ነቢዩ ኤልያስ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ኅዳር ፳፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች ! እንዴት አላችሁ? በዓመት ውስጥ ካሉት ወራት ሦስቱን ጨርሰን አራተኛውን ልንጀምር ነው! ባሳለፍናቸው ሦስት ወራት በዘመናዊ ትምህርታችንም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በፊት ከነበረን ምን ለውጥ አመጣን? አያችሁ ልጆች! በእያንዳንዷ ዕለት መሽቶ ሲነገ “ዛሬ ምን ቁም ነገር ሠራሁ?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል! እንዲህ ባደረግን ቁጥር የተሸለ ነገር ለመሥራት እንበረታለን! አሁን እንግዲህ በዘመናዊ ትምህርታችን አብዛኛዎቻችንን የተማርነውን ምን ያህል እንደተረዳን የምንመዘንበት የፈተና ወቅት ነው፤ ታዲያ በርትተን በማጥናት ዕውቀትን ልንቀስም ያስፈልጋል! በመንፈሳዊ ሕይወታችንንም መበርታት ይገባል፤ በዕለተ ሰንበት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መማር ያስፈልጋል! መልካም!!!
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ባለፈው ትምህርታችን ስለ ቅዱሳን ነቢያት፣ እነርሱ ስለ ጾሙትና የነቢያት ጾም ተብሎ ስለሚጠራው ጾም በጥቂቱ ተመልክተናል፤ እስኪ ትንሽ እናስታሳችሁ! አሁን ያለንበት ወቅት “ጾመ ነቢያት” ተብሎ በሚጠራው ወራት (ወቅት) ነው፤ ይህ ጾም ከሰባቱ ዓዋጅ አጽማትም አንዱ ነው፤ ከሰባት ዓመት ዕድሜ በላይ የሆናችሁና አቅማችሁ ለመጾም የደረሰ ጾመ ነቢያትን እንደ አቅማችሁ እየጾማችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን፤ በርቱ! ለዛሬ የምንነግራችሁ ደግሞ ስለ ከቅዱሳን ነቢያት አንዱ ስለሆነው ስለ ነቢዩ ኤልያስ ነው፡፡
ነቢዩ ኤልያስ በዘመነ ነገሥታት ከነበሩ ነቢያት አንዱ ነው፤ አባቱ ኢያሴንዩ እናቱ ደግሞ ቶና ይባላሉ፤ አባትና እናቱ በምግባር አሳደጉት፤ ከዚያም ወደ ገዳም ሄደ በጾምና በጾሎት በብሕትውና (በገዳም) ኖረ፤ እርሱ በነበረበት ዘመን ንጉሥ አክአብና ሚስቱ ኤልዛቤል የተባሉ ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን የማያምኑ በጣዖት የሚያመልኩ ነበሩ፤ ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እስራኤል ገብተው ነበር። ነቢዩ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የሚያውቅና እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሰው ነበር። በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው። እርሱም “እሺ” ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ። ነቢዩ ኤልያስ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ፤ በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር። (ድርሳን ነቢዩ ኤልያስ የታኅሣሥ ወር)
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ሕዝቡን እግዚአብሔር ከክፉ ነገር እየጠበቀ፣ የእርሱን ስጦታ እየተመገበ ይኖር ነበር፤ እነርሱ ግን ለቤል (ለበዓል) ለተባለ ጣዖት የሚሰግዱ ነበሩ። ይህን ጊዜ ግን ነቢዩ ኤልያስ ወደ አክአብ ዘንድ ሄዶ ጣዖት ማምለክ እንደ ሌለበት ሳይፈራ ገሠጸው፤ (ተቆጣው) ጣዖት የሚያመልክ ከሆነ የሚመጣውን መከራ እንዲህ በማለት ነገረው፦ ‹‹በፊቱ የቆምኩት እስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናም አይሆንም፤ (፩ኛመጽሐፈ ነገሥት ፲፯፥፩) ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ተከለከለ። ሕዝቡ በኃጢአቱና ጣዖት በማምለኩ ምክንያት ዝናም ስላልዘነበ እህል በማጣት ተጐዳ። ነቢዩ ኤልያስን ግን አምላካችን በዋሻ ተቀምጦ ቁራ የሚበላውን እያመጣለት ይመግበው፣ ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር።
ከዚያም እግዚአብሔር ሕዝቡ በረኀብ እንደተጎዳ ይመለከት ዘንድ ለነቢዩ ኤልያስ ምግብ ይወስድለት የነበረውን ቁራ አስቀረበት፤ ነቢዩ ኤልያስም ምግብ ፍለጋ ሰራፕታ ወደ ተባለ ሥፍራ ሄደ፤ በዚያም ነቢዩ ባሏ የሞተባትና ዮናስ የተባለ ልጅ የነበራትን ሴት አገኘ፤ እርሷም እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷን በበረከት ሞላው። ታዲያ አንድ ቀን ልጇ ታሞ ሞተባት፤ ነቢዩ ኤልያስም በጸሎቱ የሞተውን ልጇን (ሕፃኑ ዮናስን) ከሞትም በጸሎቱ አስነሳላት። (፩ኛነገሥት ፲፯፥፲፯)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ነቢዩ ኤልያስ “ለምን ጣዖት ታመልካላችሁ” በማለት ዝናም እንዳይዘንብ ቢያደርግም እግዚአብሔር ለሕዝቡ አዘነ፤ ነቢዩ ኤልያስም ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የዘጋውን ሰማይ ከፍቶት ዝናም እንዲዘንብ አደረገ፤ ሕዝቡንም ሰብስቦ ጣዖት የሚያመልኩም መጥተው መሥዋዕት እንዲሠው አስደረገ፤ ነገር ግን ያመልኩ የነበረው ራሳቸው ሰዎች የሠሩትን ጣዖት ነውና ጣዖቱ ጸሎታቸውን አልሰማቸውም፤ ነቢዩ ኤልያስ ግን ገና የእግዚአብሔርን ስም ሲጠራ መሥዋዕቱን ተቀበለለት፤ በዚህም ለሕዝቡ የጣዖታትን ከንቱነት እንዲሁም የእግዚአብሔርን አምላክነት ተረድተው አመኑ፤ ንግሥት ኤልዛቤልም ይህንን ስትሰማ እያልን ልትገድለው ባለች ጊዜ ከፊቷ ፈቀቅ አለ፡፡ (ወደ ሌላ ቦታ ሄደ)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ነቢዩ ኤልያስ በዘመኑ ብዙ ድንቅ ነገርን አድርጓል፤ ስለ እውነት ይመሰክር ነበር፤ ለተበደሉ ይከራከር ነበር፤ ለምሳሌ አንድ ጊዜ ኤልዛቤል የተባለችው ንግሥት ናቡቴ የተባለን ሰው አስገድላ መሬቱን ነጠቀችው፤ ነቢዩ ኤልያስም ሳይፈራ ወደ ንጉሡ እና ሚስቱ በመሄድ ናቡቴን ገድለው መሬቱን መንጠቅ እንደሌለባቸው በማስገንዘብ ተናገራቸው፤ በዚህም ሊገድሉት አሳደዱት፤ እርሱ ግን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ሊገድሉት አልቻሉም፤ ነቢዩ ኤልያስ ብዙ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ፣ ስለ እግዚአብሔር እያስተማረ፣ ሰዎች ከጣዖት አምልኮ እንዲወጡ እየመከረ ከኖረ በኋላ ከዚህ ምድር የሚለይበት ጊዜ ደረሰ፤ የእርሱ ደቀ መዝሙር ለነበረው ነቢዩ ኤልሳዕ መጎናጸፊያውን ሰጠው፤ እግዚአብሔርም በእሳት ሠረገላ ጭኖ ወደ ብሔረ ሕያዋን (የቅዱሳን ሰዎች መኖሪያ) ወሰደው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ነቢዩ ኤልያስ ታሪኩ ብዙ ነው፤ በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፈ ነገሥት ተመዝግቦ ይገኛል፤ እኛ ግን ለግንዛቤ እንዲሆናችሁ ጥቂቱን ታሪክ ነገርናችሁ፤ ብዙ ቁም ነገር እንደምትቀስሙ ተስፋ እናደርጋለን፤ ከነቢዩ ኤልያስ ታሪክ የዓለማት ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደሆነ፣ ጣዖት ማምለክ እንደማይገባ፣ እንደ ኤልዛቤል በሰዎች ላይ ክፋት ማድረግ እንደማያስፈልግ፣ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ስለ እውነት መመስከር እንደሚገባ፣ በእግዚአብሔር መታመን፣ ጾመኛ፣ ጸሎተኛ፣ ለተበደሉና ለተቸገሩ መርዳት እንዳለብን እንማራለን፡፡
ነቢዩን ኤልያስን ንጉሥ አክአብና ኤልዛቤል ሊገድሉት ሲሉ እግዚአብሔር ከእነርሱ ከልሎ በዋሻ ውስጥ አስቀምጦ አሞራ ምግቡን እንዲያመጣለት እንዳደረገ ሁሉ እግዚአብሔር ለሚታመኑት፣ ከልብ ለሚከተሉት፣ እውነትን ለሚናገሩና ለሰው ለሚያዝኑ እርሱም እንደሚረዳቸውም ተመልክተናል፤ ስለዚህም በሃይማኖታችን የጸናንና በምግባር የጎለበትን እንሁን! ሥነ ምግባር ያለው፣ ለወላጆች ታዛዥ፣ በሁሉ ነገር ጎበዝና፣ ንቁ ልጆች ልንሆን ያስፈልጋል!
የነቢዩ ኤልያስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ታኅሣሥ አንድ ቀን እና ጥር ስድስት ቀን ይከበራል፡።
አምላካችን እግዚአብሔር ከነቢዩ ኤልያስ በረከቱን ያድለን፤ አሜን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!