ዕረፍት ያጣች ነፍስ!
በሕይወት ሳልለው
እግዚአብሔር አምላካችን በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረን በክብር ነውና ከአለመኖር ወደ መኖር ያመጣንም በእስትንፋሱ ነበር፡፡ «እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ»፤ (ዘፍ ፪፥፯)፤
አባታችን አዳም ባደረገው ስሕተት ከገነት ተባሮ ወደ ምድር ከወረደ በኋላ ኑሮው የከፋ ነበር፤ ብዙም ተፈትኗል፤ ገነት ሳለ ደስታን እንጂ መከራን አላወቀም፤ ነገር ግን እዚህ ምድር ላይ በፍርሃትና በጭንቀት ይኖር ነበር፡፡ ከልብሰ ብርሃንም ተራቆተ፤ ተበረደ፤ የበለስ ቅጠል ቆርጦም ለበሰ፤ በመከራውም ጊዜ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፉ የሠራውን ኃጢአቱን በማሰብ ያለማቋረጥ ያለቅስ ነበር፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላም በተገባለት ቃልኪዳን መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እስኪያድነው ድረስ በምድር ብዙ ተሠቃይቷል፡፡
ሰው ድኅነትን የሚያገኘው በክርስትና ሕይወቱ ውስጥ ለእምነትና ለሃይማኖቱ መሥዋዕትነት በመክፈል፤ ዘወትር በክርስቲያናዊ ሥርዓት፤ በምስጋናና በሕገ እግዚአብሔር ሲኖር ነው፡፡ ነገር ግን ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በኃጢአት ማዕበል ውስጥ ተዘፍቃለች፤ መከራ፤ ሥቃይ፤ ችግር፤ እንዲሁም ጦርነት በየሀገሩ በዝቷል፡፡ ትንቢቱም እንደሚገልጸው «ሕዝብ በሕዝብ ላይ፤ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኃብ፤ ቸነፈርም፤ የምድር መናወጥም ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ ያንጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ ያን ጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ» (ማቴ. ፳፬፥፯-፲)፡፡
በዚህች ምድር ላይ ስንኖር ልንፈተን እንችላለን፤ በዕለት ክንዋኔያችን ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ ሊገጥመን ይችላል፡፡ ከጥንት ጀምሮ አእምሮአችንን ለመቆጣጠርና ትዕግስትን አስጨርሶ ተስፋ ለማስቆረጥ የሚፈታተነን ጠላት ዲያብሎስ የማሳቻ መንገዱ ብዙ ነውና በእምነት ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው ለውድቀትና ለጥፋት የቀረበ ይሆናል፤ ዕረፍትን የሚሻ ሰው ግን በተስፋ ውስጥ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔ እንዳለው፤ ለእያንዳንዱ ለተቆለፈ መዝጊያ አንድ ወይም ብዙ ቁልፎች እንዳሉትና ለእያንዳንዱ ውድቀትም መነሻ እንዳለው ይታወቃል::
ሰላምና ፍቅር ከእኛ ሲርቅ ማንነታችንን መጥላት፤ የእኛ ያልሆነውን ባዕድ ጠባይ መቀበል እንጀምራለን፤ ነፍስ ግን ሁሌም ፈጣሪዋን ትፈልጋለች፤ እናም ትጨነቃለች፡፡
ዛሬም ያለው ትውልድ ከነፍሱ ይልቅ ለምድራዊ ሕይወቱ ይለፋል፤ ነገር ግን ከንቱ ልፋት ነው፡፡ «ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ነፋስንም እንደመከተል ነው»መጽሐፈ መክብብ ፩፥፲፬፡፡የሰው ልጅ ኅሊናውን ሳይክድ ለእምነቱ ተገዝቶ ሲኖር ወደ ፈጣሪው መቅረብ ይቻለዋል፤ ሁል ጊዜም አምላኩን ሲያስብ፤ በተስፋም ሲኖር፤ ወደ ክብር ቦታው እንደሚመለስ በማመን በጎ ሥራን አዘውትሮ ይተገብራል፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ሰው ፈጣሪውን ያስባል፤ ይፈራል፤ ያከብራል እንዲሁም በሕጉ ይመራል፤ ከራሱም አልፎ ለሌሎች ጥሩ ማድረግን ይመኛል፤ ያደርጋልም፡፡
እርግጥ ነው ጠባያችን እንደመልካችን ይለያያል፤ እግዚአብሔር አምላካችን በቃሉ «ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሉአት» እንዳለው (ዘፍ. ፩፥፮)፤ በዓለማችን በቢሊዮን የምንቆጠር ሰዎች አለን፡፡ እናም ተከባብሮ የመኖር ውዴታና ግዴታ የእኛ ቢሆንም ኃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ ክፋት፤ ተንኮል፤ በደል፤ ጥላቻ፤ ግድያ ከዛም አልፎ ባዕድ አምላኪም በዝቷል፡፡ ፈውስና በረከት ማጣት፤ በምሬትና በሰቆቃ ውስጥ ለመኖር መንስኤው የኃጢአት መብዛት ነው፤ ክፉውም ሆነ ደጉ የሥራችን ውጤት ነው፡፡
በዚህ ምድር ስንኖር ሥጋችንንም ዋጋ በማሳጣት ለነፍሳችን ልንኖርላት እንደሚገባ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል አስተምሮናል፤ «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፤ ነፍሱንም ቢያጣ፤ ለሰው ምን ይረባዋል? ሰውስ ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር?» (ማቴ. ፲፮፥፳፮)፡፡
ሰላም ፍቅር ማጣት
የባዶነት ስሜት
ማንነትን መጥላት
በምሬት አንደበት
ክፉ ነገር ማውጣት
ርኩሰት በኃጢአት
ነፃነትን መሻት
ነፍስ ስታጣ ዕረፍት
የተጨነቀች ዕለት
«እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ፤» (ማቴ.፲፩፥፳፰) ይለናልና ፈጣሪያችንን አብዝተን እንለምነው፤ እንጸልይ እንጹም፤ ዕረፍት ያጣች ነፍሳችንን እናሳርፋት፡፡
መመለስ /ክፍል ሁለት/
የካቲት 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ዝምታቸው አስፈራኝ፡፡ “እባክዎ አባቴ ይርዱኝ” አልኩ የሰፈነውን ጸጥታ ሰብሬ፡፡
ዐይኖቻቸውን ከመስቀላቸው ላይ ሳይነቅሉ ‹‹ልጄ ነገ ከእኔ ስላለመኮብለልህ ምን ማረጋገጫ አለኝ?” ስጋታቸውን ገለጹ፡፡
“አመጣጤ የመጨረሻዬ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ውስጤ ተሰብሯል፡፡ ታከተኝ አባቴ!” የተቋረጠው የዕንባ ጎተራዬን ነካካሁት፡፡ ይፈልቅ ጀመር፡፡
ለመወሰን ተቸግረው በትካዜ ከያዙት የእጅ መስቀላቸው ጋር የሚሟገቱ ይመስል እያገላበጡት ዝምታን መረጡ፡፡
እኔ ደግሞ ውሳኔያቸው ናፈቀኝ፡፡ መልስ እሰኪሰጡኝ ድረስ እኔም በለቅሶና በዝምታ አገዝኳቸው፡፡
“አንድ ነገር ታደርጋለህ፡፡” ቀና ብለው እንኳን አላዩኝም፡፡ ዐይኖቻቸውን መስቀላቸው ላይ ተክለዋል፡፡
“ከቃልዎ አልወጣም – የፈለጉትን ይዘዙኝ፡፡”
“በጥሞና እንድታደምጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዶግማዋንና ቀኖናዋን አገልጋዮች ካህናትም ሆንን ምዕመናን የመጠበቅ ግዴታ አለብን፡፡ አበ ነፍስን በሚመለከት ቤተክርስቲያናችን ስርዓት ሰርታለች፡፡ በዚህም መሰረት አንድ ምእመን በቅድሚያ ንስሐ ለመግባት ሲወስን በጾም ፤ በጸሎት ፤ በስግደትና በጎ ምግባራትን በመስራት ራሱን ማረቅ አለበት፡፡ ስለኃጢአቱ የሚጸጸት፤ ዳግም ያንን ኃጢአት እንደማይሰራ የቆረጠ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ንስሐ አባት ሲመርጥም በጸሎት በመታገዝ እግዚአብሔር መልካም አባት እንዲሰጠው መለመን አለበት፡፡ የንስሐ አባት ከያዘ በኋላ ሌላ ለመቀየር መነሳሳት አይቻልም፡፡ መቀየር ካለበትም በቂ ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ አበ ነፍሱ በሞት የተለዩ ከሆነ ፤ የሐይማኖት ህጸጽ ካለባቸው ፤ የአካባቢ ርቀት በየጊዜው እንዳይገኛኑ ከገደባቸው፤ የሥነ ምግባር ችግር ካለባቸው፤ እንዲሁም ሌሎች መግባባት የማያስችሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ አበ ነፍስ መቀየር ይቻላል፡፡ ለመቀየር ሲታሰብም ከአበ ነፍሱ ጋር ተነጋግሮና ተሰነባብቶ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ አበ ነፍስን መቀየር አይቻልም፡፡ አሁንም የተጓዝክበት መንገድ ትክክል ባለመሆኑ ሁሉንም አባቶች ይቅርታ ጠይቀህ፤ ቀኖና ተቀብለህ ስታጠናቅቅ ሊያሰናብቱህ ይገባል፡፡ በመካከላችሁ ያለውን አለመግባባት በመፍታት ከተግባባችሁ ግን ከአንዳቸው ጋር ትቀጥላለህ፡፡ አበ ነፍስ መቀያየር መፍትሔ አይሆንህም፡፡ ካልተሳካልህ ብቻ ነው አሰናብተውህ ወደ እኔ የምትመጣው፡፡” አሉኝ በተረጋጋና አነጋገር፡፡
በድንጋጤ ደነዘዝኩኝ፡፡ ፍጹም ያልጠበቅሁት ውሳኔ፡፡ “እንዴት እችላለሁ አባቴ?” አልኩኝ እየተርበተበትኩ፡፡
“በትክክል የቤተክርስቲያን ልጅ ነኝ ብለህ የምታምን ከሆነ ሥርአቷንም የመጠበቅ ግዴታ አለብህ፡፡” አሉኝ ኮስተር ብለው፡፡
አቋማቸው የሚወላውል አልነበረም፡፡ ትክክል እንደሆኑ ውስጤ አምኖበታል፡፡ ነገር ግን አሻፈረኝ ብዬ ከኮበለልኩባቸው አባቶች እግር ስር ወድቄ ይቅርታ መጠየቁ ተራራ የመውጣት ያህል ከብዶ ታየኝ፡፡
ጭንቅላቴን እያሻሹ “አይዞህ፡፡ ክርስትና የሚኖሩት እንጂ በአቋራጭ ለክብር የሚበቁበት መድረክ አይደለም፡፡ በማስተዋል መጓዝ ይገባሃል፡፡” ብለው አቡነ ዘበሰማያት ደግመው፤ በእግዚአብሔር ይፍታህ ደምድመው ተሰናብተውኝ ከአጠገቤ ሔዱ፡፡
ተንበርክከኬ የቻልኩትን ያህል አነባሁ፡፡ ትኩስ የሚያቃጥል ዕንባ ፈሰሰኝ፡፡ መረጋጋት ተሳነኝ፡፡፡ለረጅም ደቂቃዎች እንደተንበረከክሁ ቆየሁ፡፡
ጉዞ ወደ መጀመሪያው አበ ነፍሴ . . . ፡፡
ለሦስት ቀናት ያህል ከራሴ ጋር ስሟገት ቆይቼ በሌሊት አዲስ አበባ ወደሚገኘው ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አመራሁ፡፡ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቼ የኪዳን ጸሎት እስከሚጀመር ድረስ የግል ጸሎቴን አደረስኩ፡፡
የኪዳን ጸሎት እየደረሰ ሳለ እግረ መንገዴን የንስሐ አባቴን ፍለጋ ዐይኖቼን አንከራተትኩ፡፡ አልነበሩም፡፡ ከኪዳን ጸሎት በኋላ በየመጠለያው ፈለግኋቸው፡፡ የሉም፡፡
ወደ አንድ አባት ጠጋ ብዬ “ይቅርታ አባቴ መምሬ ወልደ ገብርኤልን ፈልጌ ነበር፡፡ የት አገኛቸው ይሆን?” አልኳቸው፡፡
በደንብ ካስተዋሉኝ በኋላ “መምሬ ወልደ ገብርኤል የሚባሉ እዚህ የሉም፡፡” አሉኝ፡:
“ተቀይረው ይሆን?” ጥርጣሬዬን ገለጽኩላቸው፡፡
“አልሰማህም እንዴ? እሳቸው እኮ ካረፉ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡”
አፌ ተሳሰረ፡፡ ድንጋጤ ወረረኝ እኔ የገደልኳቸው ያህል ተሰማኝ፡፡
“እሰከ ዛሬ እንዴት አላወቅህም?”
“አላወቅሁም አባቴ፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡” አልኩኝ ባደረግሁት አሳፋሪ ተግባር በመጸጸት፡፡ ራሴን እየወቀስኩ ካህኑን አመስግኜ ከግቢው ወጣሁ፡፡
ሁለተኛውን አበ ነፍሴን ለማግኘት ጥረት አደረግሁ፡፡ የንስሐ ልጆቻቸውን ለሚቀርቧቸውና ለሚያምኗቸው አባቶች ሰጥተው ወደ አውሮፓ መጓዛቸውን አረጋገጥኩ፡፡
ሦስተኛው አበ ነፍሴን ፍለጋ ቀጠልኩ . . .፡፡
ተሳካልኝ፡፡ የፈጸምኩትን ድርጊት በመጸጸት ነገርኳቸው፡፡ በተፈጥሮ ቁጡና በክርስትና ሕይወት ወለም ዘለም ማለት አያስፈልግም የሚል አቋም ስላላቸው ለመጥፋቴ ምክንያት እንደሆኑኝ ከመንገር ወደ ኋላ አላልኩም፡፡
“ልጄ ፈተና ሆንኩብህ? በመጥፋትህ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ተመልሰህ በመምጣትህ ደስ ብሎኛል፡፡” በማለት በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ ቀጥለውም ”መቆጣቴ ለክፋት ሳይሆን ክርስትና በዋዛ ፈዛዛ የሚኖሩት ባለመሆኑና መንፈሳዊ ጥንካሬን የሚጠይቅ፤ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚያስፈልግ ስለማምን ልጆቼን ለማጠንከር ነው፡፡ ክርስትና እንደ ወርቅ ተፈትኖ ነጥሮ መውጣትን ይፈልጋልና፡፡ ስለዚህ ልጄ አትቀየመኝ፡፡” በማለት እንድረጋጋ መንገዶችን አመቻቹልኝ፡፡ ቁጡነታቸው ስለሚያስፈራ እንዴት አድርጌ እፊታቸው እቆማለሁ? እያልኩ ነበር ሳስብ የነበረው፡፡ ራሳቸውን መውቀስ ሲጀምሩ ተረጋገሁ፡፡
አጠገባቸው አስቀምጠው ጭንቅላቴን እያሻሹ “አየህ ልጄ! – የክርስትና ጉዞ እስከ ቀራንዮ ድረስ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ጉዞው ከባድና እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ ተሸክመኸው የምትጓዘው መስቀሉን ነው፡፡ መውደቅ ፤መነሳት፤ መገረፍ ፤በችንካር መቸንከር ሕይወትንም ለእግዚአብሔር አሳልፎ እሰከ መስጠት ይደርሳል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳምንና የእኛን ልጆቹን በደል ይሽር ዘንድ፤ ከዲያቢሎስ ቁራኝነት ነጻ ያወጣን ዘንድ አምላክ ሲሆን እንደኛ ስጋን ለበሰ፡፡ በቀራንዮ መስቀል ላይ የነገሠውን አምላካችንን አስብ፡፡ የጀመርከውን የቀራንዮ ጉዞ እንደ ሎጥ ሚስት ወይም እንደ ዴማስ ያለፈውን የኃጢአት ጉዞህን ለመመልከት ወደ ኋላ የምትዞርበት ሳይሆን ፊት ለፊት የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት ፤ በመስቀሉ ስር የተገኙትን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምንና ቅዱስ ዮሐንስን ትመለከት ዘንድ ነው፡፡ በርታ፡፡” አሉኝ በፍቅር እየተመለከቱኝ፡፡
የሚናገሩት ቃለ እግዚአብሔር ማር ማር እስኪለኝ ጣፈጠኝ፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ምን ይላል መሰለህ? “የቀድሞውንስ ያለ ማወቅ ዘመን እግዚአብሔር አሳልፎታል፡፡ ዛሬ ግን በመላው ዓለም ንስሐ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዝዟል፡፡” በማለት በሐዋ. ሥራ. ምዕ.17፡30 ተጽፏል፡፡ ያለፈውን የኃጢአት ሥራዎችህን ተጠይፈህና ጥለህ በእግዚአብሔር እቅፍ ስር ትሆን ዘንድ መምረጥህ መልካም አደረግህ፡፡ ወደፊት ደግሞ ብዙ ይጠብቅሃል፡፡” አሉኝ በጥልቅ ትኩረት እየተመለከቱኝ፡፡
“አንድን የኃጢአት ግብር ከመፈጸሜ በፊት ላለመስራት እታገላለሁ፡፡ ነገር ግን ሰርቼው እገኛለሁ፡፡ ለራሴ ውሳኔዎች ውስጤን ማሰልጠን ፤ ማስጨከን ተሳነኝ፡፡” አልኳቸው በተሰበረ ልብ፡፡
“እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል አያስቀርም፤ ይቀራል ብለው የሚናገሩ አሉና፤ ነገር ግን ስለ እነርሱ ይታገሳል፡፡ ማንም ይጠፋ ዘንድ አይሻምና ንስሐ ይገቡ ዘንድ ለሰው ሁሉ ዕድሜን ይሰጣል እንጂ፡፡ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ጴጥ.3፡9 ላይ ገልጾታል፡፡ እግዚአብሔር ይመጣል በፊቱም እንቆማለን፡፡ መልሳችን ምን ይሆን? ማሰብ ያለብን ይህንን ነው፡፡ ንስሐ ለመግባት መወሰንህ መንፈሳዊ ጀግንነትህን ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ያለውን አያስቀርምና፡፡ በኋላ ከመጠየቅ ለመዳን ዛሬ ራስን ከኃጢአት በማራቅ ንስሐ መግባት ትክክለኛ መፍትሔ ነው፡፡” በማለት ሕሊናን ሰርስረው የሚገቡ የተመረጡ ቃላት በልቦናዬ ውስጥ አፈሰሱት፡፡ መልስ አልነበረኝም፡፡ ዝምታን መረጥኩ፡፡
“አሁን ውሳኔህን አሳውቀኝ፡፡ እግዚአብሔር ወደ እኔ መልሶ ያመጣህ ምክንያት ቢኖረው ነው፡፡ ይህንን ሃላፊነቴን እወጣ ዘንድ ግድ ይለኛል፡፡ አባት እሆንሀለሁ አንተም ልጄ ትሆናለህ” አሉኝ፡፡
“አመጣጤ እንዲያሰናብቱኝ ለመማጸን ነበር፡፡ ምን ያህል ስህተት ውስጥ እንደነበርኩ ተረድቻለሁ፡፡ ለዚህም የረዱኝን አባት ማመስገን አለብኝ፡፡ እግዚአብሔር ሰብሮኛል፡፡ ይጠግነኛልም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን እናፍቃለሁ፡፡ ይህ ባይሆን ተመልሼ እርስዎ ዘንድ አልመጣም ነበር፡፡ እንደወጣሁም እቀር ነበር፡፡ የመጣሁት ወስኜ ነው፡፡ እግዚአብሔር እርስዎን ሰጥቶኛልና እዳ እንዳልሆንብዎ እርዱኝ፡፡” አልኩ፡፡
“ቆም ብለህ ራስህን እንድታይ ያስፈልጋል፡፡ የሰራኸውን ኃጢአት እግዚአብሔርን በመፍራት ፤ በተሰበረ መንፈስ ውስጥ ሆነህ ልትናዘዝ ይገባሃል፡፡” አሉኝ ለመስማት ራሳቸውን እያዘጋጁ፡፡
ውስጤ የታጨቁትን የኃጢአት ኮተቶች ሁሉ አራገፍኩ፡፡
“ወደ ልቦናህ ተመልሰህ ከውስጥህ ያለውን ሁሉ አውጥተህ ዳግም ላትመለስበት ወስነሃልና የሚገባህን ቀኖና እሰጥሃለሁ፡፡ የሚሰጥህን ቀኖና በአግባበቡ በማስተዋልና በፍቅር ልትፈጽመው ይገባል፡፡ በጾም ፤ በጸሎት ፤በስግደትና በትሩፋት ከበረታህ የሚፈታተንህን ክፉ መንፈስ ማሸነፍ ትችላለህ፡፡” በማለት አባታዊ ምክራቸውን ከለገሱኝ በኋላ አስፈላጊ ነው ያሉትን ቀኖና ሰጡኝ፡፡ በአቡነ ዘበሰማያትና በእግዚአብሔር ይፍታህ ተደመደመ፡፡
“በየሳምንቱ ቅዳሜ ማታ እዚሁ እየተገናኘን በመንፈሳዊ ሕይወትህ ዙሪያ የሚገጥምህ ችግር ካለ ፤ እንዲሁም አስፈላጊ ያልካቸውን ጉዳዮች ልታማክረኝ ትችላለህ፡፡” በማለት ካበረታቱኝ በኋላ አሰናበቱኝ፡፡
ከንስሐ አባቴ እንደተለያየሁ ያመራሁት ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ባለውለታዬ የሆኑትን አባት ለማመስገን፡፡
ክርስቲያናዊ ሕይወቴን ለማስተካከልና ራሴን ለመግዛት እግዚአብሔርን እየለመንኩ፤ የንስሐ አባቴ ምክርና ድጋፍ ሳይለየኝ በተረጋጋ መንፈስ ለመኖር ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ ከምንም ነገር በላይ መንፈሳዊ ሕይወቴን ለሚያንጹ ተግባሮች ቅድሚያ ሰጠሁ፡፡ የአቅሜን ያህል በጾም፤ በስግደትና በጸሎት እየበረታሁ ነው፡፡ የንስሐ አባቴ በጥሩ ሁኔታ ቃለ እግዚአብሔር እየመገቡኝ ፤ ስደክም እያበረቱኝ መፈርጠጤን ትቼ ለሌሎች መካሪ ሆኛለሁ፡፡ ራስን መግዛት ተማርኩኝ፡፡ ያለፈው በኃጢአት የኖርኩበት ዘመን ዳግም ላይመለስ መንፈሳዊ ጋሻና ጦሬን አጥብቄ ይዣለሁ፡፡ ነገን ደግሞ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ እኖራለሁ. . . ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መመለስ /ክፍል አንድ/
የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.
ከእንዳለ ደምስሰ
ከቀኑ አሥራ ሁለት ስዓት ፡፡
ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስደርስ ልቦናዬን እየተፈታተነኝ ያለውን የዐሳብ ድሪቶ አውልቄ ለመጣል ትንፋሼን ሰብስቤ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡
ከተሳለምኩ በኋላ ከዋናው በር በስተግራ በኩል ካለው ዋርካ ሥር አመራሁ፡፡ የሰርክ ስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡ አካባቢዬን ቃኘሁ፡፡ ምእመናን አመቺ ነው ባሉት ቦታ ላይ ተቀምጠው የዕለቱን ትምህርት ይከታተላሉ፡፡ መምህሩ በሉቃስ ወንጌል ምዕ.15፥7 -10 ያለውን ኀይለ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ነው፡፡
“. . . ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢአተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል . . . ፡፡” ሰባኪው ስብከታቸውን ቀጥለዋል . . . .፡፡
የሸሸግሁት ቁስል ስለተነካብኝ ውስጤ በፍርሃት ተወረረ፡፡
— “ማን ነገራቸው? ለዘመናት ስሸሸው የኖርኩትን የንስሐ ትምህርት ዛሬም ተከትሎኝ መጣ?” አጉረመረምኩ፡፡
ቀስ በቀስ ስብከቱን እያደመጥኩ ራሴን በመውቀስ ጸጸት ያንገበግበኝ ጀመር፡፡– “ለምን ስሜታዊነት ያጠቃኛል? ለምን ወደ ትክክለኛው የክርስትና ሕይወቴ አልመለስም? ዛሬ የመጨረሻዬ ይሆናል፡፡” ውሳኔዬ ቢያስደስተኝም መሸርሸሩ አይቀርም በሚል ደግሞ ሰጋሁ፡፡ ስንት ጊዜ ወስኜ ተመልሼ ታጥቦ ጭቃ ሆኛለሁ?! አንድ መቶ ጊዜ – አንድ ሺህ ጊዜ – ከዚህም በላይ . . . ፡፡ ቃለ እግዚአብሔር በሰማሁ ቁጥር ልቤ ይሰበራል፡፡ እጸጸታለሁ፡፡ ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር እንደወጣሁ በልቦናዬ የተተከለው ቃለ እግዚአብሔር ንፋስ እንደ ጎበኘው ገለባ ይበተናል፡፡ ውሳኔዬም ይሻራል፤ ልቦናዬ ይደነድናል፡፡ ወደ ቀድሞ እሪያነቴ እመለሳለሁ፡፡ ሁልጊዜ — “የተጠናወተኝ አጋንንት ነው እንዲህ የሚሰራኝ!” እያልኩ አሳብባለሁ፡፡
ሰባኪው ቀጥለዋል፡፡ “. . . አሁንም ከክፋትህ ተመለስና ንስሐ ግባ፡፡ የልቦናህንም ዐሳብ ይተውልህ እንደሆነ እግዚአብሔርን ለምን ፡፡ /የሐዋ. ሥራ ምዕ.8፥22/ ” የበለጠ ተሸበርኩ፡፡
አመጣጤ መምህረ ንሰሐዬ ይሆኑ ዘንድ ካሰብኳቸውና ቀጠሮ ከሰጡኝ አባት ጋር ለመገናኘት ነበር፡፡ ለመምህረ ንስሐነት በራሴ ፍላጎት ያጨኋቸው አባትም ዘገዩ፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት ሳገኛቸው አብረን ተቀምጠን የተነጋገርንበት ቦታ ላይ ሆኜ እየጠበቅኋቸው ነው፡፡ ያገኘሁዋቸው ከሰንበት ትምህርት ቤቱ የቅርብ ጓደኛዬ ነው፡፡ ቀድሞ ከነበሩኝ የንስሐ አባቴ ጋር ስላልተግባባን፤ በተለይም ቁጣቸውን መቋቋም ስላቃተኝ ለመቀየር ወስኜ ነው የመጣሁት፡፡
— “ይገርማል! ስንተኛዬ ናቸው ማለት ነው? 1 – 2 – 3 . . . 4ኛ!” በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሦስት መምህረ ንስሐ ይዤ ፈርጥጫለሁ፡፡ — “ምን አይነት አባት ይሆኑ? የማይቆጡ፤ የማያደናብሩ፤ ጥቂት ብቻ ቀኖና የሚሰጡ ከሆነ ነው አብሬ የምቆየው፡፡” እንደተለመደው ለማፈግፈግ ምክንያት አዘጋጀሁ፡፡
መልሼ ደግሞ — “ምን አይነት ሰው ነኝ?! ዳግም ወደ ኀጢአት ላልመለስ ከራሴ ጋር እየተነጋገርኩ መልሼ እዚሁ አፈርሰዋለሁ እንዴ?! መጨከን አለብኝ፡፡ የሆነውን ሁሉ እናዘዛለሁ፡፡” ሙግቴ ቀጥሏል . . . ፡፡
ሰባኪው “. . . እንግዲህ ኀጢአታችሁ ይሠረይላችሁ ዘንድ ንስሐ ግቡ፤ ተመለሱም፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የይቅርታ ዘመን ይመጣል፡፡” የሐዋ.ሥራ ምዕ.3፥19 እያሉ በመስበክ ላይ ናቸው፡፡
— “ይቺ ጥይት ለእኔ የተተኮሰች ናት!” አልኩ በልቤ ሰባኪው ርዕስ እንዲቀይሩ እየተመኘሁ ፡፡ — “እውነት ግን የይቅርታ ዘመን የሚመጣልኝ ከሆነ ለምን ከልቤ ንስሐ አልገባም? እስከ መቼ በኀጢአት ጭቃ እየተለወስኩ እዘልቀዋለሁ? መርሐ ግብሩ ይጠናቀቅ እንጂ ዝክዝክ አድርጌ ነው የምነግራቸው፡፡” ቅዱስ ጊዮርጊስን በተሰበረ ልብ ኀጢአቴን እናዘዝ ዘንድ እንዲረዳኝ ተማጸንኩት፡፡
ሰባኪው በቀላሉ የሚለቁኝ አይመስልም፡፡ “. . . ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመልጥ ታስባለህን? ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሱ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርንስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሐ እንዲመልስ አታውቅምን? ነገር ግን ልቡናህን እንደማጽናትህ ንስሐም እንዳለመግባትህ መጠን የእግዚአብሔርን እውነተኛ ፍርዱ በሚገለጥበት ቀን ቁጣን ለራስህ ታዘጋጃለህ፡፡” ሮሜ. 2፡3-5 እያሉ በሚሰብኩት ስብከት ልቡናዬን አሸበሩት፡፡
— “የአሁኑ ይባስ! ዛሬ ስለ እኔ ተነግሯቸው ነው የመጡት፡፡ ወረዱብኝ እኮ!” እላለሁ፡፡ መልሼ ደግሞ — “እውነታቸውን ነው ይበሉኝ!!” ትምህርትም ሆነ እውቀት ሳያንሰኝ ከልቤ ልመለስ አለመቻሌ አሳፈረኝ፡፡
በሰ/ት/ቤት ውስጥ እንደ ማደጌና ለአገልግሎት እንደ መትጋቴ ለንስሐ ጀርባ መስጠቴ ምን የሚሉት ክርስትና ነው? ሌሎች በአርአያነት የሚመለከቱኝ፤ ‹ክርስትናን ከኖሩት አይቀር ልክ እንደ እሱ ነው!› የተባለልኝ – ነገር ግን በኃጢአት ጥቀርሻ የተሞላሁ አሳፋሪ ሰው ነኝ፡፡ ነጠላ መስቀለኛ ለብሶ፤ መድረኩን ተቆጣጥሮ መርሐ ግብር መምራት፤ ለመስበክ መንጠራራት ፤ለመዘመር መጣደፍ ፤. . . ምኑ ቀረኝ?
ጊዜው የጉርምስና ወቅት በመሆኑ ለኀጢአት ስራዎችም የበረታሁበት ወቅት ነው ፡፡ ሰ/ት/ቤት ውስጥ የማያቸው እኅቶቼን ሁሉ የእኔ እንዲሆኑ እመኛለሁ፡፡ ምኞት ኀጢአት መሆኑን ሳስብ ደግሞ መለስ እላለሁ፡፡ ግን ብዙም ሳልቆይ እቀጥላለሁ፡፡ በሥራ ቦታዬ ደግሞ ማታለልን ፤ በጉልበት የሌሎችን ላብ መቀማትን ፤ ማጭበርበር የዘወትር ተግባሬ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ስሔድ ደግሞ ሁሉን እርግፍ አድርጌ ለበጎ ስራ እተጋለሁ፡፡ — “መርዛማ ዛፍ መልካም ፍሬን ማፍራት ትችላለችን?” ራሴን እየሸነገልኩ ለጽድቅም ሆነ ለኩነኔ በረታሁ፡፡
አንድ ቀን በሰ/ት/ቤታችን ውስጥ በሥነ ምግባሩ የታወቀ፤ ለሌሎች አርአያ የሆነ እንደ እኔ አጭበርባሪ ነው ብዬ የማልገምተውና የማከብርው ጓደኛዬ የንስሐ አባት መያዙን ነገረኝ፡፡ እኔስ ከማን አንሳለሁ? ይመቹኛል የምላቸውን አባት መርጬ ያዝኩ፡፡ ተደሰትኩ፡፡ ቀስ በቀስ በሚኖረን ግንኙነት ኀጢአቴን ሳልደብቅ መናዘዝ ጀመርኩ፡፡ ዛሬ ቀኖና ተቀብዬ፤ ጸሎት አድርሰውልኝ በእግዚአብሔር ይፍታህ የተደመደመ ኃጢአቴን ገና ከአባቴ እንደተለየሁ እደግመዋለሁ፡፡ እንደውም አብልጬ እሰራለሁ፡፡ እናዘዛለሁ፡፡ ተመልሼ እጨቀያለሁ፡፡ የንስሐ አባቴን ትዕግስት ተፈታተንኩ፡፡ እሳቸውም አምርረው ይገሥጹኛል፡፡ ድርጊቴ ተደጋገመ፡፡ ሁኔታቸው ስላላማረኝ ሳልሰናበታቸው ጠፋሁ፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ የንስሐ አባት ያዝኩ፡፡
እኚህ ደግሞ በጣም እርጋታን የተላበሱ ሲሆኑ ሲመክሩኝ ደግሞ የሌሎችን ታሪክ በምሳሌነት በማንሳት ያስተምሩኛል፡፡ ቀኖና ሲሰጡኝም በትንሹ ነው፡፡ የሰራሁት ኀጢአትና የሰጡኝን ቀኖና ሳመዛዝን ኀጢአቴ ይገዝፍብኛል፡፡ የሚሸነግሉኝ ይመስለኛል፡፡
— “ጸሎት አታቋርጥ፤ መጻሕፍትን መድገም ትደርስበታለህ፤ በቀን ለሶስት ጊዜያት አንድ አንድ አቡነ ዘበሰማያትን ድገም፡፡ ለሕፃን ልጅ ወተት እንጂ ጥሬ አይሰጡትም፡፡ ስትጠነክር ደግሞ ከፍ እናደርገዋለን፡፡” ይሉኛል፡፡
የናቁኝ መሰለኝ፡፡ — “እንኳን አባታችን ሆይ እኔ ጀግናው የዘወትር ጸሎት ፤ ውዳሴ ማርያም፤ አንቀጸ ብርሃን ፤ የሰኔ ጎልጎታ፤ መዝሙረ ዳዊት፤ ሰይፈ መለኮት፤ሰይፈ ሥላሴ ጠዋትና ማታ መጸለዬን አያውቁም እንዴ?! እንዴት በአባታችን ሆይ ይገምቱኛል?” አኮረፍኩ፡፡ ጠፋሁ፡፡
ደግሞ ሌላ ፍለጋ፡፡
ሦስተኛው የንስሐ አባቴ በትንሹም በትልቁም ቁጣ ይቀናቸዋል፡፡ እንደመቆጣታቸው ሁሉ አረጋግተው ሲመክሩ ደግሞ ይመቻሉ፡፡ ነገር ግን ቁጣቸውን መቋቋም ስለተሳነኝ ከእሳቸውም ኮበለልኩ፡፡
ዛሬ ውሳኔዬን ማክበር አለብኝ፡፡ ወደ ልቦናዬ መመለስ፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 15 ላይ እንደተጠቀሰው የጠፋው ልጅ፡፡ ወደ አባቴ ቤት በቁርጠኝነት መመለስ፡፡ ልጅ ተብዬ ሳይሆን ከባሪያዎች እንደ አንዱ እቆጠር ዘንድ፡፡
ከምሽቱ 12፡30 ሆኗል፡፡
ሰባኪው አሰቀድሞ ይሰጡት የነበረውን የንስሐ ትምህርት ቀጥለዋል፡፡ “. . . በተመረጠችው ቀን ሰማሁህ፤ በማዳንም ቀን ረዳሁህ፤ እነሆ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት፡፡” 2ኛ ቆሮ. ምዕ› 6፡2 እያሉ ቃለ እግዚአብሔርን በምዕመናን ልቦና ላይ ይዘራሉ፡፡
— “እውነትም ለእኔ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት፡፡ አምላኬ ሆይ ኃይልና ብርታትን ስጠኝ፡፡ ወደ ትክክለኛው አእምሮዬ እመለስ ዘንድ፤ በኀጢአት የኖርኩበት ያለፈው ዘመን ይበቃ ዘንድ እርዳኝ!!” አልኩ የተፍረከረከውን ልቦናዬ ያጸናልኝ ዘንድ እየተመኘሁ፡፡
— “አሁን ምንድነው ማድረግ ያለብኝ? እ – በመጀመሪያ ራሴን ማረጋጋት፡፡ ከዚያም እሰከ ዛሬ የፈጸምኩትን የኃጢአት ኮተት ማሰብ ፤ በመጨረሻም አንኳር የሆኑትን መናዘዝ፡፡” አልኩ ህሊናዬን ለመሰብሰብ እየጣርኩኝ፡፡
— “ግን እኮ የኀጢአት ትንሽ እንደሌለው ተምሬያለሁ፡፡ስለዚህ ሸክሜን ሁሉ ለመምህረ ንስሐዬ መናዘዝ አለብኝ፡፡” ውሳኔ ላይ ደረስኩ፡፡
ኀጢአት ናቸው ብዬ በራሴ አእምሮ የመዘንኳቸውን አስቦ መጨረስ አቃተኝ፡፡ በድርጊቴ ተገርሜ — “በቃ የኀጢአት ጎተራ ሆኛለሁ ማለት ነው? መቼ ይሆን ሰንኮፉ የሚነቀለው? እባክህ አምላኬ በቃህ በለኝ!” ኃጢአቴን ማሰብ አደከመኝ፡፡
የዕለቱ የሰርክ ጉባኤ እንደተጠናቀቀ አበ ንስሐ ይሆኑኝ ዘንድ ቀጠሮ ያስያዝኳቸው አባት በመጠባበቅ አይኖቼ ተንከራተቱ፡፡
— “ረስተውኝ ይሆን እንዴ? – እውነታቸውን ነው – እኔ መረሳት ያለብኝ ሰው ነኝ፡፡ ለምንም – ለማንም የማልጠቅም ከንቱ ሆኛለሁ፡፡ ኀጢአት ያጎበጠኝ ምናምንቴ ነኝ!! የኀጢአት ሸክሜን የማራግፍበት ፍለጋ በመባዘን እሰከ መቼ እዘልቀዋለሁ? እውነተኛ ንስሐ መግባት ተስኖኝ እስከ መቼ እቅበዘበዛለሁ?” የዕንባ ጎተራዬ ተከፈተ፡፡ ከዓይኔ ሳይሆን ከልቤ ይመነጫል፡፡ መጨረሻዬ ናፈቀኝ፡፡
“እንደምን አመሸህ ልጄ?” አሉኝ የቀጠርኳቸው አባት ጭንቅላቴን በመስቀላቸው እየዳበሱኝ፡፡
ዕንባዬ ያለማቋረጥ እየወረደ ቀና ብዬ ተመለከትኳቸው፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መስቀል ተሳለምኩኝ፡፡ በሃምሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ ገብስማ ሪዛቸው ግርማ ሞገስ አላብሷቸዋል፡፡
“ምነው አለቀስክ?” አሉኝ አጠገቤ ካለው ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ እየተቀመጡ፡፡
ሳግ እየተናነቀኝ “ሸ- ሸ – ክሜ ከ- ከ-ብ-ብዶ-ብብ-ኝ ነው አባቴ! ም- ምንም የማ- ማልጠቅም ሆኛለሁ!!” አልኳቸው ሆድ ብሶኝ፡፡
“መጸጸት መልካም ነው፡፡ ጸጸት ጥንካሬን ይወልዳል ልጄ! አይዞህ፡፡” አሉኝ በጥልቀት እየተመለከቱኝ፡፡
— “እግዚአብሔር ረድቶኝ የመጨረሻዬ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡” አባባላቸውን ተመኘሁት፡፡
— ‹‹አምላኬ ሆይ ብርታትን ስጠኝ፡፡ ውስጤ የታመቀውን የኃጢአት ጥቀርሻ ይታጠብ ዘንድ፤ የሆነውን ሁሉ በተሰበረ መንፈስ እናዘዝ ዘንደ እርዳኝ፡፡›› አልኩኝ ለራሴ፡፡ ቀና ብዬ አያቸው ዘንድ ብርታት አጣሁ፡፡
“ስመ ክርስትናህ ወልደ ሚካኤል ነው ያልከኝ?”
“አዎ አባቴ!”
“ሰሞኑን ስንገናኝ ከንስሐ ልጆቼ ጋር ጉዳይ ይዘን ስለነበር ጉዳይህን አልነገርከኝም፡፡ ለምን ይሆን የፈለግኸኝ?”
“አባቴ በቀጠሯችን መሠረት መጥቻለሁ፡፡ በኀጢአት ምክንያት የተቅበዘበዝኩኝ፤ ኀጢአቴ ያሳደደኝ፤ ለዓለም እጄን የሰጠሁ ምስኪን ነኝ፡፡ ህሊናዬ ሰላም አጥቷል፡፡ ያሳርፉኝ ዘንድ አባትነትዎን ሽቼ ነው የመጣሁት፡፡” አልኳቸው በተሰበረ ልሳን፡፡
ለጥቂት ሰከንዶች ከራሳቸው ጋር የሚመክሩ በሚመስል ስሜት ቆይተው “ልጄ የንስሐ ልጆች በብዛት አሉኝ፡፡ ሁሉንም ለማዳረስ አልቻልኩም እኔም በፈተና ውስጥ ነኝ፡፡ አንተ ደግሞ ተጨምረህ ባለ እዳ ሆኜ እንዳልቀር ሰጋሁ፡፡ ይቅርታ አድርግልኝና ሌላ አባት ብትፈልግ ይሻላል፡፡” አሉኝ ትህትና በተላበሰ አነጋገር፡፡
“እግዚአብሔር እርስዎን አገናኝቶኛልና ወደ ሌላ ወዴትም አልሔድም፡፡ ያለፈው ይበቃኛል፡፡” አነጋገሬ ውሳኔዬን እንደማልቀይር ይገልጽ ነበር፡፡
“ያመረርክ ትመስላለህ፡፡” አሉኝ ውሳኔዬ አስገርሟቸው፡፡
“አባቴ ታከተኝ፡፡ ቆሜ ስሔድ ሰው እመስላለሁ ፤ ነገር ግን ኀጢአት በባርነት የገዛኝ ርኩስ ነኝ፡፡ የመጣሁት ከባርነት ይታደጉኝ ዘንድ ነው፡፡ እባክዎ አባቴ እሺ ይበሉኝ!” ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡
ለቅሶዬን እስክገታና አስክረጋጋ ድረስ ጠብቀው “እንዲህ በተሰበረ መንፈስ ውሰጥ ሆነህ ጥዬህ ብሄድ ሸክሙ ለራሴው ነው፡፡ አንድ ጊዜ መጥተሃልና አላሰናክልህም፡፡” አሉኝ በፍቅር እያስተዋሉኝ፡፡
“እግዚአብሔር ይስጥልኝ አባቴ!” እግራቸው ላይ ተደፋሁ፡፡
“ተው – ተው አይገባም ልጄ – ቀና በል፡፡” ብለው ከተደፋሁበት በሁለት እጃቸው አነሱኝ፡፡
“ከዚህ በፊት አበ ነፍስ ነበረህ?” አሉኝ አረጋግተው ካስቀመጡኝ በኋላ፡፡
በአዎንታ ጭንቅላቴን ከፍና ዝቅ በማድረግ ገለጽኩላቸው፡፡
“በምን ምክንያት ተለያያችሁ?”
ራሴን ለማረጋገት እየሞከርኩ ዕንባዬን ጠርጌ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡
“አባቴ ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ ከአንድም ሦስት ጊዜ የንስሐ አባት ቀያይሬያለሁ፡፡”
“ለምን?” በመገረም ነበር የጠየቁኝ፡፡
“ለእኔም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ከአንዱ እየፈረረጠጥኩ ወደ አንዱ እየሔድኩ ነፍሴን አሳሯን አበላኋት፡፡”
“ከሦስቱም እየተሰናበትክ ነው እዚህ የደርስከው?” የበለጠ ለመስማት በመጓጓት ጠየቁኝ፡፡
“ከአንዳቸውም ጋር በስንብት አልተለያየሁም፡፡ በራሴ ፈቃድ ኮበለልኩ፡፡”
ለውሳኔ የተቸገሩ በሚመስል ስሜት የእጅ መስቀላቸውን እያገላበጡ ተከዙ፡፡ በመካካላችን ጸጥታ ሰፈነ. . . ፡፡
ይቀጥላል
ቅዱስ ጳውሎስ
በልጅነት ሊገላገል በሐሳብ ያረገዘኝ፤
በማኅፀን ሰፋድሉ በትምህርቱ እኔን ስሎ፤
በመዶሻው እኔን ጠርቦ አስተካክሎ፤
እጄን ይዘህ አለማምደህ እንዲያ ስድህ፤
ቃለ ነገር ቃለ ምሥጢር እየጋትህ፤
ጠንካራውን ጥሬ ቃሉን አስቆርጥመህ፤
አንተ አብይ ባሕር የትምህርት ውቅያኖስ፤
ምርጥ ዕቃ ማዕዘን ዕብነ አድማስ፤
በእንቁላል ቅርፊት ቀድቼ የረካሁኝ ከአንደበትህ፤
ርዕሰ እውቀት አንተ አፈ ዝናም በትምህርትህ፡፡
አሕዛበ-ምድር ማንነቴን በጠብታህ ጎበኘሃት፤
የነፍሴን እርሻ አጥግበህ በልምላሜ ከደንካት፡፡
ሕሊናዬን በተመስጦ መንኮርኩር ስታከንፋት፤
ከታችኛው ከእንጡረጦስ ከበርባኖስ ስታጠልቃት፤
ዖፈ ጣጡስ መጥቀህ በረህ የነገርኸኝ፤
እንደ ሙሴ ከእግረ ታቦር ያላቆምኸኝ፤
አለማወቅ ጥቁር ካባ፤ የጨለማን መጋረጃን ያራቅህልኝ፤
ኢትትሃየድ እያለ ወራሴን ስታለምደኝ፤
ምሥጢሩን ስትቀዳ ዘቦቱን ስትነግረኝ፤
የሰብዕና ዘበኛዬ እኔን በትምህርቱ ንቅሳት ሲነትበኝ፤
ያኔ ነበር የነቀሰኝ በልቡናዬ ሕያው ቃሉን የከተበኝ፤
በጉልጓሎ በእርሻው ቦታ የጠመደኝ፤
እያረሰ ጅራፍ ቃሉን ጆሮዬ ላይ ሲያጮህብኝ፤
ከሃያው ክንድ ከመቅደሱ ከሚፈልቀው፤
ከዙፋኑ ከቃል ሥግው ከሚፈሰው፤
እንደ መስኖ ሊቀላቀል ከሚወርደው፤
ከእኔ ሕይወት ከሸለቆ ከአዘቅቱ ሲንዶሎዶል፤
የመብል ዛፍ ፍሬ በኩር ሲያበቅል፤
ያኔ ነበር ስሜ ሽቶ ከጌታ ስም ሲቀላቀል፤
ሃይማኖት የፍቅር እሳት ሲንቀለቀል፤
ተቆጠርኩኝ ግብር ገባሁ ከቤተ ወንጌል፡፡
አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብር ምን ነበር ምሥጢሩ
የክርስትና ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ
መቃብሩን ክፈቱና አበው ይመስክሩ፡፡
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ
ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ፡፡
ሐዋርያት ቁልቁል የተዘቀዘቁት
ሰማዕታት በእሳት የተለበለቡት
ቅዱሳን በገዳም ደርቀው የተገኙት
ምሥጢሩ ምን ነበር? አበው ይናገሩት፡፡
የቅዱሳንን ዐፅም ለምን እንዳልበላ፡፡
ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር
እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡
ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት?
ወይስ ሀብት ንብረት የተሟላ ቤት?
ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት?
እናንተ ገዳማት ምሥጢሩን አውሩት፡፡
ምግባር ሃይማኖቱ በእጅጉ የቀና፡፡
እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት
ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡
የጊዮርጊስ ወገን የት ነው የማገኘው?
በመሀል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው?
ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው?
የሃይማኖት ጀግና የትነው የማገኘው?
ልግባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት
ማኅበረ ሥላሴ ከቅዱሳን ቤት?
አክሱም ግሸን ማርያም ከቃል ኪዳን ቦታ
ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ?
ፈሪሐ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ
ቤተ ክርስቲያንን ያልተደፋፈረ፡፡
ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች፡፡
የወገን መመኪያ የከሀዲ መቅሰፍት
ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሣ ቀስቅሱት፡፡
እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምሥጢሩ?
የክርስቲያን ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ?
መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡
በእምነቱ የፀና የትነው የማገኘው?
ብቅ ይበል እንየው እሱ ማነው ጀግና?
መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ
የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ
እንደዚያ እንደ ጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ?
የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው
የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?
ምሥጢርን ከምሥጢሩ አንድ አድርጐ ቀምሮ
ወልድ ዋሕድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ
እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ
ከአትናቴዎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡
መሆኗን የሚያምን ማኅደረ እግዚአብሔር
ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን
ትንታግ ምላስም ጭንግፍግፉን
ልሳነ ጤዛ መናፍቅን
ወልደ አርዮስ ዲቃላውን፡፡
በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ
ጀግና ማነው ዝቅ ይበላ፡፡
እስኪ ጎርጎርዮሰ ይምጣና ጠይቁት
ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ
ምሥጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ፡፡
ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት
ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት
የጸሎት ገበሬ ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ይነሣ ቀስቅሱት
ይነሣ ጊዮርጊስ ይመስክር ምሥጢር
የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡
ዲያብሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ፡፡
ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ
መር ብለው የወጡት ከሥጋ ገበያ
ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ፡፡
ዓላማው ምንድነው የዘመኑ ወጣት፡፡
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ
ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡
የአባቴ ተረቶች
ሐምሌ 16/2003 ዓ.ም.
ከመኝታዬ የተነሣሁት አረፋፍጄ ቢሆንም አሁንም የመኝታ ቤቴን መስኮት ከፍቼ አውራ መንገዱን እየቃኘሁ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ዘወትር ከእንቅልፌ ስነሣ ሰፈራችን ሰላም ለመሆኗ ማረጋገጫዬ የመኝታ ቤቴ መስኮት ናት፡፡
“አቤቱ ቃሌን አድምጥ፣
ጩኸቴንም አስተውል፣
የልመናዬን ቃል አድምጥ፣
ንጉሤና አምላኬ ሆይ
አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለሁና
በማለዳ ቃሌን ስማኝ፤
በማለዳ ፊትህ እቆማለሁ…”
አባቴ ጸሎቱን ጨርሶ ወደ ቤት ዘልቆ አሮጌው ሶፋ ላይ ተቀምጧል፡፡
“እንደምን አደርክ አባባ”
እግዚአብሔር ይመስገን ልጄ አንቺስ እንዴት አደርሽ?”
“ጎሽ ልጄ የሚጠጣ ውሃ በጠርሙስ ሞልተሽ አምጭልኝ” የሚለው ያባቴ ትእዛዝ ከገባሁበት የሐሳብ ማዕበል መንጥቆ አወጣኝ፡፡
“የሚሚዬ አባት ለሚካኤል የጠመኩት ጠላ እኮ አላለቀም.. ከሱ ይጠጡ” እናቴ ነበረች፡፡
“ከዘንድሮስ ጠላ ውሃው ይሻለኛል ተይው” የሚለውን ያባቴን ምላሽ ስሰማ አባቴ በዘንድሮ ላይ ያለው ምሬት የተለየ መሆኑ እየገረመኝ ውሃውን አቀረብኩለት፡፡
“እሰይ እሰይ! እሰይ!” እያለ ጥሙን ይቆርጣል፡፡
“በአባቶቻችን ጊዜ ብዙ ሠርቶ እንዳልሠራ የሚሆን ሰው ማግኘት ቀላል ነበር፡፡ ስለ ብቁና ጎበዝ ሰው ምስክሩ ሥራው ብቻ ነበር ልጄ፡፡ ቢሆንም የዝና ናፋቂዎች ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ብዙኃኑ ግን ያለ አግባብ ሙገሳን እንደ ስድብ እንቆጥር ነበር፡፡ እከሌ እኮ ጀግና ነው ቢሉን ስለ ጀግንነቱ ማረጋገጫ ከእርሱው እንጂ በዝናው አናምንም ነበር፡፡
“ልጄ ዘንድሮ በዓይን የሚታይ በጎ ሥራ ጠፋ፤ እስቲ ከዓይን ተርፎ ልብን የሚሞላ ተግባር የሠራውን ሰው አሳይኝ?” ድንገተኛው ያባቴ ጥያቄ አስደነገጠኝ፡፡ አባቴ የከበደኝን ጥያቄ ከኔ ምላሽ ሳይጠብቅ መንገሩን ቀጠለ፡፡
“ዘንድሮ ጥቂት ተሠርቶ ለስምና ለዝና የሚሮጥበት ጊዜ ነው፡፡ ከተግባር ስም የቀደመበት የውዳሴ ከንቱ ዘመን፡፡” እያለ አባቴ መናገሩን ቀጠለ፡፡ “ልጄ ስላንቺ ተግባርሽ እንጂ ዝናሽ አይመስክር” የምትለዋን የዘወትር ንግግሩን አስተውያት ባላውቅም ዘወትር መስማቴን አስታውሳለሁ የዛሬው አባቴ ገፅታ ከወትሮው በተለየ መልኩ ትካዜና ደስታ አልባ ሆኗል፡፡
ምን ሊመክረኝ ይሆን እያልኩ ወደ ጉልበቱ ተጠጋሁ
“ከአባቶቻችን ሐዋርያት ትሕትናን፣ ባለብዙ ዕውቀት ሆነው እንዳላወቁ፤ ባለጸጋ ሆነው እንዳልሆኑ መምሰልን መማር ይገባናል ልጄ ስም ከሥራ መቅደም የለበትም ልጄ…”
ቀበሮ ሥጋ በአፏ የያዘች ቁራ ትመለከትና ከመሬት ሆና “እሜት ቁራ ከአእዋፍ መካከል እንዳንቺ ያለ ውብና ቆንጆ፤ አስተዋይና ባለ አእምሮ የለም” እያለች ታሞግሳት ጀመር፡፡የቁራን ዝምታ ያልወደደችው እሜት ቀበሮ ውዳሴዋን ግን አላቆመችም
“እሜት ቁራ ሆይ በምድር ለሚገኙ አእዋፍ ሁሉ ንግሥት የምትሆን ፈለግን፤ በምድር ሁሉ ዞርን ግን አላገኘንም ድንገት አንቺን አየን፡፡ በዚህ ውበትሽ ላይ ድምፅሽ ቢያምር አንቺን ለንግሥትነት እንመርጥሻለንና እስቲ ድምፅሽን አሰሚኝ አለች ቀበሮ”
ንግሥት ለመሆን የተመኘችው ቁራ በቀበሮ ሙገሳ ተታላ “ቁኢኢ..” ብላ ብትጮኸ የነከሰችው ሥጋ ወደቀ፡፡ ያሰበችው የተሳካላት እመት ቀበሮ “በዚህ ድምፅና ውበት ላይ ማስተዋል ቢጨመርበት ኖሮ እንዳንቺ ያለ የአእዋፍ ንግሥት እግር እስኪነቃ ቢኬድ አይገኝም ነበር” ብላ ተመጻደቀችባት ይባላል፡፡
ልጄ ስንቱ በውዳሴ ከንቱ ጸጋውን ተነጥቆ ከክብር ተዋርዶ ይሆን? የሰው ስስ ብልት ዝና ናፋቂ መሆኑን የተገነዘበው ዲያብሎስም እንደ ልቡ እየተጫወተብን ነው፡፡ ስንት የት ይደርሳሉ የተባሉ ሰዎች ካቅማቸው በላይ ባገኙት ዝና ተልፈስፍሰው ከእርምጃው ተገተው ይሆን?
ውሃ የሞላ ብርጭቆውን አነሣና ተጎነጨለት
እሰይ! ይኸውልሽ ልጄ ለሰው ውድቀቱ ውዳሴ ከንቱ ነው፡፡ ምእመናን ጥቂት መንፈሳዊ አገልግሎት ሠርተው የበቁ የሚመስላቸው፤ አገልግለው የማንጠቅም ባሪያዎች ነን የሚሉ እንዳልነበሩ፤ ትንሽ አስተምረው /አገልግለው/ ታይታን የሚፈልጉ አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያናችን ሞሉ፡፡ ታዲያ ትውልድ ምን ይማር ልጄ?
ለእናት ሀገሩ በቅንነት ከመሥራት ይልቅ ሀብቷን የሚቀራመታት ለድሆች ከቆመው ይልቅ ያለ አግባብ ኪሱን በጉቦ ያደለበው ስሙ ሲገን ከማየት የደለበ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ?
ከአባቴ አንደበት የሚወጡት ቃላት ፍላጻቸው ለልቤ ደርሰው አእምሮዬን ሲሞሉት ራሴን ዘወትር ብወቅስም ያለመለወጤ አናደደኝ፡፡
“ብዙ መሥራት የሚችለው ወጣት ተጧሪ ሆነ ለኔ የሚገባኝ ከመሥራት ይልቅ መዝናናትና በሱስ መጠመድ ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ነው የበዛው ልጄ..”
ከአባቴ ተረት ውስጥ ራሴን መመልከት ጀመርኩ ሁሌም አንድ ተጨባጭ ነገር ላይ መድረስ ሲያቅተኝ ልኬቴ እዚህ ድረስ ነው ብዬ ሳምን፤ በራሴ መጠራጠር ጀምሬ ነበር፡፡ ትእግስት በስሜቴ ውስጥ ሲገረጅፍ ደግሞ ግን ለምን የሚለኝ አእምሮዬ ውድቀቴን ያለ ሥራና ያለ መልካም ምግባር ዛሬም በአባቴ ቤት ተጧሪ መሆኔን አከበደብኝ፡፡
ለስማቸው የሚጨነቁት ጥቂት ሠርተው ብዙ ስም ፈለጉ እኔ ግን ያለ ሥራ ቁጭ ብያለሁ፡፡ እስከ ዛሬ የአባቴ ተረቶች እውነታቸው ከማስበው በተለየ ዘልቆ ሲታወቀኝ፣ ጠልቆ ሲዳሰሰኝ፣ ርቆም ሲታየኝ፣ ቀርቤም ሆኖ ብዥ ሲልብኝ ኖሬያለሁ፡፡ ዛሬ ግን ራሴን ተመለከትኩ፡፡
ከአባቴ ተረቶች መሠረት ዛሬ ላይ ሆኖ ትናነትን ከመናፈቅ ይልቅ የዛሬን የተግባር ሰው መሆን እንደሚገባኝ ተገነዘብኩ፡፡ የአባቴ ቃላት ተራ ተረቶች መስለውኝ ቢኖሩም ዛሬ ግን ተጨባጭ በሆነው ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚገባኝ ሲጠቁሙኝ የኖሩ የተዋቡ ምክሮች ናቸው፡፡ አባቴ በኋሊት መነጽር ትናንትን የሚያሰቃኘኝ የተግባር ሰው በውዳሴ ከንቱ ያልተበገረች ጠንካራ ሠራተኛ ጥሩ መንፈሳዊ ሰው እንድሆን ነው፡፡
አሁን አባቴ ካጠገቤ ተነሥቶ በረንዳ ላይ ተቀምጧል ዓይኖቹን ቡዝዝ አድርሀጎ የፊት ለፊቱን ያያል፡፡ እኔ ግን ዓይኖቹ በትውስታ ፈረስ ትናንትን፤ የሱን ዘመን እያሰቃኙት ይመስለኛል፡፡
የሱ በትናንት ዘመን መኖርና የድሮ ተረቶቹ ከተዘፈቅሁበት ከንቱነት ከግድ የለሽነትና ከተመጻዳቂነት የሚያወጡኝ የማንቂያ ደውሎች ናቸው ለካ!! አልኩ፡፡
ለወትሮው ሠርቼ ራሱን ከመለወጥ ይልቅ ሀብታም የትዳር ጓደኛና ዝና ፈላጊነቴ ገዝፎ አእምሮዬን የሞላኝ ነበርኩ፡፡ ለዚህ ነው ከሁሉም ነገር ውስጥ ሳልሆን ጠባቂ ሆኜ መኖሬ እስከ አሁን ከልብ ሳልሆን በማስታወሻ ደብተሬ ላይ የከተብኳቸውን በርካታ ያባቴን ተረቶች መልሼ ማንበብ እንደሚጠቅመኝ አሰብኩ፡፡
“ልጄ?”
አቤት አባባ
አሁን እንግዲህ 34 ዓመት ሞላሽ አይደል?
አዎን አባባ
አባቴ ከዚህ በላይ አልጠየቀኝም መልእክቱ ገብቶኛል ትንሽ ለሀገርሽና ለቤተ ክርስቲያንሽ የሚሆን በጎ ሥራ ሳትሠሪ ጊዜ ቀድሞሻል ማለቱ ነው፡፡
አባዬ?
“አቤት ልጄ”
ለካ እስካሁን ከኖሩት ተርታ አልተመደብኩም?
“እንደሱ ነው ልጄ እንደሱ!!
/ምንጭ፡- ሐመር 18ኛ ዓመት ቁጥር 5