ርክበ ካህናት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹ርክብ› ወይም ‹ረክብ› የሚለው ቃል ‹ተራከበ፤ ተገናኘ› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲኾን፣ ትርጕሙም ማግኛ፣ መገኛ፣ መገናኛ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፰፻፴፩)፡፡ ‹ክህነት› የሚለው ስያሜም ከጵጵስና ጀምሮ እስከ ዲቁና ድረስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን መዓርጋት የሚያጠቃልል ቃል ሲኾን ካህን (ነጠላ ቍጥር)፣ ካህናት (ብዙ ቍጥር) በአንድ በኩል ቀሳውስትን የሚወክል ኾኖ በሌላ በኩል ደግሞ የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሳውስት፣ የዲያቆናት የጋራ መጠሪያ ነው፡፡ ‹ርክበ ካህናት› የሚለው ሐረግም የካህናት መገኛ፣ መገናኛ፣ ጉባኤ (መሰባሰቢያ)፣ መወያያ፣ ወዘተ የሚል ትርጕም አለው፡፡ በአጭሩ ‹ርክበ ካህናት› ማለት – የአባቶች ካህናት ማለትም የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት (የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት) ጉባኤ ማለት ነው፡፡

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደ ተገለጸው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ተገልጦ ከዐሥራ አንዱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ በልቷል፡፡ ከምሳ በኋላም ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ‹‹ትወደኛለህን?›› እያለ ከጠየቀው በኋላ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በቅደም ተከተል ‹‹በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ፤›› በማለት የአለቅነት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ቅዱስ ጴጥሮስን ማስጠንቀቁን፤ ለፍጻሜው ግን የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንንና መላው ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳ ምሥጢር አለው (ዮሐ.፳፩፥፩-፲፯)፡፡

ይህን የጌታችንን ትእዛዝና የሐዋርያትን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባኤ ያደርጋል፤ የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (የቅዱስ ማቴዎስ በዓል) ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ርክበ ካህናት ነው፡፡ በዓሉ (ርክበ ካህናት) ወሩና የሚውልበት ቀን የበዓላትንና የአጽዋማትን ቀመር ተከትሎ ከፍና ዝቅ ቢልም በየዓመቱ የትንሣኤ በዓል በተከበረ በ፳፭ኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ ይውላል፡፡ የአጽዋማትና የበዓላት ቀመር ከመዘጋጀቱ በፊት ማለትም በቅዱስ ድሜጥሮስ አማካኝነት ዐቢይ ጾም ሰኞ፣ ስቅለት ዓርብ፣ ትንሣኤ እሑድ፣ ርክበ ካህናት ረቡዕ፣ ዕርገት ሐሙስ፣ ጰራቅሊጦስ እሑድ እንዲኾን ከመደረጉ በፊት ርክበ ካህናት ግንቦት ፳፩ ቀን ይውል ነበር (መጽሐፈ ግጻዌ፣ ግንቦት ፳፩ ቀን)፡፡

ከዚህ በኋላ በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ኛው ቀን፣ በበዓለ ኃምሳ እኩሌታ በዕለተ ረቡዕ ርክበ ካህናት እንዲዘከር የቤተ ክርስቲያን አባቶች ወስነዋል፡፡ በያዝነው ዓመት በ፳፻፱ ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ከተከበረበት ዕለት (ሚያዝያ ፰ ቀን) ጀምሮ ብንቈጥር ፳፭ኛው ቀን ግንቦት ፪ ቀን ነው፡፡ በመኾኑም የዘንድሮው ርክበ ካህናት ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ይውላል ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል (ርክበ ካህናት) ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ የቆዩ አባቶቻችን በጋራ በመሰባሰብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደዚሁም ለምእመናን አንድነትና መንፈሳዊ ዕድገት የሚበጁ መንፈሳውያን መመሪያዎችን የሚያስተላልፉበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርገው ጉባኤ የሚተላለፉ መመሪያዎችና የሚጸድቁ ውሳኔዎች ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምእመናን አንድነት፣ ለአገር ሰላምና ደኅንነት የሚጠቅሙ ይኾኑ ዘንድ ዅላችንም በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንንና አባቶቻችንን ይጠብቅልን፤ እኛንም ለአባቶች የሚታዘዝ ልቡና፣ ሓላፊነታችንን የምንወጣበትን ጥበብና ማስተዋልን ያድለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት – ካለፈው የቀጠለ

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹በእርሱ ሞት ከብረናል፡፡ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢኾን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፡፡ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ወደ ሕይወት ሥጋ ደፍሮ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ (በክርስቶስ) እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፤›› (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፲፪)፡፡

‹‹ሕማምን፣ ሞትን ገንዘብ አደረ፡፡ በሥጋው የሞተው የእኛን ባሕርይ በመዋሐዱ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፡፡ ሞት ሰው የመኾን ሥራ ነውና፡፡ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመኾን ሥራ ነውና፡፡ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን (ሞትን እና ትንሣኤን) እናውቃለን፤›› (ዝኒ ከማሁ ፸፪፥፴፭)፡፡

‹‹በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደ ኾነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፡፡ ይህ (መሞት፣ መነሣት) ለመለኮት አይነገርም፡፡ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፤›› (ዝኒ ከማሁ ፸፱፥፱)፡፡

‹‹የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን (ኃጢአትን) ሻረ፡፡ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ (ፍዳ፣ መርገምን አጠፋ)፡፡ ሲኦልን በዘበዘ፤ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፡፡ የምሕረትን በር ከፈተ፡፡ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዅሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚኾን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፤›› (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፫፥፮)፡፡

‹‹ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ እንደ ተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደ ኾነ፣ መድኃኒታችን በሚኾን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደ ሰጠን እናምናለን፡፡ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ዅሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ዅሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከኾነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ትንሣኤም ሐሰት ከኾነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፡፡ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደ መኾኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደ መኾኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከሰው መካከል ባልተደመሰሰም ነበር፤›› (ቅዱስ ሳዊሮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፬፥፲፰-፳)፡፡

‹‹ፈጣሪያችን ክርስቶስ ለጌትነቱ እንደሚገባ ሥጋ መለወጥ የሌለበት እስኪኾን ድረስ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤ ሙስና መቃብርን አጥፍቷልና፤ በሥጋ በተቀበላቸው በሚያድኑ በእነዚህ ሕማማት ከጽኑ ሞት፣ ከዲያብሎስም ሥልጣን ያድነን ዘንድ፤ ወደ ቀደመ ቦታችንም ያገባን ዘንድ፤›› (ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ፣ ሃይ. አበ. ፺፥፴፬)፡፡

‹‹ይታመም ዘንድ በተገባው በሥጋው፣ ነውር የሌለበትን ሕማም በፈቃዱ በእውነት ተቀበለ እንጂ በምትሐት እንዳልታመመ እናገራለሁ፡፡ እንደ ሕማሙ ሞትንም በመስቀል ላይ ተቀበለ፡፡ ለአምላክነቱ በሚገባ፣ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤውም የጌትነቱን ሥልጣን ገለጠ፡፡ ሥጋውንም የማይሞት አደረገ፡፡ ከኃጢአት በራቀ በንጹሕ ማኅፀን በተዋሐደው ጊዜ ለመለኮት ገንዘብ ስለኾነ በሥራው ዅሉ አይለወጥም፤›› (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፪፥፲፭)፡፡

‹‹ሕማም የማይስማማው እርሱ በሥጋ ሞትን ታገሠ፤ ብረት ወደ እሳት በገባ ጊዜ ዅለንተናው እሳት እንደኾነ እስኪታሰብ ድረስ በእሳት ዋዕይ እንዲግል፤ በመዶሻ በተመታ ጊዜ በመስፍሕ (መቀጥቀጫ) ላይ እንዲሳብ (እንዲቀጠቀጥ)፤ እሳትም ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሳለ ፈጽሞ እርሱ እንዳይመታ፤ ከብረቱም እንዳይለይ፤ ግን የመዶሻ ኃይል ሳያገኘው እንዲመታ፤ ለመዶሻ እንዲሰጥ፤ የሚያድን የጌታ ሕማም እንዲህ እንደ ኾነ ዕወቅ፡፡ በዚህ ትንሽ ምሳሌ፤ በእሳትና በብረት ተዋሕዶ ምልክትነት ፍጹም ተዋሕዶን እንወቅ፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህ መከራና ሕማምን የሚቀበል ሥጋን ተዋሕዶ በሞተ ጊዜም ከሦስት ቀን በኋላ አምላክነቱ በተገለጠበት ትንሣኤው ሞትን አጠፋው፡፡ ሥጋው በመቃብር በመቀበሩም በመቃብር ውስጥ የነበረ መፍረስ፣ መበስበስን አጠፋልን፤ ከሥሩም ነቀለው፡፡ ለዚህም ማስረጃ ከቅዱሳን ወገን ብዙ ሰዎች ተነሡ፤›› (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፮፥፶-፶፪)፡፡

‹‹ዳግመኛ እርሱ እንደ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን እንደ ተነሣ፤ ስለ ተነሣም ሥጋው የማይፈርስ የማይበሰብስ፣ የማይታመም፣ የማይሞት እንደ ኾነ እናምናለን፡፡ ሥጋውም ከእርሱ ጋር አንድ ኾኖ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአርያም በልዑል ዙፋኑ ተቀመጠ፡፡ ዳግመኛም በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ዅሉ አንድ ኾኖ በሚነሣበት ጊዜ እርሱ በጌትነት ይመጣል፡፡ ለዅሉም እንደ ሥራው ይከፍለዋል፡፡ እኛ በእነዚህ ቃላት ሳናወላውል ጸንተን እንኖራለን፤›› (ቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፱፥፴፪)፡፡

‹‹በፈቃዱ በሥጋው የእኛን ሕማም ታመመ፤ በእውነት የእኛን ሞት ሞተ፡፡ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፡፡ በፈቃዱ በተለየ አካሉ ሞትን ገንዘብ አደረገ፡፡ በሦስተኛውም ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱ ዕሪና ተቀመጠ፡፡ በኋለኛይቱ ቀንም በሙታንና በሕያዋን ሊፈርድ ይመጣል፤›› (ቅዱስ ፊላታዎስ፣ ሃይ. አበ. ፻፭፥፲፬)፡፡

‹‹በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፤ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱም ሲኦልን በዘበዘ፣ ለዅሉም ትንሣኤን ገለጠ፡፡ ፈጽሞ አልተለወጠም፤ ለዅሉ አምላክነቱን አስረዳ፤ ሙስና መቃብርን ከእኛ አጠፋ፤ በቀደመ ሰው በአባታችን በአዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ሠልጥኖብን ለነበረ ኃጢአት ከመገዛት አዳነን፤›› (ቅዱስ ዲዮናስዮስ ፻፲፩፥፲፫)፡፡

‹‹እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱን ከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፡፡ እርሱ ራሱ ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ፣ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ› እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም ‹ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ› አላት፡፡ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን፤›› (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ ፺፭)፡፡

‹‹ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው፣ ከመስቀል አውርደው፣ በድርብ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው፤›› (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ፩፥፳፱-፴፩)፡፡

‹‹ሰውን ስለ መውደድህ ይህን ዅሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ፡፡ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ፤›› (ቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ፣ ፩፥፳፬)፡፡

‹‹በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፡፡ የተወጋውን ጎኑን፣ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የኾነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ፤›› (ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት ፬፥፳፭-፳፯)፡፡

‹‹ሰማያት (ሰማያውያን መላእክት) የደስታ በዓልን ያደርጋሉ፤ ደመናት (ቅዱሳን) የደስታን በዓል ያደርጋሉ፡፡ ምድር (ምድራውያን ሰዎች) በክርስቶስ ደም ታጥባ (ታጥበው) የፋሲካን በዓል ታደርጋለች (ያደርጋሉ)፤ ያከብራሉ (ታከብራለች)፡፡ ዛሬ በሰማያት (በሰማያውያን መላእክት) ዘንድ ታላቅ ደስታ ኾነ፡፡ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን የነጻነት በዓል ታደርጋለች፡፡ የትንሣኤያችን በኩር ክርስቶስ ከሙታን ሰዎች ዅሉ ተለይቶ ቀድሞ ተነሣ፤›› (ቅዱስ ያሬድ፣ ድጓ ዘፋሲካ)፡፡

‹‹ሞትን በሥጋ በቀመሰ ጊዜ መለኮቱ በመቃብር ውስጥ ያለነፍሱ ከበድኑ ጋር ነበር፡፡ በሲኦልም ውስጥ ያለ ሥጋው ከነፍሱ ጋር ህልው ነበር፡፡ በአባቱም ቀኝ ያለ ነፍስና ያለ ሥጋ ህልው ነበር፡፡ በትንሣኤውም ጊዜ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስቀድሞ ለአይሁድ ‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ› ብሎ እንደ ተናገረ፡፡ አይሁድም ‹ይህ ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ያለቀው በዐርባ ሰባት ዓመት ነው፤ አንተ ግን በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ትላለህ› አሉት፤ ይህንንም የተናገረው ስለ ራሱ ሰውነት ነው፡፡ በተነሣም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ ተናገረ አሰቡ፡፡ በመጽሐፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የተናገራቸውን ቃል አመኑ፤ ሁለተኛም ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ልለያት መልሼም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህንንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ› ብሏል፡፡ ዳዊትም ‹አቤቱ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ይላል፡፡ ነቢዩ ‹አቤቱ አንተ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ለምን አለ? የመቅደሱ ታቦት ከኾነችው ከዳዊት ዘር ከነሣው ሥጋ ጋር በመለኮታዊ ኃይሉ ከሞት እንቅልፍ ከመንቃት በስተቀር የእግዚአብሔር መነሣት ምንድን ነው?›› (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽ. ምሥጢር ዘትንሣኤ ፸፯-፸፱)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት – የመጀመርያ ክፍል

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የድኅነታችን ብሥራት በመኾኑ ለአምሳ ቀናት ያህል በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ ወዘተ. ይዘከራል፡፡ በዚህ ሰሙን ‹‹ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን …›› እየተባለ ሞት መደምሰሱ፣ ነጻነት መመለሱ ያታወጃል፡፡ በየጊዜያቱና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጠውን ትምህርትና ምስክርነት ሰጥተዋል፤

‹‹ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ‹አባት ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ› ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ፤›› (እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት ፭፥፩)፡፡

‹‹እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፤ ሙታንንም አስነሣ፡፡ እንደ ተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ዘበቱበት፣ እንደ ሰደቡት፣ እንዲሁ በሰማይ ያሉ ዅሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፤ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፤›› (ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሃይ. አበ. ፯፥፳፰-፴፩)፡፡

‹‹እንዲህ ሰው ኾኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤›› (ሠለስቱ ምዕት፣ ሃይ. አበ. ፲፱፥፳፬)፡፡

‹‹ሞትን ያጠፋው፣ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፡፡ ሰው የኾነ፣ በሰው ባሕርይ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፤ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ፡፡ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል፤›› (ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ሃይ. አበ. ፳፭፥፵)፡፡

‹‹ሥጋው በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡ በዚያም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ፤ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ፡፡ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ (ሊቃነ አጋንንት፣ ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሡ)፡፡ የብረት ቁልፎቿም ተቀጠቀጡ (ፍዳ፣ መርገም ጠፋ)፡፡ ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃን ነፍሳትን ፈታች፤›› (ዝኒ ከማሁ ፳፮፥፳-፳፩)፡፡

‹‹ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፤ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፣ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተናገረው ቃል ዐፅም፣ ሥጋ ወደ መኾን ፈጽሞ እንደ ተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጉድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፡፡ ይህስ እውነት ከኾነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፡፡ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበስር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፡፡ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትኾን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋ ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደ ተናገረ፡፡ አባቶቻችን ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣውሥጋ ነው እንጂ ብለው አስተማሩን፤ ይህንን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም (ምልክት) በእርሱ አየ፤›› (ዝኒ ከማሁ ፴፥፴፩-፴፮)፡፡

‹‹አሁን እግዚአብሔር ሞተ ሲል ብትሰማ አትፍራ፤ ‹የማይሞተውን ሞተ ሊሉ አይገባም› ከሚሉ፤ ዕውቀት ከሌላቸው፤ ሕማሙን፣ ሞቱን ከሚክዱ መናፍቃን የተነሣ አትደንግጥ፡፡ እኛ ግን በመለኮቱ ሞት እንደ ሌለበት፤ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ሥልጣን እንደ ተነሣ እናውቃለን፡፡ ሞት የሌለበት ባይኾንስ ኖሮ በሥጋ በሞተ ጊዜ ሥጋውን ባላስነሣም ነበር፤ ሥጋው እስከ ዓለም ፍጻሜ በመቃብር በኖረ ነበር እንጂ፤›› (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፴፬፥፲፯-፲፰)፡፡

‹‹ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፤ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፡፡ የንስሐንም በር ከፈተልን፤›› (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ሃይ. አበ. ፴፮፥፴)፡፡

‹‹በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፡፡ ፍሬውንም (ሥጋውን፣ ደሙን) ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወዳልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደ ነበረው መዓርግ ደረስን፡፡ ክፉውንና በጎውን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን፤›› (ዝኒ ከማሁ ፴፮፥፴፰-፴፱)፡፡

‹‹የሕይወታችን መገኛ የሚኾን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደ ለወጠ እናምናለን፤ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ እንደ ተጻፈ፡፡ ከሰው ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፤ ዳዊት ‹በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው?› ብሎ እንደ ተናገረ፤›› (ቅዱስ አቡሊዲስ፣ ሃይ. አበ. ፵፪፥፮-፯)፡፡

‹‹በመለኮትህ ሕማም፣ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፡፡ በሥጋ መከራ የተቀበልህ አንተ ነህ፡፡ ከአብ ጋር አንድ እንደ መኾንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፡፡ ከእኛም ጋር አንድ እንደ መኾንህ በፈቃድህ የሞትህ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፡፡ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፡፡ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፡፡ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፤ ከሙታን ጋር የተቆጠርህ አንተ ነህ፤ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ ሦስት መዓልት፤ ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በዘመኑ ዅሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፤ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ እግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፤›› (ቅዱስ ኤራቅሊስ፣ ሃይ. አበ. ፵፰፥፲፪-፲፫)፡፡

‹‹እኛስ ኃጢአታችንን ለማስተሥረይ በሥጋ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ፤ ከሙታንም ተለይቶ በእውነት እንደ ተነሣ፤ ከተነሣም በኋላ በእውነት ወደ ሰማይም እንደ ዐረገ እናምናለን፡፡ በኋላም በሚመጣው ዓለም እርሱ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል፡፡ የሰውን ወገኖች ዅሉ በሞቱበት፤ በተቀበሩበት ሥጋ ከሞት ያስነሣቸዋል፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ ያለ መለወጥ ዅልጊዜ ይኖራል፡፡ እርሱ በዚህ በሞተበት፤ በተገነዘበት ሥጋ ከሙታን አስቀድሞ እንደ ተነሣ፤›› (ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም፣ ሃይ. አበ. ፶፪፥፲፩-፲፪)፡፡

‹‹የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩ ኃይልን እንጂ፡፡ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በኾነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፡፡ ከሞትም በኋላ ፈርሶ፣ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፤›› (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሃይ. አበ. ፶፫፥፳፯)፡፡

‹‹መለኮት በሥጋ አካል በመቃብር ሳለ የሥጋ ሕይወት በምትኾን በነፍስ አካል ወደ ሲኦል ወረደ፤ እንደዚህ ባለ ተዋሕዶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ከትንሣኤ በኋላ አይያዝም፤ አይዳሰስም፡፡ በዝግ ቤት ገብቷልና፡፡ ነገር ግን ምትሐት እንዳይሉት ቶማስ ዳሠሠው፡፡ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ቶማስ አመነበት፤›› (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይ. አበ. ፶፮፥፴፯-፴፰)፡፡

‹‹ክርስቶስ የሙታን በኵር እንደምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የደሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዓዛርን በሞተ በአራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፡፡ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታንን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፣ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ኾነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኵር ነው፡፡ ‹እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛም ሞት አያገኘውም› ተብሎ እንደ ተጻፈ፤›› (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይ. አበ. ፶፯፥፫-፮)፡፡

‹‹ቃል ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ በሲኦልም ካለች ከነፍሱ አልተለየም፡፡ ከነፍስ ከሥጋ በአንድነት ነበረ እንጂ፡፡ ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው፤›› (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ሃይ. አበ. ፷፥፳፱)፡፡

‹‹ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ‹በትንሣኤ ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ› ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጐመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፤ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድን ነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞትነው፤ አይለወጥም፤ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የኾነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት (እትራት) አላጠፋምና፡፡ በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፡፡ አምላክ የኾነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፡፡ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደ ኾነ ሥራውን አስረዳ፡፡ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት (እትራት) አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደ ነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በአራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ ‹ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው› ብለው አስረዱ፤›› (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሃይ. አበ. ፷፮፥፯-፲፪)፡፡

ይቆየን

በዓለ ትንሣኤን በትንሣኤ ልቡና እናክብር

በገብረ እግዚአብሔር ኪደ

ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

 ፋሲካ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ እኛን ከወደቅንበት አንሥቶና ተሸክሞ ከዚኽ ምድር ወደ ሰማያት ተሻግሯልና (ተነሥቶ ዐርጓልና)፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ሹበላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና ሕይወታችኁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯልና፡፡ ሕይወታችኁ የኾነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችኁ፤›› እንዳለን /ቈላ.፫÷፩-፬/፣ በጥምቀት ውኃ ሞቱን በሚመስል ሞት ስንሞት፣ አሮጌው ሰውነታችን እንደ ግብጻውያን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ አዲሱ ሰውነታችን ግን እስራኤላውያን ባሕሩ ተከፍሎላቸው እንደ ተሻገሩ ተሻግሯል (ተነሥቷል)፡፡

ብልየት ያለበት የቀዳማዊ አዳም ሰውነታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተቀብሮ አዲሱ ሰውነታችን ሕይወትን አግኝቶ ተነሥቷል፡፡ መሬታዊው ሰውነታችን ሞቶ ሰማያዊው ሰውነታችንን ለብሰን መንፈሳውያን ኾነን ተነሥተናል፡፡ ወደ ጥንተ ተፈጥሯችን ተመልሰናል፡፡ አኹን ከእኛ የሚጠበቀው ይኽ ተፈጥሯችንን ሳናቆሽሽ መጠበቅ ነው፤ እንደ ተነሣን መዝለቅ፡፡ ይኽን ለማድረግም ተራራ መውጣት፣ ምድርን መቆፈር፣ የእሳት ባሕርን መሻገር አይጠበቅብንም፡፡ ይኽን ጠብቀን እንድንቈይ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ፈቃዳችንን፡፡ የሚሠራው እርሱ ራሱ ነውና /ዮሐ.፲፭÷፭/፡፡ መጽንዒ (የሚያጸና) መንፈስ ቅዱስን ያደለንም ስለዚኹ ነው፡፡

የምናመልከውን አምላክ መስለን በሕይወት ሳንሻገር የመሻገርን በዓል (ፋሲካን) የምናከብረው ምን ጥቅም እንዲሰጠን ነው? ከጨለማ ሥራ ወደ ብርሃን ሥራ፣ ከፍቅረ ዓለም ወደ ፍቅረ ክርስቶስ ሳንሻገር ፋሲካን የማክበራችን ትርጕሙ ምንድነው? እኛው ሳንነሣ የመነሣት በዓልን ማክበራችን በፍርድ ላይ ፍርድ በበደል ላይ በደል ከመጨመር ውጪ የሚሰጠን ጥቅም ምንድን ነው? የምንነሣውስ መቼ ነው? በዐይናችን ጉድፍ ብትገባ ስንት ደቂቃ እንታገሣታለን? ታድያ በነፍሳችን ላይ የተጫነውን የኃጢአት ግንድ መቼ ነው የምናስወግደው? መቼ ነው ወደ ላይኛው ቤታችን ቀና የምንለው? ብዙዎቻችን በሕይወታችን ሳንሻገር ነው በዓለ ፋሲካን የምናከብረው፡፡ ክርስቲያን ኾኖ በመብልና በመጠጥ ብቻ ፋሲካን ማክበር ኢ ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡

አዲሱን ሰውነታችን ለብሰን ከተነሣን በኋላ እንደ ቀድሞ ምልልስ የምንጓዝ ከኾነ ግን ተመልሰን ወድቀናል፤ አዲሱ ሰውነታችንን አውልቀን አሮጌውን ሰውነታችንን በድጋሜ ለብሰነዋል፡፡ በእኛነታችን ውስጥ ፍቅረ ንዋይ፣ ፍቅረ ሲመት፣ ፍትወት፣ ይኽንንም የመሰሉ ዅሉ ካለ አዲሱ ሰውነታችን ከእኛ ጋር የለም፤ ቢኖርም ታሟል፡፡ በኃጢአት የመቃጠል ስሜት፣ ርኵሰትና ክፉ ምኞት ከእኛ ዘንድ ካለ አሮጌ ሰው ኾነናል፤ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ አላደረግንም፡፡ ስለዚኽ ከልቡና ሞት እንነሣና ፋሲካን እናክብር፡፡ እስከ አኹን በኃጢአት ውስጥ ካለን ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንምጣ (እንሻገርና) የመሻገርን በዓል እናክብር፡፡ ከክፉ ሥራ ወደ ጽድቅ ሥራ እንሻገርና የእውነት ፋሲካን እናክብር፡፡ ከኃይል ወደ ኃይል እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ከሞት ሥራ ወደ ሕይወት ሥራ እንነሣና የመነሣትን በዓል እናክብር፡፡

እግዚአብሔር የሚወዳችሁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ሆይ! እኛን የሚያሰነካክል ደግሞም የሚጥለን ፈርዖን (ዲያብሎስ) ተሰነካክሎ ወድቋልና ከግብጽ ሕይወታችን እንውጣ፡፡ ተነሥተንም እንሻገር፡፡ ተሻግረንም ሰማያዊውን ፋሲካ እናክብር፡፡ በግብጽ የነበሩት እስራኤላውያን የበጉን ደም በጉበኑና በኹለቱም መቃን ሲቀቡት አጥፊው ከቤታቸው እንዳለፈ አንብበናል /ዘፀ.፲፪÷፲፫/፡፡ ይኸውም በጉ በራሱ ያንን የማድረግ ኃይል ስለ ነበረው አይደለም፤ ደሙ የክርስቶስ ደም አምሳል ስለ ነበር ነው እንጂ፡፡ እኛ ግን የአማናዊውን በግ /ዮሐ.፩፡፳፱/ ደም በልቡናችን፣ በአስተሳሰባችንና በሰውነታችን ዅሉ እንቀባና (እንቀበልና) እንሻገር፡፡

ይኽን ስናደረግ በእባቡና በጊንጡ ይኸውም በዲያብሎስና በሠራዊቱ ላይ ሥልጣን ይኖረናል /ሉቃ.፲÷፲፱/፡፡ የምንበላው በግ ራሱ ሕይወት ስለ ኾነ ሞት በእኛ ላይ አይነግሥም /ዮሐ.፲፬÷፮/፡፡ በዚኽ ዓለም ሳለን ከዚኽ ደስታ ተካፋዮች ከኾንን (የመዠመሪያውን ትንሣኤ ልቡና በንስሐ ከተነሣን) በሚመጣው ዓለምም በክብር ላይ ክብር፣ በሹመት ላይ ሹመት እንቀበላለን (ኹለተኛውን ትንሣኤ እንነሣለን) /ሉቃ.፳፪÷፲፭-፲፮/፡፡ ብንወድቅ እንኳን መልሰን በመነሣት ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር፣ የክብር ክብር፣ ጌትነት የባሕርዩ በሚኾን፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰጭነት በመንግሥተ ሰማያት ጸጋ ክብር እናገኛለንና የጭንቅ ቀን ሳይመጣ በዓለ ትንሣኤን እናክብር፡፡ ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የመከረንን የሚከተለውን ኃይለ ቃል በተግባር ላይ ብናውለው እንጠቀማለን፤

‹‹በምነግራችኁ ነገር እያበሳጨኋችሁና እያሳመምችሁ እንደ ኾነ ይገባኛል? ግን ምን ላድርግ? እኔም እናንተም በምግባር በሃይማኖት የታነጽን እንኾን ዘንድ ብቻ ሳይኾን ከዚያም እናመልጥ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ከመጨማለቃችን የተነሣ እንዴት አድርጌ ላሳምማችኁ እችላለኁ? ብትሰሙኝና ብትለወጡስ እኔም ማረፍ እንኳን በቻልኩ ነበር፡፡ ስለዚኽ እስካልተለወጣችሁ ድረስ እናንተን መገሠንና መምከሬን አላቆምም፡፡ ስለ ገነመ እሳት ተደጋግሞ ሲነገር የሚበሳጭ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ግን ከዚኽ የበለጠ ያማረ የተወደደ አስደሳች ትምህርት የለም እለዋለኁ፡፡ እንዴት ይኽ አስደሳች ትምህርት ነው ትለናለህ? ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔም ወደዚያ መጣል ከደስታ ዅሉ የራቀ ነውናብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡ ስለዚኽ ነፍሳችን ከመታሠሯ በፊት የነቃን የተጋን እንኾን ዘንድ ይኽን ደጋግሜ እነግራችኋለሁ፡፡ ስሐ ይግባ እንጂ ማንም እንደ ተወቀሰ አያስብ፤ በንግግሬም የሚቆጣ አይኑር፡፡ ዅላችንም ወደ ጠባቢቱ መንገድ እንግባ፡፡ እስከ መቼስ በስንፍና አልጋ እንተኛለን? ዛሬ ነገ ማለት አይበቃንም ወይ? ሰማያዊ ቪላችንን ቀና ብለን ብንመለከት እኮ በዚኽ ምድር ይኽንን ለመሥራት ባልደከምን ነበር፡፡ እስቲ ንገሩኝ! ሩጫችንን ስንጨርስ ከሬሳ ሳጥንና ከመግነዝ ጨርቅ ውጪ ይዘነው የምንሔድ ነገር ምን አለ? ታድያ ለምን እንከራከራለን?›› (ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች፣ ገጽ ፻፶፮ – ፻፶፯)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ሰሙነ ፋሲካ (ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ)

በሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ

ሚያዝያ ቀን ፳፻፱ .

ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታት ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ የሚጠሩ ሲኾን፣ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

ሰኞ

የትንሣኤው ማግሥት ሰኞ ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሰትኾን፣ ‹ፀአተ ሲኦል› ወይም ‹ማዕዶት› ትባላለች (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡

በዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ሰኞ ደግሞ ገበሬው፡- ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ዅሉ፤ ሴቶቹ፡- ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለ ኾነች ‹እጅ ማሟሻ ሰኞ› ትባላለች፡፡

ማክሰኞ 

የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት ‹‹እኔ ሳላይ አላምንም›› ብሎ ነበር፡፡ በሳምንቱ ቶማስ በተገኘበት ጌታችን በድጋሜ ለሐዋርያት ተገለጸ፡፡ ስለዚህም ይህቺ ዕለት በሐዋርያው ቶማስ ስም ተሰይማለች (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡ 

ረቡዕ 

ጌታችን ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሣው ለአልዓዛር መታሰቢያ ትኾን ዘንድ፤ በክርስቶስ ሥልጣን የአልዓዛርን ከሞት መነሣት አይተው ብዙ ሕዝብ በጌታችን ስለ አመኑ ዕለቲቱ (ረቡዕ) ‹አልዓዛር› ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡ 

ኀሙስ 

ይህቺ ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ኾና ‹የአዳም ኀሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብላ ትከበራለች (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡

ዐርብ

ከሆሣዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ ደግሞ የጌታችን ዐርባው ጾም የሚፈጸምባት የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት ዕለት በመኾኗ በቤተ ክርስቲያን ‹ተጽዒኖ› ትባላለች፡፡ የከባድ ሥራ ማቆሚያ (ማብቂያ) ዕለት በመኾኗም በሕዝቡ ዘንድ ‹የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ› ትባላለች፡፡

ዳግኛም በመጀመርያ የሰው ልጆች አባትና እናት የኾኑት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት፤ በኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም ስለ ተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለ ፈጸመባት ‹ዕለተ ስቅለት፣ አማናዊቷ ዐርብ› ትባላለች፡፡

የሰሙነ ፋሲካዋ ማለትም የትንሣኤ እሑድ ስድስተኛዋ ዐርብ ደግሞ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቤተ ክርስቲያን› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት

በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበያይባት ‹የቁራ ገበያ፣ የገበያ ጥፊያ› ስትባል፣ በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት፤ በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት፤ በትንሣኤውም ጌታችን ከዅሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መታሰቢያ ኾና ‹ቅዱሳት አንስት› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፯-፴፫፤ ፳፬፥፩-፲)፡፡

የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ

በዚህች ሰንበት ከላይ እንደ ተጠቆመው ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ «ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!» ብሎ ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡

በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ‹አየን› ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግንሰምቼአለሁ› ብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይኾንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ የሰውን ዅሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ «ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!» በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡

ቶማስንም «ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትኹን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤» ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ምልክቱን በማየቱ፣ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ «ጌታዬ፣ አምላኬ ብሎ መስክሮ» አመነ፡፡ ስለዚህም ማለትም የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመኾኑ የትንሣኤው ሳምንት እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

በአጠቃላይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ፋሲካ የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዅሉ ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የትንሣኤ በዓል ትርጕሙና አከባበሩ

በሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ

ሚያዝያ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን!

«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቃል መገኛው ‹ተንሥአ = ተነሣ› የሚለው ግስ ሲኾን፣ ትርጕሙም መነሣት፣ አነሣሥ፣ አዲስ ሕይወትን ማግኘት ማለት ነው፡፡ ‹ትንሣኤ› በየመልኩ፣ በየዓይነቱ ሲተረጐም አምስት ክፍል አለው፤

የመጀመርያው ትንሣኤ ሕሊና ነው፤ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ) ነው፡፡

ሁለተኛውም ትንሣኤ ልቡና ነው፤ የዚህም ምሥጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡

ሦስተኛው ትንሣኤ ለጊዜው (በተአምራት) የሙታን በሥጋ መነሣት ነው፡፡ ነገር ግን በድጋሜ ሌላ ሞት ይከተለዋል፡፡

አራተኛው ትንሣኤ ክርስቶስ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ያመላክታል፡፡ የርእሰ ትምህርታችን መነሻም ይህ ነው፡፡

አምስተኛውና የመጨረሻው የትንሣኤ ደረጃ የባሕርይ አምላክ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ መሠረት ያደረገ ትንሣኤ ዘጉባኤ ሲኾን፣ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ዅሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ነው፡፡

ወደ ርእሳችን ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በምሥጢሩም፣ በይዘቱም ከኦሪቱ በዓለ ፋሲካ ጋር ስለሚመሳሰል ‹ፋሲካ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ፌሳሕ›፤ በጽርዕ (በግሪክ) ‹ስኻ› ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና አማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ (ደስታ)፣ ዕድወት፣ ማዕዶት (መሻገር፣ መሸጋገር)፣ በዓለ ናእት (የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት) ማለት ነው፡፡ የዚህም ታሪካዊ መነሻው በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ ሲኾን፣ ይህም እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት፤ ከከባድ ኀዘን ወደ ፍጹም ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነው፡፡ በዚህ ኦሪታዊ (ምሳሌ) በዓል አሁን አማናዊው በዓል በዓለ ትንሣኤ ተተክቶበታል፡፡

ፋሲካ (በዓለ ትንሣኤ) በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የኾንን ምእመናን የክርስቶስን ትንሣኤ የምናከብርበት ዕለት ነው፡፡ ይህ በዓል ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፤ ከውርደት ወደ ክብር፤ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነጻነት፤ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ ሕይወት የተሻገርንት ከበዓላት ዅሉ የበለጠ የነጻነት በዓል ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቲያኖች በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት በዓሉን እናከብረዋለን፡፡

መድኃኒታችን ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ፣ በሥልጣኑ የተነሣው መጋቢት ፳፱ ቀን በ፴፬ ዓ.ም እንደ ኾነ ታሪከ ቤተ ከርስቲያን ያስረዳል፡፡ የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው በተነሡ ሊቃውንትና ምእመናን ነው፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዓቱ ይበዛ፣ ይቀነስ እንደ ኾነ እንጂ በዓሉ መከበሩ ተቋርጦ አያውቅም፡፡

በቅብብሎሽ ከዚህ በደረሰው ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ሕማማት ግብረ ሕማማቱን ስታነብ ሰንብታ ለትንሣኤ እሑድ አጥቢያ ማታ በ፪ ሰዓት «ለጸሎት ተሰብሰቡ» ስትል የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡ ካህናቱም በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ሥርዓቱን በጸሎት ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም በቤተ ክርስቲያን ይሰባሰባል፡፡ ካህናቱ መዝሙረ ዳዊት፣ ነቢያት፣ ሰሎሞንና ውዳሴ ማርያም ከተደረሰ በኋላ «ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ» የሚለውን ግጥማዊ የደስታ መዝሙር ይዘምራሉ፡፡

ምንባቡ፣ ጸሎቱና ሌላውም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ ዲያቆኑ ነጭ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ፣ አክሊል ደፍቶ፣ መስቀል ይዞ፣ በጌታችን መቃብር በራስጌና በግርጌ በታዩት መላእክት ምሳሌ እንደ እርሱው ነጭ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ፣ ድባብ ጃንጥላ በያዙ፣ መብራት በሚያበሩ ሁለት ዲያቆናት ታጅቦ በቅድስት ቆሞ፡- «ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፣ ወከመ ኀያል ወኅዳገ ወይን፣ ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ፤ እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደ ተወው ኃያል ሰውም ጠላቱን በኋላው ገደለ፤» የሚለውን የዳዊት መዝሙር በረጅም ያሬዳዊ ዜማ ይሰብካል (መዝ. ፸፯፥፷፭)፡፡

ካህናቱም ከበሮ እየመቱና በእርጋታ እያጨበጨቡ ተቀብለው ይዘምራሉ፡፡ ሕዝቡም በጭብጨባና በዕልልታ የደስታ ዝማሬው ተሳታፊ ይኾናል፡፡ ይህ ምስባክ በዲያቆኑና በመላው ካህናት ሁለት ሁለት ጊዜ፤ በዲያቆኑና በመላው ካህናት አንድ ጊዜ (በጋራ) ይዘመራል፡፡ ይህም በድምሩ አምስት መኾኑ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ዓለም ለመዳኑ ምሳሌያዊ ማስረጃ ነው፡፡ በመቀጠል ካህኑ ትንሣኤውን የሚያበሥር ትምህርት ከማቴዎስ፣ ከማርቆስና ከሉቃስ ወንጌል አውጥቶ ያነባል፡፡ የዮሐንስ ወንጌል በቅዳሴ ጊዜ ይነበባል (ዮሐ. ፳፥፩-፱)፡፡

በማስከተል ከሊቃውንቱ መካከል ሥራው የሚመለከተው ወይም የተመደበው ባለሙያ (መዘምር) መስቀል ይዞ «ትንሣኤከ ለእለ አመነ» የሚለውን እስመ ለዓለም ከቃኘ በኋላ ለበዓሉ ተስማሚ የኾነው አርያም ተመርቶ በመቋሚያ ይዘመማል፡፡ ከዚያም «ዮም ፍሥሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን፣ እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና በሰንበተ ክርስቲያን ዛሬ ደስታ ኾነ …፤» የሚለው አንገርጋሪ በመሪና በተመሪ ይመለጠናል፤ በግራ በቀኝ እየተነሣ ይዘመማል፤ ይጸፋል፡፡

በዚህ ጊዜ «በጨለማ የነበራችሁ ሕዝቦች የትንሣኤውን ብርሃን እዩ፤ ብርሃኑንም ወስዳችሁ የብርሃኑ ተካፋይ ኹኑ፤» እያለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጀችውን ጧፍ እያበራች ታድላቸዋለች፡፡ ወዲያውኑም ‹‹ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ = ለአመነው ለእኛ ብርሃንህን ላክልን፤›› የሚለውን እስመ ለዓለም እየዘመሩ፣ መብራት እያበሩ ካህናቱና ሕዝቡ ዑደት ያደርጋሉ (ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራሉ)፡፡

መዘምራኑና ካህናቱ ከዑደት ሲመለሱ «ይእቲ ማርያም» የተባለው የኪዳን ሰላም ይጸፋና ኪዳን ተደርሶ ሲያበቃ እንደ ቦታው ደረጃ ፓትርያርክ ወይም ሊቀ ጳጳስ ወይም ቆሞስ ወይም ቄስ ዘለግ ባለ ድምፅ በንባብ «ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ» ሲሉ ካህናቱና መዘምራኑ ‹‹በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን = በታላቅ ኃይልና ሥልጣን» ብለው ይቀበላሉ፡፡ አሁንም ካህኑ «አሰሮ ለሰይጣን = ሰይጣንን አሰረው» ባለ ጊዜ መላው ካህናት «አግዐዞ ለአዳም = አዳምን አርነት ነጻ አወጣው» ይላሉ፡፡

በመቀጠል «ሰላም = ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅር» ሲሉ ዅሉም «እምይእዜሰ = ከዛሬ ጀምሮ» ብለው ይቀበላሉ፡፡ ካህኑም «ኮነ ፍሥሐ ወሰላም = ሰላምና ደስታ» ብለው ሦስት ጊዜ አውጀው «ነዋ መስቀለ ሰላም» እያሉ መስቀል ሲያሳልሙ ካህናቱና ሕዝቡም «ዘተሰቅለ ቦቱ መድኃኔ ዓለም» እያሉ ይሳለማሉ፡፡ ካህኑም «እግዚአብሔር ይፍታ» ይላሉ፡፡ ግብረ ሕማማት ሲነበብበት ከሰነበተው ጠበልም ይረጫል፡፡ የተረፈውንም ጠበል ሕዝቡ ለበረከት ወደየቤቱ ይወስደዋል፡፡

ከዚያም ልኡካኑ ለቅዳሴ እየተዘጋጁ መዘምራኑ ምስባክ መወድሱን ካዜሙ በኋላ በመቋሚያ ይዘሙታል፡፡ አያይዞም ይትፌሣሕ› የተባለውን መዝሙር ቃኝተው ከዘመሙ በኋላ «… ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ = … ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካውን ታደርጋለች፤» እያሉ ይጸነጽላሉ፡፡ አያይዘውም የመዝሙሩን ሰላም ይጸፋሉ፡፡ መንፈቀ ሌሊት ሲኾንም ቅዳሴ ተቀድሶ ሥርዓተ ቍርባን ይፈጸማል፡፡ ከዚያም ሠርሖተ ሕዝብ = የሕዝብ ስንብት ከኾነ በኋላ ካህናቱም ሕዝቡ ወደየቤታቸው ሔደው እንደየባህላቸው ይፈስካሉ (ይገድፋሉ)፡፡

የመግደፊያ ዝግጅት ለሌላቸው ነዳያንም በየመንደሩ እየተዞረ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ» እየተባለ ከሥጋውም፣ ከአይቡም፣ ከቅቤውም ከመጣጣሙም፣ ከእርጐውም ይታደላል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ» እየተባባለ በዚህ መልኩ አብሮ እየበላ፣ እየጠጣ፣ እየተደሰተ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ይሰነብታል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቀዳሚት ሥዑር

በመምህር ቸሬ አበበ

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር አምላካችን የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን፣ በክንፍ የሚበሩትን እና በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን፣ በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ነች፡፡ የመጀመሪያዋ ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ፍጥረታትን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ስላረፈባት ‹ሰንበት ዐባይ› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ይህቺን ዕለት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ እግዚአብሔር ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንዳደረገባት ዅሉ፣ የፍጥረት ርእስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አምላካችን ክርስቶስ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አርፎ የዋለባት ዕለት በመኾኗ ‹ቀዳሚት ሥዑር› ወይም ‹ቀዳም ሥዑር› ትሰኛለች፡፡ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡ የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

እመቤታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት ዅሉ የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከሐሙስ ጀምረው በማክፈል (በመጾም) እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ለሁለት ቀናት ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸምም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምእመናን የምሥራች ቄጠማ ያድላሉ፡፡

ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ ዅሉ፣ አሁንም ‹‹በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዅሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ጥንተ ማኅደራቸው ገነት መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› – ካለፈው የቀጠለ

በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን መጻጕዕን ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› ብሎ ሲነግረው ወዲውኑ ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሔደ፡፡ ከዚህ ላይ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው የዚህን በሽተኛ እምነት እናደንቃለን፡፡ ራሱን መሸከም የማይችለው መጻጕዕ ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸከም›› ሲባል አልሳቀም፡፡ ‹‹እንዴት አድርጌ ነው ደግሞ አልጋ የምሸከመው?›› ብሎ አልጠየቀም፡፡ በፍጹም እምነት ተነሣና ተሸክሞ ሔደ፡፡ የሠላሳ ስምንት ዓመት ጓደኛውን፣ ሰው ሳይኖረው አብራው የኖረችውን፣ የተሸከመችውን ባለ ውለታ የኾነችዋን አልጋ ተሸከማት አለው – ተሸክሞ ሔደ፡፡

አንድ ሰው እንኳን ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ይቅርና ለሠላሳ ስምንት ቀናት እንኳን ቢታመም እንደ ተሻለው ተነሥቶ አልጋ አይሸከምም፡፡ እስከሚያገግም ድረስ በደንብ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ራሱን ያዞረዋል፤ ይደክመዋል፡፡ የቀረ ሕመም አያጣውም፡፡ መጻጕዕ ግን የተፈወሰው ያለ ተረፈ ደዌ (ያለ ቀሪ በሽታ) ነበር፡፡ ጌታችንም ወዲያው ተነሥቶ አልጋውን እንዲሸከም አዘዘው፡፡ መምህር ኤስድሮስ እንደ ተረጐሙት መጻጕዕ የብረት አልጋውን ተሸክሞ እየሔደ የጌታን ጽንዐ ተአምራት አሳየ፡፡

ጌታችንም ከዚያ በሽታ ያዳነው በነጻ መኾኑን በሚያሳይ ኹኔታ ያችን አንዲት ንብረቱንም ‹‹ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ መጻጕዕ የተሸከመችህን አልጋ ተሸከም ተባለ፡፡ እግዚአብሔር የተሸከሙንን እንድንሸከም የሚፈልግ አምላክ ነው፡፡ ውለታ ሳንረሳ የተሸከሙንን ወላጆቻችንን የተሸከመችንን ቤተ ክርስቲያንን፣ የተሸከመችንን አገራችንን እንድንሸከም ይፈልጋል፡፡ አንድ ሊቅም ‹‹ዓለም እንደዚህ ናት፤ እናት ዓለም አልጋ መጻጕዕን ‹እንደ ተሸከምሁህ ተሸከመኝ› አለችው›› ሲሉ አመሥጥረውታል (ዝክረ ሊቃውንት 2)፡፡

ከዚህ ላይ ጌታችን ቤተ ሳይዳ ከመጣ አይቀር ዅሉንም በሽተኞች መፈወስ ሲችል ለምን አንዱን ብቻ ፈውሶ መሔዱ ጥያቄ ሊኾንብን ይችላል፡፡ ጥያቄ የሚያስነሣው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ሊቃውንቱ እንደ ጻፉት የቤተ ሳይዳው መጠመቂያ ፈውስ ከዚያ በኋላ ብዙም አለመቆየቱ ነው፡፡ የመልአኩም መውረድ ቆሞአል፡፡ ከዚያ በኋላ በሰባ ዓመተ ምሕረትም ኢየሩሳሌም መቅደስዋ ፈርሶአል፤ ተመሰቃቅላለች፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም ‹‹በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ‹ቤተ ሳይዳ› የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት፤›› ብሎ በኃላፊ ጊዜ ግስ (past perfect tense) ነው የተናገረላት (ዮሐ. ፭፥፪)፡፡

ታዲያ ጌታችን እንዲህ መኾኑን እያወቀ ምነው መጻጕዕን ብቻ ፈውሶት ሔደ? ቢባል የፈወሰው እርሱን ብቻ አይደለም፡፡ እርሱን በሥጋ ቢፈውሰውም ተአምራቱን አይተው በማመናቸው በነፍሳቸው የተፈወሱ ይበዛሉ፡፡ ‹‹ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ›› እንዲሉ አበው፡፡ በዚያ ሥፍራ በሥጋ ታመው በነፍሳቸው አምነው የዳኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ የጌታችንና የእርሱ አካል የኾነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሥራዋ ነፍስን መፈወስ እንጂ ሥጋዊ በሽታን መፈወስ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው እንጂ ጌታችን ሰው ኾኖ ይህችን ምድር በእግሩ ሲረግጥ በሽታ እንዳይኖር ያደርግ የነበረው፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ ‹‹በመስቀል ላይ በቈሰልኸው ቍስል ከኃጢአቴ ቍስል አድነኝ›› ብሎ እንደ ጸለየ እኛም የዘወትር ልመናችን ለሚከፋው ለነፍሳችን በሽታ ነው፡፡ የጌታችን ወደ ምድር መምጣት ዋነኛ ዓላማም ለነፍሳችን ድኅነትን ለመስጠት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ለሥጋ አልመጣም ማለት አይደለም፡፡ ጌታችን ‹‹ኃጢአተኞችን ለንስሐ ልጠራ መጣሁ እንጂ ጻድቃን ልጠራ አልመጣሁም … ከእስራኤል ቤት በቀር ለአሕዛብ አልተላክሁም›› ሲል መናገሩ ለጻድቃን አይገደኝም፤ ለአሕዛብ አላስብም ለማለት እንዳልኾነ ዅሉ፣ ለነፍስ ድኅነት ቅድሚያ ሰጥቶአል ማለትም ለሥጋ አይገደውም ማለት አይደለም፡፡

በመጻጕዕ ታሪክ ውስጥ የምንማራቸው ብዙ ነጥቦች ቢኖሩም ሁለት ነገሮችን ብቻ እናንሣና ይህችን አጭር ጽሑፍ እንግታ፤ ይህ ሰው ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሲሔድ ሰንበት ለሰው ድኅነት እንደ ተፈጠረች ያልተረዱ አይሁድ በቍጣ ነደዱ፡፡ ‹‹ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም፤›› አሉት፡፡ አስተውሉ! ይህ ሰው በቤተ ሳይዳ ሠላሳ ስምንት ዓመታት ሙሉ ሲማቅቅ እንደኖረ የሰውን ገመና አዋቂ ነን ባዮቹ አይሁድ ይቅሩና ቤተ ሳይዳን የረገጠ ሰው ዅሉ ያውቃል፡፡ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ወደዚያች የመጠመቂያ ሥፍራ ሲሔዱ፣ ያም ባይኾን በጎች ታጥበው ተመርጠው በሚገቡበት የበጎች በር ሲያልፉ ይህን በሽተኛ በአልጋው ተጣብቆ ሳያዩት አይቀሩም፡፡

አሁን ግን ከአልጋው ተነሥቶ የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ በአደባባይ ሲያዩት የጠየቁትን ጥያቄ ተመልከቱ፤ ‹‹እንኳን ለዚህ አበቃህ! ዛሬ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ውኃው ወረደ ማለት ነው? እሰይ ልፋትህን ቈጠረልህ!›› ያለው ሰው የለም፡፡ የተናገሩት አንድ ዐረፍተ ነገር ብቻ ነው፤ ‹‹ሰንበት ነው አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም›› የሚል ብቻ፡፡ በአይሁድ ዘንድ መጻጕዕ ድኖ ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ከመሔዱ ይልቅ ሰንበትን መሻሩ የሚያስደንቅ ትልቅ ዜና ነው፡፡ መጻጕዕም ‹‹ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ ያለህ ሰው ማን ነው?›› ብለው ጠየቁት፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህን በሽተኛ ፈጽሞ አያውቁትም ነበር ቢባል ‹‹ያዳነኝ ሰው›› ሲላቸው ‹‹ከምንድን ነው የምትድነው? ምን ኾነህ ነበር? ከየት ነው የመጣኸው?›› ይሉ ነበር፡፡

ነገር ግን መዳኑን ማየት አልፈለጉም እንጂ ማን እንደ ኾነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ እስኪ ጥያቄና መልሱ ውስጥ ያለውን ሽሽት እንመልከት፤ ‹‹ያዳነኝ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› ለሚለው ምላሽ ተከታዩ ጥያቄ ‹‹ማን ነው ያዳነህ?›› የሚል መኾን ነበረበት፡፡ እነርሱ ግን የጌታን የማዳን ሥራ ላለመስማት ጆሮአቸውን ደፍነው ‹‹አልጋህን ተሸከም ያለህ ማን ነው?›› አሉ፡፡ እንግዲህ የማዳኑን ሥራ እያዩ ከማመን ይልቅ መከራከር፣ ከማድነቅ ይልቅ የትችት ሰበብ መፈለግ ጌታን የሰቀሉ የአይሁድ ጠባይ ነው፡፡

የመጨረሻው ቁም ነገር መጻጕዕ ከዚህ በኋላ ወደ አይሁድ ሔዶ ጌታን መክሰሱና ለጌታ ሞት የመማከራቸው ምክንያት መኾኑ ነው፡፡ ይህ ሰው ‹‹ከዚህ የሚብስ እንዳይገጥምህ ደግመህ ኃጢአትን አትሥራ›› ብሎ ጌታ ቢያሳስበውም አልሰማም፡፡ ጌታ በተያዘበት በምሴተ ሐሙስ ለሊቀ ካህናቱ አግዞ ጌታችንን በጥፊ መታው፡፡ ጌታችንም ‹‹ክፉ ተናግሬ እንደ ኾነ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ ከኾነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?›› አለው (ዮሐ.፲፰፥፳፫)፡፡ ጌታችን ‹‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ› ከማለት በቀር ክፉ ቃል ተናግሬህ ከኾነ መስክርብኝ፤ የተናገርኩህ መልካም ኾኖ ሳለ ስለ ምን ትመታኛለህ?›› ማለቱ ነበር፡፡

በማግስቱ ያ ዅሉ ጅራፍና ግርፋት በጌታችን ላይ ሲደርስበት አንድም ጊዜ ‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› ብሎ አልተናገረም፡፡ የመጻጕዕ ጥፊ ይህን ያህል ዘልቆ የተሰማው ለምንድር ነው? ለዚህም የመጀመሪያው ምክንያት ከቤተ ሳይዳ ከበጎች በር ጋር የተያያዘ ምሥጢር አለው፡፡ ጌታችን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ በበጎች በር አልፎ የመጣውም ንጹሐ ባሕርይ እንደ ኾነ ለማስረዳት ነበር፡፡ ለዚህም ንጽሕናው ዋነኛው ምስክር ፈውስን የሰጠው ይህ በሽተኛ ነበር፤ እሱ ግን መታው፡፡ ‹‹በቤተ ሳይዳ ክፉ ቃል ተናግሬህ ከነበር መስክርብኝ›› ማለቱ ‹‹ነውር የሌለብኝ፣ ለመሥዋዕት የተዘጋጀሁ በግ ነኝ ለምን ትመታኛለህ?›› ሲል ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከሮማውያን ግርፋት በላይ ለጌታ ዘልቆ የሚሰማው ባዳነው ሰው መመታቱ ስለ ኾነ ነው፡፡

ውድ አንባብያን! መጻጕዕ ከሠላሳ ስምንት ዓመታት በሽታ ብቻ ዳነ፤ እኛ ግን የዳንነው ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በሽታ ነው፡፡ ጌታችን እኛን ያስነሣን ከሲኦል አልጋ ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት ያን ዅሉ መከራ ዝም ብሎ የተቀበለ ጌታ መጻጕዕ በጥፊ በመታው ጊዜ ግን ‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› ሲል ጠየቆታል፡፡ ከሌላው ሰው ይልቅ የእኛ ከዘለዓለም ሞት ያዳነን ክርስቲያኖች ዱላ ለእግዚአብሔር ይሰማዋልና፡፡ ይህም ዱላ ኃጢአታችን ነው፡፡ እናም እግዚአብሔር ዛሬም ድረስ እያንዳንዳችንን ይጠይቀናል – ‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› እያለ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› – ክፍል አንድ

በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የአይሁድ ፋሲካ ለሦስት ጊዜ ተከብሯል፡፡ የመጀመሪያው ፋሲካ ጌታችን ቤተ መቅደሱን ያጸዳበትና በቤተ መቅደስ ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩትን ያስወጣበት ሲኾን፣ በመጨረሻው የፋሲካ ሰሙንም እንደዚሁ ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደሱን አንጽቶ ጌታችን በፋሲካው ማግስት ተሰቅሏል፡፡ በሁለቱ ፋሲካዎች መካከል በነበረው ፋሲካ ነው ጌታችን ወደ ቤተ ሳይዳ የመጣው፡፡ ቤተ ሳይዳ የመጠመቂያው ሥፍራ ስም ሲኾን ከአጠገቡ ደግሞ የበጎች በር ነበር፡፡ (የበጎች በር በአሁኑ ሰዓት የቅዱስ እስጢፋኖስ በር እና የአንበሳ በር ተብሎ ይጠራል)፡፡

እንደሚታወቀው ዘመነ ኦሪት በግ መሥዋዕት ኾኖ የሚቀርብበት ዘመን ነበር፡፡ መሥዋዕት ኾነው የሚቀርቡ በጎች የሚገቡት በዚህ በር ነበር፡፡ በሩ በጎቹ ነውር እንደሌለባቸው ማለትም ቀንዳቸው እንዳልከረከረ፣ ጥፍራቸው እንዳልዘረዘረ፣ ፀጕራቸው እንዳላረረ የሚጠኑበት፤ የአንድ ዓመት ተባዕት (ወንድ) መኾናቸው የሚታይበት ሥፍራ ነው፡፡ ይህን መሥፈርት አሟልተው ያለፉ በጎች ለመሥዋዕትነት ሲቀርቡ ለዚህ ብቁ ያልኾኑትን ግን ለይተው፣ በአለንጋ እየገረፉ ያስወጡአቸዋል፡፡

በቤተ ሳይዳ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያዪቱ ወርዶ ውኃውን አንዳንድ ጊዜ ያናውጠው ነበር፡፡ ይህ መልአክ በሰው ቍስል፣ በበሽታም ዅሉ ላይ የተሾመ የስሙ ትርጓሜም ‹‹እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው›› ማለት የኾነ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ መልአኩ ውኆችን ለመቀደስ፣ ጸሎትን ከሰው ወደ ፈጣሪ ለማድረስ ወደ ውኃው ይወርድ ነበር፡፡ ይህም በየትኛውም ውኃ መዳን ባይቻለንም ቅዱሳን መላእክት የነኩት ውኃ በረከትና ፈውስ እንደሚያሰጥ የሚያስረዳ ነው፡፡ ውኃው ከተነዋወጠ በኋላ ከደዌው መዳን የሚችለው በመጀመሪያ የሚገባ በሽተኛ ነበር፡፡ በዚህ የጠበል ሥፍራ በነበሩ አምስት መመላለሻዎች በሽተኞች በተለይ አንካሶች፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር፡፡

ከሌሎች በሽተኞች በተለየ እነዚህ የውኃውን መናወጥ አይተው ለመግባት፣ በዓይናቸውም ለማየት አይቻላቸውም፡፡ ገብተውም እንኳን ቢኾን ድንገት ከእነሱ ቀድሞ የገባ ሰው በመፈወስ ስለሚቀድማቸው ሳይፈወሱ ይመለሳሉ፡፡ ስለዚህም ከውኃው መልሶ የሚያወጣቸውም ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሚያወጣቸው አጥተው ሊቸገሩም ይችላሉ፡፡ ምናልባትም በእንደዚህ ዓይነት ችግር ለባሰ ነገር የተዳረገ በሽተኛም ሊኖር ይችላል፡፡ ከእነርሱ ቀድሞ የሚድነው እንግዲህ ሁለት ዓይነት ሰው ነው፤ አንደኛው በሽታው ለመንቀሳቀስ የማያግደው ኾኖ እያለ የእነሱ ይብሳል ብሎ ሳያዝን የሚገባ ነው፡፡

እንኳን ቀድሞ የገባ ሰው ብቻ በሚድንበት ሥፍራ ቀርቶ በማንኛውም ሰዓት ቢገባ በሚዳንበት የጠበል ሥፍራ ‹‹ከእኔ በሽታ የእገሌ ይብሳል፤ እስኪ ቅድሚያ ልስጠው›› የሚል ሰው ብዙ ጊዜ አይታይም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ደካሞች ቀድመው የሚገቡ በሽተኞች ብዙ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ወደ መጠመቂያው ሊያስገቡት የሚጠባበቁ ዘመዶች ያሉት፣ አለዚያም ዘመድ የሚያፈራበት ገንዘብ ያለው በሽተኛ ደግሞ ሌላው ቀድሞ ወደ መጠመቂያው የሚገባ ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የተኛ በሽተኛ (በግእዙ መጻጕዕ) ነበር፡፡ እንግዲህ ሠላሳ ስምንት ዓመት ማለት የጕልምስና ዕድሜ ነው፡፡

መጻጕዕ የመጣው በዐሥር ዓመቱ ነው እንኳን ብንል ዐርባ ስምንት ዓመት ይኾነዋል፡፡ ይህ ሰው ከመታመሙ በፊት ለዚህ ጽኑ ደዌ የሚዳርግ ኃጢአት ለመሥራት የሚችልበት ዕድሜ ላይ መድረሱን ጌታችን ከፈወሰው በኋላ ‹‹ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ደግመህ ኃጢአትን አትሥራ›› ብሎ በማስጠንቀቁ እንረዳለን፡፡ መቼም ክፉ ደግ በማያውቅበት ሕፃንነቱ በድሎ ‹‹የልጅነቱ መተላለፍ ታስቦበት ታመመ›› ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡ ብቻ ይህ ሰው የአንድ ጐልማሳ ዕድሜ ያህል በአልጋ ላይ ኾኖ በቤተ ሳይዳ ተኝቶአል፡፡ ጠበል ሊጠመቅ ሲጠባበቅ በፀጕሩ ሽበት፣ በግንባሩ ምልክት አውጥቶአል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ግርግም ውስጥ ሲወለድም ይህ በሽተኛ በዚሁ መጠመቂያ ሥፍራ ነበረ፡፡

ድንግል ማርያም የወለደችውን ሕፃን በበረት ውስጥ ስታስተኛው ይህ በሽተኛ አልጋው ላይ ከተኛ ስድስት ዓመት ደፍኖ ነበር፡፡ ከዅሉ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሰው አልጋው ላይ ኾኖ እጅግ ብዙ ሰዎች ቀድመውት ሲፈወሱ ሲመለከት መኖሩ ነው፡፡ ከእርሱ በኋላ መጥተው ከእሱ በፊት ድነው የሚሔዱ ሰዎችን ማየት እንዴት ይከብደው ይኾን? እንደ እርሱ ብዙ ዘመን የቆዩት ሲድኑ ሲያይ ተስፋው ሊለመልም ይችላል፡፡ በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመደ ብዙ በመኾናቸው ብቻ የሚድኑ ሰዎችን ሲያይ ግን ልቡ በሐዘን ይሰበራል፡፡ ዓመቱ በረዘመ ቍጥር ተስፋ ቈርጦ ቤተ ሳይዳን ቤቴ ብሎ ከመኖር በስተቀር ምንም የሚታየው ነገር አይኖርም፡፡

እግዚአብሔርን በመከራው ውስጥ ተስፋ እያደረገ ይጽናናል እንዳንል ደግሞ እንደ ጻድቁ ኢዮብ ወይም እንደ በሽተኛው አልዓዛር ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት አልነበረውም፡፡ እንደዚያ ቢኾን ኖሮ መቼ ለዚህ በሽታ የሚዳርገው ኃጢአት ይሠራ ነበር? በቃለ እግዚአብሔር ይጽናናል ማለትም ያስቸግራል፡፡ ያም ኾነ ይህ መጻጕዕ በበሽታው እጅግ ተሰቃይቶ ነበር፡፡ ጌታችን የዚህን ሰው ችግር ብቻ ሳይኾን ብዙ ዘመን እንደዚህ እንደነበረ ያወቀው ማንም ሳይነግረው ነበር፡፡ በሽታውን ከነመንሥኤው አስቀድሞ ያውቃልና ወደዚህ የብዙ ዓመታት በሽተኛ መጣና ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› አለው፡፡ ጌታችን የሚፈልገው ይህንን ሰው መፈወስ እንጂ የራሱን ማንነት ማሳየት ስላልነበረ ‹‹ላድንህ ትወዳለህን?›› አላለውም፡፡ በዚያውም ላይ ይህ ሰው የጌታን ማንነት አያውቅም፡፡

ይህ በሽተኛ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ሲባል የሰጠው ምላሽ እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሽታ አመል ያጠፋል፡፡ በሽታው በቆየ ቍጥር ደግሞ መራር ያደርጋል፡፡ ሰዎች በበሽታ ሲፈተኑ በሰው በፈጣሪም ላይ ብዙ የምሬት ንግግር ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ጌታችን ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ ሲጠይቀው ምንም የምሬት እና የቍጣ ቃል ሳይናገር በጨዋ ሰው ሥርዓት ‹‹ጌታ ሆይ …›› ብሎ ነው የመለሰለት፡፡ በዚህ ኹኔታው መጻጕዕ ትሑት ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን የመለሰው የተጠየቀውን አልነበረም፡፡ ጥያቄው ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› የሚል ከኾነ ምላሹ ‹‹አዎን፤ መዳን እወዳለሁ፤›› አለዚያም ‹‹አይ መዳን አልፈልግም›› የሚል ብቻ መኾን ነበረበት፤ እርሱ ግን ‹‹ጌታ ሆይ! ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፡፡ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› የሚል ምላሽ ነበር የሰጠው፡፡

መጻጕዕ የጌታችንን ማንነት ባይረዳውም ጌታችን በወቅቱ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበርና ምናልባት ወደ መጠመቂያው ሊጨምረኝ አስቦ ይኾናል ያም ባይኾን ግን ከተከተሉት ሰዎች አንዱን አደራ ሊልልኝ ይኾናል ብሎ አስቦ ነበር፡፡ ‹‹ሰው የለኝም›› ብሎ የሠላሳ ስምንት ዓመታት ብሶቱን ተናገረ፡፡ ‹‹ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› ብሎ እየቀደሙት ሲፈወሱ የነበሩ ሰዎችን አስታወሰ፡፡ ጌታችንም ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ ባላሰበው፣ ባልጠበቀው መንገድ ፈወሰው፡፡ ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ሲጠባበቃት የነበረችውን የቤተ ሳይዳ ጠበል ሳያገኝ፣ በመልአኩ መውረድ ሳይኾን በመላእክት ፈጣሪ ቃል ተፈወሰ፡፡

ገባሬ መላእክት ክርስቶስ ራሱ መጥቶ አዳነው፡፡ ይህ ሰው ‹‹ለመዳን የሚያስፈልገው ምንድን ነው?›› ተብሎ ቢጠየቅ የሚመልሰው ‹‹ወደ ውኃው የሚጨምር ሰው እና የቤተ ሳይዳ ውኃ›› ብሎ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በዚህች ጠበል ካልኾነ በቀር በሌላ በምንም መንገድ ያድናል ብሎ አስቦም አልሞም አያውቅም ነበር፡፡ ጌታችን መጻጕዕ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ተስፋ ያደረጋትን ጠበል ወይም ደግሞ ወደ ጠበሉ የሚጨምሩትን ሰዎች ሳይጠቀም አምላካችን ፈወሰው፡፡ እግዚአብሔር ያለ ጠበልም እንደሚያድን ማመን ካልቻልን እምነታችን ሙሉ አይደለም፡፡

ይህ ሰው ወደ ውኃው ገብቶ ቢድን ኖሮ ‹‹ጌታዬ አዳነኝ›› ከማለት ይልቅ ‹‹መዳን ይነሰኝ? ሠላሳ ስምንት ዓመት እኮ ነው የጠበቅኩት …›› እያለ ልፋቱን ያወራርድ ነበር እንጂ ፈጣሪውን አያመሰግንም ነበር፡፡ ጌታችንም ‹‹ስታምኑብኝ ብቻ ነው የምፈውሳችሁ›› የሚል አምላክ አይደለም፣ ለዅሉም ፀሐይን የሚያወጣ፣ ዝናምን የሚያዘንም አምላክ ይህንን ሰውም ለመፈወስ እስኪያምነው አልጠበቀም፡፡ ጌታችን ጠበል ቦታ ያገኘውን ያለ ጠበል ፈወሰው ሲባል መቼም ጠበል መጠመቅ የማይወዱ ወይም በጠበል የማያምኑ ሰዎች ደስ ሊላቸው ይችላል፡፡

‹‹እኛስ ምን አልን? ጌታ እኮ ይህን በሽተኛ ጠበል ቦታ አግኝቶ እንኳን የፈወሰው ያለ ጠበል ነው›› ብለው ባቀበልናቸው በትር ሊመቱን ይፈልጉ ይኾናል፡፡ ኾኖም በዮሐንስ ወንጌል በዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ ዕውር ኾኖ የተወለደውን ሰው ጠበል በሌለበት ሥፍራ አግኝቶት እኛ እመት (እምነት) የምንለውን አፈር በምራቁ ለውሶ ከቀባው በኋላ ‹‹ሒድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ›› ብሎ ልኮታል፡፡ ጠበል ምንም የማያስፈልግ ቢኾን ኖሮ ዓይነ ስውሩን ሰው ወደ ወንዝ ወርደህ ተጠመቅ ብሎ አይልከውም ነበር፡፡ ዛሬ ለታመሙ ሰዎች ‹‹ጠበል ሒዱ›› ብለን ስንመክር ክርስትና ያልገባን፣ ክርስቶስን የማናውቅ የሚመስለው ይኖራል፡፡

አሁን ባየነው ታሪክ ውስጥ ግን ለበሽተኛው ‹‹ሔደህ ጠበል ተጠመቅ›› ብሎ የመከረው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መፈወስ የሚቻለው ክርስቶስ ‹‹ጠበል ተጠመቅ›› ብሎ ከተናገረ፤ የታመመን መፈወስ የማንችለው እኛ ኃጢአተኞቹ ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ ‹‹ሔደህ ተጠመቅ›› ብንል ምን አጥፍተናል? ጌታችን ሲያደርግ ያየነውን ነው፡፡ ‹‹እኔን ምሰሉ›› ብሎን የለ እንዴ? (ዮሐ. ፱፥፯)፡፡ በእነዚህ ሁለት ታሪኮች አምላካችን ሲፈልግ በጠበል፣ ሲፈልግ ያለ ጠበል፣ አልያም በሕክምና፤ ሲያሻው በምክንያት ሲያሻው ያለ ምክንያት፤ ሲፈልግ በቃሉ፣ ሲፈልግ በዝምታ፤ ሲፈልግ በቅዱሳን መላእክቱ፣ ሲፈልግ ያለ ቅዱሳን መላእክቱ ማዳን እንደሚቻለው እንረዳለን፡፡

ይቆየን

ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን)

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)

ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድአታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡

ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤

፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ›› ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡