ማኅበረ ቅዱሳን በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ ግብዓቶች ድጋፍ አደረገ
የማኅበረ ቅዱሳን ሙያ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሆነበት አስቸኳይ የምግብ ግብዓቶች ድጋፍ አድርጓል።
ባለፉት ጊዜያት በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች ባጋጠማቸው ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት የተጎዱ ከ1500 የሚልቁ ወገኖች በማንቡክ ከተማ ውስጥ በተለያየ ሁኔታ ከማኅበረሰቡ ጋር ተጠልለው እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህንንም ችግር የተረዳው ማኅበረ ቅዱሳን በግልገል በለስ ማእከል በኩል ከመተከል ዞን የሚመለከታቸው የመንግሥት ኀላፊዎች ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ድጋፎችን ለተጎጅዎች ለማድረስ ሲሠራ የቆየ ሲሆን በዚሁ መሠረት ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በቦታው በመገኘት ከ1.04 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሆነበት 180 ኩንታል የበቆሎ ምግብ ግብዓቶችን ለተጎጅዎች አድርሷል።
በድጋፍ ርክክብ ወቅትም የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከልን በመወከል የሰሜን ምዕራብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አገልጋዮች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ግልገል በለስ ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ግዛቸው ታደሰ፣ የመተከል ዞን ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ኀላፊ አቶ ሙሉጌታ ዐባይ፣ የዳንጉር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ጃኔ በጋራ ተገኝተው ድጋፉን ለተጎጅዎች እጅ በእጅ አስረክበዋል።
የመምሪያው ኀላፊም አቶ ሙሉጌታ ዐባይ የዞኑ መንግሥት ተጎጅዎችን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውሰው፣ ማኅበረ ቅዱሳንም ለተጎጅዎች ላደረገው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ይህ ድጋፍ የተደረገው በሀገረ አሜሪካ ከሚገኘው “ማኅበረ በዓለ ወልድ ዘሰሜን አሜሪካ” በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሸፈነ መሆኑ ተገልጿል።
የማኅበረ ቅዱሳን ሙያ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎትም በ2018 ዓ.ም ባለፉት 9 የአገልግሎት ወራት ብቻ በመላ ሀገራችን 14 የሚደርሱ ማኅበራዊ ድጋፍ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን በያዝነው ጾመ ሐዋርያትም “የጾም ቁርሳችን ለወገኖቻችን” በሚል መሪ ቃል ሰፊ የማኅበራዊ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራዎችን እየሠራ በመሆኑ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ቀውሶች የተጎዱ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ፣ ማኅበሩ በሚያደርገው የሰብአዊነት ሥራ ምእመናን እና ተቋማት የተለመደ ድጋፍ እንድታደርጉልን ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
ድጋፍ ለማድረግ፡-
#በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሒሳብ ቁጥሮች፡-
በአሐዱ ባንክ 0025393810901
በአቢሲንያ ባንክ 37235458
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000309803648
በወጋገን ባንክ 0837331610101
በአዋሽ ባንክ -01329817420400 እንዲሁም
በወገን ፈንድ፡- https://Www.wegenfund.com/mknu መጠቀም የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።
