‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው›› (መዝ፣ ፻፲፰፥፻፭)

የእግዚአብሔር ሕግ ብርሃን ነው፤ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው›› ብሎ ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው ከዚህ ከጨለማ እና ከተወሳሰበ ዓለም ከፈተና ያወጣን ዘንድ በትእዛዙ ልንኖር ይገባል፡፡ ማንኛውም ፍጡር የአምላኩን ስም የሚሰማበት ጊዜም ሆነ ሥፍራ  ይኖራልና ፈጣሪያችን እውነት እና ሕይወትም መሆኑን ተረድተን በመንገዱ መጓዝ የእኛ ፈንታ ነው፡፡  (መዝ፣ ፻፲፰፥፻፭)

‹‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ›› (ዮሐ. ፲፬፥፲፭)

ሰው አምላኩ እግዚአብሔርን ከወደደ ሁለተናውን ለእርሱ ይሰጣል፤ ከኃጢአት የነጻ ሆኖ ልበ ንጽሕ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ከፈጣሪያችን ስለምንረቅ ለሌላ ባዕድ ነገር ተገዢ እንሆናለን፡፡ ክርስቶስን በሙሉ ልባችን፤ ነፍሳችን፣ ኃይላችን ከወደድነው ግን ፍቅሩን ተረድተን ሁለመናችን ለእርሱ እንሰጣለን፤ እርሱም ደግሞ ከእኛ ጋር ይሆናል።

‹‹ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር›› (ኢሳ. ፩፥፲፰)

ብዙ ጊዜ በሕይወት በሚገጥመን ፈተናና ችግር ምክንያት ራሳችንን በመመርመር እግዚአብሔርን መማጸንን የመሰለ መፍትሔ ወይም የድኅነት መንገድ የለም፡፡ እስራኤል ከእግዚአብሔር ርቀው፤ ወደ ቃሉ መጠጋት በአቃታቸው ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ የመጣባቸው መቅሠፍት የኃጢአታቸው ውጤት ስለነበረ እግዚአብሔር አጥቦ ቅዱሳን ልጆቹ ሊያደርጋቸው የተዘጋጀ አባት በመሆኑ ‹‹ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር›› አላቸው፡፡ (ኢሳ. ፩፥፲፰)

‹‹ለታመሙት መድኃኒት አንተ ነህ›› (የዐርብ ሊጦን)

መድኃኒት ለሰው ልጅ ፈውስ መሆኑን እንረዳ ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በሥጋ በተገለጠበት ማለትም በዘመነ ሥጋዌው አስተምሯል፡፡ በዚያን ጊዜም ብዙዎች ወደ እርሱ እየቀረቡ ማንነቱን ለማወቅ ይጥሩ እና ትምህርቱንም ይሰሙ ነበር፡፡ እርሱም በመካከላቸው ሆኖ ወንጌልን ይሰበክላቸው፤ የታመሙትንም ይፈውሳቸው፤ የእጆቹን ተአምራት ዓይተውም ሆነ ሰምተው ያመኑትንም ያድናቸው ነበር፡፡ ‹‹ለታመሙት መድኃኒት አንተ ነህ›› እንደተባለው ፈውሰ ሥጋ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነም ተረዱ፡፡ (የዐርብ ሊጦን) 

ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት

በዚህ ዓመት ጾመ ሐዋርያት ሰኔ ፩፤ ጾመ ድኅነት ደግሞ ሰኔ ፫ ቀን ይጀመራሉ፡፡ በመሆኑም የምንጠቀመው በራሳችን መልካም ተግባር፤ የምንወቀሰውም በራሳችን ኃጢአት መሆኑን ተረድተን ‹ይሄ የቄሶች፤ ይሄ የመነኰሳት ነው› የሚል ሰበብ ሳንፈጥር ሁላችንም በአንድነት ብንጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድይቅርታ ጸጋና ምሕረትን እናገኛለንና ራሳችንን ለጾም እናዘጋጅ፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡ (፩ኛ ዮሐ.፩፥፯)

የሰው ልጅ ንስሓ ገብቶ ከኀጢአት ነጽቶ ቅዱስ ቊርባንን የሚቀበል ከሆነ ዳግም ሞት የለበትም፡፡ በፍጻሜ ዘመኑ ከዚህ ዓለም ተለይቶ ወደ ወዲያኛው ዓለም በሚሸጋገርበት ጊዜም ወደ ገነት እንጅ ወደ ሲኦል አይወርድም፡፡ ወደ ሲኦል ቢሄድም እንኳ ልትቀበለው አትችልም፤ ምክንያቱም በሕይወተ ሥጋ ሳለ በደመ ክርስቶስ ታትሟልና፡፡

‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› (ማር. ፭፥፴፮)

በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ለእኛ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች እምነት የድኅነታችን መሠረት ነው፤ በፈተናና መከራ ለተሞላው ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለጠላት ከመሸነፍም ሆነ በኃጢአት ከመውደቅ የሚያድነን እንዲሁም በተስፋ ነገን እንድንጠብቅ የሚረዳን እምነታችን ነው፡፡ ዘወትር በጸሎት አምላካችን ድኅነተ ሥጋን እና ድኅነተ ነፍስን ለምንማጸን እርሱ እግዚአብሔር ቸርነቱና ምሕረቱ የበዛ ነው፡፡

‹‹ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ሰው ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› (ያዕ. ፭፥፲፮)

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን አምላካችንን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሌት ከቀን ያለማቋረጥ በጸሎት፤ በጾም እና በስግደት ያገለገሉ ቅዱሳን አባቶቻችንን በማሰብ ለኃጢአተኞች ምሕረትን እንደሚያደርግ ነው፡፡ በተለይም ጻድቁ አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ተጋድሏቸውን ሲፈጽሙ በተሰጣቸው ቃል ኪዳን መሠረት እኛን ከቸነፈር እንደሚጠብቁን በማሰብ ልንጽናና ይገባል፡፡ …..
እንዲሁም ሕፃኑ ቂርቆስ በሰማዕትነት ባረፈበት ዕለት ‹‹…ስምህ በተጠራበት፣ ቤተ መቅደስህ በታነጸበት ሥዕልህ ባለበት ቦታ ሁሉ የሕፃናት እልቂት፣ የከብት በሽታ፣ የእህል እጦት፣ ረኃብ፣ ቸነፈር አይደርስም›› የሚል ቃል ኪዳን ሰጥቶታል፡፡

‹‹እግዚአብሔር ይቅርታን ይረሳልን? በቁጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?›› (መዝ. ፸፮፥፱)

ብዙዎች በአሁኑ ሰዓት ስጋትና ጭንቀት ላይ ናቸው፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ይቅርታን ይረሳልን? በቁጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?›› ብሎ በጸሎት እንደጠየቀው አዛውንቶችም የዚህ መቅሰፍት ማብቂያ የሚቆምበትን ጊዜ በመመኘት አምላካቸው ስለምን ቸል እንዳለ ሲጠይቁ ይሰማሉ፤ ምሕረትንም እንዲያበዛልን አብዝተው ሲለምኑ ይደመጣሉ፡፡ (መዝ. ፸፮፥፱)

‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው›› (ዕብ. ፲፩፥፩)

ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን በእምነት ከጸናን የማናልፈው ነገር የለም፡፡ የማንዘለው የችግር እና የመከራ ግንብ፣ የማንሻገረው ባሕር እና መሰናክል አይኖርም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር ከኖርን የሚያስፈራን አንዳች ነገር አለመኖሩን ሲያስረዳ ‹‹በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል›› ብሏል፡፡ (መዝ. ፳፪፥፬)