መመለስ /ክፍል አንድ/

የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

ከእንዳለ ደምስሰ

ከቀኑ አሥራ ሁለት ስዓት ፡፡

 

ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስደርስ ልቦናዬን እየተፈታተነኝ ያለውን የዐሳብ ድሪቶ አውልቄ ለመጣል ትንፋሼን ሰብስቤ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡

 

ከተሳለምኩ በኋላ ከዋናው በር በስተግራ በኩል ካለው ዋርካ ሥር አመራሁ፡፡ የሰርክ ስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡ አካባቢዬን ቃኘሁ፡፡ ምእመናን አመቺ ነው ባሉት ቦታ ላይ ተቀምጠው የዕለቱን ትምህርት ይከታተላሉ፡፡ መምህሩ በሉቃስ ወንጌል ምዕ.15፥7 -10 ያለውን ኀይለ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ነው፡፡

 

“. . . ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢአተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል . . . ፡፡” ሰባኪው ስብከታቸውን ቀጥለዋል . . . .፡፡

 

የሸሸግሁት ቁስል ስለተነካብኝ ውስጤ በፍርሃት ተወረረ፡፡

 

— “ማን ነገራቸው? ለዘመናት ስሸሸው የኖርኩትን የንስሐ ትምህርት ዛሬም ተከትሎኝ መጣ?” አጉረመረምኩ፡፡

 

ቀስ በቀስ ስብከቱን እያደመጥኩ ራሴን በመውቀስ ጸጸት ያንገበግበኝ ጀመር፡፡– “ለምን ስሜታዊነት ያጠቃኛል? ለምን ወደ ትክክለኛው የክርስትና ሕይወቴ አልመለስም? ዛሬ የመጨረሻዬ ይሆናል፡፡” ውሳኔዬ ቢያስደስተኝም መሸርሸሩ አይቀርም በሚል ደግሞ ሰጋሁ፡፡ ስንት ጊዜ ወስኜ ተመልሼ ታጥቦ ጭቃ ሆኛለሁ?! አንድ መቶ ጊዜ – አንድ ሺህ ጊዜ – ከዚህም በላይ . . . ፡፡ ቃለ እግዚአብሔር በሰማሁ ቁጥር ልቤ ይሰበራል፡፡ እጸጸታለሁ፡፡ ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር እንደወጣሁ በልቦናዬ የተተከለው ቃለ እግዚአብሔር ንፋስ እንደ ጎበኘው ገለባ ይበተናል፡፡ ውሳኔዬም ይሻራል፤ ልቦናዬ ይደነድናል፡፡ ወደ ቀድሞ እሪያነቴ እመለሳለሁ፡፡ ሁልጊዜ — “የተጠናወተኝ አጋንንት ነው እንዲህ የሚሰራኝ!” እያልኩ አሳብባለሁ፡፡

 

ሰባኪው ቀጥለዋል፡፡ “. . . አሁንም ከክፋትህ ተመለስና ንስሐ ግባ፡፡ የልቦናህንም ዐሳብ ይተውልህ እንደሆነ እግዚአብሔርን ለምን ፡፡ /የሐዋ. ሥራ ምዕ.8፥22/ ” የበለጠ ተሸበርኩ፡፡

 

አመጣጤ መምህረ ንሰሐዬ ይሆኑ ዘንድ ካሰብኳቸውና ቀጠሮ ከሰጡኝ አባት ጋር ለመገናኘት ነበር፡፡ ለመምህረ ንስሐነት በራሴ ፍላጎት ያጨኋቸው አባትም ዘገዩ፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት ሳገኛቸው አብረን ተቀምጠን የተነጋገርንበት ቦታ ላይ ሆኜ እየጠበቅኋቸው ነው፡፡ ያገኘሁዋቸው ከሰንበት ትምህርት ቤቱ የቅርብ ጓደኛዬ ነው፡፡ ቀድሞ ከነበሩኝ የንስሐ አባቴ ጋር ስላልተግባባን፤ በተለይም ቁጣቸውን መቋቋም ስላቃተኝ ለመቀየር ወስኜ ነው የመጣሁት፡፡

 

— “ይገርማል! ስንተኛዬ ናቸው ማለት ነው? 1 – 2 – 3 . . . 4ኛ!” በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሦስት መምህረ ንስሐ ይዤ ፈርጥጫለሁ፡፡ — “ምን አይነት አባት ይሆኑ? የማይቆጡ፤ የማያደናብሩ፤ ጥቂት ብቻ ቀኖና የሚሰጡ ከሆነ ነው አብሬ የምቆየው፡፡” እንደተለመደው ለማፈግፈግ ምክንያት አዘጋጀሁ፡፡

 

መልሼ ደግሞ — “ምን አይነት ሰው ነኝ?! ዳግም ወደ ኀጢአት ላልመለስ ከራሴ ጋር እየተነጋገርኩ መልሼ እዚሁ አፈርሰዋለሁ እንዴ?! መጨከን አለብኝ፡፡ የሆነውን ሁሉ እናዘዛለሁ፡፡” ሙግቴ ቀጥሏል . . . ፡፡

 

ሰባኪው “. . . እንግዲህ ኀጢአታችሁ ይሠረይላችሁ ዘንድ ንስሐ ግቡ፤ ተመለሱም፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የይቅርታ ዘመን ይመጣል፡፡” የሐዋ.ሥራ ምዕ.3፥19 እያሉ በመስበክ ላይ ናቸው፡፡

 

— “ይቺ ጥይት ለእኔ የተተኮሰች ናት!” አልኩ በልቤ ሰባኪው ርዕስ እንዲቀይሩ  እየተመኘሁ ፡፡  — “እውነት ግን የይቅርታ ዘመን የሚመጣልኝ ከሆነ ለምን ከልቤ ንስሐ አልገባም? እስከ መቼ በኀጢአት ጭቃ እየተለወስኩ እዘልቀዋለሁ? መርሐ ግብሩ ይጠናቀቅ እንጂ ዝክዝክ አድርጌ ነው የምነግራቸው፡፡” ቅዱስ ጊዮርጊስን በተሰበረ ልብ ኀጢአቴን እናዘዝ ዘንድ እንዲረዳኝ ተማጸንኩት፡፡

 

ሰባኪው በቀላሉ የሚለቁኝ አይመስልም፡፡ “. . . ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመልጥ ታስባለህን? ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሱ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርንስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሐ እንዲመልስ አታውቅምን? ነገር ግን ልቡናህን እንደማጽናትህ ንስሐም እንዳለመግባትህ መጠን የእግዚአብሔርን እውነተኛ ፍርዱ በሚገለጥበት ቀን ቁጣን ለራስህ ታዘጋጃለህ፡፡” ሮሜ. 2፡3-5 እያሉ በሚሰብኩት ስብከት ልቡናዬን አሸበሩት፡፡

 

— “የአሁኑ ይባስ! ዛሬ ስለ እኔ ተነግሯቸው ነው የመጡት፡፡ ወረዱብኝ እኮ!” እላለሁ፡፡ መልሼ ደግሞ  — “እውነታቸውን ነው ይበሉኝ!!” ትምህርትም ሆነ እውቀት ሳያንሰኝ ከልቤ ልመለስ አለመቻሌ አሳፈረኝ፡፡

 

በሰ/ት/ቤት ውስጥ እንደ ማደጌና ለአገልግሎት እንደ መትጋቴ ለንስሐ  ጀርባ መስጠቴ ምን የሚሉት ክርስትና ነው? ሌሎች በአርአያነት የሚመለከቱኝ፤ ‹ክርስትናን ከኖሩት አይቀር ልክ እንደ እሱ ነው!› የተባለልኝ – ነገር ግን በኃጢአት ጥቀርሻ የተሞላሁ አሳፋሪ ሰው ነኝ፡፡ ነጠላ መስቀለኛ ለብሶ፤ መድረኩን ተቆጣጥሮ መርሐ ግብር መምራት፤ ለመስበክ መንጠራራት ፤ለመዘመር መጣደፍ ፤. . . ምኑ ቀረኝ?

 

ጊዜው የጉርምስና ወቅት በመሆኑ ለኀጢአት ስራዎችም የበረታሁበት ወቅት ነው ፡፡ ሰ/ት/ቤት ውስጥ የማያቸው እኅቶቼን ሁሉ የእኔ እንዲሆኑ እመኛለሁ፡፡ ምኞት ኀጢአት መሆኑን ሳስብ ደግሞ መለስ እላለሁ፡፡ ግን ብዙም ሳልቆይ  እቀጥላለሁ፡፡ በሥራ ቦታዬ ደግሞ ማታለልን ፤ በጉልበት የሌሎችን ላብ መቀማትን ፤ ማጭበርበር የዘወትር ተግባሬ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ስሔድ ደግሞ ሁሉን እርግፍ አድርጌ ለበጎ ስራ እተጋለሁ፡፡ — “መርዛማ ዛፍ መልካም ፍሬን ማፍራት ትችላለችን?” ራሴን እየሸነገልኩ ለጽድቅም ሆነ ለኩነኔ በረታሁ፡፡

 

አንድ ቀን በሰ/ት/ቤታችን ውስጥ በሥነ ምግባሩ የታወቀ፤ ለሌሎች አርአያ የሆነ እንደ እኔ አጭበርባሪ ነው ብዬ የማልገምተውና የማከብርው ጓደኛዬ የንስሐ አባት መያዙን ነገረኝ፡፡ እኔስ ከማን አንሳለሁ? ይመቹኛል የምላቸውን አባት መርጬ ያዝኩ፡፡ ተደሰትኩ፡፡ ቀስ በቀስ በሚኖረን ግንኙነት ኀጢአቴን ሳልደብቅ መናዘዝ ጀመርኩ፡፡ ዛሬ ቀኖና ተቀብዬ፤ ጸሎት አድርሰውልኝ በእግዚአብሔር ይፍታህ የተደመደመ ኃጢአቴን ገና ከአባቴ እንደተለየሁ እደግመዋለሁ፡፡ እንደውም አብልጬ እሰራለሁ፡፡ እናዘዛለሁ፡፡ ተመልሼ እጨቀያለሁ፡፡ የንስሐ አባቴን ትዕግስት ተፈታተንኩ፡፡ እሳቸውም አምርረው ይገሥጹኛል፡፡ ድርጊቴ ተደጋገመ፡፡ ሁኔታቸው ስላላማረኝ ሳልሰናበታቸው ጠፋሁ፡፡

 

ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ የንስሐ አባት ያዝኩ፡፡

 

እኚህ ደግሞ በጣም እርጋታን የተላበሱ ሲሆኑ ሲመክሩኝ ደግሞ የሌሎችን ታሪክ በምሳሌነት በማንሳት ያስተምሩኛል፡፡ ቀኖና ሲሰጡኝም በትንሹ ነው፡፡ የሰራሁት ኀጢአትና የሰጡኝን ቀኖና ሳመዛዝን ኀጢአቴ ይገዝፍብኛል፡፡ የሚሸነግሉኝ ይመስለኛል፡፡

 

— “ጸሎት አታቋርጥ፤ መጻሕፍትን መድገም ትደርስበታለህ፤ በቀን ለሶስት ጊዜያት አንድ አንድ አቡነ ዘበሰማያትን ድገም፡፡ ለሕፃን ልጅ ወተት እንጂ ጥሬ አይሰጡትም፡፡ ስትጠነክር ደግሞ ከፍ እናደርገዋለን፡፡” ይሉኛል፡፡

 

የናቁኝ መሰለኝ፡፡ — “እንኳን አባታችን ሆይ እኔ ጀግናው የዘወትር ጸሎት ፤ ውዳሴ ማርያም፤ አንቀጸ ብርሃን ፤ የሰኔ ጎልጎታ፤ መዝሙረ ዳዊት፤ ሰይፈ መለኮት፤ሰይፈ ሥላሴ ጠዋትና ማታ መጸለዬን አያውቁም እንዴ?! እንዴት በአባታችን ሆይ ይገምቱኛል?” አኮረፍኩ፡፡ ጠፋሁ፡፡

 

ደግሞ ሌላ ፍለጋ፡፡

 

ሦስተኛው የንስሐ አባቴ በትንሹም በትልቁም ቁጣ ይቀናቸዋል፡፡ እንደመቆጣታቸው ሁሉ አረጋግተው ሲመክሩ ደግሞ ይመቻሉ፡፡ ነገር ግን ቁጣቸውን መቋቋም ስለተሳነኝ ከእሳቸውም ኮበለልኩ፡፡

 

ዛሬ ውሳኔዬን ማክበር አለብኝ፡፡ ወደ ልቦናዬ መመለስ፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 15 ላይ እንደተጠቀሰው የጠፋው ልጅ፡፡ ወደ አባቴ ቤት በቁርጠኝነት መመለስ፡፡ ልጅ ተብዬ ሳይሆን ከባሪያዎች እንደ አንዱ እቆጠር ዘንድ፡፡

 

ከምሽቱ 12፡30 ሆኗል፡፡

 

ሰባኪው አሰቀድሞ ይሰጡት የነበረውን የንስሐ ትምህርት ቀጥለዋል፡፡  “. . . በተመረጠችው ቀን ሰማሁህ፤ በማዳንም ቀን ረዳሁህ፤ እነሆ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት፡፡” 2ኛ ቆሮ. ምዕ› 6፡2 እያሉ ቃለ እግዚአብሔርን በምዕመናን ልቦና ላይ ይዘራሉ፡፡

 

— “እውነትም ለእኔ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት፡፡ አምላኬ ሆይ ኃይልና ብርታትን ስጠኝ፡፡ ወደ ትክክለኛው አእምሮዬ እመለስ ዘንድ፤ በኀጢአት የኖርኩበት ያለፈው ዘመን ይበቃ ዘንድ እርዳኝ!!” አልኩ የተፍረከረከውን ልቦናዬ ያጸናልኝ ዘንድ እየተመኘሁ፡፡

 

— “አሁን ምንድነው ማድረግ ያለብኝ? እ – በመጀመሪያ ራሴን ማረጋጋት፡፡ ከዚያም እሰከ ዛሬ የፈጸምኩትን የኃጢአት ኮተት ማሰብ ፤ በመጨረሻም አንኳር የሆኑትን መናዘዝ፡፡” አልኩ ህሊናዬን ለመሰብሰብ እየጣርኩኝ፡፡

 

— “ግን እኮ የኀጢአት ትንሽ እንደሌለው ተምሬያለሁ፡፡ስለዚህ ሸክሜን ሁሉ ለመምህረ ንስሐዬ መናዘዝ አለብኝ፡፡” ውሳኔ ላይ ደረስኩ፡፡

 

ኀጢአት ናቸው ብዬ በራሴ አእምሮ የመዘንኳቸውን አስቦ መጨረስ አቃተኝ፡፡ በድርጊቴ ተገርሜ — “በቃ የኀጢአት ጎተራ ሆኛለሁ ማለት ነው? መቼ ይሆን ሰንኮፉ የሚነቀለው? እባክህ አምላኬ በቃህ በለኝ!”  ኃጢአቴን ማሰብ አደከመኝ፡፡

 

የዕለቱ የሰርክ ጉባኤ እንደተጠናቀቀ አበ ንስሐ ይሆኑኝ ዘንድ ቀጠሮ ያስያዝኳቸው አባት በመጠባበቅ አይኖቼ ተንከራተቱ፡፡

 

— “ረስተውኝ ይሆን እንዴ? – እውነታቸውን ነው – እኔ መረሳት ያለብኝ ሰው ነኝ፡፡ ለምንም – ለማንም የማልጠቅም ከንቱ ሆኛለሁ፡፡ ኀጢአት ያጎበጠኝ ምናምንቴ ነኝ!! የኀጢአት ሸክሜን የማራግፍበት ፍለጋ በመባዘን እሰከ መቼ እዘልቀዋለሁ? እውነተኛ ንስሐ መግባት ተስኖኝ እስከ መቼ እቅበዘበዛለሁ?” የዕንባ ጎተራዬ ተከፈተ፡፡ ከዓይኔ ሳይሆን ከልቤ ይመነጫል፡፡ መጨረሻዬ ናፈቀኝ፡፡

 

“እንደምን አመሸህ ልጄ?” አሉኝ የቀጠርኳቸው አባት ጭንቅላቴን በመስቀላቸው እየዳበሱኝ፡፡

 

ዕንባዬ ያለማቋረጥ እየወረደ ቀና ብዬ ተመለከትኳቸው፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መስቀል ተሳለምኩኝ፡፡ በሃምሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ ገብስማ ሪዛቸው ግርማ ሞገስ አላብሷቸዋል፡፡

 

“ምነው አለቀስክ?” አሉኝ አጠገቤ ካለው ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ እየተቀመጡ፡፡

 

ሳግ እየተናነቀኝ “ሸ- ሸ – ክሜ ከ- ከ-ብ-ብዶ-ብብ-ኝ ነው አባቴ! ም- ምንም  የማ- ማልጠቅም ሆኛለሁ!!” አልኳቸው ሆድ ብሶኝ፡፡

 

“መጸጸት መልካም ነው፡፡ ጸጸት ጥንካሬን ይወልዳል ልጄ! አይዞህ፡፡” አሉኝ በጥልቀት እየተመለከቱኝ፡፡

 

— “እግዚአብሔር ረድቶኝ የመጨረሻዬ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡” አባባላቸውን ተመኘሁት፡፡

 

— ‹‹አምላኬ ሆይ ብርታትን ስጠኝ፡፡ ውስጤ የታመቀውን የኃጢአት ጥቀርሻ ይታጠብ ዘንድ፤ የሆነውን ሁሉ በተሰበረ መንፈስ እናዘዝ ዘንደ እርዳኝ፡፡›› አልኩኝ ለራሴ፡፡ ቀና ብዬ አያቸው ዘንድ ብርታት አጣሁ፡፡

 

“ስመ ክርስትናህ ወልደ ሚካኤል ነው ያልከኝ?”

 

“አዎ አባቴ!”

 

“ሰሞኑን ስንገናኝ ከንስሐ ልጆቼ ጋር ጉዳይ ይዘን ስለነበር ጉዳይህን አልነገርከኝም፡፡ ለምን ይሆን የፈለግኸኝ?”

 

“አባቴ በቀጠሯችን መሠረት መጥቻለሁ፡፡ በኀጢአት ምክንያት የተቅበዘበዝኩኝ፤ ኀጢአቴ ያሳደደኝ፤ ለዓለም እጄን የሰጠሁ ምስኪን ነኝ፡፡ ህሊናዬ ሰላም አጥቷል፡፡ ያሳርፉኝ ዘንድ አባትነትዎን ሽቼ ነው የመጣሁት፡፡” አልኳቸው በተሰበረ ልሳን፡፡

 

ለጥቂት ሰከንዶች ከራሳቸው ጋር የሚመክሩ በሚመስል ስሜት ቆይተው “ልጄ የንስሐ ልጆች በብዛት አሉኝ፡፡ ሁሉንም ለማዳረስ አልቻልኩም እኔም በፈተና ውስጥ ነኝ፡፡ አንተ ደግሞ ተጨምረህ ባለ እዳ ሆኜ እንዳልቀር ሰጋሁ፡፡ ይቅርታ አድርግልኝና ሌላ አባት ብትፈልግ ይሻላል፡፡” አሉኝ ትህትና በተላበሰ አነጋገር፡፡

 

“እግዚአብሔር እርስዎን አገናኝቶኛልና ወደ ሌላ ወዴትም አልሔድም፡፡ ያለፈው ይበቃኛል፡፡” አነጋገሬ ውሳኔዬን እንደማልቀይር ይገልጽ ነበር፡፡

 

“ያመረርክ ትመስላለህ፡፡” አሉኝ ውሳኔዬ አስገርሟቸው፡፡

 

“አባቴ ታከተኝ፡፡ ቆሜ ስሔድ ሰው እመስላለሁ ፤ ነገር ግን ኀጢአት በባርነት የገዛኝ ርኩስ ነኝ፡፡ የመጣሁት ከባርነት ይታደጉኝ ዘንድ ነው፡፡ እባክዎ አባቴ እሺ ይበሉኝ!” ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡

 

ለቅሶዬን እስክገታና አስክረጋጋ ድረስ ጠብቀው “እንዲህ በተሰበረ መንፈስ ውሰጥ ሆነህ ጥዬህ ብሄድ ሸክሙ ለራሴው ነው፡፡ አንድ ጊዜ መጥተሃልና አላሰናክልህም፡፡” አሉኝ በፍቅር እያስተዋሉኝ፡፡

 

“እግዚአብሔር ይስጥልኝ አባቴ!” እግራቸው ላይ ተደፋሁ፡፡

 

“ተው – ተው አይገባም ልጄ – ቀና በል፡፡” ብለው ከተደፋሁበት በሁለት እጃቸው አነሱኝ፡፡

 

“ከዚህ በፊት አበ ነፍስ ነበረህ?” አሉኝ አረጋግተው ካስቀመጡኝ በኋላ፡፡

 

በአዎንታ ጭንቅላቴን ከፍና ዝቅ በማድረግ ገለጽኩላቸው፡፡

 

“በምን ምክንያት ተለያያችሁ?”

 

ራሴን ለማረጋገት እየሞከርኩ ዕንባዬን ጠርጌ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡

 

“አባቴ ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ ከአንድም ሦስት ጊዜ የንስሐ አባት ቀያይሬያለሁ፡፡”

 

“ለምን?” በመገረም ነበር የጠየቁኝ፡፡

 

“ለእኔም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ከአንዱ እየፈረረጠጥኩ ወደ አንዱ እየሔድኩ ነፍሴን አሳሯን አበላኋት፡፡”

 

“ከሦስቱም እየተሰናበትክ ነው እዚህ የደርስከው?” የበለጠ ለመስማት በመጓጓት ጠየቁኝ፡፡

 

“ከአንዳቸውም ጋር በስንብት አልተለያየሁም፡፡ በራሴ ፈቃድ ኮበለልኩ፡፡”

 

ለውሳኔ የተቸገሩ በሚመስል ስሜት የእጅ መስቀላቸውን እያገላበጡ ተከዙ፡፡ በመካካላችን ጸጥታ ሰፈነ. . . ፡፡

ይቀጥላል