“ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ፡፡” ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ቁ.6

 

ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ዳዊት ሕይወት የተከወናውን በምሥጢር ስቦ አምጥቶ የሰማዕታትን ክብር አጎልቶ ተናግሮበታል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትን እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል አነገሠው፡፡ በዙሪያው የነበሩ ኤሎፍላዊያንን አጥፍቶ ደብረ ጽዮንን /መናገሻ ከተማውን/ አቅንቶ ሲኖር ከዕለታት አንድ ቀን ዳዊት ታመመ፡፡የዳዊትን መታመም ሰምተው፣ ካሉበት ተነስተው የዳዊትን ከተማ በተለይም ቤተልሔምን ከበቧት፡፡ ዳዊት ይህን ሰምቶ “ወይ እኔ ዳዊት! ድሮ ታመምሁና ጠላቶቼ ሰለጠኑ ሲል የኀያላኑን ልቦና ለመፈተን ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባመጣልኝ?” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች ሦስቱ ማለትም አዲኖን፣ ኢያቡስቴ ኤልያና ረዋታቸውን /የውኃ መያዣ/ ይዘው፣ ጦራቸውን አሰልፈው፣ ጠላቶቹን ድል ነስተው፣ ዳዊት ሊጠጣ የወደደውን ውኃ አመጡለት፡፡ቅዱስ ዳዊትም ያንን ውኃ አፈሰሰው “ለምን አፈሰስከው?” ቢሉት “ደማችሁን መጣጠት አይደለምን?” ብሎ፤ ይህም ከጽድቅ ገብቶ ተቆጠረለት፡፡ 2ሳሙ.23፥13-17

አባቶቻችን ይህንን ሲያመሰጥሩት የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ አባታችን አዳም ከተድላ ገነት ወደ ምድረ ፋይድ፥ ከነጻነት ወደ መገዛት፥ ከልጅነት ወደ ባርነት፥ በወረደና ፍትወታት እኩያት ኀጣውእ በጠላትነት በተነሱበት ጊዜ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተገኘ ከጌታ ጎን የተገኘ ማየ ገቦ ይጠጣ ዘንድ ወደደ፡፡ የትሩፋት አበጋዞች ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ፈጥነው ተነሱ፡፡ በአጋንንት ከተማ ተዋጉለት ይጠጣው ዘንድ የወደደውን ማየ ገቦ አመጡለት፡፡ ማለትም የአዳም ልጅነት በከበረው የክርስቶስ የደሙ ፈሳሽነት የሥጋው መሥዋዕትነት ተመለሰለት፡፡ ይህንን ለአዳምና ለልጆቹ የባህርይ አምላክ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን ፀዋትወ መከራ እያሰቡ ሰማዕታት በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጥለው “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ሰገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” ብለው ደማቸውን አፈሰሱ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፡፡ /ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ዘሐሙስ/

“ሰማዕት” ማለት ምስክር ማለት ነው፡፡ ይህ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ማፍሰስ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፥ የዳዊት ወታደሮች ስለ ዳዊት ፍቅር ብለው “ደማችን ይፍሰስ” እንዲሉ፤ ዳዊትም ያመጡለትን ውኃ መጠጣት ደማችሁን እንደመጠጣት ነው ብሎ በፍቅር ምክንያት ውኃውን እንዳፈሰሰው፥ ይህም ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት፥ የእግዚአብሔር ወዳጆች የሆኑ ቅዱሳን ሰማዕታትም እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር ሃይማኖት የሆነችው እውነተኛይቱን ሃይማኖት ወደው ደማቸውን አፈሰሱ፣ አጥንታቸውን ከሰከሱ፣ ስለዚህ እንደ ፀሐይ አብርተው በሰማያት ዛሬም ስለ እኛ እየማለዱ አሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስባቸዋለች፡፡ ሐምሌ 5 ሰማእትነት የተቀበሉበት ቀን መታሰቢያቸውን ታዘክራለች፡፡ ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘርኀ ሐምሌ ዕለቱን በማስመለከት ያገኘነውን መረጃ እንዲህ ተዘጋጅቷል፡፡

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሐምሌ አምስት በዚች ቀን የክቡራንና የዐበይት አባቶቻችን ሐዋርያት የጴጥሮስና የጳውሎስ የሰማዕትነታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ሰላም ለከ ጴጥሮስ ተልሚድ፡፡ ዘኢያቅበጽከ ተስፋ ነገረ ኑፋቄ ወካህድ፡፡ እንዘ ትረውጽ ጥቡዐ ለመልእክተ ክርስቶስ ወልድ፡፡ አመ ለሊከ ወሬዛ ቀነትከ በእድ፡፡ ወአመ ልህቀ አቅነትከ ባዕድ፡፡

ይህም ጴጥሮስ ከቤተ ሳይዳ ነበር ዓሣ አጥማጅም ነበር ጌታችንም ከተጠመቀባት ዕለት ማግሥት አግኝቶ መረጠው፤ ከእርሱ አስቀድሞም ወንድሙ እንድርያስን አግኝቶ መረጠው፡፡ መድኃኒታችንንም እስከ መከራው ጊዜ ሲአገለግለው ኖረ፤ ፍጹም ሃይማኖት፣ ለጌታውም ቅንዓትና ፍቅር ነበረው፡፡ ስለዚህም በሐዋርያት ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡

ጌታችንም ሰዎች ማን እንደሆነ ማንም እንደሚሉት ስለ ራሱ በጠየቃቸው ጊዜ ሌሎቹ ኤርምያስ ይሉሃል ወይም ኤልያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል አሉት፡፡ ጴጥሮስ ግን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህ አለ፡፡ ጌታችንም የሃይማኖት አለት የቤተ ክርስቲያንም መሠረት ነህ ብሎ ብፅዕና ሰጠው የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻ ቁልፍ ሰጥቼሃለሁ አለው፡፡

አጽናኝ የሆነ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ከተቀበለ በኋላ ተናጋሪዎች በሆኑ በዚህ ዓለም ተኲላዎች መካከል ገባ በውስጣቸውም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ፤ ቊጥር የሌላቸው ብዙዎች አሕዛብንም መልሶ የዋሆች ምእመናን አደረጋቸው፡፡

ጌታችንም የማይቈጠሩ ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችን በእጆቹ አደረገ፤ ጥቅም ያላቸው ሦስት መልእክቶችንም ጽፎ ለምእመናን ላካቸው፡፡ ለማርቆስም ወንጌሉን ተርጒሞ አጽፎታል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ፤ የከተማው መኳንንት ወደሚሰበሰቡበት ወደ ታላቁ የጨዋታ ቦታም ሔዶ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብሎ ተናገረ የሚራሩ ብፁዓን ናቸው ለርሳቸውም ይራሩላቸዋልና የዚህንም ተከታታይ ቃሎች ተናገረ፡፡ ከዚያም ከዚያ የነበሩ አራት የደንጊያ ምሰሶዎችም በሚያስፈራ ድምፅ አሜን አሉ፤ የተሰበሰቡትም ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ ደነገጡ፡፡ ከሰባ ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያደረበት አንድ ሰው ነበረ፤ ከእነዚያ ደንጋዮች ቃልን ስለ ሰማ ያን ጊዜ ጋኔኑ ጣለው ከእርሱም ወጥቶ ሔደ፡፡ መኳንንቱም ፈርተዋልና ስለዚህ ነገር እያደነቁ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡

ከከተማ መኳንንቶችም ቀውስጦስ የሚባል አንዱ ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ስሟ አክሮስያ ለምትባል ሚስቱ ዓለምን ስለ መተው ለድኆችም ስለመራራትና የመሳሰለውን ቃል ጴጠሮስ እንዴት እንዳስተማረ ነገራት፡፡ እርሷም በሰማች ጊዜ በልቧ ነቅታ ይህ ነገር መልካምና ድንቅ ነው አለች፡፡ ጴጥሮስ ያስተማረውንም ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በአንድነት ተስማሙ ከዚህም በኋላ ገንዘባቸውን ሁሉ ለድኆች ሰጡ ከዕለት ራት በቀር ምንም አላስቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ንጉሡ ስለ መንግሥት ሥራ ከርሱ ጋራ ለመማከር በቶሎ እንዲደርስ ወደርሱ መልእክትን ላከ፡፡

ቀውስጦስም ይህን በሰማ ጊዜ ገንዘብ ስላልነበረው ፈርቶ ደነገጠ ተጨነቀም፡፡ ምክንያትም አመካኝቶ ይሠወር ዘንድ ከሚስቱ ጋራ ተማከረ፡፡ እርሷ ግን ምክንያት አታድርግ ነገር ግን ወደ ንጉሡ ሒድ የጴጥሮስም አምላክ ጐዳናህን ያቅናልህ አለችው፤ እርሱም ነገርዋን ተቀብሎ ወደ ንጉሡ ሔደ፤ በመንገድም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ብዙ በረከትን አገኘ፡፡ ወደ ንጉሡም ደረሰ፤ ንጉሡም በደስታና በክብር ተቀበለው፡፡

ከሦስት ዓመት በኋላም ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ሁለቱ ልጆቹ የተመረዘ ውኃ ጠጥተው እነሆ ሙተው ነበር፤ ሚስቱም ለእርሱ መንገርን ፈራች ብዙ ምሳሌዎችን ከመሰለችለት በኋላ ነገረችው፡፡ በሰማ ጊዜም እጅግ አዝኖ አለቀሰ፡፡ ሚስቱም እንዲህ አለችው ጌታዬ ሆይ ልባችን የሚጽናናበትን እርሱ ያደርግልናልና የጴጥሮስን ፈጣሪ እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡ ሊጸልዩም በጀመሩ ጊዜ ቀውስጦስና አክሮስያ ሆይ የደቀ መዝሙሬ የጴጥሮስን ቃል ስለሰማችሁና ስለተቀበላችሁት ስለዚህ ልጆቻችሁን በሕይወታቸው እሰጣችኋለሁ የሚል ቃልን ከሰማይ ሰሙ ያን ጊዜም ልጆቻቸው ድነው ተነሡ ቀውስጦስና ሚስቱም ደስ አላቸው የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡

አሊህም ከሞት የተነሡ ልጆች ለቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሮቹ ሆኑ፤ የአንዱ ስሙ ቀሌምንጦስ ነው እርሱም ቅዱስ ጴጥሮስ ያየውንና ጌታችን በሥጋ ወደ ሰማይ በሚዐርግ ጊዜ የገለጠለትን ምሥጢር ሁሉ የነገረው ነው፤ ሰዎች ሊያዩአቸው የማይገባቸውን መጻሕፍትን አስረከበው፡፡ ይህንም ቀሌምንጦስን ሊቀ ጵጵስና ወንድሙን ዲቁና ሾማቸው፡ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ቅዱስ ጴጥሮስ አምላክን የወለደች የንጽሕት ድንግል እመቤታችን ማርያም ክብርዋን በምሳሌ አየ፡፡

በቀስት አምሳል ደመናን አይቷልና በላይዋም የብርሃን ድንኳን ነበረ በድንኳኑም ውስጥ አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም ተቀምጣለች፡፡ በእጆቻቸው ውስጥ የነበልባል ጦሮችንና ሰይፎችን የያዙ መላእክትና የመላእክት አለቆች በዙሪያዋ ነበሩ፡፡ እንዲህም እያሉ ያመሰግኗት ነበር ከእርሷ የድኅነት ፍሬ የተገኘ የሠመረች የወይን ተክል አንች ነሽ፡፡ ማሕፀንሽ የእግዚአብሔርን በግ የተሸከመ ንጽሕት አዳራሽ አንቺ ነሽ፡፡

ሁለተኛም እንዲህ ይሏት ነበር፡፡ የብርሃን እናቱ ሆይ የምሕረት መገኛ ሆይ ደስ ይበልሽ የአማልክት አምላክ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የሆነ የመድኅን ዙፋን ሆይ ደስ ይበልሽ ክብርና ምሥጋናን የተመላሽ የፍጥረት ሁሉ እመቤት ደስ ይበልሽ፡፡

መላእክትም ምሥጋናዋንና ሰላምታዋን በአደረሱ ጊዜ ክብር ምሥጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእርስዋ ተገልጦ ከእርስዋ በቀር ማንም ሊያውቀው የማይቻል ነገርን ነገራት ወዲያውኑም ምድር ተናወጸች ሊነገር የማይቻል ምሥጢራትንም ገለጠላት፡፡

ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን በሀገሩ ሁሉ ቅዱስ ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ጴጥሮስን አዘዘው፡ ጴጥሮስም ወጥቶ ሔደ፤ ኢዮጴ ወደምትባል የባሕር ዳርቻና ልድያ ወደምትባል አገር ደረሰ፡፡

በአንዲት ዕለትም በኢዮጴ ሳለ ብርህት ደመና ዞረችው፡፡ እነሆም ሰፊ መጋረጃ ወደ እርሱ ወረደች፤ በውሰጥዋም የእንስሳት የምድረበዳ አውሬዎችና የሰማይ አዕዋፍ አምሳል ነበረ፡፡ ጴጥሮስ ሆይ ተነስና አርደህ ብላ የሚል ቃልም ከሰማይ ጠራው፡፡ ጴጥሮስም አቤቱ አይገባኝም ርኩስ ነገር አልበላም ወደ አፌም ከቶ አልገባም አለ፡፡

ያም ቃል ዳግመኛ ጠራውና እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው አትበል አለው፡፡ ያም ቃል ሦስት ጊዜ መላልሶ እንዲህ ነገረው፡፡ በየንግግሩም ወደ እሪያዎች ወደ አራዊትና ወደ አዕዋፍ ስዕሎች ያመለክተው ነበር፤ ከዚህም በኋላ ያቺ መጋረጃ ወደ ሰማይ ተመለሰች፡፡

ጴጥሮስም ስላየው ራዕይ አደነቀ፤ ይህም ራዕይ ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር የሚመለሱ አሕዛብን ስለመቀበል እንደሆነ አስተዋለ፤ ለወንሞቹ ሐዋርያትም አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስንም ከወገኖቹ ጋር እንዳጠመቀው ነገራቸው፡፡

ከዚህ በኋላም ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋራ ጌታችን እንዳዘዛቸው ወደ አንጾኪያ ከተማ ገቡ፡፡ የአገሪቱንም ሁኔታ ይጠይቅ ዘንድ ጴጥሮስ ዮሐንስን ላከው ሰዎችንም አግኝቶ ክፉ ነገር ተናገሩት፡፡ ሊገድሉትም ፈለጉ፤ እያለቀሰም ተመለሰ፤ ሰውነቱም ተበሳጨች ጴጥሮስንም አለው አባቴ ሆይ የእሊህ ጎስቋሎች ክፋታቸው እንዲህ ከሆነ ወደ ነገሥታቱና ወደ መኳንንቱ ገብተን በጌታችን ስም በሰበክን ጊዜ ምን እንሆን ይሆን እንዴትስ ሃይማኖትን እናስተምራለን፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ወዳጄ ሆይ የሃያውን ቀን መንገድ በአንዲት ሌሊት ያመጣን እርሱ ሥራችንን በአንዲት መልካም ያደርግልናልና አትፍራ፤ አትዘንም አለው፡፡ከዚህም በኋላ ወደ ከተማ መካከል ገብተው ክብር ይግባውና በጌታችን ስም ሰበኩ የከተማው ሰዎችና የጣዖታቱ አገልጋዮችም በእነርሱ ላይ ተሰበሰቡ ታላቅ ድብደባንም ደበደቧቸው፤ አጎሳቆሏቸውም፤ ግማሽ የራስ ጠጉራቸውንም ላጭተው ተዘባበቱባቸው፤ አሥውም በግንብ ውስጥ ጣሏቸው፡፡

ከዘህም በኋላ ተነሥተው ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ፤ ወዲያውኑም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኪሩቤልና ሱራፌል እያጀቡት ተገለጠላቸውና እንዲህ አላቸው፡፡ መረጥኋችሁ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሆይ በዘመኑ ሁሉ እኔ ከእናነተ ጋራ እኖራለሁና አትፍሩ፤ አትዘኑም፡፡ ለመዘባበቻም በራሳችሁ መካከል ስለላጩአችሁ አታድንቁ ይህም መመኪያና ክብርን የክህነት ሥርዓትና ምልክትንም ይሆናችኋል፡፡ ካህን የሚሆን ሁሉ ያለዚህ ምልክት ሥጋዬንና ደሜን ማቀበል አይችልም፡፡

ይህ ምልክት እያለው የሚሞት ካህንም ኃጢአቱ ይሠረይለታል፡፡ ይህን ካላቸው በኋላ ከእርሳቸው ዘንድ በክብር ዐረገ፡፡ ከዚህም በኋላ ጳውሎስ መጥቶ ዮሃንስን ተገናኘው የዚህ አገር ሰዎች ያደረጉብህ ምንድነው እርሱም ስለ እኔ አታድንቅ የሐዋርያትንም አለቃ በእኔ ላይ ባደረጉት አምሳል አድርገውበታልና አለው፡፡ ጳውሎስም አጽናናቸው እንዲህም አላቸው እኔ በጌታችን ፈቃድ ወደ ከተማ ውስጥ ገብቼ እናንተንም አስገባችኋለሁ፡፡

ከዚህም በኋላ ጳውሎስ ሔዶ ምክንያትን ፈጠረ ጣዖታቸውንም እንደሚያመልክ መስሎ ሐዋርያትን እንዲያቀርቡለትና ስለ ሥራቸውም እንዲጠይቃቸው የከተማውን መኳንንት አነጋገራቸው፡፡መኳንንቱም ወደ ጳውሎስ እንዲያቀርቧቸው አዘዙ፤ በቀረቡም ጊዜ ጳውሎስ ስለ ሥራቸው ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ድንቆችንና ተአምራቶችን ለሚያደርግ ለክርስቶስ ደቀ መዝሙሮቹ እንደሆኑ ነገሩት፡፡ ዳግመኛም እናንተ እንደርሱ ማድረግ ትችላላችሁን አላቸው፡፡ እነርሱም አዎ በእርሱ ስም ሁሉን ሥራ መሥራት እንችላለን አሉት፡፡

ከዚህም በኋላ ከእናቱ ማሕፀን ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዐይኑን አበሩ፡፡ የንጉሡንም ልጅ ከሞተ በሦስት ወሩ ሥጋውም ከተበላሸ በኃላ ከመቃብር አስነሡት፡፡ ንጉሡና የከተማ ሰዎች ሁሉ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡ ጴጥሮስም ምድሩን ረግጦ ውኃን አፈለቀ፤ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው በቀናች ሃማኖትም እንዲጸኑ አደረጓቸው፡፡

ከዚህም በኋላ በሎዶቅያ ያሉ ምእመናን የቂሳሮስ ባሕር ከወሰኑ አልፎ ብዙ ሰዎችን ከአትክልት ቦታዎቻቸውና ከከብቶቻቸው ጋራ እንዳሰጠማቸው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ላኩ፤ ጴጥሮስም ተወዳጅ ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላከ፡፡ዮሐንስም ወደ እነርሱ ሲጓዝ ዳና በግ አገኘ፤ በጉንም እንዲህ ብሎ ላከው፤ ወደ ቂሳሮስም ወንዝ ሒድ የክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ወደ አንተ ልኮናል ወደ ቀድሞው ወሰንህ ትገባ ዘንድ አንተ በእግዚአብሔር ቃል የታሰርክ ነህ ብሎሃል በለው፡፡ ያን ጊዜ በጉ እንዳዘዘው አደረገ፤ ወንዙም ሸሽቶ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ቁጥር የሌላቸው ብዙዎች የከተማ ሰዎችም ይህን አይተው በጌታ አመኑ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ አልፎ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ በዚህም ሥፍራ መሠሪው ሲሞን ተቃወመው፤ እርሱንም ከአየር ላይ አውርዶ ጥሎ አጠፋው፤ ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ብዙዎች ሕዝቦች አመኑ፡፡ የከተማው ገዥ የአክሪጶስ ቁባቶችም የጴጥሮስን ትምህርት ተቀበሉ፡፡ ሌሎችም የከበሩ ብዙዎች ሴቶች ትምህርቱን በመቀበል ከባሎቻቸው ርቀው ንጽሕናቸውን ጠበቁ፡፡

ስለዚህም ነገር ቅዱስ ጴጥሮስን ሊገድሉት የሮሜ መኳንንት ተማከሩ፡፡ የአልታብዮስ ሚስትም እንዳይገድሉት ከሮሜ ከተማ ወጥቶ እንዲሔድ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ላከች፤ ምእመናን ወንድሞችም ውጣ አሉት፤ እርሱም ቃላቸውን ተቀበለ፡፡ ትጥቁንም ለውጦ ከከተማው ወጣ፡፡ በሚወጣበትም ጊዜ መስቀል ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲገባ ጌታችንን አገኘውና አቤቱ ጌታዬ ወዴት ትሔዳለህ አለው፡፡ ጌታም ልሰቀል ወደ ሮሜ ከተማ እሔዳለሁ ብሎ መለሰለት፤ ቅዱስ ጴጥሮስም አቤቱ ዳግመኛ ትሰቀላለህን አለው፡፡

ያን ጊዜም ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ እጅህ ታጥቀህ ወደ ወደድከው ትሔዳለህ በሸመገልክ ጊዜ ግን እጅህን ታነሣና ሌላ ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል ያለውን የጌታችንን ቃል አሰበ አስተዋለውም፡፡ያን ጊዜም ወደ ከተማው ተመልሶ ክብር ይግባውና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን ለወንድሞች ነገራቸው እነርሱም እጅግ አዘኑ፡፡

ንጉስ ኔሮን ቅዱስ ጴጥሮስን እንዲሰቅሉት አዘዘ፡፡ ሊሰቅሉትም በያዙት ጊዜ ወታደሮችን እንዲህ ብሎ ለመናቸው፡፤ የክብር ንጉስ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ላይ ሆኖ ስለተሰቀለ እኔ ቁልቁል ልሰቀል ይገባኛል፡፡ ወዲያውም እንደነገራቸው ሰቀሉት፡፡ ተሰቅሎ ሳለም ለምእመናን የሕይወትን ቃል አስተማራቸው በቀናች ሃማኖትም እንዲጸኑ አዘዛቸው ከዚህም በኋላ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን በቅዱስ ጴጥሮስ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡ ሰላም ለጳውሎስ ሃይማኖተ ክርስቶስ ዘአግሀደ፡፡ እስከ አቁሰልዎ በሰይፍ ወመተርዎ ክሣደ፡ ከመ ያግብእ ሕዝበ ሕየንተ ቀዳሚ ሰደደ፡፡ በላዕለ አብዳን ተመሰለ አብደ፡፡ ወለአይሁድኒ ኮኖሙ አይሁድ፡፡

በዚህችም ቀን ዳግመኛ ልሳነ ዕረፍት የክርስቶስ አንደበት የእውቀት አዘቅት የቤተ ክርስቲያን መብራት የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰማዕትነቱ መታሰቢያ ነው፡፡ እንደ ስሙም ትርጓሜ መሪ አመስጋኝ ወደብ ጸጥታ ነው፡፡ይህም ጳውሎስ አስቀድሞ በክርስቶስ ያመኑትን የሚያሳድድ ነበረ፡፡ እርሱም ከብንያም ወገን የፈሪሳዊ ልጅ ነው፡፡ ወላጆቹም ሳውል ብለው ስም አወጡለት፤ ትርጓሜውም ስጦታ ማለት ነው፡፡ ቁመቱ ቀጥ ያለ፤ መልኩ ያማረ፤ ፊቱ ብሩህ፤ ቅላቱ እንደ ሮማን ቅርፍት ደበብ ያለ፤ ዐይኑም የተኳለ የሚመስል አፍንጫው ቀጥ ያለ ሸንጎበታም፤ ጉንጩ እንደ ጽጌረዳ ነበረ፡፡

እርሱም ሕገ ኦሪትን አዋቂ ነበረ፡፡ ለሕጉም ቀናተኛ ሆኖ ምእመናን አሳዳጅ ነበረ፡፡ ወደ ሊቀ ካህናቱም ሔዶ በመንገድ የሚያገኘው ሰው ቢኖር ወንዶችንና ሴቶችን እንደታሠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይመልሳቸው ዘንድ ለደማስቆ ከተማና ለምኩራቦች የፈቃድ ደብዳቤ ለመነ፡፡

ሲሔድም ወደ ደማስቆ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜ ድንገት ከሰማይ መብረቅ ድንገት ብልጭ አለበት፤ በምድር ላይም ወደቀ፤ ወዲያውም ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የሚለውን ቃል ሰማ፡፡ ሳውልም አቤቱ አንተ ማነህ አለው፤ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾለው ብረት ላይ ብትረግጥ አንተን ይጎዳሃል አለው፡፡

እየተንቀጠቀጠም አደነቀ፤ አቤቱ ምን እንዳደርግ ትሻለህ አለው፡፡ ጌታም ተነሥና ወደ ከተማ ግባ ልታደርግ የሚገባህን ከዚያ ይነግሩሃል አለው፡፡ ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩ ሰዎችም ንግገሩን ይሰሙ ነበር፤ ነገር ግን የሚያዩት አልነበረም፡፡ ሳውልም ከምድር ተነሣ ዓይኖቹም ተገልጠው ሳሉ አያይም ነበር፤ እየመሩም ወደ ደማስቆ አስገቡት፡፡ በዚያም ሳያይ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ሰነበተ፡፡

በዚያም በደማስቆ ከደቀ መዛሙርት ወገን ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ጌታም በራእይ ተገለጠለትና ሐናንያ ብሎ ጠራው፡፡ እርሱም ጌታዬ እነሆኝ አለ፡፡ ተነሥና ቀጥተኛ ወደምትባለው መንገድ ሒድ በይሁዳ ቤትም ጠርሴስ ከሚባል አገር የመጣ ሳውል የሚባል ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን ይጸልያልና አለው፡፡

ሐናንያ ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ አቤቱ ስለዚህ ሰው በኢየሩሳሌም በቅዱሳኖችህ ላይ የሚያደርገውን ክፉ ነገር ሁሉ ከብዙ ሰዎች ሰምቻለሁ፤ ወደዚህም ከካህናቱ አለቃ አስፈቅዶ የመጣ ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ሊያስር ነው፡፡ ጌታችንም ተነሥና ሒድ በአሕዛብና በነገሥታት በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና እኔም ስለ ስሜ መከራ ይቀበል ዘንድ እንዳለው አሳየዋለሁ፡፡

ያን ጊዜም ሐናንያ ሔደ፤ ወደ ቤትም ገባ፡፡ ወንድሜ ሳውል በመንገድ ስትመጣ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይሞላብህ ዘንድ ወዳነተ ልኮኛል አለው፡፡ ያን ጊዜም የሸረሪት ድር የመሰለ ከዐይኖቹ ላይ ተገፎ ወደቀ፡፡ዐይኖቹም ተገለጡ፡፡ ወዲያውም አየ ተነሥቶም ተጠመቀ፡፡ እህልም በልቶ በረታ፡፡ ከደቀ መዛሙርትም ጋር በደማስቆ ለጥቂት ቀን ሰነበተ፡፡ በዚያው ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰበከ፤ አስተማረም፡፡

የሰሙትም ሁሉ አደነቁ እንዲህም አሉ፤ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያሳድድ የነበረ ይህ አልነበረምን ወደዚህስ የመጣው እያሠረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሊወስዳቸው አይደለምን፡፡ አጽናኝ መንፈስ ቅዱሰም አደረበት ዕውነተኛውንም ሃይማኖት ግልጽ አድርጎ አስተማረ፡፡

ለኦሪት ሕግ የሚቀና እንደነበረ እንዲሁ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠራት ሕገ ወንጌል ዕጽፍ ድርብ ቅንዓትን የሚቀና ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ በአገሮች ሁሉ እየዞረ ሰበከ፤ በጌታችንም ስም ሰበከ፡፡ ድንቆችንና ተአምራትንም አደረገ፡፡ ቁጥር የሌላቸው አሕዛብንም አሳመናቸው ነገር ግን ብዙ ጊዜ በመገረፍ በመደብደብና በመታሠር ብዙ መከራ ደረሰበት፤ መከራውንም ሁሉ ታግሶ በሁሉ ቦታ ዞሮ አስተማረ፡፡

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደተጻፈ የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ ሲጾሙና ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ እኔ እነርሱን ለመረጥሁለት ሥራ ሳውልንና በርናባስን ለዩልኝ አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ጾመውና ጸልየው እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሙአቸው፤ ከመንፈስ ቅዱስም ተሹመው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፡፡

በደሴቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፉ ወደምትባል አገር ደረሱ፡፡ በዚያም ሐሰተኛ ነቢይ የሆነ ስሙ በርያሱስ የሚባል አንድ ሥራየኛ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባል ብልህ ሰው ከሆነ አገረ ገዥ ዘንድ የነበረ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሊሰማ ወዶ በርናባስንና ሳውልን ጠራቸው፡፡ የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበርና ኤልማስ የሚሉት ያ ሥራየኛ ሰው ይከራከራቸው ነበረ፤ ገዥውንም ማመን ሊከለክለው ወዶ ነበረ፡፡

ጳውሎስ በተባለው ሳውል ላይም መንፈስ ቅዱስ መላበት፡፡ አተኩሮም ተመለከተው፤ ኃጢአትንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ የሰይጣን ልጅ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ እያጣመምህ ተው ብትባል እምቢ አልህ እነሆ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ተቃጥታለች፤ ትታወራለህ እስከ ዕድሜ ልክህም ፀሐይን አታይም አለው፡፡ ወዲያውኑም ታወረ ጨለማም ዋጠው የሚመራውንም ፈለገ፤ አገረ ገዢውም የሆነውን አይቶ ደነገጠ በጌታችንም አመነ፡፡

ከዚህ በኋላ ሒደው ወደ ሊቃኦንያ ከዚያም ወደ ልስጥራንና ደርቤን ከተማ ወደ አውራጃውም ሁሉ ገብተው አስተማሩ፡፡ በልስጥራን ከተማም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እግሩ ልምሾ የሆነ አንድ ሰው ነበረ ተቀምጦ ይኖር ነበር እንጂ ልምሾ ከሆነ ጀምሮ ቆሞ አልሔደም፡፡ ጳውሎስንም ሲያስተምር ተመልከቶ ሃይማኖት እንዳለው እንደሚድንም ተረዳ፡፡ ድምጹንም ከፍ አድርጎ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ቀጥ ብለህ ቁም እልሃለሁ አለው፤ ወዲያውኑ ተነሥቶ ሔደ፡፡

አሕዛብም ጳውሎስ ያደረገውን አይተው በጌታችን አመኑ፡፡ እርሱም በዚያ ሳለ አይሁድ ከአንጾኪያና ከኢቆንያ መጥተው ልባቸውን እንዲያስጨክኑባቸው አሕዛብንም አባበሉአቸው፡፡ ጳውሎስንም በደንጊያ ደበደቡት፤ ጎትተው ወደ ውጭ አወጡት፡፡በማግስቱም ከበርናባስ ጋራ ደርቤን ከተማ ሔዱ፡፡ በዚያችም ከተማ አስተማሩ ብዙ አሕዛብንም ሃይማኖት አስገቡ ለቤተ ክርስቲያንም ቀሳውስትን ሾሙላቸው፤ ከዚያም ወደ መቄዶንያ አልፈው ሔዱ ጋኔን ሟርት የሚያሥራትን አንዲት ልጅ አገኙ ከምታገኘው ዋጋ ለጌቶቿ ብዙ ትርፍን ታስገባ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው የሕይወትንም መንገድ ያስተምሯችኋል ብላ እየጮኸች ከጳውሎስ ኋላ ተከተለች፤ ብዙ ቀንም እንዲሁ ታደርግ ነበር፡፡ ጳውሎስንም አሳዘነችው መለስ ብሎም መንፈሰ ርኩስን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድትወጣ አዝዤሃለሁ አለው ወዲያውኑም ተዋት፡፡

ከዚህ በኋላም ሐለብ ከሚባል አገር ደረሰ፤ የጢሞቴዎስንም እናት ስሟ በድሮናን ከሞት አስነሣት፡፡ በዚያም ያዙት ለዚያች አገር ጣኦትም ሊሠዉት ወድደው በሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት፡፡ ስለ እነርሱም እየማለደ እጆቹን በመስቀል ምልክት አምሳል ዘረጋ፡፡ አሕዛብም በአዩት ጊዜ ስለዚህ ድንቅ ሥራ አደነቁ፤ ከእሳት መካከልም እንዲወጣ ማለዱት፤ ምንም ምን ሳይነካው ወጣ ሰገዱለትም ክብር ይግባውና በጌታችንም አመኑ የአገሩ ሹም አርስጦስም አመነ፡፡

ሰባቱ የጣዖት ካህናት ግን ሸሽተው ተሠወሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በጭላት አምሳል የተቀረጸውን ምስል ጠራው ምስሉም በአንባሳ አምሳል መጥቶ በምኩራቡ መካከል በጳውሎስ ፊት ቆመ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የሚያመልኩህ ካህናቶችህ ወዴት አሉ አለው፤ አንበሳውም ያሉበትን አስክነግርህ ድረስ ጌታዬ ጥቂት ታገሠኝ፤ አለው፡፡ ካህናቱም ወደተሸሸጉበት ሔዶ አንዱን አንገቱን በአፉ ይዞ እየጎተተ አምጥቶ እንደ በድን በአደባባዩ መካከል ጣለው፡፡ ሰባቱንም እንዲሁ እያንዳንዱን እየጎተተ አመጣቸው፡፡

ሕዝቡም ሊገድሏቸው ወደዱ፡፡ ጳውሎስም ዛሬ በዚህች ከተማ ማዳን እንጂ መግደል አይገባም አለ፤ ከዚህም በኋላ ሁሉንም አጠመቃቸው፤ ሃይማኖትንም አስተማራቸው፡፡ ያንንም አንበሳ የሆነ የጭላት ምስል አንበሳ ሆይ አትፍራ ስለ አገለገልከኝ እሰከምሻህ ድረስ ኑሮህ በበረሀ ይሁን አለው ያን ጊዜም ወደ በረሀ ሔደ፡፡

ጳውሎስም ከዚያ ተነስቶ አካ ወደሚባል ከተማ ሔደ፡፡ ስክንትስ ከሚባል ደቀ መዝሙርም ጋር ተገናኘ፤ አይሁድም ዜናውን ሰምተው ከአሕዛብ ጋራ ተሰበሰቡ ይዘውም ጭንቅ የሆነ ስቃይን አሰቃዩት፤ ዳግመኛም ሁለት በሮችን አመጡ ከስክንጥስ ጋራም አሥረው በከተማው ጥጋጥግ በስለታም ድንጋይ ላይ አስጎተቷቸው ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ፤ አጥንታቸውም እሰከሚታይ ድረስ ሥጋቸውም ተቆራረጠ፡፡ ወደ ጌታም ጸለዩ፤ ያን ጊዜም በሮቹ ከሚነዳቸው ጋራ ደንጊያ ሆኑ፡፡

ሕዝቡም በአዩ ጊዜ ለመኮንኑ ነገሩት እርሱም ተቆጣ ወደ እርሱም እንዲያቀርቧቸውና በደንጊያ እንዲወግሯቸው አዘዘ፤ በቅዱስ ጻውሎስም ላይ እጅግ ተቆጥቶ አንተ የሥራይ ሰው እነሆ አሠቃይሃለሁ አለው፡፡ በበሬ ቅርጽ የተሠሩ ሁለት ቀፎዎችንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፡፡ ዝፍት ሙጫና ድኝ አምጥተው በውጭ ቀላለቅለው ሁለቱን የናስ ቀፎዎች በውስጥም በውጭም ቀቧቸው፡፡ ሐዋርያትንም በውስጥ ጨምረው በእሳት ምድጃ ውስጥ አስገቧቸው፤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊትም እሳት አነደዱባቸው፡፡

መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስም ከመላእክቶቹ ጋራ መጣ እሳቱንም ከዚያ ፈልሶ ወደ ከተማ ውሰጥ ገብቶ የከተማውን ሰዎች ሁሉ እንዲከባቸው አደረገው፤ በተጨነቁም ጊዜ ጮኹ፤ አለቀሱም፡፡ መዳንን ከፈለጋችሁ ፈጥናችሁ በአደባባዩ በአንድነት ተሰብሰቡ የሚል ቃል ከሰማይ ጠራቸው፡፡ ጳውሎስም ወደ በረሀ አሰናብቶት የነበረው አንበሳ መጣ፤ ጳውሎስ በስሙ በሚያስተምርበት ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ እያለ ጮኸ፡ ከዚህም በኋላ ወደ እሳቱ ምድጃ ተመልሶ ጳውሎስንና ስክንጥስን ከእሳቱ ውስጥ ውጡ አላቸው፤ ያን ጊዜም የራሳቸው ጠጉር እንኳ ሳይቀነብር ወጡ፤ በላያቸውም ላይ የቃጠሎ ሽታ የለም፡፡

ይህንን ድንቅ ሥራ አይተው በጌታችን በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን እያሉ ጮኹ፤ ከዚህም በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው ስክንጥስንም ቅስና ሾመላቸው፡፡ከዚህ በኋላም ከሐዋርያ ፊልጶስ ጋራ ወደ ሁለት አገሮች በአንድነት ሔዱ፤ በዚያም በጌታችን ስም ሰበኩ የአገሩ አለቆችም ያዙአቸው እጆቻቸውንና እግሮቻቸውንም አሠሩአቸው በአንገቶቻቸውም የብረት ሰንሰለቶችንም አስገቡ ራሳቸውንም የሚሸፍን የብረት ቆብን ሠሩላቸው ዳግመኛም በእጅና በመሐል እጅ ጣቶችም ምሳሌ ሠርተው በእጆቻቸውና በክንዶቻቸው እያንዳንዱን የብረት እጅ ጨመሩ፡፡ ከብረቶችም ጋር ቸነከሩአቸው፡፡

ሁለተኛም እስከ አንገት የሚደርስ በትከሻ አምሳል ሠሩ፤ በፊትና በኋላም ቸነከሩአቸው፡፡ ደግሞም መላ አካላቸው ምንም እንዳይታይ የሚሽፍን የብረት ሠሌዳ ሠሩ፡፡ ከወገቦቻቸውም ጋራ ቸነከሩት፤ ችንካሮችም ተረከዛቸውን ነድለው ወደ ጭኖቻቸው እስከሚደርሱና እሰከ አቆሰላቸው ድረስ የብረት ጫማ ሠርተው እግሮቻቸውን ቸነከሩ፡፡

ደግሞ በመሸፈኛ አምሳል የብረት ሰናፊል ሠሩ፤ ቀማሚዎችም መጡ አንድ መክሊት የሚመዝን እርሳስንም አመጡ ታላቅ የብረት ጋንንም ሰባት ልጥር የሰሊጥ ቅባትን አመጡ፡፡ ስቡንና አደሮ ማሩን የእሳቱንም ኃይል አብዝቶ የሚነደውን ቅመሙን ከሙጫውና ከድኙ ጋር ቀላቀሉ፤ ከዋርካና ከቁልቋል ከቅንጭብም ደም ሰባት ልጥር አንድ የወይን አረግንና ቅባት ያላቸውን ዕንጨቶች ሁሉ አመጡ፡፡ በጋን ውስጥ ያበሰሉትንና ያሟሙትንም ልዩ ልዩ ቅመማ ቅመም አምጥተው ከሥጋቸው ጋራ እሰከሚጣበቅ በቅዱሳን ሐዋርያት ሥጋ ላይ ባሉት ሠሌዳዎች ውስጥ ጨመሩት፡፡ ከእግራቸው አስከ ራሳቸውም ከፍ ከፍ እስከሚል ድረስ በእሳት ያቃጠሉትን ያንን እርሳስ ጨመሩ፡፡ ርዝመቱ ዐስራ አምስት ክንድ በሆነ ወፍራም የጥድ ምሰሶ ላይም አቆሟቸውና ከበታቻቸው ፍሬ በሌለው በወይን ሐረግና በተልባ እሳቱን አቀጣጥለው አነደዱ፡፡ የእሳቱ ነበልባልም ከሥጋቸው በላይ ከፍ ከፍ አለ ሐዋርያ ግን ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር፡፡

ከመኳንንቱም በአንዱ ልብ ርኅራኄን አሳደረና እንዲፈቷቸው አዝዞ ፈቷቸው፡፡ በፈቷቸውና ሠሌዳውን ከሥጋቸው ላይ ባስወገዱ ጊዜ ቆዳቸው ተገፈፈና ከብረቱ ሠሌዳዎች ጋራ ወጣ፡፡ ብዙ ደምም ከሥጋቸው ጋር ፈሰሰ፡፡ ሰይጣንም በከተማው ሰዎች ልብ አደረና ሐዋርያትን ወደ እሳት ውስጥ መለሱአቸው፤ ያን ጊዜ ጌታችን ወርዶ የእሳቱን ነበልባል አጠፋው፡፡ ዝናምን የተመላች ብርህት ደመናም መጥታ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከበበቻቸው፤ በዚያችም አገር አንድ ጊዜ በደንጊያ በመውገር አንድ ጊዜም በፍላጻ በመንደፍ ብዙ ተሠቃዩ፡፡ ከዚህም በኋላ ሙታንን በአነሡ ጊዜ የከተማው ሰዎች ሁሉ አመኑ፤ አጠመቋቸውም፤ ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው፤ ካህናትንም ሾሙላቸው በቀናች ሃይማኖትም እስቲጸኑ አስተማሩአቸው፡፡ ከዚያም ወጥተው ጌታችን ወዳዘዛቸው ወደ ሌላ አገር ሔዱ፡፡

ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጳውሎስ ተገለጠለትና የመረጥኩህ ጳውሎስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን፡፡ መታሰቢያህን የሚያደርገውን፤ በስምህ ቤተ ክርስቲያን የሚሠራውንና፤ በውስጧም የሚጸልየውን ስለትንና መባንም የሚሰጠውን በመታሰቢያህም ቀን ለድሆች የሚመጸውተውን ሁሉ ካንተ ጋራ በመንግሥተ ሰማያት አኖራቸዋለሁ አለው፡ በስምህ የታነጹትንም አብያተ ክርስቲያናት መላእክቶቼን እንዲጠብቋቸው አደርጋቸዋለሁ፤ ብዙ ቃል ኪዳንም ሰጠው፡፡ በመለኮታዊ አፉ አፉን ሳመውና ከእርሱ ዘንድ ወደሰማያት በክብር ዐረገ፡፡

ከዚህም በኋላ እልዋሪቆን ወደምትባል ታላቅ ሀገር እስከሚደርስ በብዙ አገሮች ውስጥ ተመላለሰ፡፡ በዚያም የብርሃን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻለት አረጋጋቸው፤ ረዳቸውም፡፡ በመጋቢት 29 እንደጻፍነው የአገሩን ሰዎች እንዲያጠምቃቸውና እንዲያስተምራቸው አዘዘችው፡፡

ከዚህም በኋላ ወደ ሮሜ ከተማ ገብቶ በውስጧ ሰበከ፤ በስብከቱም ብዙ ሰዎች አምነው የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው፡፡ በመጻሕፍትነት ያታወቁ ዐሥራ አራት መልእክቶችን ጻፈ፤ የመጀመሪያ መልእክቱም ለሮሜ የተጻፈችው ናት፡፡ መልካም ሩጫውንም ከፈጸመ በኋላ ንጉሥ ኔሮን ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው፡፡ ራሱንም በሰይፍ እንድቆርጡት ለሰያፊ ሰጠው፤ ከሰያፊውም ጋራ አልፎ ሲሔድ ከንጉሥ ኔሮን ዘመዶች ወገን የሆች አንዲት ብላቴና አገኘቸው፤ እርሷም ክብር ይግባውና በጌታችን ያመነች ነበረች፤ ለእርሱም አለቀሰች፡፡ እርሱ ግን መጎናጸፊያሽን ስጪኝ እኔም ዛሬ እመልስልሻለሁ አላት፡፡ እርሷም መጎናጸፊያዋን ሰጠችውና ራስ ወደሚቆርጡበት ቦታ ሔደ፡፡ ለሰያፊውም ራሱን ባዘነበለ ጊዜ በመጎናጸፊያዋ ፊቱን ሸፈነ፤ ሰያፊውም የቅዱስ ጳውሎስን ራስ ቆርጦ በዚያች ብላቴና መጎናጸፊያ እንደተሸፈነ ጣለው፡፡

ሰያፊውም ጳውሎስን እንደገደለው ለንጉሥ ሊነግረው በተመለሰ ጊዜ ያቺ ብላቴና አገኘቸው፤ ያ ጳውሎስ ወዴት አለ አለችው ራስ በሚቆረጥበት ቦታ ወድቋል ራሱም በመጎናጸፊያሽ ተሸፍኗል አላት፡፡ እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ ዋሽተሃል እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ ዘንድ አልፈው ሔዱ እነርሱም የመንግሥት ልብሶችን ለብሰዋል፤ በራሳቸውም ላይ በዕንቁ የተጌጡ ዐይንን የሚበዘብዙ አክሊላትን አድርገዋል፡፡ መጎናጸፊያዬንም ሰጡኝ፤ አርሷም እነኋት ተመልከታት ብላ ለዚያ ሰያፊ አሳየችው ከእርሱ ጋራ ለነበሩትም አሳየቻቸው፡፡ አይተውም አደነቁ፤ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡የዚህም ሐዋርያ ጳውሎስ ተአምራቶቹ ቁጥር የሌላቸው እጅግ የበዙ ናቸው፡፡

ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት፤ እና የቅድስት የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡

  • ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

 

 

ክረምት

ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በዕለተ ረቡዕ የተፈጠሩት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ቀን ለመቁጠር፣ዘመንን፣ ወራትን፣ በዓላትንና አጽዋማትን ለማወቅ ወሳኝ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ዘፍ.14-19፣ ዘዳ.12፡1፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አቆጣጠር አንድ ዓመት በፀሐይ አቆጣጠር 365 1/4 ቀናት፡፡ በጨረቃ አቆጣጠር 354 ቀናት፡፡ በከዋክብት አቆጣጠር ጸደይ፣በጋ፣መጸውና ክረምት የተባሉ አራት ወቅቶች አሉ፡፡

ወቅት እንዲፈራረቅ በዘመን ላይ የተሾሙ ዓመቱን በአራት ክፍለ ዘመን የሚገዙት አራት ከዋክብት ሲሆኑ በእያንዳንዱ ወር ላይ የሰለጠኑ ከአራቱ ከዋክብት ሥር እንደ ወታደር የሚያገለግሉ ሦስት ሦስት ወታደሮች በድምሩ 12 ከዋክብት አሉ፡፡ እነዚህ ከዋክብት ወቅቶቹ ሥርዐታቸውን ጠብቀው እንዲሸጋገሩ የሚያደርጉና የእግዚአብሔር ጸጋ ለፍጥረቱ እንዲደርስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ዓመቱን ለአራት ወቅቶች የሚከፈሉትና የሚመግቡት ከዋክብት የሚከተሉት ናቸው፡-

ምልክኤል፡-

በጸደይ የሰለጠነው ኮከብ ምልክኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት/ወታደሮች/ ሚዛን በመስከረም ወጥቶ 30 ዕለት ከ 10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ሚዛን ነው፡፡ አቅራብ በጥቅምት ወጥቶ 29 ዕለት ከ40 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ጊንጥ ነው ፡፡ ቀውስ በኅዳር ወጥቶ 29 ዕለት ከ28 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ቀስት ነው፡፡ (ኬኪሮስ ማለት ረጅም መስመር ማለት ሲሆን የቀንና የሌሊት ሰዓቶች ክፍል ነው፡፡ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተዘርግቶ 60 ክፍሎች አሉት፡፡ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ሁል ጊዜ እየሄዱበት በየቀኑ አንድ ጊዜ ያልፍበታል፡፡ 5 ኬክሮስ 1 ሰዓት ነው፡፡)

ናርኤል፡-

በበጋ የሰለጠነው ኮከብ ናርኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት ወታደሮች ገዳ/ጀዲ በታኅሣሥ ወጥቶ 29 ዕለት ከ28 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ፍየል፡፡ ደላዊ በጥር ወጥቶ 29 ዕለት ከ41 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ውኃ መቅጃ ባልዲ፡፡ ሑት በየካቲት ወጥቶ 31 ዕለት ከ10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ዓሣ ነው፡፡

ምልኤል ፡-

በመጸው የሰለጠነው ኮከብ ምልኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት ሐመል በመጋቢት ወጥቶ 30 ዕለት ከ43 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ በሬነው፡፡ ገውዝ/ጀውዝ በግንቦት ወጥቶ 31 ዕለት ከ30 ኬክሮስ የሚታይ መልኩእንደ ባልና ሚስት ጥንድ ነው፡፡

ሕልመልመሌክ፡-

በክረምት የሰለጠነው ኮከብ ሕልመልመሌክ ሲሆን በሥሩ ያሉት ከዋክብት/ወታደሮች ሰርጣን/ ድርጣን በሰኔ ወጥቶ 31 ዕለት ከ26 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ጎርምጥ ነው፡፡ አሰድ በሐምሌ ወጥቶ 31 ዕለት ከ10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ አንበሳ ሰንበላ በነሐሴ ወጥቶ 30 ዕለት ከ42 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ እሸት ዛላ ነው ፡፡

በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የወቅት አቆጣጠር እንደሚከተለው ይገለጻል፡፡

  • የመጸው ወቅት ከመስከረም 26 ቀን እስከ ታኅሣሥ 25

  • የበጋ ወቅት ከታኅሣሥ 26 ቀን አስከ መጋቢት 25

  • የጸደይ ወቅት ከመጋቢት 26 ቀን እስከ ሰኔ 25

  • የክረምት ወቅት ከሰኔ 26 ቀን እስከ መስከረም 25 ቀን ሲሆኑ እነዚህን ወቅቶች በማወቅ ዘመኑን በመዋጀት ሥራው ድንቅ የሆነ አምላክ ይመሰገንበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሥርዐት ሠርታ በጸሎቱ በማኅሌቱ በቅዳሴው ወዘተ. ትጠቀምበታለች፡፡

ቤተክርስቲያን ወቅቶች ሲፈራረቁ አዲሱን ወቅት ለመቀበል ምኅላ (ጸሎት) ታደርጋለች ፡፡ ለምሳሌ ምኅላ በአተ ክረምት (የክረምት መግቢያ ምኅላ) እንደየ ዕለቶቹ እየታየ ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 23 ቀን ምኅላ ይያዛል፡፡ ይኸውም መጪው ክረምት እግዚአብሔር የሚመሰገንበትና የሚዘንበው ዝናብ ጥሩ ምርት የሚያስገኝ እንዲሆን ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ እንደጻፈው “ምድርም ብዙ ጊዜ በርስዋ የወረደውን ዝናም ከጠጣች መልካም ፍሬ ለደከሙበት ላረስዋትም ብታበቅል ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከት ትቀበላለች” ብሏል ዕብ.6፡7 ፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ወአንተ ገበርከ አድባረ ወምድረ ኵሎ፡፡ ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ ወተዘከር ዘንተ ተግባረከ፡፡ አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።ይህን ፍጥረትህን አስብ። (መዘ 74፡፡17)

“ክረምት” በደስታ ተክለ ወልድ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ በሚለው መጽሐፋቸው ሲፈታው ክረምት ከረመ ዝናም የዝናብ ወቅት በፀደይና በመጸው መካከል ያለ ክፍለ ዓመት ከሰኔ 25 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለው ወቅት ሲለው ቅዱስ ያሬድም በድጓው ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቁል ሣዕረ ውስተ አድባር ይለዋል፡፡

ጥዑመ ልሳን ካሳ ደግሞ “ክረምት” የሚለው ቃል ከርመ፣ ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ወርሃ ዝናም፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ ነጎድጓድ፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ… ይሉታል፡፡ ዘመነ ክረምት/ የዝናብ ወቅት በዘጠኝ ይከፈላል አራቱ በሚጠናቀቀው ዓመት እስከ ጳጉሜ መጨረሻ ሲሆን አምስቱ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት ውስጥ በመስከረም ናቸው፡፡ በያዝነው ዓመት ውስጥ ያለው ክፍል ፡-

  1. ዘር፣ ደመና እስከ ሐምሌ 18 ቀን

  2. መብረቅ፣ ባሕር፣ ወንዞች እስከ ነሐሴ 9 ቀን

  3. እጓለ ቁአት ፣ደሰያት ፣የሁሉም ዓይኖች እስከ ነሐሴ 27

  4. ንጋት፣ቀን፣ፍጥረት በሚል እስከ ጳጉሜን 5 ወይም 6 ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ጊዜዎች እንደ አንድ ይቆጠራሉ፡፡

የዝናብ/የክረምት ወቅት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በልዩ ሁኔታ የምታከብርበት ወቅት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ፈጣሪ መጋቢ መሆኑን በዝናብ ምልክትነት /አስረጅነት ታስተምራለች፡፡ በግብርና የሚተዳደሩ የሀገራችን ሰዎች በክረምት የዘሩት ዘር ፍሬ የሚያፈራው በክረምት እግዚአብሔር በሚሰጠው ዝናብ ስለሆነ ቸርነቱ መጋቢነቱ በዚህ ይመሰላል፡፡

ድሃ ስንሆን ተስፋችንን በእግዚአብሔር ላይ እናደርጋለን እርሱ ዝናቡን ይሰጠናል፡፡ ዘር እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በአፈር ውስጥ ይቀበራል ዝናብ ሲያገኝ አድጐ ለፍሬ ይበቃል፡፡ ስለዚህ ከሰኔ 25 – ሐምሌ 18 ያለው ወቅት ዘርዕ ደመና ተብሎ መጻሕፍት ይነበባሉ፡፡ መዝሙሮች ይዘመራሉ፡፡

የሚቀርበው ምስጋና የዝናብን ወቅት እግዚአብሔር ሰጠን ምሕረትን አደረገልን ሰንበትን ለሰዎች ሠራልን ስለዚህ እርሱን ከፍ ከፍ እናድርገው እናመስግነው በማለት ነው፡፡ እንዲሁም ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም። በማለት ቤተክርስቲያን በቅዱስ ዳዊት ምስጋና ታመሰግነዋለች፡፡ መዝ 147፡8 ፡፡

በሐምሌ 2፣5፣20፣ 15 16 አሠርገዎሙ ለሐዋርያት እየተባለ ሐዋርያት በመዝሙር ይታሰባሉ፡፡ 2ጴጥ.1፡12-18 ሐዋ.23፡10-35 ከሐምሌ 19-ነሐሴ 9 መብረቅ ነጎድጓድ ባሕር አፍላግ ጠል እየተባለ ይዘመራል መጻሕፍት ይነበባሉ ፡፡ 1ጴጥ.2፡1-12፣ ሐዋ.20፡1-2፡፡

በዘመነ ክረምት ውኃ ይሰለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህ ዘመን ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡

ወርኃ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፤ ገበሬ በወርሃ ክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሳል፡፡ ክርስቲያንም በዚህ ምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ይታገሳል፤ ክርስቲያንም በዚህ ምድር የሚደርስበትን መከራ ሁሉ በጸጋ የሚቀበለው በዚያኛው ዓለም ስለሚያገኘው ተድላና ደስታ ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እለ ይዘርኡ በአንብዕ ወበኃሤት የአርሩ፡፡ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ፡፡ ወፆሩ ዘርኦሙ፡፡ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ፡፡ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ፡፡” በማለት የመንፈሳዊ ጉዞ ምሥጠርን ከግብርና ሙያ አንጻር አመልክቶአል፡፡(መዝ.125)

“ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም ብልፅግናዋንም እጅግ አበዛህ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተሞላ ነው ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፣ በዝናም ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳቱንም ከመዛግብቱ ያወጣል ” (መዝ.64፥9) በማለት እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑንና የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡

እግዚአብሔር ክረምትን ሲያመጣና ዝናምን ሲያዘንም ብዙ ነገሮችን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ፈጣሪያችን ፈጣሪ ዓለማት ብቻ ሳይሆን መጋቢ ዓለማት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ መግቦቱም ከፍጥረቱ እንዳልተለየ ይህ አማናዊ መግቦቱም ፍጥረቱን እንደሚያስተምር እንረዳለን፡፡

በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፤ ብርድና ሙቀት፤ በጋና ክረምት፤ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም፡፡” (ዘፍ.8፥22) በማለት አምላካችን እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምቱ ብርድና ሙቀቱ ቀንና ሌሊቱ በተወሰነላቸው ጊዜ እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዓመት ውስጥ እየተፈራረቁ በሚመጡ አራት ወቅቶች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢርና ምሳሌ ጋር በማስማማት ለየወቅቱና ለዕለታቱ ምንባባትን በማዘጋጀት እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ ስለዚህ በክረምት ወቅት እግዚአብሔርን እያመሰገንን እንድናሳልፍ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ይቆየን

  • ምንጭ :-ባሕረ ሐሳብ የዘመን ቆጠራ ቅርሳችን
st mary2

በወርቅ ከተለበጠው በድንጋይ ወደ ታነፀው

ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.

ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መላክ

በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የ፬ቱ ጉባኤያት መምህር

st mary2የመጀመሪያውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ከጥንት ሰዎች የተፈቀደው ለሰሎሞን ነው፡፡ ሰሎሞን የተወለደበት ዘመን በንጉሡ ዳዊትና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ጥል ተወግዶ ፍቅር የተመሠረተበት የፍቅር ወቅት ነበር፡፡ በደለኛነቱ በነቢይ የተረጋገጠበት ንጉሥ ዳዊት በበደለኛነቱ ወቅት ከኦርዮን ሚስት በወለደው ልጁ ሞት ምክንያት የእርሱ ሞት ወደ ልጁ ተዛውሮለት እርሱ ከሞት እንዲድን ሆኗል፡፡ የእርሱን ሞት ልጁ ወስዶለት የልጁ ሕይወት ለእርሱ ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ልጅ ሞት በኋላ ያለው ዘመን የሰላምና የእርቅ ዘመን በመሆኑ የተወለደው ልጅ ሰሎሞን ተብሎ ተጠራ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ የፍቅር ስም ነው፤1ኛ ነገ12÷24

የንጉሡ ዳዊት ንስሐ ለመጀመሪያው ጊዜ ቤተ መቅደስ በምድር ላይ ለመሥራት ምክንያት ነው፡፡ የምድር ሁሉ ንጉሥ ሆኖ ተሾሞ የነበረው አባታችን አዳም በደለኛ ሳለ በገባው ንስሐ ምክንያት የአምስት ቀን ተኩል (5500 ዘመን) ቀኖናውን ሲፈጽም የተወለደለት አንድ ልጁ ክርስቶስ የእርሱን ሞት ሞቶለት፣ የራሱን ሕይወት ለአዳም ሰጥቶት ባደረገው ካሳ በአዳምና በእግዚአብሔር መካከል ለተፈጠረው ሰላምና ፍቅር መገለጫ የሚሆን ቤተ መቅደስ በሰዎች መካከል ተሠርቷል፡፡ ዘመኑ ከጌታ ልደት በኋላ ሃምሳ አራት ዓመት ገደማ እመቤታችን ባረገች በአራት ዓመት ወንጌልን ለመስማት ከአውሮፓ ከተሞች የሚቀድማት የሌለው እና በመቄዶንያ አውራጃ የምትገኘዋ ግሪካዊቷ የፊልጶስ ከተማ ፊልጵስዩስ፤ በቅዱስ ጳውሎስ ሁለተኛው የወንጌል ጉዞ ወቅት ወንጌልን ሰምታ ካመነች በኋላ የመጀመሪያው የቤተ መቅደስ ሥራ በመካከሏ ተፈጽሞላታል፡፡

ክርስቶስ በምድር ላይ ሰውን የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ ለማድረግ ሲተጋ ነበር ማደሪያ የሚሆነው ምድራዊ ድንኳን አልሠራም፡፡ ክርስቶስ የመጣው ሰውን ለመሥራት እንጂ በሰማይ ማደሪያ የሌለው ሆኖ ማደሪያ ፍለጋ የመጣ አይደለምና እንዲሁም ጊዜው ገና ስለነበር መጀመሪያ መሠራት ያለበት ሰው ነበር፡፡

ጊዜው ሲደርስ ከላይ በተጠቀሰው ዘመን ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ አስተምረው ባሳመኗት ከተማ መካከል በጥበበ እግዚአብሔር አዲስ ሕንፃ ለእግዚአብሔር ማደሪያነት ተገነባ፡፡ እስከዚያ ቀን ድረስ ሐዋርያትና ሌሎችም ደቀ መዛሙርት ለመሰብሰቢያነት ይጠቀሙበት የነበረው ካታኮምብ (ግበበ ምድር) ካልሆነ ለክርስቲያኖች ተብሎ የተገነባ ልዩ ሥፍራ አልነበረም፡፡ የአህዛብ መምህር ሆኖ የተመረጠው ቅዱስ ጳውሎስ እስኪነሣ ድረስ ከሐዋርያት አንዳቸውም ለዚህ አገልግሎት አልተመረጡም፡፡ ለእግዚአብሔር ሰዎች የተሰጣቸው ጸጋ ልዩ ልዩ ነውና በአሕዛብ መካከል ቤተ እግዚአብሔር እንዲሠራ የተፈቀደው ለቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡

እርሱ ወንጌልን ሰብኮ ወደ ሌሎቹ ሀገራት ዘወር ሲል ሕዝቡ ተሰብስበው አንድ ጥያቄ ጠየቁ፤ ወደ ቤተ ጣዖት እንዳንሔድ ከልክላችሁናል፤ ሥርዓተ አምልኮ የምንፈጽምበት ቤት ልትሠሩልን ይገባል ብለው ጠየቋቸው፡፡ ጳውሎስና በርናባስ ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ተማክረው ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰኔ በሃያ ቀን ወርዶ ሐዋርያትን ባንድ ቦታ ሰብስቦ፣ ከተራራ ላይ የተቀመጡ ሦስት ድንጋዮችን ጠቅሶ ወደ እርሱ በማቅረብ ቅድስት፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማኅሌት አድርጎ ሠርቶላቸዋል፡፡

ቤተ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተ እስራኤል ውጭ ተሠራች፤ ከከበሩ እና ተጠርበው አምረው ከቀረቡ ክቡራን ድንጋዮች ሳይሆን ተራራ ላይ ተቀምጠው ከሚኖሩ ተራ ድንጋዮች ተገነባች፡፡ በወርቅ ከተለበጠው በድንጋይ ወደ ታነፀው ተዛወረች፤ በዝግባና በጽድ የታነፀው አገልግሎት ከመስጠት ተከለከለ፤ በጢሮሳዊ የአልባስጥሮስ ግምጃ የተሸፈነው ተናቀ በነኪራም ብልሃት፣ በነባስልኤልና ኤልያብ ጥበብ የተጌጠው የጸሎት ቤት ክብሩን ለቀቀ፤ ሁሉም ነገር ከተጠበቀው ውጭ ሆነ፡፡

በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የእግዚአብሔር መልዕክት ምንድነው?

ቤተ መቅደሱ በድንጋይ ለምን ተሠራ? ከመሠረት እስከ ጣራና ጉልላት ሌላ ነገር አልተጨመረበትም፤ ድንጋዮቹም ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ዘመን በድንጋይ ላይ የሠራቸው አስደናቂ ነገሮች የተለዩ ናቸው፤ የቃና ዘገሊላውን ተአምር የተመለከትን እንደሆነ፤ የቢታንያ ድንጋዮችንም ያነሣን እንደሆነ በእነርሱ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያልተደረገ፣ ወደፊትም የማይደረግ ድንቅ ተአምር በነዚህ ድንጋዮች ውስጥ ሲደረግ እናያለን፡፡ እግዚአብሔር ሊሠራ ከወደደ በድንጋይ ልብ ውስጥም ሥራ መሥራት እንደሚችል አሳየን፡፡ ቀድሞ በነቢያቱ ዘመን ዮናስን በባሕር ልብ ውስጥ አስገብቶ እንዲዘምር አደረገ፣ ኢያሱ ሥራውን እስኪጨርስ ፀሐይን አቆመ፣ በእኛም ዘመን የአቡነ ዘርዐ ቡሩክን የጸሎት መጻሕፍት እስከወደዱት ዘመን ድረስ በዐባይ ውኃ ጉያ ውስጥ ደብቆ አቆየ፡፡

ድንጋይ ሲፈልጡት ይፈለጣል፣ ሲረግጡት ይረገጣል እንጂ መች ቀድሶ ያውቃል? መች ወንጌል ሰብኮ ያውቃል? በቢታንያ የቆመው የድንጋይ ምሰሶ ግን ይሁዳ ንስሐ እንዲገባ ተግቶ የሰበከ ብቸኛ ሐዋርያ ነው፡፡

የክርስቶስ ወደ ዓለም የመምጣት ምክንያት ይህ ነበር፡፡ እንደ ድንጋይ ኃጢአት ያፈዘዘው አዕምሯችንን ሕይወት እንዲኖረው ማድረግ! ድንጋይ ከውጪ እንጂ ከቤት ውስጥ ምን ሙያ አለው? እኛ ሁላችንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሙያ ታጥቶልን በውጭ እንድንጣል የተደረግን ሰዎች ነበርን፤ እንዲህ እንደ ድንጋይ ያለ ፈዛዛ ታሪክ በነበረን ወራት የተወለደው የማዕዘኑ ራስ ክርስቶስ በእኛ በድንጋዮች አድሮ ሥራ እንደሚሠራ ለማስረዳት ለልዩ ልዩ አገልግሎት ድንጋይን ሲጠቀም እንመለከተዋለን፡፡ የበረሃው ሰባኪ ቃለ ዓዋዲ ዮሐንስ እስራኤልን ሲገስጽ ‹‹እብለክሙ ከመ ይክል እግዚአብሔር እምዕላንቱ አዕባን አንሥኦ ውሉድ ለአብርሃም፤ እግዚአብሔር ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጅ ማሥነሳት እንደሚችል በእውነት እነግራችኋለሁ›› ማቴ3÷9 እያለ አብርሃም አባት አለን በማለት ብቻ ሊጸድቁ የሚያስቡትን ይዘልፋቸው ነበር፡፡ ሲጀመር ለአብርሃም የተገባው ቃል ኪዳን እንደ ሰማይ ከዋክብት ለሆኑት ልጆቹ ብቻ መች ሆነና! እንደ ባሕር አሸዋ በምድር ላይ ለተነጠፉት ልጆቹም ነው እንጂ፡፡

በእውነት ድንጋዮችን ልጅ አድርጎ ለአብርሃም የሚያስነሣበት ዘመን እንደደረሰ እንዲታወቅ በእነዚህ ድንጋዮች ቤቱን ሠራ፡፡ እኒህ ድንጋዮች እኮ የአሕዛብ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ በከበሩ ድንጋዮች የተሠራ፣ በዋንዛ፣ በጽድ፣ በዝግባ የተዋበ፣ በወርቅ የተለበጠ ነበር 1ኛነገ. 6÷7፡፡ ለዚህ ግን እነዚህ ሁሉ ጌጣ ጌጦች አላስፈለጉትም፤ ድንጋዮች በቂ ነበሩና፡፡ ለክርስትና የጥንቶቹ ሊቃነ ካህናት ሌዋውያንና ፈሪሳውያን አያስፈልጉትም፤ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አሕዛብ ቤተ መቅደሱን ለመሙላት አላስቸገረም፡፡

ከድንጋይስ ምን አለበት የከበሩ ድንጋዮችን ቢመርጥ ኖሮ ሊባል ይቻል ይሆናል፤ ተራራው ላይ ሥራ አጥተው የተቀመጡትን ድንጋዮች ሥራ መስጠትኮ ነው የክርስቶስ ዓላማ፡፡ በማለዳም፣ በሦስት ሰዓትም፣ በቀትርም፣ እስከ ማታ ለወይኑ ቦታ ሠራተኞችን ሊስማማ በወጣ ጊዜ የተዋዋላቸው ሰዎች ሥራ ፈቶች አልነበሩምን? ማቴ20÷1 አሁንስ ለቤቱ የመረጣቸው ድንጋዮች በሰው ዘንድ ያልታሰቡ ቢሆኑ ምን ይገርማል፤ ለክርስቶስ ማደሪያነት ከቤተ አይሁድ ቀድሞ የሚገኝ አለ ተብሎ በሰው ዘንድ ታስቦ ያውቅ ነበር? አሕዛብን እግዚአብሔር ከውሻነት አውጥቶ ልጆች ያደርጋቸዋል ብሎ ማን አስቦ ኖሯል? እግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ፤ ማቴ15÷26፡፡

ዳሩ ግን ሰው እንዳሰበው አልሆነም፤ በቃሉ የጠራቸውን ሦስቱን ድንጋዮች እንዲበቁ አደረጋቸው፤ እርሱ ይበቃል ያለው ይበቃል፤ የከለከለው ደግሞ ወርቅም ቢሆንም ተልጦ ይወድቃል፡፡ ሲፈቀድለት ጣዖት አጣኙ የሞዓብ ልጅ የእግዚአብሔር ካህን ሆኖ ተሾመ፤ ባይፈቀድለት የወርቁን ማዕጠንት በእጁ ይዞ የቃል ኪዳኑን ታቦት ሲያጥን የኖረው የአሮን ልጅ ተከለከለ፤ የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፡፡

የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ለምን በአሕዛብ ከተማ ተሠራ? አሕዛብ አማልክቶቻቸው ብዙ፣ አጋንንቶቻቸው ብዙ ናቸው፤ ቅዱስ ኤፍሬም እንደተናገረው ኃጢአት ብትበዛባቸው፤ ጸጋ እግዚአብሔር በዝታላቸው ብዙ ነገሮችን ከእስራኤል ቀድመው አግኝተዋል፡፡ ከአዳም ቀድሞ ገነት የገባው ፈያታዊ ዘይማን ከአሕዛብ ወገን ነበር፤ እስራኤል ሞትን ለፈረዱበት ጌታ ምንም እንኳን ማዳን ባይቻለውም ብቻውን የተከራከረለት ጲላጦስም ከአሕዛብ ወገን ነበር፡፡ የመጀመሪያውን የቡራኬ ሥራም የጀመረው በአሕዛብ ሀገር በግብፅ ገዳማት በገዳመ አስቄጥስ ነው፡፡ ለአሕዛብ ምን ያልተደረገ ምን አለ? ይህን ታሪካዊ ቤተ መቅደስም በቤተ አይሁድ መካከል የሠራው አይደለም፤ በአሕዛብ መካከል እንጂ፡፡

ቤተ ክርስቲያን በምኩራብ ማኅፀን ውስጥ ተፀንሶ የቆየ ፅንስ እንጂ አዲስ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን የፀነሰችው ምኩራበ አይሁድ ወልዳ መሳም ሳትችል ቀረች፤ ምክንያቱም እንደ ተወለደ በእስራኤል እንቢተኝነት ምክንያት ወደ አሕዛብ ስለገባ ነው፤ ሕንፃው በቅድስቲቷ ምድር ኢየሩሳሌም ሳይሆን ቀረ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በረከቱን ከእስራኤል እንዳራቀ፣ ክብራቸውን ወደ አሕዛብ እንደተነጠቀ ለማሳየት ነው ፡፡

አብርሃም በራዕይ የተመለከታቸው በምድራዊ አሸዋ የተመሰሉ ልጆቹ የሰማዩን ተስፋ፣ የቃል ኪዳኑን ምድር እንዲወርሱ የተወለዱለት በዚህ ጊዜ ነው፤ ዘፍ 22÷17፡፡ እንደ ባሕር አሸዋ የመንፈስ ቅዱስ ሙቀት የሌላቸው ቀዝቃዞች፣ በምድር እንጂ በሰማይ እንዳሉት ከዋክብት በላይ ለመኖር ያልታደሉ ብርሃን አልባ ድንጋዮች ናቸው፡፡ ዛሬ ግን ከከበረ የአልማዝ ድንጋይ ይልቅ ያበራሉ፤ ድንጋይነታቸውን እንዳልናቀባቸው ለማስረዳትም በመካከላቸው የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ በድንጋይ ሠርቶ አሳየ፡፡ ለካ ድንጋይም አናጢዎች የናቁት ድንጋይም ለአገልግሎት ይፈለጋል ብለው እምነታቸው እንዲፈጸምላቸው ነው እንጂ ሌላ ምንድነው? ያልታሰቡትን ድንጋዮች ባንድ ቀን ለቤቱ እንዲበቁ አደረጋቸው::

በዚያውም ላይ እግዚአብሔር ሲፈቅድ የቀደሙት ኋለኞች፣ ኋለኞች ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ፤ ቀድመን ወንጌሉን ማወቃችን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛውን የሥልጣን ሥፍራ መያዛችን፣ በቤተ መቅደሱ ማደጋችን ብቻውን ያጸድቀናል የሚመስላቸው ብዙ ወገኖቻችን ናቸው:: በወንጌል ውስጥ ብዙ ኋለኞች ፊተኞች የሆኑ ሲሆን ብዙ ፊተኞች ደግሞ ኋለኞች ሆነዋል፡፡

ቤተ መቅደሱ በእመቤታችን ስም ለምን ተሰየመ? የመጀመሪያው የመላዕክት የምስጋና መሥዋዕት በምድር ላይ የቀረበበት ቤተ መቅደስ ማኅፀነ ማርያም ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አረጋዊ መንፈሳዊ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ “ድንግል አጽነነት ርዕሳ መንገለ ከርሣ ከመ ትስማ ቃለ እመላዕክት፤ ድንግል ከመላዕክት ቅዳሴን ልትሰማ ራሷን ወደ ሆዷ ዘንበል ታደርግ ነበር” በማለት የእመቤታችንን ማኅደረ ቅዳሴነት ይናገራል፤ ጌታችን የሚፀነስበት ወራት በደረሰ ጊዜስ እመቤታችን ከቤተ መቅደስ እንድትወጣ መደረጉ ለምን ይመስላችኋል፤ ቤተ መቅደስ በቤተ መቅደስ ውስጥ መኖር ስለሌለበት እኮ ነው፡፡ በዚያውም ላይ ያኛው ቤተ መቅደስ የሌቦች ዋሻ የወንበዶች መዳረሻ ሆኗል፤ ብቸኛዋ የእግዚአብሔር ከተማ ድንግል ከዚያኛው ጋር ምን ሕብረት አላትና በዚያ ሳለች ትፅነሰው?

ከአይሁድ ቤተ መቅደስ አውጥቶ ቤተ መቅደስ አደረጋት፤ በቤተ መቅደስ ትሰማው የነበረውን የመላእክት ዜማ አሁንም በሆዷ ውስጥ ትሰማው ነበር የምድራውያኑን ካህናት ቅዳሴ በሰማዩ ካህናት ቅዳሴ ለውጣዋለች:: ይህን ለመግለጽ ነው እንግዲህ ቤተ መቅደሱን ከሦስት ድንጋዮች ሠርቶ ሲጨርስ በሰኔ በሃያ አንደኛው ቀን ከሰማያት ወርዶ ቤቱን በእናቱ ስም ሰይሞ ቆርቦ እሷንም እነሱንም አቁርቧቸዋል::

አሕዛብ በሥላሴ ለማመናቸው ምክንያት የሆነች እርሷ ናት እንጅ ሌላ ማን አለ፤ ቅዱስ ኤፍሬም እንደ ተናገረው “ለሥላሴ ስግደትን የምታስተምርላቸው” ድንግል ማርያም ናት በኦሪትና በነቢያት ከተገለጠው ይልቅ የእግዚአብሔር ምሥጢር በዝቶ የተገለጠው ጌታ ከእመቤታችን ከተወለደ በኋላ ነውና፤ በዚያውስ ላይ አሕዛብን ማን ፈልጓቸው ያውቅ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታን በእቅፏ ይዛላቸው በከተሞቻቸው መካከል የተገኘች እርሷ እኮ ናት፡፡ ድንጋዮቹ አሕዛብ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲሆኑ እመቤታችን ምክንያታቸው ናት፤ ስለዚህ ቤቱ በእርሷ ስም ተሰየመ፡፡ አሁን ሁላችንም እንደ ሐዋርያው ቃል የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሆናችን ምንም ጥርጥር የለንም 1ኛ ቆሮ3÷16፡፡ እግዚአብሔር “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አይኖርም እርሱ ሥጋ ነውና” ዘፍ6÷3 ብሎ የማለውን መሀላ እንዲረሳና በሰው ላይ እንዲያድር ሰውም ቅዱስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወደ መሆን እንዲያድግ ከእመቤታችን በስተቀር ሌላ ምን ምክንያት አለው፡፡

አምላካችን በድንጋይ ልብ ውስጥም ይመሰገናል ማለትም በአሕዛብም ዘንድ ቅዳሴው አይቋረጥበትም፤ ይህን ስጦታዋን በሰዎች መካከል ሲገልጽላት እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን በስሟ ሰይመላት፤ ከዚያም በኋላ የተነሡ መምህራን ይሄን መነሻ በማድረግ በዐራቱም መዐዝን ወንጌልን ሰብከው ብዙ የመታሰቢያ ቤቶችን በስሟ ከመሥራታቸውም በተጨማሪ ስሟን ለምዕመናን ስም እንዲሆን ፈቅደውላቸው እንዲጠሩበት አድርገዋል፡፡ በነቢይ ስለ እርሷ የተባለውም በዚህ ተፈጽሞላታል “ወይዘክሩ ስመኪ በኩሉ ትውልደ ትውልድ፤ ስምሽን ለልጅ ልጅ ያሳስቡልሻል” መዝ 44÷17፡፡

 

ቅድስት አፎሚያ

ሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ፍቃዱ ሣህሌ

በወርኃ ሠኔ መታሰቢያ ከሚደረግላቸው ቅዱሳን መካከል እግዚአብሔርን የሚፈራ የአስተራኒቆስ ሚስት የሆነች የቅድስት አፎምያን ታሪክ በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

 

ቅድስት አፎምያ በትዳር በነበረችባቸው ዘመናት እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ሴት ነበረች፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን የልደቱን፣ ወር በገባ በ21 የእመቤታችንንና ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ እንደነበር ታሪካቸው ይነግረናል፡፡

 

ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ይሰጡት የነበረውን ምጽዋት እና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባለቤቷን ጠይቃ አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው፡፡

 

ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ መሥራት ቀጠለች፡፡ የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣንም በመልካም አገልግሎት ስትበረታ ባያት ጊዜ ዝም ብሎ ሊተዋት አልወደደም፡፡ በመጀመሪያ ባል ሳታገባ ማገልገሏን ትታ፣ ሌላ ባል አግብታ፣ ልጅ ወልዳ እንድትኖር በብዙ ማባበል ጠየቃት፡፡ ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት፡፡

 

ቅድስት አፎምያ ግን ዳግመኛ ትዳር ላለመመሥረት ቃል ኪዳን እንደገባች ርግብንና ዖፈ መንጢጥን አብነት አድርጋ፤ እነሱ እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ ባል ውጪ ሌላ ባል እንደማያውቁ በመጥቀስ አሳቡን እንደማትቀበለው ገለጸችለት፡፡ ሰይጣንም አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ቢሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደአቧራ በኖ፤ እንደ ጢስም ተኖ ጠፋ፡፡

 

በሠኔ ፲፪ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ አሳቡንም የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እንደተፈታተነው ሁሉ ቅድስት አፎምያንም ለማሳመንም አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን የመሳሰሉ ደጋግ አባቶችን ታሪክ እየጠቀሰ ወደ ትዳር እንድትገባ ደጋግሞ ወተወታት፡፡

 

ቅድስት አፎምያም በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታ በቅዱስ ሚካኤልም ተራዳኢነት ታምና “የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?” በማለት በምድራዊ ንጉሥና በጭፍራው መካከል የሚኖርን የጋራ መግባቢያ መንገድ ዋቢ አድርጋ ጠየቀችው፡፡

 

ለጊዜው “በኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም” ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ፡፡ ከቤቷ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ ያለውን ምልክት አብራርታ የእሱ ግን ከዛ ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩ ወደ ትክክለኛ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን “ድረስልኝ” እያለች በጠራችው ጊዜ መልአኩም ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት፡፡

 

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ የዕረፍት ቀኗ በዚህ ቀን መሆኑን ነግሮ ቤቷን እንድታዘጋጅ አዘዛት፡፡ የበዓሉን ዝግጅት አከናውና ሥጋ ወደሙን ተቀብላ ኤጲስ ቆጶሱንና ካህናቱን እንደየመዓርጋቸው ጠርታ በቤቷ አክብራ ተቀበለቻቸው፡፡ ለነዳያንና ለጾም አዳሪዎች በኤጲስ ቆጶሱና በካህናቱ እጅ ገንዘቧን መጽውታ መንገዷን አሳመረች፡፡ ስለ ኃጢአቷ እንዲጸልዩላት ተማፅና በፊታቸው ተንበርክካ ጸለየች፡፡ ባሏ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቅፋ ስማ ከተማጸነች በኋላ ሠኔ ፲፪ ቀን በሰላም ዐረፈች፡፡

 

ይህች የታመነች ቅድስት አፎምያ በሰላም እስክታርፍ ጊዜ ድረስ የተጓዘችበትን መንፈሳዊ ጎዳና አስተውለን ይሆን? አስቀድማ ከባሏ ጋር አንድ ሆና በታማኝነት ፈጣሪዋን አገለገለችው፡፡ በኋላም የባሏን ኑዛዜ አክብራ ምንም እንኳን ኃጢአት ባይሆንባትም በሁለተኛ ትዳር ራስዋን ማጠላለፍ አልፈለገችም፡፡ በጎ ሥራ አብልጣ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ተፋጠነች እንጂ፡፡

 

ሰይጣን ልጅ አለመውለዷን ተጠቅሞ ያቀረበላትን የጋብቻ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መናፍስት ከእግዚአብሔር እንደሆኑ መርምሩ” ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘውን መመሪያ ተጠቅማ ሰይጣንን በተወክሎ እግዚአብሔር ተቃውማ አሸነፈችው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ርዳታ ያገኘችውና በሰላም ዐርፋ ወዳገለገለችው እግዚአብሔር በክብር የሔደችው በጽናት ተጋድላ ነው፡፡

 

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችንንም ይጠብቀን፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ፣ ድርሳነ ሚካኤል ዘወርኃ ሰኔ

 

 

 

 

ጾመ ሰብአ ነነዌ

 የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

ርዕሰ ደብር ብርሃኑ አካል

ጾመ ነነዌ ከአዋጅ አጽዋማት አንዱ ሲሆን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ቀን ደግሞ ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር 17 ቀን ድረስ ነው፡፡ ሲወጣ ወይም ወደፊት ሲገፉ ደግሞ እስከ የካቲት 21 ድረስ ነው፡፡ በእነዚህ 35 ቀናት/ዕለታት/ ስትመላለስ ትኖራለች፡፡ ከተጠቀሱት ዕለታት አይወርድም አይወጣም ማለት ነው፡፡

የሦስት ቀኑን ጾም የጾሙት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ሲሆኑ ከተማዋ በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ መሥራቿም ናሞሩድ ነው፡፡ ዘፍ.10፥11-12 ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የሆነ ከተማ እጅግ ሰፊና ያማረ ፤ የከተማው ቅጥር ርዝመት አሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ነበር፡፡ ሰናክሬም ብዙ ሕንፃዎችንም ሠርቶበት ነበር፡፡ /ዮናስ. 4፥11/

የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ በኃጢአታቸው ምክንያት ሊጠፉ ሲሉ ቸርነትና ምህረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስ መክሮ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ወደ ነነዌ ሕዝብ ሂድ አለው፡፡ ሉቃ.11፥30 ዮናስ የስሙ ትርጉም “ርግብ” ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ትንቢትን ተናግሯል፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል ፡፡ 2ነገ14፥25፣ ት.ዮና1፥1

እግዚአብሔርም “ሄደህ በነነዌ ላይ ስበክ” ባለው ጊዜ “አልሄድም” አለ፡፡ “አንተ መሀሪ ነህ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ስትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ፡፡” ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔር ግን ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧበማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩት ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባህሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ “በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባህር ጣሉኝ” ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነሱም “የሰው ደም በእጃችን እንይሆንብን አይሆንም” አሉት፡፡ ዕጣም ቢጣጣሉ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያው የእግዚአብሔር የማዳን መልእክት ዮናስ እንዲያደርስ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ነነዌ አደረሰው፡፡ ዮናስም ከእግዚአብሔር መኮብለል አለመቻሉን ሲረዳና ነነዌ መሬት ላይ መድረሱ ሲነገረው ለነነዌ ሰዎች “ንስሐ ግቡ” ብሎ መስበክ ጀመረ ዮናስ 1እና2 ፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ማራቸው /ዮና.3/

ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስህተት መሆኑን እግዚአብሔር ቅልን ምሳሌ በማድረግ አስረዳው፡፡ /ዮና.4/ ነቢየ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ሆኖ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል፡፡ በስንክሳር ታኅሣሥ 5 እንደሚነግረን ፤ወበልዓ አሐደ ኀምለ ይላል ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር አጥፍቶአል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የስራጵታ መበለት ሕፃን ዮናስ እንደሆነ /1ነገሥ.17፥19/ ሲያስረዳን ፤ክርስቶስ የዮናስን ከዓሣ ሆድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎታል፡፡ /ማቴ.12፥19-42/ ሉቃ.11፥30-32/፡፡

ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ናት፡፡ ይሄውም አስቴር አስቀድማ ሦስት ቀን ጾማ ጸልያ በእሥራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች ኢሳ.4፥15-16፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ልጇ ሕፃኑ ኢየሱስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ እንዳገኘችው ሁሉ ሉቃ.2፥46 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መሆኑን ገልጿል ሉቃ.13፥32፡፡

የነነዌ ሰዎች የተነሳህየን ምሳሌ ናቸው ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሕዝቦችና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለሆኑ ያሳዝኑኛል ያለው፡፡

ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለበት ወቅት እኛም ብንመለስ እና ንስሐ በንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ “ወደኔ ተመለሱ እኔም ይቅር እላችኋለሁ ”ብሎ አስተምሯል፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጾመ ነነዌ የሚከተሉትን ምሳለዎች እናገኝባታለን ታሪኩን በማስታወስ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሀሪነት የምናስታውስበት ነው፡፡ ይኸውም ፍጥረቶቹ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርጋል፡፡ ዮናስ ፈቃደኛ ባይሆን እንኳ በተለየ ጥበቡ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ሌላ ነቢይ አጥቶም አይደለም እሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለፈለገ እንጂ፡፡

በዮናስ አማካይነት የተደረጉ ተአምራትን መገንዘብና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመሆኑን ተገንዝበን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች አና ለወላጆች መታዘዝን እንማርበታለን፡፡ እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን ጸልየን ከኃጢአታችን እንድንነፃ ነው፡፡ ብንጾም እራሳችን፣ ሃገራችንን፣ እጽዋቱንና እንስሳቱም ሳይቀር በኛ በደል ምክንያት በድርቅ በቸነፈር እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ይቅር ስለሚል ነው፡፡

ጾመን እንድናበረክት ይርዳን

ይቆየን

 

limena

የጎዳና ላይ ልመና የቤተ ክርስቲያን ገጽታ የጠቆረበት ሕገ ወጥ ተግባር

 

ዲ/ን ማለደ ዋስይሁን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን መተዳደሪያ በደርግ ዘመን ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ደረጃ ማጣቷ ይታወቃል፡፡ ይህ በመሆኑ ለብዙ ደካማ ገጽታዎች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ አጥቢያዎች ለካህናት ደሞዝ፣ ለንዋየ limenaቅድሳት መግዣ፣ በአጠቃላይ ለአገልግሎቱ መስፋትና ማደግ የሚያስፈልገውን መተዳደሪያ ገንዘብ፣ ቁስ፣ ጉልበት ለማግኘት ከምእመናን ገንዘብ መለመን ግድ ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡

 

ቤተክርስቲያን አስቀድሞም መተዳደሪያዋን የምታገኘው ቤታቸው ከሆነችላቸው ከተገልጋዮቹ ካህናትና ምእመናን ነው፡፡ አማኞች ዐሥራት በኩራት ማውጣት ሃይማኖታዊ ግዴታቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ደረጃ የምእመናን ተሳትፎ ባልተሟላበት ሁኔታ አገልግሎቱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ የቤተክርስቲያን ቤተሰቦች ገንዘብ በመስጠት በመሰብሰብ የአጥቢያቸውን አገልግሎት የሰመረ ያደርጋሉ፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን በማስፋት፣ በማሳደግ ረገድ ነገሥታቱን ጨምሮ በሀገሪቱ ትልቅ ክብርና ስም ከነበራቸው ልጆቿ ጀምሮ የሚበረከትላትን መባዕ ማለትም ገንዘብ፣ መሬት፣ ወርቅ፣ ብር ወዘተ ስትጠቀም ኖራለች፡፡ በኋላ ዘውዳዊ ሥርዓቱ እንዲጠፋ ሲደረግ ቤተክርስቲያን መተዳደሪያዋ ሁሉ በመወረሱ የካህናቱ አገልግሎት ፈተና አጋጥሞታል፡፡ ስለዚህ መውጫ መንገድ ነው የተባለው የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት እንደ አንድ መፍትሔ የደረሰላት ቢሆንም አሁንም ግን በሚፈ ለገው ደረጃ አገልግሎቷን መደገፍ የሚያስችል በቂ ገቢ ባለመኖሩ ችግሩ እንዳለ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የበለጠ እየተጎዱ ያሉት ደግሞ የገጠር አብያተ ክርስቲ ያናት ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያን የምትሰ በስበውን ገንዘብ አሰባሰብና ሥርጭቱ አጠቃቀሙ የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓቱ መሻሻል ያለበት ቢሆንም ባለው ደረጃም ቢሆን በችግር ላይ ያሉ አጥቢያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ችግረኛ ገዳማትና አድባራት የሚያስፈልጋቸውን ገቢ ለማግኘት በዓመታዊ በዓላት ከምእመናን የሚያገኙት ገቢ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ልመና ለማድረግ እየተገደዱ ቆይተዋል፡፡ ልመናውንም በተለያዩ አጥቢያዎች በማድረግ የተወሰነ ገቢ አግኝቶ አገልግሎታቸውን ለማስቀጠል እየተንገዳገዱ ነው፡፡

 

ይሔ በእንዲህ እያለ በተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት ስም በጎዳና ላይ ልመና የማድረግ አካሔድ እየሰፋና እያደገ መምጣቱ ይታያል፡፡ ይሔ አካሔድ እጅግ አደገኛና የቤተክርስቲያንንም ገጽታ እየጎዳ ያለ ሕገወጥ አካሔድ ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ስም የሚፈጸም የጎዳና ላይ ልመና ገጽታ ሲገመገም አብዛኛው ስምሪት በአዲስ አበባና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የሚደረግ ነው፡፡ የሚደረጉት የጎዳና ላይ ልመናዎች በዓላት በሆኑ ጊዜያትም ከበዓላትም ውጪ የሚደረጉ ናቸው፡፡ የሚደረጉት ልመናዎች ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውጪ በተገኙ ተገቢ ባልሆኑ ጎዳናዎች ላይ ነው፡፡ የሚደረጉትን የጎዳና ላይ ልመናዎች የሚያከናውኑት ካህናት የሚመመስሉም የማይመስሉም ሰዎች ናቸው፡፡ ልመናዎቹ የሚደረጉት በቡድን ወይም በተናጠል ነው፡፡ የጎዳና ላይ ልመናዎች ሲፈፀሙ ጥላ ተዘርግቶ የቅዱሳን ሥዕላት ተይዘው ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳት ሥዕላት በክብር የተያዙ ያልተያዙም ናቸው፡፡

 

የጎዳና ላይ ልመናዎች ሕገ ወጥነት

የጎዳና ላይ ልመናዎች ሕገ ወጥ የሚሆኑባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡

1/ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ ያልያዙ የጎዳና ላይ ለማኞች


በቅዱሳን እና በአብያተክርስቲያናት ስም የሚለምኑ የተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ሁሉም ሕጋዊ የቤተክርስቲያኒቱ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው፣ ከወረዳ ቤተክህነት፣ ከሀገረ ስብከት፣ ከጠቅላይ ቤተክህነት የተጻፈ ምንም የፈቃድ ደብዳቤ ሳይዙ በሕገ ወጥነት በማጭበርበር የሚሰ ለፉም ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት የራሳቸውን የግል ወይም የቡድን ጥቅም ለማርካት ወይም የቤተክርስቲያንን ስም ለማጉደፍ በድፍረት የተሰለፉ ናቸው፡፡
እነዚህ ወገኖች ምእመናን የቅዱሳን ስም ሲጠራ ራርተው ይሰጣሉ በሚል እምነት በድፍረት ገንዘባቸውን ለመሰ ብሰብ የሚሹ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የትኛውም ሕግ በማይደግፋቸው አግባብ በማን አለብኝነት የዋሕ ወገኖችን እያታ ለሉ ያሉ ናቸው፡፡

2/ የተጭበረበሩ ደብዳቤዎች የያዙ የጎዳና ላይ ልመናዎች

አንዳንዶች ደግሞ ሕጋዊ ለማኝ ለመምሰል ከአጥቢያ የተጻፉ የሚመስሉ ከጠቅላይ ቤተክህነት የተጻፉ በሚመስሉ ደብዳቤዎችን በጎዳና ላይ ደርድረው የሚለምኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎች ሕጋዊ ማኅተም የሌላቸው ወይም ማኅተምን ቢኖራቸውም በማጭበርበር በማስመሰል የተዘጋጁ ወይም ከዚህ ቀደም ተጽፈው ቀንና ቁጥራቸው ላይ ለውጥ በማድረግ አመሳስለው የሚይዟቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕገ ወጥ ናቸው፡፡

3/ በመመሳጠር የተዘጋጁ ደብዳቤዎችን መጠቀም

በአንዳንድ አጥቢያዎች ያሉ የሰበካ ጉባኤ ሓላፊዎች ወይም ሰነዶችን ሕጋዊ የማድረግ ዕድል ያላቸው ግለሰቦች ከአጠቃላዩ የሰበካ ጉባኤ፣ ከማኅበረ ካህናቱና ከምእመናን ስምምነት ሳይደ ረስባቸው ቤተክርስቲያኑ በጎዳና ላይ እንዲለምኑለት ለተወሰኑ በስም ለተጠቀሱ ግለሰቦች ፈቃድ የሰጠ በማስ መሰል በሚወጡ ደብዳቤዎች የሚፈጸሙ የጎዳና ላይ ልመናዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎችን ይዞ አንድ መርማሪ በአጥቢያው ያሉ የሁሉንም የሰበካ ጉባኤ አባላት ወይም የልማት ኮሚቴ ዎች ስምምነት ያገኘ ወይም ያላገኘ ስለመሆኑ ማስረጃ ቢፈልግ በቀላሉ እንዲህ መሰል ደብዳቤዎች የሚወጡበትን የሙስና መንገድ ሊደርስበት ይችላል፡፡

4/ ከያዟቸው ደብዳቤዎች የፈቃድ ሐሳብ በወጣ መልኩ ልመና ማድረግ

ከየትኛውም የቤተክህነት አካል በሕጋ ዊነት የሚወጡ ደብዳቤዎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን የሚፈጽሙ ወገኖች የቤተክርስቲያንን ወይም የቅዱሳንን ስም እየጠሩ ሥዕል ይዘው በጎዳና ላይ እንዲለምኑ ፈቃድ አይሰጥም፡፡ በአብዛኞቹ የምእመናን ድጋፍ እንዲጠይቁ ፈቃድ የሚሰጣቸው አገልጋዮች ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውጪ እንዲህ ባለ ግብር እንዲገኙ አያዝም፡፡ አብዛኞቹ በተለይም ከጠቅላይ ቤተክህነት የተጻፉ ደብዳቤዎችን ስናይ ልመና እንዲፈጸም የሚያዙት ልመናው ከሚደረግበት አጥቢያ ጋር በመነጋገርና በመስማማት በዚያው በአጥቢያው ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ከአጥቢያ ውጪ የሚለምኑ ወገኖች ከያዙት የፈቃድ ደብዳቤ ሐሳብ ውጪ የሚራመዱ ከሆነ ሕገ ወጥ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

5/ ገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ የሌላቸው የጎዳና ላይ ለማኞች

በጎዳና ላይ የሚለምኑ ሁሉም ማለት ይቻላል ግለሰቦችና ቡድኖች በየትኛውም መጠን ለሚቀርብላቸው ምጽዋት የሚቀ በሉበት ሕጋዊ ደረሰኝ የላቸውም፡፡ ስለዚህ በአድባራትና በገዳማት የሚለምኑት ወገኖች የሰበሰቡት የገንዘብ መጠን ሊታወቅ አይችልም ማለት ነው፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ቤተክርስቲያን እውነተኛ ፈቃድ ስትሰጥ በሕጋዊ ደረሰኝ እንዲሰበሰብ እንጂ ከዚያ በመለስ ምንም ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ከምእመናን ቢሰበሰብ ለተለመነለት አጥቢያ በተሰበሰበው መጠን መድረሱን ወይም አለመድረሱን ከዚያም አልፎ የግለሰቦቹ መጠቀሚያ ሆኖ ቀርቶም እንደሆነ በውል ማወቅ አያስችልም፡፡

የዚህ ችግር መንሥኤ ምንድ ነው?

1/ የቤተክርስቲያን ቁጥጥር ልል መሆን


ቤተክርስቲያናችን የራሷ አካል በሆኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ስም የሚፈጸሙ ይሔን መሰል የማጭበርበር ድርጊቶች ለመቆጣጠር የዘረጋችው ጊዜያዊ ወይም ቋሚ አሠራር የለም፡፡ ቢኖርም በንቃት አልተንቀሳቀሰም፡፡ ችግሩን በቀላሉ መቅጨት የሚቻል ቢሆንም እየተባበሰ መሔዱ የአሠራር ድክመቱን ያሳያል፡፡ ቤተክርስቲያን ይሔንን ችግር መቆጣጠር የሚኖርባት ለቤተክርስ ቲያኒቱ ክብር ብቻ ሳይሆን በቤተክር ስቲያን ስም የሕዝብ ገንዘብ በግለሰቦች እየተመዘበረ በመምጣቱም ጭምር ነው፡፡ በሌላም በኩል ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያንን ለመደገፍ የሚሔዱ በትን ፈቃድ በየጎዳናው በመጥለፍ በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ጸሎት አድርሰው ተባርከው መባቸውን በሥርዓት አስገ ብተው እንዳይሔዱ የሚያደርግ ልማድ ፈጥሯል፡፡ ቤተክርስቲያን በየጎዳናው ላይ ሁሉ እንዳለች እያሰቡ በኪሳቸው ያለውን ገንዘብ እየሰጡ እንዲያልፉ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ የዚህ ሁሉ ተጎጂ ራሷ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን አውቆ ልል የሆነውን የቁጥጥር ሥርዓት ጠበቅ ማድረግ፣ ምክር መስጠት፣ ካልሆነም ከሕግ አስከባ ሪዎች ጋር በመተባበርም እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

2/ ሙስና

ቤተክርስቲያን እንዲህ መሰል ጥፋቶች በስሟ የሚበቅሉት የግልጽና ስውር የሙስና አሠራሮች በመኖራቸው ነው፡፡ የጎዳና ላይ ልመናዎች እንዲከናወኑ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተሰለፉ በየደረጃው ያሉ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሹማም ንትም እንዳሉ ይጠረጠራሉ፡፡ ለአንድ ቤተክርስቲያን የሚለመንበት በቂ ምክንያት ሳይኖር ወይም ለአንድ ለተወሰነ ጊዜ ችግር የሆነን ነገር ሁሌ እንዳለ በማስመሰል ፈቃድ በመስጠት እንዲለመን የሚያደርጉ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ቤተክርስቲያን በማሠራት ስም ፕሮጀክቱን በማራዘም ለረጅም ጊዜ እንዲለመንበት በማድረግ ወይም ካለቀም በኋላ ያለ በማስመሰል ልመናዎች እንዲ ቀጥሉ የማድረግ አሠራር አለ፡፡ በዚህም ቢያንስ ዘረፋ ወይም ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት የሚሠሩ ወገኖች አሉ፡፡

3/ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዋህነት በማመን መመጽወቱ

ክርስቲያኖች ለለመነ፣ ለጠየቀ መስጠት አግባብና ክርስቲያናዊ ሥነምግባር መሆኑን ስለሚያምኑ በቅዱሳን ስም ተጠርቶ የቅዱሳን ሥዕል ተይዞ ሲለመን ማለፍ ይከብዳቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንዲለምኑበት የተሰጣቸውን የፈቃድ ወረቀት ሐሳብ ወይም የሚቀበሉበትን ሕጋዊ ደረሰኝ የማይጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሌላም በኩል ለሚሰጡት ሽርፍራፊ ሳንቲም ደረሰኝ መጠየቅ አስፈላጊ ነው ብለው አያምኑም፡፡ ስለዚህም ለእነዚህ ሕገወጥ የጎዳና ላይ ልመናዎች መበራከት የምእመናንንም ድርሻ አለበት፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ክርስቲያኖች የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናትን ለመርዳት በሚያ ስችል መልክ ተሰባስበው ቀጣይነት ያለው ሕጋዊነትና ሥርዓት ያለው ድጋፍ ችግረኛ ለሆኑ አብያተ ክርስቲ ያናት መስጠት በመጀመራቸው የችግሩ ስፋት የሚቀንስበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ምእመናን የጎዳና ላይ ልመና የቤተክርስቲያንን የሃይማኖ ታቸውን ገጽታ የሚያበላሽና ሥርዓት ያጣ ስርቆትንም የሚያባብስ መሆኑን ተረድተው ከዚህ መቆጠብ ካልቻሉ ገንዘባ ቸውን አነሰም በዛም በግልም ይሁን በቡድን ለቤተክርስቲያን በሕጋዊ መንገድ ገቢ ማድረግ እስካልቻሉ ድረስ ችግሩ መቀጠሉ የማይቀር ይሆናል፡፡

limena1የጎዳና ላይ ልመና የሚያስከትለው ችግር

1/ የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ ማጥፋቱ

ይህቺ ቅድስትና በቸር ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተች ቤተክር ስቲያን ክብር ያላት ናት፡፡ ለብዙዎች የእግዚአብሔርን ጸጋ የምታሰጥ ባዕለጸጋ ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ‹‹እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግም›› እያለች ስታስ ተምር የኖረች ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ለምስኪኖች፣ ለተቸገሩ፣ ለደሀ አደጎች ለእጓለ ማውታ ሁሉ የምትደርስ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው›› እያለች የምታሰተምር ቤተክርስቲያን ነች፡፡

 

ቤተክርስቲያን ከምእመናን ዐሥራት በኩራታቸውን ተቀብላ የእግዚአብሔርን ገንዘብ የምታስተዳድር እንጂ ዋነኛ ተግባሯ ሙዳየ ምጽዋት መሰብሰብ አይደለም፡፡ ስብከተ ወንጌልን የማንገሥ እንጂ ማዕድን የማገልገል ፍላጎት ያላት አይደለችም፡፡ ማድረግ ሲገባት ደግሞ በሥርዓትና በታማኝነት የምትፈጽምበት አሠራር አላት፡፡

 

የጎዳና ላይ ልመናዎች ግን የቤተ ክርስቲያን መገለጫ ሆነው ተስለዋል፡፡ ማንም ጥላ ይዞ የሚለምን፣ ሥዕል ያንጠለጠለ፣ እጁን የዘረጋ ሁሉ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መገለጫ እየሆነ ነው፡፡ ሌሎች ዐበይት ቤተክርስቲያናዊ ተግባራትን ባከናወንን መጠን ክርስቲ ያኖች ሳይጠይቁ የሚያደርጉትን ነገር እኛ ግን ዐበይት ተግባሮቻችንን ቸል ብለን የጎዳና ላይ ልመና ዋነኛ የሥራ ሂደታችን ያደረግነው ያስመስላል፡፡

 

ስለዚህ ነው ቤተክርስቲያናችን የጎዳና ላይ ልመናዎችና መሰል ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት ለቤተክርስቲያኒቱ ታሪካዊነት የአርአያነት ሚና የታማኝነት ደረጃ ወዘተን የሚያኮስሱ ይሆናሉ፡፡

2/ የቅዱሳንን ክብር የሚነካ ይሆናል


ቅዱሳንን እግዚአብሔር ያከበራቸው ናቸው፡፡ ሰዎች ክብርን የሚሰጧቸው ወይም የሚቀንሱባቸው አይደሉም፡፡ እነርሱን በማክበር ግን ቤተክርስቲያንና ልጆቿ በረከት ያገኛሉ፤ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛሉ፡፡

ነገር ግን በጎዳና ላይ ልመናዎች የምናየው ነገር የቅዱሳን መላእክትን የቅዱሳን ሰዎችን ስም ጠርተው ሥዕል ይዘው የሚለምኑ ወገኖች በተለያዩ አካሔዶቻቸው ቅዱሳንን ያዋርዳሉ፡፡ በስማቸው ሕገ ወጥ ሥራ የስርቆት ተግባር መፈጸማቸው ጽርፈት ነው፡፡ ንዋየ ቅድሳት ከሥርዓት ውጪ በተያዙ መጠን ይጉላላሉ፡፡ ሥዕሎ ቻቸውን ይዘው አጓጉል ቦታዎች ቆመው መታየታቸው ጽርፈት ነው፡፡ ለቅዱሳት ሥዕላት ክብር በሚነፍግ መልኩ በአያያዝ የተጎዱ በሥርዓት ያልተሠሩ ፀሐይና ዝናብ የተፈራረቀባቸው ሥዕላትን ይዞ መቆም ለሃይማኖት ቤተሰቡም ሆነ ለሚከበሩት ቅዱሳን ክብር አለመስጠት ነው፡፡

3/ የክህነትን ክብር የሚነካ ነው

ብዙ ጊዜ በጎዳና ልመና ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ካህናት የሆኑም ያልሆኑም ወገኖች ናቸው፡፡ ነገር ግን አርአያ ክህነትን ተላብሰው ስለሚታዩ ሁልጊዜም በጎዳና ላይ ልመና የሚታዩት ካህናት ናቸው ብሎ ሰዎች እንዲያምኑ እያደረገ ነው፡፡ ካህናት የቤተክርስቲያን መልክና ምልክቶች ናቸው፡፡ በእነርሱ ውስጥ የምትከብረው ወይም ገጽታዋ የሚደበዝዘው የቤተክርስቲያን ነው፡፡ የመላው ካህናት ገጽታ ነው፡፡ ካህናትን ዘወትር የሚሰጡ ሳይሆን የሚቀበሉ፣ የሚመጸውቱ ሳይሆን የሚመጸወቱ አስመስሎ ያቀርባል፡፡ ከዚያም አልፎ በክህነት የሚፈጸመው ዋነኛ ተግባር ልመና እንደሆነ አድርገው በክህነት የሚያምኑም ሆነ የማያምኑ ወገኖች እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡

4/ የሀገርን ገጽታ ይጎዳል


ቤተክርስቲያን በሙዳየ ምጽዋት የምእ መናንን የለጋስነት ስጦታ መሰብሰቧ፣ ዐሥራት በኩራትን መሰብሰቧ በሃይማኖቱ ሕግና ሥርዓት የታወቀ መንፈሳዊ ተግባሯ ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ተመልካች ቤተክርስቲያን በአጥቢያዋ ካሉ ምእመናን ዐሥራት በኩራት ምጽዋትን ሰበሰበች ብሎ የሚነቅፋት አይኖርም፡፡ ነገር ግን በተገቢው መልኩ በተገቢው ቦታና በሕጋዊ መልክ ካልሆነ ይነቅፋል፡፡

 

የጎዳና ላይ ልመና ግን ከቤተክርስቲያን አልፎ ለሀገርም ገጽታን የሚያጎድፍ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ጎብኚዎችም ዘንድ ደስ የማያሰኝ በመሆኑ ለሀገራችን አይጠቅምም፡፡ ሀገር ልመናን በመቀነስ ሥራና ሠራተኛነትን ለማስፋፋት ጥረት ማድረግ የሚገባትም ለሰሚና ተመልካች ሳቢ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ከአጥቢያ ቤተክር ስቲያን ግቢ ውጪ ወጥቶ ከዕለታዊ ችግራቸው የተነሣ ሕዝብ ባለበት ዐደባባይ ከሚለምኑ ነዳያን ጎን ተሰልፎ ከአማ ኙም ከኢአማኒውም ለቤተክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት መግዣ፣ ለሕንፃዋ ማሠሪያ ገንዘብ ለመለመን መሞከር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

 

5/ የአጥቢያና የሀገረ ስብከቶችን ክብር ይነካል

 

የሚለመንላቸው አጥቢያዎች ስማቸው አለአግባብ በየጎዳናው ለረጅም ጊዜ መነሣቱ ክብር አይሆንላቸውም፡፡ በስማቸው ሕገ ወጥ ተግባር ሲከናወን ሲታይ አጥቢ ያውን ለሚያውቁ ምእመናንና ካህናት የሚያምም ይሆናል፡፡ ለአጥቢያው ብቻ ሳይሆን በዚህ ሀገረ ስብከት በዚህ ወረዳ ለሚገኘው ተብሎ ስለሚለመን ለዚያ ሁሉ ወገን የሚያምም ይሆናል፡፡

6/ ሥራ ፈትነትን ያበረታታል

ቤተክርስቲያን ያላት ትምህርት ‹‹ሊሠራ የማይወድ አይብላ›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ልመናዎች በአቋራጭ መክበርን ያለሥራ ያለድካም መጠቀምን የሚያመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጉዳቱ ለዜጎች ሁሉ ነው፡፡ የሚሠራውን ተስፋ የሚያስቆርጥና ተመሳሳይ የአቋራጭ መንገዶችን እየፈለገ ምርታማ ባልሆኑ ሥራዎች በመሰማራት ከዚያም አልፎ በሥራ ፈትነት በሕገ ወጥ ተግባራት ውስጥ እንዲገባ ያበረታታሉ፡፡ የቤተክርስቲያንን አርአ ያነትም ያጎድፋል፡፡

7/ ለቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ያሳፍራል

ቤተ ክርስቲያንና ቤተሰቦቿ ከሥራ ይልቅ ልመናን የሚመርጡ ስለሚያስ መስል በሌሎች ወገኖች በሚደርስብን ትችት ምእመናን ይሸማቀቃሉ፡፡ ምእመናን የሚፈለገውን ያህል በማይ ወስኑባት በማይመክሩባት ቤተክርስቲያን ውስጥ ይሔ መሆኑ ደግሞ ምእመናንን የሚያስቆጣበት ደረጃ ላይ ያደርሳል፡፡ ካህናት አመኔታ እንዲያጡ በር ይከፍታል፡፡

8/ ምእመናንን ያዘናጋል

ምእመናን ምጽዋትና ዐሥራት በኩራትን ለይተው ማድረግ እንደሚገባቸው በውል ትምህርት በበቂ ባልተሰጠበት ሁኔታ ውስጥ እንዲህ ያሉ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ልመናዎች ሲበራከቱ የዋህ ምእመናን ቤተክርስቲያንን ያገኙ ስለሚመስላቸው ዐሥራት በኩራታቸውን በአግባቡ ለማውጣት ይቸገራሉ፡፡ በጥቂቱ በመርካት ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን በአፍአ ይቀራሉ፡፡ ምጽዋታቸውንም በአግባቡ ሊሰጡ የሚችሉበት ዕድል አይኖራቸውም፡፡

9/ ሌሎች ችግሮች

የጎዳና ላይ ልመናዎች የሚያስከትሉት ሌላው ጉዳት ከሚለምኑት ሰዎች ማንነትና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚያስ ከትለው ችግር ነው፡፡ በልመና ላይ የዋሉ ሰዎች የውሏቸው መጨረሻ የት ነው? የት ያመሻሉ? የት ያድራሉ? ከእነማን ጋር ይውላሉ? የሚለው ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ ያለደረሰኝ በሕገ ወጥ መልክ የተሰበሰበውን ገንዘብ ይዘው በየመጠጥ ቤቶች ተሰይመው የሚያመሹ በርካቶች ናቸው፡፡ ተደራ ጅተው፣ ማደሪያ ተከራይተው በዓላት ባሉበት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሁሉ ቆመው ውለው ማታ ተሰባስበው ያገኙትን ገንዘብ ተካፍለው የሚበተኑ ቡድኖች አሉ፡፡ የቡድኖቹ አስተባባሪዎችም አሉ፡፡ ያዘጋጁትን የፈቃድ ደብዳቤ የሚመስል ማጭበርበሪያ ይዘው የሚለምኑ ሰዎችን አደራጅተው ደብዳቤውን ፎቶ ኮፒ አድርገው የሚያሰማሩ ከዚያም ከየለማኞቹ የድርሻቸውን ተቀብለው ለቀጣዩ ዙር ልመና ተቀጣጥረው የሚበታተኑ ሁሉ አሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚፈጸመው በቤተክር ስቲያኒቱ ስም መሆኑ ሲታሰብ የሚያሳዝን ነው፡፡

 

ሌላው አሳሳቢው ነገር በየቦታው በሚታዩ ልመናዎች የሚያስተባብሩት ወይም የሚለምኑት ሰዎች ተጠሪነታቸው ለጥቂትና ተመሳሳይ ሰዎች የመሆኑ ነገር ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የፈቃድ ደብዳቤ ብለው በሚይዙት ላይ በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ያሉ ሰዎች በያዟቸው የፈቃድ ደብዳቤዎች ላይ በአንድም በሌላ መንገድ ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በተለይም የአዲስ አበባን የጎዳና ላይ ልመናዎች ገዢ ሆነው የተቀመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ምናልባትም ሕጋዊ መልክ እንዲኖራቸው ከቤተክህነቱ አንዳንድ ግለሰቦች ጋር የጥቅም ግንኙነት ያላቸውም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የሚለምኑት ከሚያስለምኑ ሕጋዊ ነን ከሚሉ ገዢዎቻቸው ጋር ተቀናጅተው የሚፈጽሙት ጥፋት ነው፡፡

 

ሌላው አሳሳቢው ነገር የሀገሪቱን ሕግ የሚያስከብሩ ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊስ ቤተክርስቲያንን እና ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ በመፍራት ለመጠየቅ የሚደፍ ሯቸው አለመሆናቸው ነው፡፡ በፊታቸው የሚዘረጓቸውን ማስፈራሪያ ወረቀቶች አይተው ወይም የሚሰጣቸውን መጽዋች ፈርተው ወይም አይመለከተንም በማለት ወዘተ የሕግ አስከባሪዎች ስለሚያልፏቸው ጠያቂ እንደሌላቸው በማሰብ እነዚህ በቤተክርስቲያን ስም በመለመን የብዙዎችን ገንዘብ አለአግባብ እየዘረፉ ይገኛሉ፡፡

መፍትሔ

ቤተክርስቲያን በስሟ የሚፈጸሙ ልመናዎችን ለማስቆም መትጋት ያለባት አሁን ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሙስናን ከቤተክርስቲያን ለማጥፋት እሠራለሁ ብሎ እየተጋ ባለበት በዚህ ዘመን ከእነዚህ ጥቃቅን ቀበሮዎች ጀምሮ ወደ ታላላቆቹ መገስገስ ይገባዋል፡፡ ታላላቆቹ ሙሰኞች በእነዚህ ጥቃቅን መሠረቶች ላይ የቆሙ ናቸው፡፡

 

ቤተክርስቲያን እንዲህ ያሉ ሕገ ወጦችን ማጥፋት የሚገባት የቅድስና ባለቤት በሆነችው ቤተክርስቲያን ስም የሚፈጸም የስርቆት ተግባር ኃጢአት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በልመና ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ በዚሁ የጥፋት መንገድ ለመሳተፍ እየተንደረደሩ ያሉትን ለመታደግ ይረዳታል፡፡ በሌላ መልኩ ምእመናን ገንዘባቸውን በቤተክርስቲያን ስም እንዳይዘረፉ ከመጠበቅ አንጻር ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የቤተክርስቲያንን ገጽታ እንዳይጎድፍ ከመጠበቅ አንጻር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቤተክርስቲያኒቱ መሠልጠን ያለበት ሕጋዊ አሠራር ብቻ መሆኑን አስረግጦ ለማስረዳት ለማሳየት ይጠቅማል፡፡

 

ስለዚህም በቅድሚያ በቤተክርስቲያን ስም በጎዳና ላይ መለመን ከብዙ ነገሮች አንጻር ምን ያህል አግባብ ነው የሚለውን በውል በማጤን ግልጽ አቋም መያዝ ከቤተክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አስከትሎም አሁን በጎዳና ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ልመናዎችን ሕጋዊነት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ለጎዳና ላይ ልመናዎች ፈቃድ የሚሰጠው ማን ነው? ፈቃዱን ለእነማን ሰጠ? ለምን ዓላማ ሰጠ? ተግባሩ ፈቃድ በተሰጠበት አግባብ ተፈጽሟል? ፈቃዱ እስከ መቼ የሚሠራ ነው? በፈቃዱ የተሰበሰበው ገንዘብ ለታሰበው ዓላማ እየዋለ ነው? በትክክል የፈቃድ ደብዳቤው ወጣ ከተባለበት መዝገብ ቤት ወጥቷል? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን አንሥቶ የቤተክርስቲያኒቱ ታማኝ የሕግ አስከባሪ አካላት ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር መመርመርና እርምጃ ማስወሰድ አለባቸው፡፡

ከቤተክርስቲያን አስተዳደር ሌላ ግን ከመንግሥት አካላት ጋር ተባብሮ ቢያንስ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሌሎች ቁጭቱ ያላቸው አገልጋዮችም የእነዚህን የጎዳና ላይ ልመናዎች ለማስቀረትና የቤተክርስቲያናችንን ክብር ማስጠበቅ አለብን፡፡

መሰናክል ያለበትን ገንዘብ የሚሰበስብ ሰው ገንዘብ በመሰብሰቡ ኃጢአት አድርጓልና እንዳይሰበስብ ይገባዋል/ፍት.ነገ. አንቀ.16 ቁ.648/

ዳግመኛም ገንዘብ እያለው ምጽዋት ለሚቀበል ሰው ወዮለት አለ፤ ራሱን መርዳት እየተቻለው ከሌሎች መቀበልን የሚወድ ሰው ወዮለት እንዲህ ያለውን ግን በፍርድ ቀን እግዚአብሔር ይመረምረውል››/ፍት.ነገ.አንቀ.16 ቁ.634/

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት፤21ኛ ዓመት ቁጥር 7፤ ኅዳር 2006 ዓ.ም.

 

ዘመነ አስተርእዮ

 ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም.

 

ር/ደብር ብርሃኑ አካል

አስተርእዮ ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን መታየት መገለጥ ማለት ነው፡፡ ገሐድ የሚለው ቃልም በጾምነቱ ሌላ ትንታኔ ሲኖረው ትርጉሙ ያው መገለጥ ማለት ነው፡፡ በግሪክ ኤጲፋኒ ይሉታል፡፡ የኛም ሊቃውንት ቀጥታ በመውሰድ ኤጲፋኒያ እያሉ በዜማ መጻሕፍቶቻቸው ይጠሩታል፡፡ ትርጉሙም ከላይ ከጠቀስናቸው ጋር አንድ ነው፡፡

አስተርአየ የተባለው ግሥ ራሱን ችሎ ሳይለወጥ በአምስቱ አዕማድ የሚፈታ ብቸኛ ግሥ ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አስተርአየ፤ ታየ፤ ተያየ፤ አሳየ፤ አስተያየ፤ አየ ተብሎ ይፈታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዘመነ አስተርእዮ ሲያጥር ከጥር 11 ቀን እስከ ጥር 30 ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት 20 ቀናት ይሆናሉ፡፡ ሲረዝም ደግሞ ከጥር 11 ቀን እስከ መጋቢት 3 ቀን ይሆናል፡፡ ይህም 53 ቀናት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

 

ጌታን ለሐዋርያት ህፅበተ እግር ያደረገበት ቀንም ከጸሎተ ሐሙስ እስከ ጰራቅሊጦስ ቢቆጠር 53 ቀናት ስለሚሆኑ የእነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስ በጥምቀት ዕለት ለልዕልና /ጌታ ሰውን ምን ያህል እንዳከበረው/ ለማሳየት እጁን ከጌታ ራስ በላይ ከፍ እንዳደረገ ጌታም ለትህትና እጁን ከሐዋርያት እግር በታች ዝቅ አድርጎ እግራቸውን አጥቧቸዋልና ነው፡፡ ጥምቀት የህጽበት አምሳል ሲሆን፤ /ህጽበት/ መታጠብ በንባብ አንድ ሆኖ ሁለት ምሥጢራት አሉት፡፡

አንደኛ፤- ምእመናን የእንግዳ እግር እንዲያጥቡ ትምህርት ማስተማሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለሐዋርያት ጥምቀት ነው፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ቢጠመቁም መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት የጰራቅሊጦስ ነውና ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፤ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያን ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት እንደጠየቀውና ጥምቀታቸው ህጽበተ እግር መሆኑን እንደመለሰለት፡፡

 

በሌላ በኩል ከዘመነ ልደት እስከ ጥምቀት ተወልደ፤ ተሰገወ /ሰው ሆነ/ ይባላል እንጂ አስተርአየ አይባልም፡፡ ከጥምቀት በኋላ ግን አብሮ ተባብሮ ተጠምቀ፤ ተወለደ፤ ተሰገወ አስተርአየ ይባላል፡፡ ከጥምቀት በፊት አስተርእዮ ለመባሉ በሦስት ነገሮች ነው፡፡

 

አንደኛ፡- የማይታየው ረቂቅ አምላክ በበረት ተወልዶ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ ቢታይና እንደ ሕፃን ሲያለቅስ ቢሰማም ሰው ሁሉ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ሙሉ ሰው ይሆናል እንደሚባለው፤ አምላክ ነኝ ብሎ በአንድ ቀን ሳያድግ በጥቂቱ ማደጉንና ስደት እንደ ውርደት ሆኖ እንዳይቆጠር ለሰዎች ጀምሮ ለመስጠት፤ ሄሮድስም ሊገድለው ይፈልገው ስለነበር የሚሰደድበት እንጂ የሚታይበት ስላልነበረ ነው፡፡

 

ሁለተኛ፡- ሰው በተፈጥሮም ሆነ በትምህርት አዋቂ ቢሆን ለሚመለከተው ሥራና ደረጃ እስከ ተወሰነ ጊዜ ይህ ሕፃን ለእንዲህ ያለ ማዕረግ ይሆናል አይባልም፡፡ ተንከባክባችሁ አሳድጉት ይባላል እንጂ፤ አዋቂ ነው አይባልም፡፡ ያውቃል ተብሎም ለትልቅ ደረጃ አይበቃም፡፡ በየትኛውም ሓላፊነት ላይ አይሰጥም ራሱን በመግዛት ይጠበቃል እንጂ፡፡ እንዲሁም ጌታ የመንፈሳዊ እና የሥጋዊ ባለሥልጣን ቢሆንም ፍፁም ሰው ሆኗልና የሰውን ሥርዓት ከኃጢአት በቀር ለመፈጸም በበሕቀ ልሕቀ ይላል፡፡ አምላክ ነኝና ሁሉን በዕለቱ ልፈጽም ሳይል በየጥቂቱ ማደጉን እናያለን፡፡ በዚህም የተነሣ ሰው ሁሉ 30 ዓመት ሲሆነው ሕግጋትን እንዲወክል እንዲወስን እስከ 30 ዓመት መታገሡ ስለዚሁ ነው፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን ሰው ቢመቸው ይወፍራል፤ ቢከፋው ይከሳል እንጂ ቁመት አይጨምርም አይቀንስም፡፡ ስለዚህ ጌታ ሙሉ ሰው የ30 ዓመት አዕምሮው የተስተካከለለት ሰው /ጎልማሳ ሆኖ በመታየቱ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

 

ሦስተኛው፤- በ30 ዓመት እሱ ሊጠመቅበት ሳይሆን የመጀመሪያ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት መሠረት የሆኑ ጥምቀትንና ጾምን ሰርቶ በመሳየትና መመሪያ አድርጎ በመስጠት አምስት ገበያ ያህል ሰው የቃሉን ትምህርት ለመስማት፤ የእጁን ተአምራት ለማየት፤ እሱ ሙሉ ሰው ሆኖ ተገልጾ ትምህርት፤ ተአምራት የሚያደርግበት ሥራዬ ብሎ የመጣበት መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት የተፈጸመበት ዘመን ነው፡፡

 

የታየውም ብቻ አይደለም፤ አብ ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ ሲል መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ረቂቁ የታየበት የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት ስለሆነ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

 

በዚህ ምክንያትም ሌሎች በዓሎችም ይጠሩበታል፡፡ ለምሳሌ ድንግል ማርያም ጥር 21 ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይቶ በደመና ተነጥቃ ወደ ገነት በመግባት ለጻድቃን ሰዎችና ለመላእክት በሰማይና በምድር የተሰጣት ጸጋና ክብር የተገለጸበት ዕለት ስለሆነ በዓሉ አስተርእዮ ማርያም ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ አምላክ በሥጋ ከድንግል መወለዱን በዚህ አካለ መጠን ለዓለም መገለጡን አስተርእዮ ብሎ ሲናገር፤ አባ ጽጌ ብርሃን ደግሞ በማኅሌተ ጽጌ “የትንቢት አበባ እግዚአብሔር እኛን ሥጋ የሆነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንዲታወቅ ድንግል ሆይ የወገናችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግናለን” ብሏል፡፡ ዳዊትም እንዲህ አለ “በከመ ሰማዕና ከማሁ ርኢነ” መዝ. 47፡6 ፡፡ በነቢያት ይወለዳል ሲባል የሰማነው በበረት ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው እንዲሁም በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አየነው፡፡

 

christmas 1

በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ

 ታኅሣሥ 26 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

christmas 1
በፈቃደ አቡሁ ወረደ፣ኀበ ማርያም ተአንገደ፤ በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ። በጎለ እንስሳ ተወድየ፣ አምኃ ንግሡ ተወፈየ፤ ወከመ ሕጻናት በከየ፣ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ።

በአባቱ ፈቃድ ወረደ፣ በማርያም ዘንድ፣ እንግዳ ሆነ፣ እግዚአብሔር በንጹሕ ድንግልናዋ ተወለደ። በእንስሳት በረት ተጨመረ፣ የንግሡንም እጅ መንሻ፡ ተቀበለ፣ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕጻናት አለቀሰ። (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ)
እግዚአብሔር አምላክ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፈጠረ ሌሎች ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጠሩ ሰውና መላእክት ግን ፍቅሩን ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጠሩ፡፡ ዘፍ 1፡1

የሰው ልጅን /አዳምን/ ፈጥሮ የሚያስፈልገውን አዘጋጅቶ፣ ዕውቀትንና ሥልጣን ሰጥቶ፣ በጸጋ አምላክነትን ሾሞ ፣መመሪያ ሰጥቶ፣ በክበር እንዲኖር ፈቀደለት ፡፡ በመጀመሪያው ዕለትና ሰዓት ከተፈጠሩት መላእክት መካከል በክብር ይልቅ የነበረው ሳጥናኤል /የኋላ ስሙ ዲያብሎስ / አምላከነት በመሻቱ ተወርዶ ሳለ አዳምንም በተዋረደበት ምኞትና ፍላጎት እንዲወድቅ ክብሩን እንዲያጣ ከአምላኩም እንዲለይ አደረገው፤ እግዚአብሔርን፣ ጸጋውን፣ ሹመቱን፣ ወዘተ አጣ /ኃጥአ/፡፡ ኃጢአት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡

አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱና ክብሩን በማጣቱ ተጸጽቶ ንሰሐ ገባ ፡፡ ሥርየተ ኃጢአት የሚሆን መስዋእትም በማቅረቡ፤ እግዚአብሔር አምላክ ልመናውንና መስዋእቱን ተቀብሎ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ቃል ኪዳን ገባለት “መልዓትንና ዓመታትን በዚህ ምድር ላይ ሠራሁልህ፡፡ ይኸውም እነርሱ እስኪፈጸሙ ድረስ በምድር ላይ ትኖርና ትመላለስ ዘንድ ነው፡፡ የፈጠረችህና የተላለፍካት ከገነት ያወጣችህና በወደቅህም ጊዜ ያነሳችህ ዳግመኛም አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም የምታድንህ ቃሌን እልክልሃለሁ” /ገድለ አዳም/ ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው፡፡ አዳምም አምስት ቀን ተኩል የሚለውን ቃል ከእግዚአብሔር በሰማ ጊዜ የእነዚህን ታላላቅ ነገሮች ትርጓሜ ሊያስተውል አልቻለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምስት ቀን ተኩል ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት መሆናቸውን ገልጾ አርአያውና አምሳያው ለሆነው አዳም በቸርነቱ ተርጎመለት፡፡ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠው፡፡ ዘፍ 2፡7 ፣ሔኖክ 19 ፡19 ፣ ኩፋሌ 5፡6

አዳምም ይህንን ተስፋ ለልጆቹ አስተማራቸው፤ ልጆቹም ተስፋው የሚፈጸምበትን ጊዜ ለማወቅ በፀሐይ፣ በጨረቃና በክዋክብት /ዛሬም ቤተክርስቲያናችን ይህንን አቆጣጠር ትጠቀምበታለች/ ዘመናትን እየቆጠሩ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ” ያለውን የአዳኝ ጌታ መወለድን ነብያት ትንቢት እየተናገሩ፤ አበውም ሱባኤ እየገቡ ተስፋውን ይጠብቁ ነበር፡፡ ከነሱም ውስጥ:-

1. ሱባኤ ሔኖክ

ሔኖክ ሱባኤውን ሲቆጥር የነበረው በአበው ትውልድ ሲሆን ሰባቱን መቶ ዓመት አንድ እያለ ቆጥሯል። በስምንተኛው ሱባኤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናግሯል። አቆጣጠሩም ከአዳም ጀምሮ ነው። 8×700=5600ዓመት ይሆናል። 5500ዓመተ ዓለም ሲፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ ያጠይቃል።

ትንቢቱም እንዲህ ይላል። “ስምንተኛይቱ ሰንበት ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅባት ሰባኤ ናት፡፡ ሰይፍም ለርሰዋ ይሰጣታል፤ ታላቁ ንጉሥ የሚመሰገንበት ቤትም በርሰዋ ይሰራል፡፡ ምሥጋናውም ዘላለማዊ ነው፡፡” ሔኖክ 35፡ 1-2 ክፍል 91 በማለት ሲተነብይ መተርጉማን እንዲህ ይመልሱታል፡፡ ለርሰዋ ሰይፍ ይሰጣታል ማለቱ፤ ጸድቅና ኩነኔ የሚታወቅበት ወንጌል ያን ጊዜ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ማለት ነው፡፡ የታላቁን ንጉሥ ቤት ይሠራል ማለቱ፤ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቱስ የሚመሰገንበት ቤተክርስቲያን ትሰራለች ማለት ነው፡፡ ምስጋናውም ዘላለማዊ ነው ማለቱ፤ ሰውና መላእክት በአንድነት ሆነው “ሰብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ ማለት ሲሆን ስምንተኛይቱ ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠችበትን ዕለት ልደት ክርስቶስ ናት ይሏታል፡፡

2 ሱባኤ ዳንኤል

yeledeteስለ ጌታችን ሰው መሆን ጊዜ ወስኖ ሱባኤ ቆጥሮ የተናገረው ዳንኤል ነው፡፡ የዳንኤል ሱባኤ የሚቆጠረው በዓመት ነው ፡፡ ዳንኤል 70ው ዘመን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ ተብሎ በኤርምያስ የተገረውን ትንቢት እያስታወስ ሲጸልይ መልአኩ ቅ/ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጾ እንዲህ ብሎታል፡፡ “እግዚአብሔር ልምናህን ሰምቶሃልና እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ አሁንም ነገሩን መርምር ራእዩንም አስተዋሉ ኅጢአት የሚሰረይበትን ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታም የባህርይ ክብሩን ገንዘብ የሚያደርግበት ሰባው ሱባኤ ሊደርስ ሊፈጸም ነው ብለህ ወገኖችህን ቅጠራቸው ብሎታል፡፡” /ዳን 9፡22- 25 ኤር 29፡1ዐ/

ሰባ ሱባኤ አራት መቶ ዘጠና ዓመት ነው /7ዐX7= 490/ ይህ ጊዜ ከሚጠት እስከ ክርስቶስ መምጣት ያለው ጊዜ ነው /ትርጓሜ ሕዝ፡4፡6/

3. ሱባኤ ኤርምያስ

ኤርምያስ ከባቢሎን እንደተመለሰ በፈረሰው ቤተ መቅደስ ውሰጥ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ራዕይ አየ በሦስተኛው ቀንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ “ፈጣሪያችንን በአንድ ቃሉ አመሰግኑ የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግኑ ከዚህ በኋላ ሰው ሊሆን ሥጋ ሊለብስ ወደዚህ ዓለም ሊመጣ የቀረው 333 ሱባኤ ዕለት ነውና እርሱ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፡፡ አሥራ ሁለት ሐዋርያትንም ይመርጣል…፡፡” ተረፈ ኤር 11፤37 ፣38፣42-48፡፡ ኤርምያስ ሱባኤውን የጀመረበትን ትንቢቱን የተናገረበት ራእዩን ያየበት ዘመን ዓለም በተፈጠረ 5054 ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ከተነገረበት እስከ ክርስቶስ ልደት ያለው ጊዜ 446 ዓመት ነው፡፡

ይኸውም በኤርምያስ ሱባኤ አንዱ 49ዐ ዕለት ነው መላው ሱባኤ 49ዐX333 = 163,170 ዕለት ሲሆን ወደ ዓመት ሲለወጥ 163, 170÷365 =446 ዓመት

ኤርምያስ ሱባኤውን መቁጥር የጀመረበት ዘመን …….. 5ዐ54 ዓመተ ዓለም

ትንቢቱ ከተነገረበት ዓመት እስከ ክርስቶስ ልደት ……. 446 ዓመት

በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት 55ዐዐ ዓመት ሲፈጸም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቱስ መወለዱ በዚህ ይታወቃል፡፡

4. ዓመተ ዓለም

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምረው ሱባኤያትንና ሰንበታትን አውቀው ከአዳም እስከ ክርስቶስ ያለውን ዘመን ቁጥር 55ዐዐ ዓመት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ይኸውም ከአዳም አስከ ኖኅ …… 2256 ዓመት

ከኖኅ እስክ ሙሴ ……… 1588 ዓመት

ከሙሴ እስከ ሰሎሞን …. 593 ዓመት

ከሰሎሞን አስከ ክርስቶስ 1063 ዓመት

                        55ዐዐ ዓመት

ጌታችን ኢየሱስ በተነገረው ትንቢት፤ በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት /ዓመተ ዓለም፣ ዓመተ ኩነኔ ፣ዓመተ ፍዳ/ አምስት ቀን ተኩል / 55ዐዐ ዓመት/ ሲፈጸም /በእግዚአሔር ዘንድ 1ዐዐዐ ቀን እንደ አንድ ቀን ናት፡፡ 2ኛ ጴጥ. 3፤8 / በ5501 ዓመት ማክሰኞ ታኀሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡

“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ ፍጻሜ /የገባው ቃል ኪዳን፣ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባዔ/ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ያጣነውን ልጅነት ሊመልስልን፣ ከተቀማነው ርስት ሊያስገባን፣ የገባንበትን እዳ ሊከፍልልን ተወለደ፡፡

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ ፡፡ ገላ 4፣4 እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ቅዱስ ኤፍሬምም “ ቅድስት ድንግል ማርያም ፍጥረታትን ያስገኘ፤ የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችልን፡፡ የአሮን በትር ለምልማና ፍሬ አፍርታ ተገኝታ ነበር፤ ይህም ክርስቶስ በድንግልና የመወለዱ ምሳሌ ነው፡፡ እጹብ ድንቅ የሆነ ልደት በዛሬዋ ቀን እውን ሆነ፡፡ ድንግል የሆነችው ቅድስት ማርያም በድንግልና ጌታችንን መድኃኒታችንን ወለደችልን፡፡” ብሏል፡፡

“የእሥራኤል እረኛ ሆይ አድምጥ … በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” ብሎ የለመነዉ የዳዊት ልመና በእዉነት ተፈጸመ፡፡ መዝ 70፥1። የእስራኤል እረኛ፤ በእረኞች መካከል በከብቶች በረት ተወለደ። ሉቃ 2፥7፡፡ እረኞች ለእረኛቸው ዘመሩ፤ ላሞች፣ በጎችና አህዮች በበረት የተኛውን ሕፃን በትንፋሻቸው አሟሟቁ። በኦሪት ድንኳን በሙሴ ሕግ መሠረት ለመሥዋዕት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳት በልደቱ ደስ ተሰኙ፤ የነርሱን መሥዋዕት የሚያስቀር አማናዊው የእግዚአብሔር በግ ተወልዷልና።

ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እግዚአብሔር በጨለማው ዓለማችን ተወለደ። (ዮሐ.1፥9-14) ነቢያትና መምህራን ጠፍተውባት፣ የኃጢአት ጨለማ ዉጧት፣ በድንቁርና ባሕር ውስጥ ሰጥማ በነበረችው የሰው ልጆች ዓለም የእውነት ፀሐይ ወጣ። እነሆ ይህን ይገልጥ ዘንድ መድኅን በእኩለ ሌሊት በጨለማ ተወለደ፤ በተወለደ ጊዜ ግን ክብሩ በዙርያው አበራ። (ሉቃ.2፥8-9)

ለመንግሥቱ ወርቅ ተገበረለት። ኃያል መንግሥቱን ግን በምድር ላይ በትህትና ነበር የገለጣት፤ በከብቶች በረት በመወለድና በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ በመሄድ። (ሉቃ.19፥28-38) የአባታችን የዳዊት መንግሥት ያለልክ ከፍ ከፍ አለች፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የዳዊት ልጅ ሆኗልና። ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ “እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል፤ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለዉም” ብሎ የተናገረዉ ዛሬ ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ.1፥32)፡፡

በባሕርይው የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነዉ የእግዚአብሔር ልጅ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ነስቶ ሰዉ በሆነ ጊዜ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እስከ ጽርሐ አርያም ድረስ ከፍ ከፍ አደረጋት። እነሆ ንጉሥ ክርስቶስ በያዕቆብ ቤት (በምእመናን) ላይ ለዘላለም ነገሠ። ለመንግሥቱ የአሕዛብ ነገሥታት ተገዙላት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና ፍጥረታት ሁሉ ይገዙላታል። (ኤር.23፥5)

ለክህነቱ ዕጣን ተሰጠው። ክህነቱም የአበውን እና የሌዋውያንን ክህነት የምትፈጽም የዘላለም ሰማያዊት ሥራው ናት። እነሆ የአብ ሊቀ ካህናት እርሱ የሰውን ባሕርይ ከራሱ ጋር አስማማ። ራሱ ካህን፣ ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ ተቀባይ ሆኖ የፈጸማት የክህነት ሥራው የዘላለም ድኅነትን አስገኘች።

ለሞቱ ከርቤ ቀረበለት። እነሆ እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት በሞቱ ሞትን ድል ለመንሣት ነውና በልደቱ ሞቱ ተሰበከ። ከርቤ ለሞቱ ሲቀርብለት የማይሞተው እርሱ ለሰው ልጆች ሲል የሚሞት ሥጋን እንደለበሰ ታወቀ።

የአሕዛብ ነገሥታት ወርቅ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ጽሩይ፣ ንጹሕ፣ ሰማያዊ የሆነ ልቦናን እና እምነትን ለእርሱ እናቀርባለን። (1ኛ ጴጥ.1፥6) ሰብአ ሰገል ራሱ የፈጠረውን ወርቅ ገበሩለት፤ እኛም በርሱ ጸጋና ሥራ ያገኘነውን ንጹሕና ሰማያዊ እምነታችንን እናቀርብለታለን (ይሁ.3)።

ነገሥታቱ ዕጣን ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ቂም በቀል የሌለበትን፣ ከመልካም እና ከንጹሕ ልብ የሚወጣ የምስጋና ጸሎት እናቀርባለን፤ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴንም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።” እንዳለ ንጉሥ ዳዊት (መዝ.140፥2) ።

ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ለሚቀበለው ሞት ከርቤ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለሰው ልጆች ያለንን ፍቅር ለእርሱ እናቀርባለን። ነገሥታቱ እርሱ ከፈጠረው ከርቤ ወስደው እጅ መንሻ አቀረቡ፡፡ ምእመናን ደግሞ ከእርሱ ከተማርነው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከተቀበልነው ፍቅር መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን። “እርሱ ስለኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል፡፡ (1ኛ ዮሐ.3፥16)።”

ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸዉ” ብሎ የተናገረዉ ትንቢት ተፈጸመ (ኢሳ.9፥2)። የቅድስናዉ ተራራና ማደሪያው ወደ ሆነች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወስደናል፡፡ በዚች የዘላለም ሃገራችንም የሚያበራልን ፀሐያችን እርሱ ነዉ፡፡ (ራእይ.21፥23)።

እነሆ ሰው የመሆኑ ዜና የሰው ልጆች ሁሉ ደስታ ነው፡፡ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” የሚል ዜና በሰማያውያን መላእክት ተሰበከ። (ለቃ.2፥11)

የምድር ኃያላን ነገሥታት በከብቶች በረት ውስጥ በጨርቅ ተጠቅልሎ ለተኛው ሕፃን መብዓ አቀረቡ። ንጹሐንና ኃያላን የሚሆኑ የሰማይ መላእክት ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ፍቅር ሲል እንደ ሕፃን ተጠቅልሎ ሲያዩ በታላቅ ትሕትና ከእረኞች ጋር ዘመሩ። (ሉቃ.2፥13)

በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ድንቅ ነገር ተደረገ። ዳዊት በወርቅ ያጌጠ የተልባ እግር መጎናጸፊያ የለበሰባት ቤተልሔም የሰማይና የምድር ፈጣሪ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተገኘባት። ቤተልሔም ከዳዊት ዘመን አብልጣ ከበረች፤ የእግዚአብሔር ክብር አብርቶባታልና፤ የልዑላን መላእክት ዝማሬ ተሰምቶባታልና። (ሚክ.5፥2)

በዚህች ዕለት እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኞች መጣ፤ ስለዚህ ጻድቁ በኃጢአተኞች ላይ አይታበይ፡፡ በዚህች ቀን የሁሉ ጌታ የሆነው እርሱ ወደ ባሮቹ መጣ፤ እናንተ ጌቶች ሆይ እንደ ጌታችን ለአገልጋዮቻችሁ ቸርነትን አድርጉላቸው፡፡ በዚህች ቀን ባለጠጋ የሆነው እርሱ ስለ እኛ ሲል ደሃ ሆነ፡፡ እናንተ ባለጠጎች ሆይ ከማዕዳችሁ ለድሃው አካፍሉ፡፡ በዚህች ቀን እኛ ያላሰብነውን ስጦታ ከጌታ ዘንድ ተቀበልን፤ እኛም ምጽዋትን ለሚጠይቁን ድሆች ቸርነትን እናድርግ፡፡ ከእኛ ይቅርታን ሽተው የመጡትን ይቅር እንበላቸው፡፡ በዛሬዋ ቀን የፍጥረት ጌታ የሆነው እርሱ ከባሕርይው ውጪ የሰውን ተፈጥሮ ገንዘቡ አድርጎ በሥጋ ተገልጦአልና፣ እኛም ወደ ክፉ ፈቃድ የሚወስደንን ዐመፃ ከእኛ ዘንድ አርቀን በአዲስና እርሱ በሰጠን መንፈሳዊ ተፈጥሮ እንኑር፡፡… እኛ በአምላክ ማኅተም እንድንታተም እርሱ አምላክነቱን ከእኛ በነሳው ሥጋ አተመው፡፡…ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡

የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር ፍቅሩን እያሰብን በኃጢያታችን ምክንያት ከልባችን ያወጣነው ሁሉ ዛሬም በልባችን እንዲወለድ ያስፈልጋል፡፡ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ?” ማቴ. 2÷1
እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ?

ከንጹሕ ባሕርይ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በደስታ ይኖር የነበረ ሰው የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፉ ከንጽህና ወጥቶ ኃጢአትን ለበሰ:: ሕይወቱን አስወስዶ ሞትን ተቀበለ:: የእግዚአብሔር ልጅነቱን አስቀርቶ የዲያቢሎስ ምርኮ ሆነ:: ደስታውን አጥቶ ኃዘን አገኘው:: ተጸጽቶ የጥንት ሕይወቱንና ደስታውን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፤ ንጹህ ባሕርይው ስላደፈበት የሞት ፍርድን ሊያስቀርለት አልቻለም::

ዳግማዊ አዳም የተባለ የፍቅር አምላክ፣ የሁሉ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሞት ፍርድን ሊያስቀር ኃጢአትን ደምስሶ ከሞት ፍርድና ከገሃነም ነጻ ሊያወጣ ዘር ምክንያት ሳይሆነው ሰው ሆነ፤ ተወለደ:: “እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም።” 1ዮሐ 3:5

በዚህም መሰረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም ዘመነ ዮሐንስ መጋቢት ሀያ ዘጠኝ ቀን እሑድ ከቀኑ ሶስት ሰዓት ተጸነሰ:: በአምስት ሺህ አምስት መቶ አንድ ዓመተ ዓለም በዘመነ ማቴዎስ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ማክሰኞ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ተወለደ::

ገናና የገና ጨዋታ

ገና-ጌና-ገኒን-ገነ፤ልደት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በዓል ገና ወይም በዓለ ልደት በመባል ይታወቃል:: ገና የሚለው ቃል ገነወ አመለከ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ነው:: የጌታችን ልደትም የአምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ የመሆን ምሥጢር የተገለጠበት ታላቅና ገናና ስለሆነ ገና ተብሏል:: አምላክ አለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል እንዲል ሃይማኖተ አበው::

የገና ጨዋታ

በሃገራችን በኢትዮጵያ የገና በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ደምቆ ይከበራል:: በተለይ በገጠሩ ያገራችን ክፍል ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘ አባቶችና እናቶች ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በገና ይደረድራሉ:: ወጣቶችም የገና ጨዋታ ይጫወታሉ:: “በገና” ስሙን ያገኘው በገና በዓል ወቅት የሚደረደር በመሆኑ ነው ሲሉ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ:: በሌላም ትውፊት በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችና አዛውንቶች የሚጫወቱት የገና ጨዋታ ራሱን የቻለ ባህልና ትውፊት አለው:: የገና ጨዋታ ራሱ በተቆለመመ በትርና ሩር የተባለ ከዛፍ ሥር በተሠራ ክብ እንጨት(ኳስ) እያጎኑ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡

ሰብአ ሰገል በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም ሲሔዱ “የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት አለ” በማለት ቢጠይቁ ይህንን አስደንጋጭ ጥያቄ የሰማው ንጉሥ ሔሮድስ “እኔ ንጉሥ ሆኜ ሳለሁ ሌላ ንጉሥ እንዴት ይወለዳል” በማለት የተወለደውን ንጉሥ ለመግደል አገልጋዮቹን ከሰብአ ሰገል ጋር ሄደው ቦታውን አይተው እንዲመለሱ ላካቸው፡፡ የሔሮድስ አገልጋዮች ከተቀላቀሉ በኋላ እየመራ ያመጣቸው ኮከብ ጌታ የተወለደበትን ቦታ መምራቱን አቆመ፡፡ ሰብአ ሰገል ተጨንቀው “የኮከቡ እርዳታ ለምን ተለየን” ብለው ሲመረምሩ ከነሱ ዓላማ ውጭ ሌላ ሀሳብና ተንኮል ይዘው የተገኙ ሰዎችን አገኙ፡፡ “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔርን እርዳታ አጣን”፡፡ ብለው ሦስቱም ነገሥታት(ሰብአ ሰገል) ከአንዱ ወደ አንዱ እየተቀባበሉ በብትር እየመቱ አስወገዷቸው፡፡

ኮከቡም እየመራ ጌታ በተወለደበት ቦታ ቤተልሔም አደረሳቸው ከእረኞችና ከመላእክት ጋራ አመሰገኑት፡፡ እረኞች ጌታ በተወለደ ጊዜ ጨለማ ተሸንፎ አካባቢያቸው በብርሃን ተመልቶ መንፈስ ቅዱስ በገለጸላቸው ምስጢር ከመላእክት ጋራ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” እያሉ ሲያመስግኑና ሲደሰቱ አድረዋል፡፡ በአሉ እረኞች ክብር ያገኙበት ምስጢር የተገለጠላቸው ስለሆነ በስነ ቃል “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለም በጨዋታ እንደሚከበር እንደሆነ አበው ይናገራሉ፡፡

ይህ ትውፊት የገና ጨዋታ እየተባለ ወጣቶች አዛውንቶች በጨዋታ ያከብሩታል፡፡ ራሱ የተቆለመመውና ሩሯን የሚያጎነው በትር የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ሩሩ ደግሞ የሳጥናኤል ምሳሌ ነው:: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድረጎ የሰውን ሥጋ በመልበስ ወደዚህ ምድር እንደመጣና በሩር የተመሰለውን ሰይጣንን እንደቀጠቀጠው የሚያሳይ ምሥጢር ያለው ጨዋታ ነው::

 

 

 

sidet2

ከስደት የመመለሱ ምሥጢር

 ኅዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ

እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ሊያደርገው ያሰበውን ነገረ ድኅነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳንና ቅድመ ብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ በተለያየ መንገድ መግለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል ዕብ 1÷1:: ምክንያቱም ፈታሒነቱና መሐሪነቱ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ነው ይሏል፡፡ የሰው ልጆች በዚያ ዘመን እግዚአብሔር ፈታሒነቱን በተከፈላቸው የኃጢአት ደመዎዝ የተረዱ ሲሆን መሐሪነቱን ደግሞ በተለያየ ኅብረ አምሳል መግለጹ አልቀረም:: ከእነዚያ ብዙ ከምንላቸው ኅብረ አምሳላት አንዱ እንዲህ የሚለው ነው “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ መሆን በጀመረ ጊዜ ወንድሞቹን ሊጎበኛቸው ወደ ወንድሞቹ ወጣ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ ተመለከተ” ዘጸ.2÷11፡፡ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ላደገው ለዚያ ሰው የተነገረለት ቃል በዕውነት አስደናቂ ነው፡፡ ዕድሜው በአባቶቻችን አነጋገር አርባ ዓመት ሆኖት የነበረው ይህ ሰው በጉብዝናው ወራት ወደ ወገኖቹ ሲመጣ ከተማው መከራ የበዛበት፤ ሕዝቡ ለቅሶና ዋይታ የጸናበት አስቸጋሪ ወቅት ሆኖ ነበር የጠበቀው፡፡ የሰው ልጆች ከአስገባሪዎቻቸው የተነሣ እስከ ጽርሐ አርያም ዘልቆ የሚሰማ ጩኸታቸውን አሰምተው የጮሁበት፤ እግዚአብሔርም የሰውን ጩኸት የሰማበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የመከራው ማለቂያ፤ የመጎብኘቱ ዘመን መግቢያ ነበር ማለት ነው፤ በመከራ ዘመን የሚጎበኝ ወዳጅ ታማኝ ወዳጅ ነውና፡፡

ይህ የመጎብኘት ወራት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚመጣበት ወራት አምሳል መርገፍ የሚሆን ወቅት ነበር፡፡ በዚያኛው ወራት የተነሣው ጎበዝ በመከራ ውስጥ ለነበረው ሕዝብ የደረሰለላቸው በአርባኛው ዓመቱ ነበር፡፡ በዚህኛው ወራት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶከስም ለሕዝቡ የደረሰለት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ነው (ዘመነ አበው፣ ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ነገሥት፣ ዘመነ ካህናት) እነዚህ አራት ክፍላተ አዝማናት በእውነት የሙሴን አርባ ዓመታት ይመስላሉ፡፡ የሙሴ አርባ ዓመታት በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ በዝምታ ያለፉ ዓመታት ናቸው፡፡

እስከ አርባ ዓመት ድረስ ሙሴ ወደ ወገኖቹ ሳይወጣ ለምን ዘገየ? በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ ያደገ ሰው ቢሆንም ቅሉ ፈረዖናዊ እንዳልሆነ ከእናቱ የሰማው ገና በልጅነት ዘመኑ አልነበረምን? ቢሆንም ግን ዘገየ፡፡ የፈርዖናውያን ግፍ እስኪፈጸም፤ የእስራኤልም መከራ እስኪደመደም አልጎበኛቸውም ነበር፡፡ ዛሬ የእስራኤል የመጎብኘት ወራት ከመድረሱም ባሻገር ሙሴ ጎበዝ በመሆኑ ግብፃዊውን ገድሎ እስራኤላዊውን ማዳን የሚችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ ስለዚህም ወደ ወገኖቹ ወጣ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዝምታ ያሳለፋቸው አራቱ ክፍላተ አዝማናትም ከዚህ ጋር ተመሳሳዮች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ የቀኖና ጊዜውን እስኪያጠቃልል መንጸፈ ደይን ወድቆ ለዘመን ዘመናት ያለቀሰ ቢሆንም በአራቱም ክፍላተ አዝማናት የነበረው የእግዚአብሔር ዝምታ አንዳንዶችን “ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል አዶናይ፤ በዚህ ሰማይ እስራኤልን የሚጠብቅ ጌታ እግዚአብሔር የለምን?” ብለው በሰለለ ድምፅ እንዲናገሩ አድርጓቸዋል፡፡

የመጎብኘት ጊዜው ሲደርስ የዲያብሎስ ምክሩ እንዲፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ወደ ወገኖቹ መጣ፡፡ ይህ ወራት የአዳም ሥጋ ጎበዝ እየሆነ የመጣበት ወራት በመሆኑ በወገኖቹ ላይ የነበረውን ፍዳና መርገምን እንቢ ብሎ ያለ ኃጢአትና ያለ በደል ሆኖ ተፀነሰ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የግብፃዊው ምሳሌ የሆነው ዲያብሎስ ጉድጓዱ ተማሰ፤ ወገኖቹን ሊጎበኛቸው በመጣው በዚያ ሰው በኩል የማይደፈረው ተደፈረ፤ ግብፃዊው ተቀበረ፡፡ ይህ ጎበዝ እየሆነ የመጣው የሙሴ ወገኖች የተስፋ ምልክት እንደነበረ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን ለተደረገለት ቅዱስ ሕዝብም እግዚአብሔር ወደ ወገኖቹ የመጣባት የመጀመሪያዋ ዕለተ ፅንስ ከሲዖል እስከዚህ ዓለም ለነበሩ ነፍሳት የፀሐይ ብርሃን ብልጭ ያለባት ዕለት ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ የዓመተ ምሕረት መጀመሪያ አድርገን እንቆጥራታለን፡፡

ምንም እንኳን ሙሴ ግብፃዊውን ገድሎ ሊታደጋቸው የሚችል መሆኑን ያስመሰከረ ቢሆንም ወገኖቹ ግን በእልልታ የተቀበሉት አይደሉም፡፡ እርሱ ግን በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያምኑ ይመስለው ነበር ሐዋ.ሥራ.7÷25፡፡ እስራኤልን የመታደግ ሥራውን ግብፃዊውን በመግደል የጀመረው ያ ታላቁ ታዳጊያቸው ከሁለት ቀን በኋላ ባደረገው ወገኖቹን የመጎብኘት ሥራ ከወገኖቹ በጎ ነገርን ሊያስገኝለት አልቻለም፤ ከሀገር ወጥቶ እንዲሰደድ የሚያደርግ ክፉ ሀሳባቸውን ሰማ እንጂ፡፡ ከወገኖቹ ከንቱ ሀሳብ የተነሣ አርባ ዓመታትን ያለ ኃጢአትና በደሉ በስደት አሳለፈ የምድያምን ካህን በጎች እየጠበቀ በባዕድ ምድር ለረጅም ዘመን ተቅበዘበዘ፡፡ ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ሲሄድ የንጉሡ የልጅ ልጅ መባልን እንደ መቀማት አልቆጠረውም ራሱን ዝቅ አድርጎ በምድያማውያን ምድር ለሚገጥመው የመስቀል መከራ እንኳን የታዘዘ ሆነ እንጂ፤ የግብፅ ጌታዋ ሙሴ እንደ ባሪያ ዝቅ ብሎ የበግ እረኛ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከቀደሙት መሳፍንት ሁሉ በላይ የሆነ ስምን ሰጠው በግብፅ ካለው ተድላ ደስታ ይልቅ ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን መርጧልና መከራ በተቀበለላቸው ወገኖቹ ላይ ሹም አድርጎ ደስ አሰኘው፡፡

sidet2የአባቶቹን ዕዳ ሊከፍል የመጣው ዳግማዊው ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዓለም ነቢያትን እንዳሳደደች እርሱንም እንዲሁ አደረገችበት፡፡ ሙሴ ግብፃዊውን በገደለውና ለእስራኤልም የመዳን ተስፋን ባሳየ በሁለተኛው ቀን ከሀገር አስወጥታ እንዳሳደደች፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በሰው ልጆች ታሪክ ጉልህ ስፍራ የነበረውን ቁራኝነትን በማጥፋት ይቅርታውን አሐዱ ብሎ በጀመረበት በሁለተኛ ልደቱ ሲገለጥ በገዛ ወገኖቹ በካህናትና በነገሥታት ምክር ከሀገር ወጥቶ ተሰደደ፡፡ ሙሴ ወደ ወገኖቹ የመጣባት ሁለተኛይቱ ቀን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም በሥጋ የመጣባት ሁለተኛይቱ ልደቱ ሲነጻጸሩ እጅግ ይገርማሉ፡፡ ስለ ወገን እንጂ ስለ ራስ መኖርን የሚያስንቁ ዕለታት! እንደዚያኛው ወራት በዚህም ወራት ስለ ሕዝቡ የሚቆረቆር ሌላ ሙሴ ለምድር ተወልዶላታል፡፡ እግዚአብሔርነቱን እንደ መቀማት ሳይቆጥረው የባሪያውን መልክ ይዞ ከሰማይ ወደ ምድር መጣ፡፡ በብዙ ሠራዊት ዘንድ ጌታ የሆነው እርሱ ከአብ ጋር ተካክሎ ሲኖር ሳለ በፈቃዱ ከክፉ ወገኖቹ መካከል ተለይቶ ወደ ምድረ አፍሪቃ ተሰደደ፡፡ ሙሴን የሕዝቡ መከራ ውል ብሎ እየታየው በፈርዖን ቤት በደስታ መኖርን እንደከለከለው ከሕዝቡ ጋርም ስለሕዝቡ መከራ መቀበልን እንዲመርጥ እንዳደረገው ኢየሱስ ክርስቶስንም በሕዝቡ የደረሰው ግፍ ከሰማይ ወደ ምድር አመጣው፤ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች እስኪል ድረስ አስጨነቀው ፡፡

ሙሴ ስለ ሕዝቡ ወደ ምድረ አፍሪቃ ወርዶ በግ ጠባቂነትን ሥራ አድርጎ ኖረ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱን የገለጠው በዚህ ስም እንደነበረ ቅዱስ ወንጌል ምስክርነትን ይሰጠናል “እኔ የበጎች እረኛ ነኝ” እንዲል ዮሐ10÷11፡፡ በእውነት እዚህ ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ዐሳብ እስኪ በደንብ ተመልከቱት፡፡ ለአርባ ዓመታት ግብፃዊነትን ስሙ አድርጎ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን ተቀብሎ ይኖር የነበረው ሰው ሙሴን አስነስቶ በጉብዝናው ወራት ወገኖቹን አስጎበኘው፡፡ ያንን ተከትሎ ግብፅን ለቆ እንዲወጣ አድርጎ ከሌሎች ዐርባ ዓመታት በኋላ ተመልሶ ወገኖቹን እንዲያድናቸው አደረገው፡፡ እግዚአብሔር ጥበበኛ አምላክ ነው፤ ያባቶቹን የያዕቆብንና የአስራ ሁለቱን አባቶች ስደት የሚመልስ ትውልድ አስነስቶ ከግብፅ በተገኘው ሰው ግብፅን በዘበዛት፡፡ ይህንንም በማድረጉ በዚህኛው ወራት ለኛ ሊያደርጋት ያሰባትን በጎ ነገር አስቀድሞ ነገረን፡፡ በዚያኛው ወራት ሕዝቡን የታደገው መሪ በግብፅ ምድር ተወልዶ በፈርዖን ቤት ያደገ ነው እንዳልን ሁሉ በዚህኛው ዘመን ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስም ከግብፃዊው ሰው ከአዳም የተገኘ ተገኝቶም ስለ ወገኖቹ የሚቆረቆር ሆነ፡፡ በአባ እንጦንስ አነጋገር ግብፃዊ ማለት ሥጋዊ ስሜቱን ብቻ የሚንከባከብ ሰው ስያሜ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ወደ ገዳማቸው እንግዳ ሲመጣ ስለመጣው እንግዳ መረዳት ሲፈልጉ እንግዳውን ለሚቀበለው ደቀ መዝሙር የሚያቀርቡት ጥያቄ “ግብፃዊ ነው? ወይስ ኢየሩሳሌማዊ?” የሚል ነበር:: ሥጋዊው በግብፃዊ መንፈሳዊው በኢየሩሳሌም ይሰየማሉና፡፡

የሙሴ እናት በፈርዖናዊው የባርነት ወቅት ሳለች ሙሴን ወለደች ለሌላው ትውልድ መድኃኒት እንዲሆን ታስቦም ለሦስት ወራት ሸሸገችው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የተወለደው ዓለም በዲያብሎስ ብርቱ የዐመጻ ውጊያ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ነበር፡፡ በተወለደበት ወቅት ብዙ ሕፃናት ለሞት የተዳረጉ ቢሆንም እርሱ ግን ለብዙዎቹ ለመዳናቸው፤ ለመነሣታቸው የተሾመ ነበርና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ሶስት ዓመታትን ሸሸገችው፡፡ ከዚያም በኋላ በግብፃውያን መካከል አድጎ ለግብፃዊቷ ዓለም ይደርስ ዘንድ ስደትን ገንዘብ አደረገ የአባቱ ያዕቆብ እና የሌሎችም ቅዱሳን ስደት እንዲያበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰደደ፡፡ ሲሰደድ ከጥቂቶቹ በስተቀር ስደቱን ማን አወቀ? ሕዝቡን ሲያወጣ ግን በሁሉም ዘንድ የተገለጠ ነበር፡፡ ስደቱ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ መዳን ምክንያት ይሆናል ብሎ ማን አሰበ? ግን ሆነ፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አፍሪቃ ምድር ተሰዶም እንደ ሙሴ በእግዚአብሔር መልአክ እስኪጠራ ድረስ በምድረ አፍሪቃ መቀመጥን መረጠ ዘጸ3÷4፤ማቴ2÷20፡፡ ለዚህም ነው በመነኮሳቱ መጽሐፍ “ንዑ ንርአዮ ለወልደ መንክራት” ተብሎ የተጻፈው፡፡ ሙሴ ከግብፅ አስማተኞች ጋር ባደረገው ክርክር አሸንፎ ሕዝቡን ይዞ በመኮብለል ከግብፅ ወጣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በግብፅ ያሉትን ገዳመ ሲሐትን፤ ገዳመ አስቄጥስን ባርኮ፤ በግብፃውያን የሚመሰሉ አጋንንትን አባሮ እስክንድርያን መንበር አደረጋት፡፡ ከዚያ እስከ ዛሬ ግብፅ ያፈራቻቸው ቅዱሳን ሁሉ የዚያ ስደት ውጤቶች ናቸው፡፡ በሙሴ ወደ ግብፅ መመለስ የሞቱትም በሕይወት ያሉትም እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደ ተመለሱ፤ አማናዊው ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስም በስደቱ ለሞቱትም በሕይወት ላሉትም አባቶቻችን ተስፋ እያደረጓት ሳያገኟት ከሩቅ እየተሳለሟት ወደ አለፏት ቅድስት ምድር መንግሥተ ሰማያት ለመመለሳቸው ምልክት ሆነ፡፡ የክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወደ ግብፅ መሄድ ከገነት ወደ ሲኦል ያለውን የሰው ልጆች ስደት የሚያመለክት ሲሆን፤ ከግብፅ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው መመለስ ደግሞ ከሲኦል ወደ መንግሥተ ሰማያት ያደረግነውን የይቅርታ ጉዞ ያሳያል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሙሴ መታዘዝና ወደ ግብፅ መውረድ ሕገ ኦሪት በሙሴ ተመሠረተች፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መስቀል የደረሰ መታዘዝ ወንጌል ተመሠረተች፡፡ ለሁሉም ግን መሠረቱ ስደት መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡ በዚያኛው ወራት በሙሴ የተመሰረተችው ማኅበር በዚህኛው ወራት በኢየሱስ ክርስቶስ ለተመሰረተችው ማኅበር ምሳሌ ነበረች፡፡ አባቶቻችን ነቢያቱ የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን እንደ ስደተኛ ቆጥረው “ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ፤ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ ተመለሽ” መኃ 7÷1 እያሉ ሊያዩአት ሲመኙ ነበሩ ጊዜው ሲደርስ የሄሮድስ ሞት የስደት ዘመኗን አሳለፈው፡፡ ሔሮድስ የዲያብሎስ ምሳሌ ሲሆን ዲያብሎስ በመስቀል ራስ ራሱን ተቀጥቅጦ ሲሞት ቤተ ክርስቲያን ግን መኖር ጀመረች፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ በጠላቶቿ ላይ ድልን እየተቀዳጀች፤ ጠላቶቿን አሳልፋ ባለ ማለፍ ጸንታ ትኖራለች፡፡

እመቤታችን የሄሮድስን ሞት ከሰማች በኋላ ቁስቋም ከሚባል ተራራ ላይ ሆና ደስታዋን አብረዋት መከራን ከተቀበሉት ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር አከበረች፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ደስታ የሚጀምረው በተራራ ላይ ነው፡፡ እመቤታችን ደብረ ቁስቋም ላይ ሆና ከአባቷ ዳዊት ጋር “ርኢክዎ ለኃጥእ አብየ ወተለዐለ ከመ አርዘ ሊባኖስ ወሶበ እገብዕ ኃጣዕክዎ፤ ኃጥእ ሔሮድስን ከፍ ከፍ ብሎ ተመለከትኩት ስመለስ ግን አጣሁት” መዝ 36÷35 ብላ ዘመረች፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ቀራንዮ ላይ ለዘመን ዘመናት ያስጨነቃት ዲያብሎስ ተወግዶላት የሞቱትንም በሕይወት ያሉትንም አንድ አድርጋ በደስታ ዘመረች፡፡ የዚያኛው ወራት ስደት ለቀደመው የእግዚአብሔር ሕዝብ ከግብፅ መውጣት፤ የዚህኛው ወራት ስደት ለአሁኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሲኦል መውጣት ፊታውራሪ ነው፡፡ ያኛው ሕዝብ በዚያኛው ስደት እንደተዋጀ ይሄኛው ሕዝብ ደግሞ በዚህኛው ስደት ተዋጀ፡፡ ምክንያቱም ስደቱ ስደታችንን ሲያመለክት መመለሱ መመለሳችንን ያሳያልና፡፡

 

አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል

 መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም. 

በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል አምላካችን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፤ እንደ ሕፃናት ቀስ በቀስ አድጎ፤ ወንጌልን ለዓለም ሰብኮ፤ ለሰው ልጆች ቤዛ ይሆን ዘንድ፤ በሞቱ ሞትን ይሽር ዘንድ፤ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በትንሣኤውም ለሰው ልጆች ትንሣኤን አወጀ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የነበረውንም የጥል ግድግዳ አፈረሰ፡፡ የሰው ልጆች ያጣነውን የእግዚአብሔር ልጅነትንም አገኘን፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርኁከ ከመ ያመስጡ እምገጸ ቅስት ወይድኅኑ ፍቁራኒከ” ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው መዝ.49፡4 እንዲል፡፡ “ጠላቶቻችንን በአንተ ድል አናደርጋቸዋለን” በማለት የመስቀልን ክብርና አሸናፊነት አብስሯል፡፡መዝ. 43፡5፡፡

“እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኀኒተ በማዕከለ ምድር” እግዚአብሔር ዓለም ከመፈጠሩም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኀኒትን አደረገ፡፡ መዝ. 73፡16 በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደተቀኘው እግዚአብሔር የሰውን ልጆች ለማዳን የቃልኪዳን ቦታዎችን በዚህች ምድር ላይ አዘጋጅቷል፡፡ በዓለም ላይ ቃል ኪዳን ከተሰጣቸው ቅዱሳት መካናት መካከል አብዛኛዎቹ በኢትዮጵያ ሀገራችን ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በግምባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አንዷ ናት፡፡ አባቶቻችን “ግሸን ደብረ ከርቤ መካነ መስቀሉ ለክርስቶስ እንተ ይእቲ ኢየሩሳሌም” የክርስቶስ መስቀል መንበር የሆነችው ግሸን ደብረ ከርቤ ናት ይህችውም ኢየሩሳሌም ናት በማለት ግሸን ደብረ ከርቤ ከኢየሩሳሌም ጋር እኩል መሆኗን መስክረውላታል፡፡

የጌታን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መስቀል በቅድስት እሌኒ በ325 ዓ.ም. ከተቀበረበት ከወጣና በክብር ለረጅም ዓመታት በኢየሩሳሌም ከተቀመጠ በኋላ ዐረቦች ኢየሩሳሌምን በመውረራቸው ምክንያት በአረማውያን እጅ እየተማረከ ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር ሲንከራተት ቆይቷል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖችም በመስቀሉ መማረክ ያዝኑና ይበሳጩ ስለነበር ጦራቸውን አሰልፈው መስቀሉ ወደሔደበት ሀገር በመዝመት ጦርነት ያካሔዱ ነበር፡፡

በ778 ዓ.ም. አራቱ አኅጉራት ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ በአራቱ የመስቀሉ ክንፍ የተያያዙት ምልክቶችን በማንሳት የተከፋፈሉ ሲሆን በወቅቱ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ዐረቦች በእስክንድርያ ለሚኖሩ አባቶች የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሮቹ እና እጆቹ ተቸንክረው የተሰቀለበትን ሙሉ መስቀል ላኩላቸው፡፡ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስም በክብርና በጥንቃቄ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡

የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር መስቀሉ ለብዙ ዘመናት በግብፅ እስክንድርያ ከቆየ በኋላ የግብፅ እስላሞች ቁጥራቸው በመበራከቱ በክርስቲያኖች ላይ የመከራ ቀንበር ስላጸኑባቸው ከዚህ ስቃይ ይታደጓቸው ዘንድ ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት “ንጉሥ ሆይ በዚህ በግብፅ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንስተህ አስታግስልን” ብለው ይልካሉ፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት ደግሞ የግብፅ ንጉሥ አቡነ ሚካኤልንና አቡነ ገብርኤልን በማሰሩ ምክንያት ከዚህ አስከፊ ችግር እንዲታደጓቸው ክርስቲያኖች መልእክት እንደላኩባቸው ይገለጻል፡፡ መልእክቱ የደረሳቸው ፄ ዳዊትም ስለ ሃይማኖታቸው በመቅናት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት አሰልፈው ወደ ግብፅ ይዘምታሉ፡፡ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከልም እርቅ እንዲወርድ ተደረገ፡፡

የግብፅ ክርስቲያኖችም ዐፄ ዳዊት ስላደረጉላቸው መልካም ነገር እጅ መንሻ ይሆናቸው ዘንድ ብዛት ያለው ወርቅና ብር ያቀርባሉ፡፡ ዐፄ ዳዊት ግን ፍላጎታቸው ወርቅና ብሩን መውሰድ ሳይሆን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ፡፡ በጥያቄያቸውም መሠረት ተሰጣቸው፡፡ “መስቀልየ ይነብር በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ አይተው ስለነበር ጉዟቸውን በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ያደርጋሉ፡፡ በመንገድም እያሉ ያርፋሉ፡፡ ዐፄ ዳዊት መስከረም 10 ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከግብፃውያን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ተቀጸል ጽጌ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

ከዐፄ ዳዊት በኋላ በቦታቸው የተተኩት ዐፄ ዘርዐያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ በማየታቸው መስቀሉን በ1443 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በተለያዩ ቦታዎች ለማሳረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ በደብረ ብርሃን፤ በሸዋ ደርሄ ማርያም፤ በጨጨሆ፤ በአንኮበር፤ በመናገሻ አምባ፤ በእንጦጦ፤ ወዘተ አሳርፈውት አልተሳካላቸውም፡፡ በመጨረሻም መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም. በራዕይ በተነገራቸው ቅዱስ ስፍራ በግሸን ደብረ ከርቤ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አኑረውታል፡፡

የተራራው ተፈጥሯዊ አቀማጥ ሲመለከቱት አንድ ጥሩ አናፂ ከጥሩ እንጨት ባማረ ጌጥ ጠርቦ የሰራው ግሩም የእጅ መስቀል ይመስላል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም መሠረቱ የተጣለውና ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽ የበቃው በ514 ዓ.ም. በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት አባ ፈቃደ ክርስቶስ በሚባሉ አባት ነው፡፡ አባ ፈቀደ ክርስቶስ የዐፄ ካሌብ የንስሐ አባት ሲሆኑ በየመን ሀገረ ናግራን ላይ የነበሩ የእግዚአብሔር አብና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁለት ጽላቶችን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው በመምጣት በግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ በማኖር ሲቀደስባቸውና ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደረስባቸው ቆይተዋል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም የአሁኑን ስም ከማግኘቷ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ስሞች ስትጠራ የቆየች ሲሆን ደብረ ነጎድጓድ፤ ደብረ እግዚአብሔር፤ ደብረ ነገሥት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና መጻሕፍት ለአፍሪካ የደረሰው የመስቀሉ ቀኝ ክንፍ ብቻ ነው ሲሉ፤ የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አበው ሊቃውንት ግን አጥብቀው እንደሚቃወሙት መጻሕፍት ያረጋግጣሉ፡፡ መስቀሉ ለአራቱ ክፍለ ዓለማት ሲከፋፈል መስቀሉ ላይ ተለጥፈው የነበሩት ምልክቶች በማንሳት ለሦስቱ ክፍለ ዓለማት እንደተሰጠና ለአፍሪካ ግን ሙሉ መስቀል እንደደረሰ ይመሰክራሉ፡፡ ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ በግሸን ደብረ ከርቤ በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው መስቀል የቀኝ እጁ በኩል ብቻ ሳይሆን ሙሉው የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያያናችንም ይህንን መሠረት በማድረግ መስከረም 21 ቀን በየዓመቱ በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በድምቀት ታከብራለች፡፡

  • ምንጭ፡- አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል 1990 ዓ.ም.

ግሸን ደብረ ከርቤ የቃል ኪዳን አምባ ቀሲስ በላይ ተገኝ 1996 ዓ.ም.

ቅዱሳት መካናት በኢትዮጵያ ዘመድኩን በቀለ 1992 ዓ.ም.