መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
ብዙኃን ማርያም
ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡
፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎች ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ‹ብዙኃን ማርያም› እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡ እነዚህ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው (ዘፍ. ፲፬፥፲፬)፡፡
የሕንዱ ፓትርያርክ የመስቀል በዓልን በአዲስ አበባ አከበሩ
በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተመሠረተችው የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ስትኾን፣ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌልና ካህናት እንደዚሁም ወደሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን እንዳሏትና ሠላሳ በሚኾኑ አህጉረ ስብከቷ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በመወጣት ላይ እንደምትገኝ ታሪኳ ያስረዳል፡፡ በ፳፻፲ ዓ.ም የሚከበረውን በዓለ መስቀል በማስመልከት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተዘጋጀው ልዩ ዕትም መጽሔት በገጽ 12 – 13 እንደተጠቀሰው፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ካልዕ በሕንድ ምሥራቅና ማላንካራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቶማስ መንበረ ፓትርያርክ ሰባተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማርቶማ ዲዲሞስ ቀዳማዊን በመተካት ከስምንት ዓመታት በፊት ስምንተኛው ፓትርያርክ ኾነው ተሹመዋል፡፡
የምስል ወድምፅ ዝግጅቱ ተመርቆ በነጻ ተሠራጨ
በመናፍቃን ተታለው የተወሰዱ ምእመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ እና በሚሊዮን የሚቈጠሩ ወገኖችን በማስተማር የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ማድረግ ማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ ነድፎ ከሚያከናውናቸው ዐበይት ተግባራቱ መካከል መኾናቸውን የጠቀሱት ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ውብእሸት ኦቶሮ ናቸው፡፡ የምስል ወድምፅ ዝግጅቱን ለምእመናን በነጻ ለማዳረስ መወሰኑ ማኅበረ ቅዱሳን ሕዝበ ክርስቲያኑ በሃይማኖቱ ጸንቶ እንዲኖር ለማበረታታት እና የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲፋጠን ለማድረግ የሚተጋ ማኅበር ለመኾኑ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል – ዋና ጸሐፊው፡፡ ከዚህ የበለጠ ብዙ ሥራ ከማኅበሩና ከምእመናን እንደሚጠበቅም አስታውሰዋል፡፡
በሁለት ቋንቋዎች ብቻ የሚግባቡና በቍጥር ከዐሥር ሚሊዮን የማይበልጡ ምእመናን የሚገኙባት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከስምንት በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዳሏት ያወሱት አቶ ውብእሸት፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙና ወደ አምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን ባለቤት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ብቻ በቂ አለመኾኑን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ይህን ጉዳይ የተገነዘበው ማኅበረ ቅዱሳን፣ የአየር ሰዓት በመከራየት በአሌፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ በማስታወስ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብሩን አጠናክሮ ለመቀጠል ያመች ዘንድ በገንዘብም፣ በቁሳቁስም፣ በሐሳብም ምእመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ ዋና ጸሐፊው ጠይቀል፡፡
ዘመነ ክረምት – የመጨረሻ ክፍል
ዘመነ ክረምት ዕፀዋቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በሪቅ፣ በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፤ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ዅሉ እኛም ተወልደን፣ አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፤ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፤ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፤ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡ በመኾኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በእርሻ ልቡናችን በመዝራት (በመጻፍ) እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡
ተአምረ ማርያም በጼዴንያ
‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፷፯፥፴፭) እግዚአብሔር አምላካችን በልዩ ልዩ መንገድ ለሰው ልጅ ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ከዓለት ላይ ውኃ እያፈለቀ ሕዝቡን ያጠጣል፡፡ እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸውም፣ በልብሳቸውም፣ በጥላቸውም ሙታንን በማስነሣት፤ ሕሙማንን በመፈወስ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው፤ ቅዱስ ጳውሎስም በልብሱ ቅዳጅ ያደርጓቸው የነበሩ ተአምራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከግዑዝ ዓለት ውስጥ ውኃ የሚያፈልቅ አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዶ ካከበራት ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዝ እንዲፈስ ቢያደርግ ምን ይሳነዋል? ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጣቸው ጸጋ በልብሳቸውና በሰውነታቸው ጥላ ተአምራትን ማድረግ እንደ ተቻላቸው ዂሉ አምላክን በማኅፀኗ የተሸከመችው ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምም በሥዕሏ ወዝ ብዙ ሕሙማንን መፈወስ ይቻላታል፡፡ ከቅዱሳን ልብስና ጥላ የእርሷ ሥዕል ይከብራልና፡፡
ዘመነ ክረምት – ክፍል ስምንት
በማቴዎስ ወንጌል ፲፫፥፩-፳፫ ተጽፎ እንደምናገኘው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ሕይወትን ከዘርና ፍሬ ጋር በማመሳሰል አስተምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ገበሬ ዘር ሲዘራ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ከመብቀሉ በፊት በወፎች እንደ ተበላ፤ በጭንጫ ላይ የተጣለውም ወዲያውኑ ቢበቅልም ነገር ግን ጠንካራ ሥር ስለማይኖረው በፀሐይ ብርሃን እንደ ጠወለገ፤ በእሾኽ መካከል የወደቀው ደግሞ ሲበቅል በእሾኽ እንደ ታነቀ፤ ከዂሉም በተለየ መልኩ በመልካም መሬት ላይ የተጣለው ዘር ግን አድጎ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ እንደ ሰጠ የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህም ምሳሌ አለው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተረጐመው በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ክርስቲያን ምሳሌ ነው፤ ሙሉ እምነት ስለማይኖረው በመከራው ጊዜ አጋንንት ይነጥቁታልና፡፡ በጭንጫ ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል፣ ነገር ግን ተግባራዊ የማያደርግ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምእመን በጠንካራ እምነት ላይ የጸና አይደለምና በሃይማኖቱ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ይሰናከላል፡፡ በእሾኽ መካከል የተዘራውም ቃሉን የሚሰማ ነገር ግን በዚህ ዓለም ዐሳብና ባለጠግነት ተታሎ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር
የዘመናት አከፋፈል በአራቱ ወንጌላውያን እና ዘመን የሚለወጥበት ሰዓት
ማቴዎስ ዘመኑን ከምሽቱ ፩ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከሌሊቱ ፮ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
ማርቆስ ዘመኑን ከሌሊቱ ፯ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከጠዋቱ ፲፪ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
ሉቃስ ዘመኑን ከጠዋቱ ፩ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከቀኑ ፮ ሰዓት (በቀትር) ይፈጽማል፡፡
ዮሐንስ ዘመኑን ከቀኑ ፯ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከቀትር በኋላ ከምሽቱ ፲፪ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
ዝክረ ዐውደ ዓመት
ዘመን በተለወጠ ቍጥር ከሰው ልጆች ስሜት ጋር አብሮ የሚንቀሳቀስ ተስፋ አለ፡፡ በጥፋት ዘመን ሰማይ በደመና ተሸፍኖ፣ ከላይ ዝናም፣ ከታች የሚፈልቀው ጎርፍ የኖኅ ሰዎችን አስጨንቋቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ምድር ላይ ለውጥ ታየ፡፡ ነፋስ ነፈሰ፡፡ ብርሃን ፈነጠቀ፡፡ አበባ አበበ፡፡ የኖኅ መልእክተኛ የኾነችው ርግብም ‹‹ማየ አይህ ነትገ፤ የጥፋት ውኃ ጐደለ›› እያለች ርጥብ ቄጠማ በአፏ ይዛ መጥታ ስታበሥረው የኖኅ ሰዎች ከመርከቧ ወደ መሬት ሲወርዱ በመጀመሪያ አበባ፣ እንግጫ፣ ቄጠማ፣ የለመለመ ሣር … አገኙ፡፡ እግዚአብሔርንም በአንቃዕድዎ ልቡና አመሰገኑና በዓላቸውን አከበሩ፡፡ በዚህም አምሳል ክረምት አልፎ መሬት በምታሸበርቅበት በምታብበት ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ አዲስ ዓመታችንን እናከብራለን፡፡ ሰውም ከመሬት የተገኘ በመኾኑ እንደ ዕፀዋትና እንደ አበቦች ዅሉ በመስከረም ወር በተስፋ ስሜት ይለመልማል፡፡ ያጣው አገኛለሁ፣ የታመመው እድናለሁ ብሎ በቁርጥኝነት ይነሣሣል፡፡ በዘልማድም እምነቶች ይገለጻሉ፤ ‹‹በዮሐንስ እረስ፣ በማቴዎስ እፈስ … ጳጕሜ ሲወልስ ጎታህን አብስ … ጳጕሜ ሲበራ ስንዴህን ዝራ›› እያሉ ገበሬዎች ይናገራሉ፤ ይተነብያሉ፡፡ ገበሬዎች ገና በግንቦት ወር የክረምቱን አገባብ ለይተው የሚዘሩትን ዘር ደንብተው የሚያውቁ ሜትሮሎጂስቶች (የአየር ጠባይዕ ትንበያ ባለሙያዎች) ናቸው፡፡
በአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት
የተወደዳችሁ ምእመናን! ‹‹ዐዘቅቱ ዅሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ዅሉ ዝቅ ይበል፡፡ ጠማማውም የቀና መንገድ ይኹን፡፡ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይኹን፡፡ ሥጋም የለበሰ ዅሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ›› ተብሎ እንደ ተነገረው (ሉቃ. ፫፥፫-፮) በኑፋቄ የጎደጎደው ሰውነታችንን በቃለ እግዚአብሔር በመሙላት፤ በትዕቢት የደነደነውን ተራራውን ልቡናችንን በትሕትና በማስገዛት፤ በክፋት የተጣመመው አእምሯችንን በቅንነት በማስጓዝ፤ በኀጢአት የሻከረውን ልቡናችንን በንስሐ በማስተካከል አዲሱን ዓመት የመልካም ምግባር ዘመን እናድርገው፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትኾኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ›› በማለት እንዳዘዘን (፩ኛ ቆሮ.፭፥፯)፣ በኀጢአት እርሾ የተበከለውን ሰውነታችንን በጽድቅ ሕይወት እናድሰው፡፡ በአዲሱ ዓመት በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር ከቻልን ከጊዜ ጋር የሚጣጣም አዲስ ሕይወት ይኖረናል ማለት ነው፡፡
በአውሮፓ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ ተካሔደ
በጥናት ጉባኤው ማጠናቀቂያ ዕለትም ከጥናት አቅራቢዎች መካከል ፕሮፌሰር ዴቪድ ፊልፕሰን ‹‹በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ይህን ዐውደ ጥናት በማዘጋጀቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ የሚሠሩ ምርምሮችን ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጋር ለመወያየት እድል ፈጥሮልኛል›› በማለት አስተያየት ከሰጡ በኋላ ዐውደ ጥናቱን ያዘጋጀውን ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነዋል፡፡ ሌሎች ጥናት አቅራቢዎችና ተሳታፊዎችም በጉባኤው እንደ ተደሰቱ ገልጸው ወደፊትም ይኽን ዓይነቱ የጥናት ጉባኤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም ለዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ለሉንድ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ሰበካ ጉባኤ፣ ለሉንድ ዩኒቨርሲቲ፣ ለፕሮፌሰር ሳሙኤል ሩቢንሰን፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ላቀረቡና መልእክት ላስተላለፉ ምሁራን፣ ለተጋባዥ እንግዶች እና በጉባኤው ለተሳተፉ ምእመናን የዐውደ ጥናት ዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በኮሚቴው፤ ዲያቆን ዓለምነው ሽፈራው ደግሞ በአውሮፓ ማእከል ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡