“ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ” (ማቴ. ፪፥፲፫)
ከዲ/ን ሚኪያስ ዉባለ
ስለ ስደተ ክርስቶስ ስናስብ ቀድመን የምናስባት አንድ ሀገር አለች እሷም ግብጽ ናት። ግብጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱና ልዩ ቦታ ካላቸው ጥንታውያን ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በብሉይ ኪዳን ስለ ግብጻውያን ስናነብ በክፉ ጊዜ እንደመሸሸጊያና መጠለያ ሆና አገልግላለች ለምሳሌ ያክል አብርሃም በምድረ ከነዓን የረኃብ ዘመን በመጣ ጊዜ ከረኃብ ለማምለጥ ወደ ግብጽ ወርዶ ነበር፣ እግዚአብሔር አምላክ ዮሴፍን ምክንያት አድርጎ ያዕቆብንና ቤተሰቦቹን ከጽኑ ረኃብ እንዲተርፉም አድርጓል።(ዘፍ. ፲፪፥፲ ፤ ዘፍ. ፵፭፤፭)
በሐዲስ ኪዳንም በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቃል ለዮሴፍ ተነሥተህ እናቱንና ብላቴናውን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ ተብሎ የተነገረው ወደዚች ሀገር ነው። (ማቴ. ፪፣፲፪-፲፫) በስደታቸው ሰዓትም አንዳንድ ክፉ ሰዎች ቢገጥሟቸውም ፍቅራቸውን ሲገልጹ የነበሩ በክርስቶስ ያመኑ ብዙዎችም ነበሩ። ሁለቱ ወንበዴዎች በበረሃ አግኝተዋቸው አይሁዳዊ ዳክርስ ልብሳቸውን ለመግፈፍ ንብረታቸውን ለመዝረፍ ሲፋጠን ግብጽዊው ጥጦስ ግን በልቡናው ርኅራኄ አድሮበት ለፍቅሩ በመሳሳት “እነዚህ ሰዎች የቤተ መንግሥት ሰዎች ናቸው አሳዘኑኝ ወደዚህ ቦታ የመጡት ያለ ምክንያት አይሆንምና አንቀማቸው እንተውላቸው” በማለት ለጌታ ያለውን ፍቅርና ርኅራኄ ገልጧል።
አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ግብጽ የተሰደደውም እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም፤ እንደ ሚሰደድ ትንቢት ተነግሮለት ነው እንጂ፤ ለዚህም እንደ ምሳሌ ከደቂቀ ነቢያት አንዱ ሆሴዕ “እምግብጽ ጸዋዕክዎ ለወልድየ፤ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” ሲል ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ደግሞ “ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብጽ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ ጌታችን ፈጣን ደመና በተባለችው በእመቤታችን ጀርባ ተጭኖ ወደ ግብጽ ይወርዳል በማለት ተናግሯል። (ሆሴ. ፲፩፥፩ ፤ ኢሳ. ፲፱፥፩)
ግብጽ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈ አምልኮተ ጣዖት በስፋት የነበረባት ሀገር ነበረች። ይህ የአምልኮ ባዕድ ልማዳቸው በእስራኤላውያን እንኳን ሳይቀር ልምድ ሆኖባቸው ከግብጽ ምድር ሲወጡ በመንገድ ላይ ወርቅ አቅልጠው ጣዖት እስከማምለክ ደርሰዋል። (ዘጸ. ፴፪)
ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ?
- ለቤዛነት(ለካሣ)
እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቶስ ወደ ግብጽ የመሰደዱን ነገር ስናስብ እንዲሁ ከሄሮድስ ለማምለጥ ብቻ የተደረገ አድርገን አናስበውም፤ ከዚህ ከፍ አድርገን ለሰው ልጆች የተደረገ ካሳ እንደሆነ እናምናለን። በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት አዳም አታድርግ የተባለውን ነገር በማድረጉ ከገነት ተባረረ(ተሰደደ)። ይህ ስደቱ ግን ለሱ ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቹም ከእግዚአብሔር ልጅነት ርቀው ስደተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የፈጠረው በተድላ ገነት በሐሤት እና በምስጋና እንዲኖር ነው እንጂ ከእርሱ ርቆ ተስፋ አጥቶ ተንከራቶ እንዲኖር አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ “መጽሐፍ እንዲህ ብሎናል የመጀመሪያው ሰው አዳም በነፍስ ሕያው ሆኖ ተፈጠረ ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው” እንዲል ሁለተኛው አዳም ሕይወትን ሰጥቶታል። (፩ኛ ቆሮ ፲፭፤፵፭)
ስለዚህ አዳም ባለመታዘዙ የደረሰበትን ቅጣት ክርስቶስ ሁለተኛ አዳም ሆኖ ተቀብሎ የአዳምን የስደት ዕዳ በራሱ ስደት ካሠለት። ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ስደቱ ከዲያብሎስ መፈተኑ እስከ መስቀል ሞቱ እና ዕርገቱ ያሉት ተግባራት በሙሉ እኛን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ለማውጣት የተደረጉ የቤዛነቱ(ካሣ) አካል ናቸው።
- ዲያብሎስን ለማሳደድ
አጋንንትን ከግብጽና ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለመስደድ ነው፤ ጌታ ገና ከመወለዱ በፊት ለልደቱ ሃያ አራት ቀን ሲቀረው መካነ ልደቱ ቤተልሔምን በመላእክት አስጠብቋት ነበር፡፡ አጋንንት በውስጣቸው አድረው ይመለኩባቸው የነበሩ ጣዖታትም ተሰባብረው ጠፍተዋል። ይህንንም ጌታ ወደ ግብጽ በተሰደደ ጊዜ ራሳቸው አጋንንት በኢየሩሳሌም ማደሪያ እንዳሳጣኸን በዚህም ልታሳድደን መጣህን ብለው እንደ መሰከሩ በነገረ ማርያም ተጽፏል።
ጌታችን ወደ ግብጽ የተሰደደበት ሁለተኛው ምክንያት እነዚህ አጋንንት ማደሪያ ካደረጓቸው የሰው ልቡና እና ከጣዖቱ በማስወጣት አጋንንትን ለማሳደድ ነው፡፡ ይህንም ቴዎዶጦስ የተባለው ሊቅ “ጌታ ተሰደደ ሲባል ብትሰማ ፍጡር ነው ብለህ አትጠራጠር፤ ፈርቶ ሸሸም አትበል፤ የጌታ መሰደድ ዲያብሎስን ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለማሳደድ እንደሆነ እመን እንጂ” ብሎ የተሰደደው ዲያብሎስን ለማሳደድ መሆኑን ገልጧል። (ተረፈ ቄርሎስ ፲፥፭) ይህ ሊቅ ጌታ የተሰደደው ዲያብሎስን ለማሳደድ ብቻ ሳይሆን ሰው መሆኑን ለሚጠራጠሩ፣ ምትሐት ነው ለሚሉትም በትክክል ሰው መሆኑን ለማስረዳት እንደ ተሰደደ በዚሁ ምዕራፍና ቁጥር ይገልጻል፡፡
- ለአርአያነት
ጌታችን ወደዚህ ምድር ከመጣባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ አርአያነት ነው። በአርአያነት ያስተማረን ብዙ ትምህርቶች አሉ ከእነሱም መካከል በገዳመ ቆሮንቶስ ጹሞ ጹሙ፣ ቆርቦ ሐዋርያትን አቁርቦ ቁረቡ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ በእደ ዮሐንሰ ተጠምቆ ተጠመቁ፣ በጌቴሴማኒ ጸልዮ ጸልዩ፣ የሐዋርያቱን እግር አጥቦ “እኔ መምህራችሁ ስሆን እንዲህ እንዳደረኩኝ እናንተም እንዲሁ አድርጉ” የሚሉት ይገኙበታል። ይህንንም በወንጌል ነግሮናል “እኔ የዋህ ልቤም ትሑት ነውና ከእኔ ተማሩ” ማቴ ፲፩፣፳፱። የስደቱንም ነገር ስናነሣ የተሰደደው ስደታችንን ባርኮ እናንተም እንዲሁ በሃይማኖታችሁ መከራ ሲገጥማችሁ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ሽሹ ብሎ አርአያ ለመሆን ነው። እንዲሁም በሕይወታችን ችግር፣ ስደትና የስደት መከራ ሲገጥመን ጌታችን በስደታችን አብሮን አለ ብለን እንድንጽናና አዲስ ነገር እንዳይሆንብን አርአያ ሆኖናል።
እመቤታችን በስደቷ ጊዜ ልጇ እንዳይሞትባት ቀን ሐሩረ ፀሐዩ ሌሊት ቁረ ሌሊቱ እየተፈራረቀባት እሾሁ እየወጋት እንቅፋቱ እየመታት ከሰው ለመሰወር በበረሃው ስትሄድ ግሩማን አራዊት ያስደነግጧት ነበር፤ ሰው ወዳለበት መንደር ስትሔድ ሰዎች የሄሮድስ ሠራዊት እንዳይከተሏት ትሰጋለች። ይህን ሁሉ መከራ መቀበሏ ግን በስደትና በልዩ ልዩ መከራ ክርስተያኖች ሲሰቃዩ በስደት የደረሰባት የድንግል ማርያምን መከራ ሲያስቡ ጽናት ይሆናቸዋል፤ ለምን ይህ ሁሉ መከራ አገኘን ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ ተስፋ ይሆናቸዋል። ስለዚህ “ለምን ይህን ሁሉ መከራ ደረሰብን” ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ተሰደደች። አምላካችን “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።” (ማቴ. ፭፥፲-፲፩) ብሎ ስደትን ባርኮ ሰጠን።
- ትንቢቱን ለመፈጸም
እግዚአብሔር ሊያደርግ ያሰበውን ፈቃዱን ሁሉ ነቢያትን ትንቢት እያናገረ፣ መጻሕፍትን እያጻፈ ምሳሌ እያስመሰለ ነው እንጂ እንዲሁ ‘እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ’ በድንገት የመጣ አያደርግም። ስደቱንም በተነገረለት ትንቢት መሠረት ፈጽሟል።
ከነዚህም ትንቢታት መካከል ስለ እመቤታችንና ጌታ ስደት ፡-
ነቢዩ ኢሳይያስ (፲፱፥፩) “ናሁ እግዚአብሔር ይነብር ዲበ ደመና ቀሊል” እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፡፡ በማለት ሲናገር ከሙሴና ከአሮን ጸሎት የተነሣ የግብጻውያን የእጃቸው ሥራ መጥፋቱን፣ እግዚአብሔር በናቡከደነጾር አድሮ ወደ ግብጽ መምጣቱን፣ ጣዖታትን ማጥፋቱን የተነበየበት ከመሆኑ በላይ በማርያም ጀርባ ታዝሎ በፈጣን ደመና በተመሰለች ከእመቤታችን ጋር ወደ ግብጽ ተሰዷል።
ነቢዩ ሆሴዕ (፲፩፣፩) “እስራኤልን ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድኩት ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት” እስራኤል በግብጽ ሳሉ እንደተመረጡ ከዚያም አገር አውጥቶ መንግሥት ይሆኑ ዘንድ እንዳበቃቸው የተናገረበት ትንቢት እንደ መሆኑ የጌታችን ወደ ግብጽ መሰደድ ሄሮድስ እስኪሞት በዚያ መቀመጡን ከዚያም መመለሱን የሚያመለክት መሆኑን ቅዱስ ማቴዎስ የነቢዩን ቃል ፍጻሜ አድርጎ ተናግሯል፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፭)
ትንቢተ ስምዖን፡- “ባንቺ ደግሞ ሰይፍ ያልፋል አላት” (ሉቃ. ፪፥፴፬) ስምዖን በንጉሡ በጥሊሞስ ጊዜ መጻሕፍትን /ብሉያትን/ ከጥንቱ ዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ ለማስተርጎም ሰባ ሊቃናትን ባዘዘበት ወቅት ስምዖን “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች” የሚለውን ቃል ሲተረጕም ቢከብደው “እንዴት ድንግል ትፀንሳለች ብዬ ልተርጕም” ብሎ ሴት ትወልዳለች በማለት ቢጽፍ ተኝቶ ሲነሣ የጻፈው ጠፍቶ ድንግል ትፀንሳለች የሚል ተጽፎ ያገኛል፡፡ ይህ መሆኑ ቢገርመው የእግዚአብሔር መልአክ ይህንን ሳታይ አትሞትም አለው። ክርስቶስ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄድ ይህ ተፈጽሞለታል። ለእመቤታችን ግን ሰይፍ የተባለ መከራ ባንች ያልፋል ብሎ ትንቢትን ተናግሯል። የተናገረው ትንቢት በእመቤታችን የሕይወት ዘመን ሁሉ በልጅዋ ምክንያት ሰይፍ የተባለ መከራ አልፎባታል ።ይሄንንም እመቤታችን በስደቷ አሳልፋዋለች።
- አምልኮ ጣዖትን ለማጥፋት
ግብጽ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ረገጣት ጊዜ ድረስ ከነገሥታቶቿ ጀምሮ ጣዖትን የሚያመልኩ አሕዛብ የነበሩ ሕዝቦች ነበሩባት፡፡ ግብጽ ለዓለም ጣዖት አምልኮን ካስተማሩ አራት ሀገራት መካከል አንዷ ናት። እነዚህ አገራትም ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ግብጽና ሮም ሲሆኑ ፋርስ በሰው ምስል የተሠራ ጣዖትን፣ ሮም በወፍ አምሳል የተሠራ ጣዖትን፣ ባቢሎን በአራዊት(ዘንዶ) አምሳል የተሠራ ጣዖትን ማምለክ ለዓለም ሲያስተምሩ ግብጽ ደግሞ በእንስሳት (ላም) የተሠራ ጣዖት ማምለክን የጀመረች አገር ናት። (ሮሜ ፩፥፳፪ ትርጓሜ) ከተማዋ በጣዖታት የተሞላች ነበረች፡፡ ለዚህም ጌታችን ጣዖታትን ሊያፈርስ ወደ ግብጽ ተሰደደ፤ ገና ወደ ከተማዋ ሲገባ በጣዖታቱ ላይ ያደሩ አጋንንት ይጮሁ ጣዖታቱም ይሰባበሩ ጀመር።
ውድ የግቢ ጉባኤ ልጆች የክርስቶስ ወደ ግብጽ መሰደድ ከእኛ ሕይወት ጋር ይገናኛል፤ ክርስቶስ ከተወለደበት ከይሁዳ ምድር ተለይቶ ባሕሉ፣ ቋንቋውና አምልኮው ወደሚለይ ወደ ግብጽ ተሰደደ።
እኛም የግቢ ጉባኤ ልጆች ከለመድነው፣ ከኖርንበት፣ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከአከባቢ ተለይተን ወደማናውቀው አዲስ አከባቢ (ዩንቨርስቲ) እንቀላቀላለን። ታዲያ ያንን አዲስ አከባቢ እንደ አዲስ ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል። ክርስቶስ ወደ ግብጽ ምድር ሲሰደድ እግዚአብሔርን የማያውቁ ጣዖትን የሚያመልኩ ሰዎች ነበሩ፤ እርሱም ያንን አምልኮተ ጣዖት አጥፍቷል።
በግቢ ቆይታችን ብዙ ዓይነት አስተሳሰቦች፣ ብዙ ዓይነት ሥነ ምግባሮችና መጥፎ ሱሶች ይገጥሙን ይሆናል። እነዚህን ግን ቤተ ክርስትያን መጠለያ አድርገን ልናሳልፋቸው ይገባል። ምን አልባትም እኛ ወደማንፈልገው ዩኒቨርሲቲ፣ የትምህርት መስክ ብንመደብ እንኳን እግዚአብሔር ባወቀ በዚያ የምንፈጽመው ሥራ ስላለ ነው። ከክርስቶስ ስደት ትዕግሥትን እንደ ምንማር የሚገጥሙን እያንዳንዳቸውን ነገሮች በትዕግሥት ልናሳልፋቸው ዋጋ ልንቀበልባቸው ይገባል። መጽሐፍም “እስከ መጨረሻ የሚጸና ይድናል” ይላልና (ማቴ. ፳፬፥፲፫) መጽናት ይገባናል።
የስደት ዓይነተች
- አእምሮአዊ ስደት
ይህ ዓይነቱ ስደት አንድ ሰው በአካሉ በአንድ ቦታ እየኖረ ነገር ግን በአእምሮውና በሐሳቡ ሰላም አጥቶ በትካዜና በጭንቀት የሚንከራተትበት የውስጥ ስደት ነው። አእምሯችን በዓለም ሐሳብ ሲወሰድ ሰላም ያጣል ይንከራተታል። ይህንን ስደት ማለፍ የምንችለው ተስፋችን እግዚአብሔርን በማድረግ ነው “ጌታ ቅርብ ነው በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ” (ፊል. ፬፣፮)
- አካላዊ ስደት
አካላዊ ስደት ማለት አንድ ሰው ከለመደበት አከባቢ፣ ከሀገሩ ወይም ከቤተሰቡ ተለይቶ ወደ አዲስ ቦታ የሚያደርገው ስደት ነው። ለዚህ ምሳሌያችን የጌታችን ስደት ነው።
የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች እነዚህ የስደት ዓይነቶች ሲገጥሟቸው የሚያልፉበት ጥበብ
- በግቢ ጉባኤ ሥርዐተ ትምህርት በአግባቡ መማር
- የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትን መሳተፍ
- በግቢ ጉባኤ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ መቀላቀል ሲችሉ በቀላሉ ማለፍ ይችላሉ።
እኛ ክርስቲያኖች በዚህች ምድር ስንኖር “በዓለም ስትኖሩ መከራ አለባችሁ” (ዮሐ. ፲፮፥፴፫) እንዲል ሐዋርያው መከራ ልንቀበል ግድ ነው፤ ክርስትያን ተብለን በክርስቶስ ስም ተጠርተናልና፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በኖረበት ዘመኑ በስደትና በመከራ ነው ዘመኑን የፈጸመው፤ እርሱ መከራ እንደ ተቀበለ እኛም እንድንቀበል ነግሮን “እኔ ዓለምን እንዳሸነፍኩት ታሸንፋላችሁ” (ዮሐ. ፲፮፥፴፫) በማለት ተስፋውን ሰጥቶናልና ውድ የግቢ ጉባኤ ልጆች የዓለም ክፉ ምኞት ሁሉ አስወግዳችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ትቀድሱ ዘንድ ይገባል።
ከቤተሰብ ተለይታችሁ በአካል ወደ ግቢ ጉባኤ ስትሄዱ በግቢ የሚገጥሟችሁን ልዩ ልዩ ፈተናዎች ትሻገሩ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስና እናቱ ድንግል ማርያምን ይዛችሁ መሄድ አለባችሁ።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!