ጾመ ፍልሰታ፡- ታሪክ፣ ምስጢር፣ ምሳሌ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቶች
ከዲ/ን ኃይለማርያም ታደሰ
ጾመ ፍልሰታ (የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጾም) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሉት ሰባቱ አዋጅ ጾሞች መካከል ምእመናን በታላቅ ፍቅር፣ ናፍቆትና መንፈሳዊ ተጋድሎ ከሚጾሟቸው ጾሞች አንዱ ነው። ይህ ጾም ከሐዋርያት ሕይወት፣ ከእመቤታችን ዕረፍትና ዕርገት፣ እንዲሁም ከሀገራችን ጥንታዊ የአብነት ትምህርት ቤት ሥርዓት ጋር ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ምሥጢራዊ ቁርኝት አለው።
፩. የጾሙ ስያሜ
“ጾመ ፍልሰታ” (ፍልሰታ)
ፍልሰታ የሚለው ቃል “ፈለሰ” ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን፣ ትርጉሙም “ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ፣ መሻገር፣ ወይም መፍለስ” ማለት ነው። ጾመ ፍልሰታ ማለት ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ፣ ሥጋዋ ከመቃብር ተነሥቶ ወደ ሰማይ (ወደ ገነት) መፍለሱን (ማረጉን)ና መሻገሩን የሚያመለክት በመሆኑ ጾሙ “ጾመ ፍልሰታ” ተባለ፤ ይኸውም የሥጋዋ መፍለስ መታሰቢያ ነው።
ለምን የማርያም ጾም ተባለ?
ጾሙ “የማርያም ጾም” የተባለበት ምክንያት ጾሙ ቀጥታ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት (ሞት)፣ ትንሣኤና ዕርገት (ፍልሰት) ታሪክ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው። ሐዋርያት የጾሙት የእመቤታችንን ሥጋ ለማግኘትና ዕርገቷን ለማየት በመመኘት ስለነበር ጾሙ ለእሷ ክብርና መታሰቢያ ተለይቶ የተሰጠ በመሆኑ የማርያም ጾም ተባለ።
ሐዋርያት ለምን ጾሙ? (ታሪካዊው መነሻ)
ሐዋርያት የጾሙት የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገት በዓይን ለማየት ነው። የታሪኩ ዝርዝር በመጻሕፍቶቻችን ላይ እንደሚከተለው ሰፍሯል፦
- የእመቤታችን ዕረፍት፦ እመቤታችን በ፷፬ ዓመቷ በጥር ፳፩ ቀን ስታርፍ፣ ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ በክፉ ቅናት “ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ተነሣ፣ ወደ ሰማይ ዓረገ እያሉ ሕዝቡን አሳቱ፤ አሁን ደግሞ የእርሷን ሥጋ ይዘው ሊያታልሉን ነው” በማለት አልጋዋን ለመገልበጥና ሥጋዋን ለማቃጠል ሞከሩ። ታውፋንያ የተባለ አይሁዳዊ አልጋዋን ሊገለብጥ እጁን ሲዘረጋ የእግዚአብሔር መልአክ እጁን ቀጥቶታል።
- ሥጋዋ መነጠቁ፦ በዚህ ጭንቅ ወቅት ጌታችን በደመና መጥቶ የእመቤታችንን ሥጋና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራቸው።
- የሐዋርያት መጾም፦ ከዮሐንስ በስተቀር ሌሎቹ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደደረሰ አያውቁም ነበር። በኋላም ዮሐንስ ከገነት ሲመለስ ታሪኩን ነገራቸው። ሐዋርያትም “ዮሐንስ ያየውንና የተረዳውን ምሥጢር እኛ ሳናይ አንቀርም” ብለው የእመቤታችንን ሥጋ ለማግኘት በነሐሴ መጀመሪያ ጾም ጀመሩ።(ስንክሳር ዘነሐሴ ፲፮)
- ትንሣኤና ዕርገቷ፦ በሁለተኛው ሳምንት (በ፲፬ኛው ቀን) የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችንን ሥጋ ከገነት አምጥቶ ሰጣቸውና በጌቴሰማኒ ቀበሯት። በ፫ኛው ቀን (ነሐሴ ፲፮) እንደ ልጇ በልጇ ሥልጣን ተነሥታ ስታርግ፣ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ሲመጣ መለእክት ሲያሳርጓት በሰማይ አገኛት። ምልክት የሚሆን የመግነዙን ሰበዝ ሰጠችው። ሌሎቹ ሐዋርያት እርሱ ያየውን ምስጢር እንዲያዩ በሚቀጥለው ዓመት ነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ለሁለት ሳምንት በመጾማቸው፣ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችን ሁላቸውንም በቅዱስ ትንሣኤዋና ዕርገቷ ተገልጣ ባረከቻቸው። ሐዋርያት የጾሙት ይህንን ታላቅ ሰማያዊ ክብር ለማየት ነበር።
፪. ጾመ ፍልሰታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር
ጾመ ፍልሰታ በሁለት ዋና ዋና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቶች ላይ የቆመ ነው። የመጀመሪያው የጾሙ ሥርዓትና ሕግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእመቤታችን ዕረፍትና ዕርገት (ፍልሰታ) በትንቢትና በምሳሌ የገለጠ መሆኑ ነው።
ሀ) የጾሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታላላቅ ምሥጢራትን ለማየት፣ መለኮታዊ መግለጥን ለመቀበልና ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ለማግኘት፣ ታዓምራትን ለመሥራት ጾም እና ጸሎት አስፈላጊ ነው። (ማቴ ፲፯፥፳፩)
ሐዋርያት ፍልሰታን የጾሙት የሚከተሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አብነቶች በመከተል ነው፦
- የጌታችን አብነት (ማቴ ፬፥፪)፦ ጌታችን የሰው ልጆችን ለማዳን በጾም እንደጀመረ ሁሉ ሐዋርያትም የእመቤታችንን ትንሳኤ ለማየት ጹመዋል።
- የሙሴ አብነት (ዘጸአት ፴፬፥፳፰)፦ ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕግና ቃሉ የተቀረጸባቸውን የቃል ኪዳን ጽላቶች ለመቀበል ፵ ቀንና ፵ ሌሊት በጾም ቆይቷል። ሐዋርያትም አማናዊቷን የቃል ኪዳን ጽላት (የእግዚአብሔር ቃል ሰው የሆነባት እመቤታችንን) በትንሣኤና በዕርገት ክብር ለማየት በጾም ተግተዋል።
- የኤልያስ አብነት (፩ነገሥት ፲፱፥፰)፦ ነቢዩ ኤልያስ በጾም ከበረታ በኋላ ወደ ሰማይ በሠረገላ እሳት የመነጠቅ (የማረግ) ምሥጢር ተገልጦለታል። ሐዋርያትም የእመቤታችንን ወደ ሰማይ የማረግን ምሥጢር በዓይናቸው ለማየት ጾመዋል።
- የዳንኤል አብነት (ዳንኤል ፲፥፪–፫)፦ ነቢዩ ዳንኤል ሰማያዊውን ራእይና የነገሩን ምሥጢር ለመረዳት ሦስት ሳምንት (፳፩ ቀን) ሙሉ ቅባትነት ያለውን መብል ሳይበላ በትሕትና ጾሟል። ሐዋርያትም ምሥጢር እንዲገለጥላቸው የጾሙት ጾም የዳንኤልን አብነት የተከተለ ነው።
ለ) የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት (ፍልሰታ) በትንቢትና በምሳሌ
- የመቅደስ ታቦት የመነሣቷ ምሳሌ (መዝሙር ፻፴፩፥፰)፦ “አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።” እግዚአብሔር አምላክ ሙሴ የሠራትንና የቃል ኪዳኑ ሰሌዳዎች የተቀመጡባትን የጥንቷን ታቦት ይዞ ወደ ሰማይ አላወጣትም፤ ነገር ግን “የመቅደስህ ታቦት” የተባለችው እውነተኛዋና አማናዊቷ ታቦት ድንግል ማርያም ናት። ጌታ ወደ ሰማይ እንደ ዓረገ ሁሉ ታቦቱ፤ ማደርያው ወደ ዕረፍት ወደ ሰማይ እንዳስነሣት ይህ ጥቅስ ትልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክር ነው።
- የሙሽራይቱ መነሣት (መኃልይ ፪፥፲–፲፩)፦ “ውድ እኅቴ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ፤ እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ።” ሰሎሞን በትንቢት መንፈስ እንዳየው፣ ጌታችን እናቱን ከምድራዊ መከራ (ከክረምትና ከዝናብ ምሳሌ) በኋላ ወደ ሰማያዊው ክብር “ተነሺ፤ ነዪ” ብሎ እንደጠራትና ሥጋዋ ከመቃብር ተለይቶ እንደ ፈለሰ (እንደ ዓረገ) ማሳያ ነው።
- ፀሐይን የተጎናጸፈችው ሴት ራእይ (ራእይ ፲፪፥፩)፦ “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የተጎናጸፈች ጨረቃም ከእግሮችዋ በታች የነበረች በራስዋም ላይ የዐሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።” ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን በሰማያዊ ክብር ውስጥ ሆና አይቷታል። እርሷ በምድር ላይ አርፋ በሥጋ ወደ ሰማይ ባታርግ ኖሮ፣ ዮሐንስ በራእዩ በሰማይ ባለ ክብርና አክሊል አያያትም ነበር።
፫. የደቀ መዛሙርትና የእመቤታችን ቀረቤታ
በደቀ መዛሙርቱ (ሐዋርያት) እና በእመቤታችን መካከል ያለው ቀረቤታ የወላጅና የልጅ፣ የመምህርና የደቀ መዝሙር ዓይነት ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ አደራ (ዮሐ. ፲፱፥፳፯)፦ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚወደውን ደቀ መዝሙር ዮሐንስን “እነኋት እናትህ” አለው። ዮሐንስም “ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ወደ ቤቱ ወሰዳት” ይላል። ይህም ዮሐንስ መላውን ሐዋርያት በኋላም ውልደ ጥምቀትን ወክሎ እመቤታችንን እንደ እናት እንዲቀበል የተደረገበት ምሥጢር ነው።
- የሐዋርያት ማእከል መሆኗ (ሐዋ. ፩፥፲፬)፦ “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር” ይላል። ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በፊትና በኋላ ሐዋርያትን በአንድነት አሰባስባ የምታጽናናቸው፣ የምታስተምራቸውና የምትጸልይላቸው እርሷ ነበረች።
፬. በሃገራችን ከጥንት የመጣው የደቀ መዛሙርትና የእመቤታችን ወዳጅነት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንትና ተማሪዎች ይህንን የሐዋርያት አብነት (ሞዴል) ቀጥታ ወደ ራሳቸው ሕይወት አምጥተውታል።
ሀ) “በእንተ ስማ ለማርያም” (ስለ ማርያም ስም) እና የቆሎ ተማሪዎች ሕይወት
የአብነት ተማሪዎች (የቆሎ ተማሪዎች) ቤተሰብና ሀብት ትተው በየገዳማቱና በየአድባራቱ ሲማሩ፣ ምግባቸውን የሚሹት ከሕዝቡ ነው። መንደር ውስጥ ሲገቡ “በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለ ማርያም” ይላሉ። ሕዝቡም ለእመቤታችን ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ የተማሪዎቹን መዝገብ (የምግብ ከረጢት) በምግብ ይሞላል። ይህ ሥርዓት እመቤታችን የዕውቀት ብቻ ሳይሆን የዕለት ጉርስ እናት መሆኗን ያሳያል።
ለ) የተለየ ምሥጢር መግለጧ (ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ እንደ አብነት)
አራቱ ወንጌላውያን ስለ ክርስቶስ ሲጽፉ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ከምድራዊ ልደቱና ታሪኩ ይነሣሉ። ቅዱስ ዮሐንስ ግን “በመጀመሪያ ቃል ነበረ…” (ዮሐ ፩፥፩) ብሎ ረቂቁን መለኮታዊ ምሥጢር (ነገረ መለኮትን) በቀጥታ ከሰማይ ነው የጀመረው። ሊቃውንቱ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት፦ ዮሐንስ እመቤታችንን በቤቱ አብሯት ስለኖረና እርሷን ስለአገለገለ፣ ካደገችበት ከቅድስተ ቅዱሳን የተማረችውንና በልቧ ጠብቃው የነበረውን ሰማያዊ ምሥጢር ሁሉ ስለነገረችው ነው ይላሉ። ለዚህም ነው “ነባቤ መለኮት” የተባለው። የኢትዮጵያ ቅዱሳንም (እንደ ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ) የድርሰትና የትርጓሜ ምሥጢር የተገለጠላቸው በእመቤታችን አማላጅነት ነው።
ሐ) በጭንቅ ጊዜ ፈጥና መድረሷ እና “ሰላም ለኪ”
በአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ “ፈተና” የሚባለው ቸነፈር (ረሃብ)፣ ትምህርት የመያዝ/የመሸምደድ መቸገር፣ የጤና እክልና የመሳሰሉት ናቸው። ተማሪዎች ትምህርት አልገባ ሲላቸው ወይም በጨነቃቸው ጊዜ ሌሊት ማኅሌት ቆመው ወይም በግላቸው ተንበርክከው “ሰላም ለኪ እንዘ ንሰግድ ንብለኪ…፤ ሰላም ላንቺ ይሁን እያልን እንሰግድልሻለን…” የሚለውን ጸሎት በዕንባ ይደግማሉ። እሷ “ መርኆ ጥበብ፤ የጥበብ መክፈቻ” ተደርጋ ስለምታመን፣ የትምህርት ቤቱን ፈተናና መከራ ሁሉ በሰላም ያልፉታል።
ስለዚህ ውድ አንባቢዎች እመቤታችን ድንግል ማርያም ዛሬ በምድር ነገ በሰማይ ለሚገጥሙን ማንኛውም ጥያቄ መልስ የምናገኝባት የሕይወት ትምህርት ቤት፣ መዝገበ ምሥጢር ሕልማችንና እንቆቅልሻችን ሁሉ የሚፈታባት መሆኗን ተረድተን በረድኤቷ ጥላ ሥር ለመጠለል ጾሟን በትጋት መጾም ይጠበቅብናል።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!