ዐቢይ ጾም
‹ዐቢይ›› የተባለው የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነት ጾሞ የመሠረተው ጾም ስለሆነ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ካሉት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት ረጅሙ (፶፭ ቀን ያለው) ስለሆነ ደግሞ ‹‹ሁዳዴ›› ይባላል፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማና የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙትን ስምንት ሣምንታት ለትምህርት፣ ለአዘክሮና ለምስጋና በሚመች መልኩ ልዩ ስያሜዎች ሰጥቷቸዋል፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ሳምንት (ሰንበት) የሚነበቡ፣ የሚተረጎሙ፣ የሚዘከሩ፣ የሚዘመሩ ልዩ ልዩ መጽሐፍ ቅዱሣዊ ኩነቶችና አስተምህሮዎች አሉ፡፡