ኀለፈ ክረምት
ከዲ/ን ኃይለማርያም ታደሰ
“እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ፤ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፤ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ።” (መኃልይ ፪፥፲፩)
ይህን ኀይለ ቃል የተናገረው ጠቢቡ ሰሎሞን ሲሆን በመኃልየ መኃልይ ተመዝግቦ ይገኛል። መኃልይ ማለት ምስጋና ግጥም ቅኔ ማለት ነው። (ትርጓሜ መኃልይ ፲ቱ ወ፭ቱ ነቢያት ገጽ ፻፴፭ ሊቀ ጠበብት አስራደ ባያብል)
“ኀለፈ ክረምት” ፦ ክረምት አለፈ የዝናብ ወቅት ሄደ ማለት ሲሆን ከሰኔ ሃያ ስድስት እስከ መስከረም ሃያ አምስት ቀን ድረስ ያለው የዝናም ወራት ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል።(መኃ. ፪፥፲፩)
“ቆመ በረከት” ፦ ከመስከረም ሃያ ስድስት ቀን እስከ ኅዳር ስድስት ቀን የልምላሜ፣ የአበባና ፍሬ፣ ወራት የሆነ አርባ ቀን ዘመነ ጽጌ ተተካ ማለት ነው። (ሊቀ ጠበብት አስራደ ባያብል የማኅሌተ ጽጌ ትርጓሜ የመጀመሪያ እትም ፲፱፻፱፰ ዓ.ም ገጽ ፲፩)
ይህ ጥቅስ የተፈጥሮን መፈራረቅ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅን የሕይወት ጉዞ፣ የመከራ ማክተምና የተስፋን መባቻ የሚያበሥር ታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር የያዘ ነው። ክረምት በራሱ የራሱ የሆነ ጥልቅ ምሳሌያዊ ትርጉም አለው። ይህንን መነሻ በማድረግ የክረምትን ምሳሌነትና በሕይወታችን ላይ ያለውን አንድምታ እንደሚከተለው እንመለከተዋለን።
፲. የክረምት ምሳሌነት በክርስቲያናዊ እይታ
፩.፩. ዘመነ ብሉይ (የሕግና የትንቢት ዘመን)
ክረምት የዘመነ ብሉይ ምሳሌ ነው። ዘመነ ብሉይ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ተለይቶ፣ በኀጢአት ጨለማ ውስጥ የወደቀበትና መጻኢውን መሢሕ (ክርስቶስን) በጉጉት ይጠባበቅ የነበረበት ወቅት ነው። ልክ የክረምት ምድር በደመና ተጋርዳ የፀሐይን ብርሃን እንደምትናፍቅ፣ በብሉይ ኪዳንም የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የድኅነት ብርሃን ይናፍቅ ነበር። “ክረምት አለፈ” ሲል ይህ የጨለማና የተስፋ መቁረጥ ዘመን አብቅቶ፣ አማናዊው ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠበት ዘመነ ወንጌል (ዘመነ ሐዲስ) መተካቱን ያበሥራል።(ትርጓሜ መኃልየ መኃልይ ፪፥፲፪)
የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምዕራፍ ፪፥፲፩–፲፫ አንድምታ ትርጓሜ “እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናቡም አልፎ ሄደ። አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፤ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ። በለሱ ጐመራ፤ የወይኖችም አበቦች መዓዛቸውን ሰጡ። ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነዪ።“ (መኃ.፪፥፲፩–፲፫)
ብሎ የተናገረውን በሚከተሉት ዐበይት መንፈሳዊ ምሥጢራት (ምሥጢረ ሥጋዌ እና ምሥጢረ ቤተ ክርስቲያን) ማየት ጥሩ ነው።
፩. ምሥጢረ ሥጋዌ (ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን)
ይህ ትርጓሜ የሰው ልጅ ከኀጢአትና ከዲያብሎስ ቁራኝነት ወጥቶ ያገኘውን የነፃነት ዘመን ያመለክታል፦
- “ክረምት አለፈ፤ ዝናቡም አልፎ ሄደ“ ፦ ክረምት የተባለው የጨለማ፣ የጣዖት አምልኮ፣ የዲያብሎስ አገዛዝ እና የኀጢአት ዘመን ነው። ዝናብ የተባለው ደግሞ በሰው ልጅ በደል ምክንያት የመጣው መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ (የገሃነም ፍርድ) ነው። ይህ ሁሉ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ተወግዷል። ከልደት እስከ ስቅለት (ሞት) በተፈጸመው የድኅነት ሥራ መከራው አብቅቷል። “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው” እንዲል(ኢሳ. ፱፥፪)
- “አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ“ ፦ አበቦች የተባሉት ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ናቸው። በክርስቶስ በዓለም ላይ መልካም ፍሬን ያፈሩ ቅዱሳን መገለጣቸውን ያሳያል። “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴ. ፭፥፲፮)
- “የዜማም ጊዜ ደረሰ“ ፦ የኃዘንና የልቅሶ ዘመን አብቅቶ፣ የወንጌል ብሥራት እና የምስጋና ጊዜ መድረሱን ያበሥራል። “ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ ይሉ ነበር።” (ሉቃ. ፪፥፲፫–፲፬)
- “የቁርዬው (የርግብ) ቃል ተሰማ“ ፦ የመንፈስ ቅዱስ ረድኤትና የክርስቶስ የወንጌል ድምፅ በምድር ሁሉ መሰማቱን ያመለክታል። ይህም ደግሞ የመንገድ ጠራጊው የቅዱስ ዮሐንስ የበረሃ ስብከት ድምፅ የሐዋርያት የወንጌል ስብከት መምጣቱን ያመለክታል።
- “በለሱ ጐመራ፥ የወይኖችም አበቦች መዓዛቸውን ሰጡ“ ፦ በለስ የተባለችው ቀድሞ ፍሬ አልባ የነበረችው የሰው ልጅ ሕይወት ስትሆን፣ አሁን ግን በደምና በጸጋ (በክርስቶስ የማዳን ሥራ) መጐምራቷን (መለወጧን) ያሳያል። የወይን አበቦች ምእመናን በሃይማኖት አብበው የመልካም ምግባር መዓዛ ማውጣታቸውን ያስረዳል።
፪. ምሥጢረ ቤተ ክርስቲያን እና የድንግል ማርያም ምሳሌ
ከዚህ ኀይለ ቃል የሚቀጥለውን ክፍል ብንመለከተው የቅድስት ድንግል ማርያምና የቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ ምሳሌ ሆኖ ይተረጎማል፦
- ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነዪ“ ፦ ሙሽራው ክርስቶስ ሙሽሪትን (ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን) ከብሉይ ኪዳን መከራና ከሞት ጥላ ወጥታ ወደ አዲሱ የጸጋ ዘመን እንድትገባ ጥሪ ማቅረቡ ነው። ወይም ድንግል ማርያምን ሲሆን ደግሞ ከስደት ወደ ገሊላ ነይ ተመለሽ የሚል ምሥጢርን ይይዛል።
- የሰው ልጅ ተፈጥሮ (በቤተ ክርስቲያን የተመሰለው) ከኀጢአት ክረምት ወጥቶ በክርስቶስ ትንሣኤ ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ብርሃን የሚታይባት ዘመነ መጸው መሻገሯን ያረጋግጣል።
፫. ታሪካዊ አንድምታ (የእስራኤል ከባቢሎን ምርኮ መመለስ)
ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የእስራኤልን ሕዝብ ከባቢሎን ምርኮ ነፃ መውጣትና ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ በምሳሌነት ስንመለከተው፦
- “ክረምት አለፈ“፦ በባቢሎን የነበረው የ፸ ዓመት የስደት፣ የባርነትና የመከራ ዘመን ማክተሙን ያመለክታል።
- “ዝናቡም አልፎ ሄደ“፦ በምርኮ ሳሉ ያገኙአቸው የነበሩት መቅሠፍቶች፣ የጠላቶቻቸው ዛቻና ለቅሶ መቆሙን ያሳያል።
- “አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ“፦ ከስደት የተመለሱት እነ ዘሩባቤል፣ ዕዝራና ነህምያ የኢየሩሳሌምን መሠረት ለመጣልና ቤተ መቅደሱን ለመሥራት መነሣታቸውን ያመለክታል።
- “የዜማም ጊዜ ደረሰ“፦ እስራኤላውያን በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ሰቅለውት የነበረውን መሰንቆአቸውን አውርደው፣ እግዚአብሔርን በደስታ የሚያመሰግኑበት ጊዜ መቃረቡን ያሳያል። (ዕዝ. ፩፥፩-፲፩) የቂሮስ አዋጅና የሕዝቡ መነሣት (ነህ. ፪፥፩-፰) የኢየሩሳሌም ቅጥር ለመሥራት መፈቀዱ (መዝ. ፻፴፯፥፩–፬) “በባቢሎን ወንዞች አጠገብ…” የሚለው የልቅሶ ዘመን ማክተምን የሚያመላክት ነው።
፬. ሥነ–ፍጥረትና የሰው ልጅ ተፈጥሮ (የነፍስና የሥጋ አንድነት)
የሰው ልጅ ዕድሜ መንፈሳዊ ጉዞ ከዓመታት መለዋወጥ ጋር ያነጻጽሩታል፦
- “ክረምት አለፈ“ ፦ አንድ ሰው በካህናት ፊት ንስሓ ገብቶ ከኀጢአትና ከክፉ ምግባር ጨለማ ሲወጣ ክረምት የተሰኘው የነፍሱ እድፍ ይወገዳል።
- “አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ“ ፦ ከንስሓ በኋላ በሰው ሕይወት ላይ የሚታዩት መልካም ምግባራት (ፍቅር፣ ሰላም፣ ትዕግሥት) እንደ አበቦች ናቸው።
- “በለሱ ጐመራ“፦ በንስሓ የታደሰች ነፍስ ለበጎ ፍሬ መዘጋጀቷንና የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በውስጧ መሥራት መጀመሩን ያሳያል።
፩.፪. የመከራ ወቅት
ክረምት በብርድና በውሽንፍር፣ በጭጋግና በድቅድቅ ደመና የተከበበ በመሆኑ የመከራና የፈተና ምሳሌ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ሲያስተምር “ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ” (ማቴ. ፳፬፥፳) ብሏል። ይህ ቃል በክረምት ወቅት ጉዞ እጅግ ከባድ፣ መንገዱም ጭቃና ውሃ የሚበዛበት እንደሆነ ሁሉ፣ የሰው ልጅ በመከራና በፈተና ወቅት እምነቱ እንዳይናወጥና ከመንፈሳዊ ሕይወቱ እንዳይሰደድ የተሰጠ ማሳሰቢያ ነው። መከራ ከመምጣቱ በፊት እምነትን በጽኑ መሠረት ላይ መገንባት ያስፈልጋል።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ “ክረምት የተባለው ነፍስ በኃጢአት ማዕበል የምትናወጥበት፣ የጸሎትና የጽድቅ ፍሬ አልባ ሆና የምትገኝበት ወቅት ነው። ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ማለቱ ሞትና ፍርድ ሳይቀድማችሁ በንስሓ ተዘጋጁ ማለት ነው፤ ምክንያቱም በዘመነ ክረምት ፍሬ ማፍራት እንደማይቻል ሁሉ፣ በዕለተ ሞትም ንስሓ መግባት አይቻልም” በማለት ተርጉሞልናል።
“ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።” እንዲል (ማቴ. ፳፬፥፳፣ ሉቃ. ፮፥፵፰) ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ቃሉን ሰምተን ቤታችንን/ጽኑ እምነታችንን/በዓለት ላይ ልንመሠርት ይገባናል። ይህም ዓለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።” (፩ኛ ቆሮ. ፲፥፬).
፩.፫. አዲስ ብርሃንና አዲስ ተስፋ
ምንም እንኳ ክረምቱ በደመና እና በጭጋግ የተከበበ፣ በኃጢአትና በመከራ የተመሰለ ቢሆንም፣ ፍጻሜው ግን ሁልጊዜም ወደ አዲስ ብርሃን ያመራል። ጭጋጉ ሲገፈፍና ደመናው ሲጠፋ አዲስ ተስፋ ይፈነጥቃል። በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን የፈተና ጭጋጎች ዘላለማዊ አይደሉም። ከእያንዳንዱ የክረምት (መከራ) ጀርባ የእግዚአብሔር አዲስ የቸርነት ብርሃንና የተስፋ ፀሐይ መውጣቷ አይቀሬ ነው። “መከራን የሚታገሥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ተፈትኖ እግዚአብሔር ለሚወዱት ተስፋ ያደረገላቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ. ፩፥፲፪) ጌታችንም በፈተና የጸኑትን በመንግሥቱ ላይ ይፈርዱ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል። “ነገር ግን ስለ እኔ የታገሣችሁ እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ናችሁ፤ አባቴ ለእኔ እንደ ሰጠኝ እኔም ለእናንተ መንግሥትን አዘጋጅላችኋለሁ፤ በመንግሥቴ በማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ በወንበሮችም ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዱ ዘንድ ።” (ሉቃ. ፳፪፥፳፰-፴)
በሕይወታችን ውስጥ አንዳንድ ጊዜ የኃጢአት፣ የጭንቀት፣ የበሽታና የኀዘን ጭጋግ ይከበናል። ተስፋ የቆረጥንና ብርሃን የራቀን ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን መዝሙረኛው ዳዊት እንዲህ ይላል፦ “መቅሠፍቱ ከቍጣው ነውና፤ መዳንም ከፈቃዱ ነውና፤ ማታ ልቅሶ ይሰማል፤ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል።” (መዝ. ፳፱፥፭)
- ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ መኃልይን ሲተረጕም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የክረምቱ ማዕበል ሲያልፍ፣ ነፍስ ከክፉ መንፈሳዊ ውርጭ ትነቃለች። የፍርሃትና የጥርጣሬ ጭጋግ ተገፎ፣ የክርስቶስ የፍቅር ብርሃን በልባችን ውስጥ ይበራል። ያኔ ነፍሳችን አዲስ የተስፋ ሕይወትን ትለብሳለች።“
እግዚአብሔር አምላክ መከራችንን በጊዜው ወደ ደስታ የመለወጥ ሥልጣን አለው። ነቢዩ ኤርምያስ በመጽሐፈ ሰቆቃው ላይ እንደገለጸው፦ “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው።” (ሰቆ. ፫፥፳፪–፳፫)
በመሆኑም አሁን ያለንበት የሕይወት ፈተና ምንም ያህል ጨለማ ቢሆንም፣ “እነሆ ክረምት አለፈ” የሚለው መለኮታዊ ቃል ዛሬም በሕይወታችን ላይ እንደሚፈጸም ማመን አለብን። ጭጋጉ ያልፋል፣ ብርሃኑም ይወጣል።
በግቢ የሚያስጨንቃችሁ እንደጉም የከበባችሁ መከራ እንዲሁም ልዩ ልዩ ፈተናዎች አልፈው ወደብርሃን የምትወጡበት ጊዜ ይመጣልና፣ የማያልፍ እስከሕይወታችሁ መጨረሻ የሚኖር እንዳልሆነ መረዳት ይኖርባችኋል።
ክረምት በነፋሱ በጎርፉ ሁሉን ጠራርጎ ሲወስድ የማያልፍ መስሎ ተስፋ ያስቆርጣል፤ በግቢ ትምህርቱ በምትጠብቁት ልክ ሳይሄድላችሁ፣ ከመናፍቃንና ከአሕዛብ በኩል የተለያዩ ጫናዎች ሲደርስባችሁ፣ የሥጋ ፈቃድ(የዓይን ዓምሮት የሥጋ ፍትወት) ሲንጣችሁ፣ የሳይንሱ የፍልስፍናው እንዲሁም የተለያየ ርእዮተ ዓለም ሲያውካችሁ የሚያልፍ አይመስላችሁም፤ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ያልፋሉ፤ ሲያልፉ ግን በበረከት እንዲያልፉ በሁሉ በኩል ተግታችሁ ሥራችሁን ሠርታችሁ በመንፈሳዊ በርትታችሁ ስትገኙ ነው።
፩.፬. የመከራ ዘር ማበብና ማፍራት
በክረምት ወቅት ዘሪው በብርድና በዝናብ ውስጥ ሆኖ ዘሩን በምድር ውስጥ ይዘራል። ያ በመከራና በልቅሶ የተዘራ ዘር ግን በምድር ውስጥ በስብሶ አይቀርም፤ ይበቅላል፣ ያብባል፣ በመጨረሻም ፍሬ ያፈራል። የእኛም መንፈሳዊ ሕይወት እንዲሁ ነው። በመከራና በፈተና ውስጥ ሆነን በዕንባና በትዕግሥት የምንዘራው የጽድቅና የእምነት ዘር፣ ጊዜው ሲደርስ ለክብርና ለደስታ ፍሬ ይበቃል። መከራ የሕይወታችን ማጠቃለያ ሳይሆን፣ ወደ ላቀ መንፈሳዊ ፍሬያማነት የምንሻገርበት ድልድይ ነው።
ክረምት ዘሪው በብርድና በዝናብ ውስጥ ሆኖ ዘሩን በምድር ውስጥ የሚጥልበት ወቅት ነው። ይህ ተግባር ከፍተኛ ትዕግሥትና መሥዋዕትነትን ይጠይቃል። ዘሩ በምድር ውስጥ ጠፍቶ የሚቀር አይደለም፤ ነገር ግን በስብሶና ታሽቶ አዲስ ሕይወት ይዞ ይበቅላል።
መጽሐፍ ቅዱስ የመከራንና የፍሬን ግንኙነት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፦ “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ። በሄዱ ጊዜ፥ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ።” (መዝ. ፻፳፭፥፭-፮)
ጌታችን ራሱ ለእኛ ሕይወትን ለመስጠት እንዴት መከራን እንደተቀበለና እንደሞተ ሲያስረዳ የዘርን ምሥጢር ተጠቅሟል፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።” (ዮሐ. ፲፪፥፳፬)
ማጠቃለያ “እነሆ ክረምት አለፈ” የሚለው ቃል ዛሬም ለሁላችንም ትልቅ የምሥራች ነው። በሕይወታችሁ ውስጥ ያለው የኃጢአት ጭጋግ፣ የበሽታ ሥቃይ፣ የልብ ስብራትና የጭንቀት ክረምት ምንም ያህል ቢበረታም፣ ፈጽሞ እንደማይቀጥልና እንደሚያልፍ ልታምኑ ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ ከእያንዳንዱ የክረምት ውሽንፍር በኋላ የጸደይን አበባና አዲስ ተስፋ ያዘጋጃል።
ፈተናዎቻችንን በትዕግሥት አልፈን፣ በመከራ የተዘራው እምነታችን አብቦና አፍርቶ ለአዲሱ የሕይወት ብርሃን እንድንበቃ የእግዚአብሔር ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!