“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ.፫፥፰)
በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
ክፍል ሁለት
ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የመገለጡ (ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የመወለዱ) ነገር እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ወፍ ዘራሽ ድንገት የሆነ አይደለም፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት ከተሰደደ በኋላ ተከትሎ እግዚአብሔርን ያህል አምላክ፣ ልጅነትን ያህል ጸጋ፣ ገነትን ያህል ቦታ አጥተን እንዴት መኖር ይቻለናል ብለው ስለ በደላቸው ንስሓ በመግባታቸው አብዝተውም በማልቀሳቸው ወደ ልባቸውም በመመለሳቸው እግዚአብሔር ምሕረት እንደሚያደርግላቸው ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይህም ተስፋ፡- “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ፤ በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በሜዳህ ድሄ፣ በመስቀል ተሰቅዬ በሞቴ አድንሃለው” የሚል ነው፡፡ (መጽ. ቀሌምንጦስ)፡፡
ይህንንም ተስፋ እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን ከሰጣቸው በኋላ በየዘመኑ ቅዱሳን አበውን እያስነሣ በተለያየ ምሳሌ እያሳየ በራእይ እየገለጠ፣ በነቢያት ላይ አድሮ ትንቢት እያናገረ ሕዝቡን ሲያጽናና በተስፋ ሲጠብቅ ነበር፡፡ ያ የተስፋ ጊዜ ሲደርስ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ (ተወለደ)፡፡
ለዚህም ነው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲኖች በላከላቸው መልእክቱ:- “ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ፣ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ፣ እኛ የልጅነትን ክብር እንድናገኝ በኦሪት የነበሩትን ይዋጅ ዘንድ ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ”(ገላ.፬፥፬) ያለው፡፡ እንደ ተስፋ ቃሉ ከጊዜው ሳይቀድምና ሳያሳልፍ ጊዜውና ሰዓቱ ሲደርስ ተወለደ፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወለደ፡፡ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”(ኢሳ.፯፥፲፬) በማለት እመቤታችን ቅድመ ወሊድም ሆነ ድኅረ ወሊድ ድንግል እንደሆነች ጠቅሶ እርሷ እመ አማኑኤል፣ እርሱ ደግሞ አምላክ ወሰብእ መሆኑን አስረድቶ አምላክ እንዲወለድ አስቀድሞ መወለድ ነቢዩ ኢሳይያስ አብሥሮናል፡፡
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ (የመወለዱን) ዓላማ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ከብዙ በጥቂቱ ብንመለከት፡-
የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ
ሰይጣን (ዲያብሎስ) የሚገለጥባቸው የራሱ ባሕርያት አሉት፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ትዕቢት፣
ነፍሰ ገዳይነት፣ ሐሰተኝነት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ትዕቢት፡- ዲያብሎስ እየተዋረደ ከብሬአለሁ የሚል፣ ወደ ጥልቁ እየወረደ ወደ ከፍታ እየወጣሁ ነው፣ የሚል ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቁቶ ሳለ የክብር ካባ ደርቤአለሁ የሚል፣ ውድቀቱን ትንሣኤ አስመስሎ የሚናገር ሐሰተኛ ነው፡፡
የዲያብሎስን (የሰይጣንን) ትዕቢት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል “አንተ በንጋት የሚወጣ የአጥቢያ ኮከብ ሆይ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ? ወደ አሕዛብም መልእክትን የላክህ አንተ ሆይ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቀጠቀጥህ! አንተም በልብህ፡- ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ ዙፋኔንም ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፣ በሰሜንም ዳርቻ በረዣዥም ተራሮች ላይ እቀመጣለሁ፣ ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፣ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፡፡ ዛሬ ግን ወደ ሲኦል ትወድቃለህ ወደ ምድር ጥልቅም ትወርዳለህ” (ኢሳ.፲፪፥፲፫) ይላል፡፡
ይህ ስሑት የትሕትና ተቃዋሚ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ሊሆኑ የሚወዱ ሁሉ የትዕቢትን ካባ አውልቀው ትሕትናን እንደ ልብስ ሊለብሱት እንዲገባ ያስተማረው፡፡ አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ምንጩ ከዲያብሎስ የሆነውን ትዕቢት እንደሚጠላና ትዕቢት የሚያዋርድ ትሕትና ግን የሚያከብር መሆኑን በወንጌል አስተምሮናል፡፡ “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ይከብራልና” (ማቴ.፳፫፥፲፪) እንዲል፡፡
“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት ቅዱስ ዮሐንስ የተናገረውም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከከፍታ ወደ ዝቅታ ወርደን፣ በሲኦል ባርነት፣ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዘን ወደ ነበርን ወደ እኛ ንጽሕት ዘር ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በፍጹም ትሕትና መወለዱንነው፡፡ “አምላክ ሰው ሆነ” ስንልም የሚደንቀን በፍጹም ትሕትና በቤተልሔም በከብቶች በረት መወለዱ ነው፡፡
ነፍሰ ገዳይነት፡–
ዲያብሎስ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ እርሱም የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ ዲያብሎስ ነፍስን ከእግዚአብሔር እንድትለይ ኃጢአት በማሠራት እንድትበድል በማድረግ፤ ሥጋን በጭካኔ አንዱ በሌላው፣ ወንድም በወንድም፣ ልጅ በአባት፣ አባትም በልጅ ላይ፣ ወንድም በእኅቱ ላይ፣ እኅትም በወንድሟ፣ ባል በሚስቱ፣ ሚስትም በባልዋ ላይ በክፋት እንዲነሣሱ በማድረግ የገዳይነትን ሥራ ይሠራል፡፡ ይህም ከጥንት ጀምሮ አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን እንዲበሉና ሕገ እግዚአብሔርን እንዲተላለፉና እንዲሞቱ ያደረገ ነው፡፡ እንዲሁም በቃኤል ላይ አድሮ አቤልን ያስገደለ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዲያብሎስ ነፍሰ ገዳይነት እንዲህ በማለት ተናግሯል፡፡ “የአባታችሁንም ፈቃድ ልታደርጉ ትወዳላችሁ እርሱ ከጥንት ጀምሮ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡”(ዮሐ.፰፥፵፫)::
ሐሰተኝነት፡– ዲያብሎስ (ሰይጣን) ሐሰተኛ ነው፡፡ ሐሰተኛ ብቻም ሳይሆን የሐሰት መገኛ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላእክት ከተማ ሐሰትን ከራሱ አፍልቆ ተናግሯልና ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደጠቀሰው “በእርሱ ዘንድ እውነት የለምና ሐሰትንም በሚናገርበት ጊዜ ከራሱ አንቅቶ ይናገራል ሐሰተኛ ነውና የሐሰትም አባት ነውና”(የሐ.፰፥፵፬)፡፡
ዓለሙን ሁሉ እያሳተ ኃጢአትን ጽድቅ፣ ውርደትን ክብር አስመስሎ እያሳየ ከእግዚአብሔር የሚለየው ይኸው የሐሰት አባት የተባለው ዲያብሎስ ነው፡፡ በየትኛውም ምክንያት ይሁን ሰው ኃጢአት የሚሠራው የራሱ ስንፍና እንዳለ ሆኖ በዚህ ሐሰተኛ በሆነው በሰይጣን ወጥመድ ነው፡፡
ሰይጣን(ዲያብሎስ) የሐሰት መገኛ ነው፡፡ የሐሰት አባት የተባለውም ሐሰትን ከራሱ አፍልቆ የሚናገር የሐሰት አስተማሪ ስለሆነ ነው፡፡ ዲያብሎስ(ሰይጣን) እነዚህንና መሰል ክፉ ተግባራትን የሚፈጽም እና የሚያስፈጽም በመሆኑ ይህንን እኩይ ተግባሩን ከሰው ልቡና ነቅሎ ለመጣል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠበትን ዓላማ ሁለተኛውን ክፍል በቀጣዩ ዝግጅት እንመለከታለን፡፡ እስከዚያው ቸር እንሰንብት፡፡