የሦስቱ ቀናት ጾም

የካቲት፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ሦስት ቁጥር በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ብዙ ትርጉሞች እንዳለው ቅዱሳት መጻሕፍት ይገልጻሉ፡፡ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በዋነኛነት የምናነሣው ስለ ቅድስት ሥላሴ ሦስትነት ነው፡፡ ‹‹አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ናቸው›› እንዲል፤ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደውም በዕለተ እሑድ ሦስት ሰዓት ላይ ነው፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰው በሦስት ሰዓት ነው፤ እመ አምላክም የመፀነሱን ብሥራት ከቅዱስ ገብርኤል የሰማቸው በዚሁ ሰዓት ነው፡፡ (ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት/በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀ፣ ፲፱፻፺፫ ዓ.ም)

አምላካችን በተወለደ ጊዜም የዜናውን ብሥራት ሰምተው እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ ያመጡለት ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ቁጥራቸው ሦስት እንደ ሆነ ቅዱስ ወንጌል ይገልጻል፡፡ (ማቴ.፪፥፲፪) ተአምረ ማርያም ደግሞ እመ አምላክ ድንግል ማርያም ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር ሆና ጌታችን ኢየሱስ ፲፪ ዓመት በሆነው ጊዜ በቤተ መቅደስ ለሦስት ቀናት ያህል ፈልጋ እንዳጣችው ይነግረናል፡፡

ጌታችን በዘመነ ሥጋዌ በምድር ላይ ስብከተ ወንጌልን ያስተማረው ለሦስት ዓመታት ነው፤ በቀራንዮ አደባባይ መከራና ሥቃይ የተቀበለው ለሦስት ሰዓታት ነው፤ በመልዕልተ መስቀል ላይ ከሞተም በኋላ የተነሣው ከሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በኋላ ነው፡፡ (ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት/በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀ፣ ፲፱፻፺፫ ዓ.ም) ይህን ብቻ አነሣን እንጂ በነገረ መላእክትና በቅዱሳን ገድል ውስጥ ሦስት ቁጥር ለብዙ የእግዚአብሔር ሥራዎች ላይ ሲውል ይስተዋላል፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ፣ ገድለ ቅዱሳን)

ለምሳሌ ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አጋእዝተ ዓለም ሥላሴን  ‹‹አሐዱ  አብ  ቅዱስ  አሐዱ  ወልድ  ቅዱስ  አሐዱ  ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ  አብ  ቅዱስ  ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስም ቅዱስ ነው››  በማለት ያመሰገኑት በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ሄዶ በአንደበቱ ሊገልጸው የማይችለውን ምሥጢር እንደ ተመለከተ ቅዱስ ወንጌል ይገልጻል፡፡ ብዙ ምሳሌዎች መግለጽ ቢቻልም ጊዜ ይገድበናል፡፡ (ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣፪ ቆሮ.፲፪፥፪)

ለዚህ ርእሰ ጉዳይ ትኩረት ያደረግነው ግን አምላካችን ስለ አዘዘው የሦስቱ ቀናት ጾም ነው፡፡ ለማንኛውንም ጥፋትም ሆነ በደል ሥርየት የምናገኘው በጾም፣ በንስሓ፣ በጸሎት፣ በምጽዋት እንዲሁም በስግደት በመሆኑ አምላካችን ሊያድነን ስለ ወደደ ይህን ሥርዓት ሠርቶልናል፡፡ በታሪክ መጻሕፍት ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው በበደላቸው ምክንያት የነነዌ ሕዝብ ሊጠፉ በመሆናቸው ከሕፃናት ጀምሮ እስከ አረጋዊ ብቻም ሳይሆን እንስሳት ጭምር የጾሙት የሦስት ቀናት ጾም ‹‹ የነነዌ ጾም›› ተብሏል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የነነዌ ከተማን በሦስት ቀናት ውስጥ ሊያጠፋት እንደ ሆነ ለነቢዩ ዮናስ ሲነግረው ትእዛዙን ከመቀበል ይልቅ ወደ ቴርሰስ ከተማ ለመኮብለል የወሰነው፣ ልብና ኩላሊትን የሚመረምረውንና ምንም ምን ከእርሱ የማይሠወረውን ፈጣሪ ማታለል ስለሚችል ሳይሆን ሐሰተኛ ነቢይ ላለመባል ፈርቶ ነበር እንጂ፡፡

ቸር፣ መሐሪና ይቅር ባይ የሆነው አምላካችን የነነዌ ሕዝብ በንስሓ፣ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ካልተመለሱ ነነዌ  እንደምትጠፋ እንዲያስተምርና እንዲያስጠነቀቅ ካዘዘው በኋላ በቸርነቱ ሲምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እንደሚባል አስቦ መሸሽን መረጠ፡፡ ‹‹ተነሥና ወደ ነነዌ ሀገር ግባ፤ በድለውኛልና ነነዌ በሦስት ቀን ትጠፋለች ብለህ ስበክ›› አለው። ዮናስ ግን ‹‹የአንተ ምሕረት እጅግ የበዛ ሲሆን ትጠፋለች ብዬ ተናግሬ እሳት ከሰማይ ሳይወርድ ቢቀር ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን?››  አለና ከእግዚአብሔር ሊሸሽ መንገድ ጀመረ። (ዮናስ ፩፥፩-፫)

እግዚአብሔር አምላክም እንደ ስሙ ትርጓሜ የዋህ የነበረውን የዮናስን ልብ ያውቃልና በድንቅ ጥበቡ የጉዞውን አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ነነዌ ምድር ወሰደው፡፡ ታላቅ ነፋስን ይጓዝበት በነበረበት መርከብ ላይ ላከ፤ መርከቡም ሊሰበር ደርሶ ተሳፋሪዎቹን ሁሉ አሸበረ፤ ሆኖም ግን ምክንያቱን ለማወቅ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወጣ፤ አንቀላፍቶ የነበረው ዮናስም ‹‹ይህ ማዕበል በእኔ ምክንያት የመጣ ነውና ወደ ባሕሩ ጣሉኝ›› አላቸው፤ እነርሱም እውነቱን ሲረዱ እርሱ እንዳላቸው ባሕር ውስጥ ጣሉት፤ ቀጥሎም አምላክ ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አንበሪ አዘጋጀ፤ ዮናስንም ከዋጠው በኋላ በሆዱ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ቆየ፤ ይህም ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ለመኖሩ ምሳሌ ነው፡፡ (ዮናስ ፩፥፬-፲፯፣ ማቴ.፲፪፥፵-፵፩)

ከዚያም ዓሣ አንበሪው ዮናስን በየብስ እንዲተፋው አደረገ፡፡ ዮናስ ወደ ነነዌ ከተማ ከደረሰ በኋላ የሦስት ቀን መንገድ ዙሮ መስበክ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ነገር ግን የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም፤ ‹‹በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች›› አለ። የነነዌ ሰዎችም የእግዚአብሔርን ቃል አምነው ተቀበሉ፡፡ ማቅ ለበሱ፤ ድንጋይም ተንተራሱ፤ ንጉሡ ስልምናሶር ሳይቀር ከዙፋኑ ወርዶ መጐናጸፊያውን አወለቀ፤ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። ሕፃናት ጡት ተከለከሉ፤ እንስሳትም ጭምር ለሦስት ቀናት ያህል ከሚበሉት ተከለከሉ፡፡ ‹‹ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?›› እንዲል፡፡ (ዮናስ ፫፥፰-፱)

በእርግጥም አምላካችን እግዚአብሔር ወደ እርሱ በመመለሳቸው ምክንያት ለሕዝቡ ምሕረትን አድርጎ የነነዌ ሰዎችን እንዳዳናቸው ከትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ እንረዳለን፡፡ ነቢዩ ዮናስን ግን ይህ ነገር ደስ እንዳላሰኘው ከዚህ በኋላ በተጻፈው ታሪክ እናያለን፡፡ ‹‹ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፤ እርሱም ተቈጣ። ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና። “አቤቱ፥ እለምንሃለሁ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽም፣ ምሕረትህም የበዛ፣ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር፡፡ አሁንም አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ” አለው። እግዚአብሔርም “በውኑ ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን?” አለ።

ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፤ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፤ ከተማይቱንም የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፤ ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው። በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፤ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት፡፡ ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ፤ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ሞትን ፈለገና “ከሕይወት ሞት” ይሻለኛል አለ። እግዚአብሔርም ዮናስን “በውኑ ስለዚህች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን?” አለው። እርሱም “እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል” አለ። እግዚአብሔርም “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፣ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፣ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” አለው፡፡›› (ዮናስ ፬፥፩-፲፩)

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ፈጣሪያችን በአርአያውና በአምሳሉ ለፈጠረን ለእኛ ለሰዎች እንደሚያዝን፣ ተጸጽቶ ለሚመለስ ደግሞ ምሕረትን እንደሚያደርግ በዚህ ለነቢዩ ዮናስ በምሳሌ አድርጎ በነገረው መሠረት እንረዳለን፡፡ አምላከ ምሕረት እግዚአብሔር በከፋ ደረጃ ለበደሉት ለነነዌ ሰዎች ምሕረትን ያደረገው በሦስት ቀን ጾም ብቻ ነው፡፡ እኛም በሦስቱ ቀናት ጾም እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ባሕርይውን ዝቅ አድርጎ፣ ሥጋን ለብሶ፣ በምድር እንደ ሰው ተመላልሶ፣ መከራን ተቀብሎና ተሰቅሎ፣ በሦስተኛ ቀን በትንሣኤው ትንሣኤን የሰጠን በሦስተኛው ቀን ነውና ይህን ድንቅ ጥበብና የአምላክ ሥራ በዘመከርና በማመን በእውነት መንገድ ተጉዘን በምጽአት ቀን  ሕይወትን ልናገኝ እንዲሁም መንግሥተ ሰማያትን ልንወርስ ይገባናል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሰምቶ፣ ልመናችንን ተቀብሎና ጾማችንን አስቦ ምሕረትን ያድርግልን፤ አሜን!!!