በዓለ ግዝረት

የጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ግዝረት በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ ልሳነ ዕፍረት ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ክርስቶስ በሥጋው ግዝረትን ተቀበለ፡፡ ለአባቶች የተሰጠውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ፤›› በማለት እንደ ተናገረው (ሮሜ.፲፭፥፰) የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጽሟል፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ በስምንተኛው ቀን እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ግዝረት ይፈጸምለት ዘንድ ሕፃኑ ጌታችንን ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ ስሙም ገና በሥጋ ሳይፀነስ የእግዚአብሔር መልአክ ባወጣለት ስም ‹‹ኢየሱስ›› ተብሎ ተጠራ (ሉቃ.፪፥፳፩-፳፬)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ሲገረዝ የሊቀ ካህን ልጅ ነው ብለው ሊገርዙት ወደ እርሱ መጡ፡፡ ጌታችን ግን ወደ ምድር የመጣው ለትሕትና ነው እንጂ ለልዕልና አይደለምና ወሰዱት አለ (ትርጓሜ ወንጌለ ሉቃስ)፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አረጋዊው ዮሴፍን ‹‹እንደ ሕጉ ልጄን እንዲገርዘውና ስሙንም እንድንሰይመው ብልህ የሆነ ገራዥ ሰው አምጣልኝ፤›› አለችው፡፡ ጻድቁ ዮሴፍም እንዳዘዘችው የሚገርዝ ባለሙያ ይዞ መጣ፡፡ ባለሙያውም በእናቱ በንጽሕት ድንግል ማርያም ክንድ ላይ ሕፃኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባየው ጊዜ ‹‹እንድገርዘው በጥንቃቄ ያዙት›› አላቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ‹‹ባለሙያ ገራዥ ሆይ! ደሜ ሳይፈስ ልትገርዘኝ ትችላለህን? በዕለተ ዓርብ በመስቀል ስሰቀል ካልሆነ በስተቀር ደሜ አይፈስምና፡፡ ጐኔን በጦር ሲወጉኝ ያን ጊዜ ውኀና ደም ይፈሳል፡፡ ይኸውም ለአዳምና ለሚያምኑ ልጆቹ መድኃኒት ይሆናል፤›› አለው፡፡

የክብር ባለቤት ጌታችን የተናገረውን ይህን ቃል ባለሙያው በሰማ ጊዜም አደነቀ፡፡ ዕቃውንም ሰብስቦ ተነሣና ከጌታችን እግር በታች ወድቆ ሰገደ፡፡ ያንጊዜም ምላጮቹ በእጁ ላይ እንዳሉ እንደ ውኀ ቀለጡ፡፡ ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም ‹‹ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፡፡ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ ይህ ልጅሽ ስለ እርሱ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የሕያው አምላክ ልጅ ነው፤›› አላት፡፡

ጌታችንም ባለሙያውን ‹‹እኔ ነኝ! ትገዝረኛለህን ወይስ ተውክ? ወይስ የአባቶቼ አባቶች እንዳደረጉ ላድርግ?›› አለው፡፡ ባለሙያውም መልሶ ‹‹የአባቶችህ አባቶች እነማን ናቸው?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ጌታችንም አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ የሕዝቡ ሁሉ አባት እንደ ሆኑ ካስገነዘበው በኋላ ‹‹ለእነርሱም ይህ ግዝረት አስቀድሞ ከአባቴ ዘንድ ተሰጣቸው›› በማለት የግዝረትን ሕግ አስረዳው፡፡ ባለሙያውም ይህን ምሥጢር ሲሰማ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር እነጋገር ዘንድ አልችልም፡፡ በአንተ ህልውና መንፈስ ቅዱስ አለና፤›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት መሰከረ፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችን ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ ‹‹አባት ሆይ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ አስቀድሞ ግዝረትን የሰጠሃቸው፤ ያቺን ግዝረት ዛሬ ለእኔ ስጠኝ›› አለ፡፡ ያንጊዜም ያለ ሰው እጅ በጌታችን ላይ ግዝረት ተገለጠ (የግዝረት ምልክት ታየ)፡፡ ከዚህ ላይ ጌታችን ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር አብ ልመና ማድረሱ የለበሰው ሥጋ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ መሆኑንና ጸሎት ማቅረብ የሚስማማው ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ ነው እንጂ በእርሱና በአብ መካከል ልዩነት ኖሮ አይደለም፡፡

ጌታችን ድንግልናዋን ሳያጠፋ ከድንግል ማኅፀን እንደ መወለዱ ግዝረቱም አይመረመርም፡፡ በተዘጋ ቤት ወደ ሐዋርያት እንደ ገባና እንደ ወጣ ሁሉ እርሱ በሚያውቀው ረቂቅ ጥበብ ከሥጋው ምንም ምን ሳይቈረጥ፣ ምንም ደም ሳይፈሰው መገረዙ ተገለጠ፡፡

ገራዡም የጌታችንን ቃል ከመስማቱ ባሻገር በሥጋው ላይ የተደረገውን ተአምር ባየ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ከክብር ባለቤት ከጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ወድቆም ሦስት ጊዜ ሰገደና ‹‹በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእስራኤልም ንጉሥ ነህ!›› በማለት በክርስቶስ አምላክነት አመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ያየውንና የሰማውን ሁሉ እየመሰከረ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ኅብረት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያለ ጥርጥር በፍጹም ልባችን ከምእመናን ጋር ይሁን!፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፤ ጥር ፮፤ የሉቃስ ወንጌል አንድምታ