“ልትድን ትወዳለህ?” (ዮሐ.፭፥፭)
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የዐቢይ ጾም ሳምንታትን በቅዱስ ያሬድ ስያሜ መሠረት አራተኛውን ሳምንት መጻጉዕ ብላ ታከብራለች። “መፃጉዕ” ማለት “ድውይ፥ በሕመም የሚሰቃይ፥ የአልጋ ቁራኛ” ማለት ነው። ይህንንም ስያሜ እንዴት እንደመጣ ለማየት በዕለቱ የሚነበበውን የወንጌል ክፍል ብንመለከት እንዲህ ይላል። “ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ‘ልትድን ትወዳለህ’ አለው። ድውዩም ጌታ ሆይ አዎን! ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም እንጂ፤ ነገር ግን እኔ በመጣሁ ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል አለ። ጌታ ኢየሱስም ‘ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፤ ያም ቀን ሰንበት ነበረ” ይላል። (ዮሐ.፭፥፭-፲)