ጉባኤ-ቃና መጽሔት-ነሐሴ-2016-ዓ.ም

ጉባኤ-ቃና መጽሔት-ነሐሴ-2016-ዓ.ም

ቅድስት

ትዕግሥት ባሳዝነው

ሰውነቴን ሳስብ በትዕቢት መዛሉን፣                                                   ሰው ከንቱ፣ ሰው መና፤ ከአምላኩ ተጣልቶ፣

ከንቱነቴን አየሁ በስስት መድከሙን፣                                               ለዲያቢሎስ ግብር፣ ለክፋት ያደረ ያልተሰጠን ሽቶ፣

እኔነቴን አየሁ ማምለኩ ገንዘብን፡፡                                                      ሲሰግድ የሚያድር ለቂም ሐውልት ሠርቶ፣

ይህን ሁሉ ሠርቼ አምላክ ላንዴ ባየው፣                                             ሲዘምር የሚያድር በጥላቻ ሰክሮ፣

እኔን ለማዳን መች ተሣነው፡፡                                                              ሲቀድስ የሚውል በመለያየት ጸንቶ፣

አምላክነቱን ረስቶ ሰው የሆነ መስሎት፣                                            ሰው ከንቱ፣ ሰው መና በትዕቢት ተውጦ፣

ዲያብሎስ ሊያስተው ቢፈትነው በትዕቢት፣                                    ሽማግሌን አሳዝኖ፣ ታላቁን አቅልሎ፣

አርባ ቀን አርባ ሌት፣                                                                         ለስስት ተገዝቶ ባለእንጀራን ክዶ፣

ጾምን አስተባብሮ በመቆም ለፀሎት፣                                                ገንዘብን የሚያመልክ ከሰውነት ወጥቶ፡፡

ዲያቢሎስ አፈረ ወጥመዱ ከሽፎበት፡፡                                               ጾሙንም በትዕቢት፣ ጸሎትን በስስት፣

አምላክ በእኒህ ኃጢያት ቢፈተንም ቅሉ፣                                         ምፅዋትን በፍቅረ ንዋይ፣

ዳሩ ለእኛ ነበር ለክርስቲያን ሁሉ፣                                                    እንዲህ ቢያታልል ወደ አምላኩ ሳያይ፣

ክርስቲያን ከተባልን ከክርስቶስ ወስደን፣                                         እርሱ ግን ይታያል ሥራውም በአዶናይ፣

ጾምንም ከጾምናት ከአምላክ ተምረን፣                                              እናም እንዲህ አልኩኝ አምላኬን ስማጸን፣

ታዲያ ለምን ይሆን ትዕቢት ያሳበጠን፣                                            ጾምህን ስንጾም ትዕቢታችን ይራቅ፣

ስስት ያጎበጠን፣ ገንዘብ ያስመለከን?                                                ጸሎትህን ስንጸልይ ትኅትናችን ይድመቅ፡፡

ጾማችንን ሳንሽር ጸሎታችን ሳንተው፣                                             አባት ሆይ ስንልህ ስስታችን ይጥፋ፣

በኃጢያት ደልበን በበደል የኖርነው፣                                               አምላካችን ስንል ፍቅርችንን አስፋ፣

ንስሓን ረግጠን ልጅነት ያጣነው፡፡                                                     ፍቅረ ነዋይም ይጥፋ፣

ሰው ከንቱ፣ ሰው መና፤ በዓለም የታለለ፣                                          በጾምህ ቀድሰን፣ በጸሎትህ አጽናን፣

በሰም ብቻ ከብሮ በግብሩ የተጣለ፣                                                   ዛሬም እንደ ጥንቱ ስንጠፋ ፈልገን፣

ሰውነቱ ከብዶት ሰው መሆን የረሳ፣                                                   አባታችን ስንል ልጆቼ ኑ በለን፣

ለዲያቢሎስ ግብር ለእርሱው እጅ የነሳ፣                                           ዛሬም ስንበድል በንስሓ ማረን፣

ጓደኛውን ክዶ አምላኩን ያስቆጣ፣                                                    በፍቅርህ አክመን፣ በቁስልህ ፈውሰን፣

የሌለውን ሽቶ ያለውንም ያጣ፡፡                                                          በሞትህ አድነን በመስቀልህ ጋርደን፣

በበደሉ ደልቦ በክፋት የኖረ፣                                                              ቅድስቷን እንቀድስ ከበደል አረቀህ ፣

ቂም በቀልን ቋጥሮ ሕጉንም የሻረ፣                                                    ጾምህን አስጀምረን,

በባልጀራው መኖር እርሱ እንቅልፍ ያጣ፣                                        ትዕቢት፣ስስት፣ ፍቅረ ንዋይ አጠፋ ከልባችን።

ከሰውነት ክብር ከሥርዓት የወጣ፡፡

ደወል ቤት

                                                ደወል ቤት                                            
አንድ ሰው ነበረ…
በልጅነቱ ዕድሜው በቤቱ የኖረ፣
ከደጁ ላይጠፋ ኪዳኑን ያሰረ፤
ሲለፋ ሲደክም ሲሮጥ ሲንደረደር
ከጾም ከጸሎት ጋር ሲተጋ ሲታትር፣
በሥጋ በመንፈስ እንደቃሉ ሚኖር፡፡
    ያቀደው ባይሞላ ድካም ቢሆን ትርፉ
ታናናሽ ያላቸው እየተውት ሲያልፉ፣
ልቡ ተቀይሞ ከአምላኩ ተኳርፎ
ለቅዳሴ ቆሞ ግንብ ተደግፎ
በኑሮው በዕድሉ በዕድሜው ሲቆዝም
ዘርዝሮ ሲያላምጥ ያልጨበጠውን ህልም፣
አንደበቱ ታስሮ በኩርፊያ መቀየም
ተንሥኡ ሲባል…. ዝምምም ፡፡
ሰላም ለናንተ …ዝምምም፡፡
በፍርሀት ስገዱ ወደ ምሥራቅ እዩ
ተሰጥኦ መልሱ እጅ ንሱ ጸልዩ፣
ዝምምም…
የውዳሴው ዜማ ሲፈስ ሲቀዳ
ልሳን እንደሌለው እንደማያውቅ ድዳ፣
በዓለም ዙረት ድካም ልቡ ከስላ ነድዳ፡፡
“ምን ፈልገህ ነው?” ሲል ፈጣሪን ሲሞግት
ከአንደበቱ ጸሎት ከመዝሙረ ዳዊት፣
“ለምን” ብቻ ቀርታው ከእልፍ አእላፍ ቃላት፤
ዝ ውእቱ ሲባል… ዝምምምም
ስብሐት ሲባል…ዝምምምም…
ስላልተነገረች የሀሳቡ ቀለም፣
ስላልተጠየቀች የህልውናው ትልም፡፤
በታጠፈ አንጀቱ በበረዳት ነፍሱ
የጥያቄ ዓይኖቹ በዕንባ ሳይርሱ፣
ላፍታ ሳይላወስ ያ ትንታግ ምላሱ…
መጽናናት ሳያሻው የአዋቂ ጥገና
የኤልያስ እሳት ወይ የሙሴ መና፡፡
ሁሉ በእርሱ እንዲሆን ሀሳቡ እያወቀ
አካሉ እያለቀ ልቡ እየተፋቀ፣
ወይ መቅደስ አልገባ ወይ ከፊቱ አልራቀ፡፡
በዓለም ሥርቆት ኃጢአት አልተጨማለቀ፣
በአመንዝራ ስሜት እቅፍ አልወደቀ!
ደጀ ሰላም ቆሞ ሁሌ እንደጠየቀ፡፡
ተሰጥኦ አይሻ ይትበሀል አያምረው
“ለምን” ሲል ፈጣሪን ሠርክ እንደጠየቀው፣
በቤትህ አድጌ ቃልህ ቃሌ ሆኖ
ዕጣፈንታ ዕድሌ በእጅህ ተወስኖ፣
የአካሌ ግንባታ ከአፈርህ ተዘግኖ…
ልጅነቴ አንተ ጋር የዕድሜዬ እኩሌታ
ኪዳን ሠርክህ ሆኖ የኑሮዬ ዋልታ፣
እንቅልፍ የማይወስደኝ ደወልኽን ሳልመታ፡፡
ለነፍሰ ገዳዮች ለሌባ ቀማኛ
ያልከለከልካትን ሲሳይና አዱኛ፣
ለኔ እንዴት ነሳኸኝ ምን ባስቀይምህ ነው
ለማትረባ እንጀራ አቅሜን ምትፈትነው?!
ለምን? ለምን? ለምን? ፊቴ ደስታን አጣ
ጽድቅን መለመኛ ጸሎት ሳይታጣ?!
እንጀራ ልመና ከመቅደስህ ልምጣ፡፡
ባሻገርከኝ ገደል ባለፍኩት ፈተና
በመከራዬ ውስጥ አውቅሀለሁና፣
አታይም አልልም ባጉል ምንፍቅና፡፡
ለሰው የሚሻውን እንድትሰጥ ባውቅም
ነገር ግን በቃሌ ስጠኝ አልልህም፡፡
ከጸሎት ቆጥሬ የሲሳይን ድካም
ለምን ራበኝ ብዬ ዕንባ አላባክንም
ነገር ግን…
ኪዳን ላይ ብታጣኝ ከደጀ ሰላምህ፣
የቅዳሴ ድምጼን ባይሰሙ ጆሮችህ፣
ወዴት ጠፋ ብለህ መጠየቅ አያሻም
ከእንግዲህ መጥቼ ምንም አልጠይቅም፣
ቆፍሬ ለማደር ወጥቻለሁ እኔም፡፡
አለና ዞር ሲል ለመሄድ ሲነሣ
ከመቅደሱ ቅጥር ወድቆ የተረሳ፣
አጥንቱ ተሰብራ ሥጋው ተቆራርሳ
መለመን ያቃተው ´ሚሄድ በዳበሳ
አረጋዊ አየና ልቡ ደነገጠ!
ከጎን በመኪና በውድ ነገሮች በተንቆጠቆጠ
ጤና ያጣ ወጣት መሬት ያልረገጠ፣
በልዩ መሳሪያ ብረት ተደግፎ
ወደ ቤተ መቅደስ በጎን ሲሄድ አልፎ፣
የልቡ ደወል ቤት አንድ ጊዜ ደወለ
ምን ጎደለኝ ብሎ ቃጭሉ አቃጨለ፡፡
ያኔ ሽፋሽፍቱ ሳያውቅ ዕንባ አዘለ
ድምጹ ከአንደበቱ ወጣ ፈነቀለ፡፡
ንሴብሕ ንዌድስ ንግባእኬ እያለ፡፡
እናም…
በጆሮህ ያልገባ ካይን የተከለለ
በድህነትህ ውስጥ በማጣትህ መሀል ጸጋና ሀብት አለ፡፡

                                                                                                             በቃለጽድቅ በላይነህ

በምሕረትህ ጎብኘኝ

ለዘመናት ከአንተ ስሸሽ እንደኖርኩኝ፣
ለማትጠቅመኝ ዓለም ለፈራሽ ሥጋዬ እንደተጨነኩኝ፣
ነፍሴን እንዳስራብኳት እንደተጠማሁኝ፣
አለሁ እኔ ባሪያህ ለተፈጠርኩለት መኖር እንዳቃተኝ፡

ጊዜ እንደሰጠኸኝ እንደጨመርክልኝ ማለዳ አስባለሁ፣
ለሥጋዬ ድካም ቀኔን ስጀምረው ደግሞ እዘነጋለሁ፡፡
አምላክ ሆይ ለምስኪን ልጅህ ግለጥልኝ፣
ዕድሜዬ ሲጨምር የኖርኩ ሲመስለኝ፣
ከተቀመጠልኝ ከተጻፈው ቀኔ ቁጥር እንደቀነስኩኝ፡፡

  • ወይ እኔ መሔዴ ወይ አንተ መምጣትህ፣
    የማይቀር ነውና ልጅህን መጥራትህ፡፡
    ጌታ ሆይ ባሪያህን በምሕረትህ ጎብኘኝ፣
    ለልቤ ልብ ሆነህ ማስተዋሉን ስጠኝ፣
    በዘላለማዊው በማያልፈው ቤትህ ሕይወት እንዲኖረኝ፡፡

                  ሳምራዊት ሰለሞን
ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሐረር ጤናና ሕክምና ሳይንስ ግቢ ጉባኤ

መስክርላት

ጥበብን በልክህ ሰፍታ ምታለብስህ፣
ሁሌም እንዲያምርብህ እንድትታይላት የምትለግስህ፣
ከማያልቅ ምንጯ ከጥልቅ ባሕሯ የምታስጎነጭህ፣
ያስከበረችህ ናት ተዋሕዶ እናትህ፣
በታናሽነትህ ደካማውን አንተን ታላቅ ያረገችህ፡፡

በደጇ መጣልን በቤቷ መውደቅን፣
እንድትመኝ ሁሌም በውስጧ መኖርን፡፡
ታሰማለች ድምጿን ትመለስላት ዘንድ፣
ከዘላለም ሕይወት ከሚለየው መንገድ፡፡
ስብዕና እንዲኖርህ ያልጎደለው ሰላም፣
ፈሩን ያለቀቀ ያልበረዘው ዓለም፡፡
እርሷን ተከተላት በትሕትና ሆነህ፣
ለታመምከው ለአንተ ለተጎሳቆልከው ፈውስ እንድትሆንህ፡፡

የኀላህን ዘመን የነበርክበትን፣
ክፉ ቀኖችህን ያሻገረችህን፡፡
እውነትን ሳትለቅ ለሁሉም ግለጣት፣
በእሷ መኖርህን በእሷ መክበርህን ሁሌ መስክርላት፡፡

  • ሳምራዊት ሰለሞን
    ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሐረር ጤናና ሕክምና ሳይንስ ግቢ ጉባኤ

ማስተዋሉን ስጠኝ

                ማስተዋሉን ስጠኝ

ያ መልካም ገበሬ ለበጋው የሚሆን ምርቱ የናፈቀው፣

ሕይወት የሚያድል ዘር በክረምት ጊዜው፡፡

                ይዘራ ጀመረ ወንጌሉን በሙሉ በወደደው መሬት፣

                የሚሰበስበው ለእርሱ የሚያደርገው ፍሬ እንዲሆንለት፡፡

ከፊሉ በመንገድ እንዲሁ ወደቀ፣

የሰማይ አዕዋፍ እየተመገቡት ያለፍሬ አለቀ፡፡

                ሌላም መጠን ያህል ደገኛው ከዘራው፣

                በመሬት ሆነና ጥልቅ አፈር በሌለው፡፡

ቢቀበልም እጅግ በሐሴት ተሞልቶ፣

በችግሩ ካደ ጊዜዋን ያልፋት ዘንድ ማፍራቱን ሰውቶ፡፡

                ደግሞ ከተቀረው ከዚያ ከመልካም ዘር ፣

                በእሾህ የታነቀ እንዳያፈራበት የተያዘም ነበር፣

                የዓለምን ትካዜ መከራ ሐሳቧን ተሸክሞ ‘ሚኖር፡፡

ከመልካሙ መሬት የወደቀው ቃሉ፣

ሠናይ ፍሬ ኖረው ተወዳጅ በሁሉ፡፡

                የሰማያውያን  ቃል አዳምጦታልና፤

                በተግባር ቢኖረው የእርሱ አደረገ መልካሙን ጎዳና፡፡

አምላክ ሆይ ያ ዘርህ በእኔ ልብ የላከው፣

ከሚቆረጠው ተክል ፍሬን ካላፈራው፣

በዓለም ትካዜ በእሾህ ከታነቀው፡፡

                መካከል ነውና ባሪያህን አስበኝ፣

                ከመልካሙ መሬት ዘርህን እንዳሳርፍ ማስተዋሉን ስጠኝ፡፡

 

                                ሳምራዊት ሰለሞን

                ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሐረር ጤናና ሕክምና ሳይንስ ግቢ ጉባኤ

ሰሚ ያጣው የሕፃናት ጩኸት

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

ቀኑ ወረፋውን ለጨለማው ለመልቀቅ በማመናታት ላይ ያለ ይመስላል፡፡ የአዲስ አበባ ምድርም የፀሐይን ብርሃን በሰው ሠራሽ ብርሃን ለመተካት ፓውዛዎቿን ስልም ቁልጭ እያደረገች ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው እየተሯሯጠ ነው፡፡ ጠዋት ሥራ የገባው ወደ ቤቱ ለመመለስ፣ ማታ የሚሠራው ደግሞ በአዲስ መንፈስ ለመሥራት ጥድፊያ ላይ ነው፡፡

ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተነሥቼ በድካም የዛለ ሰውነቴን ለማሳረፍ ወደ ቤቴ እያመራሁ ነው፡፡ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ዋናውን አስፓልት አቋርጬ ቀጥታ በድባብ መናፈሻ አድርጌ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ግቢን ትቼ ወደ ታች ስታጠፍ በርቀት የሚስረቀረቅ የሕፃናት ኅብረ ድምፅ ሰማሁ፡፡ ምን እንደሚሉ አይሰማም፤ የድምፃቸው ጣዕመ ዜማ ግን ልብን ሰርስሮ ይገባል፡፡

Read more

ከማያምነው ጸጉር አስተካካይ ጋር የተደረገ ውይይት

አንድ ሰው ጸጉሩንና ጺሙን ለመስተካከል ወደ አንድ ጸጉር ቤት ይሄዳል፡፡ ጸጉር አስተካካዩም ሥራውን መሥረት ከጀመረ በኋላ ከደንበኛው ጋር ጥሩ የሆነ ውይይት ይጀምራሉ፡፡

ብዙ ጉዳዮችን እያነሡ ከተወያዩ በኋላ “ነገርን ነገር ያነሣዋል” እንዲሉ ውይይታቸው ነገረ እግዚአብሔር ጋር ይደርሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ጸጉር አስተካካዩ “እኔ እግዚአብሔር አለ ብዬ አላምንም::” በማለት ይናገራል፡፡ ደንበኛውም በመገረም “እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ?” በማለት ይጠይቀዋል፡፡ “እንግዲህ እግዚአብሔር እንደሌለ (አለመኖሩን) ለማረጋገጥ ወደ ጎዳና ወጥተህ ነገሮችን ማየት ይኖርብሃል፡፡ እስኪ ንገረኝ እግዚአብሔር ቢኖር በየመንገዱ የምታያቸው ብዙ የታመሙ ሰዎች ይኖሩ ነበር? በየጎዳናው የምታያቸው ወላጅ የሌላቸው ሕጻናት ይኖሩ ነበር? እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ መከራም ሆነ ስቃይ የሚባል ነገር ባልኖረ ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ ክፉ ነገሮች የሚፈቅድ ደግሞ ፍጥረቱን የሚወድ አምላክ ነው በዪ ማሰብ አልችልም፤ ይከብደኛል፡፡” ደንበኛውም ትንሽ አሰብ ካደረገ በኋላ እንደገና ጉንጭ አልፋ ክርክር መክፈት ስላልፈለገ ምንም ነገር ሳይመልስ ዝም አለ፡፡

Read more