‹‹ትዕግሥትን ልበሱ!›› (ቈላ.፫፥፲፪)

ሰኔ ፮፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በሕይወታችን ውስጥ እጅጉን አስፈላጊ መጨረሻውም አስደሳች የሆነው ነገር ትዕግሥት ነው፤ በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ ሆነን የምንጋፈጠውን ችግር፣ መከራና ሥቃይ በብርታትና በጽናት ለማለፍ የምንችለው ትዕግሥተኛ ስንሆን ነው፡፡ መታገሥ ከተቃጣ ሤራ፣ ከታሰበ ክፋት፣ ከበደልና ግፍ ያሳልፋል፤ ልንወጣው ከማንችለው ችግርም እንድንወጣ ይረዳናል፡፡

በዚህ ዓለም ስንኖር በቤተ ሰቦቻችን፣ በዘመዶቻችን እንዲሁም በጎረቤቶቻችን መካከል ወይም ከትዳር አጋሮቻችን ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች፣ ችግሮች ወይም ጥሎች ይከሠታሉ፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ውስጥ እልባት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ወይም ደግሞ ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ሀገራትም በማኅበረሰባዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ወይም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ምክንያት ሲከፋፈሉ፣ ሲጋጩና ወደ ጦርነት ሲገቡ ተመልክተናል፡፡

ይህ ሁሉ ግን በትዕግሥት መታለፍ የሚችል እንደሆነ ከሐዋርያው ከቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ትዕግሥትን ልበሱ!››  ከሚለው ቃል እንማራለን፡፡ (ቈላ.፫፥፲፪) የሚገርም ነው! ሰው ትዕግሥትን መልበስ እንደሚቻለው ሐዋርያው ጽፎልናል፡፡ ትዕግሥትን እንደ ልብስ መልበስ እንደሚቻል በቃሉ ነግሮናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ትዕግሥትን ልበሱ ሲል እጅጉን ትዕግሥተኛ እንድሆን ሲያስረዳን ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ትዕግሥተኛነት ያስተማረን እርሱ ራሱ ትዕግሥተኛ በመሆን ነው፤ አይሁድ ያለ በደልና ጥፋቱ በጲላጦስ ፊት ከሰው ሲፈርዱበትም ሆነ በቀራንዮ አደባባይ ሲያሠቃዩት እንደ አምላክነቱ በኃይሉ ሳያስቆማቸው ሁሉንም መከራና ሥቃይ በትዕግሥት ተቀብሎልናል፡፡ ይህን ሁሉ ስለ ሰዎች ፍቅር ሲል አደረገው፡፡ እኛም ሰዎች ለአምላካችን ፍቅር ስንል ምድራዊ መከራንና ሥቃይን ልንቀበል እንደሚገባ ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡

ማንኛውም ችግር ሲደርስብን ከመቾኮል የነገን በማሰብ መታገሥ፣ ጠላቶቻችንን ከመጥላት ይልቅ በፍቅር ትዕግሥት ማድረግ፣ ኑሮ ሲመርብን ከመማረርና ሰልችቶን ተስፋ ከመቁረጥ የወደ ፊት ሕይወታችን መልካም እንደሆነ በማሰብ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ጌታችን ለሐዋርያት ‹‹በዓለም ሳለችሁ መከራ አለባችሁ›› ብሎ አስተምራቸዋልና የሚፈትነንም ሆነ መከራ መስቀሉን የምንሸከመው ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ልንወርስ እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ (ዮሐ.፲፮፥፴፫)

በመጽሐፍ ቅዱስ ከተመዘገቡት የጻድቃን ታሪክ ኢዮብ እጅግ ትዕግሥተኛ እንደሆነ ይነገራል፤ ይህ ሰው አስቀድሞ እጅግ ባለጸጋ የነበረና ትዳሩ የተባረከለት የእግዚአብሔር ሰው ነበር፡፡ በመጽሐፈ ኢዮብ እንዲሁም በመጽሐፈ ስንክሳር (ግንቦት ሁለት ቀን) ላይ ታሪኩ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

ኢዮብ ትውልዱ አውስጢድ በሚባል ሀገር ሲሆን ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ከክፋ ሥራም የራቀ እንደነበር ይነገርለት ነበር::  (ኢዮ.፩፥፩) እግዚአብሔርም በዘመኑ እንደርሱ ያለ እውነተኛ ደግ ሰው እንዳልነበረ መስክሮለታል:: ይህን ጊዜም ሰይጣን ቀንቶ ኢዮብን እንዲፈትነው እግዚአብሔር ጠየቀ:: አምላካችንም እግዚአብሔር የኢዮብን ትዕግሥት ስለሚያውቅ ሰይጣንን በኢዮብ ላይ አሠለጠነው፡፡

ከዚህ በኋላም የኢዮብ ገንዘብ ሁሉ በአንድ ቀን ጠፋ፤ በደዌ ሥጋ ከራሱ ጠጉሩ እስከ እግሩ ጥፍሩ ድረስ ተመትቶ በአስጨናቂ ደዌ ውስጥ ለብዙ ጊዜ ኖረ፤ እግዚአብሔርን ግን ፈጽሞ አላማረረም:: ነገር ግን ‹‹ረገማ ለዕለት ዘተወልደ ባቲ፤ ……የተወለደበትን ቀን ረገመ::›› (ኢዮ.፫፥፩) ከብቶቹ፣ ገንዘቡ፣ ሀብትና ንብረቱ ሁሉ በጠፋ ጊዜም ‹‹እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን አለ:: (ኢዮብ ፩፥፳፩)

ጻድቁ ኢዮብም በዚህ መከራ ውስጥ ሲኖር ወዳጆቹና ሚስቱ አብዝተው ይዘልፉት ነበር:: ሚስቱም መከራና ችግሩን ተቋቁሞ እንዲያልፍ ከማጽናናት ይልቅ እንዲህ ብላ መከረችው:- ‹‹እስከ መቼ ድረስ በሞኝነት ትኖራለህ፤ እንግዲህስ ስደበውና ሙት፤ ዳግመኛ እግዚአብሔርን ደጅ እጠናዋለሁ፤ መከራውንም እታገሣለሁ፤ የቀድሞ ኑሮዬን ተስፋ አድርጋለሁ ትላለህ›› አለችው::

ዳግመኛም አለችው:: ‹‹እንዲህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እንሆ ስም አጠራርህ ጠፋ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼ ሞቱ:: እኔም ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ላይረቡኝ ላይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምኩ:: አንተም በመግል ተውጠህ፣ በትል ተከበህ ትኖራለህ፤ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ፤ እኔም እየዞርኩ፣ እቀላውጣለሁ፤ ከአንዱ ሀገር ወዳንዱ ሀገር ካንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ:: ከድካሜ በእኔ ላይ ከመጣው ከችግሬም ዐርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኽው ሙት›› አለችው::

ኢዮብም የሚስቱን ንግግር በትዕግሥት ከሰማ በኋላ እንዲህ አላት፦ ‹‹ይህን ሁሉ እግዚአብሔር ለመልካም አደረገ፤ ሥርዓት እንዳልተሠራባቸው አሕዛብ ሴቶች እንዳንዲቱ ተናገርሽ፤ ከዚህ ቀድሞ በጎውን ነገር ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበልን፤ ከዚህ በኋላ መከራውን እንታገሥም ዘንድ›› አላት:: (መጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ሁለት)

ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር አምላክ በምሕረት ጎበኘው፤ ከደዌ ሁሉ ፈውሶ ጤነኛ አደረገው፤ የተባረኩ ወንዶችና ሴቶችንም ሰጠው፤ ዳግምም ከነበረው ሀብት እጥፍ ሰጥቶ ባለጸጋ አደረገው፡፡ (ኢዮብ ፵፪፥፲-፲፫)

የጻድቁ ኢዮብ ታሪክ በምድራዊ ሕይወታችን የሚያጋጥሙን የትኛውንም ዓይነት ችግርና መከራ ማለፍ እንደሚቻል ያስተምረናል፡፡ ምክንያቱም ኢዮብ አንድ ሰው ሊኖረው ከሚገባው ንብረት በላይ የነበረው ሀብት እንዲሁም የተባረከ ቤተ ሰብ የነበረው ሲሆን ያንን ሁሉ በአንድ ጊዜ በማጣቱ በአምላኩ ሳይማረር በትዕግሥት የመከራ ጊዜው እንኪያልፍ ጠብቋል፤ የትዕግሥቱን ፍሬ መብላት እንደቻለ ተመልክተናል፡፡ ስለዚህም እኛ ይህን ምሳሌ በማድረግ ልንኖር ይገባናል፡፡ በተለይም በዚህ መከራና ችግር በበዛበት ጊዜ በኑሮአችን የሚያጋጥሙንን የቤተ ሰብ፣ የማኅበራዊም ሆነ የኢኮኖሚያዊ ችግር በትዕግሥት ማለፍ እንደሚቻለን በማመን እንኑር!

አምላካችን እግዚአብሔር ትዕግሥቱን ያድለን፤ አሜን!