መራሕያን
መምህር በትረማርያም አበባው
ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፈው ትምህርታችን ላይ አኀዝ ወይንም የግእዝ ቊጥሮችን አይተን ነበር፡፡ በዚያም መሠረት ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና የዚህን ሳምንት ትምህርት ‹መራሕያን› በሚል ርእስ አዘጋጅተን አቅርበንላችኋልና በጥሞና ተከታተሉን፡፡
የሚከተሉትን ጥያቄዎች ወደ ግእዝ ቊጥር ቀይሩ!
1) 456
2) 72
3) 4734
መልሶች
፩.456-፬፻፶፮
፪.72- ፸፪
፫.4734-፵፻፯፻፴፬
መራሕያን
በግእዝ ቋንቋ ቁልፍ የሆኑ ዐሥር መራሕያን አሉ። ‹መራሕያን› የሚለው ቃል መርሐ መራ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ መሪዎች ማለት ነው። መራሕያን በሰዋስው ውስጥ ወንድ(ወ) እና ሴት(ሴ) አንድና ብዙን፣ ሩቅና ቅርብን የሚያሳውቁን ቁልፍ ቃላት ናቸው። ዐሥሩ መራሕያን የሚባሉትም፡-
በግእዝ….በአማርኛ
፩) አነ……….እኔ
፪) ንሕነ…….እኛ ናቸው።
፫) አንተ……….አንተ
፬) አንትሙ…..እናንተ (ወ)
፭) አንቲ………አንቺ
፮) አንትን……እናንተ (ሴ)
፯) ውእቱ…..እርሱ
፰) ውእቶሙ/እሙንቱ….እነርሱ (ወ)
፱) ይእቲ……….እርሷ
፲) ውእቶን/እማንቱ….እነርሱ (ሴ)
መራሕያን በተለያየ አከፋፈል ይከፈላሉ። በጾታ ስንከፍላቸው ሴት እና ወንድ ናቸው። ለሴት የሚሆኑ መራሕያን ‹‹አንቲ፣ ይእቲ፣ ውእቶን/እማንቱ፣ አንትን›› ናቸው። ለወንድ የሚሆኑ መራሕያን ደግሞ ‹‹ውእቱ፣ ውእቶሙ/እሙንቱ፣ አንተ፣ አንትሙ›› ናቸው። አስተውል! በግእዝ ቋንቋ ሴቶችን እናንተ ስንልና ወንዶችን እናንተ ስንል የተለያየ ነው። በእንግሊዘኛው ደግሞ ሴቶችን እናንተ ስንል፣ ወንዶችን እናንተ ስንል፣ አንዱን ወንድ አንተ ስንል፣ እና አንዷን ሴት አንቺ ስንል በሁሉም ተመሳሳይ ነው፡፡ በግእዝ ሴቶችን እናንተ ስንል አንትን እንላለን። ወንዶችን እናንተ ስንል አንትሙ እንላለን። እንዲሁም ሴቶችን እና ወንዶችን እነርሱ ስንል ወንዶችን እነርሱ ስንል ውእቶሙ/እሙንቱ እንላለን። ሴቶችን እነርሱ ስንል ውእቶን/እማንቱ እንላለን። ሴት እና ወንድ ተቀላቅለው ካሉ ደግሞ ውእቶሙ/እሙንቱ፣ አንትሙ እየተባለ በወንዶች አንቀጽ ይነገራል። ከመራሕያን ለሴትም ለወንድም የሚያገለግሉ፣ ጾታ የማይለዩ ‹‹አነ፣ እና ንሕነ›› ናቸው። ሴትም እኔ ስትል ‹አነ› ትላለች። ወንድም እኔ ሲል “አነ” ይላል። ወንዶችም እኛ ሲሉ ‹ንሕነ› ይላሉ። ሴቶችም እኛ ሲሉ ‹ንሕነ› ይላሉ።
ሌላው መራሕያን በነጠላና በብዙ ይከፈላሉ። ነጠላ የሚባሉት አንድን ግለሰብ የሚያሳውቁ ናቸው እኒህም፦ አነ፣ ውእቱ፣ ይእቲ፣ አንቲ እና አንተ ናቸው። ብዙ የሚባሉት ደግሞ ንሕነ፣ ውእቶሙ/እሙንቱ፣ ውእቶን/እማንቱ፣ አንትሙ እና አንትን ናቸው። በቅኔ ቤት ትምህርት ደግሞ ቅርብና መደብ ሩቅ መደብ ተብለው ይከፈላሉ። ቅርብ መደብ የሚባሉት በቅርበት የምንናገራቸውን ነው። እነዚህም አነ፣ ንሕነ፣ አንተ፣ አንትሙ፣ አንትን፣ አንቲ ሲሆኑ በአጭሩ አንደኛ መደብ እና ሁለተኛ መደቦች ቅርብ መደብ ይባላሉ። ሩቅ መደብ የሚባሉት ሦስተኛ መደቦች ናችው እነዚህም ‹‹ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ፣ ውእቶን›› ናቸው። ከአሥሩ መራሕያን ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ፣ አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ አነ እና ንሕነ ተነሥተው ይነበባሉ። እሙንቱ እና እማንቱ ወድቀው ይነበባሉ (ሥርዓተ ንባባቸው ወዳቂ ንባብ ነው)። አንትን እና ውእቶን ተጥለው ይነበባሉ (ሥርዓተ ንባባቸው ተጣይ ነው)።
መራሕያን በአገልግሎታቸው በሦስት ይከፈላሉ። እኒህም የስም ምትክ ሆነው ሲያገለግሉ፣ አመልካች ቅጽል (ሆነው ሲያገለግሉ እና ነባር አንቀጽ ሆነው ሲያገሉ ናቸው። መራሕያን የስም ምትክ ሆነው የሚያገለግሉት ከግስ በፊት ሲመጡ ነው። የስም ምትክ ሆነው ሲያገለግሉ የሚኖራቸውም ትርጒም ከላይ ከአንድ እስከ ዐሥር የተጻፈው ነው። ለምሳሌ ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል ሲል ‹ተዐቢ› የሚለው ቃል ግሥ ስለሆነ ይእቲ ደግሞ ከግሥ በፊት ስለመጣ የሚኖረው ትርጒም ‹እርሷ› ይሆናል ማለት ነው። በዚህም መሠረት ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል ሲል እርሷ ከኪሩቤል ትበልጣለች ማለት ነው። መራሕያን ነባር አንቀጽ ሆነው ሲያገለግሉ የሚኖራቸው ትርጉም እንደሚከተለው ነው።
ግእዝ….አማርኛ
፩) አነ…..ነኝ፣ ነበርኩ፣ አለሁ (የተሰመረባቸው የ ‹ለ› ፊደላት ጠብቀው ይነበባሉ)
፪) ንሕነ….ነን፣ ነበርን፣ አለን
፫) አንተ…ነህ፣ ነበርክ፣ አለህ
፬) አንትሙ…ናችሁ፣ ነበራችሁ፣ አላችሁ
፭) አንቲ….ነሽ፣ ነበርሽ፣ አለሽ
፮) አንትን…..ናችሁ፣ ነበራችሁ፣ አላችሁ
፯) ውእቱ….ነው፣ ነበረ፣ አለ
፰) ውእቶሙ/እሙንቱ…ናቸው፣ ነበሩ፣ አሉ
፱) ይእቲ….ናት፣ ነበረች፣ አለች
፲) ውእቶን/እማንቱ…..ናቸው፣ ነበሩ፣ አሉ
መራሕያን እንደ ነባር አንቀጽ ሲያገለግሉ መሆንን እና መኖርን ያሳውቃሉ። እንደ ነባር አንቀጽ የሚተረጎሙትም ከስም ወይም ከዓረፍተ ነገር በኋላ ሲመጡ ነው። ማርያም ይእቲ እሙ ለክርስቶስ ሲል ‹ይእቲ› የሚለው መራሒ ማርያም ከሚለው ስም በኋላ ስለመጣ ሊተረጎም የሚችለው በነባር አንቀጽ ነው። ስለዚህም የክርስቶስ እናቱ ማርያም ናት ይላል ማለት ነው። በተጨማሪም ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ ሲል ‹ውእቱ› የሚለው መራሒ ከዓረፍተ ነገር (ከስም) በኋላ ስለመጣ በነባር አንቀጽነቱ ይተረጎማል። ስለዚህም በመጀመሪያ ቃል ነበር ተብሎ ይተረጎማል። መራሕያን አመልካች ቅጽል ሆነው ሲያገለግሉ የሚኖራቸው ትርጉም ደግሞ እንደሚከተለው ነው።
ግእዝ…..አማርኛ
፩) አነ………..እኔ.
፪) ንሕነ………………..እኛ
፫) አንተ………..አንተ
፬) አንትሙ…….እናንተ
፭) አንቲ………..አንቺ
፮) አንትን…….እናንተ
፯) ውእቱ………ያ
፰) ውእቶሙ/እሙንቱ…እነዚያ
፱) ይእቲ……..ያች
፲) ውእቶን/እማንቱ….እነዚያ
መራሕያን በአመልካች ቅጽልነት የሚተረጎሙት ከስም በፊት ሲመጡ ነው። ለምሳሌ ውእቱ ቃል ሥጋ ኮነ ከሚለው ዓረፍተ ነገር ‹ውእቱ› የሚለው መራሒ ‹ቃል› ከሚለው ስም በፊት የመጣ ስለሆነ በአመልካች ቅጽልነቱ ይተረጎማል። ስለዚህም ‹‹ያ ቃል ሥጋ›› ሆነ ተብሎ ይተረጎማል። በነባር አንቀጽ ጊዜ ‹ውእቱ› በተለየ በአስሩም መራሕያን ይተረጎማል። ለምሳሌ ‹‹አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም›› ቢል። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ይላል። ውእቱ ‹ናችሁ› ተብሎ ተተርጉሟል። ነኝ፣ ነሽ፣ ናት….ወዘተ እያለ በአስሩም ይተረጎማም። ሁለት መራሕያን ተከታትለው ሲመጡ የመጀመሪያው መራሒ በስም ምትክ ይተረጎማል። ቀጥሎ ያለው መራሒ ደግሞ በነባር አንቀጽ ይተረጎማል። ለምሳሌ ‹‹አነ ውእቱ ገብርኤል ዘእቀውም በቅድመ እግዚአብሔር ቢል›› አነ የሚለው መራሒና ‹ውእቱ› የሚለው መራሒ ተከታትለው መጥተዋል። ስለዚህ የመጀመሪያው በስም ምትክ እኔ ተብሎ ይተረጎማል። ሁለተኛው ደግሞ በነባር አንቀጽነቱ ‹ነኝ› ተብሎ ይተረጎማል። ስለዚህም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ›› ተብሎ ይተረጎማል።
በባለቤትነት የሚያገለግሉ ሌላ ዓይነት ዐሥሩ መራሕያን አሉ እነዚህም ድርብ መራሕያን ይባላሉ። ትርጒማቸውም የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ግእዝ………አማርኛ
፩) ለልየ……..እኔ ራሴ
፪) ለሊነ…..እኛ ራሳችን
፫) ለሊከ……አንተ ራስህ
፬) ለሊክሙ………እናንተ ራሳችሁ(ወ)
፭) ለሊኪ……..አንቺ ራስሽ
፮) ለሊክን…….እናንተ ራሳችሁ(ሴት)
፯) ለሊሁ……እርሱ ራሱ
፰) ለሊሆሙ……..እነርሱ ራሳቸው(ወ)
፱) ለሊሃ……..እርሷ ራሷ
፲) ለሊሆን….እነርሱ ራሳቸው(ሴ)
በምሳሌ ለማየት ያህል ‹‹ለሊነ ነአምር ኵሎ ዘኮነ፤ እኛ ራሳችን የሆነውን ሁሉ እናውቃለን›› ማለት ነው።
ሌላው የምንመለከተው ደግሞ ተሳቢ መራሕያንን ነው። እነዚህም ዐሥር ሲሆኑ የሚከተሉት ናቸው፦
ግእዝ……አማርኛ
፩) ኪያየ…..እኔን
፪) ኪያነ…..እኛን
፫) ኪያከ…….አንተን
፬) ኪያክሙ…..እናንተን(ወ)
፭) ኪያኪ…….አንቺን
፮) ኪያክን….እናንተን(ሴ)
፯) ኪያሁ…..እርሱን
፰) ኪያሆሙ..እነርሱን(ወ)
፱) ኪያሃ……እርሷን
፲) ኪያሆን….እነርሱን(ሴ)
በምሳሌ ለማየት ያህል ‹‹ኪያከ እግዚኦ ነአኵት፤ አቤቱ አንተን እናመሰግንሀለን›› ተብሎ ይተረጎማል። በመጨረሻም ‹የዘ› ዝርዝር በዐሥሩ መራሕያን ሲዘረዘር እንመለከታለን።
ግእዝ…..አማርኛ
፩) ዚኣየ……የእኔ
፪) ዚኣነ…..የእኛ
፫) ዚኣከ….የአንተ
፬) ዚኣክሙ…የእናንተ(ወ)
፭) ዚኣኪ……የአንቺ
፮) ዚኣክን….የእናንተ(ሴ)
፯) ዚኣሁ…..የእርሱ
፰) ዚኣሆሙ…የእነርሱ(ወ)
፱) ዚኣሃ…..የእርሷ
፲) ዚኣሆን….የእነርሱ
የመልመጃ ጥያቄዎች
፩) በሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች ያሉትን መራሕያን አገልግሎታቸውን ለዩ!
ሀ) ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም
ለ) አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም
ሐ) አነ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት
መ) ውእቱ ሚካኤል ያፈቅረነ
፪) የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉም
ሀ) ኪያየ አፍቅሩ
ለ) ኪያክሙ ተወክፈ
ሐ) ለሊነ ንመውት
መ) ኪያሃ ናፈቅር
፫) የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ተርጉም
ሀ) የእኛ ወንዝ
ለ) የአንቺ ትሕትና
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!