ይሁዳ እና የሰዎች ስሑት አረዳድ
ከዲ/ን ኃይለማርያም ታደሰ
“የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ።” (ማቴ. ፳፮፥፳፬)
ውድ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሞት አሳልፎ ስለሰጠው ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ የሚናገር ነው። ይህ ሰው ስሙ ከግብሩ ያልተባበረ ነው ይሁዳ ማለት ታማኝ ማለት ሲሆን፣ ግብሩ ግን ቆርሶ ላጎረሰው ቀዶ ላለበሰው ከነበደሉ ለተቀበለው አባቱና አምላኩ ያልታመነ ነው።
“የአስቆሮቱ” (Iscariot) የሚለው መጠሪያ ግን የተሰጠው ከትውልድ ቦታው በመነሣት ነው። “የአስቆሮት ሰው የሚሆን ያሲያዘው ይሁዳ” እንዲል ትርጓሜ ወንጌል (ማቴ. ፲፥፬) “የአስቆሮት ሰው የሚሆን ይሁዳ” (ማቴ. ፳፮፥፲፬) በዕብራይስጥ “ኢሽ–ኬርዮት” (Ish Kerioth) ማለት “የኬርዮት ሰው“ ማለት ነው። ኬርዮት በይሁዳ ምድር ደቡባዊ ክፍል የምትገኝ አንዲት ትንሽ ከተማ ናት፤ ይህም ሐጾር የምትባለውም ቂርያትሐጾር” ከተባለችው ከተማ ቂርያት የተገኘ ስም ነው። (ኢያሱ ፲፭፥፳፭) አባቱ “ስምዖን“ ይባላል። (ዮሐ. ፮፥፸፩፤ ፲፪፥፬፤ ፲፫፥፪፤ ፲፫፥፳፮)
በይሁዳ ዙሪያ የተነገሩ ትንቢቶች
በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ማንነት፣ ክሕደት እና አምላካችን ስለተሸጠበት የብር መጠን በርካታ ትንቢቶች ተነግረዋል። ዋና ዋናዎቹ የትንቢት ክፍሎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦
- የማዕድ አጋር የመሆኑ ትንቢት
“የሰላሜ ሰው የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።” (መዝ. ፵፩፥፱) ፍጻሜው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ራት ላይ ይህ ትንቢት በእርሱ ላይ እንደሚፈጸም ሲናገር፦ “ነገር ግን መጽሐፍ፦ እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው።” ብሏል። (ዮሐ. ፲፫፥፲፰) ለጊዜው ንጉሥ ዳዊትን ከድቶ ከአቤሴሎም ጋር ለተሰለፈው ለአኪጦፌል የተነገረ ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን የዳዊት ልጅ የተባለው ክርስቶስን ለከዳው ለይሁዳ ነው።
- ጌታውን በሠላሳ ብር የመሸጡ ትንቢት
ነቢዩ ዘካርያስ አስቀድሞ “እኔም፦ ደስ ብሏችሁ እንደ ሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፤ ያለዚያ ግን ተዉት አልሁ። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ። እግዚአብሔርም፦ የተስማሙበትን የከበረውን ዋጋዬን በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኖርሁት።” በማለት ተናግሯል። (ዘካ. ፲፩፥፲፪-፲፫) ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ለመስጠት ከካህናት አለቆች ጋር የተስማማበትና በኋላም የተጸጸተ መስሎ ብሩን በቤተ መቅደስ የጣለበት ክፍል ነው። (ማቴ. ፳፮፥፲፭፤ ፳፯፥፫-፭)። በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ይህ ትንቢት በኤርምያስ እንደተነገረ “በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው፦ ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ። ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት የሚል ተፈጸመ።” እያለ ወንጌላዊው ማቴዎስ ይነግረናል። (ማቴ. ፳፯፥፱) የአንድምታ ሊቃውንት ይህንን ሲያብራሩት ኤርምያስ የመሬቱን መገዛት ተንብዮ ነበር።(ኤር. ፴፪፥፲፬) ዘካርያስ ደግሞ የብሩን መጠን ተናግሯል፤ ማቴዎስ ግን የሁለቱንም ትንቢት በአንድ ላይ አጠቃሎ በዋናው ነቢይ በኤርምያስ ስም ጠራው በማለት ያስታርቁታል።
- የሸክላ ሠሪው መሬት ትንቢት
“ሂድ፥ ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ… “ (ኤር. ፲፱፥፩-፲፩፤ ኤር. ፴፪፥፮-፱) የካህናት አለቆች የደሙን ዋጋ (፴ውን ብር) ተቀብለው ለባዕድ አገር ሰዎች መቃብር የሚሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት፤ ያም መሬት እስከዛሬ “የደም መሬት” (አኬልዳማ) ይባላል። (ማቴ. ፳፯፥፯-፰)
- የሐዋርያነት ሥልጣኑ በሌላ ስለመተካቱ
“ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ። (መዝ. ፩፻፱፥፰) የትንቢቱን ፍጻሜ ደግሞ ጌታ ካረገ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዋርያት መካከል ቆሞ የዳዊትን ትንቢት ጠቅሶ በይሁዳ ምትክ ማትያስን በመምረጥ ተፈጽሟል። (ሐዋ. ፩፥፲፮-፳) «ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት» ማለት ይሁዳ ከ፲፪ቱ የሐዋርያት ቁጥርና ክብር ወጥቶ በቦታው ቅዱስ ማትያስ መተካቱን ያሳያል።
ሀ. የይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ መስጠትና የክርስቶስ ስቅለት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን አንድምታ ትርጓሜ እና በሊቃውንት ትምህርት መሠረት ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ባይሰጠውም እንኳ የክርስቶስ ስቅለትና ሞት አይቀርም ነበር። ሊቃውንቱ ለዚህ የሚሰጡት ዝርዝር ምሥጢራዊ ማብራሪያ እንደሚከተለው ይቀርባል፦
- ስቅለቱ የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅድ መሆኑ
የክርስቶስ ሰውን የማዳን ተግባር ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ በልበ ሥላሴ ይታወቃል። “እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ” በድንገት በይሁዳ ክሕደት ምክንያት የተፈጠረ ክስተት አይደለም። ቅዱስ መጽሐፍ ”ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፤ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።” (፩ኛ ጴጥ. ፩፥፳-፳፩) “ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል” እንዲል ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር የታረደው ተብሏል። (ራእይ ፲፫፥፰)
እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው ሐሳቡና በቀደመው ዕውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። (ሐዋ. ፪፥፳፫)የአንድምታ ማብራሪያው “ክርስቶስ የሞተው በእግዚአብሔር በታወቀው ሐሳቡና በወሰነው ፈቃዱ ነው፤ ማለትም እግዚአብሔር ወዶ መክሮ ባደረገው ሥጋዌ እንዳያችሁት መጠን ወይም (ቅድምናውን ሥጋዌውን እንዳያችሁት መጠን) ለኃጥኣን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።“ ይላል። ስለዚህ አምላክ ለሰው የሰጠው የነጻነት ፈቃድና የሰውን ልጅ የማዳን ዘለዓለማዊ ዕቅድ በሰዎች ክፋት ወይም በይሁዳ ታማኝ መሆን አለመሆን አይወሰንም።
- ይሁዳ ባይኖርም አይሁድ ጌታን ለመያዝ ይፈልጉ ነበር።
አይሁድና የካህናት አለቆች ይሁዳ ወደ እነርሱ ከመምጣቱ በፊትም እንኳ ጌታን ለመግደልና ለመስቀል በተደጋጋሚ ይመክሩ ነበር። ክርስቶስን የመግደል ሐሳብ በአይሁድ ለሦስት ዓመት ያህል የታሰበ ዕቅድ ነበር፤ ይሁዳ የመጣው አይሁድ መክረው ከጨረሱ በኋላ ነው። “ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ“ (ዮሐ. ፲፩፥፶-፶፫)
“ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል አለ። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤ ነገር ግን፦ በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን አሉ።” (ማቴ. ፳፮፥፪-፭)
የይሁዳ ሚና ምን ነበር? ይሁዳ ያደረገው ነገር ቢኖር አይሁድ በሕዝቡ ረብሻ እንዳይነሣ በመፍራት ሕዝብ በሌለበት በምሽት በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ለይቶ ማሳየት ብቻ ነበር። ይሁዳ ባይኖር ኖሮ አይሁድ በሌላ መንገድ ወይም በሌላ መሪ መያዛቸውና መስቀላቸው አይቀርም ነበር።
- የይሁዳ ክሕደት “ምክንያት” እንጂ “አስገዳጅ” አልነበረም (Foreknowledge vs Predestination)
ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ እንደሚሰጥ ትንቢት ተነግሯል። (መዝ. ፵፩፥፱) ይሁዳን ወስኖበት አይደለም። እግዚአብሔር በዘላለማዊ ዕውቀቱ (Foreknowledge) ይሁዳ በገዛ ነጻ ፈቃዱ የሚያደርገውን ክፋት አስቀድሞ በነቢያት ተናገረ እንጂ፣ አንዳንዶች እንደሚሉትይሁዳ ለዓለም መዳን የተሠዋ “መሥዋዕት” ወይም “አጋዥ” አይደለም።
ጌታችን ራሱ በወንጌል የተናገረው ቃል “የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር ።” (ማቴ. ፳፮፥፳፬) የአንድምታው ምሥጢር ደግሞ “ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል” ማለት ስቅለቱና ሞቱ የአምላክ ፈቃድና የትንቢት ፍጻሜ ስለሆነ አይቀርም ማለት ሲሆን፣ “ለዚያ ሰው ወዮለት” ማለቱ ግን ይሁዳ ወደ ክሕደት መግባቱ በገዛ ክፉ ፈቃዱና በስግብግብነቱ ምክንያት በመሆኑ ለፍርዱ ተጠያቂ መሆኑን ያሳያል።
ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው ላይ ይህንን ምሥጢር ሲያጠቃልለው እንዲህ ብሏል፦ «ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ባይሰጠው ኖሮ ክርስቶስ አይሰቀልም ነበርን? በፍጹም ይሰቀል ነበር! እርሱ የመጣው ለዚህ ነውና። ይሁዳ ጌታን አሳልፎ የሰጠው የሰውን ልጅ ለማዳን አስቦ ሳይሆን በገንዘብ ፍቅር ተገፋፍቶ ነው። እግዚአብሔር ግን የይሁዳን ክፋት ለዓለም ድኅነት መገኛነት ተጠቀመበት። ይሁዳ ባይከዳ ኖሮ የክርስቶስ ስቅለት በሌላ መንገድ ይፈጸም ነበር፤ ይሁዳ ግን ከሐዋርያነት ክብር ሳይወጣ በታማኝነት ይኖር ነበር» Homily 81: On Matthew 26:24)
- የአምላክ ፍጹም ትሕትና እና ትዕግሥት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁዳ እንደሚከዳው አስቀድሞ እያወቀ፣ በመጨረሻው ራት ላይ እግሩን አጥቦታል፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙንም ሰጠው። (ዮሐ. ፲፭፥፭) የወንጌል አንድምታ “ጌታ የይሁዳን እግር ያጠበው፣ እርሱ በገዛ ፈቃዱ ለጥፋት ቢሮጥም አምላክ ግን እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ የፍቅርና የንስሓ ዕድል እንዳልነፈገው ለማሳየት ነው።” ይላል።
- የክርስቶስ ሞት የፍቅር መሥዋዕትነት እንጂ የግዴታ አለመሆኑ
በነገረ መስቀል ትምህርት ክርስቶስ የሞተው በፈቃዱ እንጂ በይሁዳና በአይሁድ አስገዳጅነት አይደለም። (ዮሐ. ፲፥፲፰) ይሁዳ ጌታን አሳልፎ በሰጠበት በጌቴሴማኒ «እኔ ነኝ» ባለው ጊዜ ወታደሮቹ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወድቀዋል። (ዮሐ. ፲፰፥፮) ሊቃውንት ይህንን ሲተረጉሙ፦ “በአንድ ቃሉ መሬት የጣላቸው አምላክ፣ ሊይዙት የቻሉት ለዓለም ድኅነት ሲል ራሱን ዝቅ አድርጎ ስለሰጣቸው ብቻ እንደሆነ ለማሳየት ነው።” ይላሉ።
- ይሁዳ የመኮነኑ ምክንያት መካዱ ብቻ ሳይሆን ተስፋ መቁረጡ ነው።
በነገረ ድኅነት ትምህርት በመስቀል ላይ የፈሰሰው የክርስቶስ ደም የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ያስተሠርያል። (፩ኛ ዮሐ. ፩፥፯) ይሁዳ ራሱን ከማጥፋቱ በፊት ወደ ቀራንዮ መስቀል ሥር ሄዶ ቢሆን ኖሮ የመስቀሉ ደም እርሱንም ያድነው ነበር። የይሁዳ ትልቁ ስሕተት ኃጢአቱ ከክርስቶስ የማዳን ኃይል አስበልጦ ተስፋ በመቁረጡ ነው።
ለ. የአስቆርቱ ይሁዳ አሟሟት
የአስቆሮቱ ይሁዳ አሟሟትን በተመለከተ የተጻፉት ክፍሎች፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ምሥጢር መረዳት ለሚያነቡ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እጅግ የሚጋጩ ከሚመስሉ ታሪኮች መካከል ዋነኛው ነው። በመጀመሪያ ሁለቱ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ታሪኩን የመዘገቡበትን መንገድና ግጭት የሚመስለውን ነጥብ ስንመለከት “ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ።”ይላል። (ማቴ. ፳፯፥፭) ካህናቱም በገንዘቡ የመቃብር ቦታ እንደገዙበት ይናገራል።
በሌላኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ይሁዳ ሲናገር “ይህም ሰው በዓመፅ ዋጋ መሬት ገዛ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ”ይላል። (ሐዋ. ፩፥፲፰ ) ከዚህ ጋር ተያይዞ የአንድምታ መጽሐፍ ይሁዳ የሞተው በጌታ ዕርገት ሰዓት ነው ይላል።
ጥያቄው፦ ይሁዳ የሞተው ታንቆ ነው ወይስ በግንባሩ ተደፍቶ ተሰንጥቆ? መሬቱንስ የገዛው ይሁዳ ራሱ ነው ወይስ የካህናት አለቆቹ? የሞተው በታነቀ ጊዜ ወይስ በዕርገት የሚለው ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ አገላለጽ ተዘግቦ ስናየው የሚጋጭ ቢመስልም ሊቃውንት ያቀኑታል፤ የአንድምታ ሊቃውንት የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ (ማቴ ፳፯፥፭) እና የሐዋርያት ሥራ አንድምታ (ሐዋ ፩፥፲፰) ላይ ይህንን ታሪክ ፍጹም በሚስማማ መንገድ በሚከተሉት ሦስት ታላላቅ ምሥጢራት ያብራሩታል፦
- የአሟሟቱ ቅደም ተከተል
አይሁድ ጌታን እንይዛለን ሲሉ በተአምር ሲያመልጣቸው ያይ ስለነበር እሱም እንደልማዱ በተአምር ያመልጣል እኔም ወርቄን እንደያዝሁ እቀራለሁ ብሎ ሠላሳ ብር ተቀብሎ አሳልፎ ሰጣቸው። ጊዜው ደርሶ ይሞት ዘንድ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ ጻድቅ ሰው አስገደልኩ፣ ንጹሕ ደም አስፈሰስኩ ብሎ ሠላሳውን ብር ይዞ ተቀበሉኝ አላቸው።
አይሁድም አንድ ጊዜ የወደድከውን ሰጥተንሀል፤ የወደድነውን ሰጥተኸናል፤ አንተ ከእኛ፣ እኛ ከአንተ ምንም የለን ለራስህ ዕወቅ አሉት። በዚህ ጊዜ ይሁዳ ጌታን አሳልፎ በመስጠቱ ከፍተኛ ጸጸትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገባ። ጌታችን በፈቃዱ ለሞት መሰጠቱንና በተአምር እንደማያመልጥ ባወቀ ጊዜ፣ ይሁዳ በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፦ “ጌታአሁን ይሞታል፤ እርሱ ወደ ሲዖል ወርዶ እዚያ ያሉትን ነፍሳት በሙሉ ሊያወጣቸው ነው። ስለዚህ እኔ ቀድሜ ልሙትና ሲዖል ልጠብቀው፤ ሲመጣ እኔንም አብሮ ያወጣኛል” በዚህ የተሳሳተ ሐሳብ ተገፋፍቶ ሄዶ በገመድ ዛፍ ላይ ታነቀ።
ይሁዳ ሊታነቅባት የሞከራት ያቺ ዛፍ (በትውፊት የበለስ ዛፍ ናት) በተአምር ቁልቁል እያጎነበሰችና ወደ ላይ እየተነሣች “ንስሓ ግባ እንጂ አትሙት” እያለች ለ፯ ሰዓታት ያህል መከረችው። ይሁዳ ግን ንስሓ መግባትን እምቢ ስላለ በመጨረሻም ቀትር ላይ ከዛፏ ላይ ሲንጠለጠል ገመዱ ተበጥሶ ወደ መሬት ወደቀ። (አንድምታ ትርጓሜ ዘግብረ ሐዋርያት ፩፥፲፰)
- መሬት ላይ መውደቁና በሕመም መቆየቱ
ይሁዳ ከዛፉ ላይ ሲወድቅ ሆዱ ተቀዶ አንጀቱ ተዘረገፈ። ዕለቱን ግን አልሞተም። ይልቁንም በጽኑ ቁስልና ሕመም ተመቶ፣ አንጀቱ ተዘርግፎ ሳለ ነጋድያን ሲያልፉ አይተው “ለዘመዶቹ ያ ክፉ ሰው ወድቆ ይንፈራገጣል” ብለው ነግረዋቸውል። አንጀቱ ተሸክፎ (ታስሮ) ወደ ቤቱ ተወሰደ።
- የጌታ ማረግ እና የይሁዳ ፍጻሜ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ በ፵ኛው ቀን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ማረጉ (መውጣቱ) በኢየሩሳሌም ከተማ ታላቅ ዜና ተሰማ። ይሁዳ በቤቱ በቁስል ተኝቶ ሳለ፣ የቤቱ ሰዎችና በዙሪያው የነበሩት ሁሉ እየሮጡ መጥተው “ያ የሸጥከው የናዝሬቱ ኢየሱስ እነሆ ዛሬ በታላቅ ክብርና በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ (ወጣ)!” አሉት።
ይሁዳ ይህንን ታላቅ የምሥራች ሲሰማ፣ ጌታ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ “እኔንም ያወጣኛል” ብሎ አስቦ የነበረው ሐሳብ በሙሉ እንደከሸፈና እርሱ ግን በምድር ላይ ተለይቶ እንደቀረ ባየ ጊዜ በከፍተኛ ድንጋጤ፣ ጸጸትና ፍርሃት ተውጦ ከአልጋው ላይ ተነሥቶ ለማየት ሊወጣ ሲል፣ የቤቱ መቃን (የበሩ መወርወሪያ) በኃይል መታው። አንድም አያለሁ ብሎ ሲወጣ መላእክት የእሳት ጦር ይዘው ታዩት። ወደ አልጋ እሸሻለሁ ሲል የአልጋው ጫፍ ጎኑን ቀደደው። በዚያ ቅጽበት የታሰረው ሆዱ ተቀዶ፣ የቀረው አንጀቱ በሙሉ ተዘርግፎ፣ በግንባሩ ተደፍቶ በዚያው በዕለተ ዕርገት ፍጹም ክፉ አሟሟትን ሞተ።
ስለዚህ ማቴዎስ ይሁዳ ራሱን ያጠፋበትን የመጀመሪያውን ምክንያት (መታነቁን) ሲመዘግብ፤ ጴጥሮስ ደግሞ ከዛፍ ላይ ወድቆ መሬት ላይ መፈጥፈጡን እንዲሁም በሥጋው ላይ የደረሰበትን የአንጀት መጎልጎል መዝግቦታል። ሊቃውንት ደግሞ አስከሬኑ የደረሰበትን የመጨረሻውን(መሰነጣጠቁን) እና አሳልፎ የሰጠው አምላክ ወደ ሰማይ ማረጉን አመሥጥረው አስተማሩን።
ለ. መሬቱን ማን ገዛው? (በይሁዳ ስም መገዛቱ)
ወንጌላዊው ማቴዎስ መሬቱን የገዙት የካህናት አለቆች እንደሆኑ ይናገራል። ምክንያቱም የደም ዋጋ ስለነበረ ወደ መቅደስ ግምጃ ቤት ሊያስገቡት አልፈቀዱም። (ማቴ. ፳፯፥፯) ቅዱስ ጴጥሮስ ግን “ይህም ሰው በዓመፅ ዋጋ መሬት” ይላል። ሊቃውንቱ በአንድምታው ሲተረጉሙት መሬቱ የተገዛው በይሁዳ ገንዘብ እና በይሁዳ ስም ስለነበረ፣ በሕግና በታሪክ ደረጃ መሬቱን እንደገዛው ተቆጥሮበታል ማለት ነው። ልክ አንድ ሰው በገንዘቡ ሌላ ሰው ሄዶ መሬት ቢገዛለት፣ “እገሌ መሬት ገዛ” እንደሚባለው ሁሉ።
እንዳጠቃላይ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ አስቀድሞ ማወቅ እንጂ አስቀድሞ መወሰን የሚባል አስተምህሮ የለም። “አስቀድሞ መወሰን ፤ predestination” ትምህርት የኦግስቲን የግል ፍልስፍናዊ እምነቱ ነው። ለሰው ልጅ እግዚአብሔር ነጻ ፈቃድ ሲሰጠው “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” ብሎ የመብላትም አለመብላትም ሙሉ መብት ሰጠው፤ ይህ ሲባል ግን ትእዛዙን ሽሮ እንደሚበላ በመለኮታዊ ዕውቀቱ ያውቅ ነበር።
“አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ ደይ እዴከ ኀበዘፈቀድከ፤ እሳትና ውሃ አስቀምጬልሃለሁ እጅህን ወደፈቀድከው ስደድ” ሲል ለሰው ልጅ በጎ የመሆን ክፉ የመሆን ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶታል፤ “እምቅድመ ይፍጥሮ ለሰብእ የአምር ግብሮ፤ ሰውን ሳይፈጥረው በፊት ሥራውን ያውቃል” እንዲል ማናችንም ክፉ ወይ በጎ እንደምንሆን ሳንፈጠር ያውቀናል። ያውቀናል ማለት ግን ያስገድደናል ማለት አይደለም። ከክፋታችን ብንመለስ ዕድሜ እንደሚጨመርልን የሕዝቅያስ ታሪክ ያስገነዝበናል። (ሕዝ. ፳፥፩-፭)
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!