“እነሆ÷ ድነሃል ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” (ዮሐ.፭፤፲፬)
ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉንም በሥርዓት የምታከናውን ስንዱ እመቤት ናትና በዐቢይ ጾም ከሚገኙት ሰንበታት ውስጥ ዐራተኛውን ሰንበት መጻጉዕ ብላ ሰይማዋለች፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብንወድቅ እንደሚያነሣን፣ ብንታመም እንደሚፈውሰን ለማስተማር፣ እንዲሁም ደግሞ ከመጻጉዕ ሕይወት እንማር ዘንድ መታሰቢያውን አደረገች፡፡ “ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” እንዳለ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ እንሸጋገር ዘንድ፣ የአምላካችንን ቃል መፈጸም እንደሚገባን፣ እሰከ ሞትም መታመን እንዳለብን ያስተምረናል፡፡