ጸሎተ ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ጌታችን ምሥጢረ ቊርባንን ከምሥጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ የገለጠበት ዕለት ነው፡፡ በወንጌልም እንደተጻፈው ፋሲካውን የሚያከብሩበት ቀን ሲደርስ ጌታ ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሒዳችሁ ፋሲካን እንበላ ዘንድ አዘጋጁልን አላቸው፤ እነርሱም በየት እንድናዘጋጅልህ ትወዳለህ አሉት? ወደ ከተማ ገብታችሁ የውኃ ማድጋ የሚሸከም ስምዖን የተባለ ሰው ታገኛላችሁ፤ ወደ ገባበት ቤት እርሱን ተከተሉት፤ መምህር ከደቀ መዛሙርቶቼ ጋር ፋሲካ የሚያደርግበት አዳራሽ ወዴት ነው ይልሃል? በሉት እርሱ የተነጠፈውንና ታላቁን አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም ፋሲካን አዘጋጁልን አላቸው፤ እነርሱም ወደ ተላኩበት ከተማ ገብተው አልዓዛርን የውኃ ማድጋ ተሸክሞ አገኙት፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም ለስምዖን ጌታ በቤቱ ፋሲካን ሊያዘጋጅ መሻቱ እንደሆነ ነገሩት፤ እርሱም የፍጥረታት ጌታ በቤቱ ሊመጣ እንዳለ አስቦ ተደሰተ፤ ወደ ሚስቱ አክሮሲናም ሔዶ ይህ አልዓዛርን ከሞት ያስነሳ እኔንም በኃጢአቴ ይቅር ይለኛል፤ ያነጻኝ ዘንድ ከሐዋርያት ጋር በቤታችን ይመጣል አላት፤ አክሮሲናም እጅግ ተደሰተች፡፡

ጌታችንም ጊዜው ሲደርስ ከሐዋርያት ጋር በአንድነት መጣ፤ ስምዖንም ከቤቱ ወጥቶ ሮጦ ከጌታ እግር ሥር ሰገደ፤ ወደ ቤቱም ከሐዋርያት ጋር አስገባቸው፡፡ ይሁዳ ግን ይህን ሰዓት አልነበረም፤ ውጪ ከሻጭና ለዋጭ ጋር ገንዘብ ሲደራደር ነበር፤ ስምዖንም ለሚስቱ አክሮሲና ጌታና ሐዋርያት የሚገቡበት በእግራቸው የሚረግጡት ምንጣፍ እንድታነጥፍ አዘዛት፡፡ አክሮሲና ግን የጌታን መልክ አታውቀውም ነበር፤ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ጸሎት ሲጸልዩ አይታ ‹‹ከእናንተ ውስጥ መምህሩ ማነው›› አለቻቸው፤እነርሱም ዝም አሉ፤ መልከ መልካም ወደ ሆነውና የጌታ ወዳጅ ወደሆነው ዮሐንስ ተመልክታ እርሱ ይሆን አለች፤ ጴጥሮስ ግን ቀበል አድርጎ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ከውስጠኛው ክፍል ቆሞ ይጸልያል፤ ጌታ እርሱ ነው›› አላት፡፡ እርሷም ገብታ ሰገደችለት፤ ይሁዳም በመጨረሻ ሳጥን ተሸክሞ መጣ፤ ጠባቂውንም እኔ የጌታ ደቀ መዝሙር ነኝ አለው፡፡ በር ጠባቂውም እለእስክንድሮስም የተነጠፈውን እስካጥፍ ጠብቅ ብሎ ዘለፈው፤ ልብሱንም አንስቶ አስገባው፤ /ግብረ ሕማማት ፭፻፹፫-፫፻፹፭/፡፡

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል (ማቴ. ፳፮፥፯-፲፫)፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን በግብጽ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡ ሙሴም የታዘዘውን ለሕዝቡ ነገረ፤ ዅሉም እንደ ታዘዙት ፈጸሙ፡፡ በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ መቅሠፍት ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብጻውያንን ቤት በሞተ በኵር ሲመታ፤ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ አልፏል፡፡ ፋሲካ መባሉም ይህን ምሥጢር ለማስታወስ ነው (ዘፀ. ፲፪፥፩-፳)፡፡

በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች አገር እንደ መኾኗ ይህን ሥርዓት ትፈጽም ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ‹ፋሲካ› ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ጌታችን በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ ምሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስም ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናል፡፡ ስለዚህም ክርስቶስን ‹ፋሲካችን› እንለዋን (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯፤ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፰-፲፱)፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ስያሜዎች

 ጸሎተ ሐሙስ

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ ያደረሱበትን መከራ በማሰብ የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ሆሳዕና ማግስት ጀምሮ ሰሙነ ሕማማትን በሐዘን፣ በጸሎትና በስግደት ታሳልፈዋለች፡፡ ለቀናቱንም የተለያየ ስያሜ ሰጥታ ሥርዓቱን ታከናውናለች፡፡ በዚህም መሠረት፡-

  • ሰኞ፡– አንጽሆተ ቤተ መቅደስ(በቤተ መቅደስ ሲሸጡና ሲለውጡ የነበሩትን ያስወጣበት) ፣ እንዲሁም አምላክ ሲሆን የእኛን ሥጋ ተዋሕዷልና ተራበ፡፡ ለምልማ ከነበረችው በለስ ፍሬ ይበላ ዘንድ ጎበኛት ነገር ግን ፍሬ አጣባት፡፡ በለሷንም ረገማት፡፡ ስለዚህም መርገመ በለስ ተባለ፡፡
  • ማክሰኞ:የጥያቄ ቀን፣ የትምህርት ቀን
  • ረቡዕ፡- የምክር ቀን (አይሁድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገድሉት ዘንድ የተማከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን ነው፡፡ ይሁዳም በሰላሣ ብር አሳልፎ ሊሰጣቸው የተስማማበት ቀን ነው፡፡

 ጸሎተ ሐሙስ

ስለ ሦስቱ የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ይህን ያህል ካልን ጽሁፋችንን ጸሎተ ሐሙስ ላይ ትኩረት አድርገን እንቀጥላለን፡-

ጸሎተ ሐሙስን ሕፅበተ ሐሙስ፣ የምስጢር ቀን፣ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፣ የነፃነት ሐሙስ እየተባለም ይጠራል፡፡

ሕጽበተ ሐሙስ

ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ “ሕጽበተ ሐሙስ” ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን” ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምሥጢር ቀን

ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ “የምሥጢር ቀን” ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ፤ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ በማለት እርሱ ከእኛ፤ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምሥጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ

መድኃኒታችን ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ይህ ዕለት “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ይባላል (ሉቃ. ፳፪፥፳)፡፡ “ኪዳን” ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለ ሆነ ሐሙስ “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ

ይህ ዕለት ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለ ሆነ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላል፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፡፡ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ በማለት ከባርነት የወጣንበትን፤ ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመኾኑ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላል (ዮሐ. ፲፭፥፲፭)፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡ ባሮች ሳይሆን ወዳጆች ተብለን በክርስቶስ ተጠርተናልና፡፡

በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ሆሉ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፲፬፥፲፮ የሚገኘውን ሰፊ ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎችም ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ያካትታሉ፡፡ ጌታችን እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ ለደቀ መዛርቱ ምሥጢሩን በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲቻለው በሰፊ ማብራርያ እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን ከዚህ እንማራለን፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠውም በዚሁ ዕለት ከምሽቱ በሦስት ሰዓት ነው (ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፰)፡፡

በጸሎተ ሐሙስ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ሥርዓት

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደ ተለመደው ይከናወናሉ፡፡ መንበሩ (ታቦቱ) ጥቁር ልብስ ይለብሳል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፤ ቤተ ክርስቲያኑም በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ ሕጽበተ እግር ይደረጋል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በየቤቱ ደግሞ ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

ሕጽበተ እግር

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፡-

ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

 ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲሆን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ሁሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *