‹‹እርሱ እንደተናገረው ተነሥቶአል›› (ማቴ. ፳፰፥፮)

እንኳን አደረሰን!

በዝግጅት ክፍሉ

ሚያዚያ ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በዕለተ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ በመንፈቀ ሌሊት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከመቃብር ተነሣ፤ ነቢዩ ዳዊትም ‹‹እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ›› ብሎ እንደተናገረው አምላካችን ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል፡፡ ትንሣኤ ሙታንን እናከብርም ዘንድ ይገባልና ክርስቲያኖች በሙሉ ደስ ይበለን! (መዝ. ፸፯፥፷፭)

በማቴዎስ ወንጌል ‹‹እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶአልና፤ ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ፡፡ መልኩም እንደ መብረቅ ነጭ ነበር፡፡ እርሱንም ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁ ታወኩ፤ እንደ በድንም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፡፡ በዚህ የለም፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል›› ተብሎ እንደተጻፈው መድኃኒዓለም ብርሃንን ተጎናጽፎ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን በክብር ተነሥቶአል፡፡ (ማቴ.፳፰፥፪-፮)

አስቀድመው ነቢያት በትንቢት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ከኃጢአት ባርነት ነጻ እንደሚያወጣውና ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል በዕለተ ዐርብ መከራ ሥቃይ ተቀብሎ፣ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶና ተቀብሮ በሦስተኛው ዕለትም ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ ተናግረው ነበር፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ ስለ ትንሣኤ ሙታን ሲመሰክር እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል፤ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን፡፡›› (ሆሴ. ፮፥፪)

ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ገልጾ እንደሚነሣ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ ‹‹ልጄ ሆይ፥ ከመሰማሪያህ (ከመቃብር) ወጣህ፡፡ እንደ አንበሳ ተኛህ፤ አንቀላፋህም፡፡ እንደ አንበሳ ደቦል የሚቀሰቅስህ የለም›› የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡  ‹‹የሚቀሰቅስህ የለም›› የሚለውን ኃይለ ቃል ተጽፎ ስንመለከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ አስነሽ ሳይሻ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ የሚያስረዳ ነው፡፡ ጌታችንም በራሱ ሥልጣን እንደሚነሣ እንዲህ በማለት አስተምሯል፤ ‹‹እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፡፡ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና›› እንዲል፤ ይህ የሚያስረዳን ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በፈቃዱ እንደ ሞተና በሥልጣኑ እንደ ተነሣ ነው፡፡ (ዘፍ. ፵፱፥፱፣ ዮሐ. ፲፥፲፯)

ጌታችን ኢየሱስ ስለ ትንሣኤው ቀድሞ ለደቀ መዝሙርቱ እንዳስተማራቸው በወንጌልም ተጽፎአል፡፡ ‹‹ሽማግሎችና የካህናት አለቆች፣ ጻፎችም የሰውን ልጅ ይነቅፉት ዘንድ ብዙ መከራም ያጸኑበት ዘንድ እንዳለው፥ እንደሚገሉትና በሦስትኛው ቀንም እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀምር›› እንዲል፡፡ (ማር. ፰፥፴፩)

ሆኖም ግን የጌታችን ትንሣኤ በትምህርቱ የተገለጸ ቢሆንም የእርሱን ከሙታን ተለይቶ መነሣት በዐይኑ ሳያይ በእጁ ሳይዳስስ ለማመን የተቸገረ ሰው እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የጌታችንን የተቸነከሩትን እጆቹንና እግሮቹን፣ በጦር የተወጋውን ጎኑን ካላየና ካልዳሰሰ የክርስቶስን መነሣት አላምን ብሎ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ሐዋርያቱ በተሰበሰቡበት ዝግ ቤት ጌታችን ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ብሎ የተወጋውን ጎኑን አሳይቶ በክብር መነሣቱን እስከሚያረጋግጥለት ድረስ የጌታችንን ትንሣኤ ለማመን እንደተቸገረ በዮሐንስ ወንጌል ተጽፏል፡፡ (ዮሐ. ፳፥፲፱-፳፬)

በአሁኑ ጊዜም የጌታችን ትንሣኤ የማያምኑ እንዳሉ እሙን ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለዐይን በሚታየው እውነት እንዳታምኑ ማን አታለላችሁ?›› ብሎ እንደ ተናገረው ዛሬም ስለ ምሥጢረ ትንሣኤው መስማትም ሆነ መናገር የማይፈልጉ እንዲሁም የማይረዱ መናፍቃን አሉ። ሐዋርያውም ስለነዚህ ሰዎች ሲናገር በመጨረሻው ዘመን ብዙ ዘባቾች እንደሚኖሩና ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ጌታ ይመጣል፤ ትንሣኤ ሙታን ይደረጋል፤ ያላችሁት የት አለ? እያሉ የሚክዱና የሚያስክዱ መሆናቸውን ገልጿል። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ሙታን ሲያስተምር እንዳፌዙበት ሁሉ ለዚህ ትውልድም የሙታን ትንሣኤ ሲነገር የሚቀልዱና የሚዘብቱ በርካቶች ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ የአቴና ሰዎችን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ በጌታችን ትንሣኤ አምነው በትንሣኤው ክብርን እንዲወርሱ ቢያስተምራቸውም ብዙዎቹ ግን ድኅነትን ከመፈለግ ይልቅ ፌዝን መረጡ።  (የሐዋ. ፲፯፥፴፪፣ ገላ. ፫፥፩፣ ፪ ጴጥ ፫፥፩-፲፰)

ጌታችን ኢየሱስ በወንጌል ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ›› በማለት ሲያስተምርም ትምህርቱን ያልተረዱና የሐዋርያትንም ስብከት የሚያቃልሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚህም ትውልድ ስለትንሣኤ ሙታን ሲነገራቸው የማያምኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸው የታወቀ ነው። (ዮሐ. ፲፩፥፳፭)

በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የእነርሱም ትንሣኤ ነው፤ የጌታችን ትንሣኤ የሙታንን ሁሉ መነሣት ያረጋግጣልናል፡፡ በጌታችን ትንሣኤ ለምናምን ወይም ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት ተስፋ ስለምናደርግ፣ መልካም ሥራ ለምንሠራ ሰዎችም ትንሣኤ ጌታ ሲያስተምር ‹‹በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ፡፡ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፥ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ›› ብሏል፡፡ (ዮሐ. ፭፥፳፰)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የተነሣበት ዕለት መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ ተወግዶ፣ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ፣ ፍጹም ነጻነት፣ የማይለወጥ ደስታ፣ የተገኘበት ስለሆነ ፋሲካ ይባላል፡፡ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበትን ቀን ፋሲካ ብለውታል፤ ፋሲካ የደስታ፣ የዕርቅ፣ የሰላም፣ የድኅነት ቀን ነውና። ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከመላቀቅ፥ ከኃጢአት ባርነት እስራት ከመፈታት የሚበልጥ ምንም ደስታ ሊኖር አይችልምና ዕለቱን ፋሲካ ብለንም እንጠራዋለን።