በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

‹‹ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን›› (ሮሜ ፰፥፴፭-፴፮)

ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራን፣ ሞትንና ስደትን፣ የመቀበል ታሪኳ ዛሬ የተጀመረ ባይሆንም በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ይሀረንና መሰል መተኪያ የሌለው ሕይወት የሚያጠፋና ሥጋት ላይ የሚጥሉ ተፈጥሮአዊ፣ ሰብአዊ ክብሩን የሚያራክስ ተግባራት እንዳይደገሙ ለማድረግ በሚጥርበት ዓለም ችግሩ በተለይም በሀገራችን እየተባባሰ መቀጠሉ እጅግ ያሳስበናል፡፡

በአርሲ ዞን በሹርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሠላሳ ስድስት፣ እንዲሁም በሶሌዲገሉና ጢጆለቡ በተባሉ ቀበሌዎች ሃያ ስምንት ኦርቶዶክሳዊያን ከየቤታቸው ተለቅመው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ከእነዚህም ሰባቱ ሴቶችና ሃያ አንዱ ወንዶች ናቸው፡፡ በዚህ ጥቃት የሰባ ዓመት አዛውንትና የሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ሕፃናት ይገኛሉ፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊትም በዲገሉ ማርያም ቤተክርስቲያን አምስት ምእመናን ሰማዕት ሲሆኑ የሦስት ምእመናን ቤት ተቃጥሏል። በሮቤ አንዲቶ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም አጥቢያ በዓለ ድንግል ማርያምን አክብረው በመመለስ ላይ የነበሩ ሦስት ኦርቶዶክሳዊያን ጨለማን ተገን ባደረጉ ገዳዮች ሰማዕትነት የተቀበሉ መሆኑን ከሀገረ ስብከቱ ሪፖርት ደርሶን ከሐዘናችን ገና ሳንጽናና ይባስ ብሎ በማዕከላዊ ጐንደር ሀገረ ስብከት የጐንደር ዓቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት የአቋቋም መምህር የሆኑት መምህር ፍሥሐ አለምነው ባልታወቀ ግለሰብ በድንጋይ ተወግረው መገደላቸው እና ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም. ከሌሊቱ ዐሥራ አንድ ሰዓት ላይ የማዕከላዊ ጐንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት በኲረ ትጉሃን ዘርዓ ዳዊት ኃይሉ ባልታወቁ ግለሰቦች በጥይት ተመተው መገደላቸው በእጅጉ ከማዘናችንም በላይ የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያረጋግጥ አድራጐት ሆኗል፡፡

በዚህ መግለጫ በቅርብ የተፈጸመውን ለማቅረብ ተሞከረ እንጅ ተመሳሳይ ግድያና፣ ስደት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የየዕለት ዜናችን ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ለአብነትም ያህል በወለጋ፣ በጐንደር፣ በጐጃም፣ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በመሳሰሉት እየተፈጸመ ያለው ድርጊት መንግሥትና ሕገ መንግሥት ባለበት ሀገር፣ የውጭ ወራሪና ድንበር ተሻጋሪ ጠላት ሳይኖርብን፣ እርስ በርሳችን በምናደርገው መጠፋፋት፣ ሃይማኖት ተኮር ጥላቻዎች፣ የንጹሐን ሕይወት መቀጠፉና የሀገርን ሀብት መውደሙ እኛንም ሆነ በመላው ዓለም መፍቀሬ ሰብእ የሆኑ የሰብዓዊ ክብር አስጠባቂ ተቋማትን ሳይቀር ማሳዘኑ ቀጥሏል፡፡

ይህ ሁኔታ በታሪክ ከመመዝገቡ በላይ የዜጎች በሕይወት የመኖር፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ የአካልና የንብረት ደኅንነታቸው መጠበቅ፣ የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት መከበር፣ የዜጎች ሁለንተናዊ ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ግዴታ ያለባቸውን አካላት በሙሉ በምድርም ሆነ በሰማይ ተጠያቂ የሚያደርግ ጉዳይ ነው፡፡ እየተፈጠረ ባለው አስከፊ መከራ፣ በጭካኔ የተሞላ ድርጊት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማጣት የዜጎችን ሕይወት፣ አካልና ንብረት፣ የእምነት ተቋማትን፣ መተኪያ የሌላቸው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶችና መስሕቦችን ሲያወድም፣ በሀገር ሁለንተናዊ ደኅንነትና በሕዝቦች ትሥሥር ላይ የፈጠረው አለመተማመን በቀላሉ የማይመለስ አደጋ ነው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከተከሰተው ረኃብ፣ ድርቅ፣ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት በተጨማሪ በየቦታው በተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ምክንያት በርካቶች ቀያቸውን ለቀው፣ መነኰሳት ገዳማትን ትተው ተሰደዋል፤ ወላድ እናቶች፣ ሕሙማንና አረጋውያን በሕክምና እጦት እያለቁ ነው፣ ሕፃናትና ወጣቶች ከጤናማ እድገትና ከትምህርት ገበታ ተደናቅፈዋል፡፡

በመሆኑም

፩. ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ከግጭትና ከጦርነት፣ ከእርስ በእርስ መገዳደል ወጥተው በውይይትና በምክክር፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት የታላቋን ሀገር መልካም ስምና ክብር እንዲሁም የዜጎቿን ሁለንተናዊ ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ተግባር ቅድሚያ እንዲሰጡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

፪. በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ንጹሐን ምእመናንና ተቋማት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች  በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ መንግሥትና የሚመለከታችሁ ሁሉ ዋስትና እንድትሰጡ፣ ወንጀል ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ድርጊቱንም መላው ዓለም እንዲያወግዘው ቋሚ ሲኖዶስ በአጽንዖት ይጠይቃል፡፡

፫. ከቤተ ክርስቲያን አልፎ የሀገርና የዓለም ሀብት የሆኑ ቅዱሳን መካናት፣ እንደ ዝቋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ አሰቦት ደብረ ወገግ አቡነ ሳሙኤል ገዳም እና አካባቢው፣ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳምና አካባቢው የመሳሰሉ ሁሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት አደጋ የተጋረጠባቸው በመሆኑ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እናሳስባለን።

፬. በመጨረሻም በየቦታው የሚያጋጥሙ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለማስቀረት ይቻል ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እያሳሰብን ለቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራው መሳካትም በየደረጃው ያላችሁ አህጉረ ስብከት የስጋት መረጃዎችን ለሚመለከተው ሁሉ በማሳወቅ ግዴታችሁን እንድትወጡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ለሞቱት የተዋሕዶ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን አስበ ሰማዕትታን እንዲከፍልልን፣ ለወገኖቻቸው ሁሉ መጽናናት እንዲሰጥልን፣ ስለ ስሙና ስለ ሰብዓዊ ማንነታቸው በመከራና ሥጋት ወስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ ጽናቱንና ብርታቱን እንዲሰጥልን፣ አጥፊዎችን እንዲገሥጽልን፣ ስደትና አለመረጋጋትን እንዲያርቅልን፣ የሀገራችንን አንድነትና ሰላም፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሕልውና እንዲጠብቅልን የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ታኅሣሥቀን ፳፻፲፮ ..

አዲስ አበባኢትዮጵያ