“በአንዳች ነገር አትጨነቁ” (ፊልጵ. ፬፥፮)
ከዲ/ን ኃይለጊዮርጊስ ግርማሞገስ
ውድ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች እንደምን አላችሁ? የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን! የድኅነታችን መጀመሪያ የሆነች እመ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ምስጋና ይድረሳት።
- የጭንቀት ምንነትና ምንጮች
ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ላሉ ሰዎች በላከው መልእክት ላይ “በአንዳች ነገር አትጨነቁ” ይላል። በዘመናችን ግን ‘መጨነቅ’ የሚለው ቃል ‘ማሰብ’ ከሚለው ቃል ጋር በማመሳሰል ሰው እንዴት ስለ ሕይወቱ ሳይጨነቅ/ሳያስብ ሊኖር ይችላል? ማለት የተለመደ ሆኗል፤ ነገር ግን መጽሐፍ አትጨነቁ እንጂ አታስቡ አይልም።
“የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” (ዘፀ. ፳፥፰) ፤ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” (መክብብ ፲፪፥፩) ፤ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ” (፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፭)፤ “እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሓም ግባ” (ራእይ ፪፥፭) የሚሉትና የመሳሰሉት የሰው ልጅ ከምታስብ ነፍስ የተፈጠረና ማሰብም የሚገባው እንደሆነ ማስረጃ ናቸው። እንደ ሰውነቱ ማሰብ ከሚገባው ልክ ሲወርድም ቅዱስ ዳዊት “ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም ልብ እንደ ሌላቸው እንደ እንስሳትም መሰለ” (መዝ. ፵፰፥፲፪) ይለናል። ስለዚህ ማሰብ አምላክን፣ ራስን፣ አካባቢን ማስተዋልና ለተፈጠርኩበት ዓላማ እንዴት ብዬ ልኖር ይገባኛል ብሎ የማጤን ሂደት ነው።
መጨነቅ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ጌታችንም በወንጌል “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማነው?” (ማቴ. ፮፥፯) እንዳለ መለወጥና መቀየር በማንችላቸው ነገሮች ላይ ሥልጣን እንዳለው ሰው መሆን፤ ውጤት በሌለው ነገርም አእምሮን መወጠር ነው። ይህ ጭንቀት በዋናነት ከሁለት ነገሮች ይመነጫል።
1.1. የእግዚአብሔርን ሥራ ዘንግተን ሁሉን ነገር በራሳችን ለመፈጸም ስንታገል፣
የፈጠረን ሁሉን ያከናወነልን እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከእኛ ጋር እንደሆነ መዘንጋት እንዲሁም ሁሉን በራሳችን አቅም፣ ችሎታ እና ዕውቀት ለመፈጸም መታገል ጭንቀትን ያመጣል። ጌታችን በወንጌል እንዲህ ይለናል፡- “በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተ እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፤ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለእኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና። በእኔ የማይኖር ቢኖር እንደ ደረቅ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጥሉታል፤ ሰብስበውም በእሳት ያቃጥሉታል።” (ዮሐ. ፲፭፥፬-፮)
የወይን ግንድ ከሆነው ከክርስቶስ ተለይተው ፍሬ ለማፍራት የደከሙ ብዙዎች ናቸው፤ በግብጻውያን በግፍ ተይዘው የነበሩት እስራኤላውያን በ፵ ቀን ብቻ ተጉዘው ሊወርሷት የነበረችውን ምድረ ርስት በመንገድ ሲባዝኑ ፵ ዓመታት ሙሉ የዞሩት ከዚያ የግፍ አገዛዝ ነጻ ያወጣቸውን እግዚአብሔርን ትተው በእርሱ ላይ ያንጎራጎሩ፤ እርሱንም ትተው የወርቅና የብር አማልክትን ለራሳቸው ሲያደርጉ ሰለነበር ነው።
እግዚአብሔር ሁሉን የሚሠራበት ጊዜ አለው፤ እኛም በእርሱ ታምነን ሕይወታችንን መምራት ይገባናል። ስለዚህም “ሁሉን በራሴ ማድረግ እችላለሁ፤ ከወይኑ ግንድ ተለይቼም እንኳ ቢሆን የወይንን ፍሬ ማፍራት ይቻለኛል” ብሎ መታገል ወደ ጭንቀት ያመራናል፤ ከግንዱ የተለየ ቅርንጫፍ ምንም አያደርግምና ያለጌታችን ምንም ልናደርግ አንችልም።
በነነዌ ወደሚገኙ ምእመናን ዘንድ እንዲያስተምር የተላከውን የዮናስን ሕይወት ስናስታውስም የነነዌን ሰዎች ቃለ እግዚአብሔርን አስተምሮ በንስሓ እንዲመልስ እግዚአብሔር ቢልከውም የአምላኩን ትእዛዝ መፈጸምን ገሸሽ ብሎ ወደ ተርሴስ በመርከብ ሊሸሽ ቢሞክር የደረሰበት ወደ ባሕር መጣል ሲሆን፣ በባሕሩ መካከልም በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት መዓልትና ሌሊት የመቆየት ጭንቅ ገጥሞታል። (ዮናስ ፩) ስለሆነም ለእግዚአብሔር ተልእኮን ወደ ኋላ በማለት ለሕይወታችን የሚተርፋት ጭንቀት ብቻ ይሆናል።
የመጀመሪያ የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ንጉሥ ሳኦል በተመሳሳይ መልኩ ሊያቀርበው የማይገባው፣ ከካህናት በስተቀር ማንም የማያቀርበው እንዲሁም እንዳያቀርብ አስቀድሞ የተነገረውን ትእዛዝ ዘንግቶ ሳሙኤል እስከሚመጣ ቸኩሎ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሲያቀርብ ከንግሥናው ተሻረ፤ ለጭንቀትም ተላልፎ ተሰጠ። (፩ኛ ሳሙ. ፲፫፥፰-፲፬)
1.2. የሥጋ ፈቃዳችንን ከፈቃደ ነፍሳችን ስናስበልጥ፣
በፈቃደ ነፍሳችን የሥጋችንን ፈቃድ ማሸነፍ ሲያቅተን ሕይወታችን በጭንቀት ይሞላል። የሥጋ ፈቃድዋ ብዙ ነውና። በዚህ ምክንያት አምላካችንን ያሳዘኑ ከትውልድ ብዙዎች ቢሆኑም በዚህ ጽሑፍ የምናያቸው ኤሳውና የጲጢፋራ ሚስት ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሚነግረን ያዕቆብና ኤሳው ለብኵርና ከእናታቸው ማሕፀን ጀምሮ ሲታገሉ ቆይተው ኤሳው በኵር ሆኖ ተወለደ። ነገር ግን በእስራኤላውያን ዘንድ ትልቅ ክብርና ዋጋ የሚያስገኝ ብኵርና አደን ሳይቀናው ቀርቶ ረኀብ ሲጸናበት የጊዜያዊው የሥጋ ፈቀዱን ለመፈጸም የተሰጠውን ብኵርና በማቃለል በምስር ወጥ ሸጠው። ይህንን ሲፈጽም የአባቱን ቡራኬ አጣ፤ ይህም ለጭንቀት አሳልፎ ሰጠውና ወንድሙ ያዕቆብን ለመግደል ተነሣ። (ዘፍ. ፳፭፥፳፪-ፍጻሜ)
የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በግብጽ በግዞት ቤት በነበረበት ወቅት የቤቱ ባለቤት የሆነው የጲጥፋራ ሚስት የዮሴፍን ውበት ወድዳ አብሯት ይተኛ ዘንድ ዘወትር ትወተውተው ነበር፤ ላልተገባ የዝሙት ተግባር ስትጋብዘው ጥያቄዋን ዮሴፍ ውድቅ ሲያደርገው ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ በመግባት አሳሰረችው። (ዘፍ. ፴፱) ኀጢአት በንስሓ ካላስወገዱት ጭንቀትን ይወልዳል፤ ጭንቀት ደግሞ መልሶ በኀጢአት ረመጥ ውስጥ እንድንዘፈቅ ያደርገናል።
- ከግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የሚጠበቁ ተግባራት፣
ስለ ጭንቀት ምንነትና መነሻ ይህን ያህል ካልን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመማር የተገኙ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ራሳቸውን ከዚህ ጭንቀት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይገባል? ወደ ሚለው እንምጣ።
- ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት፣
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የምናሳልፈው ጊዜ ሰውነታችን ዐይናችን ያየውን ሁሉ ልያዝ ልጨብጥ የሚልበት በነፋስ እና በእሳት በሚመሰልበት ዕድሜ ውስጥ ነውና የሥጋ ፈቃድ እጅጉን ያይላል።
ይህ የሥጋ ፈቃድ ልጓም(መያዣ) ካልተዘጋጀለት ሕይወትን ሁሉ የማበላሸት አቅም ያለው ጊዜ ነውና ጥንቃቄ ይፈልጋል። ስለሆነም ይህን ወደ ኀጢአት የሚመራ የሥጋ ፈቃድ ነፍሳችንን ወደ እግዚአብሔር በምትመራ በነፍስ ፈቃድ ቁጥጥር ሥር ማድረግ የሚገባ ነው። የሥጋ ፈቃድ ያላሸነፈውና የነፍሱን ፈቃድ የተከተለው ቅዱስ ዮሴፍ “በእግዚአብሐር ዘንድ እንዴት ኀጢአትን እሠራለሁ” በማለት ከጲጥፋራ ሚስት ፊት ሸሽቶ ሩጦ እንደወጣ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ለታመነው ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ላስገዛው ዮሴፍ ሞገስ እንደሆነውና በግብጽ ሁሉ ላይ አዛዥ እንዳደረገው እንመለከታለን። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል፡-
“ተአምራትን ማድረግ ትፈልጋላችሁን? እንኪያስ በዘፈን የደነቆረን ጆሮ መዝሙር እንዲሰማ አድርጉት፡፡ ሴትን በመመኘት የታወረው ዐይን ፈጣሪውን እንዲያይ አድርጉት፡፡ በስርቆት የሰለለ እጅ በምጽዋት እንዲዘረጋ አድርጉት፡፡ ወደ ኀጢአት ቤት በመሄድ ሽባ የሆነውን እግር ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲሮጥ አድርጉት፡፡ ሐሜትን በማውራት ዲዳ የሆነውን ከንፈር መልካም ንግግርን እንዲናገር አድርጉት፡፡ ከተአምራት ሁሉ የበለጠ ተአምር ይህ ነው፡፡”
- ሥራን በአግባቡ መሥራት፣
ሌላኛው ጭንቀትን የምናስወግድበት መንገድ ከእኛ የሚጠበቀውን ሥራ በአግባቡ በመሥራት ነው። ራስን በሥራ መጥመድ እና የሚሠራውን ሥራ በአግባብ መሥራት ነው። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “ሥራህን ሥራ” የሚል ለዘመናት በልባችን ጽላት ታትሞ የሚኖር ምክር ለግሰውናል። እግዚአብሔር በሰጠው አካል፣ አእምሮና ኅሊና ከእርሱ የሚጠበቀውንና የሚችለውን ተግባር የሚሠራ ሰው አእምሮው በሥራ የተጠመደ ነውና አንዳችም የሚጨነቅበት ምክንያትና ጊዜ የለውም።
የምንሠራው ሥራም በአግባቡ ሊሆን ይገባል፤ ሌሎችን የሚያሳዝን፣ ፍቅር የሌለበት ሥራ ከሆነ ለጊዜው የሚያስደስት ቢመስል እንኳ በኋላ የማይወጡት ጭንቀት ውስጥ ያስገባልና “ሁሉ በሥርዓትና በአግባብ ይሁን” (፩ቆሮ. ፲፬፥፵) እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ሥራችን ሁሉ በሥርዓትና በአግባብ ልንከውን ይገባናል።
- መጸለይ (ልመናችሁን አስታውቁ) (ፊልጵስዩስ ፬፥፮)
ቅዱስ ጳውሎስ አትጨነቁ ብቻ ብሎ አልተወንም፤ የሚያሳስባችሁን ነገር ሁሉንም በጊዜው በሚፈጽም በአምላካችሁ ፊት አቅርቡ ሲል፤ “ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።”ፊልጵስዩስ፬፥፮)ብሎናል። እንደ ግቢ ጉባኤ ተማሪ በግቢ ሕይወት ውስጥ ብዙ ለጭንቀት የሚጋብዙ ነገሮች አሉ፤ እነዚህን ልናልፋቸው የሚገቡት ግን እግዚአብሔር ሁሉን በጊዜው እንደሚያስተካክልልን በሙሉ እምነት እርሱን በጸሎት በመለመን ነው።
ነቢዩ ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅን ስናስታውስ በባዕድ ሀገር በባቢሎን በነበሩበት ዘመን የአሕዛብን ምግብ እንዲመገቡ ሲሰጣቸው አይሆንም እያሉ ጥራጥሬ እየተመገቡ ሥጋ ከሚበሉት ይበልጥ አምረው ተገኝተዋል፤ ንጉሡ ላቆመው ሐውልት እንዲሰግዱ ሲገደዱ “አንሰግድም” ሲሉ ይደርስባቸው ከነበረው ጭንቀትና መከራ ሁሉ ይድኑ የነበረው ሁሌም እግዚአብሔርን ስላልረሱ ፤ ልመናቸውንና ምስጋናቸውን ወደ አምላካቸው ዘወትር ያቀርቡ ስለነበር ነው።
ስለሆነም ምንም ያህል የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆን እግዚአብሔርን አብሮን እንዲሆን ከጭንቀቱም ውስጥ እንዲያስወጣን መለመን ይገባል እንጂ ነገርን እያብሰለሰሉ መጨነቅ ተገቢ አይደለም።
- የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም፣
“የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሠኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።”(ሮሜ ፲፪፥፪) እንደተባለ ማመዛዘን በሚችል ልቡናችን እንዲሁም በእግዚአብሐር ፈቃድ የተጻፉ መጽሐፍትን እያነበብን ቃሉንም እየሰማን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ቅዱስ ፈቃዱንም ልናውቅ ይገባናል።
መጻሕፍት ገና ሳይጻፉ በሕገ ልቡና ስለ አምላኩ ተረድቶ የተከተለ አባታችን አብርሃምን ስንመለከት እኛም ልቡናችንን መርምረንን “ይህ ነገር እግዚአብሔርን ደስ አያሰኘውም” ብለን ልንተዋቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ እንረዳለን።
የፈረሰውን የእግዚአብሐርን ቤተ መቅደስ አጥር ቅጥር ያነጸውና “ከመጀመሪያውም ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ ያነብ ነበር።” (ነህ. ፰፥፲፰) የተባለለት ነህምያን ስናስብ ደግሞ የትኛውም ሁኔታ ላይ ብንሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን መመልከት በእነርሱም ውስጥ እርሱ ባወቀ ያጻፋቸውን ፈቃዳቱን እና ትእዛዛቱን መመርመር ማወቅ እነርሱንም መፈጸም እንደሚገባ እንገነዘባለን።
ስለሆነም የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ዙሪያቸውና አካባቢያቸው በፍጥነት በሚለዋወጥ ዘመን ውስጥ የሚገኙ ናቸውና ቅዱስ ጳውሎስ “ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፣ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፤ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።” (ኤፌ. ፭፥፲) እንዳለ ዘመኑን እየዋጁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር ተገቢ ነው።
- የምንማረው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጭምር መሆኑን ማስተዋል፣
ቅዱስ ዳዊት በሕፃንነት ዘመኑ በአባቱ ቤት በጎች እየጠበቀ በነበረበት ዘመን በጎቹን ሊበላ የመጣን አንበሳ ታግሎ ያሸንፍ የነበረበትን ኃይል እግዚአብሔር ይሰጠው የነበረው፣ በእስራኤላውያን ላይ ይዘባበት የነበረውን ፍልስጥኤማዊውን ጎልያድን ማሸነፍ ይችል ዘንድ እያለማመደው ነው። “ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም።”(፩ኛ ሳሙኤል ፲፯፥፶) እንደተባለ፣ እኛም አሁን የምንማረው ትምህርት እንዲሁ “ተምረው ተመረቁ” ለመባል ብቻ አይደለም፤ “ቅጥርን የሚጠግንን ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፤ ነገር ግን አላገኘሁም።”(ሕዝ. ፳፪፥፴) እንዳለ አምላካችን በነቢዩ ቃል፤ ለቤተ ክርስቲያን በጎደለባት በኩል ለመሙላት እንደ ምንማር ሁሌም ቢሆን ማስታወስና ማስተዋል ይገባናል።
- ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ደግሞ በእኛ አቅም መተግበር የማንችላቸው ጉዳዮችን ነው።
ከእኛ አቅም በላይ የሆኑና በእኛ ችሎታ ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባናል፤ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ከሚገጥሟቸው ከእነርሱም አቅም በላይ የሆኑ ነገሮች ውስጥ ሁለቱን እንመለከታለን።
- የማንፈልገው ዩኒቨርሲቲ ብንመደብ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን መረዳት፣
አስቀድመን ታሪኩን ለምሳሌ ያነሣነውን የነቢዩ ዮናስን ታሪክ ስንመለከት፣ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት የተሰጠውን ወደ ነነዌ የመሄድ ትእዛዝ በመሸሽ ኮብልሎ ነበር፤ ዕቅዱ ግን አልተሳካም፤ ታላቅ ማዕበል በሚሄድባት መርከብ ላይ ተነሥቶ፣ ወደ ባሕር ውስጥም ተጥሎ በዓሣ ሆድ ውስጥ መቀመጥ ግድ ሆኖበታል።
ዮናስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተቀብሎ የተመደበበት ቦታ ቢሄድ ይህ ነገር አይደርስበትም፤ አገልግሎቱንም ይፈጽም ነበር፤ እኛም በሕይወታችን በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆኑ ከእኛ አሳብ እና ዕቅድ መሉ ለሙሉ የማይገናኙ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ወዳልጠበቅነውና ወዳላሰብነው ዩኒቨርሲቲ መመደብንም ለመልካም ነው ብለን መቀበል ተገቢ ነው። እኛ መልካም ነው ብለን ያሰብነው ቦታ የምንጎዳበት ሁኖ እግዚአብሔር ጠብቆንም ይሆናል፤ በዚህኛው በተመደብንበትም የተሻለ የምንማርበት እርሱንም አገልግለን የምንከብርበት ስለሆነም ይሆናልና፤ ይህን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብሎ መቀበል ይገባል።
- ያልመረጥነው የትምህርት ዘርፍ ውስጥ ቢመድቡን የእግዚአብሔር ጥሪ መሆኑን መገንዘብ፣
ሌላው ለግቢ ተማሪ ፈታኙ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ሊማር ካሰበው የትምህርት ዘርፍ የተለየ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ መግባት ነው፤ እግዚአብሔር ሰውን በተለያየ መንገድ ይጠራል፤ ወደ ተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲገባም በማድረግ ሰውን ወደ እርሱ ይስባል። ከእነዚህም አንዱ ወዳላሰብነው የትምህርት ዘርፍ መግባት ነው። እረኞች የነበሩትን ሳኦልና ዳዊትን ወደ ንግሥና፤ ቀራጭና ዓሣ አጥማጅ የነበሩትን ስምዖን፣ ጴጥሮስ ብሎ ወደ ሐዋርያነት፤ ለዳንኤልና ዮሴፍ በባዕድ ሀገር ከባርነት ወደ ባለሥልጣንነት፤ ሌሎችንም ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ ይህ ይሆናል ብለው ወዳላሰቡት ከፍታ የጠራቸው የጠበቃቸው እግዚአብሔር በሁላችንም ላይ ልዩ ክቡር የሆነ ዓላማ አለውና፤ ጌታ ሆይ ይህን ጥሪ ለሕይወት አድርግልኝ ብለን ተቀብለን መማር፣ በተማርነውም ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን ማገልገል ከሁሉም የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የሚጠበቅ ኀላፊነት ነው።
አሁንም ወንድሞቻንና እኅቶቻችን የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ያልተገባ መንገድን ትታችሁ የቅንነቱን፤ የኀጢአቱን ትታችሁ የንጽሕናውን፤ የሐሰቱን ትታችሁ የእውነቱን፤ የክፉውን ትታችሁ የበጎውን ፤ የጠቡን ትታችሁ የፍቅሩን፤ የመራገሙን ትታችሁ የመመራረቁን ልቡና የማባከኑን ትታችሁ የመሰብሰቡን፤ የማይገባውን ትታችሁ የሚገባውን፤ የማይመሰገነውን ትታችሁ የሚመሰገነው እርሱን ያዙ። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለን ጌታችን ቅርባችን ሁሌም ከጎናችን ነው፤ የሚያስጨንቃችሁን ነገርም ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!!!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!