መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – የመጨረሻ ክፍል
ጌታችን ለኒቆዲሞስ እንዲህ በማለት የነገረው ይመስላል፤ ‹‹ኒቆዲሞስ ሆይ እየነገርሁህ ያለሁት ስለ ሌላ ልደት ነው፡፡ ስለምን ነው ንግግሬን ወደ ምድራዊ ነገር የምታወርደው? የምነግርህ ነገር ስለምን በተፈጥሮ ሕግ እንዲገዛ ታደርጋለህ? ይህ ልደት በሥጋ (በምጥ) ከሚደረገው ትውልድ የተለየ ነው፡፡ አጠቃላይና የተለመደ ከኾነ ልደት ራስህን አውጣ፡፡ እኔ ሌላ ልደት በሚገኝበት መንፈሳዊ ዓለም ሾሜሃለሁና፡፡ ሰዎች ዂሉ ከዚህ አዲስ ልደት እንዲወለዱ እወዳለሁ፡፡ አዲስ ዓይነት ልደትን ይዤ ወደ ምድር መጥቻለሁ፡፡ ሰውን የፈጠርሁት ከምድር አፈርና ከውኃ ነበር፡፡ ይህ ያገለግለኛል ብዬ የፈጠርሁት ምርጥ ዕቃ የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቶ አግኝቸዋለሁና እንደገና ከአፈርና ከውኃ ልሠራው አልፈቅድም እንደገና በውኃና በመንፈስ እንዲወለድ እፈቅዳለሁ እንጂ፡፡››
ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – ሦስተኛ ክፍል
ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጣ፤ ከፍ ያሉ ነገሮችን አዳመጠ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ተራ ሰው የሚገልጣቸው አይደሉም፡፡ ማንም ሰውም ከዚህ አስቀድሞ ሰምቷቸው አያውቅም፡፡ በቅፅበት ኒቆዲሞስ ወደ ከፍታ ወጣ፤ ነገር ግን መረዳቱ ጨለማ ነበር፡፡ ነገር ግን በራሱ ማስተዋል ገና የቆመ በመሆኑ ሊሸከማቸው ስላልቻለ ወደቀ፤ የጌታን ቃል እንዴት ሊሆን ይችላል? በማለት ጠየቀ፡፡ ጌታ የተናገረውን ነገር እንዲያብራራለት ሰው ከሸመገለ በኋላ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን በማለት ማብራሪያ ጠየቀ፡፡ ኒቆዲሞስ ስለ መንፈሳዊ ልደት ሰምቷል፡፡ ነገር ግን በመንፈስ አልተለማመዳቸውም (አያውቀውም)፡፡ የተማመነውም ቁሳዊ መረጃ ላይ ነው፤ ይህን ትልቅ ምሥጢር ለመረዳትና ለመተርጐም ምሳሌ አድርጎ ያቀረበው የሰውን የሥጋ ልደት ነው፡፡ ይህን ኹኔታ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፤ ‹‹ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፡፡ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ኾነ ሊያውቀው አይችልም›› (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፲፬)፡፡
ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – ሁለተኛ ክፍል
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኒቆዲሞስን ‹‹ኒቆዲሞስ ሆይ፥ ስለ ምን በምስጢር በምሽት መጣህ? ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ የእግዚአብሔር የሆነውንም ነገር እንደሚናገር እያወቅህ፡፡ ስለምን ከእርሱ ጋር ነገሮችን በግልጽ አልተወያየህም?›› ዓይነት ጥያቄዎችን አልጠየቀውም፡፡ አልወቀሰውምም፡፡ ነቢዩ እንዲህ ይላል፤ ‹‹አይጮኽም፤ ቃሉንም አያነሣም፡፡ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም፡፡ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጨስንም ክር አያጠፋም›› (ኢሳ. ፵፪፥፫)፡፡ ጌታ ራሱ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ዓለሙን ላድን እንጂ በዓለሙ ልፈርድ አልመጣሁም›› (ዮሐ. ፲፪፥፵፯)፡፡ የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና ተመልከቱ! ‹‹እኔ ዂሉን በራሴ ማድረግ ይቻለኛልና የማንም ርዳታ አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ የያዝኩት ኀይል የአባቴን ኀይል ነው …›› አላለም፡፡ ይህንን ቢል ለሚያዳምጡት ወገኖች ቃሉን መቀበል ከባድ በኾነ ነበር፡፡
ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – የመጀመሪያ ክፍል
ወንጌላዊው እንደ ነገረን ኒቆዲሞስ ጌታ ከእግዚአብሔር እንደ መጣ አወቀ፤ አመነም (ዮሐ. ፫፥፪)፡፡ ነገር ግን ምናልባት ኒቆዲሞስ ጌታ ትምህርቱን ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያስተምር ሊያስብ ይችላል፡፡ የሕጉን ጥሬ ትርጕም እንጂ ፍካሬያዊ ትርጕም አልተገነዘበም፡፡ የአይሁድን ኑሮ ሊያሻሽል የመጣ ነው ብሎም ሊያስብ ይችላል፡፡ የኒቆዲሞስ አመለካከቱና ልምዱ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን አዲስ ሕይወት ለመቀበል አያበቃውም፡፡ በአዲሱ ልደት የሚገኘው የጸጋ ልጅነት አይገነዘበውም፡፡ የመንፈሳዊው ሕግ ጥቅም ግን ይህ ነበር፡፡ ሥጋዊውን ከመንፈሳዊ ምድራዊውን ከሰማያዊ መለየት ያስችላል፡፡ ጌታ የኒቆዲሞስን አሳቡን፣ ልቡን፣ ስሜቱን፣ ዕውቀቱን ዂሉ ወደ ሰማያዊ ነገር እንዲያሸጋግረው ፈቀደ፡፡ ይህን በማድረግ ከሰማይ የወረደው እርሱም በሰማይ የነበረው እንደ ኾነ ይገነዘባል፡፡ ወደ ሰማይ መውጣትም የሚቻለው እርሱ ነው፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ወገኖችን ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው፤ ከፍ ያለውንም ነገር እንዲመለከቱ የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡
ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጨረሻ ክፍል
በአጠቃላይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር መጽሐፉ የመናፍቃንን ስሕተትና የስሕተታቸውን ምክንያት ነቅሶ በማውጣትና መጽሐፋዊ የሆነ መልስ በመስጠት መናፍቃንንና ስሑታንን ገሥጿል፡፡ የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ለተነሡ ኑፋቄዎች መልስ መስጠት ቢሆንም ሌሎችንም ጉዳዮች በማንሣት መልስ እንደ ሰጠ ከላይ ተመልክተናል፡፡ “አዲስ መናፍቅ እንጂ አዲስ ኑፋቄ የለም” እንደሚባለው በመጽሐፉ የተጠቀሱ መናፍቃን ትምህርቶች ዛሬም ድረስ በተለያዩ አካላት እንደ አዲስ ሲጠቀሱና ሲነገሩ እንሰማለን፡፡ በዘመናችን የተነሡ መናፍቃንና ግብረ አበሮቻቸው የሚያስተምሩትም ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የለየችውና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንት መልስ የሰጡበት እንጂ አዲስ የተገለጠላቸው ትምህርት አለመሆኑን መረዳት ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ ትምህርቷን ያልሰሙ አላዋቂዎች ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን እንደማትሰብክ አድርገው ይናገራሉ፡፡
ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – ሦስተኛ ክፍል
አባ ጊዮርጊስ የክርስቶስን አምላክነት በመሰከረበት በዚህ አንቀጹ የሚከተለውን ትምህርት አስተምሯል፤ “ስለ ትሕትና ነገር መናገርን እናስቀድም፤ ኃይል በሴት ማኅፀን አደረ፤ እሳትም በሥጋና በደም መጐናጸፊያ ተጠቀለለ፡፡ ሕፃናትንም የሚሥል በሕፃናት መልክ ተሣለ፤ የሔዋን አባት ከሔዋን ሴት ልጅ ተወለደ፤ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ በጉልበት ታቀፈ፤ እሳት በተሣለባቸው በአራቱ እንሰሳ ላይ የሚጫን በላምና በአህያ መካከል ተኛ፡፡ ሥጋዊን ሁሉ የሚመግበው የጡት ወተትን ተመገበ፡፡ በጊዜና በዘመናት የሸመገለ በየጥቂቱ አደገ፤ በታናሽነታቸው ጊዜ ሕፃናትን የሚጠብቃቸው በሜዳ ላይ ዳኸ፤ ለዓመታቱ ቁጥር ጥንት የሌለው በሰው መጠን ጐለመሰ፤ ተራሮችን በኃይል የሚያቆማቸው ደከመ፣ ወዛም፡፡ ኪሩቤል ሊነኩት ሱራፌልም ሊዳስሱት የማይቻላቸው እግሮቹ በአመንዝራይቱ ሴት፣ ልብሶቹም ደም በሚፈስሳት ሴት ተዳሰሰ፡፡”
ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – ሁለተኛ ክፍል
አርጌንስ (ኦሪገን) መዓርገ ርቀትን (‹ቀ› ይጠብቃል) ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አብ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድም እንደዚሁ ከመንፈስ ቅዱስ እንደሚበልጥ አድርጎ ይናገራል፡፡ ዛሬም በዚህ ኑፋቄ የወደቁና “አብ ይበልጠኛል፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ” ብሏል በማለት ኢየሱስ ክርስቶስን ከአብ እንደሚያንስ አድርገው የሚናገሩ አሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ እነዚህን ኀይለ ቃላት እንዲህ ይተረጉማቸዋል፡፡ “ከዕርገቱ በፊት ‹ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ› ያለው ለሰውነት የሚገባ ትሕትናን እያሳየ ነው፤ ለእነርሱ በጸጋ አባታቸው ነው፣ ለእርሱ ግን በእውነት የባሕርይ አባቱ ነው፡፡ ለእነርሱ በእውነት አምላካቸው ነው፤ ለእርሱ ግን ሰው ስለመሆኑ ነው፡፡” ለአርጌንስም “እኛ ግን ‹በሥላሴ መዓርግ የመብለጥም ሆነ የማነስ ነገር የለም፤ በመለኮት አንድ ናቸው እንጂ› ብለን እናምናለን” በማለት ይመልስለታል፡፡
ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጀመሪያ ክፍል
አባ ጊዮርጊስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል፤ የሚበዙት የምስጋና ድርሰቶች ናቸው፡፡ ከጻፋቸው ብዙ መጻሕፍት መካከል አንዱ መጽሐፈ ምሥጢር ነው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር በቤተ ክርስቲያናችን ከሚጠቀሱ የዕቅበተ እምነት መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ሲሆን የአባ ጊዮርጊስ የነገረ ሃይማኖት ሊቅነቱ የተመሰከረበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ አባ ጊዮርጊስ በነገረ እግዚአብሔር ላይ ጽርፈት የተናገሩ መናፍቃንን ለመገሠጽና ለእነርሱ መልስ ለመስጠት የጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ በምን ዓይነት ቅንዐተ መንፈስ ቅዱስ ተነሣሥቶ መልስ እንደሰጠ ሲነግረን “… የቅዱሳንን ዜናቸውን ለመናገር ፍቅር ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ከሐዲዎችን እነቅፋቸው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር ክርስቶስን እንዳመሰግነው ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ሰይጣንን አወግዘው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር የክርስቶስን ሐዋርያት እንድከተላቸው ያስገድደኛል፤ ቅንዐትም ዝንጉዎችን እንድዘልፋቸው ግድ ይለያኛል፤ ፍቅር ሰማዕታትን አወድሳቸው ዘንድ ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ጠንቋዮችን እንድዘልፋቸው ያስገድደኛል” በማለት ይገልጽልናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዐይን
መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ምንጭና ራስ ነው፡፡ ማንኛውም ትምህርት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወይም ሥርዐት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሰው ጋር የሚጋጭ ከሆነ በቤተ የቤተ ክርስቲያናችን ተቀባይነት የለውም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የትምህርተ ሃይማኖት ዋና ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የሥርዐትና የታሪክ ዋና ምንጭም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘውን የምትፈጽም፣ የምታስተምርና የምትኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስንም እንድናነበውና እንድንማርበት አዘጋጅታ የሰጠችን እርሷው ናት፡፡ ይሁንና አንዳንድ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱስን የሚከተሉ መስለው ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ያልሰበከች አስመስለው ስለሚያቀርቡ ተንኮላቸውን ተረድተን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የማይለውን እንደሚል አድርገው በማቅረብና አጣመው በመተርጎም የሚስቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ከሁሉ የምትቀድመውን ቤተ ክርስቲያን እየተቃወሙ እርሷ ለዓለም ሁሉ የሰጠችውን ቅዱስ መጽሐፍ የተቀበሉ የሚያስመስሉት፡፡
አንቀጸ መድኃኒት ቤተ ክርስቲያን – ካለፈው የቀጠለ
ክርስቲያኖች በዚህች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስንኖር ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት እያደገ እየጠበቀ ይሔዳል፡፡ ይህ አንድነትም በጊዜ ሒደት፣ ወይም በተለያየ ቦታ በመሆን የሚቋረጥ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ቅዱሳን መላእክትን እንዲሁም በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብፁዓን፣ በገነት፣ በዐጸደ ሥጋና በዐጸደ ነፍስ ያሉትን ምእመናን ሁሉ የምትይዝ አንዲት ኅብረት ናት ማለታችንም ስለዚሁ ነው (ዕብ. ፲፪፡፳፪-፳፬)፡፡ በዐጸደ ነፍስ ያሉት ምእመናን በንስሓ የተመላለሱ፣ ሩጫቸውን የጨረሱና ድል ያደረጉ ሲሆኑ፥ በዐጸደ ሥጋ ያለን ደግሞ ሩጫችንን ገና ያልጨረስንና በተጋድሎ ውስጥ የምንገኝ ነን፡፡ ሐዋርያው እንዲህ እንዳለ፡- “እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን” (ሮሜ. ፲፪፡፭)፡፡ ይህ ትምህርት የነገረ ሃይማኖት መሠረት ነው፡፡ እንዲህ የተባለበትም ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ምንነትና ማንነት ላይ ያለን ልዩነት ለጠቅላላ ነገረ ሃይማኖት መለያየት ምክንያት ስለሚሆን ነው፡፡