢት በከንቱ ውዳሴ ለመጣል የተንኮል ወጥመዱን ይዘረጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ›› (፩ቆሮ. ፲፥፲፪) እንዳለ ጠላት ቀርቦ በትዕቢት እንዳይጥለን ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ‹‹ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ  እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል›› ተብሎም ተጽፏልና፡፡ (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፭)

ሐ/ በጸሎት በመትጋት

ጸሎት ከዲያብሎስ የሚላኩብንን የጥፋት ፍላጻዎች ጋሻ ሆኖ የሚመክት መሣሪያችን ነው፡፡ ስለዚህ ዘወትር ሳናቋርጥ በጸሎታችን እግዚአብሔርን በማመስገን፣ ልዕልናውን፣ ቸርነቱንና አዳኝነቱን በማሰብ፣ በፍጹም ልባችን ሆነን ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ፤ ‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤›› (ማቴ. ፳፮፥፵፩) ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ስለሆነም የዲያብሎስን ፈተና ልንቋቋም ከምንችልባቸው መንፈሳውያት ኃይሎቻችን መካከል ጸሎት ዋነኛው መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡

መ/ ሕዋሶቻችን ከክፉ ሥራ በመጠበቅ

ዲያብሎስ እኛን ለማሳት የሚጠቀመው የገዛ ሕዋሶቻችን ነው፡፡ እነርሱን መቆጣጠር ከቻልን በዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄ አንታለልም፡፡ ዓይናችን የሚያየውን ክፉና በጎ ነገር፣ ጆሮዋችን የሚሰማውን ሐሰትና እውነቱን ነገር መምረጥ ስንችል፣ አንደበታችን እውነትን ሲናገር፣ እግሮቻችን ወደተቀደሱ ሥፍራዎች ሲያዘወትር ዲያብሎስ በቀላሉ ቀርቦ አያስተንም፡፡ በአጠቃላይ ሕዋሶቻችን ከኃጢአት ሥራ ተለይተው በጎ ነገርን መሥራት ሲጀምሩ በጎን ከክፉ ስለምንለይ በዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄው ወጥመድ በቀላሉ አንወድቀወም፡፡

ሠ/ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ በመልበስ

ክርስቲያን ዘወትር በንቃት በመዘጋጀት ሕይወቱን ይመራል እንጂ በዘፈቀደ አይመራም፡፡ ‹‹ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን›› (ሉቃ.፲፪፥፴፭) ተብሎ በወንጌል እንደተጻፈው፤  ቅዱስ ጳውሎስ የዲያብሎስን ውጊያዎች በድል አድራጊነት ለመወጣት ምን ማድረግ እንዳለብን ሲያጠይቅ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ›› ብሎናል፡፡ (ኤፌ ፮፥፲፩)  የጦር ዕቃ የተባሉትን ጾም ጸሎትና መንፈሳዊ ተጋድሎን ጋሻና ጦር አድርገን ከዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄው ወጥመድ ማምለጥ ይቻላል፡፡

ረ/ በረድኤተ እግዚአብሔር በማመን

ዲያብሎስ በማስመሰል ርኅራኄው ለፈተና ወደ በሕይወታቸን ሲመጣ ‹‹ለምን ወይም እንዴት›› አንበል፤ ይልቅስ በእግዚአብሔር ረድኤት ማመን ይገባናል፤ እግዚአብሔር ማንንም በክፉ አይፈትንምና፡፡ ‹‹ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና››፡፡ (ያዕ. ፩፥፲፫) ይልቅስ እንኳን እኛ ጌታችንም ተፈትኗል፤  ‹‹እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና›› (ዕብ. ፪፥፲፰) ተብሎ የተጻፈልን በፈተናችን ሁሉ መጽናኛ ይሆነን ዘንድ ነው፡፡ ስንፈተን ልንጨነቅ አይገባም፤ ጌታችንም ተፈትኗልና፤ ድል አድርጎም ድል የምናደርግበትን ኃይል ሰጥቶናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› (ፊል. ፬፥፲፫) ብሎ እንዳስተማረን ኃይልን የሚሰጠን አምላክ እንዳለ አምነን ዲያብሎስ በማስመሰል ርኅራኄው የሚያመጣብንን ሥውር ፈተናን በማለፍ ድል ማድረግ እንችላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፤ ከ‹‹መንፈሳዊ ውጊያዎች›› ፪ኛ መጽሐፍ፤ በብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፤ የግብፅኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፤ ውርስ ትርጉም አያሌው ዘኢየሱስ፤ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.