መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
የወደቁትን እናንሣ
ጕብኝት ባደረግንበት ወቅት እንዳስተዋልነው በማኅበሩ እየተጦሩ ከሚገኙ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ የአብነት መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ሓላፊነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያንና የአገር ባለውለታዎች በሕመም፣ በጤና እና በእርጅና ምክንያት የአልጋ ቁራኛ፣ የደዌ ዳኛ ኾነው ጎዳና ላይ በወደቁበት ወቅት ይህ ማኅበር ደርሶላቸው አስፈላጊውን ዅሉ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ በተለይ የአእምሮ ሕሙማንና ከአንድ በላይ በኾነ የጤና እክል የተጠቁ ማለትም የማየትም የመስማትም የመንቀሳቀስም ችግር ያለባቸውና ሰውነታቸውን መቈጣጠር የማይችሉ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች ኹኔታ ልብን ይነካል፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚንቀሳቀሱትም፣ የሚመገቡትም፣ የሚለብሱትም፣ የሚጸዳዱትም በሰው ርዳታ ነው፡፡ እነርሱን ያየ ሰው የማኅበሩን ዓላማ በግልጽ ይረዳዋል የሚል እምነት አለን፡፡
ዘመነ ክረምት – ክፍል አምስት
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እንዲህም ያለ መከራ በዓለም ባሉ ወንድሞቻችሁ ዅሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ›› በማለት እንዳስተማረው (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፱) በመላው ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ዛሬ በመከራ ውስጥ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል የዓለም የኑሮ ሸክም ከብዷቸው ይሰቃያሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአሕዛብና በአረማውያን ዛቻና ማስፈራሪያ ይጨነቃሉ፡፡ የክርስትና ትርጕም የገባቸውም በፈቃዳቸው በሰማዕትነት ይሞታሉ፡፡ ይህን ዅሉ ፈተና ተቋቁሞ በክርስትና ሃይማኖት ጸንቶ፣ በምግባር በርትቶ፣ በጸሎት ተግቶ የሚኖር ምእመን እርሱ ብፁዕ ነው፡፡ በሰማያዊው የእግዚአብሔር መንግሥት ለጻድቃን የተዘጋጀውን ሰላማዊና ዘለዓለማዊ ማረፊያ ይወርሳልና፡፡ እንግዲህ እኛም ሞገዱና ማዕበሉ ማለትም ምድራዊ ውጣ ውረዱና ፈተናው ቢያንገላታንም በዚህ ዓለም የሚጎድልብንን ሥጋዊው ጥቅምና የሚደርስብንን ጊዜያዊ መከራ ሳይኾን በእውነተኛው አገራችን በሰማይ የምንወርሰውን ዘለዓለማዊ መንግሥት ተስፋ በማድረግ ዅሉንም በጸጋ እንቀበል፡፡
ፅንሰተ ማርያም ድንግል
‹‹ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል …፤ ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን መረጠ፤ አከበረ፤ ለየ፤ ቀደሰ …፤›› (መዝ. ፵፭፥፬) በማለት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደ ተናገረው፣ አምላክን ለመውለድ የተመረጠችው ማኅደረ ማለኮት፤ የዓለሙን ቤዛ በመውለዷ ‹‹ቤዛዊተ ዓለም›› እየተባለች የምትጠራው፤ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረችው፤ የድኅነታችን ምክንያት የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን የተቋጠረችው (የተፀነሰችው) ነሐሴ ፯ ቀን ነው፡፡ ፅንሰቷም እግዚአብሔር በባረከውና ባከበረው ቅዱስ ጋብቻ በተወሰኑት ወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ሥርዓት ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በሥጋዊ ፈቃድ የተፀንሽ አይደለሽም፤ ሕጋዊ በኾነ ሥርዓት ከሐና እና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፤›› እንዳሉ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡
ተስእሎተ ቂሣርያ
ዛሬ ዓለም ክርስቶስን ማን ትለዋች? እኛስ ማን ብለን እንጠራዋለን? ምላሹ እንደየሰዉ የመረዳት ዓቅም ሊለያይ ይችላል፡፡ እውነታው ግን አንድ ብቻ ነው፤ በእርግጥ እግዚአብሔር አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሕዝቡን እንዳዳነ ያልገባት ዓለም ክርስቶስን ከፍጡራን ተርታ ትመድበዋለች፡፡ የእርሷ የፍልስፍና ሐሳብ አራማጆች መናፍቃንም አምላክነቱን ክደው ‹‹አማላጅ ነው›› ይሉታል (ሎቱ ስብሐት)፡፡ ሌሎችም እንደየዓቅማቸው ለክብሩ በማይመጥን ልዩ ልዩ ስም ይጠሩታል፡፡ በሐሰተኛ ትምህርታቸውም ብዙ የዋሃንን አሰናክለዋል፡፡ እርሱ ባወቀ ወደ ቤቱ ይመልሳቸው እንጂ፡፡ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን እርሱ ባለቤቱ፣ ቅዱሳን ሐዋርያትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት አንዱ፤ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር (አምላክ ወልደ አምላክ)፤ በቈረሰው ሥጋ፣ ባፈሰሰው ደሙ ከዘለዓለማዊ ሞት ያዳነን የዅላችን ቤዛ እንደ ኾነ እናምናለን፤ እንታመናለን፡፡ ይህን ሃይማኖታችንንም ለዓለም በግልጽ እንመሰክራለን፡፡
ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል ሦስት (የመጨረሻ ክፍል)
በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይኾን ሱባዔ ቢገባ ከሱባዔው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ድካሙ ዋጋ ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባዔ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነውና፡፡ ከዚህም ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርጉልናል፡፡ ስለኾነም ቅድመ ሱባዔ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ነው፡፡
ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል ሁለት
አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቈጥር፣ አዳምም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለ ነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቈጠረ ‹‹የተናገረውን የማያስቀር፣ የማያደርገውን የማይናገር ጌታዬ፤ እነሆ ‹አድንሃለሁ› ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤›› እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸሩ አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ‹‹ተንሥኡ ለጸሎት፤ ለጸሎት ተነሡ፡፡ ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይኹንን!›› በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡
ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ
ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማጸን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅጽኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው (የምንማጸነው) ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ጥቅም የለም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ አገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና፣ ወዘተ. ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች ፈጣሪውን በጸሎት ይማጸናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ኾነ በአገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፡፡ መልሱ ሊዘገይም ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት ይጠበቃል፡፡
ዘመነ ክረምት – ክፍል አራት
መጽሐፍ ቅዱስ ስንፍናን የሚያወግዝ፣ ሥራን ደግሞ የሚያበረታታ ኾኖ ሳለ ‹‹ለምንድን ነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ …› ሲል ያስተማረው?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ያህል ቃሉ አትጨነቁ ማለቱ ‹‹ለሥጋዊ ጉዳይ ቅድሚያ አትስጡ፤ እየሠራችሁ እግዚአብሔርን በጸሎት ጠይቁ›› ሲለን ነው፡፡ የሰው ልጅ ሠራተኛ ፍጥረት ቢኾንም ዝናም አልጥልለት ሲል፤ የዘራበት መሬት ሳያበቅል ሲቀር፤ የወር ደመወዙ ሲዘገይ፤ እኽል የሚሸምትበት ገንዘብ ሲያጣ፤ ወዘተ. በመሳሰሉት ፈተናዎች ውስጥ በኾነ ጊዜ ምን ልበላ ነው? ልጠጣ ነው? ልጆቼ እንዴት ሊኾኑብኝ ነው? ዛሬን እንዴት ላልፍ ነው? በሚሉትና በመሳሰሉት የጭንቀትና የተስፋ መቍረጥ ስሜቶች ሳይያዝ የዕለት ጕርሱን፣ የዓመት ልብሱን ይሰጠው ዘንድ የጠፋውን ዝናም ማምጣት፤ የደረቀውን ዘር ማለምለም፤ ባዶ የኾነውን ቤት መሙላት የሚቻለውን እግዚአብሔርን (እርሱን) በእምነት ኾኖ በጸሎት ይጠይቀው ለማለት መድኀኒታችን ክርስቶስ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ›› ብሎናል፡፡
የበረዶ ናዳ በገዳመ ናዳ
የገዳሙ ደን እና ፍራፍሬ በበረዶ ናዳ ቢወድምም ዋና አስተዳዳሪው እና ማኅበረ መነኮሳቱ ብሩህ ፊታቸው አልቀዘቀዘም፡፡ ጉባኤ ቤቱም አልተፈታም፡፡ ገዳማውያኑ በተለመደው መንፈሳዊ ቋንቋ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን! ደኅና ነን … በአትክልት ላይ እንጂ በሰውና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም … ዅሉም ነገር ለበጎ ነው … ከዚህ የባሰ አያምጣ …›› እያሉ እነርሱን ለመጠየቅና ጉዳን ለማየት የሚመጡ ምእመናንን ያረጋጋሉ፡፡ ገዳማውያን እንዲህ ናቸው፤ ተበድለው እንዳልተበደሉ፤ ተጎድተው እንዳልተጎዱ፤ ተቸግረው እንዳልተቸገሩ በማመን በኾነው ነገር ዅሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ በዚህ ዓመት በፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም እና በአካባቢው በወርኃ ሰኔ የደረሰው ጉዳት እግዚአብሔርን ወደማማረር የሚገፋፋ ከባድ ፈተና ቢኾንም የገዳሙ አባቶች እና እናቶች ግን እግዚአብሔርን ማመስገናቸውን ለቅጽበት አላቋረጡም ነበር፡፡ በስበብ አስባቡ እግዚአብሔርን ና ውረድ የምንል ምእመናን ከእነርሱ ትምህርት ልንወስድ ይገባል፡፡
ጾመ ማርያም ለቤተ ክርስቲያን ሰላም
በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጕልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍን አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በእነዚህ የጾም ሳምንታት የእመቤታችን አማላጅቷ እና ጸጋዋ በአገራችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዲያድር በሱባዔ እንማጸናት፡፡ የሁለቱ ሳምንታት ሱባዔ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር የምንልበት፣ የበደልነውን የምንክስበት፣ ሥጋውንና ደሙን የምንቀበልበት ወቅት መኾን አለበት፡፡ ነገር ግን ቀናቱን እየቈጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ሌላው ቁም ነገር በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ገብተን ውዳሴ ማርያም በደገምንበት አፋችን ሰው የምናማ፣ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከኾነ እመቤታችንን አናውቃትም፤ እርሷም አታውቀንም፡፡ እናም ‹‹መክፈልት ሲሹ መቅሠፍት›› እንደሚባለው በረከት ማግኘት ሲገባን መቅሠፍት እንዳይደርስብን ዅሉንም በሥርዓቱና በአግባቡ ልናከናውን ያስፈልጋል፡፡